Saturday, 27 January 2024 00:00

የገነነ የህይወት ታሪክ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች ከ40 በላይ ያገለገለው ገነነ መኩሪያ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት
የተለየ ሲሆን የቀብር ስነስርዓቱ በመንበረ ፅባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ተፈፅሟል።
ገነነ መኩርያ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት እንዲሁ በታሪክ ወጎች ፀሐፊና አቅራቢነት በህትመትና በብሮድካስት
ሚዲያዎች ፈር ቀዳጅና ተምሳሌት ነበር።

ገነነ መኩሪያ ከአባቱ አቶ መኩሪያ ገብረስላሴ ፥ ከእናቱ ወ/ሮ የሸዋ ወርቅ ደገፉ  መጋቢት 5በ1955 ዓ.ም በይርጋዓለም ከተማ በተለምዶ “አራዳ “ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ተወለደ ። ለቤተሰቦቹም 7ኛ ልጅ ነበር ። ከገነነ ውልደት በኋላ መላው የቤተሰብ አባላት በስራ ምክንያት ይርጋለምን በመልቀቅ የተወሰነ ጊዜ አጄ ከተማ ከኖሩ በኋላ በቀጣይ ኑሮአቸውን ሙሉ ለሙሉ ሻሸመኔ ከተማ አደረጉ።ትንሹ ገነነ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ናኦድ ት/ቤት ፥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ሻሸመኔ አጠቃላይ ትምህርት ቤት በመማር ጨርሷል ።
ገነነ መኩሪያ በልጅነት ዕድሜው ሁለት ነገሮች  በእጅጉ ይወድ ነበር ። - ስፖርትና ስነ-ፅሁፍን - በሻሸመኔ በልጅነት ዕድሜው “ አረንቻታ” እና “ ነበልባል “ ለሚባሉ የታዳጊ ቡድኖች በግብ ጠባቂነት መጫወት የጀመረው ገነነ መኩሪያ ዕድሜው ከፍ ሲል ለ09 ቀበሌ ፥ እንዲሁም ለሻሸመኔ አውራ ጎዳና ቡድኖች ከተጫወተ በኋላ በመጨረሻም ለሜታ ቢራና ለመብራት ኃይል ቡድኖች ተጫውቶ አልፏል ።
ገነነ መኩሪያ በልጅነት ዕድሜው ከስፖርቱ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የስነ-ፅሁፍ ችሎታም ነበረው ። ማንበብና መፃፍ የሚወደው ልጅ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት ፥ ነጋዴ የሆኑት አባቱ የተለያዩ ነገሮችን ሲፅፉበት ከርመው የሞላባቸውን የመዝገብ ደብተር ለእሱ ይሰጡታል ። እርሱም ከጋዜጦች ላይ እየቀደደ የሚያወጣቸውን የስፖርት ምስሎች የመዝገቡ ደብተር ላይ እየለጠፈ ለጓደኞቹ ያከራያቸው ነበር ። ትንሹ ገነነ የሰራውን ይሄንን የፎቶ አልበም ግማሹን ለመመልከት የቁልፍ (አዝራር) ፤ እንዲሁም ሙሉውን ለመመልከት ለመመልከት 5 ሳንቲም መክፈል ግዴታ ነበር ። ትንሹ ገነነ ለጓደኞቹ አልበሙን መስጠትና ክፍያውን መቀበል ብቻ ሳይሆን ስለእያንዳንዱ ፎቶ በጥልቀትም ያስረዳቸው ነበር ። ትንሹ ገነነ በዚያን ወቅት “ የአዲስ ዘመን “ ፥ እንዲሁም ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ያዘጋጀው የነበረው “ስፖርት ፋና” ጋዜጦችን ያዞር ነበር ።ትንሹ ገነነ 10 ጋዜጦችን ሲያዞር 10 ሳንቲም ክፍያ የነበረው ሲሆን ከሚወስደው ሳንቲም ይልቅ 1 ጋዜጣን ይዞ ይሄድ ነበር ።
ገነነ መኩሪያ ከእግር ኳስ ተጨዋችነቱ በኋላ በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ ወደ ጋዜጠኝነት ህይወት ገባ ። በጊዜው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለቤትነት ታትሞ የሚወጣው “መርሐ ስፖርት” ጋዜጣ ላይ ፅሁፎቹን በተባባሪነት ማስቀመጥም ጀመረ ።ሁሌም አዲስ ሀሳብን ከአእምሮው የሚያፈልቀው ሰው በጋዜጠኝነቱ ደግሞ ትልቅ ተቀባይነት እያገኘ መጣ ። ገነነ መኩሪያ በሂደትም ለብስራተ ወንጌል ሬዲና ፥ ለኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተባባሪ በመሆን እጅግ ብዙ ፅሁፎችን መስጠትም ጀመረ ። ከጊዜያቶች በኋላ የግል ጋዜጦች የመታተም ነፃነት ሲያገኙ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነችው የግል የስፖርት ጋዜጣ “ሻምፒዮንን” ማሳተም ጀመረ።በኋላም በስፖርት ወዳዱ ቤተሰብ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ በሀገራችን የስፖርት ጋዜጦች ታሪክ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘችውን “ሊብሮ” ጋዜጣን ማሳተም ጀመረ ።በዚህች ጋዜጣ ውስጥ ዘመንና ጊዜ የማይሻራቸው ብዙ ተከታታይ ታሪኮችንም ለአንባቢዎች በማድረስ ራሱን በደንብ መግለፅ ችሏል ።
ጋዜጠኛ ፥ አዲስ ሀሳብ አፍላቂ ፥ እንዲሁም የታሪክ መዝገብ የሆነው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ በጋዜጦች ካስቀመጣቸው ዘመን ተሻጋሪ ሀሳብና ታሪኮች ውጪ እጅግ ልዩ ተብለው የሚጠሩ መፅሀፎችን በመፃፍ ለንባብ አብቋቷል ።
ከእነዚህ ውስጥ
ገነነ መኩሪያ የሚያስበው አእምሮውን ፥ የሚናገርበት አንደበቱን ፥ የሚፅፉ እጆቹን ያለመታከት ለእኛ ሲሰጠን የኖረ ትልቅ የሀገር ባለውለታችን ነው ።
ገነነ መኩሪያ ያልዳሰሰው ሀሳብ ፥ ያልገለፀው ጉዳይ የለም ።
ገነነ የሰጠን በዋጋ የሚለፅ ፥ በዋጋ የሚተመን አይደለም ።
ተንቀሳቃሹ ላይብረሪ ተብሎ የሚጠራው የታሪክ መዝገባችን ገነነ መኩሪያ በ1995 ዓ.ም ጋብቻው ከወ/ሮ አስቴር አየለ ጋር በመመስረት ናኦድ ገነነ እና ኤሎሞ ገነነ የሚባሉ ልጆችን አፍርተዋል ።አስቱዬ ፥ ናኦድዬ ፥ ኤሎምዬ እያለ የሚጠራቸውን ቤተሰቦቹን በእጅጉ የሚወደው ገነነ ፥ ለባለቤቱ ተወዳጅ ባል ፥ ለልጆቹ ኩራት የሆነ አባት ነበር ።
ገነነ መኩሪያ ለሀገራችን ስፖርትና እግር ኳስ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦ በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተሰናዳው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አገልግሎት CAF GOLDEN ORDER OF MERIT AWARD ሜዳይ በክብር ተበርክቶለታል ። ይህም በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው ተሸላሚ ጋዜጠኛ ያድርገዋል ።
ትውልዱ ይርጋለም ከተማ የሆነው ፥ ትልቁ የታሪክ ማህደራችን ፥ እጅግ ብዙ ነገሮችን ሳይቆጥብና ሳይሳሳ ሲሰጠን ከኖረ በኋላ በተወለደ በ61 ዓመቱ ፥ ጥር 14 ቀን ከድካሙ አርፏል ።
ለመላው ቤተሰቡና ወዳጅ ዘመዶቹ ሁሉ እግዚአብሔር መፅናናትን ይስጥልን ።



Read 768 times