Saturday, 08 March 2014 12:48

የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት ተስፋዎችና ፈተናዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሱፕር ኢንዱራሊ እና አሶሴሽኑ
የሱፕር ኢንዱራሊ የሞተር ስፖርት ውድድሮችን ከ3 ዓመት በፊት ከሞተር ስፖርት አሶሴሽኑ ጋር በመተባበር እንዲጀመር ያስቻሉት 3 የስፖርቱ አፍቃሪዎች እና የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡  የመጀመርያው የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪ የሆነው እና በሞተር ብስክሌት በማስጎብኘት፤ ሽያጭ እና ጥገና በማድረግ የሚታወቀው ፍላቭዮ ቦናዮ ነው፡፡ ሌሎቹ ሁለት ግለሰቦች የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪዎችና በኢትዮጵያ የሞተር ስፖርት አሶሴሽን ቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ አንደኛው  በዓለምአቀፍ የዴቨሎፕመንት ተቋም ድርጅት የሚሰራውና የሞተር ብስክሌት ውድድሮች እና ተወዳዳሪዎች ተወካይ የሆነው ክሪስቶፍ  አምበርት ነው፡፡  ሌላኛው  በሞተር ስክሌት ውድድሮች ከፍተኛ ልምዱን በማጋራት የሚንቀሳቀሰውና በገጠር አካባቢዎች የሚካሄዱ  የመኪና ውድድሮችን በመምራት እና የተወዳዳሪዎቹ ተወካይ ሆኖ የሚያገለግለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኤክስፐርቱ ሲሞኒ ፌራሪ ነው፡፡ የውድድሩ ስያሜ  የተገኘው ኢንዱሮ ከሚባል የሞተርሳይክል የውድድር አይነትን ለመግለፅ ከሚጠቅም የጣሊያን ቃል እና ራሊን ደግሞ የመኪና ውድድር ይወክላል ተብሎ ሁለቱን ስያሜዎች በማጣመር ሱፕር ኢንዱራሊ ተብሎ የተፈጠረ ነው። የሱፕርኢንዱራሊ የመኪና እና የሞተር ብስክሌት ውድድር የተመሰረተበት ዋና ዓላማ አሶሴሽኑ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት የሚያገኙ ውድድሮችን በማዘጋጀት  የመንግስትን ትኩረት እና ድጋፍ ለማነሳሳት በመታሰቡ ነው፡፡ በሱፐር ኢንዱራሊ አማካኝነት በመኪናና በሞተር ብስክሌት  በየዓመቱ በገጠር አካባቢዎች ቢያንስ ሁለት ውድድሮችን ለማዘጋጀት በጠነሰሱት የመነሻ ሃሳብ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ውድድሩን በተሳካ መንገድ ማካሄድ ተችሏል፡፡  
 ባለፈው ሳምንት  በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ቀበሌ 3ኛው የሱፕር ኢንዱራሊ የመኪና እና የሞተር ብስክሌት ውድድር በኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች እንዳሉ  ማስተዋል ተችሏል። የመጀመርያው ተስፋ ሰጭ ሁኔታ ከውጭ አገር ተሳታፊዎች እንዲመጡ አባላቱ እና አሶሴሽኑ  ከፍተኛ ጥረት አድርገው ስለተሳካላቸው ነው። ከጅቡቲ የመጡ ከ10 በላይ  የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪዎችን ኛው ሱፕርኢንዱራሊ አሳትፏል፡፡ በቅተዋል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ካታጎሪዎች በመኪና እና የሞተር ብስክሌት ውድድሮቹ ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች በብዛት መሳተፋቸውና በውጤታቸው ደረጃ ውስጥ በመግባት  ተሸላሚ መሆናቸው አበረታች ነው፡፡ በተለይ አንዳንድ ወጣት ኢትዮጵያውያን የሞተር ስፖርት አፍቃሪዎች ባላቸው አቅም መኪኖቻቸውንና የሞተር ብስክሌቶቻቸውን በመለስተኛ ጋራጆች ጠግነው ለውድድር በመቅረብ ያለቸውን የተሳትፎ ፍላጎት በማሳየት ለውድድሩ አዘጋጆች መነቃቃትን ፈጥረዋል። በሱፕርኢንዱራሊ ውድድር በተለይ በሞተር ብስክሌቶች የተካሄደው ውድድር በተወዳዳሪዎች አስገራሚ ብቃት በመወዳደደርያ ሞተሮች ጥራት እና አቅም የተሳካ ነበር፡፡ በአንፃሩ በመኪና ውድድሩ በስፖርቱ አንጋፋ የተሳትፎ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች የነበሩ ቢሆንም ብዙዎቹ የመወዳደርያ መኪናዎች ከ10 ዓመት በላይ ያገለገሉ መሆናቸው እና በየካታጎሪው የተወዳደሩ መኪኖቹ ባላቸው አቅም እና አይነት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበራቸው ያን ያህል የሚያረካ ፉክክር እንዳይታይ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ  በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ በነበረው ዝግጅት የተሻለ ነው፡፡ በገጠር አከባቢ የሚገኘውን መወዳደደርያ ስፍራ በብቃት ተሰናድቷል፡፡ በውድድሮች ወቅት አስፈላጊው ጥበቃ እና ደህንነት እንዲኖር በእቅድ ተሰርቷል፡፡ የውድድሩ ተመልካቾችን በዝተዋል። ከሞተር ስፖርት አሶሴሽን ጋር በስፖንሰር ድጋፍ ሰጪ ሆነው እስከ ስምንት ኩባንያዎች መስራታቸውም እንደ ውጤት ሊጠቀስ ይችላል። የሱፕርኢንዱራሊ ውድድሮችን ለማካሄድ የሞተር ስፖርት አፍቃሪዎች ያደረጉትን ጥረት በተባባሪነት በመደገፍ እና ከስፖርት ኮሚሽን ጋር ተቀራርቦ በመስራት የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽንም ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን በአሁኑ ወቅት 265 አባላት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 150ዎቹ የስፖርቱ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡ በአዲስ የቦርድ መዋቅር መስራት ከጀመረ አንድ አመት ያልሆነውን አሶሴሽን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት አቶ ኤርምያስ አየለ ናቸው፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅነት በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ኤርምያስ አየለ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ምሩቅ መሆናቸው ከሞተር ስፖርት ጋር ያላቸውን ቅርበትን ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኤርምያስ አየለ የሱፕርኢንዱራሊ ውድድርን ለማዘጋጀት 150ሺ ብር ገደማ ወጪ መደረጉን ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ ውድድሩ ስኬታማ እንደነበርና በቀጣይ ሌሎች ውድድሮችን ለማዘጋጀት በአሶሴሽኑ በኩል ለሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤቶች የተገኙበት ነበር ብለዋል፡፡ ዘንድሮ በአሶሴሽኑ የሚካሄዱ ሌሎች ሶስት ውድድሮች እንዳሉ ያስታወቁት አቶ ኤርምያስ፤ በመጋቢት እና በግንቦት ወር መጨረሻ ሁለት የከተማ ዙር የመኪና ውድድሮች እንደሚካሄዱ እና በሰኔ ወር ደግሞ በላንጋኖ አካባቢ ልዩ የራሊ ውድድር  ለማዘጋጀት እቅድ አለን ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሞተር ስፖርት እንቅስቃሴ ከ65 ዓመታት በላይ ታሪክ አለው፡፡  በአሶሴሽኑ አባላት እና  የስፖርቱ አፍቃሪዎች በሚያደርጉት ጥረት  በየዓመቱ በሚካሄዱ የተለያዩ ውድድሮችን ህልውናውን ጠብቆ ቆይቷል። ይሁንና በኢትዮጵያ የሞተር ስፖርት እንቅስቃሴ በሽልማት መጠን ማነስ፤ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን በብዛት ባለማሳተፍ፤ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የውድድር መኪናዎች በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ
ተሳትፎ ባለማግኘት ጉልህ ለውጥ እና እድገት እያስመዘገበ አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በ1965 ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረውና ከፍተኛ እውቅና ያገኘ 5000 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሃይላንድራሊ ተካሂዶ ነበር፡፡ ከዚሁ ታሪካዊ ውድድር በኋላ ግን ተመሳሳይ ደረጃ ያለውን ውድድር ለማዘጋጀት አልተቻለም፡፡ ከታሪካዊው የኢትዮጵያ ሃይላንድ ራሊ በኋላ በተለይ በ1970 ዎቹ መጀመርያ  ተቀማጭነቱን በአዲስ አበባ ባደረገው የጣሊያን ስፖርት ክለብ ጁቬንትስ አማካኝነት ለስምንት አመታት ከ41 በላይ ውድድሮች ተደርገዋል፡፡  ውድድሮቹ በተሳታፊዎች ብዛት እና በውድድር ደረጃቸው የላቁ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ውድድሮች በኋላ የሞተር ስፖርት አሶሴሽኑ እንቅስቃሴ ለሁለት አስርት አመታት ተስተጓጉሎ ቆይቶ መነቃቃት የጀመረው በ1990ዎቹ መግቢያ ነበር፡፡ አሶሴሽኑ በስፖርቱ ፍቅር የወደቁ አባላቱን መልሶ በማስተባበር በስፋት መንቀሳቀስ ጀምሮ ከ26 በላይ የከተማ እና የገጠር አካባቢ የመኪና ውድድሮችን በየዓመቱ በማካሄድ የስፖርቱን ተወዳጅነት ሲያጎለብት ቆይቷል፡፡
ሞተረኛው ፍላቭዮ ቦናዮ  
ባለፈው ሰሞን በተካሄደው 3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ ከመኪናው ውድድር በተሻለ በተወዳዳሪዎች ምርጥ ብቃትና ተመጣጣኝ የመወዳደደርያ ሞተር ብስክሌቶች አስደናቂ ፉክክር የተደረገበት የሞተር ብስክሌት ውድድሩ ነበር፡፡ ለውድድሩ መሳካት ደግሞ የሞተር ስፖርት አሶሴሽን አባልና የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪ የሆነው ፍላቭዮ ቦናዮ ያበረከተው ሁለገብ አስተዋፅኦ ይመሰገናል።  በኢትዮጵያ  የተወለደው ፍላቭዮ ከሞተር ጋር የተዋወቀው ገና በታዳጊነቱ ነው፡፡ በቤተሰባቸው ሞተር ብስክሌቶችን ለመጓጓዣ መጠቀም ባህል ነበር፡፡ እንደውም እናቱ በሞተር ብስክሌት ወደ ትምህርት ቤት ያመላልሱት እንደነበር ፍላቭዮ ቦናዮ ያስታውሳል፡፡ በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ ላይ የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪዎችን ከጅቡቲ በመጋበዝ፤ የመወዳደርያ ሞተሮችን በማቅረብ እና የውድድሩን ሂደት በማስተባበር ከፍተኛ ሚና የነበረው ፍላቭዮ በውድድሩ የመጀመርያ ዙር ከሞተሩ ላይ ያስፈነጠረው የመከስከስ አደጋ ገጥሞት ነበር፡፡ መለስተኛ ህክምና ከወሰደ በኋላ በቀሩት ሁለት ዙሮች የሞተር ብስክሌቱን በከፍተኛ ብቃት ነድቶ ሁለተኛ በመውጣት በስፍራው የነበሩ ተመልካቾችን አድናቆት አትርፏል፡፡ ፍላቭዮ ቦናዮ ከሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪነቱ ባሻገር በሞተር ብስክሌት ጉዞ አገርን በማስጎብኘት እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም ሞተሮችን ከውጭ አስመጥቶ ይሸጣል፤ የመለዋወጫ እቃዎችን ያቀርባል፡፡ የጥገና አገልግሎትም በመስጠት በስፋት ይንቀሳቀሳል፡፡ አፍሪካን ራይዲንግ አድቬንቸርስ ቱርስ በተባለ ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሞተር ጉዞ ጉብኝት ማድረግ ለሚፈልጉ ቱሪስቶች  ምርጥ የሞተር ብስክሌቶችን በማቅረብ እና በራሱ ሞተር ጉዞውን በመምራት ይሰራል ፡፡ ፍላቭዮ በዚህ ኩባንያው የሚጠቀምባቸው 15 ሞተር ብስክሌቶች  ኬቲኤም የሚባሉ ሲሆን የኦስትሪያ ስሪቶች ናቸው፡፡ ኬቲኤም ሞተሮች  ለገጠር መንገዶች እና ለረጅም ርቀት  ጉዞዎች ተመራጮች እንደሆኑ የሚገልፀው ፍላቭዮ ከአውሮፓ ፤ ከአሜሪካ እና ከአውስትራሊያ የሚመጡ ቱሪስቶችን በብቃት እያስተናገደ እንደሆነ ተናግሯል። ለሞተር  ብስክሌት ማሽከርከርያነት እንደኢትዮጵያ የሚመች ሌላ አገር የለም የሚለው ፍላቭዮ የአየሩ ፀባይ፤ መልክዓምድሩ፤ አሸዋው፤ ተራራው፤ በርሃው በአጠቃላይ  የህዝቡ ባህልና አቀባበል ለዚህ ምክንያት ነው ይላል፡፡ ደንበኛ የሞተር ብስክሌቶች ዋጋቸው ከ80ሺ እስከ 500ሺ ብር እንደሚደርስ የገለፀው አሶሴሽኑ ከውጭ አገር ሞተር ብስክሌቶችን በማስመጣት ወጣቶችን በስፖርቱ እንዲያድጉ በማበረታት መስራት አለበት ሲል ይመክራል።  በኢትዮጵያ የሞተር ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ከ35 ዓመታት ልምድ እንዳለው የሚናገረው ፍላቭዮ፤  የሞተር ብስክሌት ውድድሮች በተለይ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በተሻለ ደረጃ እንደነበሩ  በወቅቱ የነበረው  አሶሴሽን ሞተር ብስክሌቶችን ከውጭ በማስገባት ለወጣት ስፖርተኞች የተሳትፎ እድል በመፍጠር ይሰራ እንደነበርና በዓመት ውስጥ እስከ አምስት የሞተር ብስክሌት ውድድሮች እየተዘጋጁ ከፍተኛ እድገት እየታየ  የነበረበትን ሁኔታ ባለፉት 3 ዓመታት ለመመለስ ጥረት ላይ ነን ብሏል፡፡
በመኪና ውድድር አንጋፋ የሆኑ፤ ተደጋጋሚ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁ ተወዳዳሪዎችን በመለየት ወደ አገር ውስጥ ከቀረጠ ነፃ የመወዳደርያ መኪኖችን እንዲያስገቡ የሚያስችል አሰራር መፈጠር አለበት የሚሉት የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኤርምያስ አየለ፤ ይህን ተግባር ለማከናወን አሶሴሽኑ እና እና የፌደራል ስፖርት  ኮሚሽን በጋራ ተቀናጅተው አስፈላጊውን መስፈርት በማውጣት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበው፤ መንግስት  ለስፖርቱ እድገት ፈታኝ ሁኔታዎችን እየፈጠረ የሚገኘውን የመወዳደርያ መኪናዎች ችግር ለመቅረፍ ከቀረጥ ነፃ መኪኖች የሚገቡበትን አሰራር እንደሚፈቅድ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የውድድር መኪኖች አርጅተዋል፤ መፍትሔውስ
የሞተር ስፖርት  እንደ ቅንጦት ተግባር መታየት የለበትም የሚለው የሱፕኢንዱራሊ ተባባሪ አዘጋጅ እና የሞተር ብስክሌት ተወዳዳሪ የሆነው ክሪስቶፍ  አምበርት ሲሆን ፤ በተለይ የሞተር ብስክሌት ውድድር ለተወዳዳሪዎችም ሆነ ለአዘጋጆች ዝቅተኛ ወጭ ስለሚጠይቅ በየትኛውም አገር ሊዘወተር የሚገባ ተወዳጅ የስፖርት ውድድር እንደሆነ ያስገነዝባል። በኢትዮጵያ የሞተር ስፖርት እንቅስቃሴ ከፍተኛ እድገት ለማሳየት የማይቻልበት ምክንያት ምናልባት በመወዳዳርያ መኪናዎች  ያለው ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሳይቀየር መቀጠሉ እንደሆነ የሚያመለክተው ክሪስቶፍ፤ ብዙዎቹ የመወዳደርያ መኪናዎች ከ10 ዓመታት በላይ ያገለገሉ፤ ያረጁ እና የወቅቱን ደረጃ የማያሟሉ መሆናቸው የውድድሮችን ማራኪነት አደብዝዞታል ይላል፡፡ አሶሴሽኑ ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮችን የመንግስትን ትኩረት ለማግኘት ጥረት መደረጉን የገለፀው ክሪስቶፍ ሃምበርት፤  የመወዳደርያ መኪናዎችን ወደ አገር ውስጥ ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት በየውድድሮቹ የሚገኙ ስኬቶች አስተዋፅኦ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ የውድድር መኪናዎች ዋና ግልጋሎታቸው ለውድድር ብቻ እንደሆነ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን እንደሚገነዘብ አምናለሁ የሚለው ክሪስቶፍ፤ ከተወዳዳሪዎች መካከል ብዙዎቹ በራሳቸው ወጭ መኪኖችን ገዝተው ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በተደጋጋሚ ለሚያነሱት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ  መገኘቱን ተስፋ እናደርጋለን ብሏል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን  በውድድሮቻችን ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ እንደገለፁ ያመለከተው ክሪስቶፍ  አምበርት ፤ እነዚህ ወጣቶች ወቅቱን የጠበቀ የውድድር መኪናዎችን እና መለዋወጫዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እንዲችሉ አስፈላጊው ትብብር መንግስት ቢያደርግላቸው ለስፖርቱ እድገት ጠቃሚ እርምጃ ይሆናል በሚል ይመክራል፡፡ ባለፈው ሰሞን በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ ከተሳተፉ የመኪና ተወዳዳሪዎች አንዱ ሰርጂዮ ኦሊቬሮ ነው፡፡ሪክ አውቶ የሚባል ኩባንያን በመወከል በኢትዮጵያ  የሞተር ስፖርት ውድድሮች ላለፉት 10 ዓመታት የተወዳደሩት ሰርጂዮ ኦሊቬሮ  ተሳትፏቸው  ለስፖርቱ ካላቸው ፍቅር የመነጨ እንደሆነና በየውድድሮቹ በሚያስመዘግቡት ውጤት ተበረታትው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ ውድድር ላይ   ሰርጂዮ ኦሊቬሮ  ሲነዷት የተመለከትኩት የውድድር መኪና ቶዮታ ኮሮላ ኮንክዌስት የምትባል ስትሆን የተሰራችው በደቡብ አፍሪካ  ነው፡፡ በዚህች መኪናቸው በደቡብ አፍሪካና በአጎራባች አገራት በተካሄዱ በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ በማድረግ ብቻ ሳይሆን በማሸነፍም እውቅና ማትረፋቸውን የነገሩኝ ሚስተር ሰርጂዮ በአንድ ወቅት በዚምባቡዌ የተዘጋጀ ራሊ ላይ ከቱርቦ መኪኖች ጋር በመወዳደር ማሸነፋቸው የማይረሱት ገድል እንደሆነ አውግተውኛል፡፡ ይህችን ታሪከኛ ቶዮታ ኮሮላ ኮንኬስት መኪና ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው መወዳደር የጀመሩት ከ12 ዓመታት በፊት እንደነበር ያስታወሱት ሰርጂዮ አሊቬሮ ከመግባቷ በፊት ተገልበጣ ከጥቅም ውጭ ሆና ስለነበር አዲስ ሞተር እና ቦዲ አሰርተውላት ያስመጧት በአጠቃላይ እስከ 200ሺ ብር ወጭ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።  በደቡብ አፍሪካ በሚዘጋጁ የመኪና ውድድሮች  ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በአዳዲስ መኪናዎች ለመወዳደርና ያሏቸውን መኪናዎች ብቃት ለማሳደግ የሚያስፈልጓቸውን የመለዋወጫ እቃዎች ሲገዙ ከቀረጥ ነፃ በመሆኑ ብዙም ወጭ የለብንም ነበር የሚሉት ሰርጂዮ ኦሊቬሮ መኪናቸው ወደ ኢትዮጵያ ካስገቡ በኋላ በየዓመቱ በሚካሄዱ ውድድሮች ብቃቷ እየቀነሰ መምጣቱን በቅሬታ ይገልፃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለሚዘጋጁ የመኪና ውድድሮች ብዙም ዋጋቸው ያልተወደደ ምርጥ  መኪናዎችን ከደቡብ አፍሪካ ማስመጣት እንደሚቀል የሚመክሩት ሚስተር ሰርጂዮ ኦሊቬሮ፤ ብዙዎቹ መኪናዎች ዋጋቸው ከ10 ሺ ዩሮ ጀምሮ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የውድድር መኪና በሞተሩ ጉልበት ፤ በፍሬን እና በነዳጅ መስጫ ክፍሎቹ፤ በጎማው ፤ በባሌስትራው እና በተለያዩ የመኪናው አካላት የተለየ ጥንካሬ እና ብቃት የሚያስፈልግ በመሆኑ ከመደበኛው በዋጋው ይወደዳል፡፡ አንዳንድ መደበኛ መኪኖችን በተለያዩ የሞዴፊክ ስራዎች አጠናክሮ ለውድድር ብቁ አድርጎ ለማዘጋጀትም ብዙ ወጭ ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያ መኪኖችን ለውድድር በደንብ አዘጋጅቶ ለመስራት አቅም ያላቸው መካኒኮች እና ጋራዦች ቢኖሩም ብቁ መኪኖችን ከውጭ ማስገባት መንግስት በሚጥለው ቀረጥ ከባድ መሆኑ የመኪና ውድድሮችን ማዳከሙን የሚናገረው ደግሞ የከተማ ውስጥ የመኪና ውድድሮችን በማስተባበር እና ተወዳዳሪዎችን በመወከል  በአሶሴሽኑ የቦርድ አባል ሆኖ የሚያገለግለው ኸርነስቶ ሞሊናሪ ነው፡፡ ኸርነስቶ ሞሊናሬ  በሞተር ስፖርት ተወዳዳሪነት የ20 ዓመታት ልምድ ካላቸው ስፖርተኞች ዋናው ተጠቃሽ ሲሆን በኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን በሚዘጋጁ ውድድሮች ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ በንቃት ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ኤምአይኤስኤሲ የተባለ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት የሆነው ኸርነስቶ ሞሊናሪ እና ረዳት ሾፌሩ ኢሚሊዮ ግራፌቲ የሚነዷት መኪና ፎርድ ኤስኮርት የተባለች ናት፡፡  በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ ከነበሩት የውድድር መኪናዎች ባላት ግዙፍ የሞተር ጉልበት እና ብቃት የተለየችው የእነ ኸርነስቶ ፎርድ ኤስኮርት   በካታጎሪ 1 የተዘጋጀውን ውድድር አሸንፋለች፡፡ ተመሳሳይ ብቃት እና ጉልበት ካላቸው መኪኖች ጋር ውድድሮችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚናገረው ኸርነስቶ ሞሊናሪ በቀጣይ ጊዜያት በየካታጎሪው የሚወዳደሩ መኪናዎች በዝተው አስደናቂ ፉክክር የሚደረግባቸውን ሁኔታዎች እናፍቃለሁ ብሏል፡፡ በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ አግኝቼ ካነጋገርኳቸው የመኪና ተወዳዳሪዎች መካከል አዲስ አበባ ውስጥ የማተሚያ ቤት ያለው ሳሚ ጁሴፔ ሙሳ እና የራሱን የግል ትምህርት ቤት የሚያንቀሳቅሰው ረዳት ሾፌሩ ሳቫሪዮ ጉላ ይጠቀሳሉ። ጁሴፔ እና ሳቫሪዮ በውድድሩ የሚወዷትን መኪናቸውን በማሽከርከር በመሳተፋቸው  ብቻ እርካታ እንደሚሰማቸው ይገልፃሉ፡፡ ኦፔል ካዴት ጂኤስአይ የተባለችው መኪናቸው ባለ 2000 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያላት ስትሆን ካምቢዮው ብቻ 7ሺ ዩሮ የተገዛ ነው፡፡ በጣሊያን ይኖር በነበረ ጊዜ በህገወጥ የጎዳና ላይ የመኪና ሽቅድምድሞች ረጅም ጊዜ ይወዳደር እንደነበር ለስፖርት አድማስ የገለፀው ጁሴፔ በኢትዮጵያ መኖርና መስራት ከጀመረ በኋላ በስፖርት ውድድሩ ተሳትፎውን እንደቀጠለ ይናገራል።  በጣሊያን ጎዳናዎች በገንዘብ ውርርድ በሚካሄዱ የመኪና ሽቅድምድሞችን በሚኒ ኩፐር መኪናው እየተሳተፈ ደህና ገቢ ያገኝ እንደነበር የሚያስታወሰው ጁሴፔ ፤ ውድድሩ ህገወጥ ስለነበር በፖሊስ መኪና ከተወረሰችበት በኋላ እንደተወው አጫውቶኛል፡፡ ገልጿል፡፡ ጁሴፔ እና ሳቫርዮ ኦፔል ካዴት መኪናቸውን ከ13 ዓመታት በላይ ስለተወዳደሩባት በመሸጥ አዲስ መወዳደርያ የመግዛት ፍላጎት ነበራቸው፡፡ መኪናዋ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እስከ 200 ሺ ብር እንደምታወጣም ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ወደ ኢትዮጵያ  አዲስ መኪና ለማስገባት እና ኦፔል ካዴት መኪናቸውን ለመቀየር ከባድ ወጭ ስለሚጠይቅ ሽያጩን አልደፈሩትም፡፡
አማራጭ መፍትሄ ያደረጉት ደግሞ ከየእንዳንዳንዱ ውድድር በፊት ከፍተኛ የጥገና እና የሞዲፊክ ስራ በማከናወን ብቃቷን መጠበቅ ነው፡፡ የሞተር ስፖርት ከቤተሰቡ እንደወረሰው ለስፖርት አድማስ የተናገረው ሌላው የመኪና ተወዳዳሪ ሉካ ኦሊቬሮ ይባላል፡፡  አያቱ፤ አባቱ እና አጎቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በደቡብ አፍሪካ በሚካሄዱ የሞተር ስፖርት ውድድሮች በተሳትፏቸው እንደሚታወቁ የሚናገረው ሉካ ኦሊቬሮ ፤ ከረዳት ሾፌሩ ጥበቡ ቸርነት ጋር  በ3ኛው ሱፕርኢንዱራሊ የተሳተፈው ፔጆት 309 1.9 ጂቲአይ በተባለች መኪና ነው፡፡ ይህችን መኪና ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ጥገና በማድረግ ሲያዘጋጃት መቆየቱን የገለፀው ሉካ ኦሊቬሮ በሱፕርኢንዱራሊው ፈታኝ የመወዳደርያ ጎዳና መበላሸቷ እንደማይቀር ባውቅም በመኪና ውድድሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ መፎካከርን እና ፈተናዎችን ማለፍ በሚፈጥረው የጀበደኛነት ስሜት ጋር ፍቅር በመውደቄ ያን ያህል አያሳስበኝም ብሎ ወደፊት አዲስ የውድድር መኪና ለመግዛት ምኙ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል፡፡
የስፖርቱ የወደፊት አቅጣጫዎች
ከኢንዱራሊ ውድድሮች አዘጋጆች አንዱ የሆነው ሲሞኒ ፌራሪ በሰጠው አስተያየት በኢትዮጵያ ውስጥ የሞተር ስፖርት ውድድሮችን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በአሶሴሽኑ አባልነት የሚንቀሳቀሱ በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪዎች ለረጅም አመታት የስፖርቱ ሂደት እንዲቀጥል በተሳትፎ የሚያደርጉት ጥረት በየዓመቱ በመደበኛነት ውድድሮች እንዲዘጋጁ አስችሏል ያለው ሲሞን ፌራሪ  ፤ወደፊት  በእነዚህ ውድድሮች ላይ የውጭ አገር ተሳታፊዎች እየበዙ ከመጡ፤ የመወዳደርያ መኪናዎችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ከተቻለ ፤ በአሶሴሽኑ በኩል ከፍተኛ የቱሪዝም መስህብን የሚፈጥሩ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ውድድሮች ለማዘጋጀት እንደሚቻል አስገንዝቧል፡፡
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመኪና እና የሞተር ስፖርት ውድድር ማዘጋጀት የታሪክ ሃላፊነት እንደሆነ የገለፀው ደግሞ ክሪስቶፍ ሃምበርት ነው፡፡ ድሮ በሃይለስላሴ ዘመን የ5000 ኪሎሜትር ውድድር ሃይላንድ ራሊ በሚል ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ውድድር መዘጋጀቱን የሚያስታወሰው ክሪስቶፍ ሃምበርት ተመሳሳይ ደረጃ ያለውን ውድድር ለማዘጋጀት አሶሴሽኑ የተሟላ ብቃት እንዳለው በልበሙሉነት ይናገራል፡፡
ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሞተር ስፖርት ውድድር በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ ለቱሪዝም እድገት አስተዋፅኦ ይኖረዋል የሚለው ክሪስቶፍ  አምበርት፤ በኬንያ የሳፋሪ ራሊ ከመላው ዓለም በርካታ ተወዳዳሪዎችና የስፖርት አፍቃሪዎችን በመማረክ ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝበት በምሳሌነት ጠቅሶ ወደፊት አሶሴሽኑ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች በርካታ ተመልካች በማግኘት፤ ከተለያዩ አገራት ታዋቂ ተወዳዳሪዎች በብዛት በማሳተፍ እና ስፖርቱን የሚያፈቅሩ ቱሪስቶችን በመማረክ ለስፖርቱ እድገት በመስራት እና ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት እቅዳችን ነው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ከአባላቱ ጋር በትኩረት እየሰራ ያለው ውድድሮችን በብዛት እና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በብዛት ለማካሄድ መሆኑን ጠቅሶ ይህ ሁኔታ ለስፖርቱ እድገት የሚያግዙ የመንግስትን ድጋፎችን ለማግኘት እንደሚያስችል ስለታመነበት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ለሞተር ብስክሌት ውድድሩ ከጅቡቲ ተወዳዳሪዎችን  የጋበዝነው ካለን መተዋወቅ ተነስተን ነው የሚለው  ፍላቭዮ በበኩሉ ወደፊት ከኬንያ እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ተወዳዳሪዎችን በተለያዩ ግንኙነቶች ተጠቅሞ በመጋበዝ ውድድሩን በተሻለ ለማድመቅ ጥረት እናደረጋለን ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮች ስናዘጋጅ ለውድድሩ የሚቀርበውን ሽልማት ማሳደግ ያስፈልጋል ያለው ፍላቭዮ ቦናዮ በአውሮፓ፤ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ እንደሚካሄዱ ውድድሮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሞተር ስፖርት ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅም መኖሩን በእርግጠኛነት እናገራለሁ ሲል ተናግሯል፡፡

Read 2610 times