• በሴሚናሩ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል
ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ 17ኛውን የበይነ ዲስፕሊን ሴሚናር አካሂዷል። በዚህ ሴሚናር ላይ ለፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ሃሳቦች እንደቀረቡ ተገልጿል።
የዩኒቨርስቲው መስራች እና ፕሬዝዳንት ወንድወሰን ታምራት (ዶ/ር) የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የዋጋ ግሽበት፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እና የፋይናንስ ስርዓቶችን የሚደግፉ የሕግ ማዕቀፎችን ጨምሮ በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች በሴሚናሩ ላይ እንደቀረቡ ተናግረዋል። አያይዘውም፣ ይህ ሴሚናር ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ላለፉት 17 ዓመታት በጥናት እና ምርምር ዙሪያ ካከናወናቸው ስራዎች አንዱ መሆኑን በመጠቆም፣ ሴሚናሩ የትምሕርትና ማሕበራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የበይነ ዲስፕሊን አቀራረብ በመከተል ከተለያዩ የትምሕርት ዘርፎች የተውጣጡ ምሁራን አሁን ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሔ ሃሳብ የሚያበረክቱበት ስለመሆኑ አመልክተዋል።
በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ በሚገኘው የቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ፣ ዋናው ግቢ የተካሄደው ይህ ሴሚናር ተመራማሪዎችን፣ ባለሞያዎችን እና ባለድርሻ አካላትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአካዳሚያዊ የሃሳብ ልውውጥና ሂሳዊ አስተያየቶች የሚቀርቡበት መድረክ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ሴሚናሩ በይነ ዲስፕሊናዊ ገጽታን የተላበሰ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርስቲን ጨምሮ፣ ከአርባምንጭ፤ ወራቤ፤ ባሕር ዳር፤ ወልድያ እና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች ጥናታዊ ጽሁፋቸውን እንዳቀረቡ አስረድተዋል።
በሴሚናሩ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ተሰንደው ጥቅም ላይ እንዲውሉ “ይደረጋል“ ያሉት ወንድወሰን (ዶ/ር)፣ ለፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ሃሳቦች እንደቀረቡ ተናግረዋል። አክለውም፣ 12 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው፣ በሴሚናሩ ተሳታፊዎች ውይይት እንደተደረገባቸው ነው ያስታወቁት።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

