Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 November 2011 15:11

የአውሮፓ ሞዴል ባርሴሎና፤ ማን. ሲቲ ወይስ አርሰናል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሃያላን ክለቦች በእዳ እና በኪሳራ መንቀሳቀሳቸው እንዲቆም ካልተደረገ በአውሮፓ እግር ኳስ በሚካሄዱ ታላላቅ ውድድሮች የሚቀረው የአርሰናል ክለብ ብቻ ይሆናል ተባለ ፡፡የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከ2014 የውድድር ዘመን ወዲህ በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ክለቦች እንቅስቃሴ የፋይናንስ ጨዋናት እንዲሰፍን የሚያስገድድ ደንቡን ተግባራዊ ሲያደርግ እንደ ባርሴሎናና ማንችስተር ሲቲ አይነት ክለቦች ከውድድሮች መታገዳቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ፊፋና የአውሮፓ እግር ኳስ በሚያስተዳደሩት የዓለም እግር ኳስ እያደረጉ ያሉት ጫና የማይቆም ከሆነ በታላላቆቹ ሊጎች የሚገኙ ከ20 በላይ ክለቦች ራሳቸው የሚያስተዳድሩትን ሱፕር ሊግ መጀመራቸው እንደማይቀር ሰሞኑን ገልፀዋል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሸል ፕላቲኒ በአህጉሪቱ ያሉ ክለቦች በኢኮኖሚ ቀውስ ዘመን ከሚያገኙት ገቢ የላቀ ወጪ በማውጣት በኪሳራ መንቀሳቀሳቸውን በተደጋጋሚ እየተቸ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ስፖርቱን መቀጠል ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡

በአውሮፓ እግር ኳስ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ላይ ታተኮረ ኮንፍረንስ ሰሞኑን በዙሪክ ሲከናወን ሃያላን ክለቦች 20 ወይም 16 ክለቦች የሚሳተፉበትን የራሳቸውን ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ለመጀመር እንደሚወስኑ ያስጠነቀቁት ለፕላቲኒ ማስፈራርያ በሰጡት ምላሽ ነው፡፡ ክለቦች የራሳቸውን የሊግ ውድድር መስርተው ተጨዋቾቻቸው በብሄራዊ ቡድን ውድደሮችና የወዳጅነት ጨዋታዎች የሚበዘበዙበትን ሁኔታ ለማስቀረት፤ ግዙፎቹ የእግር ኳስ አስተዳዳሪዎች በተለያዩ ደንቦች የሚያደርሱትን ጫና ለማቀዝቀዝና በዓለም ዙርያ የሚኖራቸው የቲቪ ስርጭት ገቢ ለማጎልበት እንሰራለን ይላሉ፡፡ ብሄራዊ ቡድኖች እኛ ደሞዝ የምንከፍላቸውን ተጨዋቾችን በየሁለት ዓመቱ ለ120 ቀናት ወስደው መጠቀማቸው አማርሮናል የሚለው የአውሮፓ ክለቦች ህብረት ፕሬዝዳንትና የባርሴሎና ክለብ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳንድሮ ሮሴል ሲሆኑ ክለቦች እግር ኳሱን ከሚመሩት አካላት ጋር ስምምነት ካልፈጠሩ የራሳችንን አህጉራዊ ውድድር በተናጠል ማዘጋጀት ብቸኛው መፍትሄ ይሆናል ብለዋል፡፡ ክለባችን የ180ሺ አባል ደጋፊዎቹ ንብረት እንጅ ለባለሃብት ሽያጭ የቀረበ አይደለም የሚሉት የባርሴሎና ክለብ ፕሬዝዳንት ሳንድሮ ሮሴል ክለባቸው በ5 አመታት የኮንትራት ውል ለኳታር ፋውንዴሽን የማልያ ስፖንሰርሺፑን በ140 ሚሊዮን ፓውንድ ለመሸጥ የወሰነው በከፍተኛ ወጪ ክለባቸውን ካጠናከሩ የአውሮፓ ሃያል ክለቦች ጋር በተፎካካሪነት ለመቀጠል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የስፔን ክለቦች ከሪያል ማድሪድና ከባርሴሎና እኩል በጀት አለመያዛቸው ተፎካካሪነታቸውን ያቀጨጨው ሲሆን ሁለቱ ክለቦች ከላሊጋው 20 ክለቦች የቴሌቭዠን ስርጭት መብት 66 በመቶ ድርሻ መያዛቸው ልዩነቱን አባብሶታል፡፡ በስፔን ላሊጋ ከሚወዳደሩ ክለቦች ሳንታንዴርና ዘራጎዛ ዘንድሮ በእዳ ቀውስ ኪሳራ ገብተዋል፡፡ በስፔን ላሊጋ ለተጨዋቾች ያልተከፈለ 80 ሚሊዮን ፓውንድ እዳ መመዝገቡና ከእንግሊዝ ክለቦች እንደማንችስተር ሲቲ ያሉት በየአመቱ 190 ሚሊዮን ፓውንድ ኪሳራ በመያዝ መቀጠላቸውም ለእግር ኳሱ የፋይናንስ ቀውስ ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከሚወዳደሩ 20 ክለቦች 16 የሚሆኑት የውድድር ዘመኑን በኪሳራ እያካሄዱ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአውሮፓ የእግር ኳስ ታላላቅ ሊጎች ከሚወዳደሩ ክለቦች 46 በመቶው ኪሳራ በማስመዝገብ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከ650 በላይ ክለቦች በሚያገኙት 14 ዶላር 17 ዶላር ወጪ እያደረጉ መስራታቸውን ለማቆም ቆርጦ ተነስቷል፡፡ በ1980ዎቹና 90ዎቹ በደጋፊዎች ብዛትና በጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ይታወቅ የነበረው የጣሊያኑ ሴሪኤ ውድድር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአቅም ማነስና በክለቦች ፉክክር መዳከም መጎዳቱም ይገለፃል፡፡ በሴሪኤው የምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት እጅግ መቀነስ፤ የአስልጣኞች ወደ ተለያዩ አገራት ሊጎች መኮብለል፤ የስታድዬሞች ወና መሆን እና የሙስና ተግባራት መብዛት የክለቦችን የገቢ መጠን እጅግ አቀዝቅዞታል፡፡
ክለቦች በተጨዋቾች ግዢ በገቡት ፉክክር ለአንድ ተጨዋች ዝውውር እስከ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ እያቀረቡ መስራታቸው የቀውስ መንስኤ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ በአውሮፓ ከሚገኙ የሊግ ክለቦች እዳ 56 በመቶውን ድርሻ የያዙት ደግሞ የእንግሊዝ ክለቦች ናቸው፡፡
በ2008 እኤአ ላይ በዱባዩ ባለሃብት ሼክ መንሱር በ330 ሚሊዮን ፓውንድ የተገዛው ማን ሲቲ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ከ2 ወራት በፊት በ80 ሚሊዮን ፓውንድ የራሱን የስፖርት ማዕከል ለመገንባት ያለው እቅድ የእድገት እንቅስቃሴው አካል መሆኑን አሳውቋል፡፡ የማንሲቲ ባለሃብ ሼክ መንሱር የሃብት መጠናቸው 4.9 ቢሊዮን ዶላር ሲገመት በአጠቃላይ ቤተሰባቸው የ150 ቢሊዮን ዶላር ሃብት እንዳለው ይነገራል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን በ23 ነጥብና እየመራ የሚገኘው የኦስትላንዱ ክለብ ማንችስተር ሲቲ በእንግሊዝ የክለብ እግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛውን ኪሳራ አስመዘግቧል፡፡ በሜዳ ላይ ካለፈው የውድድር ዘመን ጀምሮ ውጤታማ እየሆነ ያለው ክለቡ በፋይናንስ እንቅስቃሴው ግን ገቢው ከወጪው ጋር ሳይመጣጠን ኪሣራ እንደበዛበት ያለፈው የውድድር ዘመን የፋይናንስ ሪፖርቱ አመልክቷል ፡፡ በዱባይ ባለሀብቶች ከ4 ዓመታት በፊት የተያዘው ማን ሲቲ ባለፈው የውድድር ዘመን ያስመዘገበው ኪሳራ 121 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን ይህ ኪሳራ ዘንድሮ ወደ 190 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያድግ ይችላል፡፡ ለተጨዋቾች ግዢ ብቻ ባለፉት 4 ዓመታት 450 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣው ክለቡ ያለፈው የውድድር ዘመን ገቢው 125 ሚሊዮን ፓውንድ ሆኖ ለተጨዋቾች ደሞዝ ደግሞ 133 ሚሊዮን ፓውን በዓመት መክፈሉ ኪሳራውን አባብሶታል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የኤፍ ኤካፕ ዋንጫ ድል ከ35 ዓመታት በዃላ ያስመዘገበው ማን ሲቲ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ማለፉ ሲታወስ ዘንድሮ ለአራት ዋንጫዎች በከፍተኛ ጥንካሬ ግስጋሴ መያዙ እየደረሰበት ያለውን ኪሳራ ሸፍኖታል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከ2014 ጀምሮ ተግባራዊ በሚያደርገው ህጉ ክለቦች በሚያገኙት ገቢ ልክ ወጪያቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያስገድድ ሲሆን ማን ሲቲ አሁን እየተከተለ ያለው አሰራር የቅጣት ሰለባ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ማንችስተር ሲቲ አተሃድ ኮምፕሌክስ የተባለውን የስፖርት መንደር ከእነ ክለቡ ስታድዬም ለማስገባት በ400 ሚሊዮን ፓውንድ ያደረገው የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ክብረወሰን ሆኖ የተመዘገበ ነበር፡፡ አርሰናል በኤምሬትስ ስታድዬም እና በአጠቃላይ በስፖርት መንደሩ ለ15 ዓመታት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ያደረገው በ90 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ከመሆኑ ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ልዩነት ይታይበታል፡፡ይሄ የስታድዬም የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለአውሮፓ የስፖርት ፋይናንስ ጨዋነት ህግ ጥሩ ማመልከቻ ነው፡፡ በስታድዬም እና በተለያዩ የስፖንሰርሺፕና የንግድ ስምምነቶች የአውሮፓ ሊጎች ታላላቅ ክለቦችን የመፎካከር አቅም አጥተው በችግሮች ተወጥረዋል፡፡ በደሞዝ ክፍያ መናር፤ በተጨዋቾች ግዢ ሃብታም ክለቦች ገበያውን መቆጣጠራቸው በአውሮፓ እየተለመደ መምጣቱ የህጉን አስፈላጊነት ያጠናከረው ሆኗል፡፡ክለቦች በእግር ኳሱ ከፍተኛ የሚባለውን መዋእለ ንዋይ ሲያፈሱ በእዳ መንቀሳቀሳቸው ስፖርቱን መቀመቅ እንዳይከት የሰጉ ብዙ ናቸው፡፡ተጨዋቾች ወደ ማን ሲቲ የሚሄዱት በክፍያ ተማልለው እንጅ ዋንጫዎችን ለማግኘት አስበው አለመሆኑን በተደጋጋሚ የሚገልፁት የአርሰናሉ አርሰን ቬንገር ናቸው፡፡

 

Read 7492 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 15:13