Saturday, 30 March 2013 14:58

ለጋዜጠኝነት ሞያው የተንገላታው ነጋ ወልደሥላሴ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ጊዮርጊስ ከአፄ ምኒልክ ሐውልት ፊት ለፊት ባለ አደባባይ አሮጌ መፃህፍት ደርድሮ ከሚሸጥ ነጋዴ “ፔሌ ከሊስትሮ እስከ የኳስ ንጉስ” የሚል ርእስ ያለው መፅሐፍ አገኘሁ፡፡ 206 ገፆች ያሉት መፅሐፍ የታተመበትን ዘመን አይገልፅም፡፡ በጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ ተተርጉሞ የቀረበው መፅሐፍ በ2 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡እጄ የገባውን ጥራዝ ወደ ማንበቡ ስሸጋገር መፅሐፉ ብቻ ሳይሆን ተርጓሚውም ሊታወስ የሚገባው ሰው መሆኑን አስተዋልኩ፡፡ “የኦሎምፒክ መንፈስ ከክርስቶስ ልደት በፊትና ዛሬ” በሚል ርእስ በ1963 ዓ.ም መፅሐፍ ያሳተመው ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ፤ በሁለቱም መፃህፍቱ የውስጥና የሽፋን ገፆች ላይ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን በአድናቆት የተሞሉ አስተያየቶች አስፍረውለታል፡፡

* * *

ከትግራይ (አድዋ) ኮብልሎ በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በትሬንታ ኳትሮ ተጭኖ ነው፡፡ በእረኝነት በመሰማራት ነበር ከሥራ ጋር መተዋወቅ የጀመረው፡፡ በትውልድ መንደሩ እያለ እስከ 4ኛ ክፍል የመማር እድልም አግኝቷል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ያልሞከረው ሥራ የለም ማለት ይቻላል፡፡ የቤት ሠራተኞች “አሽከር” ተብለው በሚጠሩበት ዘመን በሰው ቤት ተቀጥሮ በአሽከርነት ሰርቷል፡፡ በሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ ያገለገለበት ዘመን ነበር፡፡ እንቁላል ነግዷል፡፡ ጋዜጣም አዙሮ ሸጧል። በግል በጀመረው ንግድ የራሱን ገንዘብ ሲይዝ ከሌሎች ጋር በሽርክና ነግዷል፡፡ በኋላ ላይ ራሱን ችሎ የግሉ ሱቅ ከፍቶ ለተወሰነ ጊዜ ብቻውን ለመነገድ ሞክሯል፡፡ በሱቁ የጀመረው ንግድ ለኪሳራ ሲዳርገው ዝቅ ማለትን ሳይፈራ የሱቅ በደረቴ ንግድ ጀመረ።

እሱም አልሆን ሲለው በልብስ ሰፊዎች ሱቅ በዘምዛሚነት ተቀጠረ፡፡ ወደ ስፖርት አምርቶ በአማተር ቦክሰኝነት በአዲስ አበባና በድሬደዋ ለውድድር የቀረበበት ጊዜ ነበር፡፡ ደላላ ሆኖም ሰርቷል፡፡ በድለላ ሥራው የተጭበረበረ ዕቃ ገዝቶ ለእስር ቤት ተዳረገ። ከወህኒ ቤት ሲወጣ በጋራዥ ተቀጠረ፡፡ እዚያ መካኒክነትና ሹፍርናም ተማረ፡፡ በጋራዡም ብዙ አልቆየም፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በተላላኪነት ተቀጠረ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ነፍሱ እፎይ ማለት የጀመረችውና የነፍሱ ጥሪ ከሆነው ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር መገናኘት የቻለው፡፡ ነጋ ወልደሥላሴ በሬዲዮና በጋዜጣ በሚያቀርባቸው ስፖርታዊ ዘገባዎች ታዋቂ ከመሆኑ በፊትም በጋዜጠኝነት ሙያ ዘርፍ ብዙ ከመድከሙ ባሻገር ፅናትና ትእግስት የሚጠይቅ ቀላል የማይባል ውጣ ውረድ ገጥሞታል፡፡

ከላይ ያቀረብኩትን ጨምሮ ስለ ነጋ ወልደሥላሴ ማንነት “በኦሎምፒክ መንፈስ” መፅሐፍ የጀርባ ገፅ ላይ ምስክርነቱን ያሰፈረው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን፤ ነጋ ወልደሥላሴ ወደ ጋዜጠኝነት የገባበትን ሂደት በዚህ መልኩ ይገልፀዋል፡- “በሀገራችን ጋዜጠኞች አሉ ቢባል አብዛኞቹ ወደሙያው የገቡት በአጋጣሚ ነው፡፡ ነጋ ግን ሙዝዝ ብሎ ያለማቋረጥ በር አንኳኩቶ እንዲከፈትለት አሰልችቶ ነው ሊባል ይችላል፡፡ እኔ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ውስጥ ሳለሁ እንደዛሬው የስፖርት ጋዜጠኛ ሳይበረክት፤ ፍቅሩ ኪዳኔ ወደ ኮንጐ ሄዶ ዘወትር የስፖርት ዜና ሲያመጣልኝ አስታውሳለሁ። (በዚያው ወቅት ነጋም ስፖርታዊ ዜናዎችን ሲያመጣልኝ) ግማሹን ቅርጫት ውስጥ እጥልበታለሁ። ግማሹን እቆራርጥበታለሁ፡፡ አንደኛ የስፖርት ስሜት አልነበረኝም፤ ሁለተኛ አፃፃፉ እንደ ፍቅሩ ቀልድ የለውም ነበር፡፡ ነጋ ግን ተስፋ አይቆርጥም፤ አይታክትም ነበር፡፡

ቅርጫት ውስጥ የተጣለበትን፣ ግማሹ የተቆራረጠበትን “አልጠቀመም መሰለኝ?” ይልና አሁንም ሌላ ይዞ ይመጣል፡፡ መመላለሱ እያሳዘነኝ በይሉኝታ ብቻ የማትምለት ጊዜ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ግን የስፖርቱን ገፅ በሙሉ ለመያዝ በቃ፡፡” ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ “የኦሎምፒክ መንፈስ” መፅሐፉን ባሳተመበት በ1963 ዓ.ም የግል የሕይወት ታሪኩን የያዘ ዳጐስ ያለ መፅሐፍ ሊያሳትም መሆኑን ሲነግረኝ እንዲያቆየው መከርኩት የሚለው ጋዜጠኛና ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን፤ ነጋ ወልደሥላሴ በትምህርቱ ብዙ ሳይገፋ ለዚያ ደረጃ መድረስ በመቻሉ፣ የተሰጥኦውንና የችሎታውን መጠን በማወቁ፣ የአገራችን ስፖርት እንዲያድግና እንዲስፋፋ በመትጋቱና ላመነበት ጉዳይ ከባለስልጣናት ጋር ሁሉ ለመሟገት ድፍረት የነበረው በመሆኑ እንደሚያደንቀው መስክሮለታል፡፡ ጋዜጠኛና ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ስለ ነጋ ወልደሥላሴ በሰጠው አስተያየት፤ “ከስፖርት ባለስልጣኖች ጋርም በሐሳብ እንደተጋጨ ነው” የሚለውን እውነት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በሌላ ጊዜና ቦታ አረጋግጠው መስክረውታል፡፡

“ፔሌ ከሊስትሮ እስከ የኳስ ንጉሥ” የሚል ርእስ ባለው የነጋ ወልደሥላሴ መፅሐፍ ውስጥ ስለተርጓሚው ያላቸውን አድናቆት በፅሁፍ ካሰፈሩት አንዱ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው፡፡ ተተርጉሞ የቀረበው የፔሌ ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ሥራ ነው ያሉት አቶ ይድነቃቸው ስለ ተርጓሚው ሲናገሩ፡- “አቶ ነጋ ወልደሥላሴ፤ ከብዙ ዘመን ጀምሮ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ ከመሆናቸው በፊት በጋዜጣ በመፃፍ፣ በሬዲዮ በመናገር ያገራችንን ስፖርት ለማሳወቅ ብዙ የጣሩ ስለሆነ ረድተውናል፤ ረድተናቸዋልም፡፡ ከዚያም በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ያስተያየት መጋጨት በመጣ ጊዜ በቀጥታም ሆነ ጉዳዩ በሚመለከተው ክፍል በኩል ተቋቁመናቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት በሚያስፈልገው መንገድ ተባብረን መሥራታችንን አላቋረጥንም፡፡”

የበጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት እንደራሴና የኢትዮጵያ ፉትቦል ሬዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል ታምራት ይገዙ በበኩላቸው፤ ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ ተርጉሞ ስላቀረበው መጽሐፍና ፀሐፊ በሰጡት አስተያየት፤ “ነጋን ያደነቅሁትና ያመሰገንኩት ግን አሁን አይደለም፤ በብዙ መቶ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚራራቁትን የየአህጉሩ ሰዎች በአንድ ኦሎምፒክ ከተማ በማገናኘት ለሰው ልጅ፣ ለዓለም ሥልጣኔ፣ ለወዳጅነት፣ ለሰላምና ፍልስፍና ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተውን የኦሎምፒክን መሠረተ ዓላማና ታሪክ (የኦሎምፒክ መንፈስ መጽሐፍ) አዘጋጅቶ በቀረበበት ጊዜ ነው” ብለዋል፡፡ ይህ መረጃ የፔሌ ታሪክ ከ “የኦሎምፒክ መንፈስ” መጽሐፍ በመቀጠል መታተሙንም ያመለክታል፡፡ የስፖርት ጠቃሚነት ዜና ለመሆን የማይመረጥ በሁሉም ሰዎች ዘንድ የሚታወቅ እውነት ነው የሚል ሀሳብ አንስተው “በአሁኑ ጊዜ ዜና ነው ተብሎ ሊገመት የሚገባው ነገር ቢኖር በስፖርት አማካይነት በዓለም ላይ ዝናና ሞገስ ሊያገኙ የቻሉትን ሰዎች የሕይወት ታሪክ መመርመር ነው” ያሉት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን አንደኛ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ሥዩም ሐረጐት ሲሆኑ ነጋ ስፖርቱን ለማስተዋወቅ ላደረገው ድካም በፌዴሬሽን ሥም ምስጋና አቅርበውለታል፡፡

“ፔሌ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ አይደለም፡፡ ግን በኳስ ጨዋታ ያተረፈው ታላቅ ዝና በመላው ዓለምና በተለይም አያቶቹ በፈለሱባት በአፍሪካ ባዕድ አድርጐ የሚመለከተው የለምና፤ ነጋ ወልደሥላሴ የዚህን የታላቅ ስፖርተኛ የሕይወት ታሪክ ተርጉሞ በማዘጋጀት ለወጣቶቻችን ትምህርት የሚሆን ምሳሌ ስላቀረበ በዚህ ጥረቱ ላመሰግነው እወዳለሁ” የሚል መልዕክት በመጽሐፉ ያሰፈሩት ደግሞ በሕዝባዊ ኑሮ ዕድገትና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሕዝብ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳት አቶ ሙላቱ ደበበ ነበሩ፡፡ “ፔሌ ከሊስትሮ እስከ የኳስ ንጉሥ” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ተተርጉሞ ለአንባቢያን የደረሰበት ሂደትም የሚያስገርም ታሪክ አለው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለስልጣናት ሀሳብ ሲያበቃ “ይህንን ሳያነቡ ወደሌላው አይለፉ” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር የቀረበው ጽሑፍ፤ የትርጉም ስራው እንዴት ለአንባቢያን መድረስ እንደቻለ ዝርዝር ታሪኩን ያመለክታል፡፡ ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ፤ የፔሌን ታሪክ ተርጉሞ ለማቅረብ ሲያቅድ ሥራው ብዙ እንደማያስቸግረው ገምቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዘመኑ በፔሌ የሕይወትና የሥራ ታሪክ ዙሪያ ታትመው የቀረቡ 12 ያህል መፃሕፍት ታትመው መሰራጨታቸውን ሰምቶ ነበር፡፡ ከመፃሕፍቱ ግን አንዱንም ማግኘት አስቸጋሪ ሆነበት፡፡

ያሰበው ነገር ከግምቱ ውጭ ሲሆንበት ሌላ አማራጭ ማፈላለግ ያዘ፡፡ ግብፆች ወደ አረብኛ የተረጎሙትን የፔሌን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ አገኘ፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የአረብኛ ፕሮግራም ክፍል ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ አህመድ አሕመዲን የአረቢኛውን መጽሐፍ እያነበቡ ወደ አማርኛ በቃል ሲተረጉሙለት፣ ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ ወደ ጽሑፍ በመለወጥ የመጽሐፉ ሥራ ተጀመረ፡፡ ከአራት ወር በኋላ የመተርጎም ሥራው ተጠናቀቀ፡፡ መጽሐፉ ታትሞ ለአንባቢያን እንዲደርስ አህመድ አሕመዲን፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ነጋሽ ገ/ማርያም፤ ማዕረጉ በዛብህ እና ገዳሙ አብርሃ ብዙ እገዛና ትብብር እንዳደረጉለት የሚገልፀው ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ፤ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተደረገለትን ትብብር እንዲህ ሲል ገልፆታል፡፡ “መጽሐፉ ተዘጋጅቶ ለመታተም የሚበቃበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ግን የማሳተሚያ ገንዘብ ከየት ይምጣ? በቢሮ ጠረጴዛዬ ውስጥ ተቆልፎበት ተቀመጠ፡፡

ራሴን ለማሞገስ ሳይሆን በተፈጥሮዬ ሰውን መጠየቅና ማማከር እወዳለሁ፡፡ ይህ በመሆኑም ይመስለኛል የፔሌ መጽሐፍ በአደባባይ ለመታየት የበቃው፡፡ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ልመንህ መጽሐፉ ታትሞ ከወጣ በኋላ እየተሸጠ እዳዬን እንድከፍል ፈቀዱልኝ፡፡ ይህ ባይፈጸምልኝ ኖሮ ምኞቴ ሁሉ ሕልም ሆኖ ይቀር ነበር” ጋዜጠኛ ነጋ ወልደሥላሴ “የኦሎምፒክ መንፈስ” እና “ፔሌ ከሊስትሮ እስከ የኳስ ንጉሥ” በሚል ርዕስ ካሳተማቸው ውጭም ሌሎች መፃሕፍትን አሳትሟል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ መፃሕፍቱ ግን ከገበያ ጠፍተዋል፡፡ በ1963 ዓ.ም አዘጋጅቶት የነበረው ግለ ሕይወት ታሪኩን ጨምሮ ሥራዎቹ ዳግም ታትመው ለሕዝብ ቢቀርቡ ለአንባቢያን ብዙ ቁም ነገር እንደሚያስተላልፉ እኔ ያገኘኋቸው የጋዜጠኛው ሁለት መፃሕፍት አረጋግጠውልኛል፡፡

Read 2708 times