Saturday, 27 April 2013 12:03

የጋዜጠኞቻችን ነገር!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

ያላነበበ ጋዜጠኛ ለማንም አይጠቅምም 

የአገራችን ጋዜጠኝነት ሲነሳ ብዙዎቻችን “ድንቄም ጋዜጠኛ” ብለን ባየነው ነገር ከንፈራችንን እናጣምም ይሆናል፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን በሃገራችን ጋዜጠኝነትን ዋጋ ያሳጡት ነገሮች ብዙ ስለሆኑ ተመካክረን የቻልነውን ያህል ብናቀና ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በመንግስት ምክንያት ከተፈጠሩት ችግሮች ውጭ ያሉትን ማለቴ ነው፡፡ ለነገሩ ሁሉም ነገር መነሻው የፖሊሲ ችግር ስለሆነ እሱን መንካቱ አይቀርም፡፡ አሁን አሁን በሃገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች ስለተከፈቱ የተወሰነውን ቴክኒካዊ ችግር መፍታት ይቻላል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ስለዚህም ከእኛ በሚጠበቁት ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ፡፡

ኤም ኤል ስቴይን፣ ስለጋዜጠኝነት በጻፉት መጽሃፍ ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “At school ,you should learn not only how to read and write your own language well,but you should also learn history, government, working with numbers and the sciences. If your school teaches journalism, learn it. It will give you an idea of what newspaper work is, and will also help you to decide whether you really wish to become a journalist. አንድ ጋዜጠኛ ትምህርት ቤትም ገብቶ መማር ያለበት በቋንቋው እንዴት ማንበብና መጻፍ እንዳለበት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይልቅስ ስለታሪክ፣ ስለ መንግስት፣ከቁጥር ጋር የተያያዙ ነገሮችንና ሌሎችንም ተጨማሪ ሳይንሶችን ማወቅ አለበት፡፡

ትምህርት ቤት ገብቶ መማሩ ጋዜጣና መጽሄት እንዴት እንደሚሰራ ግንዛቤ ይሰጠዋል፡፡ “Read every thing you can,especially newspapers and news magazines….Read books on history ,science,foreign countries and their peoples and what is happening in the world. Seek good books,not only for what they say,but for how they say it.Reading makes the mind richer for any job,but it is especially desirable for a young journalist. ስቴይን እንደሚሉት ጋዜጠኛ ያገኘውን ማንበብ አለበት፡፡ በተለይ ጋዜጦችና መጽሄቶችን። መጽሃፍትን ሲያነብብ በታሪክ፣ ሳይንስ፣የውጪ ሃገራትና ህዝቦቻቸው እንዲሁም፣ በዓለም ላይ የተፈጠሩ ነገሮች የሚያስቃኝ መፅሃፍትን ማንበብ አለበት፡፡ መጽሃፍትን ፈልጎ ሲያነብም የሚያነበው ምን እንደሚሉ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ያሉበትን መንገድ ለይቶ ለማጤን መሆን አለበት፡፡ እውነት ለመናገር ጋዜጠኛ ካላነበበ መሳቂያ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እንደ ኤም ኤል ስቴይን፤ ጋዜጠኛ ለመሆን ኮሌጅ ገብቶ መማር ያስፈልጋል፤ የሚሉና አይ መማር ሳይሆን ዋናው ተሰጥዖ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይሁንና አሜሪካ ውስጥ ብዙዎቹ ጋዜጦች ኮሌጅ ገብቶ የተማረውን ይመርጣሉ።

ምክንያቱም ጋዜጣ እንዴት እንደሚዘጋጅ ያውቃሉና! በርግጥ ራሳቸው አንብበው ሁሉን ነገር የሚያውቁም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በኛ ሃገር አሁን የምናያቸው ሁኔታዎች እንዲህ አይነት ቢሆኑም ከፍተኛ የንባብ እጥረት እንዳለ ይታያል፡፡ ይህ የሚታየው ደግሞ በጋዜጠኞቹ ብቻ ሳይሆን አምደኛ ነን ብለው በመጽሄቶችና ጋዜጦች ላይ በሚጽፉትም ዘንድ ነው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ከሁሉ ቀድሞ የሚያነብበትንና የሚጽፍበትን ቋንቋ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት ይላሉ-ስቴይን፡፡ የኛ ሃገር ጋዜጠኞችን ማዳመጥና ማንበብ ግን ዘግናኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ የሬድዮና ቴሌቪዥን ዜናዎችና ፕሮግራሞች ስታዳምጡ እነዚህ ሰዎች እውነት ጋዜጠኛ ናቸው

ብቻ ሳይሆን አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸውብላችሁም ትጠይቃላችሁ፡፡ የግስና የስም አረባቡን ጉዳይማ ተውት፡፡ ቀኑን ሙሉ ሃገራቶች፣አልባሳቶች፣መጽሃፍቶች ሲሉላችሁ ይውላሉ፡፡ ጋዜጠኝነት በሌላው አገር ብዙ ታላላቅ ሰዎች የሚወጡበት ሞያ (ፕሮፌሽን) ነው፡፡ ለምሳሌ ጆሴፍ ፑሊትዘር የኒውዮርክ ወርልድ ኤዲተርና ባለቤት፣ ታላቅ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ታዲያ ሲጽፍም ማንንም ሳይፈራ እውነት ይጽፋል፡፡ (ምናልባት ነፃነት ስላለ ይሆን?) ብቻ ታዋቂና ደፋር ነበር፤ ሲሞት እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ለኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ስጥቶ ስለነበር፣ በስሙ የተቋቋመው የፑሊትዘር ሽልማት ድርጅት መልካም የተባሉ ጋዜጠኞችን ይሸልማል፡፡

ሌላው ነገር ጋዜጠኛ ለሁሉም የሙያ ዘርፎች ቅርብና ብቁ መሆን መቻሉ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ታላላቅ ነጋዴዎች፣የመንግስት ባለስልጣናት ወዘተ ለመሆን ከሌላው ሰው የተሻለ አቅምና እድል እንዳላቸው ሙያውን ያጠኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ጆን ኤፍ ኬኔዲን በመጥቀስ እስከ ታላቋ ሃገር ፕሬዚደንትነት መድረስ የቻሉ እንዳሉ ያሳያሉ፡፡ የጋዜጣ ወይም የመጽሄት አምደኞችም እንደ ጋዜጠኛ የራሳቸው ሃላፊነትና ብቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እኛ ሃገር ለረዥም ጊዜ የቆየው አምደኛ ኤፍሬም እንዳለ ይመስለኛል፡፡ በእንጨዋወት አምዱ፡፡ ይሁንና ሁሉም አምዱን የሚሞላበት ሳይሆን አምዱን የሚመጥን ዕውቀት ያስፈልገዋል፡፡ ሳይንስ ከሆነ ሳይንስ፣ ኪነ -ጥበብ ከሆነ ኪነጥበብ፤ ፖለቲካ ከሆነ ፖለቲካ፣ወዘተ…ይሁን እንጂ አንዳንዶቹን ስናይ የይድረስ ይድረስ ፣ከፊሉ በተረት፣ከፊሉ በስሜት ብቻ የተሞሉ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ አምደኛ መሆን ቀላል አይደለም፤ ከፍተኛ ትጋትና ጥልቅ ንባብ ይሻል፡፡

ጋዜጠኛ ሃገር የሚመራበት አቅም ያለው አዋቂ እንጂ የመጣለትን የሚያወራ “ቱልቱላ” አይደለም። ይመስገነው እኛም ሃገር በጣም ጐበዝ ወጣት ጋዜጠኞች አሉ፡፡ ሬዲዮ ፋና ውስጥ ያሉና እዚያ ሰርተው ወደ ሌላ ቦታ የገቡ ምርጥ ልጆች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ወ/ሮ ሶሎሜ ታደሰ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ በነበረችበት ጊዜ የነበረውን የዝግጅት ስብጥርና ውህደት የምንረሳው አይመስለኝም፡፡ ያኔ ኤፍ ኤም 97.1 የነበሩ ምርጥ ጋዜጠኞችም እንዴት ሚድያውን አድምቀውት እንደነበር አይረሳም፡፡ እጅግ ሳቢና አስደናቂ ነበረ፡፡ የህትመት ውጤቶችን በተመለከተ የሁላችንም ግድ የለሽነት ያለ ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኛ አመለካከትና የፖለቲካ አቋም ጋር የማይሄድ ከሆነ ተቀብለን አናስተናግድም፡፡

አንዳንዶቻችን ደግሞ ጽሁፎች ከኛ አቅም በላይ ከሆኑና ግራ ካጋቡን ተቀምጠን መወያየት ስለምናፍር አንቀበለውም። እውነት ለመናገር ሁሉንም ነገር ማወቅ አይጠበቅብንም፡፡ ሌሎችን ማማከር ግን ነውር አይደለም፡፡ ይህንን ማድረግ ስለሚያቅተን ብዙ ነገሮችን እየተበላሹ ነው፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎቻችን ሊቀየሩ ይገባል። አምደኞቻችን በማያውቁት ጉዳይ ዘው እያሉ ባያበላሹ ደስ ይለኛል፡፡ በተለይ ከኋላችን ለሚመጡ ወጣቶች በጣም መጠንቀቅ ይገባናል። ያላነበበና ለዕውቀት ያልተጋ ጋዜጠኛ ለራሱም ለህብረተሰቡም አይጠቅምም፡፡

Read 2892 times