Saturday, 17 August 2013 11:28

“መንግስት ህገመንግስቱ ሲጣስ ከዳር ቆሞ አይመለከትም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

አቶ ሽመልስ ከማል፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ
መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተካሄዱ ስላሉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ምን ይላል? በተለይ አንድነት ፓርቲ የፀረሽብር ህጉን ለማሰረዝ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዴት ያየዋል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ከሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ጋር በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

በተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተካሄዱ ስላሉ ሰላማዊ ሰልፎች የመንግስት አቋም ምንድነው?
ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መልኩ ማንም ሰው በፖለቲካ የመደራጀት መብት አለው፡፡ ዝም ብለን ካየነው ህገመንግስታዊ መብትን ተጠቅሞ ሃሳብን መግለጽ ነው፡፡ ይህን መብት የማጣጣምና የመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ባይቃወሙና ባይሰባሰቡ ነው እንጂ የሚደንቀው ይህን ማድረጋቸው ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሚያነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ የበርካታ ዜጐች ስጋት የሆኑ ጉዳዮችም አሉ፡፡ በተለይ ከአክራሪ ጽንፈኛ ሙስሊም ቡድኖች ጋር አንዳንድ ፓርቲዎች የፈፀሙት ያልተቀደሰ ጋብቻ አሳሳቢ ነው፡፡ በሀገራችን ህገመንግስትም ፖለቲካ እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ስብሰባዎች፣ የፖለቲካ ሰልፎች እንኳን ሃይማኖተኞችን ሊቀላቅሉ፣ የሃይማኖት ተግባራት ከሚፈፀምባቸው ቦታዎች በተወሰነ ርቀት መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ግን ሁለቱ መቀያየጥ የሌለባቸውን ነገሮች ሲያካሂዱ እያየናቸው ነው፡፡ ይሄ ለነሱም ሆነ ለማንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ተገቢ ያልሆነ ህገመንግስቱን የሚፈታተን አካሄድ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ይህ ተግባር የህግን የበላይነት የሚፈታተን መሆኑን አውቀው እርምጃቸውን ማስተካከልና መታረም አለባቸው ማለት ነው፡፡ ህገመንግስቱ ያሰመረባቸው ቀይ መስመሮች መታለፍ የለባቸውም፡፡ በሌላ በኩል ይሄ ስጋት ጽንፈኛ አክራሪነት የአለም ስጋት የሆነበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህን መነሻ አድርጐ ርካሽ ተወዳጅነት ለማግኘትና ጊዜያዊ ጥቅምን ለማግኘት የሚያስቡ ሃይሎችን ማወደስና ከእነዚህ ጋር መተቃቀፍ ለማንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ የሀገራችን ሙስሊሞች የማንም መጠቀሚያ አንሆንም እያሉ በአደባባይ ሲናገሩ እያየናቸው ነው፡፡ በየአደባባዩ የጠሩትና ሚሊዮኖችን እናስከትላለን ብለው የለፈፉለት ሰላማዊ ሰልፍ፣ በመቶዎችና በአርባዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይዞላቸው ሲመጣ ያዩ ተቃዋሚዎች፣ ሌላ ሃይል እናገኝበታለን ብለው የገቡበት ስሌት አደገኛ ስሌት ነው፡፡ ከሽብርተኝነት ጋር የተፈጠረ ድሪያ ነው የሚሆነው፡፡ እንዲህ አይነቱን ነገር ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል፡፡ መጥፎ አካሄድ ነው፡፡ ካለፈው ስህተታቸው ትምህርት መውሰድ አለባቸው፡፡ ህገመንግስቱ ሲጣስ ዳር ቆሞ የሚመለከት መንግስት አይደለም ያለው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በህግ ተወስኖባቸውና ተፈርዶባቸው አሸባሪ ተብለው በፍ/ቤት የተረጋገጠባቸውን ሰዎች፣ እንደሰማዕታት አድርጐ መደገፍ፣ አሸባሪነትን መደገፍ ነው፡፡ ይሄ ለሽብርተኝነት እውቅና መስጠት ማለት ነው፡፡ ከወንጀል ጋር በሚያደርጉት ድሪያ ባህሪያቸውን እያሳዩ ነው፡፡ ወንጀል ጠቀስ የሆኑ ጉዳዮችን እየነካኩ መሄድ አንደኛው ባህርያቸው መሆኑን የሰሞኑ ድርጊታቸው ማሳያ ነው፡፡ አባሎቻቸው እንኳ ሽብርተኛ ሆነው ከተገኙ ራሳቸውን መነጠል ነው ያለባቸው፡፡
በሠልፎቹ ከሚጠየቁት ጉዳዮች መካከል መንግስት ምላሽ ያሻቸዋል ብሎ የተቀበላቸው የሉም? በተለይ ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ?
ዝም ብሎ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የሚያነሷቸው ካልሆነ በቀር፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ በኩል መንግስት የዜጐችን የሰብአዊ መብት አያያዝ አተገባበር በጣም በተጠናከረ መልኩ እያሻሻለና አድማሱን እያሰፋ በመሄድ፣በቅርቡ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ መተግበሪያ (አክሽን ፕላን) ያወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚያ ላይ የእያንዳንዱን ዜጋ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ጥበቃ ለማስተግበር የሚያስችሉ ዝርዝር መርሃ ግብሮችን ነው ያወጣው፡፡ ተቋማት ያለባቸውን ችግሮች በተጨባጭ አይቷል፡፡ ለዚህም መወሰድ ያለባቸውን መፍትሔዎች በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ የዜጐችን ሰብአዊ መብት ለመጠበቅና አያያዙን ለማዳበር ተግቶ የሚሰራ መንግስት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ዝም ብሎ ከዳር ወጥቶ ማረጋገጫ የሌለውን ነገር መናገር ተገቢ አይደለም፡፡ መንግስትን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ከአደባባይ መፈክርና ከአንደበት ግልጋሎት በተረፈ በጣም የሚያሳስበው ጉዳይ መሆኑን አውቆ፣ ከፖሊሲ አፈፃፀሞቹ ጋር አመጋግቦ ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡
በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ያሉት ሰላማዊ ሰልፎች እና ህዝባዊ ስብሰባዎች በመንግስት ላይ ጫና የመፍጠር አቅም የላቸውም?
እንዴት ነው የሚፈጥሩት! ጐንደር በጠሩት ሰልፍ ላይ 200 የሚሆን ሰው ነው የተገኘው፡፡ በሌሎችም ቦታዎች ተመሳሳይ ነው፡፡ እነሱ “ለምንድነው ስብሰባችን ባዶ የሆነው?”፣ “አዳራሻችን ባዶ የሆነው?” ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ጣታቸውን ወደ ውጪ ከመደንቆር ይልቅ የህዝቡን ፍላጐት ማየትና ወደ ውስጣቸው መመልከት አለባቸው፡፡ መንግስት እንኳንስ በጣት የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ወጥተው ቀርቶ፣ በማንኛውም ሁኔታ ህጋዊ ስራውን ከመስራት የሚያግደው ሃይል አይኖርም፡፡ በመርህ ደረጃ ሃሳብን ይዞ ለመውጣት ቁጥር ወሳኝ ነው የሚል ድምዳሜ ባይኖረኝም፣ በመርህ ደረጃ የሚታየው እውነታው ነው፡፡
መንግስት ተጨባጭ የሆኑ ጥቆማዎችና አስተያየቶች ሲደርሱት ቁጥራቸውን ወሳኝ አያደርገውም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን እነዚህ ሰልፎች ያረጋገጡት ማህበራዊ መሠረታቸው እጅግ ጠባብ መሆኑንና ህዝባዊ ድጋፍና ይሁንታ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ለመሸፋፈን መንግስት ጫና በማድረጉ ሰው ሊወጣልን አልቻለም ሲሉ ነው የሚደመጡት፣ ይሄ መሠረት የሌለው ውንጀላ ነው።
አንድነት ፓርቲ የፀረ ሽብር አዋጁን በማሰረዝ የሚሊዮኖችን ድምጽ እያሰባሰበ ነው፡፡ የሚሰባሰበው ድምጽ አዋጁን ሊያሰርዘው ይችላል?
በይሆናል እና በግምት የሚሰጥ መልስ የለም፡፡ የፀረ ሽብር ህጋችን ከተለያዩ የአለም ሀገራት ተጠንቶ የተቀረፀ ነው፡፡ የዜጐቻችንን ደህንነት ከሽብር ጥቃት ለመከላከል የህግ ከለላ ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ህጉ ተቀርጿል፡፡ በህጉም እስካሁን ሊከሰቱ ይችሉ የነበሩ አያሌ ሙከራዎችን ማክሸፍ ችለናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ስጋት የሚገባቸው ወገኖች እነማን እንደሆኑ ጥርጥር የለውም፣ ዜጐች ግን ስጋት ላይ አይወድቁም፡፡ ህጋዊ ፓርቲዎችንም ስጋት ላይ አይጥልም፡፡ ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን አጣቅሶ ለመሄድ ያሰበ ካለ ግን ድንጋጌው ስጋት ላይ ሊጥለው ይችላል፡፡ ዜጐች ግን ሙሉ ድጋፍ የሰጡት ህግ ነው፡፡
ህጉን ድምጽ በማሰባሰብ ማሰረዝ አይቻልም ማለት ነው?
የህግ አወጣጥ ስርአት በህገመንግስቱ የተደነገገ ነው፡፡ ህግ የሚወጣው በህግ አውጪ አካላት ነው። እነዚህ አካላት ከማውጣቱ ባሻገር ህጉን መሻርም ማሻሻልም ይችላሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የህግ የበላይነት ለማክበርና ለህገመንግስታዊ ስርአት እውቅና ለመስጠት የሚያንገሸግሻቸው ተቋማት እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ህገመንግስታዊ ተቋማትንና ህጋዊ አሠራሮችን ለመቀበል የማይፈልጉ ፓርቲዎች ናቸው ይህን የሚያደርጉት፡፡ የፈለጉትን የመመኘትና የማለም መብት አላቸው፣ ለምን አለማችሁ ተብለው አይጠየቁም፡፡ ለዚህ ሰፊ ነፃነትና የፖለቲካ ምህዳር አለ፡፡ ስለዚህ ማለምና ማሰብ ይችላሉ፡፡

Read 3328 times