Saturday, 13 July 2013 11:12

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሻምፒዮና የመጀመርያ ጨዋታ ታደርጋለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በ3ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሩዋንዳ አቻውን ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም ሊያስተናግድ ነው፡፡ CHAN የሚባለውና የአፍሪካ አገራት በውስጥ የሊግ ውድድሮቻቸው በሚጫወቱ ተጨዋቾቻቸው በሚሰሩት ብሄራዊ ቡድን የሚካፈሉበት ሻምፒዮንሺፕ ላይ ኢትዮጵያ የምትጫወተው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ሻምፒዮናው በ2014 እኤአ ላይ ለ3ኛ ጊዜ የሚዘጋጀው በደቡብ አፍሪካ ሲሆን ከሴካፋ ዞን 3 ብሄራዊ ቡድኖች የተሳትፎ ኮታ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሻምፒዮናው ቅድመ ማጣርያ ከኤርትራ ጋር ተደልድሎ ነበር፡፡

ኤርትራ ከተሳትፎ ራሷን በማግለሏ በ3ለ0 የፎርፌ ውጤት የኢትዮጵያ ቡድን በቀጥታ ለመጨረሻው የደርሶ መልስ የማጣርያ ግጥሚያዎች ደርሷል፡፡ በሴካፋ ዞን በሚደረጉ የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች ከኢትዮጵያና ሩዋንዳ ባሻገር ብሩንዲ ከሱዳን እንዲሁም ታንዛኒያ ከኡጋንዳ የሚጋጠሙ ይሆናል፡፡ አሙቫቢ ወይም ተርቦቹ በሚል ስሙ የሚታወቀው የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን በ2011 እኤአ ላይ በተደረገው 2ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮና ተሳታፊ እንደነበር ሲታወስ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2009 እኤአ ላይ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ በተደረጉት ሁለቱም ሻምፒዮናዎች ማጣርያዎችን እንኳን አልተካፈለም ነበር፡፡

በዋና አሰልጣኝ ኤሪክ ኒሺሚያማና የሚሰለጥነው የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ያለፈውን 1 ሳምንት በየቀኑ ልምምድ እየሰራ ቆይቷል፡፡ ቡድኑ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ የቆየው በአዲስ አበባው ጨዋታ ጠንካራ ብቃት ለማሳየት ነው ዋና አሰልጣኝ በመልሱ ጨዋታው በአማሃሮ ስታድዬም ኢትዮጵያን ጥሎ ያልፋል ብለዋል፡፡ 1ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮና በኮትዲቯር አስተናጋጅነት በ2009 እኤአ ላይ ሲካሄድ በፍፃሜ ጨዋታ ዲሪ ኮንጎ 2ለ0 ጋናን በማሸነፍ የመጀመርያዋ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ በ2011 እኤአ ላይ ደግሞ 2ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮናን ሱዳን አዘጋጅታ ቱኒዚያ 3ለ0 በሆነ ውጤት አንጎላን በመርታት ዋንጫውን ወስዳለች፡፡

Read 2745 times