Saturday, 05 October 2013 10:54

ፍልስፍና ከመላዕክቱ ዳንስ ባሻገር

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

የፍልስፍና ትምህርት በሃገራችን የዘመናዊ ትምህርት አጀማመር ጋር ቀዳሚነት ቢኖረውም፤ በእኔ ግምት አብሯቸው ከተጀመሩት የትምህርት ዓይነቶች በተለየ ሁኔታ በተሳሳተ አረዳድ ምክንያት በሃገራችን የዕድገት ጎዳና ትክክለኛውን ስፍራ እንዳይዝ ተደርጓል። የእድሜውን ትልቅነት ያህል የሰባ ሲሳይ እንዳንዝቅበት ያደረጉን ምክንያቶች ምናልባትም ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ሊሆን ስለሚችል፣ ለጊዜው ተወት እናድርገውና ስለ ትምህርት መስኩ ትንሽ ጉብኝት እናድርግ። ከሃገራችን ነባራዊ ሁኔታዎችና ወደፊትም ለታሰቡ የሃገር ልማት አቅጣጫዎች ጋር ሊኖረው የሚችለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ባጭሩ ዳሰስ ዳሰስ እናድርገው። ጉብኝታችንን (ቅልብጭ ያለ እንዲሆንና ጥሩ ትውስታ እንዲኖረን) በአምስት የጉዞ ምእራፎች ብቻ እንወሰን።
ሀ)ሳይንስና ፍልስፍና ምንና ምን ናቸው? ፍልስፍና የሳይንስ መላምቶችን በመፈተሽና የሃሳብ ቅራኔዎቻቸውን በማጥራት በኩል የሚጫወተውን ሚና ያህል የምርምር ዘዴውን አግባብነት በማጥናት በኩል ከፍተኛ ሚና አለው። በቶማስ ኩኧን/ The structure of Scientific Revolution/ አስተምህሮ መሰረት፤ የሳይንስ እድገት በዕውቀት ውርርስ ከቀደምቱ ሳይንቲስቶች ወደ ኋለኞቹ በቀጥታ የሚተላለፍ ሳይሆን በሳይንሳዊ አብዮት የበፊቱን ሳይንሳዊ አስተምህሮ ባፍጢሙ በመድፋት በሚመጣ አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ የተመሰረተ ነው። ሳይንቲስቶቹ አዲስ ግኝት እንኳን ቢያገኙ፣ ከበፊት ከተለመደው እውቀት መዋቅር ውጭ ስለሚሆንባቸው፣ በድፍረት አዲስ ነገር አግኝቻለሁ ለማለት የኖረው የአስተሳሰብ ጫና ስለሚይዛቸው አዲስ ግኝታቸውን ከማስተዋወቅ ይቆጠባሉ። ነገር ግን በግዜ ሂደት ነባሩ የሳይንስ እውቀት እክሎች እየበዙበት ይመጣና ደፋር ወጣት የሆኑ ሳይንቲስቶች አፈራርሰው ይጥሉታል። በዚህን ግዜ ከዚህ በፊት ከነበረው አስተሳሰብ የተለየ አዲስ አይነት አስተሳሰብ ይወለዳል/paradigm shift/። እናም የሳይንስ ፍልስፍናችን አብዮታዊ ይሆናል ማለት ነው።
ፊዮርባንድ የተባለው የሳይንስ ፈላስፋ ስለ ምርምር ዘዴዎች ትችት በማቅረብ ይታወቃል። እንደ እርሱ ትምህርት ከሆነ፣ እያንዳንዱ የጥናት መንስኤ ለራሱ በሚስማማ መልኩ የጥናት ዘዴ ሊበጅለት ይገባል እንጅ አንድ ወጥ ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴ እሚባል ነገር የለም። ሁሉም የየራሱ ልዩ ባህሪያት አሉት፤ ስለዚህም ለየራሱ ልዩ ባህሪያት የሚስማማ የተለያየ የጥናት ዘዴ ነው መጠቀም ያለብን። የእኔ አተያይ ከሌሎች የተለየ እንደመሆኑ መጠን የእኔ የጥናት ዘዴም ችግሩን ይፈታልኛል ብዬ በማስበው አቅጣጫ አዲስ የጥናት ዘዴ መቀየስ ይገባኛል እንጅ ከዚህ በፊት የተፈተሸና የተረጋገጠ የሚባል አንድ ወጥ የጥናት ዘዴ መከተል የለብኝም ይላል።
ሰር ካርል ፖፐር ደግሞ ለምናጠናው ርእሰ ጉዳይ ማስረገጫ የሚሆን መልስ ከመፈለግ ይልቅ የማይሰራባቸውን መንገዶች በቀላሉ ማግኘት ይቻላልና ያነሳነውን የጥናት መላምት ማስረገጥ ሳይሆን ማፉረሽ ነው ያለብን ብሎ ያስባል። ስለዚህም የጥናት ዘዴዎች መላምቶቻቸውን ማፉረሽ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል እንጅ የተለመደውን ትክክለኛ መፍትሄ ፍለጋ ጥናቶች መባዘን የለባቸውም። መላምቶቻችንን ሁሉ አፉርሸን ከጨረስንና ከመካከላቸው ለማፉረሽ የከበደን ወይም ያቃተን መላምት ካለ ምናልባትም ትክክለኛው መፍትሄ እርሱ ነው ይለናል።
ለ)እውቀትና ፍልስፍና፥ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች? ፍልስፍና ነፍሱን ከሰጠባቸው የምርምር ምእራፎቹ ውስጥ አንዱ እውቀት ምንድ ነው የሚለው ጥያቄ ነው። እውቀት ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ፣ ፍልስፍና ነፍስ ካወቀችበት እድሜዋ ጀምሮ እስካሁንም ድረስ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይዋ ነው። እውቀት በስሜት ህዋሳቶቻችን እርዳታ ከአካባቢያችን ጋር በምናደርገው መስተጋብር የሚገኝ ነው ወይስ ደግሞ ተለዋዋጭነት የሚያጠቃቸውን በትክክል መለካትና መፍረድ የማይችሉትን የስሜት ህዋሳቶቻችንን ሳንጠቀም ንጹህ አእምሯችንን በመጠቀም የምናገኘው ውሳኔ ነው እውቀት የሚባለው? ቋሚ ዘላቂ የማይነዋወጥ የሚባል እውቀት አለ ወይስ እውቀት እንደየ ዘመኑ እና የሰዎች ስልጣኔ መጠን የሚለዋወጥ ነው? አንድን እውቀት እውቀት የሚያስብለው መስፈሪያ መለኪያው ምንድ ነው? እነዚህን እና መሰል የእውቀት ርእሰ ጉዳዮችን የሚያብጠረጥረው ፍልስፍና ምእራፍ Epistemology በመባል ይታወቃል።
ታላቁ አወዛጋቢው ፈላስፋ ዴቪድ ሂዩም አንድን ነገር/ጉዳይ አወቅን ስንል፤ ባወቅነው ነገር/ጉዳይና በእውቀቱ መካከል ምን አንድ የሚያደርጋቸው ሰበብ አለ ይለናል። በምሳሌም ሲያስረዳ ጥቁር ደመና ስናይ ሊዘንብ ነው እንላለን፤ ነገር ግን በጥቁር ደመና እና በዝናብ መካከል ያለው ሰበባዊ ትስስር ምንድን ነው? ይህንን መግለጽ አንችልም። ከዚህ በፊት ጥቁር ደመና መጥቶ ከዚያም ዝናብ ወርዶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ትናንትና እንደዚያ ሆኗል ማለት ዛሬም እንደሚደገም ማስረገጫ ሊሆነን አይችልም። ሰበባዊ ትስስራቸውን መግለጽ ካልቻልን ደግሞ ስለ ጉዳዩ እውቀት የለንም ማለት ነው።
ሬኔ ዴካርት በተራው እውቀት የምንለው ጉዳይ በንጹህ ልቦናችን አውጠንጥነን የምናገኘው ጉዳይ ነው ይለናል። በንጹህ ልቦናችን ለማሰብ ግን ከስሜት ህዋሳቶቻችን የሚመጡ መልእክቶችና ሹክ የሚለንን ያልተጨበጠ መንፈስ እንዳያሳስቱን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል ይለናል። የፈጣሪም እርዳታ ያስፈልገናል። ስለሆነም በዚህ አይነት መንገድ የምናገኘው እውቀት ማወቅ ስለፈለግነው ጉዳይ መቅኔ/essence/ፍንትው አድርጎ የሚገልጽ ይሆናል ማለት ነው።
ሐ)ባህልን በጉባኤ? ባህልና ፍልስፍና እርስ በርስ እንደተጣበቁ መንቶች ባህል ፍልስፍናን ይጎትታል፤ ፍልስፍናም ያለባህል መራመድ ይሳነዋል። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ትልቅ የፍልስፍና ትኩረት እየተሰጠው የመጣ አዲስ የፍልስፍና ምእራፍ ደግሞ ባህል ነው። ባህል እንዴት በባህል ልዩነቶች ውስጥ እራሱን ጠብቆ መኖር ይችላል? የተለያዩ ባህሎች እርስ በእርስ ሳይዋዋጡ በመገናዘብና በመቻቻል አብረው እንዴት መኖር እንደሚችሉ ትኩረት ሰጥቶ ያጠናል፤ ይህ የፍልስፍና ምእራፍ። እንደ መፍትሄም የባህል ጉባኤ ያስፈልገናል ይለናል(እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የባህል ሃብታም ሃገራት)።
የአንድ ሁለት ባህሎች ውይይት ሳይሆን መላው ባህሎችን ያካተተ ጉባኤ ያስፈልገናል። ባህሎች እርስ በእርስ መተዋወቅ፣ መገናዘብና መረዳዳት ይኖርባቸዋል። ያለበለዚያ የአንዱ ባህል መጥፋት ወይም መዋጥ ለቀሪዎችም ባህሎች ስጋት ይፈጥራል። ህልውናቸው በመዋጥና ላለመዋጥ በሚደረግ ትግል ውስጥ ይንጠለጠላል ማለት ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ እንጅ ሁሉንም ባህሎች የሚያጠፋ፣ ለማናቸውም የማይጠቅም ፍጻሜ ይኖረዋል።
መ) የዕድገት ሥነ ምግባር? ይህ የፍልስፍና ምእራፍ፣ እድገት በስነ ምግባር ማእቀፍ ውስጥ መታሰብና መተግበር እንዳለበት ያሳስባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የእድገት ፍሬው የሰውን ህይወት መለወጥ ነውና የእድገት መንገዳችንም ሰውን ቅድሚያ በሚሰጥ መልኩ እንጅ ቁስ አካላትን ሰው ላይ ለማንገስ መሆን የለበትም። እድገት የሰውን ድሎት የሚያጎናጽፍ እንጅ በተቃራኒው የቁስ አካላት ባሪያ የሚያደርገው መሆን የለበትም። የአንድ ሃገር ልማት የሚለካው በሰው ልማቷ ነው ወይስ በቁስ ልማቷ የሚለው ሙግት የዚህ ፍልስፍና ምእራፍ ዋና አካል ነው።
የልማት ስነ ምግባር ካልን የልማት ኢ−ስነምግባርስ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ የፍልስፍና ምእራፍ እናም አንድን ድርጊት ሙስና የሚያደርገው ምኑ ነው እያለ ይፈላሰፋል። ሙስና አለማቀፋዊ መለኪያው ምንድን ነው? አካባባዊ ብያኔውስ ምን ይመስላል? ሙስና እንደ አንድ የፍልስፍና ርእሰ ጉዳይ በዚህኛው ምእራፍ ትብጠረጠራለች።
ሠ)ትምህርትና ፍልስፍና፥ምሳርና እጀታው? በአገራችን ውድ ወጭ ከሚጠይቁ የመንግስት ዘርፎች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ አንደኛው ትምህርት ነው። ታዲያ ፍልስፍና የሌለው ትምህርት እጀታ የሌለው ምሳር እንደ ማለት ነው። ምሳርና እጀታው ሲጣመሩ/ሲዋደዱ ጉቶውን ግንዱን ዛፉን መቆራረጥ ይቻላቸዋል፡፡ አንዳቸው ያላንዳቸው ትብብር ግን ይህንን መስራት አይቻላቸውም። ትምህርት ለአንሃገር ስለሚያበረክተው አላማ፤ የማስተማር ዘዴ እና ትምህርቱ ለማን መቅረብ እንዳለበት ለመበየን የሚያስችል ፍልስፍና ሳይኖረው ዝርው ከሆነ፣ ከዚያ ትምህርት ፍሬ ከመጠበቅ ይልቅ እጅ እግርን አጣጥፎ የአለምን ፍጻሜ መጠበቅ ይቀላል።
የትምህርት ፍልስፍና ለአንድ ሃገር ስለሚያስፈልጉ ትምህርቶች አላማ፤ ትምህርቱ ምን ምን ርእሰ ጉዳዮችን እንደሚያካትት እና ትምህርቱ በምን ዘዴ መቅረብ እንዳለበት ለመበየን የሚረዳ የፍልስፍና ምእራፍ ነው። ለአንድ ሃገር ምን ያህል የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት፣ ምን ያህል ደግሞ የህብረተሰብ ሳይንስ ትምህርት ያስፈልጋታል ብሎ ለመወሰን የትምህርት ፍልስፍና ትልቅ ሚና ይጫወታል። ፍልስፍናን አስወግዶ ትምህርትን ማሰብ እራሱ ለማሰብ የሚከብድ ጉዳይ ይመስለኛል። ፍልስፍና የሌለው የትምህርት ስርአት፣ አቅጣጫ ጠቋሚ እንደ ሌለው መርከብ ማለት ይሆናል።
አንዳንድ የትምህርት የፍልስፍና ተሟጋቾች፤ ዜጎችን የሚፈልጉትን ትምህርት መርጠው እንዳይማሩ አማራጭ ማሳጣት በተዘዋዋሪ የዜጎችን የመናገርና የማሰብ መብት እንደ መገደብ ይቆጠራል ይላሉ። ምክንያቱም ተናጋሪ ጋዜጠኞችን ከማፈን ይልቅና አሳቢ ፈላስፋዎችን ከመቆጣጠር ከምንጩ ከትምህርት ቤት በመዝጋት፣ ተተኪዎች እንዳይወጡ ዘላቂ ቁጥጥር ይሆናልና ነው። ነጻ ዜጎች ባሏት ሃገር ምን አይነት ትምህርት እንማር የሚለው ጥያቄ የሚመለሰው ሁሉንም የትምህርት ዘርፍ ለዜጎች ምርጫ ክፍት በማድረግ እንጅ በመንግስት መመሪያ ይህን ተማሩ፣ ያንን አትማሩ እየተባለ መሆን የለበትም። ያለበለዚያ ግን የዜጎች የምርጫ ነጻነት ታፍኗል ማለት ነው።
በአንድ ወቅት ለውይይት የቀረበ በትምህርት ሚኒስቴር የተረቀቀ የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ሰነድ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲተች፣ አንዳንድ የትምህርት ክፍሎቹ በአንድ መርፌ ላይ ስንት መላዕክት ይደንሳሉ እያሉ ጊዜ የሚያባክኑ ናቸው ይላል። በአውሮፓ የመካከለኛው ዘመን እየተባለ የሚጠቀሰው ዘመን የነበረው የትምህርት ስርዓት ሙሉ በሙሉ በሚያስችል ሁኔታ በቤተክርስቲያን ቁጥጥር ስር ስለነበር፣ የፍልስፍና ሙግቶችም በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ይዘታቸው ያመዝን ነበር፤ ከነዚህም ውስጥ በአንዲት መርፌ ላይ ስንት መላእክ ይቆማሉ የሚለው ጥያቄ የመላእክትን ረቂቅ ባህሪ ለመመርመር የቀረበ የዚያ ዘመን ጥያቄ ነበር። አንጋፋው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የመላእክቶቹን ዳንስ ጉዳይ እያነሳ በአንዳንድ ትምህርት ክፍሎች ላይ ሲሳለቅ የነበረው ካለማውቅ ሊሆን ይችናልና የነፍሱ እንዲደርስ (በጆንያ የሚሰፈር ምርት የሌለው ትምህርት የዩኒቨርሲቲዎቻችንን ቅጥር ግቢ እንዳይረግጥ እግድ ተጥሎ በታልና) ፍልስፍና እንዴት ለኢትዮጵያ ገበያ አስፈላጊ እንደ ሆነ እንዲህ እናሳያለና።

Read 3643 times