አራት ኪሎ አካባቢ መጽሐፍ ሲገዛ ያገኘነውና ልጁን መካነኢየሱስ ት/ቤት የሚያስተምረው አቶ አሻግሬ ሲሳይ የአንደኛ ክፍል መማሪያ መፃሕፍት ለመግዛት ከአንድ ሰዓት በላይ ወረፋ መጠበቁን ተናግሯል፡፡ ሌሎች ወላጆች በበኩላቸው ከሁለት ሰዓት በላይ ወረፋ ጠብቀው ባለማግኘታቸው ሁለት እና ሦስት ጊዜ ለመመላለስ ጊዜ እና ጉልበት ማባከናቸውን ይናገራሉ፡፡
መፃሕፍቱን የሚያከፋፍለው የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻ እና ማከፋፈያ ድርጅት ሥነምግባር መኮንን አቶ ግርማ ረጋሳ በአዲስ አበባ አራት መፃሕፍት ማከፋፈያዎች እንዳሉዋቸውና በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች በተማሪ መታወቂያ በሽሮሜዳ፣ አራት ኪሎ፣ ጉርድሾላ መሳለሚያ መደብሮች መፃፍት እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎችንስ ብለን ለጠየቅናቸው ያለን ቅጂ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ለግል ትምህርት ቤት መሸጡን አቁመናል፤ ብለውናል፡፡