Administrator

Administrator

የእጩዎች ጥቆማ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 መሆኑ ተነግሯል

ነሐሴ ወር መጨረሻ ለሚካሄደው 12ኛው የበጎ ሰው ሽልማት፣ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም የእጩ ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል የሽልማት ድርጅቱ የቦርድ አመራሮች አስታወቁ። አመራሮቹ ይህን ያስታወቁት ባለፈው ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
“በጎ ሰዎችን በመሸለምና እውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ” በሚል መሪ ቃል ባለፉት 11 ዓመታት ለአገርና ለወገን አብነት የሚሆን አኩሪና በጎ ስራ የሰሩ የሀገርና የወገን ባለውለታ በጎ ሰዎችን ሲሸልምና ሲያከብር የቆየው የቆየው የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት፤ ዘንድሮም ለ12ኛ ጊዜ በ10 ዘርፎች በጎዎችን ለመሸለም  በዝግጅት ላይ መሆኑን በመግለጫው ተነግሯል፡፡
በጎዎች የሚሸለሙባቸው አሥሩ ዘርፎች፡- መምህርነት፣ ኪነጥበብ፣ በጎ አድራጎት፣ ንግድ ኢንዱስትሪና ስራ ፈጠራ፣  በመንግስታዊ ተቋማት ሐላፊነት፣ ቅርስ ባህልና ቱሪዝም፣ ማህበራዊ ጥናት፣ ሚዲያና ጋዜጠኝነት መሆናቸውም ተብራርቷል።
የዘንድሮው የኪነ ጥበብ ዘርፍ ሽልማት፣ በኪነ ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ትኩረቱን ማድረጉ ለየት ያደርገዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም ተተኪ የኪነጥበብ ትውልድ በማፍራት ረገድ ተቋማቱ ያላቸውን ጉልህ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም የቦርድ አመራሮች ጨምረው ገልፀዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የ10ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት፣ የጋዜጠኝነት ዘርፍ አሸናፊ የነበረው ጋዜጠኛ ግርማ ፍሰሃ  ሽልማቱ የፈጠረበትን ስሜት፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ የተቀበለውን የሃላፊነት ስሜትና የስራ ተነሳሽነት በመግለፅ፣ ልምዱን ያካፈለ ሲሆን፤ የሽልማት ድርጅቱ በቂ  ድጋፍ ቢደረግለት በርካታ በጎዎችን ሊያፈራ እንደሚችል ተናግሯል፡፡
የበጎ ሰው ሽልማት ላይ ሊሸለሙ ይገባቸዋል የሚሏቸውን በጎዎች ለመጠቆም በ+251977232323 ስልክ ቁጥር ቴሌግራም፣ ቫይበርና ዋትስአፕን በመጠቀም ወይም በኢሜይል አድራሻ፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በመላክ እንዲሁም በ150035  የፖስታ ሳጥን ቁጥር በመጠቀም፣ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ለአንድ ወር ያህል  ጥቆማ መላክ እንደሚቻል ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ሰዊት ጌታቸው፣ አንዱአለም አባተ (የአፀደ ልጅ) ፣ አዲሱ ሸዋ ሞልቶትና ደራሲና ጋዜጠኛ  በኩረ ትጉሃን ጥበቡ በለጠ አብራርተዋል።


ነገ በአአዩ ባሕል ማዕከል እንገናኝ።
 

ምንጩን ተከትሎ የሚጓዘው አረንጓዴ ውሃ ፣ በጠፍጣፋ ቡናማ ድንጋዮች ዙሪያ ትናንሽ የኳስ  አረፋዎች እየፈጠረ በጸጥታ ይፈስሳል። በወንዙ ዳርቻ የበቀሉትና ትካዜ ያጠላባቸው የሚመስሉት ዛፎች በውሃ ውስጥ ነጸብራቃቸው ይስተዋላል። ማርኒ ሳሩ ላይ ተቀምጣ ወደ ኩሬው ድንጋይ ትወረውራለች። ከዚያም እየሰፉ የሚመጡትን ክቦችና በጭቃማው የኩሬው ዳርቻ የሚፈጠሩትን ትንንሽ ሞገዶች ታስተውላለች። ማርኒ ስለ ሙጭሊቶቿ (የድመት ግልገሎቿ) እያሰበች ነበር። ባለፈው አመት ስለተወለዱት ሙጭሊቶች ሳይሆን በዚህ ዓመት ስለተወለዱት ሙጭሊቶች  ነበር  የምታስበው። እናቲቱ ድመት - ፒንኪ የዛሬ ዓመት የወለደቻቸው ሙጭሊቶች  ወደ ሰማይ ቤት መሄዳቸውን  ለማርኒ የነገሯት ወላጆቿ ነበሩ፡፡  አዲስ የተወለዱትን ድመቶች ሳትጠግባቸው ነበር ያጣቻቸው፡፡ ሙጭሊቶቹን ከሦስት ቀን በላይ ለማየት አልታደለችም።
“እግዚአብሔር በገነት አብረውት እንዲኖሩ ወስዷቸዋል።” ነበር ያሏት አባቷ።
ማርኒ አባቷ ያሏትን  ልትጠራጠር አትችልም፡፡ አባቷ ሃይማኖተኛ ናቸው። የእግዚአብሔር አገልጋይ፡፡ ሰንበት ት/ቤት በየሳምንቱ ያስተምራሉ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥም ትልቅ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ከምእመናኑ የተሰበሰበውን ገንዘብ እየቆጠሩ በአንድ ትንሽ ቀይ መዝገብ ላይ ያሰፍራሉ። በአዘቦት  ቀናትም እንዲሰብኩ ተመርጠዋል። ማታ ማታ ለቤተሰባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ምዕራፍ ያነባሉ። ማርኒ ባለፈው ምሽት ለንባብ ፕሮግራሙ በሰዓቱ ባለመድረሷ ከአባቷ ዋጋዋን አግኝታለች። አባቷ “ልጅ ካልተቀጣ መረን ይለቃል” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው። እናም ማርኒ አባቷን በፍፁም ልትጠራጠር አትችልም። ለእሷ፤ስለ ሙጭሊቶቹና ስለ እግዚአብሔር የሚያውቅ ፍጡር ካለ እሳቸው ብቻ ናቸው፤ አባቷ።
ሆኖም ማርኒ ለብዙ ጊዜያት ድንገት ስለተሰወሩት ሙጭሊቶች እያሰበች መገረሟና ግራ መጋባቷ አልቀረም፡፡ በዓለም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የድመት ግልገሎች እያሉ እግዚአብሔር ለምን አራቱንም የእርሷን ሙጭሊቶች ለመውሰድ መረጠ?  እግዚአብሔር ይህን ያህል ራስ ወዳድ ነው እንዴ?
ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ግን ስለ ሙጭሊቶቹ እንዳታስብ የሚያደርጓት በርካታ ጉዳዮች ተከናውነዋል። ትምህርት ቤት የገባችበት የመጀመሪያ ዓመቷ ነበር። ለመጀመሪያው የትምህርት ቀን ስትሰናዳም ሆዷን ባር ባር ብሏታል - ትንሽ ተሸብራ ነበር፡፡ ደብተር፣ እርሳስና መጽሐፍት መገዛት ነበረባቸው። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ትምህርቱን ወድዳው ነበር። ከፊደላትና ቁጥሮች ጋር ያደረገችው የመጀመሪያ ትውውቅ አስደስቷታል። ውሎ አድሮ ግን ማርኒ ትምህርት እየሰለቻት ሲመጣ፣ የገና በዓል በአንፀባራቂ የበረዶ ብናኞች ታጅቦ ከተፍ አለ። የገና ስጦታ ሸመታው፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰማያዊ መብራቶቹ፣ ወዲህና ወዲያ እየተንገዳገዱ ከአንዱ ጥግ የቆሙት  የገና አባት፣ እንዲሁም በዋዜማው የሚከናወነው የቤተ ክርስቲያን የሻማ ስነ-ስርዓት፡- እነዚህ ሁሉ ክንዋኔዎች ማርኒ ስለ ሙጭሊቶቹ እንዳታስብ አድርገዋት ነበር።
በመጋቢት ወር፤ ጎላ ያሉ እንቅስቃሴዎች እየተዳከሙ ሲመጡ፣ የማርኒ እናት መንታ ህፃናትን ወለደች። ማርኒ መንትዮቹ መጀመሪያ ላይ እንዴት ትንንሽ እንደነበሩና ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን እንዴት በቀስታ እያደጉ እንደመጡ አስተውላ ተገረመች። በሰኔ ወር ላይ መንትዮቹ ሦስት ወር ሆኗቸው ነበር። በዚህ ወቅት ህፃናቱ በደንብ አድገዋል። የማርኒ ትምህርት ቤት ተዘግቷል። የገና በዓልም ተመልሶ የማይመጣ በሚመስል ሁኔታ ካለፈ ረዥም  ጊዜ አስቆጥሯል። ሁሉም ነገር ለማርኒ አሰልቺ መሆን ጀምሯል። በዚህ ወቅት ነበር ማርኒ ድንገት ያልጠበቀችውን ዜና የሰማችው፡፡ ፒንኪ ሌሎች ትንንሽ ድመቶችን በቅርቡ ትወልዳለች ተባለ፡፡ ይህን ዜና አባቷ ለእናቷ ሲነግሩ የሰማች ዕለት ደስታዋን መቆጣጠር አልቻለችም ነበር። ወዲያው ነበር አዳዲስ ለሚወለዱት ድመቶች ቁርጥራጭ ጨርቆችና የጥጥ ልብሶች ማዘጋጀት የጀመረችው፡፡ የሚተኙበትም ሳጥን አዘጋጀችላቸው፡፡
ሁሉም ነገር ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ አንድ ምሽት ላይ  ፒንኪ ወደ በረቱ ተደብቃ በመሄድ ስድስት የድመት ግልገሎችን ተገላገለች።  ግልገሎቹ ግራጫና በችኮላ የተረጨ የሚመስል ጥቁር ነጠብጣ ቀለም ያለባቸው ናቸው፡፡ ማርኒ ግልገሎቹን ከመጠን በላይ ወደደቻቸው፡፡ ሆኖም እጅግ ፈርታና ስጋት ገብቷት  ነበር። እግዚአብሔር እንዳለፈው ዓመት ቢወስዳቸውስ ?
“ማርኒ! ምን እየሰራሽ ነው?”
ወደ ኋላዋ ዞራ መመልከት አልነበረባትም። ማን እንደሆነ አውቃለች- አክብሮቷን ለማሳየት ግን ዞር አለች፡፡ ከአባቷ የተቆጣ ፊት ጋር ነበር የተፋጠጠችው፡፡
“ድንጋይ እየወረወርኩኝ እየተጫወትኩ ነው” ስትል ማርኒ በቀስታ መለሰች።
“ዓሳዎቹ ላይ?”
“አይደለም አባዬ። ዝም ብዬ ነው የምወረውረው”
“ከሀይማኖት ትምህርታችን የድንጋይ ውርወራ ሰለባ ማን እንደነበር እናስታውሳለን አይደል?” አሉ አባቷ የአዋቂነት ፈገግታ በፊታቸው ላይ እየተነበበ።
“ቅዱስ እስጢፋኖስ” አለች ማርኒ።
“በጣም ጥሩ” አሉ አባቷ፤ ፈገግታቸው ከፊታቸው ላይ እየጠፋ።
ወዲያው፤ “እራት ደርሷል” አሏት።
ማርኒ በአሮጌው ቡናማ ደረቅ የብረት ወንበር ላይ ተቀመጠች። አባቷ በጥቁር ቆዳ የተለበጠውን የቤተሰቡን የድሮ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ በጥሞና የምትከታተል ትመስላለች። መጽሐፍ ቅዱሱ የተላላጠና በርካታ ገጾቹም የተቀዳደዱ ናቸው፡፡ እናቷ ከአባቷ ጎን እጆቿን ጭኖቿ ላይ አደራርባ ተቀምጣለች። “አምላክ እንዴት ጥሩ ነገር ቸሮናል” የሚል ፈገግታ ተፈጥሮአዊ ውበት በተቸረው ፊቷ ላይ ይነበብ ነበር።
“ህፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግስት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” ብለው ንባባቸውን ጨረሱና በዝግታ መጽሐፍ ቅዱሱን አጠፉት። ለብዙ ደቂቃዎች ማንም ምንም ነገር ሳይተነፍስ በዝምታ  ቆየ።
“ማርኒ፤ የትኛውን መጽሐፍና የትኛውን ምዕራፍ ነው አሁን ያነበብነው?”
“ቅዱስ ማርቆስ፤ ምዕራፍ አስር” አለች ማርኒ፤ በቅንነት በተቃኘ ድምጸት፡፡
“ደህና!” አሉ አባቷ።
የማርኒ እናት፤ “የክርስቲያን ቤተሰብ ማድረግ ያለበትን ተግባር ነው የፈጸምነው።” የሚል ፈገግታ በፊታቸው ላይ ይስተዋላል።
“ሜሪ፤ ለእኛ ቡና፣ ለማርኒ ደግሞ አንድ ብርጭቆ ወተት ብታዘጋጂስ?” አሉ የማርኒ አባት ሚስታቸውን።
“እሺ!” አሉ እናቷ  ከተቀመጡበት ተነስተው ወደ ወጥ ቤት እየተራመዱ።
የማርኒ አባት አሮጌውን መጽሐፍ ቅዱስ እያገላበጡ ይመረምሩታል። የተቀዳደደውን ገጾች በጣታቸው ይደባብሱታል። ከቢሊዮን ዓመት በፊት የኖሩት ዘር ማንዘሮቻቸው ድንገት በመጽሐፍ ቅዱሱ ገጾች ላይ ያፈሰሱትን የወይን ጠጅ በአትኩሮት እየተመለከቱ ነበር።
“አባዬ” አለች ማርኒ፤ በተጣደፈ ቅላጼ፡፡ ከመጽሐፉ ላይ ቀና ብለው ተመለከቷት። በፊታቸው ላይ ቁጣም ሆነ ፈገግታ አይስተዋልም።
“የድመቷ ልጆችስ?”
“እነርሱ?” አባቷ በሆዳቸው ነገር የያዙ ይመስላሉ።
“አሁንም እግዚአብሔር ይወስዳቸዋል?” ጠየቀች  ማርኒ።
“ምናልባት” አሉ አባት። ከዚህ ሌላ ምንም መናገር  አልቻሉም።
“አይችልም! አይወስዳቸውም!” ማርኒ ማልቀስ ጀመረች።
“እሜቴ! እግዚአብሄር ማድረግ የሚችለውና ማድረግ የማይችለውን ነገር አለ እያልሽ ነው እንዴ?” አሉ አባቷ።
“አይደለም አባዬ” አለች ማርኒ።
“እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያደርጋል!” አሉ አባቷ።
“አዎ እሱማ ያደርጋል” አለች በተቀመጠችበት እየተቁነጠነጠች። “ግን ለምን የእኔን ትንንሽ ድመቶች በድጋሚ ይወስዳል? ሁልጊዜ ለምን የእኔን ብቻ?”
“እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ይብቃ። አሁን ፀጥ በይ ማርኒ!” አሉ አባቷ፤ በቁጣ።
“ግን ለምን የእኔን?” ማርኒ ጥያቄዋን ቀጠለች።
አባቷ ድንገት ከተቀመጡበት እመር ብለው ተነሱና ወንበሩን ተሻግረው ወደ እርሷ አለፉ። ያንን ድምቡሽቡሽ የልጅ ፊቷን በጥፊ አጮሉት!! ደም ከከንፈሯ ጠርዝ ላይ በቀጭኑ መፍሰስ ጀመረ። በእጇ መዳፍ ደሟን ጠራረገች።
“ስለ እግዚአብሔር ለመጠየቅ አንቺ ገና ልጅ ነሽ”  ምራቃቸው ከንፈራቸው ላይ ተዝረክርኮ ነበር።
ክንዷን በእጃቸው አንጠልጥለው ከተቀመጠችበት አስነሷት። “አሁን ፎቁ ላይ ውጪና ቶሎ ወደ መኝታ!” አሏት በቁጣ።
ማርኒ ለመከራከር አልዳዳትም፡፡ እንደገና መፍሰስ የጀመረውን ደሟን እየጠራረገች ደረጃውን መውጣት ጀመረች። ደረጃውን ስትወጣ የእንጨት መደገፊያውን በእጆቿ እያሻሸች በእርጋታ ነበር የምትራመደው።
“ወተቱ ይኸው” ብላ እናቷ ስትናገር ማርኒ ሰማቻት።
“አያስፈልግም!” አባትየው ቁርጥ ያለ መልስ ሰጡ።
ማርኒ ከፊል ብርሃን የተላበሰው ክፍሏ ውስጥ አልጋዋ ላይ ተጋድማ ነበር። በመስኮቱ የሚገባው ብርቱካናማ ቀለም ያለው የጨረቃዋ ብርሀን፣ ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ሃይማኖታዊ ሥዕሎች ላይ እያንፀባረቀ ክፍሉን ከድቅድቅ ጭለማ ነፃ አውጥቶታል። ወላጆቿ መኝታ ክፍል ውስጥ እናቷ ከመንትዮቹ ጋር የምታወራ ይመስል እያጉተመተመች፣ የሽንት ጨርቃቸውን እየቀየረችላቸው ነበር። “የእግዚአብሔር ትንንሽ መላዕክት” አለች እናቷ፡፡ አባቷ ህጻናቱን እየኮረኮሩ ያስቋቸዋል፡፡ ማርኒ፤ “መላእክቱ“ ሲስቁ እየሰማች ነው። ከወፍራም ጎሮሯቸው እየተንደቀደቀ የሚወጣውን ጥልቅ ሳቅ እያዳመጠች ነበር፡፡
በዚህ ምሽት አባቷም ሆኑ እናቷ ደህና እደሪ አላልዋትም። እንደውም ከነአካቴው ወደ መኝታ ቤቷ ድርሽ ያለ ሰው አልነበረም። ማርኒ ቅጣት ላይ ናት።
 በበረቱ ውስጥ ከግልገል ድመቶቹ ጋር ጨዋታ ይዛለች፤ ማርኒ፡፡ ከአስር ደቂቃ በፊት እናቷ የላከቻትን መልዕክት ሳታደርስ እዚሁ በረት ውስጥ አንዷን ግራጫ ድመት እያጫወተች ነው፡፡ የድርቆሹ ሽታ አየሩን በሙሉ አውዶታል። አገዳዎቹ ወለሉን በሙሉ ስለሸፈኑት እግር ያደናቅፋሉ። ሁለቱ ላሞች እግራቸው በሽቦ በመቁሰሉ እንዲያገግሙ ግንቡ መጨረሻ ላይ ነው የታሰሩት፡፡ ትንንሾቹ ድመቶች ከማርኒ አገጭ ስር ያለውን አየር በፊት መዳፎቻቸው እየዳሰሱ ይጮሃሉ።
“ማርኒ የት ነች?” ከቤቱና ከበረቱ መካከል ቆመው አባቷ አምባረቁ፡፡
ቤት ውስጥ የእናቷን ጥሪ ስትሰማ ማርኒ መልስ ለመስጠት ከጅላ ነበር።
“የሄለንን የምግብ ሙያ መጽሐፍ እንድታመጣ ብራውን ጋ ልኬያታለሁ። ከሄደች ሃያ ደቂቃ ሆኗታል።” አለች እናቷ።
“ብዙ ሰዓት አለፈኮ”  አሉ አባቷ። አባቷ በአቧራማው መሬት ላይ ሲራመዱ የትልቁ ጫማቸው ኮቴ ወታደራዊ ምት ያስተጋባል።
አንድ ችግር እንዳለ ማርኒ አውቃለች። ማየት የሌለባት ነገር ሊፈጸም መቃረቡን ተረድታለች። የድመት ግልገሎቹን ወደ ቀዩ ወርቃማ ሳጥናቸው ከተተቻቸውና ሁኔታውን ተደብቃ ለመመልከት ወደ አገዳው ክምር እየዳኸች ሄደች።
አባቷ ወደ በረቱ ውስጥ ገቡና ከቧንቧው ውሃ በባልዲ ሞልተው ትንንሽ ድመቶቹ ፊት ለፊት አስቀመጡ። እናትየዋ ድመት ፒንኪ “እስ” ብላ የቁጣ ድምጽ አሰማችና፣ ጀርባዋ ላይ ጉብታ ፈጠረች። አባቷ ፒንኪን በእጃቸው አንስተው ባዶ ገረወይና ውስጥ ዘጉባት። ከፒንኪ የወጣው አሰቃቂ ቁጣና ጩኸት ቦታውን የአሜሪካ የእርሻ ስፍራ ሳይሆን፣ የአፍሪካ የእንስሳት መጋለቢያ ሜዳ አስመስሎት ነበር።
ማርኒ በሁኔታው በሳቅ ፈረሰች። ሆኖም የአባቷን በሥፍራው መኖር አሰበችና ሳቋን ወዲያው ገታች።
አባቷ የድመት ግልገሎቹ ወደ ተቀመጡበት ሳጥን ዞረው ተመለከቱ። አንዷን  ግልገል በጥንቃቄ ማጅራቷን ይዘው ከሳጥኑ ውስጥ አወጧት። አሸት አሸት አደረጓትና የባልዲው ውሃ ውስጥ በጭንቅላቷ ደፈቋት። ግልገሏ ድመት ባልዲው ውስጥ በስቃይ ስትንፈራፈር ይሰማ ነበር፤ የውሃ ፍንጥቅጣቂዎችም አየሩ ላይ ሲፈናጠሩ ይስተዋላል። የማርኒ አባት ፊታቸውን አጨፍግገው ግልገሏን ሙሉ በሙሉ ወደ ውሃው ውስጥ ጨመሯት። ደፈቋት! ወዲያው ግልገሏ መንፈራገጡን አቆመች። ማርኒ በፍርሃት የሲሚንቶውን ወለል በጣቶቿ እየቧጠጠች ነበር። በዚህም  ሳቢያ ጣቶቿ ክፉኛ ቆሰሉ፡፡
ግን ለምን? ለምን? ለምን? ለምን?
ወዲያው አባቷ ከባልዲው ውስጥ የተዝለፈለፈውን የግልገሏን በድን አወጡት፡፡ ደም የመሰለ ነገር ከድመትዋ  አፍ ላይ ተዝለግልጎ ይታያል፡፡ ምላሷ ይሁን አንጀቷ፤ ማርኒ አላወቀችም።
የማርኒ አባት ስድስት በድን የፀጉር ኳሶች የመሰሉ ነገሮች ማዳበሪያ ከረጢት ውስጥ ጨመሩ። ስድስቱም ግልገሎች ከመቅጽበት ተጠናቀቁ። በመጨረሻም፣ እናትየዋን ከገረወይናው ውስጥ አወጧት። ፒንኪ እየተንቀጠቀጠች ነበር፡፡ በደከመ ድምጽ “ሚያው” ብላ እየጮኸች ሰውየውን ተከተለቻቸው። ሰውየው ዞር ብለው ሲመለከቷት “እስ!” እያለች ቁጣዋን ታሰማለች፡፡
ማርኒ ለረዥም ሰዓት ሳትንቀሳቀስ ባለችበት ተቀምጣ ቆየች፡፡ ስለሌላ ስለምንም ጉዳይ እያሰበች አልነበረም። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ስለተፈጸመው አሰቃቂ የሞት ፍርድ እያሰበች ነበር። በትናንሽ ድመቶቹ  ላይ ተግባራዊ ስለሆነው የሞት ፍርድ!! ጠቅላላ ሁኔታውን ለመረዳት የተቻላትን ሁሉ ሙከራ አደረገች። አባቷን የላከው እግዚአብሔር ነው? ግልገሎቿን እንዲገድል የነገረውስ እርሱ ነው? ግልገሎቿን ከእሷ እንዲቀማ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው? እውነት እግዚአብሔር ከሆነ ዳግመኛ ከመንፈሳዊው ፊት ቀርባ ቁርባን አትቆርብም፡፡ ከሲሚንቶ ጋር የተቀላቀለ ደም ከጣቶቿ ላይ እየተንጠባጠቡ ከተቀመጠችበት ተነስታ ወደ ቤት ውስጥ ገባች።
“የምግብ አሰራር ሙያ መጽሐፉን አመጣሽ?” ጠየቀቻት እናቷ፤ ማርኒ የወጥ ቤቱን በር ዘግታ ስትገባ። “ሚስ ብራውን አላገኘችውም። ነገ እልከዋለሁ ብላለች።” ውሸቷ ራሷን ማርኒን አስገርሟታል።
“ሙጭሊቶቼን  እግዚአብሔር ወሰደብኝ!” ብላ  ድንገት ማርኒ ጮኸች። እናቷ የተደናገረች ትመስል ነበር። “አዎ” ብቻ ነበር መልሷ፡፡
“እግዚአብሔርን እበቀለዋለሁ!! እርሱ እንዲህ ሊያደርግ አይችልም! አይችልም!” እያለች ከወጥ ቤቱ ተስፈንጥራ ወጥታ የፎቁን ደረጃ መውጣት ጀመረች።
እናቷ ቆማ እየተመለከተቻት ቢሆንም፣ እንቅስቃሴዋን ግን  መግታት አልቻለችም።
ማርኒ ኮውፊልድ ደረጃውን ስትወጣ በዝግታ  እየተራመደችና ለስላሳውን የእንጨት መደገፍያ በእጇ እየታከከች ነበር።
ቀትር ላይ ዋልተር ኮውፊልድ ከእርሻ ቦታ ሲመጡ፣ የሳህንና የብርጭቆ ኳኳታ ከዋናው ቤት ሰሙ፡፡ በፍጥነት ወደ ሳሎኑ  አመሩ፡፡ ደረጃው ስር ሚስታቸውን ወድቃ አገኟት። ጠረጴዛው ተገለባብጧል። እቃዎች  ተበታትነዋል፡፡ ሳህኖች ተሰባብረዋል።
“ሜሪ! ሜሪ! ተጎዳሽ?” አሉ ዋልተር፤ በፍጥነት ወደ ሚስታቸው ጎንበስ ብለው።
የማርኒ እናት ዓይኖቿ በእንባ ጭጋግ ተሸፍነው “ዋልት! የፈጣሪ ያለ! ዋልት- ውድ መላዕክቶቻችን- ገንዳ ውስጥ -አዎ! ውድ መላእክቶቻችን!!!” አለች የእንባዋ ጎርፍ በፊቷ ላይ እየፈሰሰ።




Tuesday, 28 May 2024 15:50

ለውድ አንባቢያን፡-

 ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ ከዚህ ቀደም ያላጋጠመ ትልቅ ስህተት ተፈጥሯል፡፡ በብርሃንና ሰላም ማተምያ ቤት በተከሰተ “የቴክኒክ ችግር” ሳቢያ፣  የሌላ  ጋዜጣ ገጾች ተቀላቅለው (ከእኛ ዕውቅና ውጭ) ለሥርጭት በቅቷል፡፡ ጋዜጣው ለሥርጭት ከመብቃቱ በፊት ስህተቱን ብናውቅ ኖሮ፣ ከሥርጭት ማገድ እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን እኛም መረጃው የደረሰን ከውድ አንባቢያን በመሆኑ ከማዘንና ይቅርታ ከመጠየቅ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ ከማተምያ ቤቱ ጋር በነበረን የ25 ዓመት ገደማ የጠበቀ የሥራ ግንኙነት፣ በየጊዜው ትናንሽ ስህተቶች ቢፈጠሩም፣ የአሁኑን ያህል ከባድ ስህተት አጋጥሞን አያውቅም፡፡ ከማተምያ ቤቱ ማናጅመንት ጋር በመነጋገር ስህተቱ የተፈጠረበትን ትክክለኛ  ምክንያት ለማወቅና ዳግም መሰል ስህተቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ እየጣርን ነው፡፡ የራሳችንንም መፍትሄዎች እናበጃለን፡፡ ለአሁኑ  ስህተት ግን ውድ የጋዜጣውን አንባቢያን በድጋሚ ከልባችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ የጋዜጣችንን የጥራት ደረጃ የማሳደግና ተነባቢ የማድረግ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል
አዲስ አድማስ - የእርስዎና ቤተሰብዎ!!

ከኤልያስ ጋር ስትሰሪ ራስሽንም ጭምር ሰርተሽ ነው የምትወጪው


ሙሉ አልበም መስራት አንድ ልጅ አርግዞ እንደመገላገል ነው፡፡ ድካም ውጣ ውረድ፣ ጭንቀት፣ የሆርሞን መቀያየር አለው ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ትክክል ነው፡፡ የተባለው ነገር ሁሉ አለውና ተገላግያለሁ ማለት ይቻላል፡፡
አልበሙ በወጣ በአራተኛው ወይም በአምስተኛው ቀን ላይ ነው የተገናኘነው፡፡  “ማያዬ” አልበምሽን አድማጭ እንዴት እየተቀበለው ነው? ለጥያቄው በጣም ፈጠንኩ እንዴ?
አልፈጠንሽም፤ ምክንያቱም አንድ ነገር ጥሩ መሆኑን ከጅምሩ ማየት ይቻላል፡፡ ብዙ ሰው እያደመጠው ጥሩ እየሄደ ነው፡፡ አብዛኞች ወዳጆቼ አዳምጠውታል፡፡ በጣም ከማልጠብቃቸው ሰዎች ሁሉ በጣም ገንቢ አስተያየት እየመጣልኝ ነው፡፡
ከማልጠብቃቸው ስትይ….. እንዴት ማለትሽ ነው
ከማልጠብቃቸው ስልሽ በጣም ትልልቅ ሰዎች….. ሙዚቃን በዚህ ልክ ጊዜ ኖሯቸው ክሪቲካሊ አዳምጠው አስተያየት ይሰጣሉ ብዬ የማልጠብቃቸው…. ሰዎች ሁሉ አድምጠው በጣም ልብ የሚያሞቅ አስተያየት ሰጥተውኛል፡፡ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡ እኔ ትኩረቴ ስራ ላይ ብቻ ነበርና፣ ከምጠብቀው በላይ ምላሽ እያገኘሁ ነው ገና ከጅምሩ፡፡
እስኪ ትንሽ ወደ ኃላ መለስ ብለን ወደ ልጅነትሽ ዘመን እንጓዝ፡፡ በ15 ዓመትሽ ነበር ከባሌ ወጥተሽ ወደ አዲስ አበባ የመጣሽው?
ወደዚህ የመጣሁት ሳይሆን ከባሌ የወጣሁበት ነው ያ ዕድሜዬ፡፡ 10+2 እንስሳ ህክምና ነበር የተማርኩትና የግብርና ባለሙያ ሆኜ እዚያው የተወለድኩበት አጋርፋ አካባቢ የምትገኝ “ሸነካ” የምትባል ቦታ ለጥቂት ጊዜ ሰርቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ የመጣሁት በ18 ወይም በ19 ዓመቴ አካባቢ ነው፡፡  የመጣሁትም ለትምህርት ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴአትር ጥበባት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያዝኩኝ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬንም በ”ቴአትር ፎር ዴቨሎፕመንት” እዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው የተመረቅኩት፡፡
የልጅነት ጊዜሽን እንዴት እንዳሳለፍሽና ስለ ቤተሰብሽ ሁኔታ እስቲ አጫውቺኝ….
እንደነገርኩሽ ተወልጄ ያደግኩት ባሌ ነው፤ አጋርፋ በሚባል ቦታ፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ 450 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ልጅነቴንም እስከ ሀይስኩል ማጠናቀቅ ድረስ እዚያው ነው ያሳለፍኩት፡፡ ቤተሰቦቼ መምህራን ናቸው፡፡ እንግዲህ እኔም ክፍለሀገር እንደሚኖር ልጅ በአግባቡ ተጫውቼ፣ ነፍስ ካወቅኩም በኋላ አቅሜ በፈቀደ መጠን ቤተሰቤን በስራ እያገዝኩ ነው ያደግኩት፡፡
ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልሽ 10+2 በግብርና ከሆለታ ተመርቄ እዚያው ነበር ተመልሼ የተመደብኩት- ሸነካ የምትባል ቀበሌ፡፡ እዛ እየሰራሁ ታዲያ ህልሜ፣ መሆን የምፈልገው ነገር ምንድነው ብዬ ማሰብና ማሰላሰል ውስጥ የምገባባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ “በቃ የለምለም መጨረሻና ግቧ ሄዶ ነው?” ብዬ ከራሴ ጋር እሟገት ነበር፡፡ አንዳንድ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችም ነበሩ፡፡ በዚሁ መሃል ወንድሜ ተመርቆ አዲስ አበባ ገብቶ ስለነበር ተመካክረን ይዞኝ መጣ፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመግባት “COC“ አያስፈልግም ነበር፡፡ እንደገና ውጤቴም ጥሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ቀጥታ ወደ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ገባሁኝ፡፡
ቴአትርን ለመማር ያበቃሽ ገፊ ምክንያት ምን ነበር?
ዝንባሌ ነበረኝ፣ በት/ቤት በተለያዩ ክበባት እሳተፍ ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች ቴአትርን እንድመሰጥበት አደረጉኝ፡፡ አክት ማድረግ እወድ ነበር፡፡ ፊልም እናይ ነበር፤ የድሮዎቹን እነ አካፑልኮ ቤይ፣ እነ ማያና ሌሎችንም እናይ ነበር… ትዝ ካለሽ፡፡ እነዚህ ሁሉ እኔም ከተማርኩ አርቲስት መሆን እችላለሁ የሚል እምነት በውስጤ ስላደረ ቀጥታ መጥቼ ዩኒቨርስቲ ቴአትር አጥንቼ ተመርቄ ወጣሁ ማለት ነው፡፡
በት/ቤት ክበባት ውስጥ በነበረሽ ተሳትፎ ለቴአትር የነበረሽን ያህል ዝንባሌ ለሙዚቃስ ነበረሽ? ሙዚቃውን ከየት ተነስተሸ ነው እዚህ ከፍታ ላይ የደረስሽው?
ዘፋኝ ለመሆን ሀሳብም እቅድም አልነበረኝም፡፡ እኔ ሸነካ በግብርና ሙያዬ እየሰራሁ የኢትዮጵያ አይዶል ይተላለፍ ነበር። ጓደኞቼ “እንደዚህ ዓይነት የተሰጥኦ ውድድር አለ፤ ሄደሽ ብትወዳደሪ ጥሩ ነው” ይሉኝ ነበር።
በት/ቤት ከትወና በተጨማሪ ታንጎራጉሪ ነበር ማለት ነው? ጓደኞችሽ ይህን ምክር ከምን ተነስተው ሊሰጡሽ ቻሉ ብዬ ነው?
አዎ! በጣም አንጎራጉር ነበር። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝማሬ እዘምራለሁ፤ ተሰብስበን ቁጭ ስንልም የነ ጃምቦ ጆቴን፣ የነታደለ ገመቹን ኦሮምኛ ዘፈኖች ለጓደኞቼ እዘፍንላቸው ነበር። ተመድቤ የምሰራበት ቦታ (ሸነካ ማለት ነው) በአብዛኛው ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ቁጭ ስንል፣ ከገበሬዎቹ ጋር  ስንሆን፣ ጠራራ ፀሐዩን ዛፍ ስር ለማሳለፍ ቁጭ  ስንል እየዘፈንኩ አስቃቸው አዝናናቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የዘፈን ፍቅሩና ዝንባሌው አልነበረኝም፤ እውነት ለመናገር። ግግ ደግሞ እዚህ መጥቼ ቴአትር ስማር የአክቲንግ ኮርስ ማሟያ ላይ ቮካል ኤክሰርሳይስ እንሰራለን። በዚያን ጊዜ ረ/ፕ ሙሉጌታ ጀዋሬ ነበር አስተማሪዬ፤ እና “ለምን “ሙዚቃ አትሞክሪም እኔኮ ዘሪቱን ሆሊላንድ አስተምሬያታለሁ የሚገርም ድምፅ ነበራት ታስታውቅ ነበር” እያለ ይናገራል፡፡ እና ኦኬ አልኩ። አንዳንዴ አንቺ አልችለውም ወይም ፍላጎቴ አይደለም ብለሽ ትኩረት የነፈግሽው ነገር ላይ ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ፣ ያንንም ነገር ትኩረት እንድታደርጊበት ያደርግሻል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጣም የምወደውና የማደንቀው ተዋናይ አለማየሁ ታደሰ ሆሊላንድ ያስተምራልና አባቴም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲማር ዓለማየሁ ታደሰም ይማር ነበር። አባቴ አለማየሁን ይወደዋል፤ ስለሱ በጣም ይነግረኝ ነበር። ነፍሱን ይማርና ስለ ጋሽ ፍቃዱ ተክለማርያምና ስለሌሎቹም ትልልቅ ተዋንያን አባቴ ያጫውተኝ ነበር። በአጠቃላይ ቤተሰቦቼ ለአርት ቅርብ ናቸው። ይሄ ሁሉ ስላለ አለማየሁ ታደሰ የሚያስተምርበት ሆሊላንድ ገብቼ እማር ነበር። ሙሉጌታ ጀዋሬንም ሁለቱም ቦታ አገኘው ነበር። እነዘሪቱም እዚህ ተምረው ነውኮ የወጡት፣ እነ ግሩም ኤርሚያስ እዚህ ተምረው ነው እውቅ ተዋናይ የሆኑት እያልኩ ጎን ለጎን ደግሞ ሙዚቃ መሞከር ጀመርኩ። ሙከራዬ ጥሩ ነበር ግን በጣም አድካሚ ነበር፤ ልግፋበት የማልፈልግበት በርካታ ምክንያት ነበረ። ስቱዲዮ ሄደሽ ደጅ መጥናትና የመሳሰሉት በርካታ ችግሮች አሉት።
በተለይ አዲስ ሆነሽ ወደ ዘርፉ ለመቀላቀል ጉዞ ስትጀምሪ አሜኬላው ብዙ ነው አይደል….?
አዎ! በጣም እንጅ! ይህን ሙከራ ሳደርግ ድምጻዊ ደመረ ለገሰን አገኘሁት። ደመረ ያገሬ የአጋርፋ ልጅ ነው። አባቱ ለገሰ ተሰማን በጣም አውቃቸዋለሁ፡፡ የአጎቴ የቅርብ በጣም የቅርብ ጓደኛ ናቸው። ለደመረ የጀመርኩትን ሙከራ ስነግረው “አይዞሽ ቤተሰብ አይደለን… እንዴ” እያለ ያበረታታኝ ነበር። ብቻ እንደዚህ እያልኩ ቀጠልኩ። ነገር ግን ተምሬ ከወጣሁ በኋላ ከባድ ነበር።
እንዴት ማለት?
እኔ ልክ ተመርቄ  ቴአትር ቤት የምቀጠር ነበር የመሰለኝ። ግን ስራ ፈልጎ ማግኘቱ ከባድ ነበር። ቀጥታ ተዋናይት የምሆን ነበር የመሰለኝ፤ ግን ያ ባለመሆኑ ተስፋ ወደመቁረጥና ይቅርብኝ ወደ ማለት ሁሉ ሄድኩ። ምክንያቱም የኔ የሃይስኩል ጓደኞቼ ሌላ ትምርት ተምረው ደሞዝ እየተከፈላቸው ነው።  እነሱን ሳገኛቸው እኔ ገና አሁንም ስራ ፈላጊ ነኝ። እናም እንደማያዋጣኝ አምኜና ተስፋ ቆርጬ ማንኛውንም አይነት ስራ መፈለግ ጀመርኩኝ። ስራ ስፈልግ አስተማሪነት አገኘሁና ረዳት አስተማሪ ሆኜ ሂልቶፕስ ት/ቤት ተቀጠርኩኝ።
ምን ያህል ጊዜ በአስተማሪነት ሰራሽ?
ሂል ቶፕስ ት/ቤት ለጥቂት ወራት እንደሰራሁ አንድ ኦዲሽን ነበረ “ሀገር ማለት” ለሚባለው ቴአትር ማለት ነው። እዚያ ቴአትር ላይ ተሳተፍኩና በጣም የሥራ አጋጣሚዎችን ማግኘት ጀመርኩኝ። ከዚህ ውስጥ አንዱ “የኛ” ድራማ ላይ ኦዲሽን ነበር፡፡ “የኛ” ለሁለት ዓመት የሚቆይ የሬዲዮ ድራማ ነው የሚል ነገር ነበር የስሚ፤ ስሚ የሰማሁት። ድራማ ከሆነ የማውቀው ነገር ስለሆነ ልሞክር ብዬ “የኛ” ላይ ተወዳደርኩ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ “የኛ” ውስጥ ለሰባት ዓመት ቆየሁ። ከጋሽ በላይነህ አቡኔ ጋር “ሀገር ማለት”ን ለመስራት ወደ መቀሌ አብረን ሄደን ነበርና፣ ስለምንገባ ሀሳቤን ፍላጎቴን ስነግረው መረጃውን ሰጠኝ ሄጄ ኦዲሽን አደረግኩና አለፍኩኝ።
ያ ኦዲሽን ለለምለም እዚህ መድረስ ትልቅ መስፈንጠሪያ ሀይል ነበር ማለት ይቻላል?
አዎ በሚገባ! ከዚያ በኋላ ነውኮ ብዙ እድሎች እየመጡ እየሰራሁ የመጣሁት፡፡
በ”የኛ” ፕሮጀክት ውስጥ ከታቀፋችሁት አምስታችሁ መሃል ለየት ያለ የወንዳወንድ ገፀ ባህሪ ያለሽ ነበርሽ ወይም ሚሚ እንደዛ ነበረች። ለገፀ ባህሪዋ ለሚሚ ብለሽ ነው ያንን የወንዳወንድት ስታይል የተላበስሽው ወይስ ከልጅነትሽም ጀምሮ ወንዳወንድ ነበርሽ?
በጭራሽ! ሳድግ እንደ ሴት ልጅ ነው ያደግኩት፡፡ እርግጥ ሳድግ የወንድ የሚባሉ ስራዎችን እሰራ ነበር። ለምሳሌ ችቦ መስራት፣ ከጓደኞቼ ጋር እንጨት ማምጣትና የመሳሰሉትን፡፡ ታላቅ ወንድሜ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከአጋርፋ ወጥቶ ጎባ የሚባል ከተማ ነበር የተማረው። ከኔ በታች ታናሽ ወንድሜ ነው ያለው። ስለዚህ የወንድ የሚባሉትን ስራዎች እሰራ ነበር እጂ የወንዳወንድ ባህሪም አልነበረኝም።
“ሀገር ማለት” ቴአትርንም አይተሸ ከሆነ…. የተላበስኳት ገፀ ባህሪ ሴት ናት። የሚዋጣልኝም በሴትነቴ የምሰራው ነው። ከዛ ግን “የኛ” ላይ ስገባ ካስት የተደረግኩት ለሚሚ ነውና እዚያ ላይ ከ”የኛ” ውጪ የምንሰራው ስራ አልነበረም። በልዩነት የምንሰራው ለ”የኛ” ስለነበር ሁሌ ቀረፃ አለ ሁሌ ስራ ነው። ስለዚህ ሁሌ የሚሚን ገጸ ባህሪ ለማምጣት  ፀጉሬን ፍሪዝ ሳደርግ ፀጉሬ ተጎዳ። እንደዚህ ከሚሆን ለምን አልቆረጥም፣ ሁሌ የምሰራው ይህንኑ ነው ብዬ ተቆረጥኩ። ለኔ ጥሩ ነበር። ከዚያ እንደ ሴት ቀሚስ ለብሼ፣ ክፍት ጫማ አድርጌ ስተውነው አይመጣልኝም ነበር። እንግዲህ ሰባቱን ዓመት ገፀባህሪዋን ሆኜ ነው የኖርኩትም። ያኔ ባስ አይቀረኝ ባቡር እየተሳፈርኩ ዘና ብዬ ነው የኖርኩት።
በደንብ ተዋህዳሽ ነበርና ስራው ሲያልቀ ሚሚ በቀላሉ ከውስጥሽ ወጣች ወይስ አሁንም ብቅ ትልብሻለች?
ሚሚ ትንሽ ጫና ነበራት። ካራክተሯን ይዤ ቤት ስደርስ የምገባበት  አጋጣሚ  ብዙ ነበር። ወንድሞቼ ላይ ልክ እንደ ሚሚ ቆጣ የምልበትም ጊዜ ብዙ ነበር። ከዚያ ልጄን ስወልዳት እኔም አባቷም ጎፈሬ ሆነን ከምታየን ብለን ወደ ራሴ ተመለስኩ፡፡ ፕሮጀክቱም አለቀ። ታዲያ ወደራሴ ስመለስ  ከብዶኝ ነበረ። አሁንም አልፎ አልፎ የሆነ  ሰዓት  ላይ ቶኔን ቀየር ታደርገዋለች።  እርግጥ እንደ ገጸባህሪ ጥሩ ነበረች። በሚሚ ገፀ ባህሪ ሲተላለፍ የነበረው መልዕክት በጣም ቆንጆ ነበር። ወንዳወንድ ከመሆኗ አንፃር ሊተላለፍ የተፈለገው ነገር ጥሩ ነው። ሚሚ በዛ መልኩ ገጸ ባህሪዋ ሲገነባ በማህበረሰቡ አመለካከት ሴት ልጅ ወንዳወንድ ስትሆን ተፈሪ ትሆናለች የሚል ነው። ለምሳሌ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች በብርዱም በሚስቡት ቤንዚንም የተነሳ ድምፃቸው ጎርነን ያለ ነው። በዚህ ምክንያት እንደ ወንድ ይታዩና ከጥቃት ራሳቸውን ይከላከላሉ። ሚሚም ከዚህ አመለካከት በመነሳት የራሷ ላይ የለጠፈችው ስብዕና እንጂ እንደ ሚሚ አንዲት ምስኪን የገጠር ልጅ፣ ያለ እድሜዋ ተድራ ከዚያ አምልጣ የህይወት ፈተናን የተጋፈጠች ልጅ ናት- እንደምታስታውሽው። በቴአትር “Method Acting” የሚባል አለ። ይህ ማለት ገጸ ባህርያትን ወይም ስሜቶችን ተላብሰሻቸው
ትዋሃጃቸውና እያወጣሽ የምትጠቀሚያቸው አይነት የትወና ቴክኒክ- ነው ሜተድ አክቲንግ፡፡ እኛም ይሄን ስልጠና ወስደን ስለነበር፣ አሁንም ሚሚ ስታስፈልገኝ መዘዝ ብላ ተወጣች፡፡
ከ”የኛ” ፕሮጀክት ተጋሪዎችሽ  ከእነ ኪያ ራሄል፣ ጄሪና ዘቢባ ጋር ለሙያችሁ መጠናከርና ውጤታማነት የነበራችሁ የእርስ በርስ መደጋገፍ ምን ይመስል ነበር?
እኔ እንደነገርኩሽ ከክፍለ ሀገር አይደል የመጣሁት? ታዲያ ገና ከክፍለ ሀገር ስትመጪ ባይተዋርነት ይሰማሻል፡፡ ጓደኝነት ለመመስረትና የልቤ ሰው የምትይው ለማግኘት ይከብድሻል፡፡ በዩኒቨርስቲ የቴአትር ትምህርት ቤት እንደነዚህ አይነት ስሜቶችን አስተናግጃለሁ፡፡ አይናፋር ትሆኛለሽ፤ የሆነ ደባ እየተሰራብሽ እየተሴረብሽ ይመስልሻል…. ብቻ የሆነ ኮሽታ ይኖርሻል፡፡ ከነዚህ ጓደኞቼ ጋር በ”የኛ” ፕሮጀክት ገብተን ስራ ስንጀምር፣ አንዱን ሙሉ ዓመት ማለት ይቻላል ይበልጥ ጓደኝነቱ
ላይ የራስ ስብዕና ግንባታ ላይ ስልጠና ሲሰጠን ስለነበር የበለጠ ጓደኝነቱን አጥብቀን እንድንይዝ ተደርገን ነበር የተሰራብን። የውጤታማነታችንም ትልቁ ምስጢር ይሄው ይመስለናል። ጓደኝነታቸው ከሚሰማኝ ብቸኝነትና ባይተዋርነት ለመውጣት በደንብ አግዞኛል። ጓደኝነታችን ወደ ቤተሰብነት ተቀይሯል። ለምሳሌ ከአምስታችን አንዷ ጄሪ የልጄ ክርስትና እናት ነች። ተዛመድንም አይደል? ብቻ በጣም ጥሩ የጓደኝነት የቤተሰብነት ጊዜ አሳልፈናል አሁንም እንደዛው ቀጥለናል። ቀጥሎ ታዲያ ለምን አብራችሁ አትሰሩም የሚል ጥያቄ ታነሺ ይሆናል። ሁሉም ይህን ጥያቄ ስለሚያነሳው ነው። አብሮ መስራት ማቆማችን ብዙ ብዙ የራሱ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል። በዋናነት ግን እንደዚህ በቡድን። ሆነሽ ስትሰሪ አድካሚ ነው። የስሜት ሥራ ነው የምንሰራው ጥረት ይጠይቃል፣ ሰዓት ይጠይቃል፣ ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በዚህ መልኩ እኩል  ሀይል ላታወጪ ትችያለሽ። ብቻ ለስራው አመቺ ሁኔታ ጠፋ። ከዚያም እንደግሩፕ ሄደን ለመስራት መድረክ የማጣት ነገርም ፈተና እየሆነ መጣ። ይሄ ሁሉ ተደማሮ
በየፊናችን መሮጡን መረጥን፡፡ ምክንያቱም ኑሯችን ይሄው ዘርፍ ነው፤ ገቢያችን ከዚህ ነው፡፡ በተረፈ ግን ተሟልተን አምስታችንም ባንሆንም አብዛኞቻችን እንጠያየቃለን፤ እንደጋገፋለን፤ በክፉ በደግ የምንደራረስባቸው፤ የምንተጋገዝባቸው፤ የምንመካከርባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉን፡፡
ከጓደኞችሽ ጋር “አበባየሁሽ”፣ “ጣይቱና” የመሳሰሉት አይረሴ ስራዎችን ሰርታችኋል፡፡ በግል መስራት ከጀመራችሁ በኋላ “ገዳም”፣ “ላሊበላ” እና “በላ ልበልሃ” የተሰኙ ተወዳጅ ስራዎችን እነሆ በረከት ብለሽናል፡፡ ነገር ግን አልበምሽን ዘጠኝ ዓመት መጠበቅ ነበረብን? ምንድን ነው ነገሩ?
የአልበሙ ጉዞ እንዴት መሰለሽ ….የመጀመሪያዎቹን አምስት አመታት ከኤልያስ መልካ ጋር ነው የቆየሁት፡፡ ከኤሊያስ ጋር ይህን ያህል ጊዜ ስንቆይ ቀጥታ ወደ ስራው አይደለም የገባነው፡፡ ከኤሊያስ ጋር ስትሰሪ አልበም ብቻ ሳይሆን ሰርተሸ የምትወጪው፤ እራስሽንም ጭምር ነው፡፡ ኤልያስ እኔን የሚያውቀኝ “የኛ” ላይ ባለችው ሚሚነቴ ነው፡፡ እኔን ከሚሚ ወደ ለምለም ለመመለስ ብዙ ጊዜ ወስዶበታል።
ይቀጥላል…

“--መቼስ በክልሉ የታየው መከራ ከእኔ የመዘከር ችሎታ በላይ ነው፡፡ ጉድ እኮ ነው - የግድቡ እናት ወረዳ
የሆነችው ጉባ እራሷ ለስንት ዐመት ደም ፈሰሰባት፡፡ በስተመጨረሻ ከፍያለው አምዴ የሚባል እውነተኛ ወታደር
(ጄኔራል ነው) የቤኒሻንጉልን የመከራ ቀናት አሳጠረላት፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ የዚህን ሰው ስራ ፈልፍላችሁ
ብታውቁ ትህትና እና ተስፋ ይቀርቡዋችኋል፡፡--


እስቲ በህይወታችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ያያችሁትን የጉሙዝ ሰው አስታውሱ። ስሙ ማን ይባላል? የእኔው ግራኝ ጉደታ ይባላል። ያው እንደምታዩት ከስሙ ጉሙዝ መሆኑን ማወቅ የሚቻል አይደለም። ለነገሩ ይሄ የጉሙዝኛ ስም/ቃል ነው ብዬ የማስታውሰው አንድም ነገር ጭንቅላቴ ውስጥ የለም፤ ይህን ስል ከእፍረት ጋ ነው፡፡
ጋሽ ግራኝን ያገኘሁት የድሮ ቢሮዬ (ቦርዷ ዘንድ)  የፓርቲ  ጉዳይ ኖሮት  ነው፡፡ ይህ የሆነው ስራ በጀመርኩ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነበር።ታዲያ ይኼ ሰውዬ እንደ አንዳንዶቻችን፣ የእስር ቤት ደንበኛ ነው/ ነበር ማለት ይቻላል። (እንደ ጫማ ክር ሲፈቱት ሲያስሩት የኖረ....:) ለመጀመሪያ ጊዜ  ሳገኘው የነገረኝ ይኸንኑ ነው፤ ያው እንደለመደው ልቤን ሀዘን ወረረው::  በነገራችን ላይ ሰውየው አማርኛውን ይራቀቅበታል ነው የሚባለው::
በጣም ደናቂው ነገር ግን እስከ አሁን ያወራሁት  አይደለም። ዝንተዐለም በፖለቲካ ሲንገላታና ሲታሠር የምናውቀው ስጋ ለባሽ ሰው(ለሁለቱም ጾታ ያገለግላል) ነው አይደል) በእነ ጋሽ ጉደታ ጉዳይ ግን እነሱ በለውጥ የመጀመሪያ ቀናት ተፈተው፣ ሠው ሰራሽ ህልውና ባለው ፓርቲያቸው ላይ በፍ/ቤት የተሸጎረው የብረት መወርወሪያ  ተከርችሞ ቀረ። ድርጅቱ የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉ.ህ.ዴ.ን) በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ እንዲዘጋ ተወስኖበት ነበር፡፡
ፓርቲ ሲማር (ምህረት ሲደረግለት) ታውቃላችሁ? በህግም በልምድም የሚባል ነገር የለም። እና ባይኖርሳ ያለጥፋቱ ከስሞ ሊቀር ብዬ ለብርሀኑ ጸጋዬ ስልክ መታሁ፤ ያኔ የፍትህ ሚኒስትሩ እሱ ነበር። ቀጥታ ወደ ጥያቄዬ- “እባክህ ይህን ፓርቲ በምታደርገው ነገር አድርገህ በፕሬዚዳንቷ አስምረው።”  አልኩት፡፡ ብርሀኑ የመሠለውን ነገር እዳር ለማድረስ እጅግ ቀና፣ ተባባሪና ደፋር ሰው ነው። ከፍትህ መ/ቤቶች መንደር ያን አይነት ሰው ያለሱም አላየሁ። ካልመሠለው ደሞ እሱን ለማሳመን  መሞከር   ”ማገዶ ጨራሽ“ ተግባር ይባላል። እግዜር ይስጠው፤ በቀናት ውስጥ ለጉ.ህ.ዴ.ን  ይቅርታ እንደተደረገ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን፤ ፓርቲውም እንደገና ህልው ሆነ።
 ለማስታወስ ያህል ከአንድም ሁለት የይቅርታ ደብዳቤ ያለኝ ሰው ነኝ፤ በሌላ አባባል ሁለቴ ለወንጀሌ ይቅርታ ጠይቄአለሁ።  ሰውየው (የሴትየዋ ተቃራኒ ነው መሠል) ዝም ብለው ለፉ አይደል?! (ጋሽ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን ማለቴ ነው፤) መፈረም ራሱ አሠልቺ ነገር ነው። ነፍስ ይማር!!
ለማንኛውም የአቶ ግራኝና የጉ.ህ.ዴ.ን ታሪክ ማብቂያ የለውም። የምርጫውም ህግ ወጣና ቦርዱም ተሟላና “ፓርቲዎች ሠነድ አሟሉ፣ ፊርማ ጨምሩ፣ ጉባዔ አድርጉ” ወዘተ መባል መጣ። ደብዳቤ በደብዳቤ ላይ፣ እንደገና ሌላ ደብዳቤ፡፡ ጋሽ ግራኝና ፓርቲው ግን ምንም አልመለሱም። ጉ.ህ.ዴ.ን እንደገና ተጠረቀመች። ይህ ከሆነ ከአንድ ዐመት በኋላ ደርጉ (ስሙ ሁሌ ይገርመኛል) የሚባል የዛው  ፓርቲ  ወጣት ደውሎ ሁሉን ነገር ነገረኝ-አረዳኝ ብል ይሻላል። ለካ የክልሉ መንግስት ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ሰብስቦ እስር ቤት አጉሮአቸዋል። የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግስት በዚህ በዚህ በጣም ደፋር መንግስት ነው፡፡ አመንቴ የሚባለውን የቦሮ (ቦሮ የሺናሻ ማህበረሰብ ሌላ ስም ነው) ፓርቲ መሪ፣ መሳሪያ አንስቷል በሚል ጀምሮ ፓርቲውን ከመቀላቀሉ በፊት ዐቃቤ ህግ ሆኖ ሲሰራ  ሞስሷል በሚል፣ ለወራት ያከረመው ነገር የስንት ባለስልጣን  ፊት አሳይቶኛል፡፡ ተመስገን ነው መቼስ፤ ዛሬ አመንቴ የክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ ነው፡፡ የእ ነጋሽ ጉደታ ነገር ግን በደብዳቤም በደጅ ጥናትም  አልተሳካልኝም ነበር፡፡
መቼስ በክልሉ የታየው መከራ ከእኔ የመዘከር ችሎታ በላይ ነው፡፡ ጉድ እኮ ነው - የግድቡ እናት ወረዳ የሆነችው ጉባ እራሷ ለስንት ዐመት ደም ፈሰሰባት፡፡ በስተመጨረሻ ከፍያለው አምዴ የሚባል እውነተኛ ወታደር (ጄኔራል ነው) የቤኒሻንጉልን የመከራ ቀናት አሳጠረላት፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ  የዚህን ሰው ስራ ፈልፍላችሁ ብታውቁ ትህትና እና ተስፋ ይቀርቡዋችኋል፡፡ (It is just recommendation) እኔ የማውቀውን ያህል በአጭሩ ልንግራችሁ፡፡ ካጎደልኩ ካሳሳትኩ ማነው ማነች ሳይል፣ ሁሌም እውነቱን የሚናገረው የቦሮ ፓርቲ ልጅ ዮሀንስ ተሰማ  ያርመኛል፡፡
ወንድሜ ከፍያለው (ከጄኔራልነት ወንድምነት ይበልጣል ብዬ ነው) የኮማንድ ፖስቱ ሀላፊ ሆኖ እንደተመደበ የክልሉን መንግስት ጎትጉቶ ጋሽ ጉደታ እና ሌሎች በርካታ እስረኞችን አስፈታ፡፡ ከዛ እንግዲህ አብረው ያልዋሉበት ቀበሌ ያልሰበሰቡት  ስብሰባ የለም፡፡ የተስፋ ምክንያት ሁኚ ሲላት መሰለኝ፣ ቤኒሻንጉል የ Chronic Violence ( የማይድን አመጻ) ተምሳሌት እንዳልተባለች፣ ዛሬ  ጉምዝ፣ ሰው ከጫካ ወደ መኖሪያ ሠፈሩ ተመልሷል (ያልታጠቁትን ማለቴ ነው)፡፡ ታጣቂዎቹም ካምፕ ገቡ፤ በአሶሳ ዞንም ለቤ.ህ.ነ.ን እና ለበርታ ማህበረሰብ ተመሳሳዩ ተደረገ፡፡ አማራ ፣ ሺናሻ፣ አገው፣ ከምባታ እና የሌሎችም ማህበረሰቦች አባላት በመሆናቸው  በጉሙዝ ታጣቂዎች ተፈናቅለው ቻግኒ፣ ቡለን፣ ድባጤ ፣ፓዊ እና ግልገል በለስ የተባሉ የወረዳ ከተሞች ላይ  ተጠልለው ከነበሩት ብዙዎቹ ወደ መንደራቸው ተመልሰዋል፡፡ የህዝብ ትራንስፖርትም ከተቋረጠ በስንት አመቱ  ጀመረ፡፡
ጋሽ ከፍያለው ንግግር አዋቂ የሚሉት አይነት  አይደለም፡፡ ፊትለፊት ተገናኝተን ሰለማናውቅ አጭር ይሁን ረጅም አላውቅም፡፡ በስልክ ግን ለሰዓታት አውርተናል፤ አዳምጬዋለሁ ብል ይቀላል፡፡ እኔ እራሴን እንደ ታጋሽ አልቆጥርም፡፡ በተለይ ብስ ( Bullshiting) ከቁጥጥሬ ውጭ ያስወጣኛል፤ እንዲያ ያለውን ወሬ  አሳምሬ አቋርጣለሁ፡፡ ገራገሩና እውነተኛውን ጋሽ ከፍያለውን ግን  ያለመታከት አዳምደጫለሁ፡፡ የሚያወራው ነገር ሁሌም  ይነሽጠኛል፤ ያስተምረኛል (ውትድርና፣ ቅንነት፣ ግጭት  አፈታት……..ወዘተ)፡፡ ከ30 ደቂቃ በታች አውርተን አናውቅም፤ ሊያውም በቀጥታ ስልክ፡፡ ለምን ብለን ዋትስአፕ) ስለሁሉም አይነት ፖለቲከኞች እውነት እውነቱን ይናገራል፡፡ ሁለታችንም ዮሀንስንና በቤኒሻንጉል የተሻለ ቀን ለማየት ደፋ ቀን የሚሉትን ሰዎች እናደንቃለን፡፡ በ2013 መጀመሪያ አካባቢ ዮሐንስን እዚሁ አዲስ አበባ፣ የቤኒሻንጉል ፖሊሶች ሲያሳድዱት እንዳያስሩት፣ በመኪናዬ ሸሽጌ ወደሚሄድበት ይዤው ሄጄ፣   አውቃለሁ፡፡ ጋሽ ከፍያለው ግን ከሞት ሳይከለልለው አይቀርም፡፡
 የዮሐንስና መሰሎቹን ታሪክ ለሌላ ቀን ላቆየውና ዛሬ ወደ ቤኒሻንጉል ዥንጉርጉር ትዝታዎቼ ወዳመጣኝ ሰው ልምጣ- አስቻለው ፈጠነ፡፡ በቃላትና ዜማ ስለሚጠበብ  ሰው፣ ደስታን ብቻ ሳይሆን የጋራ እንጉርጉሮን (collective lamentation) ምን የመሰለ ውበት አድርጎ ስላቀረበ ሰው መናገርን የመሰለ አወላካፊ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡  የአስቻለውን ዘፈኖች በጆሮዬ ሳሆን በሆዴ የምሰማው ነው የሚመስለኝ.፤  ደግሜ ደግሜ ያልሰማሁት  ዘፈኑ ባይኖርም፣  ከመጠሪያ ስሙ ገፋ ሲልም ታጣቂዎቹ ስለፈጠሩት ግጭት ከሚወራው በስተቀር ትንሽ በሚታወቅለት የጉሙዝን ቋንቋ ከአገውኛና አማርኛ ጋር ቀላቅሎ ስለ አዲስ አበባ እንደዘፈነበት «ዊያ ዊያ ´ የወደድኩት የለም፡፡
በዘፈኑ ውስጥ አፍቃሪው ጽጌረዳን ልውሰድሽ ኳስ ሜዳ ይላታል፡፡ የሼህ ሆጀሌ ጥንታዊ ቤተመንግስት ለሚገኝበት ጉለሌ ቅርብ ወደ ሆነው ሜዳ መሰለኝ፡፡ ወይም እኔ ቅርሱ የሚገኝበትን ስላለበት ሁኔታ ለመናገር ፈልጌ አጠጋጋሁት፡፡ ይሄ ማህልና ዳር አገናኝ የሆነን  ቅርስ አርጅቶ  የንጉስ ሆጀሌ ቤተሰቦች ብቻ ሊያስጠግኑት ከላይ ታች ሲሉ በማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡
አስቻለው ከአመታት በፊት ስለሰራው የጉምዝኛ ስራ ቪዲዮ  ግን በስድ ንባብ ከምፅፍ በተገጣጠሙ ቃላት አስቻለውን ልጠይቀው ወደድኩ::
እስቲ ንገረኝ አስቻለ
እንዴት ወዴት ሆነኸው ነው
ወዝህ ወዛቸውን የነሳው?
ከውስጥ ያወጡትን ቱም ቱምታ
የጅማታቸውን ትርትርታ
የረገጣቸውን ሆታ
የዜማቸውን ፈለግ
የኑሯቸውን ቆንጅዬ ወግ
እንዴት ብለህ ተጣባኸው?
በየት በኩል እንዴት ሆነህ
ምኑን ቀምሰህ ምኑን ምሠህ
ያንን ግርሻን ተጣላኸው?
እስኪ አሳየኝ
እንዴት አርገህ
ወንድምህን ለብሰህ  ሆንከው!?
 ጉባ፣ ማንዱራ፣ ፓዌ፣ ድባጤ፣ አሶሳ፣ ካማሺ፣ ቻግኒ፣ ቡለን ኮንሰርትህን አቅርበህ እዛው መገኘት - ለራሴ የተመኘሁት ምኞት!!


በኢትዮጵያ ለሚገኘው የፋይናንስ ዘርፍ አጠቃላይ የመረጃና  ምልከታ ያለምንም ከፍያ የሚሰጥ  የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፕላትፎርም ተከፈተ።
ፕላትፎርሙ የተጠቃሚዎችን  አቅም በማሳደግ  በኢትዮጵያ የፋይናንስ  ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተቀናጀ ሚዲያ፣ መረጃ አቅርቦትና ትንተና እንዲሁም ማማከር አገልግሎት ላይ በተሰማራው  ሸጋ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት  የበለፀገው ፕላትፎርም፤  በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ ሰዎች ያላቸውን መተማመን በመገንባት፣ የፋይናንስ ተካታችነትን ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሏል።
ከፍተኛ  የመንግሥት  የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ውስጥና ዓለም እቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት  በተከናወነው የፕላትፎርሙ ማብሰሪያ ሥነ ሥርዐት ላይ  እንደተገለጸው፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማዕከል መከፈት በተሻለ መጠን መረጃ መር ውሳኔ ሰጪነትን ለማቀላጠፍ፣ እንዲሁም በገጠርና አገልግሎቱ ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች የፋይናንስ ተካታችነትን በጥልቀት ለመደገፍ  ያስችላል ተብሏል።
ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂንና ጥራቱን የጠበቀ መረጃና ይዘትን በመጠቀም፣ ፕላትፎርሙ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን የምናይበትንና የምንጠቀምበትን መንገድ እንደ አዲስ ለማቅረብ ቆርጦ የተነሣ  እንደሆነም ተገልጿል።
የሸጋ ኢንሳይትስ (Shega Insights) ማናጀር የሆኑት አቶ ናትናኤል ጸጋው፣ “የፋይናንስ ተደራሽነትና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲለመዱ ለማገዝ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ የሆነውን ይህንን ፕላትፎርም ይዘን በመምጣታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል” ሲሉ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ተናግረዋል። በተጨማሪም፣ ይህ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ፕላትፎርም፣ ያለሟቋረጥ የሚለዋወጠውን የዲጂታል ፋይናንስ ዓለም ተጠቃሚዎች ያለ ስጋት እንዲዳስሱና እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው በማለት ገልጸዋል።
የአዲሱ ፕላትፎርም ዋንኛ  አላማ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምልከታዎች: በድርጅቱ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ኦርጂናል አጫጭር ጽሑፎች፡ የተዛማጅ ነባራዊ ሁኔታ ጥናቶች (case studies) እንዲሁም ሪፖርቶችን በማቅረብና ዘርፉ ውስጥ ለሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት የአገሪቱን ሁኔታ ያገናዘቡ መረጃዎችን  በመስጠት የኢትዮጵያን ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በውል እንዲረዱ ማስቻል   ሲሆን  ፕላትፎርሙ   ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውና የተመረጡ የዜና ዘገባዎችን፣ ሪፖርቶችን፡ ምዘናዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን የሚያብራሩ ልዩ ልዩ ግብዓቶችን አጠቃልሎ የያዘ በቀላሉ ተደራሽ የሆነ የመረጃ ምንጭ እንደሆነም ተገልጿል ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በ2025 እ.ኤ.አ ከአገሪቱ አዋቂ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሕዝብ 70 ከመቶው የፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ተካታች እንዲሆን፣ እንዲሁም ከፍያዎችን ለመፈጸምና ለመገበያየት ዲጂታል አካውንት አዘውትሮ እንዲጠቀም ግብ ሰንቋል። ለዚህ ግብ መሳካት ይህ ፕሮጀክት  ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አገሪቱ ከግጭትና ቀውስ አዙሪት አልወጣችም ብሏል
· መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻለም ይላል
· ጠንካራ ተፎካካሪዎች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት በዝቷል


ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፤ የተመሰረተበትን የአምስተኛ አመት በዓል በተለያዩ ኹነቶች ሲያከብር መሰንበቱን ገልጿል፡፡ ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግም የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፤ የፓርቲውን የአምስት አመት አጠቃላይ ጉዞ፣ ስኬቶቹን፣ ተግዳሮቶቹንና ውስንነቶቹን በመገምገም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይቷል ተብሏል፡፡

ነእፓ- የዛሬ 5 ዓመት?!
“ከዛሬ አምስት አመት በፊት ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሲመሰረት፣ ግዙፍ ራእይና ተልእኮ ሰንቀን፣ በርካታ ዓላማዎችንና ግቦችን ከፊታችን አስቀምጠን፣ በከፍተኛ የሀገር ፍቅርና በጋለ የስራ ስሜት ነበር፣” ይላል-ፓርቲው በመግለጫው፡፡ ወደ ኋላ አምስት ዓመት መለስ ብሎም ዕቅዶቹን፣ ራዕዩን፣ ግቦቹን፣-- ያስታውሳል - ፓርቲው፡፡
“ነእፓ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ሲመሰረት መላ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ዋጋ የከፈሉለት እንዲሁም በታላቅ ተስፋና ጉጉት የተቀበሉት “የፖለቲካ ሪፎርም” ዳር እንዲደርስ የበኩላችንን ለማበርከት ቃል ገብተን ነበር፣
“የዛሬ አምስት አመት ነእፓን ህያው ስናደርግ ሀገራችንን ወደተሻለ ማህበረ-ኢኮኖሚ የእድገት ደረጃ ለማስፈንጠር፣ ጠንካራ ዴሞክራሲ፣ የፖለቲካ መረጋጋትና ሰላም የሰፈነባት፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ የተረጋገጡባት ሀገር ለመመስረት ተስፋ ሰንቀን ነበር፣
“የነፃነትና የእኩልነት መንገዳችንን አሀዱ ብለን ስንጀምር የተራራቁትን አቀራርበን፣ የተጣሉት አስታርቀን፣ የተለያዩትን አንድ አድርገን፣ በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሰፍን አልመን ነበር፣
“የነእፓን ጉዞ አንድ ብለን ስንጀምር ድህነትና ኋላ ቀርነት፣ ድርቅና ርሀብ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት መገለጫዋ የሆነችውን ሀገራችንን ከተዘፈቀችበት አዙሪት ለማላቀቅና፣ የወገናችንን የተሰበረ ልብ ልንጠግን ቃል ገብተን ነበር፣
“ነእፓ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ሲቀላቀል ሚዛናዊነት፣ ምክንያታዊነት፣ አብሮ ማሸነፍ፣ ከሴራና ከጥሎ ማለፍ ፖለቲካ መራቅ የትግላችን አልፋና ኦሜጋ እንዲሆኑ፣ ግልጽ ዓላማዎችና ስልቶች ነድፈን ነበር፡፡
“በጉዟችን መነሻ ላይ የቀን ጉርስ፣ የአመት ልብስ እንደ ሰማይ የራቃቸውን የድሀ ድሀ ዜጎቻችንን ቢያንስ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ ትምህርትና ጤና የመሰሉ ለአንድ ሰብአዊ ፍጡር የሚገቡ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለሁሉም ዜጎቻችን እንዲሟሉ የበኩላችንን ለማበርከት በከፍተኛ ቁጭትና ህዝብን የማገልገል ፍላጎት ነበር፡፡” የሚለው ፓርቲው፤ ሁሉም ነገር በምኞት የቀረበት ይመስላል፡፡
አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች
ነእፓ በመግለጫው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት አስቸጋሪ በሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችና የፖለቲካ ምህዳር ውስጥም ሆኖ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደቻለ፣ አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችንም ማስመዝገቡን ጠቁሟል። ፓርቲው፤ ፈጸምኳቸው ከሚላቸው ስራዎቹና ስኬቶቹ ጥቂቶቹን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡
“ከጅምሩ “ፓርቲ እጩ መንግስት ነው” የሚል ጠንካራ እምነት አንግበን፣ መንግስት ለመሆን ከሚያስፈልጉን ጉዳዮች መካከል በርካታ የፖሊሲ ሰነዶችን አዘጋጅተናል፡፡ ባለፉት አምስት አመታት ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጥናት ላይ የተመሰረቱ አማራጭ ሀሳቦችን አመንጭተናል፡፡ ለሀገርና ለህዝብ አይጠቅሙም ያልናቸውን የመንግስት ፖሊሲዎችና አሰራሮች እንዲወገዱ ሞግተናል፣
“ባለፉት አምስት ዓመታት የነእፖ የትግል ስልቶች ማለትም ሚዛናዊነት፣ ምክንያታዊነትና አብሮ ማሸነፍ በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ እንዲሰርጹ ጥረት አድርገናል፡፡ በእኒህ ዓመታት ሚዛናዊነትንና ምክንያታዊነትን መርህ አድርገን ባሰናዳናቸው ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣናቸው የአቋም መግለጫዎች፣ ባዘጋጀናቸው ሁነቶችና የውይይት መድረኮች የተካረረው የሀገራችን ፖለቲካ እንዲለዝብ፣ ዋልታ ረገጥ የፖለቲካ ባህላችን ወደ መሀል እንዲመጣ አዎንታዊ ሚና ተጫውተናል፡፡
“የብሄራዊ መግባባት አጀንዳ ከቃል አልፎ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር በጉልህ የሚታይ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡ እጅግ ግዙፍ የሆነው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ በመንግስት ተወስዶ መተግበር ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ፣ ሂደቱ እንዳይበላሽ፣ እንዳይጠለፍና የመንግስትና የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ታሪካዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት አድርገናል፣ “የሰሜኑ የሀገራችን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ይፈታ ዘንድ የጦርነትን አስከፊነትና የሰላምና ጥቅም አጉልተን ስለ ሰላም ሰብከናል፡፡ የጦርነት ጥሩ፣ የሰላም መጥፎ የለውም ብለን ከሰላም ጎን ቆመናል፡፡ ጦርነት ይቁም ማለት ዋጋ በሚያስከፍልበት፣ ስለ ሰላም መናገር ነውር በሆነበት በዚያ አስጨናቂ ወቅት ሰላምን ሰብከናል፣
 “ገዢው ፓርቲና መንግስት ስህተት ሰርተዋል ብለን ስናምን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ተቃውመናል፡፡ ጠንካራና በመርህ የሚመራ ተቃዋሚ ለመሆን ለሀገርና ለህዝብ የገባነውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ታትረናል፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲ ኃላፊነታችንን ከጭፍን ተቃዋሚነትና “ስህተት ፈላጊነት” እንዲሁም መርህ አልባ የገዥ ፓርቲ ደጋፊነት ነጻ ሆነን ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም የቆመ እውነተኛና ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል፣
“የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ፓርቲና መንግስት እንዲለያዩ አጥብቀን ሞግተናል፣ የሀገራችን እድገት ነቀርሳ የሆነው ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች እንዲቆሙ፣ የመንግስት ሹማምንት በስልጣናቸው ሲባልጉ ሽንጣችንን ገትረን ሞግተናል፡፡ በሀገር ሰላምና በዜጎች ደህንነት ላይ በደረሱ ጥቃቶች የህዝብ ድምጽ ሆነን ድምጻችንን አሰምተናል፣
 “መንግስት ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ምቹ የህግ ማእቀፍና በቂ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ለረዥም ዘመናት በገነገነው ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስርአት፣ ዛሬም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ እንቅፋቶችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በሀገራችን ማየት የምንፈልገው ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ይወለድ ዘንድ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የሚደረጉ ልዩ ልዩ ጫናዎች እንዲቆሙና  ምቹ ምህዳር ለመፍጠር የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ አጥብቀን እናሳስባለን፣
“የልማት የመጨረሻ ግብ የዜጎችን ህይወት ምቹና ደስተኛ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት በልማት ስም የሚያካሂዷቸው ፕሮጀክቶች የዜጎችን ህይወትና ደህንነት ታሳቢ ያደረጉ፣ በቂ ጥናት የተደረገባቸው፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ውይይትና መግባባት የተደረሰባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት አመታት መንግስት በልማት ስም የሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች፣ ዜጎችን ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ሲዳርጉ ተስተውሏል፡፡ በመሆኑም መንግስት የሚፈጽማቸውን ፕሮጀክቶች በግልጽነትና ኃላፊነት ስሜት እንዲያካሂድ፣ በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችል ማበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለማስወገድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እናሳስባለን፣
ሀገራችን ካለችበት የግጭትና የጦርነተ አዙሪት ትላቀቅ ዘንድ ብሄራዊ መግባባት ብቸኛውና ምትክ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ መላው የሀገራችን ህዝቦችና የፖለቲካ ኃይሎች ያምናሉ፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሀገራዊ መግባባት እውን ይሆን ዘንድ ከፓርቲው ምስረታ ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁትን ሀገራዊ ምክክር ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት የአገራዊ ኮሚሽን ማቋቋሙና ይኸው ኮሚሽን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በአንጻሩ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከጽንሱ ጀምሮ የግልጽነትና የአሳታፊነት ችግር አለበት በሚል በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች ከሂደቱ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሀገራዊ ምክክር መሰረቱና የመጨረሻ ግቡ በቁልፍ የፖለቲካ ተዋናዩች መካከል መተማመንን መፍጠር ነው ብሎ የሚያምን ሲሆን፣ መተማመን የሌለበት ሀገራዊ ምክክር ውጤቱ ጊዜና ገንዘብ ከማባከን ያለፈ እንደማይሆን ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም የሀገራዊ ምክክር ይሳካ ዘንድ መንግስትና የምክር ኮሚሽኑ ሂደቱን ግልጽ፣ አሳታፊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲመሩት እያሳሰብን፣ በተመሳሳይ የፖለቲካ ኃይሎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካት ሀገራችን ካለችበት ውስብስብ ችግር ትወጣ ዘንድ ብቸኛው አማራጭ “ምክክር” መሆኑን በመረዳት፣ ለሂደቱ መሳካት የቡኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፣
“ከዛሬ ስድስት አመት በፊት የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም፣ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ያደረጓቸውና ለረዥም ጊዜ ሲመኟቸው የኖሩ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ማበራዊ ፍትህ፣ ሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ያገኙ ዘንድ ገዢው ፓርቲና መንግስት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን፣
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ በአጎራባች ክልሎች መካከል የሚፈጠሩ የወሰንና የማንነት ግጭቶች ይገኙበታል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሁለት አመት የተካሄው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እልባት ቢያገንም፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች አሁንም ውጥረት እንደነገሰባቸው ናቸው፡፡
 በአፋርና በሱማሌ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች በሚፈጠር ግጭት የበርካታ ወገኖቻችን ደም እየፈሰሰ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ በሌሎች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በወሰንና በማንነት ጉዳዮች በሚፈጠር ጉዳት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡ የወሰንና የማንነት ጉዮችን ለመፍታት ከአመታት በፊት ተቋቁሞ የነበረውና ሰፊ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው “የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን” የሚጨበጥ ስራ ሳይሰራ በመፍረሱ ችግፎቹ ዛሬም ቀጥለዋል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል መንግስትና የክልል መስተዳድር አካላት፣ በወሰን ምክንያት በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችና በዚህ ምክንያት የሚፈሰውን የዜጎች ደምና የሚወድመውን የሀገር ሀብት ለመታደግ አስፈላጊውን እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፣
 “ሀገራችን ለገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የእርስ በእርስ ጦርነት በአፋጣኝ ይቆም ዘንድ መንግስትም ሆነ ነፍጥ አንግበው የሚታገሉ ኃይሎች ለሰላም ቅድሚ እንዲሰጡ እያሳሰብን፣ ሀገራችን ካለችበት የቀውስ አዙሪት በአጭር ጊዜ ተላቃ ሰላም፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ የሰፈነባት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የተረጋገጠባት ሀገር ትሆን ዘንድ መላው የሃገራችን ህዝቦችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡”
እንግዲህ የ5 ዓመት ለጋ ዕድሜ ብቻ ያለው ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ሃገሪቱ የወጣችውን የወረደችውን፣ ህዝቧ የገጠመውን ያሳለፈውን -- መከራና ውጣ ውረድ፤ ግጭትና ጦርነት፤ ሞትና ሰቆቃ፣ ድህነትና እጦት ከሞላ ጎደል በመግለጫው አካቶታል፡፡ ራሱ ፓርቲው ያበረከተው አስተዋጽኦና አሉታዊ ተጽዕኖ ምን እንደሆነ ለማወቅ ግን መጠነኛ ጥናትና ፍተሻ ይፈልጋል፡፡ ወደፊት እንመለስበት ይሆናል፡፡



በተባበሩት መንግስታት፣ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ)፤ በኢትዮጵያ 8.8 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምሕርት ገበታ ውጭ ሆናቸውን አስታውቋል። ድርጅቱ ባለፈው ሰኞ ባወጣው የሩብ ዓመት ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ከትምሕርት ገበታ ውጭ የሆኑ ሕጻናት ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል።
በዩኒሴፍ የሩብ ዓመት ሪፖርት መሰረት፤ወደ 3 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሕጻናት የትምህርት ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም፣ ካለፈው ዓመት አጋማሽ አንስቶ ከትምህርት ውጭ የሆኑ ሕጻናት ቁጥር በከፍተኛ መጠን መደጉ ተመልክቷል፡፡
ባለፈው መጋቢት ወር ፣ 156 ሺ ያህል ሕጻናት ብቻ የድንገተኛ የትምህርት ድጋፍ እንዳገኙ የሚያትተው ሪፖርቱ፤ ለ ግሩመንስኤ ናቸው ያላቸውን ክስተቶች ዘርዝሯል። በስድስት ክልሎች የበልግ ወቅት ዝናብን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ 8.8 ሚ. ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ተገለጸ የተከሰቱ የጎርፍና በሰባት ክልሎች ያጋጠሙ የድርቅ አደጋዎች ለችግሩ መንስዔ እንደሆኑ
ተጠቁሟል፡፡ በፈረንጆቹ 2024 ዓ.ም የመጀመሪያ ሦስት ወራት ውስጥ የትምህርት መሰረተ ልማቶች ውድመት የ4 . 5 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘጉ ት/ ቤቶች ብዛት በ18 በመቶ ማደጉን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡በዚህ ሩብ ዓመት 21 ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቀውስ ለተጠቁ አካባቢዎች ድንገተኛ የትምህርት ድጋፍ ቢያደርጉም፣ ተጨማሪ
የድጋፍ ዓይነቶችና የሰብዓዊ ዕርዳታ እቅርቦት ከሌለ፣ አስከፊ ሁኔታ እየተፈጠረ ችግሩን ሊያሰፋው እንደሚችል ዩኒሴፍ ስጋቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ 10 ሚሊዮን ያህል ሕጻናት የትምህ ርት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውየዩኒሴፍ መረጃ ያሳያል።

በቀጣዮቹ 10 ቀናት ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል


ከመጪው ሰኔ  ወር እስከ መስከረም በሚዘልቀው የክረምት ወቅት መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ ስለሚኖርና አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አሳስቧል።  የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ፤ በቀጣዮቹ 10 ቀናት ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ በተደጋጋሚ በሚመታው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና፣ በመጪዎቹ ወራት ከመደበኛው መጠን ከፍ ያለ ዝናብ ሊጥል እንደሚችል የገለጸው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፤ ማዕከላዊና ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ አብዛኛው ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ በሱዳንና በኬንያ ጠረፎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአንጻሩ ምዕራብ ኢትዮጵያና ሰሜን ምስራቅ ደቡብ ሱዳን ከመደበኛው ከፍ ያለ ደረቅ የአየር ንብረትን የሚያስተናግድ መሆኑን ገልጿል። ክረምቱ ኢትዮጵያና ኤርትራን በመሳሰሉ ሀገራት ቀደም ብሎ መታየት ሲጀምር፣ በጅቡቲ እንዲሁም በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ዘግየት ብሎ እንደሚጀምር ኢጋድ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው መረጃ፤  በቀጣዮቹ አሥር ቀናት ሰፊ ቦታዎችን ያካተተና የተጠናከረ ዝናብ እንደሚኖር አመላክቷል። በዚህም በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና፤ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ ከመደበኛው ከፍለ ያለ ዝናብ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።  በተመሳሳይ  በአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብና ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም አዊ ዞኖችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ከፍ ያለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

Page 2 of 708