Saturday, 06 July 2013 11:17

“የፍልስምና ፫” መረቦች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

ሕይወት የጤዛ ጠብታን ያህል አንሣ የምትታሰበን ጊዜ አለ፡፡ በተለይ ፍልስፍናና ሃይማኖት ውስጥ! ከዚያ ጤዛ ውስጥ ግን ፀሐፍት ዝንታለም የሚኖር ቀለም ያወጣሉ። ያንን ያወጡትን ቀለም በየመልኩ እንደየዘመኑ ያቀጣጥሉታል፡፡ ትውልድ ደግሞ ያንን ምድጃ አቅፎ ይቃጠላል፤ ወይም ይሞቃል…ለዚህ ነው ጠለቅ ያሉ ፍልስፍናዊ ሃሳቦችና ፍልስፍና የተሻሹ፣ ወይም የተቀላቀሉ ግጥሞችም በየጅማቶቻችን ሥር እየነደዱ የሚያነድዱን! ሕያው የሆነ አሳቢን ማለቴ እንጂ ፍሙ ቢጫንባቸው ሕይወታቸውን ሙሉ በድብርት የሚተኙ ሰዎች እንደሚበዙ ዘንግቼው አይደለም! ጥበብ የማንን በር እንደምታንኳኳ ይታወቃል፡፡ ከጭራሮ አጥር ጋር አትቀልድም…ከብረት በር ጋር ትቧቀሳለች እንጂ! ዛሬ የምዳስሰው መጽሐፍ የፍልስፍናውና የሃይማኖቱን ሰፈር ስለሚነካ ነው ልቤ እየዘለለች ጥበብ አጥር ላይ ፊጥ ማለት ያማራት፡፡ ስለጥበብ አናወራም፡፡ ጥበባዊ መዐዛ ስላለው የቴዎድሮስ ተክለአረጋይ መጽሐፍ ግን እኔ ጥቂት እላለሁ። አንባቢዎቼ ደግሞ ያነብቡና እኔንና መጽሐፉን እያመሳከሩ ያነብባሉ፡፡

ቴዎድሮስ “ፍልስፍና 1 እና 2” እያለ የሀገራችንን ሰዎች ፍልስፍናና እምነት በመፈልፈል ወደ 3ኛ አድርሶናል፡፡ ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔቱ ቴዎድሮስ በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ በሚሠራበት ጊዜ አንጀት የሚያርሱ ቃለ ምልልሶችን በድፍረት ስለሚሰራ ብዙዎቻችን በአድናቆት አንገታችንን ነቅንቀንለታል፡፡ ታዲያ እነዚህ መጽሐፍትም በቃለ ምልልስ መልክ የቀረቡ ስለሆነ ሸጋ አድርጐ ይሠራዋል የሚል እምነት ይዘን ያነበብን ይመስለኛል። በእነዚህ መጽሐፍት ውስጥ ትልቁ ነገር አጠያየቁ ቢሆንም ተገቢ ሰዎችን አስሶ ማግኘትም ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን መሠረት አድርጐም ባሁኑ “ፍልስፍና ፫” - የፍልስፍና መምህርና የቀለም ተመራማሪ፣ የአዕምሮ ሀኪሞች፣ የሥነ ከዋክብት አዋቂ (ወዳጅ) እና ሌሎችን አካትቶ አቅርቧል፡፡ የኔ ትኩረት ግን ወደሰው ልጆች ጥያቄ ቀረብ የሚሉትንና ነፍስን የሚንጡትን ፍልስፍና ጉዳዮች ማየት ነው፡፡ በዚህ ትኩረት ደግሞ አቶ ዜና ላይኩኝ (የእምነት የለሽነት ተከታይ) አቶ ተፈሪ ንጉሤ (የገዳ ሥርዓት ተንታኝ)፣ ቀዳሚዬ ይሆናሉ፡፡

የጌታሁን ሄራሞ (ኬሚካል ኢንጂነር) የቀለም ትንታኔ ጥሞና የሚጠይቅ፣ አዲስና ያልተለመደ ሳይንስ ስለሆነ እርሱን ለብቻ ማጤን የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ሌሎቹም ብዙ መልክ አላቸው፡፡ የኔ ቀዳሚ ተመስጦ ግን የገዳ ሥርዓት ተንታኝ ላይ ነው፡፡ ስለገዳ ሥርዓት አቶ ተፈሪ ያነሱት ነገር “ኢትዮጵያዊ በመሆኔ እኮራለሁ” ለሚለው አባባል ትልቅ አቅም የሚጨምር ይመስለኛል። የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ከግሪክ ሥልጣኔ ዘመን የቀደመ መሆኑን አቶ ተፈሪ መናገራቸው፤ ቴዎድሮስም ይህንን ነገር ጉዳዬ ማለቱ በራሱ ትልቅ ደስታ ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያውያን የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላና የፋሲል ግንብ ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲም ማህፀኖች መሆናችን… አቦ ደስ ይላል! ይህንን ነገር ከጓዳ አውጥቶ በአደባባይ መናገርም በራሱ ታሪክ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ አንድ ሰው አባ ገዳ ሆኖ ለመመረጥ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ብቻ መሆን የለበትም፤ በባህሉ መሠረት ሌላው ብሔርም በጉዲፈቻና በሌላም መንገድ የብሔሩ አባል ሆኖ ሊመረጥ ይችላል፡፡ (ለመሆን የሚጠበቅበት ጊዜ ግን አለ) አቶ ተፈሪ አንድ ልጅ ወደ አባገዳነት የሚደርስበትን እርከን ሲናገሩ “አንድ ሕፃን እስከ 8 ዓመቱ ድረስ “ኢቲመኮ” ነው የሚባለው፡፡ እነዚህ ሕፃናት ገና እንደተወለዱ በዚያ ዓመት ያለው አባ ገዳ አባላት ነው የሚሆኑት፡፡ ልጆቹ በዚህ ዕድሜያቸው የሚማሩት ዋናው ነገር ማህበራዊ ግንኙነት ነው። ህዝቡን ማወቅ፣ ባህሉንና ቋንቋውንም ማወቅ አለባቸው፡፡ እንዲታወቁ ሊማሩ ግድ ይላል፡፡ ከ9-16 ዓመት እድሜ ያሉት ደግሞ “ደበሌ” ይባላሉ። እነሱ ደግሞ ልምምድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ልምምዱ ውሃ ዋና፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ከብቶች መጠበቅ፣ መላላክ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ደበሌ ፎሌ፣ ዶሪ የሚባሉትን የዕድሜ እርከኖች ሲያልፉ 40 ዓመት ይሞላቸዋል፡፡ ከዚያ ከ41-48 ያለው የነርሱ አባገዳ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በሕብረተሰቡ ውስጥ የፍትህ መጓደል ሲከሰት በቀጥታ የሚመለከተው በፎሌ የዕድሜ ክልል ያለውን ነው፡፡ በኦሮሞ ብሔር የውሃ ዋና፣ ተኩስና የመሳሰሉት ሥልጠና የሚወሰድበት ዕድሜ ይህ ነው፡፡ 40 ዓመት ሲሞላው ሕዝብን ለማስተዳደር ይወዳደራል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር አንድ ሰው ምንም ያህል በሕዝቡ ቢወደድና አስተዳደሩ የተመቸ ቢሆን ከስምንት ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ እንዳይቆይ ሥርዓቱ ይከለክላል፡፡ ምርጥ ዴሞክራሲ! የአቶ ተፈሪ ቃለ ምልልስ ስለ ገዳ ሥርዓት ሲያወራ የሴቶችን መብት፣ የሕፃናት ፓርላማ ጉዳይ ሁሉ ያነሳል፡፡

ለገዳ ሥርዓት ይህ አዲስና ብርቅ አይደለም በማለት፡፡ ያ ብቻ አይደለም ስለግሪክ ፍልስፍና ቀዳሚ ያለመሆን ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “ሶቅራጥስ ግብጽ መጥቶ ነው የተማረው። ሶቅራጥስ አንድም ነገር አልጻፈም፡፡ ፕሌቶ ነው የጻፈው፡፡ ፕሌቶ ደግሞ አርስቶትልን ያስተምራል። ታሪክ የሚያረጋግጥልን፣ ብዙ ተሸላሚ መጽሐፍት ለምሳሌ ማርቲን ባርናል የፃፈው The Black Atena” መጽሐፍ የሚያሳየን የግሪክ ፍልስፍና የሚባለው የአፍሪካ ፍልስፍና እንደሆነ ነው፡፡ ጆርጅ ጀምስ “The Stolen legacy” የሚለውን መጽሐፍ ጽፎ በአምስተኛው ቀን ተገድሏል፡፡ ያስገደለው የግሪክ ፍልስፍና የግሪክ ሳይሆን የአፍሪካ ፍልስፍና መሆኑን በግልጽ ስላሳየ ነው፡፡ አቶ ተፈሪ ብዙ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ከገዳ ጋር በተያያዘ ስለዋቄ ፈና ተንትነዋል፡፡ እኔን ያረካኝና ያስደሰተኝ ጠቅለል ያለው የገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ውልደትና ውበት በሀገራችን መሆኑ ነው፡፡ ምናልባት በሌሎቹ ነገሮች ወደኋላ እንደተመለስነው በዚህም ወደኋላ ተመልሰናል የሚያሰኝ ይመስለኛል፡፡ ይሁንና በእኒህ ተንታኝ ላይ ያየሁዋቸው ችግሮች አሉ፡፡

አንደኛው “እምነቴ ፕሮቴስታንት ነው” ማለታቸው paradox (አያዎ) ነው፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ስለሚነትኑት የዋቄፈና እምነት ሲያወሩ ሰይጣን የሚባል ነገር የለም፤ ከሁሉ በላይ የሆነ አምላክ ብቻ ነው እያሉ አጠቃላይ የክርስትናንና ሌሎቹንም እምነቶች በዋቄ ፈና ወገን ሆነው ይናገራሉ፡፡ መልሰው ደግሞ ጓደኞቼ ስለ ክርስቶስ አወሩልኝና ፕሮቴስታንት ሆኜ ነበር ይላሉ፡፡ የሚያምኑት ግን በዋቄፈና ነው፡፡ ስለዚህ የሚጫወቱበትን ሜዳና መለያ ቀይረዋል፡፡ አሁን ያሉበትን እምነት እንጂ ቀድሞ የነበሩበትን መናገራቸው ስህተት ነው፡፡ ለሁሉም እምነትና ፖለቲካ አሁን ያለንበት ነው ተጠቃሽ፡፡ ይሁንና ስለገዳ ሥርዓት በመረጃ በሰጡት ዕውቀት፣ ባጐናፀፉን የማንነት ክብር ተደስቻለሁ፡፡ ስድስተኛ እንግዳ ሆኖ የቀረበው ዜና ለይኩን፤ እግዚአብሔርም ሆነ ሰይጣን የሉም የሚል እምነት አለው፡፡

ቴዎድሮስ ኢ - አማኝነት ከየት መጣ? ሲል ለጠየቀው ጥያቄ ዜና የመለሰው እንዲህ ነው፡- ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ነው ኢ- አማኝነትን የፈጠረው፡፡ ከግሪክ ታሪክ ጀምሮ ብታይ አለማመን ያስገድል ነበር፡፡ ሶቅራጥስን ያስገደለችው አንዲት ትንሽ ጥያቄ ነች፤ አይደል? ግን ትክክለኛ ጥያቄ አልነበረችም፡፡ በዱሮው ዘመን የመጀመሪያው ጥያቄ “እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ከሆነ፤ ሁሉን አድራጊ ከሆነ ለምን ይህን ያህል ክፉ ነገር በዓለም ላይ ይኖራል?” የሚል ነው፡፡ ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የማንም አማኝ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ለእኔማ እግዚአብሔር የለም፡፡ ስለሌለ በዓለም ላይ ክፉ ነገሮች ብዙ አሉ፡፡ በመኖራቸው አዝናለሁ፡፡ ግን የሕይወት መንገድ ነው፡፡” እያለ ነው ዜና የሚቀጥለው፡፡ እዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ቴዎድሮስ (ጠያቂው) እና ዜና (ተጠያቂው) በሃሳብ ቡጢ ሁሉ ይገጥማሉ፡፡ ዜና መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሳል፤ ሌሎች መጻሕፍትንም ጭምር፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ “የእግዚአብሔርን መኖር ፋይዳ እና ጥበቡ ሌላ ቢቀር በሥነ ምግባር ትምህርት ቤትነቱ እንኳ አስፈላጊ አይሆንም?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ዜና አይሆንም፡፡ ግብረገብን የፈጠረው ሃይማኖት አይደለም፡፡ ከሰብዕና ላይ ነጥቆ የወሰደው ነው፡፡ ቡድሂስቶች ጋ ሂድ፡፡

ከኛ የበለጡ ደጐች ናቸው፡፡ ክርስትና ወይም እስልምና አይደለም ደግ ያደረጋቸው፡፡ ክርስትናን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን አያውቁም፡፡ ማንኛውም ሃይማኖተኛ ጥቅምን አስቦ ነው እግዚአብሔርን ያመነው፤ ዘላለማዊ ሕይወትን ለማግኘት፡፡ እኔ ደግ ስሆን ግን ምንም አስቤ አይደለም፡፡ ደግ መሆን ስላለብኝ፤ ሌላ ሰው ደግ ቢሆንልኝ ፋለምፈልግ ነው፡፡ ሁሉንም ሃሳቡን መዘርዘር ባልችልም ዜና ለይኩን መጽሐፉ ውስጥ የተሻለ ምክንያት ይዘው ከተሟገቱት ወይም ከተነተኑት ይመደባል፡፡ ምናልባት የጥያቄው አቅጣጫ ብቻ ይህንን ያደርጋል ማለት አይቻልም፡፡ መልስ የመስጠት አቅሙም የበረታ ነው፡፡ ይሁንና ቀደም ባሉት አንቀፆች ላይ ስለቡድሀ ሃይማኖት ሲጠቀስ፣ እነርሱም አምላክ አለ ብለው ስለሚያምኑ ከእርሱ እምነት ጋር ይጋጫል፡፡ በእርሱ መልስ ከሄድን ክርስትናና እስልምናን ብቻ የሚሞግት ነው፡፡ ይህንን ቴዎድሮስን እንዴት ዝም ብሎ እንዳለፈ አልገባኝም፡፡

አንዳንድ ቦታ ጥሩና ተገቢ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ መገኘቱ ነው ቴዎድሮስን የልብ አድራሽ የሚያደርገው፡፡ እዚሁ ዜና ጋ ሌላም ግራ አጋቢ ነገር አለ፡፡ “ደግ እንዲያደርግልኝ ደግ አደርጋለሁ” ይላል፤ ይህ ማለት’ኮ እርሱ ጥቅም ፈልገው ነው እንዳላቸው ሰዎች ጥቅም መፈለጉን ነው የሚያሳየው፡፡ ከዚያም ስለ ቡድሂስቶች ሲናገር “ከኛ የበለጡ ደጐች ናቸው፡፡” በማለት ይገልፃል፡፡ እሱ ማነው?...አማኝ ነው እንዴ? የተጋጨ ሃሳብ ነው፡፡ እንዴት ልብ እንዳላለው አልገባኝም፡፡ እዚህ ጥራዝ ውስጥ በጣም የደነቁኝና የተመቹኝ ያሉትን ያህል ቀለል ያሉብኝና ከዛፍ እንደረገፈ ቅጠል ዝም ብለው የተንኮሻኮሹብኝም አሉ። ለምሳሌ የሥነ ክዋክብቱ ጉዳይ ምንም ስሜት አልሰጠኝም፡፡ ገለባ ሆኖብኛል፡፡

ይህንን ስል ግን ተጋባዡ ዕውቀቱን አላካፈለም እያልኩ አይደለም፡፡ በቂ የሆነ አቅም ያለውና ለቦታው ተመጣጣኝ ሰው ነው፡፡ “ፍልስምና” በሚለው የጥበብ ሰማይ ላይ የዚህ ዓይነት ፈዛዛና ተራ ሃሳቦች ሚዛን ደፊ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ ምናልባት ባለፉት ዓመታት የወጡ የህትመት ውጤቶች ጉዳዩን እያነሱ አሰልችተውን ይሆን? ከፍልስምናም ዘር ጡንቻ ያለው የየዕለቱ ሞጋች ሲሆን ደስ ይላል፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል የተሰጡ ሁለት ሃሳቦችም በዚሁ መጽሐፈ የተጋጩ ይመስለኛል፡፡ የዶክተር መስፍንና የኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ሃሳቦች፡፡ ዶ/ር መስፍን፤ ሕፃን ልጅ ሲወለድ አእምሮው እንደነጭ ወረቀት ነው ሲሉ፣ ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ደግሞ የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ጠቅሶ የሰው ልጅ ሲወለድ ከእናቱ ማህፀን የተወሰነ ዕውቀት ይዞ ነው እያለ ይሞግታል፡፡ የአዳማ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህሩ ፈቃዱ ቀነኒሳም በብዙ ዘርፎች ፍልስፍናን ይተነትናል፡፡ ያሁኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መምህር ግን ከቀድሞው መምህር እሸቱ አለማየሁ ጋር ሲተያዩ የዕውቀት ልዩነት የተፈጠረ ይመስላል። መጋቢ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁኮ ልበ ብርሃን፣ ጣፋጭና ልዩ ዓይንና አተያይ ያላቸው ብሩና ናቸው። ከሃይማኖቱ ጐራ ተለቅ ያለ ሃሳብ፣ አንፀባርቀዋል፡፡ በጥቅሉ “ፍልስምና ፫ ለእኔ እጅግ በተሻለ ሁኔታ በሳል ሰዎችን የያዘችና አዳዲስ ነገሮችን ያሳየች ናት። አንዳንዴ እየሾለኮ ያመለጡ ሃሳቦችን የቴዎድሮስ መረብ ማስገር ቢሳነውም! ዕውቀትና በሣል ሃሳብ የሚገኘው ታዋቂ ከመሆን ሳይሆን ከአዋቂነት ስለሆነ ጥሩ ጥሩ ሃሳቦች ተነስተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም!

Read 3021 times