Saturday, 13 June 2015 14:54

‹‹የሰው ዘር መገኛ››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

ዳርዊን እና ወንጌል ሊታረቁ ይችላሉን?

የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለሁ፤ ከጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ መምህራችን ቢሮ ሄድን፡፡ የሄድንበትን ጉዳይ አሁን አላስታውሰውም፡፡ ይሁንና በዚያ አጋጣሚ መምህራችን ያለውን አንድ ነገር እስከ ዛሬ አስታውሰዋለሁ፡፡ ወደ እርሱ ቢሮ የሄድንበትን የትምህርት ጉዳይ ተነጋግረን ከጨረስን በኋላ፤ መምህራችን የእግዚአብሔርን ህልውና የሚጠይቅ ሐሳብ ያለው አንድ ግጥም አነበበልን፡፡ ከዚያም ከመሀላችን አንዱ፤ ‹‹ግን አንተ በእግዚአብሔር አታምንም›› ሲል ጠየቀው፡፡ መምህራችን ፈጠን ብሎ ‹‹እኔ አላምንም›› አለ፡፡
ጨዋታው ቀጠለ፡፡ ወሬያችን እንደ ፈሰሰ ውሃ የራሱን መንገድ እየፈለገ ሄዶ፤ መምህራችን በኢህአፓ ዘመን ያጋጠመውን ችግር ከሚያወራበት ቦታ ደረስን፡፡ ሲያወራ ቆይቶ፤ ‹‹በስመ አብ [በስማም] ያኔ የተፈጠረው ችግር›› ብሎ ወሬውን ሊቀጥል ሲል፤ ከመሐላችን አንዱ በጣም ሳቀ፡፡
‹‹ምነው?›› አለ መምህራችን፡፡
‹‹አሁን እኮ በስማም አልክ››
‹‹አይ እሱ ልማድ ነው›› በማለት፤ እንደ ዋዛ መልሶለት ጨዋታውን ቀጠለ፡፡
ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው ሌላ ነገር አለ። ሐይማኖተኛ መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ የኮሌጅ፣ የዩኒቨርስቲ ወይም የሁለተኛ ደረጃ መምህር፤ ያለ አንዳች ሰቀቀን ‹‹የአዝጋሚ ለውጥ›› ቲዮሪን ሊያስተምር ይችላል። ‹‹የእሱ እንኳን እንጀራ ሆኖበት ነው›› ብለን እንለፈው። መምህሩም የዳርዊንን ቲዮሪ እንደማይቀበለው ገልፆ ሊያስተምር የሚችል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም በትምህርቱ አሰጣጥ ላይ የእርሱ እምነት መንፀባረቅ የለበትም። ስለዚህ ‹‹ፖለቲካዊ ትክክለኝት›› ይህን እንዲያደርግ ያስገድደዋል፡፡ የእርሱ ዕዳው ገብስ ነው፡፡
ደግሞ ሌላ ነገር ልጨምር፡፡ አንድ ጓደኛዬ ስድስተኛ ክፍል ሳለች ያጋጠማትን ነገር ነገረችኝ፡፡ ‹‹ለኅብረተሰብ ፈተና ስዘጋጅ እያለሁ፤ ጓደኛዬ መጥታ፤
‹አምና የመጣ አንድ ጥያቄ ልንገርሽ› አለችኝ፡፡
‹ምንድነው?› አልኳት፡፡
‹ሰው የተፈጠረው…………..ሀ). ከክሮግማኖን ለ). ከአዳም እና ሔዋን ሐ). በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት መ). መልሱ የለም› ብላ ጥያቄውን ስትነግረኝ፤ በልቤ አንድ ነገር አሰብኩ፡፡ ከአስሩ ጥያቄ መልሳቸውን በትክክል የማውቃቸውን ቆጥሬ ከአምስት በላይ ከሆኑ ‹አዳም እና ሔዋን› ብዬ እመልሳለሁ፡፡ ከአምስት በታች ከሆኑ …….› ብዬ አሰብኩ፡፡ ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንደዚያ ማሰቤ ይቆጨኛል፡፡ አዝናለሁ›› አለች  እንደ መተከዝ ብላ። የማዘኗ እና የመቆጨቷ ነገር አልገባኝም፡፡ ስለዚህ፤  ‹‹ለምንድነው የሚቆጭሽ? ምንድነው የሚያሳዝንሽ?›› አልኳት፡፡
‹‹አሁን ለአንተ ስነግርህም እንደ ንስሐ በማሰብ ነው›› አለችኝ፡፡
ነገር የማጋነን ችግር ውስጥ የገባች መሰለኝ፡፡ በመጨረሻም፤ ‹‹ያን ጊዜ፤ ለአንድ ማርክ ብዬ እንደዚያ ማሰቤ ያሳዝነኛል›› አለችኝ፡፡ እንዳሰብኩት፤ ነገር የማጋነን ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከምሯ ነው፡፡ ከልብ ተቀበልኳት፡፡
ይህች ጓደኛዬ እንደ መምሬ በዝንጋኤ አልተኛችም፡፡ ጥያቄው ሲቀርብላት፤ ‹‹በኅብረተሰብ ሳይንስ የተማርነው ምንድነው?›› በሚል ልማዳዊ ተግባር መልስ ለመስጠት አልተጣደፈችም፡፡ ነገሩን በልማዳዊ አባባል አለባብሳ አላለፈችውም፡፡ ቆም ብላ አስባለች፡፡ የቻርልስ ዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ ሐልዮት አትቀበልም፡፡ ያን ጊዜ፤ ‹‹ትምህርታዊ ትክክለኝነት›› ወይም ማርክን በማሰብ፤ ጨርሶ የማታምንበትን ነገር እንደ መልስ ለማቅረብ ማሰቧ እንኳን ዘግንኗታል፡፡ የአስተማሪው ብዙ ምርጫ ያለው አይመስለኝም፡፡ ተማሪውም ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ግን ነገሩን እንደ’ኔ መምህር ተራ የቋንቋ ልማድ አድርጎ ከማየት ወይም ከዝንጋኤ መራቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ኢ-አማኒ መሆናቸውን የሚገልፁ፤ እንደ ማክሲም ጎርኪ ያሉ ፀሐፊዎችም ‹‹መንፈሳዊ›› ወይም ‹‹ነፍስ›› የሚል ቃል ሲጠቀሙ፤ እንደ ዘይቤ ወስደውት ይሆናል፡፡ ለምሣሌ ጎርኪ ‹‹On Literature›› በሚል መፅሐፉ፤ ‹‹እኔ ‹ነፍስ› የሚለውን ቃል የምጠቀምበት እንደ ዘይቤ ነው›› ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡   
እንደ ተማሪ ‹‹ትምህርታዊ ትክክለኛነት፤ እንደ መምህር ‹‹ፖለቲካዊ ትክክለኛነት›› እያስገደዳቸው የዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ ሐልዮት የመቀበል ዕዳ ሊወድቅባቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር የሌለባቸው፤ እንዲያውም ህይወታቸው እና በግልፅ የሚታየው እምነታቸው ከዳርዊን ጋር የሚጋጭ ሆኖ ሳለ፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›› ሲሉ የሚናገሩ አንዳንድ የሐይማኖት አባቶችን ማየት ግን ግራ ያጋባል፡፡ እነዚህ አባቶች፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›› ሲሉ በተደጋጋሚ እሰማለሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመገኛኛ ብዙሃን የቀረቡ፤ አንዳንድ የሐይማኖት ሰዎች፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›› ሲሉ እናንተም ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ታዲያ እነዚህ አባቶች፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ›› ሲሉ ምን ማለታቸው ይሆን? ‹‹ኢትዮጵያ አዳም የተፈጠረባት ሐገር ነች›› ማለታቸው አልመሰለኝም፡፡   
ለምሣሌ፤ የዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ የማይቀበል አንድ የባህል ወይም የቱሪዝም ተቋም የሥራ ኃላፊ፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ›› ቢል፤ ነገሩ ‹‹ከኢኮኖሚያዊ ትክክለኝነት›› ጋር መያያዙ ግልፅ ነው፡፡ ከዚያ የተለየ ነገር እንዲልም አይጠበቅም፡፡ የሐይማኖት አባቶች ጉዳይ ግን ግራ ያጋባል፡፡ የዳርዊን ሐልዮት እና የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል አይጋጩባቸውም ማለት ነው?
 አንዳንድ ሰዎች፤ ‹‹ሳይንስ እንደ ድሮው ሐይማኖትን የሚፃረር ሆኖ አይታይም፡፡ ይልቅስ፤ የሳይንስ አንዳንድ ግኝቶች ሐይማኖትን የሚያግዙ ሆነዋል›› በማለት ይገልፃሉ፡፡ ኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke) የተባለ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ባቀረበው አንድ ጥናታዊ ፅሁፍ፤ በምዕራቡ ዓለም፤ ‹‹ሳይንስ እና ሐይማኖት ወይም እምነት እና አመክንዮ አይጋጩም›› የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውንም ይጠቅሳል፡፡ በዚሁ ጥናታዊ ፅሑፍ፤ ሐንክ ሃኔግራፍ (Hank Hanegraaff) የተባለ ታዋቂ አሜሪካዊ ፀሐፊ፤ ‹‹Adam and Eve: Fact or Fiction›› በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ መፃፉን የሚጠቅሰው ኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke) በዚሁ መጣጥፍ መነሻ፤ የሚከተል ጥያቄ እና መልስ መስፈሩን ይናገራል፡፡
ጥያቄ፤ መፅሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ይዘት እንዳለው የሚያምን አንድ ጓደኛዬ፤ በቅዱስ መፅሐፍ የተጠቀሰው የአዳም እና የሔዋን ታሪክ፤ እንዲሁም ውድቀታቸው በቀጥታ ሊወሰድ አይገባውም ብሎ ያምናል፡፡ ታዲያ የዚህ ጓደኛዬን ሐሳብ የሚደግፍ ቃል በመፅሃፍ አለ?
መልስ፤ በፍፁም! የአዳም እና የሔዋን ታሪክን እንዲሁም ነገረ-ውድቀት እና ሞታቸውን እንደ ዘይቤአዊ አገላፅ መውሰድ (Figurative allegory አድርጎ)፤ ጠቅላላ የመፅሐፍ ቅዱስን ቃል በከፋ መልክ የሚፃረር አስተያየት ነው፡፡
ሐንክ ሃኔግራፍ፤ በአሜሪካውያን ዘንድ ሰፊ ዝና ያለው ሰባኪ ነው፡፡ አሜሪካውያን ‹‹Bible Answer Man›› እያሉ ይጠሩታል፡፡ በየዕለቱ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች እየቀረቡለት ምላሽ ይሰጣል፡፡ የሚሰጠው ምላሽ፤ በመላ አሜሪካ በሚገኙ ከመቶ የሚበልጡ የሬዲዮ ጣቢያዎች ይተላለፋል፡፡
ሐንክ ሐኔግራፍ፤ ከመፅሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ጥቅሶችን እየወሰደ፤ የአዳም እና የሔዋንን ታሪክ ሥነ መለኮታዊ ፋይዳ እና ታሪካዊ ትክክለኛነቱን ካስረዳ በኋላ፤ ‹‹የአዳም እና የሔዋንን ታሪክ ቃል በቃል መቀበል እና እውነተኛነቱን ማረጋገጥ ለአንድ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረዳ፡፡ እንዲህም አለ፤
‹‹አየህ፤ በአዳም እና ሔዋን ታሪክ ላይ የሆነ ጥርጣሬ ካሳደርክ፤ በመፅሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ይዘት እና የህይወት መመሪያ ቃል መሆኑ ላይ ጥያቄ ማንሳት ይኖርብሃል። በሰው ልጅ የሐጥያት ባርያ መሆን፣ በእግዚአብሔር ፀጋ ድኅነት በማግኘቱ ወዘተ ላይ ጥያቄ ማንሳትህ አይቀርም። በእነዚህ ጉዳዮች ጥያቄ ካነሳህ ክርስትያንነትህ ያበቃለታል፡፡››
የ‹‹ኢ-አማኒያን›› መፅሔት አዘጋጅ፤ እንዲሁም የአሜሪካ ኢ-አማንያን የፕሬስ ዳይሬክተር የሆነው ፍራንክ ዚንድለር፤ (Frank Zindler) በአንድ መጣጥፉ የሚከተለውን ይላል፤
‹‹ባዮሎጂ፤ በክርስትና እምነት ላይ ያመጣው ትልቅ አደጋ የአዝጋሚ ለውጥ ቲዮሪ ነው፡፡ ዛሬ አዳም እና ሔዋን በምድር ላይ ኖረው ያለፉ እውነተኛ ሰዎች አለመሆናቸውን አውቀናል፡፡ የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ታሪክ ፈራርሷል፡፡ እናም አዳም እና ሔዋን እውነተኛ ሰዎች ካልሆኑ፤ የመጀመሪያው ሐጢያት (original sin) የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ የመጀመሪያው ሐጢያት የሚባል ነገር ከሌለ፤ ድኅነት አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ድኅነት አስፈላጊ ካልሆነ፤ አዳኝ አያስፈልግም፡፡ አዳኝ የማያስፈልግ ከሆነ ኢየሱስ ምን ይሰራል፡፡ እንደኔ ሐሳብ የአዝጋሚ ለውጥ ቲዮሪ፤ የክርስትና እምነት መግነዝ ነው›› ሲል ጽፏል፡፡ በስመ አብ ማለት አሁን ነው፡፡
ሰባኪው ሐንክ ሐኔግራፍ በበኩሉ፤ የአዝጋሚ ለውጥ ሐልዮት ከክርስትና እምነት ጋር የሚጋጭ መሆኑን በመግለፅ፤ ለሬዲዮ አድማጮቹ ‹‹የቻርልስ ዳርዊንን ቲዮሪ እንዳትቀበሉ›› ሲል ጥሪ ያደርጋል፡፡ ለፍራንክ ዚንዲለር፤ ከአዳም እና ሔዋን ታሪክ ይልቅ ተቀባይነት ያለው ሳይንስ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ተቃራኒ አቋም ያላቸው ሁለት ሰዎች፤ የሚጋሯቸው ሁለት ነጥቦች አሉ፡፡ አንደኛ፤ ሁለቱም ሰዎች፤ የዘፍጥረት ትረካ እና የአዝጋሚ ለውጥ ሐቲት የሚያጋጩ መሆናቸውን ያምናሉ፡፡ ሁለተኛ፤ ‹‹የሳይንስን (የአዝጋሚ ለውጥ) ትረካን መቀበል ክርስትናን መካድ ነው›› ይላሉ፡፡
ከፍ ሲል በጠቀስነው የኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke) ጥናታዊ ፅሑፍ እንደ ተጠቀሰው፤ የሐንክ ሐኔግራፍ እና ፍራን ዚንድለር የክርክር ሎጂክ ለብዙ አሜሪካውያን ፀነን ይልባቸው ይሆናል፡፡ ሆኖም፤ ሁለቱ ተከራካሪዎች ይስማሙባቸዋል ያልናቸው ሁለት ነጥቦች፤ የአሜሪካ የዕውቀት ማህደር ጥንታዊ ጓዝ ናቸው፡፡ የዘፍጥረት እና ‹‹የአዝጋሚ ለውጥ›› ክርክር የተለመደ የአሜሪካውያን ባህላዊ ጓዝ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ፤ አንዳንድ የአሜሪካ ቤተክርስቲያናት፤ በተጠቀሱት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። ‹‹እምነት እና አመክንዮ›› (Faith and Reason) እንዲሁም፤ ‹‹እዩር መፅሐፍ ቅዱሳዊ ንባብ›› (Reading the Bible intelligently) የሚሉ ሥልጠናዎችን ለወጣቶች (ጎልማሶች) ይሰጣሉ፡፡ ኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke)፤ ‹‹በእነዚህ የትምህርት መስጫ ክፍሎች እግር ጥሎት የገባ ሰው፤ በእነዚህ ክፍል ውስጥ የሚሰማው ውይይት የሚከተለውን ይመስላል›› ይላል፡፡
አሊስተር፣ እኛ በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሰዎች ወይም ወንጌላውያን በእዕምሯቸው ያብሰለስሉ የነበረው ጥያቄ ምን እንደሆነ ለማሰብ ሳንሞክር፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእኛን ዘመን ጥያቄ እንዲመልስልን እንሻለን፡፡ ምሳሌ፤ ሊሆን የሚችለው ዘፍጥረትን በማንበብ ስለ አዝጋሚ ለውጥ ሂደት ለመረዳት መሞከራችን ነው፡፡ ሆኖም ዘፍጥረትን በፃፉት ሰዎች፤  አዕምሮ ውስጥ የሳይንስ ጥያቄ ይኸ አልነበረም፡፡ የአዝጋሚ ለውጥ ሂደት የሚያስጨንቃቸው ሰዎች አልነበሩም፡፡ የዘፍጥረት ዋና መልዕክት፤ ‹‹ከዚህ ከምናየው ዩኒቨርስ ጀርባ፤ እግዚአብሄር አለ›› የሚል ነው። እኔም ያለ አንዳች ጥርጥር ይህን አምናለሁ፡፡
ዳን፤ እኔ መፅሐፍ ቅዱስ፤ ሳይንሳዊ ጥያቄዎች አለመመለሱ አያስጨንቀኝም፡፡ ምክንያቱም፤ ሳይንስ የህይወትን ውስብስብ ጥያቄዎች ለመመለስ አይሞክርም፡፡ ያን ለማድረግም አይችልም፡፡
አሊስተር፤ አዎ፤ መፅሐፍ ቅዱስ፤ የሳይንስን ጥያቄ አይመልስም፡፡ ይህም እንደ እንከን ሊታይ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ክበብ ውጪ ያለ መሠረታዊ ጥያቄን ለመመለስ ነው የሚሞክረው፡፡ ሳይንስ፤ ዕውቀት የሚገኝበት አንድ ጎዳና ነው፡፡ አንድ የዕውቀት መንገድ ብቻ ነው፡፡
እኛ አሁን እያደረግን ያለነው፤ ለሳይንስ ጥያቄ መፅሐፍ ቅዱስ ምላሽ እንዲሰጠን መፈለግ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፤ ለእንዲህ ዓይነት ዕውቀት መፍቻ ቁልፍ የለውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ፅፈው ያኖሩልን ሰዎች፤ እንደዚህ ያሉ ሳይንሳዊ ጥያቄዎች አልነበራቸውም፡፡ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፤ በሳይንሳዊ ትርጉም ሳይሆን፤ በ‹‹ሥነ-ግጥማዊ›› ትርጉም ለማየት መሞከር አለብን፡፡
የእነዚህ ሁለት ሰዎች ንግግር በሳይንስ እና በሐይማኖት መካከል እርቅ ማውረድ አይደለም፡፡ አንዱን ይዘው፤ አንዱን ለመጣል አይፈልጉም፡፡ የሁለቱ ሰዎች ንግግር፤ በሳይንስ እና በእምነት መካከል ግጭት መኖሩን የሚቀበል አስተሳሰብን የሚገዳደር አመለካከት ነው፡፡ ነገሩን በሳይንስ መንገድ ብቻ ለማየት የሚሞክሩ ሰዎች (literalist science)፤ እንዲሁም በሐይማኖት ብቻ ለማየት የሚጣጣሩ ወገኖች (literalist religion)፤ ካሉበት አንዲት መንደር ገብተው፤ ሦስተኛ መንገድ እየፈለጉ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ አዲስ የጥበብ ጥያቄ ቀያሾች ናቸው፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ ጠቢባን፤ እነዚህን ሰዎች ‹‹አገናዛቢ ሐይማኖታውያን›› (reflexive spiritualists) ይሏቸዋል፡፡
የሆነ ሆኖ፤ ቻርልስ ዳርዊን እና ወንጌል ሊታረቁ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ አሁንም መልስ አላገኘም፡፡ አሁን በምዕራቡ ዓለም ያለው አዝማሚያ እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ነው፡፡ ታዋቂው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ማክስ ዌበር፤‹‹ትምህርት ሲስፋፋ ሐይማኖት እየጫጫ እና እየተዳከመ  ይመጣል›› ይል ነበር፡፡ በተቃራኒው፤ ‹‹አሁን ያ ድምዳሜ ስህተት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ተቋማዊ ሐይማኖታዊነት እየተዳከመ ቢመጣም፤ ሰዎች ከሐይማኖት ርቀዋል የሚል ድምዳሜ መያዝ አይቻልም፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ አለማየታችን፤ ሊያታልለን አይገባም›› የሚሉ ጸሐፊዎችም አሉ፡፡ እንደ ምሳሌ፤ የ9/11 አደጋ በተከሰተ ጊዜ በርካታ አሜሪካውያን ወደ ቤተ እምነቶች መጉረፍ መጀመራቸውን የሚጠቅሱም አሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም እንደሚታሰበው ሴኩላሪዝም የተስፋፋበት አይደለም፡፡ የምዕራቡ ዓለም፤ ከሞት በኋላ ህይወት የለም የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ ከሞት በኋላ ያለውን ሁኔታ እግዚአብሔር ፈቅዶልኝ አይቼ ጎብኝቼ መጣሁ ብለው፤ የወዲያኛውን ዓለም በሚደንቅ ሁኔታ እየገለፁ የፃፉ ሰዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ አማኑኤል ስዌደንቦርጅ ነው፡፡
አማኑኤል ስዌደንቦርጅ (Emanuel Swedenborg)፤ ‹‹ገነት እና ሲዖል›› (Heaven and Hell) የሚል መፅሐፍ አለው፡፡ መፅሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1758 ዓ.ም ሲሆን፤ የተፃፈውም በላቲን ቋንቋ ነበር፡፡ በአሜሪካ፤ የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ትርጉም  የታተመው፤ በ1812 ዓ.ም ሲሆን፤ እኔ ያነበብኩት መጽሐፍ፤ በጆርጅ ኤፍ. ዶሌ የተተረጎመ የ1994 ዕትም ነው፡፡ አማኑኤል ስዌደንቦርጅ (Emanuel Swedenborg) ከፃፋቸው በርካታ መጽሐፍት እንደ ትልቅ ሥራ የሚቆጠረውም ‹‹ገነት እና ሲዖል›› (Heaven and Hell) ነው፡፡  በዚህ መጽሐፉ፤ ስዌደንቦርጅ በመንፈሳዊው አውራጃ ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ‹‹ገጠመኝ ወይም አየሁ›› ያለውን በዝርዝር ገልፆ ያስነብበናል፡፡ መጽሐፉ በጣም የተደራጀ ሐሳብ ያለው እና ሰማያዊ ኑሮን በዝርዝር የሚያትት ነው፡፡ ስዌደንቦርጅ፤ ስለ ዩኒቨርሳል ንግግር (universal speech)፤ ከሞት በኋላ ስላለው ነገር፤ ስለ ግብዝ እና ቅዱስ ፍቅር፤ ስለ መናፍስት ዓለም እና ስለሌሎች በርካታ ነገሮች በዚሁ መጽሀፍ ያጫውተናል፡፡ በገነት እና ሲኦል የተገለፀው ሐሳብ ለ200 ዓመታት ያክል ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሮ ነበር፡፡
‹‹ስዌደንቦርጅን፤ በዘመነ አመክንዮ (age of reason) የተፈጠረ፣ ድንቅ እና ወጥ ሀሳብ ያለው አሰላሳይ ነው›› በማለት የሚያደንቁት አሉ፡፡ መጽሐፉ ‹‹ከሞት በኋላ ምን ይገጥመን ይሆን?›› የሚል ሀሳብ ብዙ ለሚያሳስባቸው ሰዎች ትንሽ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡
በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ አያዋዊ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ እጃችን፤ ግዙፍ ነገሮችን ዳሶ ይለያል፡፡ ዓይናችን ቀለም እና ቅርፅን ይለያል፡፡ የዕለት ተለት ህይወት ኑሮአችን አድማሱ ጠባብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ነፍሳችን ከፍ ካለ ኮረብታ ወጥታ ማህለቅት የለሽ እውነታን ለቅጽበት የምትመለከትበት አጋጣሚ አለ፡፡ አያዋዊው ነገር ይህ ነው። በሌላ አገላለፅ፤ በጣም ውስን የዕድሜ ገደብ ያለው የሰው ልጅ፤ ዘላለምን ለመመልከት መቻሉ አያዋዊ ያደርገዋል፡፡ በዘላለም መስኮት ብቅ ብለው በቅጽበት እውነታን ለማየት የሚችሉ ፃድቃን ወይም ገጣሚዎች ወይም ፈላስፎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሁላችንም በሆነ የደስታ እና ዘና የማለት ስሜት ውስጥ ስንሆን በጨረፍታ ነገሩን ለማየት የሚያስችል ዕድል ሊገጥመን ይችላል፡፡ ከእውኑ በላይ እውን የሆነ እና ከዘወትራዊ ኑሮ የላቀ የእይታ መስኮት አለ፡፡
በእርግጥ፤ ለኛ እውናዊ ዓለም ማለት በዙሪያችን የከበበን ግዘፋዊ አካባቢ ነው፡፡ ለመሆኑ፤ በዙሪያችን የከበበንን ግዘፋዊ ዓለም እና ግዘፋዊው ዓለም የሚነግረን ነገር እሙናዊ ነውን? እንዲህ ያለ ጥያቄ ለአንድ ገጣሚ ብናነሳለት፤ ‹‹አይ እነዚህ ነገሮች ከመንፈሳዊ ራዕይ የበለጠ ዕሙናዊ አይደሉም፡፡ የክሎዛፕ እይታዎች ናቸው እንጂ›› ሊል ይችላል፡፡
ገጣሚው ምን ማለቱ ነው? የምንዳስሰው እና በዙሪያችን ያለ ነገር በመንፈሳዊ ዕይታ (mystical vision) ከምንመለከተው ነገር በበለጠ ጎልቶ የሚሰማ ነው፡፡ ግን ያ ተጨባጭ ነገር ትርጉሙን ለመረዳት ያስቸግራል። በመንፈሳዊ ዕይታ ስናየው ግን የተሟላ እና ትርጉሙ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ከተሳግንበት የጊዜ እና የቦታ ቅርቃር ወጥተን፤ በሦስት የጊዜ አውታር ተቦጫጭቆ የነበረው ህልውና ከመቅጽበት አንድ ወጥ ሆኖ፤ ግዘፉ ዓለም ባዕድ እና ግራ አጋቢ መሆኑ ቀርቶ፤ መነሻ እና መድረሻው በውል የሚታወቅ፤ አስፈሪነቱ እና ግራ አጋቢነቱ ተወግዶ፤ ፍርሀትና ስጋት ጠፍቶ፤ ሁሉም ነገር ምላት አግኝቶ፤ የመኖራችን ትርጉም ሲገለጥልን ራሳችንን እና ዓለምን ይበልጥ እናውቀዋለን፡፡ እናም ጥያቄው፤ ‹‹የትኛው ነው እሙናዊ?›› የሚለው ነው፡፡ ይህችን እይታ የቀመሰ ገጣሚ ወይም ፈላስፋ ወይም ጻዲቅ፤ ያቺን የቅጽበት እይታ መልሶ ለማግኘት ይማስናል፣ አብዝቶ ይደክማል፡፡
ለጠቀስነው የስዌደንቦርጅ መጽሀፍ መግቢያ የጻፉት ኮሊን ዊልሰን እንደሚሉት፤ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምርጥ ምርጥ ገጣሚያን እና የኪነጥበብ ሰዎች ያቺን የቅፅበት ዕይታ መልሶ ለማየት ሲዳክሩ፤ በመንፈስ ጣመን የሞቱ ብዙዎች ናቸው፡፡  ስለ ስዌደንቦርጅን ሌላ ጊዜ አጫውታችኋለሁ፡፡

Read 3671 times