Saturday, 21 September 2013 11:38

ኢትዮጵያ ከናይጄርያ፤ የዳዊት እና የጎልያድ ፍጥጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከናይጀሪያ ጋር ወሳኙን የመጀመርያው ጨዋታ ጥቅምት 3 በአዲስ አበባ ስታድዬም ያደርጋል፡፡ ይሁንና መስከረም 28 እና 29 ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን አዲስ አመራሮች በጠቅላላ ጉባዔ ለመሾም እቅድ በመያዙ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ትኩረት እንዳያሳጣ ያሰጋል፡፡ ተተኪውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለማስመረጥ ግልፅ ያልሆነ ዘመቻ በየአቅጣጫው በሚደግ ላይ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሚሆኑ እጩ ተወዳዳሪዎች ማሳወቂያ ጊዜው እስከ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ እንደተራዘመም ታውቋል። ጎን ለጎን በተጧጧፈው የምረጡኝ ዘመቻ የጠቅላላ ጉባዔው ባለድርሻ አካላት መጠመዳቸው አላስፈላጊ መጨናነቅ እየፈጠረ ነው፡፡ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚቀጥለው ወር ለሚያደርጋቸው የዓለም ዋንጫ የደርሶ መልስ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ከፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ አዲስ አመራሮች ምርጫ የቅድመ ትኩረት ያስፈልገዋል።

ስለዚህም በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ፤ የስራ አስፈፃሚዎች እና ፕሬዝዳንት ምርጫ ከብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ፍልሚያዎች በኋላ መደረግ እንዳለበት እየመከሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጥቅምት 3 ለሚጠብቀው ወሳኝ የመጀመርያ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከዝግጅቱ ጎን ለጎን እጅግ የሚያስፈልገውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከጋናና ካሜሮን ጋር ለማድረግ ጥረት ላይ እንደሆነም እየተገለፀ ነው። ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች ከኢትዮጵያ ጋር ለመጫወት ፍላጎት ማሳየታቸውም ተዘግቧል፡፡ ከዛምቢያ ጋር ተጨማሪ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሊኖር ይችላልም ተብሏል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎቹ በእቅድ ደረጃ መኖራቸው በሰፊው እየተወራ ቢሆንም ግጥሚያዎቹ በእርግጠኝነት ስለመደረጋቸው የተገኘ ማረጋገጫ የለም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከድልድሉ በኋላ ናይጀሪያን በማሸነፍ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ መነሳሳታቸውን ሰሞኑን ሲገልፁ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ደግሞ ከጥሎ ማለፍ ድልድሉ በኋላ በሰጡት አስተያየት በአፍሪካ ዋንጫ ተገናኝተው ከነበረው የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ስለደረሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ያለአንዳች ፍራቻ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ ፉክክር እናደርጋለን ብለዋል፡፡ የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያን በቀላሉ በማሸነፍ ለ5ኛ ጊዜ አገራቸውን በዓለም ዋንጫ ለማሳተፍ እንደሚችሉ እየፎከሩ ናቸው፡፡ ናይጄሪያውያን ከዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ በፊት ለጎል ስፖርት ድረገፅ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚደርሳቸው የተነበዩት በአንደኛ ደረጃ 42.2 በመቶ ድምፅ በመስጠት ነበር፡፡

ግምታቸው በመሳካቱም ተደስተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ በይፋ ከተነገረ በኋላም ደስታው ቀጥሏል፡፡ በናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና ሌሎች የሙያ ማህበራት የሚሰሩ የተለያዩ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን መቶ በመቶ አሸንፈን ዓለም ዋንጫ እንሄዳለን በሚል አስተያየት የአገራቸውን ሚዲያዎች አጨናንቀዋል። ተቀማጭነታቸውን በናይጄርያዋ መዲና ያደረጉ በርካታ የስፖርተ ተንታኞች እና ባለሙያዎች ኢትዮጵያን ጥሎ ማለፍ እንደሚቻል በሙሉ ድምፅ ተንበየዋል፡፡ ኪክኦፍ ናይጄርያ ለተባለ ሚዲያ ‹‹ጥሩ ድልድል አግኝተናል›› ሲሉ የተናገሩት የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ ለኢትዮጵያ በደንብ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግና ቀላል ተጋጣሚ ተገኝቷል በሚል መዘናጋት እንዳይፈጠር ሲመክሩ ከፍተኛ አልቲትዩድ ባላት አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ደጋፊዎች ፊት የሚደረገው የመጀመርያው ጨዋታ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ፀሃፊ የመልሱ ጨዋታ ከአቡጃ ስታድዬም ይልቅ በካላባር ከተማ በሚገኘው ኢስዋኔ ስታድዬም ቢደረግ ይጠቅማል የሚል ሃሳብም አቅርበዋል። ምክንያታቸውም በአቡጃ ካሉት ደጋፊዎች በካላባር ከተማ ያሉት የተሻሉ ናቸው የሚል ነው፡፡ የአቡጃ ስታድዬም ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥገና ላይ በነበረበት ወቅት የብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በካላባር በሚገኘው ዩጄ ኤስዋኔ ስታድዬም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሌሎች የፌደሬሽኑ አንዳንድ ባለስልጣናት ቡድኑ በካላባር እንዲጫወት የፈለጉት፡፡ የፌደሬሽኑ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ በአቡጃ ወይም በካላባር መደረጉን የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና ተጨዋቾች እንደሚወስኑ ይጠበቅ ነበር፡፡

የናይጄርያ ወሳኝ እና ውዱ ተጨዋች የሆነው ጆን ኦቢ ሚኬል እና አንጋፋው ተጨዋች ጄጄ ኦካቻ ከኢትዮጵያ ጋር በመደልደላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ በመድረስ ጥንካሬውን አሳይቷል ያለው ኦካቻ አሁን ያለው የናይጄርያ ቡድን ግን ሙሉ ለሙሉ የማሸነፍ ብቃት እንዳለው ተናግሯል፡፡ ጆን ኦቢ ሚኬል በበኩሉ በአንድነት እና በትኩረት ከሰራን ኢትዮጵያን በሰፊ ውጤት አሸንፎ ለማለፍ እንደማንቸገር ተስፋ አደርጋለሁ ብሎ ተናግሯል፡፡ እስከወሩ መጨረሻ እረፍት ለማድረግ ከቤተሰባቸው ጋር አሜሪካ የገቡት ዋና አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ግን ናይጄርያውን በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ድልድል ከኢትዮጵያ ጋር በደረሳቸው ድልድል ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን ውስጥ መግባታቸውን አልወደዱትም፡፡ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በማቅለል ወደ ሜዳ አንገባም፣ እነርሱ እዚህ የደረሱት ጠንክረው በመስራታቸው እንጅ በስህተት አይደለም“ በማለት ለቢቢሲ አስተያየት ሰጥተዋል። የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቴክኒካል ኮሚቴ ሊቀመንበር ሙሳ ታሌ በበኩላቸው ለዓለም ዋንጫ ጥሎማለፍ ምእራፍ የደረሱት 10 ብሄራዊ ቡድኖች ጠንካሮች መሆናቸውን ሲናገሩ ንስሮቹ ኢትዮጵያን ሽንፈት የማከናነብ አቅም እንዳላቸው ገልፀው በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታዎች ከአፍሪካ እና ከአፍሪካ ውጭ ከተገኙ ቡድኖች ጋር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመምከር በተጨማሪም መላው ናይጄርያውያንና በአገሪቱ ያሉት የሃይማኖት ተቋማት ፀሎት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌሎማላላም ቦላጂ አብዱላሂ የተባሉት የናይጄርያ ስፖርት ሚኒስትር በበኩላቸው ንስሮቹ ኢትዮጵያን እንደቀላል ተጋጣሚ በመመልከት ለዓለም ዋንጫ በታሪካቸው ለአምስተኛ ጊዜ የሚያልፉበትን አጓጊ እድል እንዳያበላሹ አስጠንቀቀዋል፡፡ ናይጄርያው የፊፋ ቴክኒካል ኢንስትራክተር ኦጊቦንዴ ለሱፕር ስፖርት በሰጠው አስተያየት ‹‹እግር ኳስ ዲሞክራት ነው፡፡ በየትኛውም ጊዜ እና ጨዋታ ቡድኖች የሚፋለሙት 11ለ11 ነው። በ1998 ሴኔጋል ፈረንሳይን እንደምታሸንፍ የገመተ አልነበረም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለመቋቋም በትኩረት እና በጥንቃቄ መዘጋጀት ይገባል። የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር በፍፁም አትመሳሰልም። ሰላዮች አሰማርተን እንኳን አቋማቸውን ብናጠና አይበጀንም። ኢትዮጵያውያኑ ኳስ ይዘው ይጫወታሉ፡፡ እኛ ደግሞ በፍጥነት እና በጉልበት እንጠነክራለን፡፡ ይህን ልዩነት በመጠቀም ኢትዮጵያን ጥሎ ማለፍ እንችላለን፡፡›› ብሏል፡፡ የሁለቱ አገራት የቅርብ ዓመታት የእግር ኳስ ታሪክ እንደሚያሳየው ናይጄርያ ኢትዮጵያን በቀላሉ ለማሸነፍ ችግር የለባትም፡፡ ከዓለም ዋንጫው የደርሶ መልስ ትንቅንቆች በፊት ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሰባት ጨዋታዎች ተገናኝተው ናይጄርያ 4ቱን ስታሸንፍ፤ ኢትዮጵያ አንዱን ብቻ አሸንፋ ሁለቴ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከወር በኋላ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረጉ የመልስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ ለስምንተኛ እና ዘጠነኛ ጊዜ ይፋጠጣሉ ማለት ነው፡፡ ጎል ስፖርት በድረገፁ በሰራው ትንተና ናይጄርያ እና ኢትዮጵያ የተገናኙበትን ጨዋታ ከጎልያድ እና ከዴቪድ ፍጥጫ ጋር አመሳስሎታል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ በወረቀት ላይ ሲታይ ማን የአሸናፊነት ግምት እንደሚኖረው ለመገመት የሮኬት ሳይንቲስት መሆን አይስፈልግም ያለው የጎል ስፖርት ዘገባ ፤ ይሁንና ናይጄርያ ቀላል ግምት የምትሰጣቸውን ቡድኖች ለማሸነፍ ሁሌም ስትቸገር መስተዋሉን ጠቅሶ ፤ ምናልባትም ይህን ሁኔታ በመጠቀም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ሻምፒዮኗን ናይጄርያ ጥለው በማለፍ እግር ኳስ አፍቃሪ ህዝባቸውን ለዓለም ዋንጫ የሚያስተዋውቁበት ታሪክ ሊሰሩ ይችላሉ ብሏል፡፡ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ ይፋ ከሆነ በኋላ ጎል ስፖርት በድረገፁ አንባቢዎችን አሳትፎ በሰራው የውጤት ትንበያ ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ በመጀመርያ ጨዋታቸው አዲስ አበባ ላይ ሲፋለሙ 22.2 በመቶ 2ለ0 እንዲሁም 22 በመቶ 1ለ0 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ ሲገምቱ ሌሎች 22 በመቶ ደግሞ ናይጄርያ 2ለ1 ከሜዳ ውጭ ታሸንፋለች ተብሏል። በእርግጥም የኢትዮጵያ እና የናይጄርያ የዓለም ዋንጫ ትንቅንቅ የዳዊት እና የጎልያድ ፍጥጫ መሆኑን በተለያዩ ንፅፅሮች ማመልከት ይቻላል፡፡ 5 በከፊል የፕሮፌሽናል ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጨዋቾችን በሙሉ ቡድኑ ያካተተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዝውውር ገበያ ተመኑ 775ሺ ፓውንድ ሲሆን ፤ ከ18 በላይ ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን በአውሮፓ ታላቅ ሊጎች ያሰማራው የናይጄርያ ቡድን ግምቱ 19.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡

የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በ17 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች በመሳተፍ ሶስት ጊዜ ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በዓለም ዋንጫ ለአራት ጊዜያት በ1994፤ በ1998፤ በ2002 እና በ2010 እኤአ ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ነው። በአፍሪካ ዋንጫ 10 ጊዜ በመሳተፍ 1 ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንፃሩ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ከቅድመ ማጣርያ ምእራፍ ማለፍ ተስኖት የቆየ ነው፡፡ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ናይጄርያ ከዓለም 36ኛ ከአፍሪካ 4ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ኢትዮጵያ ግን ከዓለም 93ኛ ከአፍሪካ 25ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ቅድመ ትንበያዎችን ፉርሽ ማድረግ ይቻላል? በተለያዩ የስፖርት ዘጋቢ ድረገፆች በ20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል ለማለፍ የሚችሉ 5 ብሄራዊ ቡድኖች እነማን እንደሚሆኑ ለመገመት በተሰሩ ቅድመ ትንበያዎች ለመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከደረሱት 10 ብሄራዊ ቡድኖች ዝቅተኛው የማለፍ ግምት የተሰጠው በተለይ ለኢትዮጵያ ነው ፡፡ በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ ከኢትዮጵያ እና ከናይጄርያ ፍልሚያ ባሻገር ጋና ከግብፅ ፤አይቬሪኮስት ከሴኔጋል ፤አልጄርያ ከቡርኪናፋሶ እና ካሜሮን ከቱኒዚያ ይገናኛሉ፡፡ በማላዊ የሚሰራ አንድ የዓለም ዋንጫ ብሎግ የሚሰራበት ድረገፅ የአስሩ ብሄራዊ ቡድኖችን የማለፍ እድል ለማስላት አንባቢዎቹን የሰጡትን ድምፅ በመመርኮዝ በሰራው ግምት 19 በመቶ ድምፅ በማግኘት አይቬሪኮስት ግንባር ቀደም ነች፡፡ ጋና 18 በመቶ፤ ናይጄርያ 14 በመቶ ፤ግብፅ 13 በመቶ ፤ ካሜሮን 11 በመቶ ፤ አልጄርያ 7 በመቶ፤ ቱኒዚያ እና ኢትዮጵያ እያንዳንዳቸው 5 በመቶ እንዲሁም ሴኔጋል እና ቡርኪናፋሶ እያንዳንዳቸው 4 በመቶ ለማለፍ እድላቸው ተገምቷል፡፡

ላቲኖስ ስፖርት የተባለው ድረገፅ በበኩሉ በሰፊ ትንተና ባቀረበው ግምታዊ ስሌት ለምእራብ አፍሪካ ቡድኖች ያደላ ትንበያን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደላቲኖስ ስፖርት ትንበያ በአምስቱ የጥሎማለፍ ድልድሎች በደርሶ መልስ የሚደረጉትን ጨዋታዎች በማሸነፍ ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚያልፉ 5 ቡድኖች ናይጄርያ፤ ጋና፤ አይቬሪኮስት፤ ቡርኪናፋሶ እና ካሜሮን ናቸው ፡፡ ጊቪሚስፖርት በድረገፁ የሰራው ትንበያ ደግሞ ለሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ሙሉ የማለፍ እድል በመስጠት አይቬሪኮስት፤ ናይጄርያ፤ ቱኒዚያ፤ ግብፅ እና አልጄርያ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ይበቃሉ ብሏል፡፡ ታዋቂው ዓለም አቀፍ የስፖርት ዘጋቢ የሆነው ብሊቸር ስፖርት ለዓለም ዋንጫ ጥሎማለፍ ምእራፍ የደረሱትን የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ልምድና ውጤት ያላቸው እና ብዙም ግምት የሌላቸው ቡድኖች እንደተሰባሰቡበት በመግለፅ፤ 10ሩ ብሄራዊ ቡድኖች ያላቸውን ወቅታዊ አቋም እና የፊፋ እግር ኳስ ደረጃ በማገናዘብ ለዓለም ዋንጫ የሚያልፉት አይቬሪኮስት፤ ናይጄርያ፤ ጋና፤ አልጄርያ እና ቡርኪናፋሶ ናቸው በሚል ገምቷል፡፡ ዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፉ… የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚያልፉ 5 አገራትን ለመለየት ለሚደረግ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ከደረሱ አስር ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ መሰለፉ ፈርቀዳጅ ውጤት እና ድንቅ ስኬት ነው፡፡ እጅግ የሚያጓጓው ትልቅ ታሪክ ግን በዓለም ዋንጫ መድረክ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፍ ነው፡፡

ለምን ቢባል ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ስለሚኖሩት ነው። የመጀመርያው ጥቅም ኢትዮጵያን በዓለም የእግር ኳስ ካርታ ላይ በወርቃማ ቀለም እንድትሰፍር ማስቻሉ ነው። ይህም የአገሪቱን የስፖርት እንቅስቃሴ በከፍተኛ እድገት ማቀላጠፍ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የቱሪዝም፤ የዲፕሎማሲ፤ የባህልና የኢኮኖሚ ገፅታ በመገንባት ከፍተኛ ውጤት ይገኝበታል፡፡ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ 32 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ከሆነች ብሄራዊ ቡድኑ በተሳትፎው ብቻ እስከ 14 ሚሊዮን ዶላር ከፊፋ በኩል የሚከፈለው ይሆናል፡፡ ይሄው የገንዘብ ድርሻ በተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች፤ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶች ሽያጭ እና ንግዶች እስከ 24 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ አልፎ ከ32 ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ከሆነ በኋላ በምድብ ድልድል ከየትኛውም አገር ጋር መገናኘቱም ሌላው ትልቅ እና የሚያጓጓ ታሪክ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከብራዚል፤ ከስፔን፤ ከጃፓን ጋር ትመደብ ይሆናል፤ ወይም በሌላ ምድብ ከአሜሪካ፤ ከሆላንድ፤ ከኢራን እና ከጀርመን ልትገናኝ ትችላለች። በአጠቃላይ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ አልፎ ከየትኛውም አገር ተገናኝቶ የሚደለደልበት ምድብ እና የሚያደርጋቸው ሶስት ጨዋታዎች የሚኖራቸው የታሪክ አሻራ ከፍተኛ ትኩረት የሚያስገኝ ይሆናል። የዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ መብቃት 2006ን በሁሉም ዘርፍ ልዩ የዓለም ዋንጫ ዓመት ያደርገዋል፡፡ ለመጪው እና ተተኪው ትውልድ የሚፈጥረው የአገር ፍቅር መንፈስ እና መነቃቃት በገንዘብ ሊለካ የማይችል ይሆናል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በታላቁ የዓለም አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ በመብቃታቸው ኢትዮጵያዊ ተጨዋች በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ኢንዱስትሪው ተፈላጊነት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በአገር አቀፍ ደረጃ በእግር ኳስ እና በሌሎች ስፖርቶች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ አቅም የሚያድጉበት እድል ከመፈጠሩም በላይ በጅምር እና በእቅድ ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በቶሎ ተገንበተው ስራ እንዲጀምሩ እና እንዲስፋፉ ተፅእኖ ይፈጥራል።

Read 5875 times