በጉብዝናህ ወራት የመጦሪያህን ነገር አስብ! ከድሬዳዋ ጅቡቲ መንገደኞችንና ለንግድ ሥራ የሚንቀሳቀሱ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎችን የሚያመላልሰው ባቡር የዘወትር ደንበኛ ነበሩ፡፡ በድሬዳዋ ከተማም እኔ ነኝ ያሉ እውቅ የኮንትሮባንድ ነጋዴ በመሆናቸው ወ/ሮ ፋጡማ ሮብሌን የማያውቅ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ አልነበረም፡፡ በወጣትነትና በጐልማሳነት የዕድሜ ዘመናቸው ከፊናንስ ወታደሮች እየደበቁ፣ አንዳንዴም እየተሻረኩ ደህና ጥሪት ለመያዝ ችለው ነበር፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱ ከጉምሩክ ፍተሻ ሲያልፍ አትራፊ፣ በኬላ ላይ በሚደረግ ፍተሻ ሲወረስ ደግሞ እጅግ አክሣሪ መሆኑን ቀድሞውኑ ያውቁ ነበርና በየጊዜው የሚያጋጥማቸው ነገር ሣይረብሻቸው ለዓመታት በዚሁ ንግድ ዘለቁ፡፡ የኩባንያ ሠራተኛ የነበሩት ባለቤታቸው በሞት ስለተለዩዋቸውና ሰባቱን ልጆቻቸውን የማሣደጉና የማስተማሩ ኃላፊነት በእሣቸው ትከሻ ላይ ብቻ በመውደቁ፣ ቀን ከሌት ሣይሉ የሚባትሉ ትጉህ ነጋዴ ነበሩ፡፡
በኮንትሮባንድ ንግዱ ላይ የሚደረገው ፍተሻና ቁጥጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሲሄድ ሁሉም ነገር እንደቀድሞው ቀላል አልሆንላቸው አለ፡፡ በደካማ አቅማቸው እሣት ከላሱ ነጋዴዎች እየተጫረቱ የሚያመጡትን ልባሽ ጨርቆች ኬላ ላይ የፊናንስ ወታደሮች ያስቀሩባቸው ጀመር፡፡ ለምግብ እንጂ ለሥራ ያልደረሱት ልጆቻቸው ይህንን የእናታቸውን ችግር ለመረዳት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ አልነበሩምና ችግራቸውን ለብቻቸው ለመወጣት መፍጨርጨራቸውን ቀጠሉ፡፡ ጨከን ብለው የኮንትሮባንድ ንግዱን ጥለው ወደ ሌላ ሥራ እንዳይሰማሩ አልችለውም የሚል ሥጋት ያዛቸው፡፡ ምን አድርጌ? …እኔ … ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሥሠራው የኖርኩትና የማውቀው ሥራ ይህንኑ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ሥራ አላውቅ፡፡ ጭንቀቱ ፈተናቸው፡፡ እስኪ ትንሽ ቀን … ነገ ምን እንደሚመጣ ማን ያውቃል … ተስፋቸውን ሰንቀው ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ አንዴም ሲያስከፋ አንዴም ሲያስደስታቸው የኖረው የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ከቀናቶች በአንደኛው ቀን የመኖር ተስፋቸውን የሚያጨልምና ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል አጋጣሚ ፈጠረባቸው፡፡
ከድሬዳዋ ጅቡቲ መንገደኞችን አሣፍሮ ይጓዝ የነበረው ባቡር በመገልበጡ፣ በባቡሩ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት መንገደኞች አብዛኛዎቹ የሞትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው፡፡ እንደ ዕድል ሆነናም ወ/ሮ ፋጡማ በአደጋው ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ከሞት ከተረፉት መንገደኞች መካከል አንዷ ሆኑ፡፡ ሁኔታው እጅግ አሣዛኝ ነበር፡፡ በአደጋው በወ/ሮ ፋጡማ እግሮችና እጆች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ እነዚያ ሮጠው የማይጠግቡት እግሮቻቸው ያለ ድጋፍ አልንቀሣቀስ አሏቸው፡፡ የሰው እጅ አላይም ብለው ሲታትሩ የኖሩት እናት፤ አካል ጉዳተኝነት ከቤት አዋላቸው፡፡ የወ/ሮ ፋጡማን ቤት ችግር ገባው፡፡ ልጆች ኑሮን ለመቋቋም አቅም አጡ፡፡ ህይወት ፈተና ሆነችባቸው፡፡ የወ/ሮ ፋጡማ ልጆች ይህንን የህይወት ፈተና እንደ እናታቸው ተጋፍጠው ለመቋቋም የሚያስችላቸውን አቅም አላገኙም፡፡ ቀስ እያሉ ከፈተናው እየወደቁ ቀሩ፡፡ ከወለዷቸው ሰባት ልጆቻቸው መካከል ደካማና ህመምተኛ እናትን የመጦርና የመንከባከብ፣ ታናናሽ እህትና ወንድሞችን የማስተማርና የማሣደግ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚችል ልጅ ማግኘት የማይቻል ሆነባቸው፡፡
የሚሆነውን ሁሉ አልጋ ላይ ሆነው ከማየት የዘለለ ነገር የማድረግ አቅም አጡ፡፡ እነዛ የነገን ተስፋ የሰነቁባቸው፣ ተምረውና አድገው ይጦሩኛል ያሏቸውና ያለ አባት ያሣደጓቸው ሰባት ልጆቻቸው በየተራ ይህቺን ዓለም እየተሰናበቷት ሔዱና እናታቸውን ብቸኛ አደረጓቸው፡፡ ህይወት ይብስ ጨለመች፡፡ ሰባት ልጆቻቸውን ሞት የነጠቃቸውን እናት፤ ከልጆቻቸው መካከል አንደኛዋ አያት አድርጋቸው ነበርና ከዚሁ ህፃን ጋር ኦና ቤታቸውን ታቅፈው ቀሩ፡፡ እንደ ቀድሞው እዚህም እዚያም ብለው ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ ነገር ጠፋ፡፡ ይህንን ሁኔታ የተረዱት የአካባቢያቸው ሰዎች እዛው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው “ዳዊት የአረጋውያን መጦሪያ ድርጅት” እንዲሄዱ መከሩአቸው፡፡ ወደ ድርጅቱ ሲመጡም የእሳቸው ዓይነት እጣ ፈንታ የገጠማቸውን በርካታ አረጋውያን በማየታቸው እንደገና የመኖር ተስፋቸው ለመለመ፡፡ ወ/ሮ ፋጡማ ዛሬ በማዕከሉ በየቀኑ ለቁርስ ብቻ የምትሰጣቸውን ምግብ ለመቀበል ማልደው እያነከሱ ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡
ይህቺኑ ከድርጅቱ የምትሰጣቸውን ምግብ ከሚያሣድጉት የልጃቸው ልጅ ጋር እየተቃመሱና ለነፍስ ያሉ በጐ አድራጊ ግለሰቦች በሚያደርጉላቸው የአልባሳት እርዳታ ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ፡፡ እኚህን እናት ያገኘኋቸው Help age Ethiopia የተባለ ድርጅት ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሁለት የአረጋውያን መርጃ ማዕከላትን ባስጐበኘን ወቅት ሲሆን ወ/ሮ ፋጡማ በዳዊት የአረጋውያን መረጃ ማዕከል ውስጥ የሚረዱ እናት ናቸው፡፡ አሰገደች አስፋው የአረጋውያን መረጃ ማዕከልም በጉብኝት ፕሮግራሙ በጋዜጠኞች የተጐበኘ የአረጋውያን መረጃ ማዕከል ነው፡፡ ሁለቱም ማዕከላት በግለሰቦች የራስ ተነሳሽነት የተቋቋሙ ቢሆንም ለአረጋውያኑ የእርዳታ አገልግሎት የሚሰጡት በተለያዩ መንገዶች ነው፡፡ ወ/ሮ ፋጡማ ሮብሌን ያገኘሁበት “ዳዊት የአረጋውያን መርጃ ማዕከል” ለአረጋውያኑ እርዳታና እንክብካቤ የሚያደርገው አረጋውያኑ በመኖሪያ ቦታቸዉ ላይ ሆነው በየዕለቱ ጠዋት አንድ ጊዜ የምግብ አገልግሎት በመስጠት ሲሆን ህክምናና አልፎ አልፎ ደግሞ የአልባሣት ድጋፍም ያደርግላቸዋል፡፡ በወ/ሮ አሰገደች አስፋው መጦሪያ ማዕከል ውስጥ ያየኋቸው አረጋውያን ግን ሙሉ ኑሮአቸው በዚሁ ድርጅት ውስጥ ሆኖ፣ በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ እየተመገቡ የቀንና የሌሊት ልብስ ተሰጥቶአቸው ህክምናም እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡
በሁለቱም የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከላት ዘር፣ ሃይማኖትና ብሔር ቦታ የላቸውም፡፡ 950 አረጋውያን የሚረዱበት የ“ዳዊት አረጋውያን መርጃ ማዕከል” ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት በቀለ እንደነገሩን፤ ማዕከሉ ከተለያዩ በጐ አድራጊ ድርጅቶች የሚያገኘውን እርዳታ ለእነዚህ አረጋውያን እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡ አረጋውያኑን ከአንድ ጊዜ በላይ ለመመገብ የማዕከሉ አቅም አለመፍቀዱን ተነግሮናል፡፡ ከማዕከሉ እርዳታ ከሚያገኙት አረጋውያን ብዙዎቹ ልጆቻቸው በህይወት የሌሉና እጅግ ከፍተኛ በሆነ የድህነት ህይወት ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ በማዕከሉ ውስጥ የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማንም አግኝተናል፡፡ እነዚህ አረጋውያን ከዕድሜያቸው መግፋት በተጨማሪ በሽታው ባስከተለባቸው አዕምሮአዊና አካላዊ ህመም ሣቢያ እንደ ልባቸው ተሯሩጠው የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት አይችሉም፡፡ ማዕከሉ ደግሞ የሚሰጣቸው በቀን አንድ ጊዜ ለቁርስ የምትሆን ሩዝ፣ ዳቦ ወይም ቅንጬ ብቻ ነው፡፡
ይህ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት ለሚገባው የኤች አይቪ ኤድስ ታማሚ የሚበቃ አይደለም፡፡ ሆኖም አረጋውያኑ በዚህች ብቻ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ሰዓቱን ጠብቆ መወሰድ የሚገባውን መድሃኒት ለመውሰድ አረጋውያኑ ምግብ እስኪሰጣቸው አይጠብቁም፡፡ በባዶ ሆዳቸው ይውጡታል፡፡ ይህ ደግሞ ዕድሜ፣ ረሀብና በሽታ ያደከማቸው አረጋውያን አንጀት የሚችለው አይደለም፡፡ ይህንን ሁኔታ ማዕከሉ ታሳቢ አድርጐ በተለይ ለኤች አይቪ ህሙማን የተለየ እንክብካቤና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ ሌላው በዳዊት የአረጋውን መርጃ ማዕከል ውስጥ ያገኘናቸው አዛውንቶች ትልቅ ችግር የመኖሪያ ቤት እጦት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ አረጋውያን ወደ ማዕከሉ የሚመጡት ልጆቻቸውን ወይም ቤተሰቦቻቸውን በሞት ሲነጠቁና ጧሪና ረዳት ሲያጡ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በየእምነት ተቋማቱ ደጃፍ እና በየጐዳው ላይ የወደቁ አረጋውያን ቁጥር በርካታ ነው፡፡ በዳዊት የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ውስጥ ያገኘኋቸው ተረጂ አረጋውያን እንዳጫወቱኝ፤ በቅርቡ ሁለት የዚህ ማዕከል ተረጂ የነበሩ አዛውንቶች በጅብ የመበላት ክፉ እጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ይህ እጣ ፈንታ በሌሎችም በእድሜ በገፉና ጧሪና ቀባሪ ባጡ አረጋውያን ላይ የማይደርስበት ምክንያት የለም፡፡ ሌላው በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ አረጋውያንን ሰብስቦ እርዳታና ድጋፍ የሚያደርግላቸው ማዕከል የወ/ሮ አሰገደች አስፋው የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ነው፡፡
በአንዲት እናት በጐ ፈቃደኝነት የተቋቋመው ማዕከሉ፤ ዛሬ አንድ መቶ ሰላሳ ረዳትና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን ሰብስቦ ይጦራል፡፡ ሰማንያ የሚደርሱትን ደግሞ እዚያው በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እርዳታ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ አሰገደች አስፋው፤ የሞላ ቤት ንብረታቸውን ሸጠው፣ ወርቅና ጌጣቸውን በገንዘብ ለውጠው አረጋውያኑን ወደ መጦርና መንከባከቡ ሥራ ሲገቡ “አበደች” ያላላቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ እድሜያቸው የገፉ ሰዎችን መርዳትና መንከባከብ፣ የተቸገሩን ማገዝ ደስታ ከሚሰጧቸው ተግባራት መካከል ዋንኞቹ ነበሩ፡፡ ይህ በልጅነት እድሜ የተጀመረው ያጡትን የመርዳትና የመደገፍ ፍላጐት እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ አልተዋቸውም፣ እንደውም ሀብትና ንብረትን አስንቆ ከአረጋውያንና ከደካማ ሰዎች ጋር አብሮ መኖር ይበልጥ ደስታ እንዲሰጣቸው አደረጋቸዉ እንጂ፡፡ ልጆቻቸው ከአገር ውጪ ቢሆኑም በእናታቸው ሀሳብና ስራ ላይ ተቃውሞ የላቸውም፡፡ ይልቁንም አቅማቸው በፈቀደ መጠን እናታቸውን ለማገዝ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ይህን የወ/ሮ አሰገደችን ብርቱ ጥረትና ቀና ተግባር የተመለከተው የአለማያ ዩኒቨርሲቲም ለወ/ሮ አሰገደች ሰባት የወተት ላሞችን በእርዳታ ሰጣቸው፡፡ እርዳታና ድጋፍ አድርጉልኝ ማለት የማይሆንላቸው እኚህ ሴት፤ ከብቶቹ ገቢ ለማስገኘት እንዲችሉና በራሳቸው ገቢ ለመተዳደር እንዲበቁ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከሉን ባቋቋሙበት የተንጣለለ ሜዳ ላይ የጓሮ አትክልቶችንና የፍራፍሬ እርሻዎችን ማልማት ጀመሩ፡፡
ከእርሻ የሚያገኙትን ፍራፍሬ ለገበያ በማቅረብ እና ከወተት ላሞቹ ከሚገኘው የወተት ምርት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የወ/ሮ አሰገደችን ሀሳብ ከግብ ለማድረስ አቅም ሆናቸው፡፡ “እኛ እርዳታና ልመና አናውቅም ሠርተን እንኖራለን፡፡ የድሬዳዋ ህዝብ ደግሞ ደግ ነው፡፡ ተለይቶንም አያውቅ፡፡ ሁሌም ከጎናችን ነው” የሚሉት ወ/ሮ አሰገደች፤ ዛሬ ለማዕከሉ ገቢ ማስገኛ የሚሆን የሚከራይ ህንፃ በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ለስራ እንጂ ለወሬ እምብዛም ቦታ የማይሰጡት ወ/ሮ አሰገደች፤ ስለማዕከሉና ስለሚሰጡት እንክብካቤና ድጋፍ ብዙ መናገር አይፈልጉም፡፡ “እኔ ያደረግሁት ነገር የለም፡፡ ሁሉም በፈጣሪና በድሬዳዋ ህዝብ የሆነ ነው፡፡” የሚል ነው ምላሻቸው፡፡ እዚሁ መጦሪያ ማዕከል ውስጥ አግኝቼ ያነጋገርኳቸው አቶ አድነው ሸዋረጋ የተባሉ የ78 አዛውንት ወደዚህ ማዕከል ከመጡ ሶስት አመት እንደሆናቸው አጫውተውኛል፡፡ በማዕከሉ የሚደረግላቸውን እንክብካቤና ድጋፍ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “እኔ ቃል የለኝም፡፡ በህይወቴ ሁሉ ከኖርኩባቸዉ ጊዜያት እዚህ ማዕከል ውስጥ ያሳለፍኩት ሦስት አመታት እጅግ የተለዩና አስደሳች ነበሩ፡፡ ንፁህ በልቼ ንፁህ ለብሼና ንፁህ መኝታ ላይ ተኝቼ እየኖርኩ ነው፡፡ የወጣትነትና የጉልምስና ዘመኔን የኖርኩት ወደፊት ምን ያጋጥመኛል የሚል ስጋትና ሀሳብ ሳይኖርብኝ ነው፤አስቤውም አላውቅም ነበር፤ ለካ ጌታ ይሄን አዘጋጅቶልኝ ነው፡፡ ልጆች አልወለድኩም፡፡
ግን ጧሪና ተንከባካቢ እግዚአብሔር ሰጥቶኛል” ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚኖሩት አራት ሚሊዮን አረጋውያን መካከል አብዛኛዎቹ እጅግ በከፋ ድህነትና ችግር ውስጥ እንደሚኖሩ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ አረጋውያን መካከል መደበኛ ወርሃዊ የጡረታ ገቢ የሚያገኙት 500ሺ ያህሉ ብቻ እንደሆኑና ቀሪዎቹ አረጋውያን ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በሚያገኙት ጥቂት ገንዘብ እንደሚተዳደሩ መረጃው ይጠቁማል፡፡ አረጋውያኑ ከተተኪው ትውልድ ክብርና እንክብካቤ የማግኘታቸው ሁኔታ በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን የጠቆመው መረጃው፤ ለዚህም ምክንያቱ አረጋውያንን የመጦር ባህልና ወግ መሸርሸሩና ቤተሰባዊ ትስስሩ እየላላ መምጣቱ ዋንኞቹ ናቸው ይላል፡፡ አረጋውያን ረዳትና ደጋፊ እንዲያጡ ከሚያደርጓቸው ሌሎች ምክንያቶች መካከል ስደትና ኤች አይ ቪ ኤድስ እንደሚገኙባቸው የጠቆመው መረጃው ፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ስራና ትምህርት ፍለጋ ወደ ዋና ከተሞች የሚፈልሱ ወጣቶች አዛውንት ወላጆቻቸውን ለከፋ ድህነትና ረጂ አልባነት እንደሚዳርጓቸው አመልክቷል፡፡
ትኩስ የወጣትነት ጉልበትና ብሩህ አእምሯቸውን ለሀገራቸውና ለወገናቸው ዕድገትና መሻሻል ሲገብሩ ኖረው የዕድሜ ጀምበራቸው ስታዘቀዝቅ፣ ጉልበታቸው ሲደክም፣ ጧሪና ተንከባካቢ ሲያስፈልጋቸው፣ ጀርባችንን ልንሰጣቸው አይገባንም፡፡ እነዚህ ሁለት በግለሰቦች ተነሳሽነት የተቋቋሙት የአረጋውያን መርጃ ማዕከላት በስፋት ሊሰራባቸውና በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ መንግስትም ሆነ ዜጎች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት ያሻል፡፡ የዛሬው ወጣት የነገ አረጋዊ መሆኑ አይቀርምና በጉብዝና ወራት የመጦሪያን ነገር ማሰቡም ተገቢ ነው፡፡