Saturday, 11 May 2013 14:02

የፋሲካ ሰሞን

Written by  ዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(3 votes)

ጊዜው አመሻሽ ላይ ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ጠቁሮ የዋለው ሰማይ የዝናም ሸክሙን አራግፎ ፀጥ ብሏል። ጨረቃ ደምቃ ወጥታለች፡፡ ኮከቦችም በጠራው ሰማይ ላይ ተዘርተዋል፡፡ ከጭቃ ጭቃ እያማረጥኩ ከቤቴ መዳረሻ ወዳለችው ቡና ቤት እንደልማዴ አመራሁ፡፡ በጠጪዎች መሀል አልፌ ጥግ አካባቢ ተቀመጥኩና የምጠጣውን አዘዝኩ፡፡ የቀረበልኝን ድራፍት እያጣጣምኩ ዙሪያዬ እቃኛለሁ፡፡ ሁለት ወጣቶች ተከታትለው ገቡና በተለምዶ ባለጌ ወንበር የሚባለውን ስበው ተቀመጡ፡፡ ያዘዙት ድራፍት እንደመጣላቸው የተመካከሩ ይመስል ባንድ ትንፋሽ ጨለጡትና ድጋሚ አዘዙ፡፡ በመካከላቸው ንግግር የለም፡፡ አንደኛው ፀጉሩን እያፍተለተለ መሬት መሬት ይመለከታል፡፡ አንደኛው ደግሞ በመስኮቱ አሻግሮ ሰማዩን ይቃኛል፡፡ “አየህልኝ?” የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡

ዘወር አልኩ፡፡ ፀጉሩ ገብስማ የሆነ ጠና ያለ ሰው ካጠገቤ ተቀምጧል። ሌላ ሰው በቅርበት የለም፡፡ ጥያቄው ለኔ መሆኑ ነው፡፡ “ምኑን?” አልኩት “እነዚህን ሁለት ወጣቶች” አለኝ ወደተቀመጡበት በጣቱ እየጠቆመ፡፡ በዚያ ቅዝቃዜ የመጀመሪያውን ድራፍት እንዴት በፍጥነት እንደጨለጡት እሱም እንደኔ ታዝቧቸው ኖሯል፡፡ “እና?” አልኩት “ምልከታቸውን ልብ ብለህልኛል?” “ምልከታቸውን ስትል … ” “አንደኛው በመስኮት አሻግሮ ሰማዩን፣ ሌላኛው ጫማው የተሸከመውን ጭቃ ሲመለከት ታያለህ? እናማ ወዳጄ በነሱ እይታ ሁለት ነገሮችን አስተዋልኩ።” “ምንና ምን?” “ትዝታና ተስፋን” “እንዴት?” “እንዴት ማለት መልካም! ትዝታ ያ ወጣት ጫማው ላይ እንደተሸከመው ጭቃ ነው፡፡ እንደ ልብ አያራምድህም፡፡ ያስጐነብስሃል፡፡

ትናንትህን እየቆዘምክ ልራመድ ብትል ያዳልጥሃል … ብትነሳም በትዝታህ ተጨማልቀህ ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬህን አልተጠቀምክበትማ … ዛሬህን አልሰራህበትማ! … ትርፍ ከተባለ ከትዝታህ የምታተርፈው ፀፀት ብቻ ነው፡፡” አለኝና ቢራውን አንስቶ ተጐነጨ፡፡ “እውነት ነው “አንድ ሰው ማርጀቱን የሚያውቀው በተስፋ መኖሩን ትቶ በትዝታ መኖር ሲጀምር ነው” የሚል አባባል አለ!” ሰውየው ግንባሩን እያኮሳተረ አፈጠጠብኝና “ከመኖርህ ያተረፍከው የራስህ የሆነ አባባል የለህም?” አለኝ፡፡ አከርካሪዬን የተመታሁ ያህል ተሰማኝ፡፡ በድንጋጤ የምናገረው ጠፋኝ፡፡ ሰውዬው ቀጠለ። “…ለነገሩ አንተን እንዲህ አልኩህ እንጂ እኔም ከኖርኩት ህይወት እንደ ጥፍጥሬ ፈልቅቄ ያወጣሁት የራሴ የሆነ አባባል የለኝም፡፡ እነዚያ ሁለት ወጣቶች እንደተቀመጡበት ባለጌ ወንበር በሰብዕናችን ስንባልግ፣ በየዕለቱ ሌላውን ለመምሰል ስንጥር የኛን ማንነት ቀብረነዋል…” ቢራውን ጨልጦ ድጋሚ አዘዘ። “የዚያኛውስ ወጣት ምልከታ ?” “እ … ያኛውን ወጣት ደግሞ ተመልከተው---- ቀና ብሎ ሰማይ ሰማዩን ይመለከታል … በሰማዩ ላይ ምን አለ? … ኮከብ … የተስፋ ተምሳሌት ነው፣ ቀና ብለህ በዘመንህ ሰማይ ላይ የሚያበራ የተስፋ ኮከብህን ፈልግ እንጂ … በትዝታህ ብቻ እየቆዘምክ በፀፀት ጊዜህን አትግፋ … ደግሞ አስተውል … ፋሲካን ልናከብር ሽር ጉድ ስንል ትርጓሜውንም ይዘን መሆን አለበት” “እንዴት?” “እንዴት ማለት መልካም … አየህ ወዳጄ ከሁለት ሺ ዓመት በፊት ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ተነሣ! አይደለም? “አዎን!” “አየህ ስለኛ ኃጢያት ሆኖ በመስቀል ላይ ሲፈፀም፡፡

ሞትን ለዘልዓለም ድል ነስቶታል፡፡ ለኛም ትንሣዔ ሆኖለታል፡፡ ይህ ማለት በኛ ሕይወት ውስጥ ትንሳዔ ዕለት በዕለት ነው፡፡ በኛ ውስጥ የተዋረደውን ማንነታችንን ወደ ክብር ለመመለስ ቀና ብለን በዘመናችን ሰማይ ላይ የተስፋችንን ኮከብ ከፈለግን ለሞተው ማንነታችን ትንሣዔ አለ፡፡ የትንሣዔን ኃይል ደግሞ ሞት ሊቋቋመው አይችልም … ተስፋ መቁረጥን … ተስፋ በማድረግ … እያሸነፈን … የክፋትን ምንጭ በመልካምነት እየጠረግን … ጥላቻን በፍቅር እየለወጥን … በመስቀል ላይ የተሠራውንና የተቀበልነውን ፍቅር ዕለ በዕለት ሕይወታችን ካደረግነው በየዕለት ኑሯችን ትንሣኤ አለ፡፡” ቢራውን ጨልጦ ተነሣ፡፡ የሰውዬው ጨዋታ ጥሞኛል፡፡ በኔ ግብዣ ጥቂት እንዲቆይ ጠየቅሁት፡፡ ስለ ግብዣዬ አመስግኖኝ ፣ መቆየት እንደማይፈልግ ነግሮኝ ወጣ፡፡ ይህ ከሆነ ሶስት ዓመት አለፈው፡፡ በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ትንሣዔ በየዕለቱ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ በፋሲካ ሰሞን ግን ያንን ሰው አስታውሰዋለሁ፡፡

Read 1707 times