Saturday, 27 April 2013 12:11

ጊዮርጊስ ከዛማሌክ — ክፍል 2

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ፈረሰኞቹና ነጮቹ ጦረኞች አቻ ናቸው!? በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ኢትዮጵያን የወከለ ክለብ ወደ ምድብ ድልድል ሊገባ እንደሚችል ሰሞኑን እየተዘገበ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት ወደ ካይሮ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከግብፁ ክለብ ዛማሌክ ጋር 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት መለያየቱ ይታወሳል፡፡ ጊዮርጊስ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ያለው እድል 80 በመቶ እንደተሳካም እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በጊዮርጊስ እና ዛማሌክ መካከል የሻምፒዮንስ ሊጉ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታው በካይሮ የአየር መከላከያ ስታድዬም የተደረገው ያለተመልካች ነበር። ለጊዮርጊስ እጅግ ጠቃሚ የሆነችውን ከሜዳ ውጭ የተመዘገበች ጎል ያስቆጠረው ኡመድ ኡክሪ ሲሆን የዛማሌኩ ሳላህ ሶሌማን የፈጠረውን ስህተት በመጠቀም በ63ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ነበር፡፡ ዛማሌክ አቻ የሆነው ደግሞ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ቡርኪናፋሳዊው የክለቡ ተጨዋች አብዱላህ ሲሴ ባስቆጠረው ግብ ነው፡፡

ከጨዋታ በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማይክል ክሩገር በመልሱ ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ያገባናት ጎል ብትኖረንም የምንቸገር ይመስለኛል ብለው ሲናገሩ፤ ዛማሌክ በአህጉራዊ የክለብ ውድድሮች ከጊዮርጊስ የላቀ ልምድ በመያዙ ሊጠቀም እንደሚችል ገልፀው በመልሱ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ክለቦች ፈርቀዳጅ የሆነውን ውጤት ወደ የምድብ ድልድል በመግባት እናሳካለን ብለዋል፡፡ የዛማሌኩ አሰልጣኝ ብራዚላዊው ዮርቫን ቪያሪያ በበኩላቸው በካይሮው ጨዋታ ዛማሌክ የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ትርጉም እንዳልነበረው በገለፁበት አስተያየት፤ በመልሱ ጨዋታ ዛማሌክ ከጊዮርጊስ ጋር እኩል እንድል እንደያዘ እና በዘመናዊ እግር ኳስ በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ መጫወት ልዩነት የለውም እንደሌለው ተናግረዋል። የዛማሌክ አምበል የሆነው ግብጠባቂው አብዱልዋይድ አልሰይድ በበኩሉ‹‹ መጥፎ ጨዋታ ነበር። ከመሸነፍ በመትረፍ ለጥቂት አቻ ወጥተናል፡፡

የመልሱ ጨዋታ ፈታኝ ይሆናል፡፡ ሃሳባችን አሸንፈን ወደ ሚኒ ሊግ ውድድሩ መግባት ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡ በሁለቱ ክለቦች የሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ ታሪክን በመንተራስ ባላቸው ውጤታማነት ላይ በተሰራ ስታትስቲካዊ ስሌት ዛማሌክ ከሜዳው ውጭ የማሸነፍ እድሉ 22 በመቶ ሲገመት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ድል የማድረግ እድሉ 80 በመቶ ተሰልቷል፡፡ ዛማሌክ ከሜዳው ውጭ አቻ የሚወጣበት እድል 22 በመቶ ሲሆን የመሸነፍ እጣው ደግሞ 56 በመቶ ተገምቷል፡፡ ጊዮርጊስ በሜዳው አቻ የሚወጣበት ደግሞ 20 በመቶ ሲሆን የሚሸነፍበት ሁኔታ 0 በመቶ ነው፡፡ ጎል ዶት ኮም ለአንባቢዎቹ በሰጠው የውጤት ትንበያ እድል ደግሞ 61.5 በመቶ የሚሆኑት ለዛማሌክ ድል ግምት ሲሰጡ 15.4 በመቶው ጊዮርጊስ አቻ እንደሚሆን እንዲሁም 23.1 በመቶው አቻ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል ተንብየዋል፡፡ በታሪክ ፤ ሀብትና ደረጃ ዛማሌክ ስፖርት ክለብ ከተመሰረተ 102 ዓመት ሲሆነው_ቅዱስ ጊዮርጊስ 80 ዓመት እንኳን አልሞላውም። በግብፅ ከአልሃሊ እኩል በርካታ ደጋፊ ያለው ዛማሌክ በሌሎች የሰሜን አፍሪካ አገራት እንዲሁም በአረቡ አለም ብዙ ደጋፊዎችን በመማረክ ሲታወቅ ጊዮርጊስ ከአገሩ አልወጣም፡፡ ዛማሌክ ነጮቹ ጦረኞች በሚል ቅፅል ስም ሲጠራ ነጮቹ ጦረኞች ፈረሰኞቹ ወይንም ሳንጃው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቅፅል መጠርያ ናቸው፡፡

ዛማሌክ ስፖርት ክለብ ከእግር ኳስ በእጅ ኳስ፤ በአትሌቲክስ፤ በመረብ ኳስ በቅርጫት ኳስ የሚሰራ ሲሆን በአገር ውስጥ እና በአፍሪካ ውድደሮች ከፍተኛ ስኬት አለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከእግር ኳስ ባሻገር የሚንቀሳቀሰው በአትሌቲክስ እና በሴቶች እግር ኳስ ብቻ ነው፡፡ የዛማሌክ ክለብ ስፖንሰሮች ዮርክ ኤሲስ፤ኢጅፕት ኤር፤ አዲዳስ እና ቶታል ኢጅፕት ሲባሉ ክለቡ እስከ 69 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ከማንቀሳቀሱም በላይ ቢሸጥ እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስፖንሰሮች ቢጂአይ ኢትዮጵያ እና ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ ዋንኞቹ ሲሆኑ፤ ክለቡ የሚያንቀሳቅሰው ካፒታል በግልፅ የማይታወቅ እና በሽያጭ ዋጋው ያልተተመነ ነው። የዛማሌክ የማሊያው ስፖንሰር አዲዳስ ሲሆን የጊዮርጊስ ደርባን ሲምንቶ ነው፡፡ ከ29 በላይ ሊቀንመበሮችን በሃላፊነት የሾመውን ዛማሌክ ይህኑኑ ሃላፊነት ከ2 አመት በፊት ለ3ኛ ጊዜ በመረከብ የሚሰሩት ግብፃዊው ሚሊዬነር ማመዱ አባስ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ሲሆኑ ከአፍሪካ ቢሊዬነሮች አንዱ የሆኑት ክቡር ሼህ መሀመድ አላሙዲ የክለቡ የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡ በዋንጫ መደርደርያው 183 ዋንጫዎችን ያስቀመጠው ዛማሌክ 11 ጊዜ የግብፅ ፕሪሚዬር ሊግን፤ 21 ጊዜ የግብፅ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን፤ 5 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግን፤ 3 ጊዜ የካፍ ሱፐር ካፕ ድሎችን ተጎናፅፏል፡

፡ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን 25 ጊዜ፤ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን 7 ጊዜ የኢትዮጵያ ሱፕር ካፕን 7 በአጠቃላይ ሌሎች ዋንጫዎችን ጨምሮ ከ50 በላይ ዋንጫዎችን አልሰበሰበም፡፡ ዛማሌክ በአፍሪካ የክለብ ውድደሮች 11 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች አሃዛዊ እና ታሪካዊ መረጃዎች አሰባሳቢ የአፍሪካ ክለቦች ደረጃ ደግሞ ከአፍሪካ አምስተኛ ከዓለም 134ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡ ኤምቲኤን የተባለው ድረገፅ ብቻ ከአፍሪካ ምርጥ 10 ክለቦች ተርታ የኢትዮጵያውን ቅዱስ ጊዮርጊስ 10ኛ ላይ አስቀምጦታል። ድረገፁ ጊዮርጊስን ከዚህ የምርጥ ክለቦች ተርታ ያስገባው በአህጉራዊ ውድደሮች ባለው ውጤታማነት አይደለም። ጊዮርጊስ በአገር ውስጥ የክለቦች ውድድር ባለው ስኬት፤ በአደረጃጀቱ፤ ከፍተኛ አቅም ባላቸው ክለቡን የሚደግፉ ባለሃብቶች በደረጃው ተጠቅሷል፡፡ በዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን በትራንስፈርማርከት ድረገፅ በሁለቱ ክለቦች የተጨዋቾች ስብስብ ላይ በተሰራ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን ዛማሌክ ጊዮርጊስን በእጅጉ ልቆ ይገኛል፡፡ ዛማሌክ በዋናው ቡድን 22 ግብፃውያን እና 2 ምእራብ አፍሪካ አገራት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ይዟል፡፡

የቡድኑ አማካይ እድሜ 25.87 አመት ነው፡፡ የዛማሌክ ተጨዋቾች ሁሉም በዝውውር ገበያ ዋጋ ተመን ሲኖራቸው በድምሩ እስከ 8.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ አንድ የዛማሌክ ተጨዋች አማካይ ዋጋ ጊዮርጊስን በገጠመው ቡድን 510ሺ ፓውንድ ነበር፡፡ የቡድኑ ውድ ተጨዋች 875ሺ ፓውንድ የዝውውር ገበያ ዋጋ ተመን ያገኘው መሃመድ አብዱልሻፊ ነው፡፡ ከስምንት በላይ ተጨዋቾችን ለግብፅ ብሄራዊ ቡድን ባስመረጠው የዛማሌክ ክለብ ጋር ሁለት የሌላ አገር ዜጎች ይገኛሉ፡፡ እነሱም በ300ሺ ፓውንድ የዋጋ ተመን የተሰጠው ቡርኪናፋሶዊ አጥቂ አብዱላዊ ሲሴ እና 700ሺ ፓውንድ ያወጣል ተብሎ በተከላካይ አማካይነት የተመዘገበው የካሜሮኑ አሌክሲስ ሜንዶሞ ናቸው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተጨዋቾች ዝስብስብ በዝውውር ገበያ ዋጋ አለው ተብሎ ተመን የተሰጠው ኡጋንዳዊው የ23 አመት አጥቂ ማይክ ሴሴርሙጋ ነው፡፡ ለሴሴርሙጋ የወጣለት የዝውውር ገበያ ዋጋ ተመን ደግሞ 100ሺ ፓውንድ ነው፡፡ በዚሁ ተጨዋች ብቻ ሙሉ የጊዮርጊስ ክለብ 100ሺ ፓውንድ በትራንስፈር ማርኬት ተተምኗል፡፡ የአንድ ተጨዋች አማካይ ዋጋ በሚል የተገመተው 5ሺ ፓውንድ ብቻ ነው፡፡ ከ26 ተጨዋቾች 5 የሌላ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የሙሉ ቡድን አማካይ እድሜ 19.4 ነው፡፡

Read 3647 times