Tuesday, 14 May 2024 00:00

ውበት-ዘመም መድበል፤

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

‹‹ከዘራፊው ማስታወሻ››
                    


        ‹‹እኔም ሄድ መለስ፣ አልልም በዋዛ፤
ከውበት ቢርቁ፣ ዕውነት አይገዛ፤››
በሊቀ-ሊቃውንት ሥም፣ በባለቅኔዎች ዎረታ፣ በገጣሚያን ችሮታና ሥጦታ፤ በሁሉም ሥም ሰብሰብ ብለን ግጥምን እናወድስ!...
ግጥም ስለ ግጥም!
በለበቅ ስንኞቹ ደርሶ ትውስ የሚለንን ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅንን ‹አፈሩን ያቅልልላቸው› ብለን እንጀምር፤ ዓለምንና ስብጥርጥር ዕውነታዋን በግጥሞቹ ፈክሮ ላስኮመኮመን ለሙሉጌታ ተስፋዬ እንማልድ፤ የዓላማ ጽናትን፣ የሥነ-ውበትንና የሥነ-ግጥምን ተራክቦ በልቡናችን ለጣፈልን ለደበበ ሰይፉ ኮፊያችንን አውልቀን እናጎብድድ! በሥሜት የወዘወዘንን፣ ጣመንና ዕርካታን ያጋባብንን ገብረክርስቶስ ደስታን እንዳንረሳው፤ ውበት ዘመሙን ዮሐንስ አድማሱን እንደምን መዘንጋት ይቻል ይሆን? የአርአያዎቻችን መንፈስ በአገራችን ያረብብ፤ ለዛቸው በልቡናችን ይስረቅረቅ፤ ግጥም ይፍላ፣ ይሙላ… እሰይ!
ወደ አሁናችን እንስከንተር…
…ዛሬአችን የውብአረግ አድምጥ መድበል ነው፤ ውብአረግ አድምጥ ‹‹ከዘራፊው ማስታወሻ›› የተሰኘ የግጥም መድበል እንካችሁ ብሎናል፤ መድበሉ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ (131) ገጾች አሉት፤ የኅትመት ዘመኑ ደግሞ 2016 ዓ.ም. ነው…     
…ከብስል መካከል ጥሬ አተር እንደማግኘት ነው፤ ነጋ-ጠባ አይሰምርም፤ አይከስምም፤ ክስተት በእየቀን የሚከሰት አይሆንም፤ በዓመታት መካከል አንድ ድንቅ ሥጦታ ይከሰታል፤ እንሆ አንድ የግጥም መድበል! የግጥም አውራነት የማያከራክር ነውና፣ የግጥምን አውራነት ያላደባዩ፣ ብሉይነቱን ያልሸረሸሩ፣ ቅኔአዊነቱን ያላከሰሙ እና ዘመን ተሻጋሪነቱን ጥርጣሬ ውስጥ ያልዘፈቁ ግጥሞችን እንቋደስ።
በዚህ መድበል ውስጥ፣ ውብአረግ አያሌ ውብ ግጥሞችን ጀባ ይለናል፤ ውሃ ላይ የተንቸረፈፈ ዘይት፣ ውሃው በሰፋ ልክ ሰፍቶ የውሃው ይዞት ሲጠብብ ዕኩል ይጠብባል፤ የዘይቱ ሕልውና በውሃው የተወሰነ ነው ማለት ነው፤ ግጥምም በስፋትና በድግምግሞሽ ሲነበብ ትርጉሙ እየሰፋ ይመጣል።


በገጽ 107 ላይ፣ ‹‹ቅኔ ውደጂ›› በሚል ግጥም፡
‹‹በቅኔ ነው የምንፈታው፤
በግጥም ነው የምንረታው፤››
እንዲል ገጣሚው፣ ‹‹ከዘራፊው ማስታወሻ›› የተሰኘ የግጥም መድበል፣ ሲነበቡ አዲስ ትርጉምን የሚሰጡ ግጥሞችን አቅፏል፤ ትርጉማቸው ሰፊ፣ ይዘታቸው ጠያቂ፣ አቀራረባቸው ጥበባዊ፣ ቋንቋው የሚመጥን/ግጥማዊ፣ ልጬኛና መርማሪ ግጥሞችን አስተውዬአለሁ። በርካታ በፍላትና በጥብቀት፤ በተብከንካኝ ጠባያቸው የሚወደዱ ግጥሞች ይስተዋላሉ፤ መድበሉ ተናዛዥ፣ ዘብዛቢ፣ ዘጋቢ፣ ነጋሪ፣ ተራኪ፣ የተንዛዛ፣ ሳይሆን፤ ሀሳብ ይዞ ገላጭና ሰዓቢ ቋንቋን በመጠቀም ግጥሞችን የሚያቀርብ ነው፤ ግጥም እንዲያ ነው ወጉ!
በመሆኑም፣ ከገጽ 84 ላይ ‹‹ለሰነፍ አይስጠው›› በሚል ግጥም ስር፡-
‹‹አታድለው አቦ፣ ጥበብ ለሰነፉ፣ አትጨው ለቅኔ፤
በሰም አስጀምሮ፣ በስም ነው ብያኔ፤›› ይለናል ውብአረግ።
አሁን፣ አሁን የሚታተሙ የግጥም መድበሎች በተለያየ ‹ዋግ› የለመሹ እንደሆኑ መካድ ዘበት ነው፤ ገጣሚ ከአንድ ሥፍራ ተቸንክሮ የሮሮ ዜማውን ብቻ የሚያስተጋባ መሆን የለበትም፤ ከጣመን ውስጥ ጣዕም መፈለግ አለበት፤ በተበላሸ ትላንቱ ተገንትሮ ተስፋ ቢስነትን ብቻ መስበክ አይጠበቅበትም፤ ገጣሚነት ጉድለትን መሙላት ነው ትርጉሙ፤ ዛሬ የዘመመ ነገ እንደሚቃና መጠቆም መቻል፣ ከማጥና ከድጥ ማምለጥ እንደሚቻል ጥበባዊነት በተሞላ መንገድ መጠቆም የገጣሚ የቤት ሥራ ነው።


ማኅበረሰባዊ ውርክብን (societal trauma) በውርድ በቁሙ መናዘዝ ሳይሆን፣ ከዚያ ዓይነት ጣጣ የመሽሎኪያ መንገድ መገኘት አለበት በግጥም ውስጥ፤ የኖርነውን መልሶ ማቅረብ መዘገብ ነው ቅሉ፤ በግጥም ንባብ ወቅት፣ የሥነ-ልቡና ሳንካዎችን እንዴት መርታትና መግታት እንዳለብን ትምህርት ማግኘት አለብን።
ከዚህ ባለፈ፣ ዛሬ ላይ የጀገነ ገጣሚ ነገ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅና፤ ከመኮፈስ ሥሜት ገሸሽ ቢል መልካም ነው፤ ግጥም የዓለምን መልከ-ብዙ ዕውነታ በወጉ ተርጉሞ የሚያቀርብ የኪነ-ጥበብ ዓይነት ነው፤ ሕይውትን ከውበት ማጋባት፤ ግጥምን ከውበት ማዳራት የገጣሚ ኃላፊነት ነው፤ ግጥምን ጊዜ ባይገታው፣ ወረት ባይረታው ይመረጣል…
…‹‹ከዘራፊው ማስታወሻ›› ከላይ በተዘረዘሩ ዕክሎች የተደነቃቀፈ አይደለም፤ ገጣሚው የአንድ መድበል አካል የሆኑ እንደ ጣኦስ መልክ የተንቆጠቆጡ ግጥሞችን አስነብቦናል፤ ዛሬው ገንትሮት አያላዝንም፤ በማግኘት ጦንችቶ አይጎፈላም፤ መድበሉ የትናንት፣ የዛሬ እና የነገ ድምር ነው፤ አንድ ተወዳጅነትን ካገኘበት ጎኑ መካከል፣ የግጥም ሀሳቦቹን እንደ ዜና ያለመዘገቡ ነው፤ ፍካሬ እጅ እግር አውጥቶ ፊት ለፊት እናገኛለን። ነገን ይኩላል፤ ያበቃል፤ ያነቃል፤ ይፈክራል፤ ይተረጉማል፤ ቅኔ ይወርዳል።
ለዚህም፣ በገጽ 108 ላይ፣ ‹‹እኔስ ማታ ማታ›› የሚል ርዕስ ባለው ግጥም፡-
ወይ በዘመን ኑሩ፤
በወቅት ተመከሩ፤
ወይ ከዓለሜ ሽሹ፣ ልኑር እንደራሴ፤
በሳቅ ላይ ማንባትን፣ አልቻለችም ነፍሴ፤››
በማለት ወቅትን የማጤንን አስፈላጊነት አሳይቷል፤ ግጥሙ ተፈራራቂ ሥሜቶችን የሚጎበኝና አልፎም አማራጭ የሚሰጥ ነው።


መድበሉ በማኅበረሰብ ተኮር ጉዳዮች ተደነቃቅፎ አያደናቅፈንም፤ ጥቁምታን ይቸራል እንጂ፤ ተፈጥሮን የተንተራሱ ስንኞች በእየቦታው ይስተዋላሉ፤ ውበት ከተፈጥሮ ተጋምደው፣ መዝማዥ ርዕሰ-ጉዳዮች በግጥማዊ ቋንቋ ተሸግነው ለማጣጣም የተቸረልን ጥዑም ብፌ ነው…          
…ኑማ ‹‹ከዘራፊው ማስታወሻ›› ውስጥ ግጥሞችን እያጣቀስን እናውጋ…
…ገጣሚው በዚህ መድበል ውስጥ ሥነ-ውበት ላይ ተንተርሶ ሲሰናኝ እንመለከታለን፤ የግጥም ሀሳቦቹን የሚያቀርብልን ይትባሃል ውበት-ዘመም ዘዬን የተላበሰ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ግጥሞች በምሰላ አሃድ፣ በፍካሬ፣ በዘይቤአዊነት እና በማስረግ ስልት የደመቁ ናቸው። ለአብነት ያህል፡-
‹‹እንዳለመወለድ›› (ገጽ 19) የሚለውን ግጥም እንመልከት፤ እዚህ ግጥም ገላ ውስጥ እንደዚህ የሚሉ ስንኞችን እናገኛለን፡-
‹‹አምላኩም እንደሰው፣ ካልሸለሙት አይበርድ፤
ሊገፉት ካልዳዱ፣ ለምሕረት አይረግድ፤››
ይለናል፤ በእነዚህ ስንኞች ውስጥ አንድ ብልሃት ይጠቁማል ገጣሚው፤ ለዘመኑ ችግራችን ማብረጃ የሚሆን ምስ ነው የተወከለው፤ እግዚሔሩን ነው በሰው ልክ የመሰለው፤ ፍትሕ ተነፍጓልና፣ ፍትሕ ለማግኘት ሲል መፍትሔ ሲያሯሩጥ ይገኛል። ገጣሚ ፍትሕና ርትዕ ፈታሽ ነው፤ ፍትሕ በየትና እንዴት ይገኛል? በምን ዓይነት መልኩ ዕውን ይሆናል? የሚሉ የጋራ ሥሜቶችን በግጥሞቹ ገላ ይጠቁማል። በተጨማሪ፣ ግጥሙ ከጠየቀው ጥያቄ በላይ የአቀራረቡ ጥበባዊነት ሰዓቢ ነው።


ዘለስ ብለን ሌላ ምሳሌ እንጥቀስ፤ ገጽ 22 ላይ ‹‹በበልግ እንገናኝ›› ከሚል ግጥም የተወሰኑ ስንኞችን መዝዘን እንመልከት፡-
‹‹እኮ በጸደዬ?
ምንድር ነው ጉልጓሎ?
ያፈራው ሳይገባ፣ በሬ ሳይነጭ ውሎ?
አንተ የበሬው ጌታ፣ ከጊዜ አታጣላኝ፤
ለፍቶ አደር ነኝና፣
ከብቶቼን አጥግቤ፣ በበልግ እንገናኝ፤››  
በማለት ተሰናኝቷል፤ በዚህ ግጥም ገላ ውስጥ ጊዜ አለ፤ ወቅቱን ያልዋጀ ግብር መጨረሻው መውደቅ እንደሆነ ዕሙን ነው፤ ነገሮች ጊዜያቸውን ጠብቀው የተጓዙ እንደሆን፣ ዕምርታ ይከተላል እያለን ነው ገጣሚው። ይኼንን ሀሳብ እንዲያስኬድለት በወቅት የሚሠራን አንድ ገበሬ ወክሎ አቅርቧል፤ የገበሬውን የአኗኗር ይትባሃል በቆንጆ ቋንቋ ፈክሮና አዟዙሮ በማመላከት፣ የጊዜ አጠቃቀማችንና በወቅት የመመራት ዘዴአችንን ጠቁሟል። ታዲያ፣ ግጥም የሚያስተምር ከሆነ እንዲህ አዟዙሮ ያስተምር እንጂ እግር ስር ቁጭ አድርጎ በቸኩ ሂደቶች ውስጥ አያቸከን ባይ ነኝ።
እንሰልስ፤ ገጽ 18 ላይ ‹‹ይኼማ እንደዚያ ነው›› የሚል ግጥም አለ፤ የሚከተሉ ስንኞችን መርጬአለሁና እንመልከት፡-
‹‹እንዳለፍነው ትናንት፣ እንዳየነው ዛሬ፤
ባሕርይ አይደለም ወይ፣ አገርሽ አገሬ፤››
ሲል ይሰማል፤ መውደድ መናፈቁን በጊዜ ተክቷል፤ መውደድ መኖር ነው፤ መኖር ደግሞ ትናንትን አልፎ ዛሬን ማጣጣም ነው፤ አገርም እንዲያ ነው፤ ትናንት የነበረ፤ ዛሬም የቀጠለ፤ ስለሁሉም ሙከራ ይበል ብዬአለሁ!
ከዚህ በተለየ፣ ገጣሚው ‹ሥነ-ቃል፣ ሥነ-ቃል› የሚሸቱ ስንኞችን በተለያዩ ግጥሞች እየሰገሰገ ውበትን ፈጥሯል፤ ገጣሚ በቋንቋ ላይ መጀገን እንዳለበት ይታመናል፤ የገጣሚ መብቱን ተጠቅሞ በውበታቸውና በውክልናቸው የተዋቡና ገላጭ የሆኑ ሐረጋትንና ስንኞችን እየወረደ ይፈክራል።


በቋንቋ መርቀቅንና መቦረቅን ይሻል ይኼኛው ነጥብ፤ እንዲያ ሲባል፣ በመራቀቅ ሰበብ ሥሜትና ዕውነትን ማምታታት አይጠበቅም፤ ገጣሚው የሚጠቀማቸው ቃላት ትርጉማቸው ከሐረግ-ሐረግ፣ ከስንኝ-ስንኝ የተቃረነ መሆን የለበትም፤ ሆኖም፣ ለቃላት አገባባዊ ፍቺ፣ ለውክልናቸውና ለተለያዩ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ሥነ-ውበታዊ ዋጋቸው ከፍ ያሉ ቃላትን በመጠቀም መግጠም ይቻላል።  
ለምሳሌ ከገጽ 121 ላይ፣ ‹‹ይልቅ አንቺም ውለጂ›› የሚል ግጥም አለ፤ የሚከተሉ ስንኞችን ለይተን እንመርምር…
‹‹ከጋጣሽ ውስጥ የከተመች፣
ይኼው በቅሎ ወልዳ ሳመች፤››
ከላይ የተዘረዘሩ ስኝኖች አንዲትን አካል በምን ዓይነት ደረጃ እንደሚያሳጡ መገንዘብ ቀላል ነው፤ እሷ ተጃጅላ ሳለች፣ የማትወልደው በቅሎ ወልዳ አሳየች፤ የሚወልድ በቅሎ እንደሌለ ቢታወቅም፣ ግጥሙ የመውቀስና የመተቸት ጥንካሬ አለው፤ በማኅበረሰባችን ሰነፎችን ለመተቸት ቢያገለግል ትርጉም ይሰጣል። በተጨማሪ፣ ከገጽ 118 ላይ የሰፈረውን ‹‹ተፈጥሮና ሳቅሽ›› የተሰኘ ግጥም ማየት ይቻላል፤ እዚያ ውስጥ…
‹‹ክህደት ቢሸብበው፣ ታሰረ አንደበቱ፤
በእንባ እየተገፋ፣ ዕውነት ሆነ ሞቱ፤››
እና ከገጽ 113 ላይ፣ ‹‹አወይ ደጋሚዬ›› ከሚል ግጥም፡-
‹‹ከወፎች ዜማ ጋር፣ አብራ ስትደግመኝ፤
አወይ ንጋት ስሻ፣ አቤት ጸሎት ስመኝ፤››
የሚሉ ስንኞች በሕዝብ ዘንድ በነጻነት የሚነገሩ ሥነ-ቃሎችን የሚመስሉና ለማዜም አመቺ እንደሆኑ መናገር ይቻላል።
ከዚህ በተጻራሪ፣ አንዳንድ የዜማ ፍሰትን የሚያስተጓጉሉ ቃላት፣ የተወሰኑ ግጥሞችን በነጻነት እንዳናዜም ከልተውናል፤ እነዚህም፣ ገጣሚው የተጠቀማቸው አንዳንድ አያያዥ ቃላቶች ሲሆኑ (ለምሳሌ፡- እንደ፣ ታዲያ፣ እና፣ ስለዚህ፣ ይኼው…ወዘተ. የመሳሰሉ) ያልተመጠኑ በመሆናቸው፣ በንባብ ወቅት መናጠብን ያስከትላሉ።    
በአጠቃላይ፣ በተራ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የማይዘበዝቡ ግጥሞች የዚህ መድበል ጸጋዎች ናቸው፤ ገጣሚው፣ አንባቢን በሀሳቡ ያበቃል፣ ያነቃል፤ ፍካሬ፣ ዘይቤአዊነት፣ የምሰላ አሃድ እና ሥነ-ቃላዊ ለዛን በሥነ-ግጥም መሞከር የዚህ መድበል በጎ ገጽታዎች ናቸው። ቢያነብቡት ይወዱታል፤ የተከበረ ግብዣዬ ነው፤ አመሰግናለሁ!  

      
ከአዘጋጁ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 194 times