Saturday, 31 August 2013 11:58

“የቁጫ ህዝብ እንደ አንድ ብሔር እውቅና ይሰጠው” የሚሉ ሽማግሌዎች የሚሰማን አጣን አሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

እውቅና ሊያሰጥ የሚችል በጥናት የተደገፈ ማስረጃ ለመንግስት አቅርበናል ብለዋል
መንግስት የህዝቦችን ጥያቄ በህግ አግባብ ምላሽ እንዲሰጥ “ሰመጉ” አሳስቧል

ባለፈው ሳምንት ከጋሞጐፋ ዞን ቁጫ ወረዳ፣ በአንድ መለስተኛ ሎንቺና ተሳፍረው አዲስ አበባ የገቡ 50 የአገር ሽማግሌዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር ከቤተመንግስት ጀርባ ተሰብስበው ነበር፡፡ ሽማግሌዎቹ የቁጫ ወረዳ ህዝብ የራሱ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህልና አለባበስ ያለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጥያቄያቸው ከአስር አመት በላይ ሲንከባለል ቢቆይም ምላሽ ባለማግኘቱ በጥር ወር 2005 ስለ ወረዳው ህዝብ ማንነት፣እንደ አንድ ብሄር እውቅና ሊያገኝ ስለሚችልባቸው መስፈርቶች፣ ስለ ባህሉ፣ በህዝቡ ላይ ስለተደረጉ ጥናቶችና ውጤቶቻቸው የሚገልፅ ባለ 20 ገፅ ማስረጃ ለፌዴሬሽን ም/ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤትና ለኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማስገባታቸውን የአገር ሽማግሌዎቹ ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩ ወደ ፌደራል የመጣበትን ምክንያት ሲያስረዱም “የህዝቡ የማንነት ጥያቄ ላለፉት በርካታ አመታት በክልሉና በዞኑ ወደ ጎን በመገፍተሩ ነው” ብለዋል ሽማግሌዎቹ፡፡ ችግሩ እያፈጠጠ የመጣው ደግሞ የቁጫ ተወላጅ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በቁጫኛ (ቁጫቶ) መማር ሲገባቸው በጋሞኛ እንዲማሩ በመደረጉና ህዝቡ በግድ “ጋሞ ነህ” እየተባለ እንዲያምን በመገደዱ እንደሆነ እነዚህ የአገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ጥር ወር ላይ ጉዳያቸውን ለፌደራል መስሪያ ቤቶች ካስገቡ በኋላ፣ መፍትሄ ይገኛል ብለው ቢጠብቁም የባሰ ነገር መከሰቱን የሚናገሩት ሽማግሌዎቹ፤የህዝቡን የማንነት ጥያቄ ያስተባበሩና የደገፉ የተባሉ 13 ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ይሄም የወረዳውን ህዝብ እንዳስቆጣ ገልፀዋል፡፡ የአገር ሽማግሌዎቹ በማስረጃነት አቀረብነው እንደሚሉት የጥናት ውጤት፤ የቁጫ ወረዳ በደቡብ ክልል ጋሞጎፋ ዞን ውስጥ የሚገኝ እና 33 ቀበሌዎችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡ ወረዳው በደቡብ ምዕራብ የሚገኝ ሲሆን በስተሰሜን ከወላይታ፣ በስተሰሜን ምዕራብ ከዓውሮ፣ በስተምዕራብ ከጎፋ፣ በስተምስራቅ ከባሮዳ እንዲሁም በስተደቡብ ምስራቅ ከጋሞ የሚዋሰን ነው፡፡ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በ2000 ዓ.ም ባወጣው መረጃ፤ የወረዳው ህዝብ ቁጥር ከ200ሺህ በላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ወረዳው እንደነጋሞ ካሉት ጎረቤት አካባቢዎች ጋር ተስማምቶ እንደሚኖር የጠቀሱት ሽማግሌዎቹ፤በወረዳው ውስጥ ካሉ 33 ቀበሌዎች ስድስቱ ራሳቸውን ጋሞ ብለው እንደሚያምኑና ከእነሱም ጋር በሰላምና በመግባባት ለረጅም ጊዜ እንደኖሩ፣ አሁንም እየኖሩ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
ሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ.ም 13ቱ ሰዎች ሲታሰሩ ጥያቄው የ13ቱ ብቻ ሳይሆን የ200ሺህ ህዝብ ነው በማለት ከገጠር የመጡ ከአምስት ሺህ በላይ የቁጫ ህዝቦች በወረዳው ዋና ከተማ ሰላም በር ከተማ ተሰብስበው እስር ቤቱን እንዳጨናነቁት የጠቆሙት የወረዳው ሽማግሌዎች፤የአስተዳደሩ ኃላፊዎች ይባስ ብለው ወደ ዞኑ እስር ቤት (አርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት) አምጥተው እንዳሰሯቸው ይናገራሉ፡፡ ይሄም ሳያንስ በእለቱ ተቃውሞአቸውን ካሰሙት የወረዳው ህዝቦች መካከል ከ500 በላይ ሰዎች ተይዘው ታስረው እንደነበርና ቀስ በቀስ መለቀቃቸውን የሚገልፁት እኒሁ የአገር ሽማግሌዎች፤ 13ቱ ግን አሁንም ድረስ አለመፈታታቸውን ይናገራሉ፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል፣ ደግፋችኋል፣ ህዝብን ለረብሻ አስተባብራችኋል በሚል ተጨማሪ 25 ሰዎች መታሰራቸውን የጠቆሙት ሽማግሌዎቹ፤ የወረዳው ፍ/ቤት የመጀመሪያዎቹ 13 ሰዎችና ተጨማሪዎቹ 25 ሰዎች የዋስ መብታቸው ተከብሮ እንዲፈቱ ለአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ማስተላለፉን ይናገራሉ - የፍ/ቤቱን ደብዳቤ በማስረጃነት በማቅረብ፡፡ “ይሁን እንጂ የአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበር አሁንም ሰዎችን ሊፈታ አልቻለም” ሲሉ ያማርራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ተጨማሪ 50 ሰዎች መታሰራቸውንና በ70 ሰዎች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ በመውጣቱ፣ ሰዎቹ ሸሽተው በተለያዩ ቦታዎች መበተናቸውን ሽማግሌዎቹ ይናገራሉ፡፡
የቁጫ ህዝብን ጥያቄ በተመለከተ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ሰመጉ)፤ “መንግስት የህዝቦችን ጥያቄ በህግ አግባብ ምላሽ ይስጥ” በማለት ያወጣው ልዩ መግለጫ በእጃችን ይገኛል፡፡ መግለጫው ከሐምሌ 28 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት የሚገኙትን የ13 ሰዎች ስም እና የሥራቸውን ሁኔታ ከገለፀ በኋላ፣ ባልተጣራ ጉዳይ እስር ቤት መግባታቸው ሳያንስ ከስራቸው ለማሰናበት ማስታወቂያ ያወጡባቸው መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁሟል፡፡ በጎፋ ዞን ውስጥ የጋሞ፣ጎፋ፣ዘይሴ፣ጊዲቾና አፋይዳ ብሄረሰቦች እውቅና ተሰጥቷቸው እየኖሩ በመሆኑ፣ የቁጫ ህዝብም “ቁጫ ብሄረሰብ” ተብሎ እንደ ስደስተኛ ብሄረሰብ እውቅና ይሰጠን በሚል ያቀረበውን ጥያቄ መንግስት በአግባቡ መርምሮ፣በህግ አግባብ ምላሽ እንዲሰጥ ሰመጉ አሳስቧል፡፡የቁጫ ህዝብ “ቁጫቶ” የተሰኘ ልዩ ቋንቋ እንዳለው፣የአንድ ቋንቋ ቤተሰብ ወይም ተመሳሳይ ቀበሌኛ የሚባለው ከ80 በመቶ በላይ ሲመሳሰል መሆኑን፣.ነገር ግን ቁጫ ቋንቋ ከጋሞ ጋር የሚመሳሰለው ከ77 በመቶ በታች እንደሆነ አቶ ወንድሙ ጋጋ የተባሉ ተመራማሪ ያደረጉትን ጥናት ውጤት በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ ኃ/ጊዮርጊስ የተባሉ የቁጫ ተወላጅና የሶሲዮሎጂና የሶሻል አንትሮሎጂ ምሩቅ በበኩላቸው፣ “ቬንደርና ተባባሪዎቹ የተባሉ የውጪ አገር አጥኚዎች በኦሞቲክ ቋንቋዎች ላይ በሰሩት ጥናት፣ የቁጫን ቋንቋ ራሱን የቻለ አንድ ቋንቋ ነው ብለው አረጋግጠዋል” በማለት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ አንድ ጃፓናዊ አጥኚም፣ የቁጫ ቋንቋ ጋሞኛንና ቁጫን ድንበር ለድንበር ያሉ ግን የተለያዩ ቋንቋዎች በሚል በጥናታቸው መግለፃቸውን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(5) መሰረት፣ የቁጫ ህዝብ እንደ አንድ ብሄር እውቅና ሊያሰጠው የሚያስችለውን መስፈርቶች አሟልቷል የሚሉት ሽማግሌዎቹ፤ ከመስፈርቶቹም መካከል ህዝቡ ከ50 ሺህ በላይ መሆኑ ፣የሥነልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክአምድር የሚኖሩ መሆናቸው፣ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያሏቸው መሆናቸው፣የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ (ቁጫኛ) ያላቸው መሆኑ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ መሆኑ ሲሆን ህዝቡም በህገመንግስቱ አንቀፅ 39(2) እና (3) መሰረት ጥያቄያችን ምላሽ ሊያገኝ ይገባል፣ይህን የሚሰማን በማጣታችን ወደ ፌደራል መ/ቤቶች ብንመጣም ሊያናግረን የቻለ የለም፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አንድ ሰው አነጋግረውን ነበር፣ ፌደራል በክልሎች ስራ አይገባም፣ ግን ደብዳቤ እንፅፋለን ብለውናል፣ ምንም እልባት ሳናገኝ ወደመጣንበት ተመልሰናል ሲሉ አማርረዋል፡፡
ቁጫ ከ16ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በ14 ነገስታት ትመራ የነበረች ፣ራሷን የቻለች ባለ ለም መሬት መሆኗን የገለፁት የአገር ሽማግሌዎች፤የታሰሩት ሰዎች ይፈቱልን፣ጥያቄያችን ይመለስ፤ በየቀበሌያችን ገብተው ነፃነት እንዳይሰማን ያደረጉ ታጣቂዎች ይውጡልን፣እንደ አንድ ብሄር ለመታወቅ መስፈርቶችን እናሟላለን፤ ይህን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይስማልን በማለት በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ “ከዚህ በፊት 50 የአገር ሽማግሌዎች ወደ መዲናዋ መጥተን ጠ/ሚኒስትሩን ለማነጋገር ሞክረን አልተሳካም፣ ሁለተኛውም የአገር ሽማግሌዎች ቡድን ምንም ምላሽ ሳያገኝ በእንግልት ተመልሷል” ያሉት የአገር ሽማግሌ፤ አራት እና ሰባት እየሆኑ ወደ ፌዴራሉ መ/ቤቶች ከሰባት ጊዜ በላይ መጥተው ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ያለው የወረዳው አስተዳዳሪዎች በአብዛኛው የጋሞ ተወላጆች በመሆናቸውና ቁጫ እውቅና ካገኘ የስልጣን ወንበራቸው እንዳይነጠቅ በሚፈሩ ባለስልጣናት ነው ብለዋል፡፡“ከዚህ በፊት የወረዳውን ህዝብ ስብሰባ በመጥራትና በማነጋገር በወረዳው ላሉ የጋሞ ተወላጆች እድል በመስጠት ድራማ ሰርተውብናል” ያሉት ሽማግሌዎች፤ጥያቄው የህዝብ ሳይሆን የግለሰቦች ፍላጎት እንደሆነ በማስመሰል መንግስትን ለማሳሳት በደቡብ ቴሌቪዥን የተላለፈውን ፕሮግራም አጥብቀው እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ሽማግሌዎቹ ይህን ይበሉ እንጂ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ “የጋሞን ህዝብ አንድነት ለመበታተን የተፈፀመ ሴራ ነው” ብሏል፡፡

 

Read 3797 times