Saturday, 21 October 2023 19:55

‘እርካታ’ን ሳይመነትፉን አይቀርም!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…. ሳልረሳው…. ዘንድሮም ይሄ የ‘ሀበሻ’ ስምን ‘ፈረንጅኛ’ ማድረግ አልቀረም እንዴ! (አንቺ እንትናዬ… ዋናው ስምሽ ምንም የ‘መ’ ወይም የ‘ገ’ ዘር የለው። ታዲያ ‘ሜግ’ የሚሉሽ… በየትኛው ሂሳብ ነው?) በቃ… የራሳችን ስምም አያረካን?
የምር አይገርማችሁም…. ዘንድሮ ስብሰባ ላይ እንኳን ሙሉ ለሙሉ በአማርኛ መናገር ‘የማያረካን’ መዓት ነን። “የዚህ ስብሰባ ሜይን ፐርፐዝ ያለፉትን ስድስት ወራት ፐርፎርማንስ አናላይዝ አድርጎ…. ለችግሮቻችን ሶሉሽን ለመፈለግና…” ብቻ ምን አለፋችሁ… ትንሽ ‘ፈረንጅነት’ ካልጨማመርን አንረካም።
ለነገሩ… አለ አይደል… ዘንድሮ ምንም ነገር የሚያረካን አይመስለኝም። ‘ባለህ መርካት’ የሚሉት ነገር አለ አይደል!... እዚህ አገር አይሰራም- ለቲያትር ካልሆነ በስተቀር። “የዘንድሮ ቡና አያረካም” የሚል ወዳጅ አለኝ። እንዴት ነው ነገሩ … ማለቴ… ከዋጋ ጋር ጣዕምም ይከስራል እንዴ! “አይደለም… አንድ… አሥራ አንድ ስኒ ቢመጣ የዘንድሮ ቡና ነቃም አያደርግ” ይሏችኋል። (ለካ ድሮ የቀረው ‘ዝንብ’ ብቻ አይደለምና!) ለነገሩ አንዳንድ ቦታ ‘ቡና’ ብለው የሚሰጧችሁ… አለ አይደል… ገብስ ይሁን…. ዘንጋዳ ይሁን… ‘የተቆላ’ በቆልቲ ይሁን… አታውቁትም። አሀ… ታዲያ ጣዕሙ ሳይኖር እንዴት እንርካ!
የምር ግን ምን መሰላችሁ… የፈለገ ነገር ቢኖር ሁልጊዜ በመስኮት ወደ ሌላው ሰው ቤት ስለምናይ… እንዲሁ “ወይኔ…” እንዳልን እንኖራለን። እነእንትና ቤት አዲስ ጭልፋ በተገዛ ቁጥር… እነእንትና ቤት ደግሞ “እሷ የገዛችው ጭልፋ እኔን ያቅተኛል?” እየተባለ… እርካታ ከየት ይምጣ!
እና… ብቻ ምን አለፋችሁ… ለምን እንደሆነ እንጃ’ንጂ… ‘እርካታ’ የሚባለውን ነገር … ‘ታሪካዊ ጠላቶቻችን’ ሳይመነትፉን አይቀሩም። አሀ… ታዲያ ሁሉም ቤት ይጠፋል እንዴ! የሚገርም’ኮ ነው… በአሪፍ እንትናዬ እንኳን መርካት ቀርቶ (ባይመነዘርብኝ!) አይ ‘ሼፕ’… ‘ስማይል’ ምናምን ቀርቶ ቢያንስ፣ ፋዘርዬዋ  ቡቲክ ያላቸው…” ይባል ነበር። ዘንድሮ ልጄ… አይደለም ፋዘርዬዋ… ዘመዶቿ ሁሉ ቡቲክ ቢኖራቸውም አይሰራም። ዘንድሮ ለ‘ተመላላሽነትም’ ሆነ ‘አዳር ከቤት’… ራሷ ቡቲክ ያላት እንትናዬ መሆን አለባት። አለበለዛ በተዘዋዋሪ ‘ሀብት’ መኩራት ቀራ! (ልጄ… ሙሉ ልብስ ‘ሽልማት’ ቢገኝ’ንኳ እያለ… አብሮ ሱቅ የሚከፍትና የሚዘጋ ስንት አለ መሰላችሁ!)
እኔ የምለው… እጅ ላይ ባለው ረክቶ…አለ አይደል… ‘ሌላ’ ማሰብ ሲቻል… በገዛ እጅ ‘ሰቆቃ’ ‘ፌይር’ አይመስለኝም። አሁን ለምሳሌ ባለ 47 ኢንች ቴሌቪዥን ስለሌለ… “ዘላለሜን ከሰው በታች…” እያሉ ማማረር… ብቻ ምን አለፋችሁ… በሆነ ዘዴ ‘እርካታ’ የሚባለው ነገር ተሰርቆ ተወስዶብናል።
አሁን እኛ በ47 ኢንች ቴሌቪዥን የሚታይ ነገር አለን?...ቂ…ቂ…ቂ… (እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ አይደል የሚያነሳው… እናንተ ድምጻውያን  ‘ሲስሟችሁ’ ትወዳላችሁ እንዴ! አሀ… ያስብላላ! አዳሜ ተራ በተራ እየወጣ ሲፈራረቅባችሁ… ትንሽም ሰቅጠጥ የማይላችሁ። ልጄ… ዘንድሮ ጠንቀቅ ነው ደጉ። እንዲሁ መመጭመም … ኋላ ነገር እንዳያመጣ… ደግሞ እናንተ ሴት ድምጻውያን… ስንቶቻችን መከራውን ስናበላው የከረመ… ምን ‘የነካው ነገር እንዳለ የማይታወቅ ብር’ ‘ብሬስታችሁ’ መሀል ሲወሸቅ… ትንሽም መከላከል የለም እንዴ! ብቻ… ተውት። ወደው ‘ለተሳሙት’ እኔ ምን ቤት ነኝ!)
ከዘፈን ሳንርቅ… አሁን በዘንድሮ ሙዚቃ የማይረኩ መዓት አሉ። “የዘንድሮ ዘፈን ወረርሽኝ ነው…” የሚል ወዳጅ አለኝ። በቃ… የሆነ ሙዚቃ አንድ ሰሞን ድፍን አገሩን ያጥለቀልቅና… ከዛ በቃ… እስከ ወዲያኛው ይጠፋል።
የምር’ኮ ግን ዘንድሮ ነገሬ ብላችሁ የዘፈን ግጥም ስትሰሙ… አለ አይደል ሁሉም ባይሆኑ… አንዳንዶቹ “ግጥም እንዲህም መጻፍ  ተጀመረ እንዴ!” የሚያሰኙ ናቸው። አሁን ለምሳሌ… ድሮ ለ‘ላቭ’ ሲዘፈን… ‘እርቦኝ’ “ጠኔ ይዞኝ” ምናምን የሚባል ነገር የለም።
ስለ ‘ፍቅር ረሀብ’ እንኳን ሲወራ በዘወርዋራው “ምግብማ ሞልቷል…” እየተባለ ነው። ዘንድሮ ግን… አለ አይደል… ምን ይሁን ምን ‘እርቦኛል’ ማለት ብቻ። የ‘ፍቅር’ መሆኑ በዘዴም ይገለጽልናል። አለበለዛ…”ከቻልሽ ስንዴ ካልቻልሽ ዘንጋዳ ስፈሪልኝ…” ማለት ቂ…ቂ…
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የዘንድሮ ሙዚቃ ምንም የማያረካቸው ሞልተዋል።
ብቻ ምን አለፋሁ… ችግር ነው። እርካታ ስለፈለጉት ብቻ አይገኝም። አሁን ለምሳሌ አሪፍ አሪፍ የአማርኛ ፊልሞች ይሰራሉ፡፡ ግን ሁሌ አይሳካ አይደል… ‘ጥሩ ፊልም አይቼ መንፈሴን ላርካ’ (ይባላል እንዴ!)
 ብላችሁ አንዱን አዲስ ፊልም ማየት ትጀምራላችሁ። ምን ያደርጋል… ፊልሙ ሄዶ፣ ሄዶ ታሪኩ ዋና ክፍል ላይ ሲደርስ ምን ይሆናል መሰላችሁ? ድምፁ ድርግም ብሎ ይጠፋላችኋላ። ከዚያ-- ሦስት ደቂቃ ታሳልፉትና ደሞ ይመጣላችኋል፡፡  አስራ አምስት ደቂቃ ታዩና ደሞ … ተመሳሳይ ችግር!
አለበለዛ ደግሞ… ዋናው ድርጊት ላይ ደረሰ ስትሉ… ይሙት፣ ይዳን፣ ይሩጥ ሳታውቁ ዘሎ ወደ ሌላ ድርጊት ይዘልላል፡፡ ልክ እኮ ከገጽ 40 ወደ ገጽ 66 እንደመዝለል ነው። እንግዲህ… ይሄ ፊልም መቁረጥ የሚሉት ነገር አላቸው- በመቀስ! አንዳንዱን ፊልም ስታዩ ግን… አለ አይደል… አይደለም በመቀስ… በገጀራ የከተፉት ነው የሚመስለው፡፡ እናላችሁ ‘ለእርካታ’ ባያችሁ… እንደ ፊልሙ አንጀታችሁ ‘ብጥስ’ ብሎ ታርፉታላችሁ።
ብቻ… ለምን እንደሁ እንጃ… የምናረካ ሰዎች የለን… የሚያረካ አገልግሎት የለ… የሚያረካ ‘እቃ’ የለ… ነው፣ ወይስ ጥሎብን “እኔን ለቸገረኝ ለበላሁት ሽምብራ…” ማለት ስለምንወድ ይሆን!?
አንተ ወዳጄ… ሁሉንም “ዮናኒመስሊ” የሚያረካ ነገር አውቃለሁ ያልከኝ… የ‘ሆዳችንን አንብበህ’? ነው እንዴ!? ቂ… ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1085 times