Monday, 14 August 2023 20:01

የገዢው ፓርቲ ፖለቲከኞች ምነው ተረጋጉሳ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

እስከ ዛሬስ ምን ነክቷቸው ነው ለንግግራቸውና ለተግባራቸው ሳይጠነቀቁ፣ ብሽሽቅና ምስቅልቅል ሲፈጥሩ የነበሩት?
ብዙ ሰው፣ በፖለቲካ ተንገሸገሸ፡፡ አየው፤ አየው፡፡ ከዓመት ዓመት ምን አመጣለት? ጥፋት ነው የበዛበት፡፡ እንደ መርዛማ እንደ አደገኛ ነገር፣ ፖለቲካም “ልጆች የማይደርሱበት ቦታ ተዘግቶበት ቢቀመጥ ይሻላል” ያስብላል የአገራችን ሁኔታ፡፡
ብዙ ሰው “አገርና ህይወት ላይ የፖለቲካ ድራማ ከመስራት፣ የቲቪ ድራማ ይሻላል” ብሎ ከፖለቲካ እየራቀ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል? እንደገና ጦርነት መጣበት፡፡
ሦስት ዓመት በተከታታይ በጦርነት የጨለመ የእንቁጣጣሽ በዓል? ያሳዝናል፡፡ ግን የባሰም ሞልቷል፡፡ የእልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን ህይወት ረግፏል፡፡
እርግማን ነው? አይቀሬ ዕጣፈንታ ነው?  ሁኔታችን ሲታይ፣ ጦርነትን እንደ እርግማን በአቅመ-ቢስነት አሜን ብለን የተቀበልን ይመስላል፡፡ ተስፋ ብንቆርጥ አይረግምም፡፡ ጦርነትን የሚያስቀርልንና ውጤት የሚያመጣልን የመፍትሔ ሐሳብ ሰምተን አናውቀም።
 ጦርነት እየደጋገመ የሚመጣብን ለምን እንደሆነ ምክንያቱን ባናውቅም እንኳ፣ ለማወቅ ሞክረናል ወይ?
ብንሞክርማ፣ ጥያቄያችንን እናስተካክል ነበር። ጦርነት መላልሶ እየመጣብን ነው ወይስ መላልሰን እያመጣነው ደጋግመን እየጠራነው?
መቼም እየደጋገምን የሰራነው ስህተት እየመላለስን የፈጸምነው ስህተት ቢኖር ነው ጦርነትንና መከራን ያዘወተርነው፡፡ ምን ይሆኑ የዘወትር ስህተቶቻችን? ጦነትን ማስቀረት ያቃተን ለምንድነው? የችግራችንን የመከራችንን መንስኤ ካወቅን ለመፍትሔው ይረዳናል። ግን ምን ዋጋ አለው?
 ጎራ እየለዩ እንዲሁ በጭፍን ከመወንጀል በቀር፣ ስለጦርነቶቹ መንስኤ በቅጡ የመመርመርና የማገገናዘብ ጥረት ብዙም አይታይም፡፡
ጦርነት በራሱ ጊዜ ወደ መፍትሄ ያደርሰን ይሆናል የሚለው ሃሳብም የዋህ ምኞት ወይም ክፉ ስሜት ከመሆን አላለፈም፡፡ ስለመንስኤውም ስለ መፍትሄውም ማሰብ ዋጋ የለውም ብለው ተስፋ የቆረጡ ዜጎች፣ በፖለቲካ ድራማ መሰላቸታቸው ይገርማል?
እሺ፣ የጦርነቶችን መንስኤ ማወቅ አቅቶናል እንበል፡፡ መፍትሄውም አልታየንም እንበል፡፡
ግን በየፊናችን የጦርነት ሰበብ ላለመፍጠር መሞከር አንችልም ወይ? የገዢውን ፓርቲ ባህርይ ተመልከቱ።
 በርካታ የፓርቲው ባለስልጣናትና አውራ ፖለቲከኞች በንግግርና በተግባር አዳዲስ የብሽሽቅና የስድብ፣ የኑሮና የስራ ምስቅልቅል የሚያስከትሉ ሰበቦችን በየእለቱ ሲፈጥሩ አገሬውን ፋታ ሲያሳጡ ትዝ ይላችኋል፡፡
ይሄ ፓርቲ፣ ራሱን አባላት የመቆጣጠር ዓቅም የለውም ወይ? ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነውበታል ወይ? መያዣ መጨበጫ ቢያጣ እንጂ እንዴት የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ራሳቸው አገር እንዳይረጋጋ በየቀኑ ተግተው ይዘምታሉ?
እነዚህን ጥያቄዎች በስጋት ስሜት የሚያነሱ ዜጎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከቀበሌና ከወረዳ፣ እስከ ክልልና እስከ ፊደራል… በየቦታው እንደ አዲስ እንደ አሸን የፈላው ሙስና፣…. መደበኛ ክፍያና መደበኛ አሰራር እስኪመስል ድረስ በግላጭ እያፈጠጠ የተዛመተው የጉቦ ቅብብሎሽ     ሲታይ በእርግጥም ያሳስባል፡፡ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነበት ነው? ብለን እናስባለን በስጋት፡፡
በድንገት የሚመጡ የንግድ መሰናክሎችና ክልከላዎች፣ በማግስቱ ድንገት የሚለወጡ የኮታ ገደቦችና በዘፈቀደ ተዘርግተው የሚያድሩ ኬላዎች፣ እንደገና በሣስቱ በሌላ መመሪያ ተሽረው፣ በአዳዲስ አጥሮችና በአደናቃፊ ቁጥጥሮች ተተክተው ሲመጡ፤ ምን እንበል?
ነገሩ ሁሉ ከመንግስት እጅ እያመለጠ፣ ገዢው ፓርቲ እየተበጣጠሰ ይሆን? ብለው በርካታ ዜጎች ቢያስቡ አይገርምም።
በኑሮ ችግር ላይ ተጨማሪ መከራ ማምጣት፣ በዘመቻ መኖሪያ ቤቶችን ማፍረስና ዜጎችን ማፈናቀል ምን ዓይነት ስም ይወጣላታል? አብዛኛው ዜጋ ግራ ገብቶታል፡፡ በየአቅጣጫው ከከተማ ወጣ ብሎ መስራት በጣም አስፈሪ እየሆነ ሲመጣበት፣ የግድያና የዝርፊያ ጥቃቶች ሲያጣድፉትስ ምን ያድርግ? ብዙ ሰው ይሰጋል።
በርካታ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናትና አውራ ፖለቲከኞች በየፊናቸው የሚሰጡት ምላሽና የሚናገሩት ሐሳብ ደግሞ፣ ችግርን የሚያባብስ፣ በዜጎች መከራ ላይ እየተሳለቀ የሚያላግጥ፣ ስድብንና ብሽሽቅን የሚያጋግል፣ ጥላቻን የሚያዛምት ይሆንበትና፤… ይሄ ነገር ከፓርቲውና ከመንግስት ዓቅም በላይ ሳይሆን አይቀርም ብሎ ያስባል። ደግሞም ይመስላል።
ግን ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥር ውጭ እንዳልወጣ፣ ፓርቲው በራሱ አባላት ላይ፣ መንግሥትም በራሱ ባለስልጣናት ላይ ድርሻ እንዳላቸው ማየት ይቻላል። ተመልከቱ።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በመንግሥት ባለስልጣናትና በአውራ ፖለቲከኞቹ ዘንድ ለውጥ አላያችሁም?
ትንሽ እረፍት አልሰጧችሁም? ከነገር አልተቆጠቡም?
ሁሉም በአንድ ጊዜ የተረጋጉና አደብ የገዙ ይመስላሉ። የአጋጣሚ ጉዳይ ሊሆን አይችልም።
መንግሥት ወይም ገዢው ፓርቲ፣ የራሱን ባለስልጣናት አደብ ለማስገዛት፣ የራሱን ፖለቲከኞች ሥርዓት ለማስያዝ ሲፈልግ፣… አሁንም በቂ ዓቅም እንዳለው አታዩም? በአንድ ጊዜ ሁሉም ሲረጋጉ አይታችሁ መመስከር ትችላላችሁ።
ተመስጌን ነው።
 ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሲሆኑና በየአቅጣጫው ሲያመልጡ እያሳየን በሉ። በጣም ዘግናኝ ነውና።
እሺ፣ ገዢው ፓርቲ የራሱን ፖለቲከኞች፣ መንግሥት የራሱን ባለስልጣናት መከታተልና መቆጣጠር እንደሚችል፣ በቅርብ ሳምንታት ታዝበናልና ስጋታችንን ቀለል ያደርግልናል። መልካም ነው፡፡
ነገር ግን ሌላ አስፈሪ ጥያቄ ይዞብን ይመጣል።
ታዲያ እስከዛሬስ ለምን ዝም አለ?
 በብሽሽቅና በስድብ አገርን ከሚረብሹ ተቀናቃኞች ጋር የገዢ ፓርቲ ፖለቲከኖች ተጨምረው ውዝግቦችን ሲያጦዙ ፓርቲው ለምን እስከ ዛሬ ዝም ብሎ አያቸው?
ኑሮንና ስራን  የሚያመሰቃቅሉ የጥድፊያ ዘመቻዎችን የመግታትና የራሱን ባለስልጣናት የመቆጣጠር ዓቅም እንዳለው በቅርብ ሳምንታት አይተናል። ታዲያ እስከ ዛሬ ድረስ ለምን አላስቆማቸውም? እነዚህ ጥያቄዎች በጣም ያሳስባሉ። ህሊናን ያስጨንቃሉ።



Read 948 times