Saturday, 11 May 2013 14:04

“ጀግና እወዳለሁ፤ ዘፋኝ ባልሆን ወታደር ነበር የምሆነው”

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(15 votes)

ማህበሩ የጓደኞች ነው የቤተሰብ?

የት/ቤት ጓደኞቼም የቤተሰብም አለኝ፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የተጀመረ ነው፡፡ አንዳንድ ጓደኞቼ፣ እህቶቼ ቢያልፉም እስከዛሬ ይሄው ማህበሩን እንጠጣለን፡፡ ዛሬ አንቺም ወደ ቤቴ የመጣሽው የመድሃኒያለም ማህበር ትናንት አውጥቼ ነው፡፡ በጣም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የትምህርት ቤት ጓደኞችሽ---የት ነው የተማርሽው? የቄስ ትምህርት አባታችን አስተማሪ በቤታችን ቀጥረው ነው ያስተማሩን፡፡ ከ1ኛ- 8ኛ ክፍል ደግሞ አስፋው ወሰን ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር በ21 እና በ27 ማህበር አለን፤ ማህበር ሲኖር በየቤታችን አዝማሪ ይቆማል፤ ማስንቆ የሚጫወት፡፡ ወንጂና ናዝሬትም እህቶቼ አሉ፤እዛም እየሄድን እንዝናናለን፡፡

እረ እንደው ተይኝ አልኩሽ ---- የተንፈላሰሰ ዘመን ነበር፡፡ በማህበራችሁ ቀን የሚጫወቱት አዝማሪዎቹ የሚታወቁ ነበሩ? አዎ፡፡ እነ ወረታው፣ ባይረሳው---- እንዴት ቆንጆ ድምፅ አላቸው መሠለሽ፡፡ እነሱ ወደ ቤታችን ሲመጡ ታዲያ ሁሉም ግጥም ሰጪ ነው፤ ሁሉም ተቀባይ ነው፡፡ ቤትም ባይመታም፡፡ ማሲንቆዋቸውን ይዘው ይመጣሉ፤ ጨዋታው ሌላ ነው አልኩሽ፡፡ ደሞዝ እኮ የላቸውም ግን በየወሩ ፅዋ የገባበትን ቤት ስለሚያውቁ ማህበሩ በሚወጣበት ቤት ይመጣሉ። መጀመሪያ ፀሎት ይደረግና ምሳ ይበላል፣ ከምሳ በኋላ የንስሃ አባቶቻችን ያሳርጋሉ፡፡ ከዛ በኋላ አሸሸ ገዳሜ ነው የእኔ እናት፡

ግጥም ከመስጠት ወደ ዘፋኝነት ገባሽ ማለት ነው?

ያን ጊዜ ዘፋኝነትን አልሜው አላውቅም ነበር። ድምፃዊ ሰይፉ ዮሐንስ የሚባል ወንድም ነበረኝ፡፡ ወላጅ አባታችን ዘፋኝ ሆነ መባልን ሲሰሙ የሞተ ያህል ነው ያለቀሱት፡፡ አለማወቅ እኮ ነው--- ማን ያውቀዋል ይሄንን፡፡ አባቴ በጣም አዘኑ…የወንድሜን መታመም ሲሰሙ ግን ድንጋጤአቸው ባሰ፡፡ በጣም በጣም ደግ ልጁ ነበረ፡፡ እርሱም ሞተ፤ አባቴ በጣም ተፀፀቱ --- ምን ታደርጊዋለሽ? አለማወቅ ይጎዳል። ወንድሜ በሞተ በዓመቱ ነው አባታችን የሞቱት፤ በእርሱ ሃዘን (እንባ) ወንድሜ ከሞተ ከአስር ዓመት በኋላ ነው ሙዚቃ የጀመርኩት፡፡ አባቴ ዘፈን አይወዱም ነበር፡፡ ግን በገና ነበራቸው፤ የቅዳም ሱር እለት በገናቸውን አውጥተው ሲደረድሩ ፤የገና ዕለት ጌታን እያመሰገኑ ሲጫወቱ የድምፃቸው ማማር ልዩ ነው ---- እናቴም ጥጥ ስትፈትል እያንጎራጎረች ነበር፡፡ ‹‹…ባለድሪ›› የሚለውን ዘፈን ከእርስዋ ነው የወሰድኩት። ‹‹…ገዳማይ ---- ገዳማይ ---ገዳማይ›› እያለች ታንጎራጉራለች፡፡ የእናቴን ድምፅ ወንበር ስር ተደብቀን ወይም ግድግዳ ተከልለን ነው የምንሰማት። እማዬ ድምፅዋ በጣም ነበር የሚያምርው፡፡ አሁን በህይወት የለችም፡፡

እናትሽ የሙዚቃ ስራ ስትጀምሪ በህይወት ነበሩ?

አዎ! ድምፄን የሞረድኩበትን ‹‹አንተ ባለድሪ” የሚል ዘፈን እናቴ ትወደው ነበር፡፡ በአባትዋ ጎንደሬ ስለሆነች ጨዋታው ይስባታል፡፡ የመጀመሪያ የካሴት ስራዬንም እናቴ እንዴት ትወደው ነበር መሰለሽ፡፡

ከዘፈን በፊት ምን ነበር የምትሰሪው?

“ፎር ሽፕ ትራቭል ኤጀንት” የሚባል ድርጅት ውስጥ ትኬት ኤጀንት ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ ራስ ሆቴል ዴስክ ነበረችኝ፡፡ እዛ እንግዳ ይመጣል፡፡ እንግዶችን ተቀብሎ የሚፈልጉትን መረጃ መስጠት፣ መኪና ማከራይት፣ ፎርም ማስሞላት፣ ዲፖዚት መቀበል ነበር ሥራዬ፡፡ ድርጅቱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተዘጋ። በወቅቱ የልጆች እናት፤ የቤተሰብ ሃላፊ ነበርኩ---‹‹ምን ሆኜ ነው የምኖረው..›› ብዬ ሳስብ፣ ጓደኞቼ “እነ በቀለች ክትፎ ከትፈው እየሸጡ ይኖሩ የለ፡፡ ክትፎ ክተፊ›› አሉኝ፡፡ ክትፎ ግን ሞያ ይጠይቃል አይደል-- ሞያ ለእኔ!! እኔ እናትሽ እኮ አንቱ የተባልኩ ባለሞያ ነኝ፡፡ የወላጆቼ ቤት እዚህ ካዛንቺዝ ነበር። እዛው ጊቢ ውስጥ አንድ ክፍል ተሰጥቶኝ እኖር ነበር፡፡ ክትፎ ቤት ከፈትኩ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ሰዎች ክትፎ ሊበሉ ቀብረር ያለውን ድምፃዊ ከተማ ይፍሩን ይዘውት መጡ፡፡ ያን ቀን አንድ ዕቃ ጠፍቶብኝ ተበሳጭቼ ነበር፡፡

ይሄን ያህል የተበሳጨሽው ምን ቢጠፋብሽ ነው?

አንድ ሙሉ ካርቶን ውስኪ፡፡ አንድ ዘመድ ነበር--- አውጥቶ ሽጦብኝ ብስጭት ብዬ ነበር፡፡ አልቅሼ ፊቴን ስጠራርገው የልጅነት መልክ ጥሩ ነው፣ ወለል ‹‹ፏ›› ነው የምለው፡፡ እነ ከተማ ክትፎውን እየበሉ ይጨዋወታሉ፡፡ ከዚያ ከተማ መዝፈን ማንጎራጎር ጀመረ፡፡ እኔም ከጎኑ ቁጭ ብዬ አንጎራጉራለሁ፡፡ ከዛ ከተማ ድንገት ብድግ ብሎ ‹‹እዚህ ቤት ሁለተኛ ክትፎ እንዳይከተፍ›› አለ፡፡ ‹‹ምነው አመምዎት?›› አልኩኝ ያልተስማማቸው፣ አለርጂ የሆነባቸው መስሎኝ፡፡ ‹‹ይሄን ቆንጆ ድምፅ ይዘሽ በምን ምክንያት ነው የማትዘፍኝው?›› አሉ፡፡ ‹‹ድምፅ አለኝ እንዴ?›› አልኩኝ ለራሴ ‹‹ምንድን ነው የምትጠጭው?›› አሉኝ፡፡ እኔ ግን እንኳን በዛ ጊዜ ዛሬም መጠጥ የሚባል አልቀምስም፡፡ ‹‹እረ እኔ ምንም አልፈልግም… አልጠጣም›› አልኳቸው፡፡ ሲያስጨንቁኝ ‹‹ኮካ ይሻለኛል›› አልኩኝ፡፡ ያን ጊዜ ግሩም ነበር ኮካኮላ---ከኮካኮላው ውስጥ ሳላይ ውስኪ ጨምረውብኝ….እንደ ውሃ ጭልጥ አደረኩት፡፡ ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ደስ አለኝ… ‹‹እንዴ ምን ሆኜ ነው ደስ ያለኝ…ምን አገኘሁ›› እያልኩ አስብ ነበር። ለካ ለብታ ማለት ይሄ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ሰንጥቄ ሰንጥቄ ለቀቅኩት ዘፈኑን፡፡ የማንን ዘፈን እንደዘፈንሽ ታስታውሺያለሽ?

ከተማ እኔ ቤት የተጫወተውን ባቲ፣ ትዝታን፣ ተይ ማነሽን ተጫወትኩ --- ከአሁን በኋላ ‹‹አምቦ ውሃሽን አቀዝቅዥ፣ ቆንጆ ውስኪ አቅርቢ --- እኛ እንግዳ ይዘን እንመጣለን ---- አበቃ ክትፎ ቤት›› አሉኝ፡፡ ከዛ ምን አለፋሽ --- ከአለም አንደኛ ሆንኩኝ፡፡

በማግስቱ የምሽት ክበብ ተጀመረ?

መጀመሩስ ተጀመረ፡፡ መጥተው “በይ ተጫወቺ” ሲሉኝ ከየት ይምጣ፡፡ ያቺ የለችማ የተለመደችው ብረት ለበስ…. ታዲያ ወሰድ አታደርጊም ነበር--- እኔ ምኑን አውቄው----በፊትም እኮ ወኔዬን ያመጣው ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ በኋላ እኮ ነው የነገሩኝ፡፡ ግን እየለመድኩ መጣሁ ---- ሌላ ሆነ እንግዳው፣ ደንበኞቼ በዙ---የብር አቆጣጠሬን ብታይ አስቅሻለሁ፡፡ እንግዶቼን ሸኝቼ ስጨራርስ----.ብር እቆጥራለሁ፡፡ ‹‹..አንድ..ሁለት…ሶስት..አራት.. እባካችሁ ተኙ እናንተ ልጆች---መሸ እኮ-- ነገ ትምህርት ቤት ወየውላችሁ..›› ብሩ ከእጄ ይንጠባጠባል፡፡

የሽልማቱ ብር ነው?

ሽልማቱ ተይኝ ይረግፍ ጀመር፡፡ ማን አውቆት ቁጥሩን ----ከትራሴ ስር አድርጌው ነው የማድር --- ልጆቼ በጠዋት ሲነሱ ----ገንዘቡን ለቃቅመው እየሳቁ ‹‹..አንቺን ብሎ ቆጣሪ›› ብለው ይሰጡኛል፡፡

መኖሪያሽም የስራ ቦታሽም አንድ ቦታ ነበር ማለት ነው?

መጀመርያ አዎ፡፡ በኋላ ግን ሃብት መጣ --- ካሳንቺዝ እርሻ ሚኒስቴር አካባቢ ቤት ገዛሁ፡፡ ዛሬ ንብ ባንክ ሆኗል፡፡ ታሪኩ ብዙ ነው ባክሽ…በመሃል ታመምኩ፡፡ ሶስት ወር ሙሉ እጅና እና እግሬ ተይዞ ፓላራይዝድ ሆኜ ተኛሁ፡፡ (የቤት ስልክ ጮኸና ጨዋታችንን አቋረጠን፡፡ ከካናዳ ወንድ ልጅዋ ነበር የደወለው) ከዚያልሽ --- በጠበሉም በምኑንም ብዬ ተሻለኝ፡፡

በመሃል ስራሽን አቁመሽ ነበር?

አዎ ሙሉውን አቁሜ ቤቱን አከራየሁት። መጨረሻ ላይ ያከራየኋት ሴት እገዛዋለሁ ብላ ስሙን አዛውሬላት ነበረ---በቼክ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ሰጥታኝ ነበር---ከዚያ እዛ ዱባይ የሚባል አገር ተነስታ ሄደች፡፡ ቤቱ በሃራጅ ተሸጠና ለእኔ ስድስት መቶ ሺ ብር ተሰጠኝ፡፡ ከባንክ በቀኝ እና በግራ እጄ ሶስት መቶ ሺ፣ ሶስት መቶ ሺ ብር ይዤ ስወጣ በጣም ከበደኝ፡፡ ‹‹ፈጣሪዬ በአቅሜ ነው የሰጠኸኝ..ያንን አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር..አግኝቼ ቢሆን እንዴት ነበር የምይዘው..ተመስገን ጌታዬ ይሄንኑ በረከቱን ረድዔቱን ስጠው›› ብዬ--- (በድጋሚ የቤት ስልክ ጮኸ፡፡ አሁንም ከካናዳ ሌላኛዋ ልጅዋ ደወሎ፤ ሰላምታ ሰጥታ ቆይቶ እንዲደውል ነግራው ዘጋች) የካሳንቺሱ ስራ ቆመ ማለት ነው -- አንድ ዓመት ይህል ቁጪ አልኩኝ ያለ ስራ። ከዛም ለምንድን ነው ቁጪ የምትይው ብሎ ቁምላቸው የሚባል የፋሲካ ባለቤት ተቆጣኝ፡፡ ከዛ ኦርጋኔንና የራሴን ባንድ ይዤ እዚያ ሄድኩኝ፡፡ አብረውኝ የሚጫወቱትን ሳክሲፎኒስትና ኦርጋኒስት ይዤ ማለት ነው፡፡ ‹‹ራሄል እዚህ ገብታለች›› ሲባል…ተይኝ አልኩሽ --- ሰው እንደጉድ ይጎርፍ ጀመር፡፡ ደንበኞችሽ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሥልጣናትና ባለሃብት--- ነበሩ ይባላል፡፡ እንደውም አንዴ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን ቃለ መጠይቅ ስናደርግላቸው---.የአንቺን የምሽት ክበብ በጣም ይወዱት እንደነበር ነግረውናል --- እጣ ክፍሌም እንደዛ ነገር ነው፡፡ የአዲስ አበባ መሳፍንት መኳንት፣ የራስና የደጃዝማች ልጆች፣ ማን ይቀራል…እገሌ ከእገሌ አልልሽም፡፡ የጨዋ ልጆች ይመጡ ነበር፡፡ ስርዓት ለሌለው እንኳን ስርዓት አስተምሬ ነው የምለከው፡፡ በጃንሆይም ጊዜ ከቤተመንግስት ሰዎች ጋር ነበር ቅርበቴ፡፡ በቃ ይወዱኛል፡፡ ዘፋኝ ሳልሆንም እኮ ነው፡፡

እንዴት ወደ ቤተመንግስት ለመቅረብ ቻልሽ?

ያኔ ቤተመንግስት ቱሪስቶች ሲመጡ አጉራሽ ይፈለግ ነበር፡፡ ቤተ-መንግስት ሄደን እንጀራ እናጎርሳለን፡፡ የቤተመንግስት እንጀራ እንደዚህ ሶፍት ነጭ ነበረ(በእጅዋ የያዘችውን ሶፍት እያሳየችኝ) ፈረንጆቹ ናፕኪን እየመሰላቸው እንጀራውን እንደ ሶፍት ይጠቀሙበታል፡፡ ቤተመንግስት ውስጥ በጣም ስለተቸገሩ--- እስኪ ቆነጃጅትን ፈልጉ ተባለ። አንድ እኔን በጣም የሚያውቅ ሰው ነበረ…ነፍሱን ይማርና ኮማንደር እስክንድር ‹‹ዋይን ገርል ራሄልን ጥሩ›› አለ፡፡

ዋይን ገርል ነበርሽ እንዴ?

አዎ፡፡

ዋይን ስፔሻሊስት ነኝ፡፡ እንዴት--- የት ተማርሽው? ታሪኬ ብዙ ነው አላልኩሽም፡፡ እስቲ አውጊኛ ---- ዛሬ እንግዲህ አብረን ማደራችን ነው፡፡ ግዴለም አጫውቺኝ ---- ስሚ----.ድሮ ሁለቱን ልጆቼን እንደወለድኩ ባሌን ፈታሁ ከዛ ‹‹ራስ ሆቴል ኮርስ መውሰድ አለብኝ›› ብዬ አሰብኩና ለሶስት ወር ያህል የገበታ ዝግጅት (tabel set up) የእንግዳ መስተንግዶ አሰጣጥ (how to serve the guest) ሰለጠንኩ፡፡ እንግሊዝኛውም ሌላ ነው--- እንደ አሜሪካን ነው የምናወራው፡፡ የእኛ ትምህርት ቤት እንደአሁኑ ቀላል መስሎሻል---ከሶስተኛ ክፍል በኋላ በእንግሊዝኛ ነው የምታወሪው፡፡ በተለይ በእንግሊዝኛ አስተማሪ በኩል----እኛ የተማርንበት ዘመን ሌላ ነበር፡፡ በጣም ቆንጆ ትምህርት ቤት ነው የተማርነው ግን አልሰራንበትም፡፡ እኔን ያልሽ እንደሆነ ግን በጣም የገባኝ አራዳ ስለነበርኩ በወቅቱ ሰርቼበታለሁ፡፡ እና የ‹‹ዋይን ገርል›› ኮርስ ስጨርስ ምርጫ ተሰጠኝና ጊዮንን መረጥኩ፡፡ ያኔ የነበሩት ሆቴሎች በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ዋቢ ሸበሌ ገና እየተጠናቀቀ ነበር፡፡ በተረፈ ጊዮን ሆቴልና ኢትዮጵያ ሆቴል ናቸው፡፡ እኔ ጊዮን ሆቴል ገባሁ፡፡ በአስተናጋጅነት ነው? ስለ በቬሬጅ (መጠጥ) ነበር ያጠናሁት፡፡ ስለ ኮክቴል አሰራር አውቃለሁ --- አንድ መጠጥ ከአንድ መጠጥ ጋር ኮክቴል ይደረጋል፡፡ አፕሬቲቩ፣ ዳይጄስቲቩ----የተለያዩ የዋይን ዓይነቶች አሉ--- ሬድ፣ ዋይት፣ ሮዜ፣ ድራይ፣ስዊት፣ ሚዲየም… ከምን ከምን ምግብ ጋር እንደሚወሰዱ አውቃለሁ። ካስተመሮቹ በጣም ይደነቁ ነበር፡፡ የት ነው የተማርሽው፤ የት አወቅሽው ይሉኛል፡፡ ስንት ዓመት ሰራሽ በዋይን ገርልነት? አራት ዓመት ከስድስት ወር ነው የሰራሁት። ስራውን ብወደውም እየሰለቸኝ መጣ፡፡ አንድ ቀን አኩርፌ ተቀምጬ አንድ ደንበኛችን አዩኝ። የአርጀንቲና አምባሳደር ነበሩ፡፡ ስሚ----ብዙ ካስተመሮቼ የሚያውቁኝ በጣም ሳቂታ፣ ደስተኛ፣ ተጫዋች መሆኔን ነው፡፡ የሚያኮርፍም ሰው አልወድም፡፡ ኩርፊያም አልወድም፡፡ ስለዚህ ‹‹ምነው ዛሬ አልሳቅሽም?›› አሉኝ፡፡ ‹‹ደከመኝ የሌሊት ስራ ደከመኝ›› አልኳቸው፡፡ “So?” አሉኝ፡፡ ‹‹በቃ ሰለቸኝ አስጠላኝ…›› መለስኩላቸው “Why don’t you come to my embassy, I am going to move by next week.” (ለምን ወደ እኔ ኤምባሲ አትመጪም? በሚቀጥለው ሳምንት እገባለሁ) እሽ ብዬ ሄድኩ፡፡ እቃ ግዢ ክፍል (ፐርቼዘር) አደረጉኝ፡፡ ከዚያ የጣሊያን ክልስ ፀሃፊና አራት ዘበኞች ቀጠርኩለት፡፡ ሁለት የማታ፣ ሁለት የቀን። የዘበኞች ዩኒፎርም(የቤተመንግስት ልብስ ሰፊ ነበር) እሱ ጋ ሄጄ አሰፋሁ፣ ባርኔጣቸውን አሰራሁ። ሁለት ሾፌሮችም ቀጠርኩ፡፡ የኤምባሲ ሾፌሮች የሚለብሱትን አውቃለሁ፡፡ ወጥ ቤትም ቀጠርኩ---የፅዳት ባለሙያ (ሃውስ ኪፐር) እንዲሁም አትክልተኛ ሁሉ ቀጠርኩ፡፡ ሥራ ብቻ ነው ወይስ ሌላም ግንኙነት ነበራችሁ? ኦኦ---ባለትዳር እኮ ነው፡፡ እኔ ስራውን ነው የፈለግሁት፡፡ (የቤቷ ስልክ ለሦስተኛ ጮኸ…) እንግዲህ ቻይው---- ልጆቼ አሜሪካና ካናዳ ነው ኑሮዋቸው…ልክ ሲነጋ የኔን ድምፅ ሳይሰሙ ቀናቸውን በስመዓብ አይሉም…(ከአሜሪካ ሴት ልጅዋ ነበረች የደወለችው)---ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአምባሳደሩ ሚስት መጣች፡፡ ይሄኔ ችግር ተፈጠረ። ‹‹ምንድን ነች?›› ብላ አፈጠጠች፡፡ ‹‹ይሄን ሁሉ የሰራችው እስዋ ናት›› አሏት፡፡ ‹‹ሰዎችን ከመቅጠር ጀምሮ..ፈረስ ቤቱን፣ አበባውን …የቤቱን ቀለም..ይሄን ሁሉ የሰራች እስዋ ናት›› በማለት አስረዷት፡፡ በጣም ሃርድ ወርከር ናት…ብላ ብታደንቀኝም ከጥቂት ጊዜ በኋላ አልተመቸኋትም መሰለኝ---ደሞዜም በጣም ብዙ ነበር፡፡ ምን ያህል ይደርሳል? 2ሺ ብር--- ይሄ ሁሉ ከሙዚቃው በፊት ነው አይደል-- ሙዚቃ ባልታሰበበት ጊዜ እኮ ነው የማወራሽ። እዚህና እዚያ አስረገጥሺኝ እኮ፡፡ እንዳልኩሽ የሰውየው ሚስት አልተመቸኋትም፡፡ ስርዓት አለኝ---ሰው አከብራለሁ---ሰው ስነሥርዓት ከሌለው አልወድም---ወዲያውኑ ነው የማስወግደው። ሁለተኛ ማየት አልፈልግም፡፡ እናም‹‹..በቃ ወደ ውጪ መሄዴ ነው ….›› ብዬ ስነግረው አምባሳደሩ በጣም ደነገጠ፣ ተጨነቀ፡፡ እኔ ግን ትዕግስቴና ፍላጎቴ ተዘግቶ ስለነበር ትቼው ወጣሁ፡፡ ይሄን ሁሉ ያስታወሰን እኮ ለአጉራሽነት ወደቤተመንግስት መግባትሽ ነው----.የአጉራሽነቱስ ጉዳይ--- አጉራሽነትማ----ጃንሆይ ጥሩ ጥሩ ልጆችን አምጡ ብለው አዘዙ፡፡ ‹‹እንደውም ጊዮን ሆቴል ሁለት ዌይትረስ አሉ አምጡዋቸው›› ተባለ፡፡ ቤተመንግስት ገብተን ፈረንጆችን እናጎርስ ጀመር፡፡ ፈረንጆቹ.. “Oh my God. What is this? Is this napkin or what?...’” እያሉ ይወናበዱ ነበር፡፡ ስናጎርሳቸው ደስ እንዲላቸው ብለን ፊታቸው እጃችንን እንታጠብ ነበር----ከዛ ስናጎርሳቸው ተደስተው ሊሞቱ፡፡ ቆንጆ ነሽ----አድናቆት ምናምንስ አልነበረም? “you have a beautiful smile, you Ethiopians are beautiful” ይላሉ (ውብ ፈገግታ አለሽ--እናንተ ኢትዮጵያውያን ውብ ናችሁ) ----ምን ልበልሽ--- አድናቆት በአድናቆት ነው----ልዕልቶቹም ያዩናል፡፡ የሆነ ዝግጅት ሲኖር በመካከላቸው ካናፒ እናዞራለን፡፡ ‹‹እንዴት ቆንጆ ናት›› ይሉኝ ነበር፡፡ የአልጋ ወራሽ ሚስት በጣም ያደንቁኝ ነበር፡፡ ልዕልት ተናኘ ወርቅ ነፍሳቸውን ይማረው፡፡ …አረ ተይኝ---አድናቆታቸው ራሱ ገንዘብ ነው፡፡ አክብሮታቸው…ሰላምታቸው…አመለካከታቸው..ነገረ ስራቸው ሌላ ነበር፡፡ በነገስታቱ ተሸልመሽ ታውቂያለሽ?

እጅግ በጣም ብዙ ሽልማት እንጂ…የአንገት ወርቅ፣ የእጅ ወርቅ አምባር፣እንዲሁም ሰንጋ መግዣ ተብሎ 500 ብር ተሰጥቶኛል፡፡..የእኔ ልጅ---- ባሳለፍኩት ዕድሜ ቁጭ ማለትን አልወድም፣ የሰው እጅ መጠበቅን አልወድም፣ ስራ መስራት ያስደስተኛል፣ መጫወት መደሰት ቁምነገር መስራት---እጅግ ሰው እወዳለሁ..ስራ አልንቅም፡፡ የሚገባኝን ነገር አውቃለሁ፡፡

የሰው ነገር አልነካም፡፡ ለዚህም ነው ያልነካሁት የስራ ዓይነት የለም የምልሽ----.ቆይ ልቁጠርልሽ አርጀንቲና ኤምባሲ፣ ታንዛኒያ ኤምባሲ፣ ፊሊፕስ… ሾው ሩም ውስጥ ሁሉ እሰራ ነበር፡፡ የዋቢሸበሌ ፐርሶኔል አንዴ መብራት ሊገዙ መጥተው ‹‹ምን ልትሰሪ ያለ ፊልድሽ መጣሽ?›› ብለው ዋቢሸበሌ ወሰዱኝ..እዚያ ስሰራ ደግሞ የሂልተን ሆቴል ..“ፉድና ቤቨሬጅ ማኔጀር” መጡ፣ የውጪ ዜጋ ዋናው የሂልተንን ሃላፊ ጭምር ይዘው፡፡ ‹‹ምንድን ነው የምትበሉት?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹አዘናል›› አሉ፡፡ ያዘዙትን ጠየቅሁ - ስጋ፣ ዶሮ፣ አሳ ነበር ያዘዙት፡፡ ሁለት ዓይነት ወይን ማዘዝ አለባቸው፡፡ አንድ ቀይ ዋይን፣ አንድ ነጭ ዋይን አልኩኝ፡፡ አለበለዚያ ሁለቱንም የሚያባላ ሮዜ ዋይን..አልኩና ሄጄ ጠየቅኋቸው፡፡

‹‹ምንድን ነው የምትጠጡት?

ምን ዓይነት ዋይን ላምጣላችሁ?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹የምንበላውን ካወቅሽ አንቺ ጠቁሚን ምን ይሻለናል?›› አሉኝ፡፡ ሞያዊ ትንታኔ ሰጠኋቸው፡፡ በጣም ተገረሙ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ባለሞያ አለ ብለው ተደንቀዋል፡፡ ከመሄዳቸው በፊት ‹‹ፈቃድሽ ከሆነ..ሰኞ ጠዋት ሂልተን ሆቴል እንድትመጪ›› አሉኝ፡፡ ‹‹የት ነው ሂልተን ሆቴል?›› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ ‹‹እዚህ እዚህ ቦታ….›› ብለው ነገሩኝ፡፡ ‹‹እኔ የሆቴል ስራ ሰልችቶኛል..ሆቴል እንዳይሆን ስላቸው..›› ‹‹ኖኖ እንደዚህ አይባልም..ስራ እንደዚህ አይባልም እንድትመጪ..›› አሉኝ፡፡ ሂልተን ሆቴል ሄድኩኝ---“.አይዞሽ ሲደክምሽ ማረፊያ ክፍል እንሰጥሻለን” አሉኝ፡፡ “መቼሽ ቲፑ ሌላ ነው----በጣም ቆንጆ ቦታ ነው፡፡ የተወሰነ ቦታ ነው የምትሰሪው” ብለው አግባቡኝ፡፡ (አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል) የሚል እንዴት ያለ የሚያምር የአበሻ ቀሚስ ተሰራልኝ መሰለሽ ---ላይት ብራውን እንደ ጎልዲሽ ዓይነት --- አቤት መልክ---አቤት ቁመና…፡፡ ሂልተንስ ስንት ዓመት ሰራሽ? ከአራት ዓመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ በዘፈኖችሽ ላይ ንጉሶችን ማነሳሳት ትወጂያለሽ ---.የጣይቱ ጠጅ ነው…የምኒልክ እልፍኝ-- ትያለሽ እኔ የሰርቶ አደር ልጅ ነኝ፡፡

ግን እነዚህ አብሬያቸው ያሳለፍኳቸው እንግዶች..ክብር ያላቸው፤ ለሰው ልጅ ጥሩ የሚመኙ፤ ደጎች ናቸው። እግዚአብሄር ደግሞ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው አንድ ነገር ይሰጠዋል…ሁሉን በፕሮግራም ነው የሚፈጥረው፡፡ እግዚአብሄር እኮ እኔን አድሎን ነው እንጂ---እኔ ማን ነኝ I am no body after all. ከማንም አልበልጥም፡፡ ሰው ስለምወድና ስለማከብር…አባቴ ሰርቶ አደርም ቢሆን አስተዳደጋችን እንዴት ሸጋ ነበር --- ልጆቼንም በዛ መንገድ ነው ያሰደግኋቸው፡፡

ውጪ አገር ስራዎችሽን አቅርበሽ ታውቂያለሽ?

በፍጹም፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ አምባሰል የሚባል ሙዚቃ ቤት ዋሺንግተን ናይት ክለብ ነበረው። ለስድስት ወር ለመስራት ተስማምቼ ሄጄ ---.ለአራት ወር ያህል ከሰራሁ በኋላ ኢትዮጵያኖች በግል ጠብ እርስ በእርስ ተጋደሉ፡፡ ስራውን ትቼ ወደ አገሬ መጣሁ፡፡ ብዙም እንደዚህ ዓይነት ቦታ አይመቸኝም--- የትዳርሽ ጉዳይስ--- ልጆቼን ብቻዬን ነው ያሳደግሁት.--- ጠንካራ እናት ነኝ፡፡ .ባሎች ትንሽ አስቸጋሪዎች ነበሩ፡፡ ምን ይጎለኛል---ልጆቼን ለማሳደግ ብዬ “ልውሰድም” ቢሉ እሽ አልልም---.ይሄው ልጆቼን አሳደግሁኝ ዳርኩኝ--እግዚአብሄር ይመስገን፡፡

የዘመኑን ዘፈኖች ትሰሚያለሽ? እንዴት ነው ዘፈን ድሮ ቀረ ትያለሽ ወይስ ----

ድምፁ የወጣው አሁን ይመስለኛል፡፡ ወጣቶቹ ቆንጆ ቆንጆ ድምጽ አላቸው፡፡ ሲዲውን ስሰማው ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የምሰማው ወይ ስለ ሃገር፣ ስለ አንድ ታሪክ፣ ወይም ስለኢትዮጵያ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ታሪክዋ ሰፊ ነው፡፡ አንዳንዱን እያነሱ አንስቶ መስራቱ ጥሩ ነው፡፡ የፍቅር ነገር መቼም እንዳለ ነው አያረጅም፡፡ ፍቅር ትልቅ ነገር ነው። ሁልጊዜ ግን ስለ ፍቅረኛ፣ ስለ ባል፣ ስለ ሚስት--- ተጣላኝ ታረቀኝ አባረርከኝ…መለስከኝ…እንደዚህ ዓይነት በጣም ሲበዛ ጥሩ አይደለም። አንችዬ አርጅቼ ይሆን እንዴ? ግን አይደለም…ድሮም ይሄው ነው ስሜቴ…ሁሉም ይቅር እያልኩ አይደለም፡፡ በየመሃሉ ቁምነገር ቢገባበት ማለቴ ነው፡፡ እንጂ ድምፅማ የመጣው አሁን ነው፡፡ በድሮና በአሁን ዘፈኖች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው ትያለሽ?

ምርጫቸውና የደረሱበት ቴክኖሎጂ ነው። በአብዛኛው የፈረንጅ መዚቃ፤ የፈረንጅ ሲኒማ፤ የፈረንጅ ዘፋኞች የሚሆኑትን ነው የሚሆኑት። ከአሁኑ ዘፋኞች ቴዲ አፍሮን ---- ጎንደር ብዙ የተጫወቱ ልጆች አሉ --ማዲንጎ እስከ ወንድሙ…ግሩም ናቸው፡፡ ማዲንጎን ያየሽ እንደሆን የበላይን ታሪክ አስቀምጦታል--- በደንብ --- ታምር ነው መቼም፡፡ እኔማ ያሳዝነኛል ያንን ሲጫወት፡፡ እነዚህ ቁም ነገር ያላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ባህል እኮ ተወርቶም አያልቅ፡፡ መጽሐፍም አይችለው፡፡ አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እኛ እኮ ድሮ ትምህርት ቤት ስንማር መጀመርያ ስለሃገራችን ጋራ ሸንተረር..ተምረን ነው ወደ ውጪ የምንሻገረው፡፡ አሁን ማን ያስተምራል….እዚህም አገር አማርኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ እየታየ ነው፡፡ እኛ ድሮ በትምህርት ቤት ውስጥ ባንዲራ አውርደን ክፍል እንደገባን ፀሎት እናደርጋለን፤ ከፀሎት በኋላ የሚገባው አስተማሪያችን የግብረገብ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ነው ትምህርቱ የሚቀጥለው፡፡ ኢትዮጵያ ከአለም አንደኛ ናት ብል----.አላፍርም። ስለ ሃገሬ ተናግሬም አልጨርሰው፤አቅሜም አይችለው፡፡

አገራችን፣ ህዝባችን፣ አለባበሳችን፣ ምግባችን፣ አየሩ…በክረምቱ ሰዓት ክረምቱ የታወቀ ነው፤ በበጋው ሰዓት በጋው የታወቀ ነው፣ በበልግ ሰዓት በልጉ የታወቀ ነው፤ አለቀ፡፡ አየራችን ደግሞ ልዩ ነው፡፡ የምታኮራ አገር የሚያኮራ ህዝብ ነው ያለን..ይሄ ራሱ ቢዘፈንለት አይበቃም፡፡ ስንት ካሴት በነጠላ እና በጋራ ሰራሽ.. ወደ 12 ካሴቶችን ሰርቻለሁ፡፡ “ምኒልክ” የሚለው ዘፈኔ ዜማውን የሰራሁት እኔ ነኝ፡፡ የሁሉም ካሴቶቼ ግጥም ድርሰት የይልማ ገብረ አብ ናቸው፡፡ የድምፅሽን ለዛ ስለሚያውቀው ነዋ ይልማ መርጦ የሚሰጥሽ... አዋ፡፡ ይልማ በአንድ ወቅት አንድ ስራ ገጥሞት አንድ ካሴቴ ላይ ብቻ ሶስት ዘፈኖች የሌላ ሰው ነበሩ፡፡ ከይልማ ጋር ስንሰራ ግጥሞችን መክረንባቸውና ተነጋግረን ነው - ይሄ ይውጣ ይሄ ይግባ ብለን፡፡

አንድ ጊዜ ምን ሆነ…‹‹በደሳሳ ጎጆ ቁጭ ብዬ ብቻዬን ሳለቅስ..›› ምናምን የሚል ግጥም ..መጣልኝ…እኔ እንደዚህ አይነት ነገር …ምንድን ነው በፍፁም አልዘፍንም አልኳቸው፡፡ ችግርም የለብኝ..ይቅርታ አድርጉልኝ የእኔ ስሜት ለእንደዚህ ዓይነት ነገር አይሰራም አልኳቸው፡፡ በጣም ሳቁ..ጭንቅ አልወድም ሌግዠሪ ነገር ነው የምወደው…ዝም ያለ ቆፍጠን ያለ…ለሰውም ቀለል ሲል..ነው፡፡ የእኔን ለቅሶና ሃዘን ህዝብን ስማልኝ ማለት ምንድን ነው፡፡ የሆነ ድባብ እኮ ይፈጥራል፡፡ ይቅርታ እንግዲህ እኔ እንደዚህ አይነት ታይፕ የለኝም፡፡ ከተሸመ አሰግድ፤ ጋሽ ባህሩ፣ ጋሽ ይርጋ፣ ከተማ መኮንን፣ ዳምጠው…ኡፍ ለዛ አላቸው እኮ፡፡ my God!! የማይሰለቹ እኮ ናቸው፡፡ ስሚ የዛን ዘመን ዘፋኞች..እነ ወረታው…የወረታው ድምፅ እኮ..ራሱ ጊታር ነው፤ ራሱ ሳክስፎን ነው፤ራሱ ቤዝ ጊታር ነው፤ በጣም ጎልደን ድምፅ እኮ ነው ያለው፡፡ ከብዙዎች ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ልረሳ ነው እንዴ..እረ አንቺ ልጅ ይሄ ነገር ያሰጋል----

እርጅና መጣ መሰለኝ ዕድሜሽ ግን ስንት ሆነ?

63 ዓመቴን ባለፈው የፋሲካ ዕለት አከበርኩ.---.ገና ልጅ እኮ ነኝ፡፡ መልካም ልደት፣ ረጅም ዕድሜ ተመኝተንልሻል። በሶስት መንግስታት ውስጥ በአርቲስትነት ትታወሻለሽ-- የደርግ ጊዜን ሳልነግርሽ፡፡ በምሽት ክበቤ ውስጥ ..እረ ገዳዬ፣ እንደው ዘራፌዋ፣ እንደ ኮሜዲ አድርጌ የምጫወተው ስራ ነበረኝ፡፡ እረ ገዳዬ የሚለውን በእንግሊዝኛ እለው ነበር--- እስኪ አሁን በይልኝ-- Oh killer oh killer The useless goat give birth to nine She is died and her children I love the killer I love the killer As well as the shooter When I feel tired I rest under the umberella of ጀግናዬ hair. ብታይ ሰው ይሄን እንደ ኮሜዲ ነው የሚሰማው----.ትርጓሜው ደግሞ ትክክል ነው፡፡ እረ ገዳዬ አረ ገዳዬ የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆችዋም ያልቃሉ እስዋም ትሞታለች፡፡ ስሚ እኔ ጀግና እወዳለሁ፡፡ ዘፋኝ ባልሆን ወታደር ነበር የምሆነው፡፡ በጣም በጣም ነው ወታደር መሆን.. ለመዝመት አስበሽ አታውቂም ታዲያ-- አይ ልጄቼን ከወለድኩ በኋላ ..ሃላፊነቱም አለ..።

የአሁኑ አልበምሽ..ከስንት ጊዜ በኋላ ወጣ?

ከ7 ዓመት በኋላ…ሰርቼው ቁጭ አድርጌው ነበር…ኮፒ ራይቱም አስጨናቂ ስለነበረ..ሰርቼ ቁጭ አደረኩት የሚገዛ ሲጠፋ፡፡ አቶ ቁምላቸው ገብረስላሴ የፋሲካ ባለቤት/የሚሞ ባለቤት…የተፈጠረውን አጫወትኩት፡፡ ከፈቃደ ዋሬ የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት ጋር እንደ ወንድም ነው የሚተያዩት፡፡ ተነጋገሩና ይሄው ባለፈው ለሰው አፍ አበቁልኝ፡፡

ምን ያህል ገቢ አገኘሽበት ?

እሱን ተይው ከአሁን በኋላስ ምን ታስቢያለሽ?

አገሬ ላይ ቁጪ ብዬ እግዚአብሄርን ማመስገን ነው…የምስጋና መዝሙር ነው ሃሳቤ፡፡ ደስተኛ ነኝ…እንምታይው ሁሉ ሙሉ ነው..ተመስገን ለእግዚአብሄር ምን ይሳነዋል፡፡ አይንሽን አሞሽ ነበር? አዎ…ሼክ ሙሃመድ አሊ አሙዲ ናቸው ያሳከሙኝ…፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ እወዳቸዋለሁ…እንኳን ለፋሲካና ለዳግማይ ትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ ብዬ እጅ እነሳለሁ፡፡

Read 6536 times