Sunday, 12 May 2024 20:11

ሰሙነ ሕማማት እና የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ

Written by  እንዳለጌታ ከበደ
Rate this item
(1 Vote)

 (ክፍል ሁለት)

በሀዲስ ኪዳን ውስጥ በጨረፍታም ሆነ በምላት፣ ስማቸው ከተጠቀሱ ‹ሰዎች› መካከል ይሁዳ እና በርባን የደራስያንን ቀልብ ሲስቡ እናነባለን፡፡  በተደጋጋሚ ሕይወታቸው ሲዘከርና ሲፈከር እናያለን - በተለይ በሕማማተ ሰሞን፡፡
አንዳንዶቹ ደራስያን በስፋት የሚታወቀውን ታሪክ ለማብራራት ሲተጉ፣ አንዳንዶች ደግሞ በወንጌል ከተጻፈው በተቃራኒ ወገን ቆመው ‹ይፈጥራሉ›፤ በዚህ የተነሳ ይርቁናል፤ ይርቁብናል፡፡ ዛሬ ሦስት ትርጉም የሆኑ ልብወለድ መጻሕፍት ላይ ብቻ - ያውም በወፍ በረር እይታ - ማተኮር ወደድኩ - ባለፈው ዕትም ተመልሼ እመጣለሁ ብዬ ቃል በገባሁት መሰረት፡፡
ዐቢይ ደምሴ የታዋቂው ደራሲ የፓር ላገርቪስትን (Par Lagerkvist) ‹ባራባስ› የተሰኘውን ልቦለድ ተርጉሞ ለንባብ ያበቃው በ1988 ዓ.ም ነበር፡፡ ደራሲው የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነው፡፡  እርግጥ ልቦለዱ በሌላው ዓለም በተሰጠው ክብር ልክ እኛ አገር በበቂ ሁኔታ ቦታ ተሰጥቶታል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ እንደሌሎቹ የተርጓሚው ሥራዎች (‹ብርቅርቅታ›ንና ‹ጃኩሊን›ን ልብ ይሏል) ‹ባራባስ› እምብዛም ሲነገርለት አይደመጥም፡፡ ምናልባት አሳታሚው ጌጃ ቃለሕይወት ቤተክርስቲያን ሥነጽሑፍ ክፍል ሥርጭቱን በውስን ቦታ በማድረጉም ሊሆን ይችላል፡፡
የሆነው ሆኖ ‹ባራባስ› (በርባን እንደማለት ነው)፣ ‹በርባንን ፍታልን፤ ኢየሱስን ግን ስቀለው!› በሚለው ሕዝባዊ ጩኸት ላይ መሰረቱን የጣለ ልቦለድ ነው፡፡ ኢየሱስ ተሰቀለ፤ በርባን ተፈታ፡፡ ከዚያስ? የበርባን ሕይወት ምን መስሎ ቀጠለ? ነው፣ ዋናው ታሪክ፡፡ ቀጣይ ሕይወቱ እንዴት ሆነ? እንደ በፊቱ ወንበዴነቱን ገፋበት? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መልኩ አልነገረንም፤ አልነገረንም ማለት ግን የጠለሸ ታሪክ ተተርኮበታል ማለት አይደለም፡፡ ደራሲው ግን በበርባን ሕይወት ያንን ዘመን፣ ያን ክርስቶስ ትቷት የሄደችውን ዓለም ይዳስስልናል፡፡ የሰቃዮች ድምጽ ተጽፏል፡፡ ደራሲው የተሰቀለውን ብቻ አይደለም የተከተለው፡፡


ተራው ሰውስ ምን አለ? በየመሸታ ቤቱ፣ በየአውራ ጎዳናው ምን ተወራ? በከተማው ስለተሰቀለው ሰው፣ ሀዘኔታዎች፣  ቁዘማዎች፣ መከፋቶች፣ የድባቴ ድምጾች ነበሩ? ወይስ ‹እሰይ የት አባቱ› ዓይነት ድምጾች? በርባን በሕይወት እያለ ቦታ ያልሰጠው ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላ ግን እጅጉን መረመረው፡፡
እርግጥ ባርባን በስተመጨረሻ  መሰቀል አልቀረለትም፡፡ ወንበዴነቱ ተደምስሶ ራሱን ለአዲስ ተልዕኮ ካዘጋጀ በኋላ ነው፣ ክርስቶስን በመከተሉ ከሃዋርያው ጴጥሮስ ጋር ተቆራኝቶ እንዲሰቀል የተፈረደበት፡፡ የደራሲው ትኩረት ግን ግልጽ ነው - ‹ወደ ጌታ ተመለሱ› የሚል መልዕክት ማስተላለፍ፡፡
ሌላኛው መጽሐፍ ‹ኢየሱስ - የሰው ልጅ›  (Jesus –The Son of Man) የተሰኘው ነው፡፡ ይህ ድርሰት ካህሊል ጂብራን ከጻፋቸው ዕውቅ ልቦለዶች መካከል አንዱ ነው፤  ወደ አማርኛ ቋንቋ አሳምሮ የተረጎመው ደግሞ ጲላጦስ ነው - ኃይለጊዮርጊስ ማሞ፡፡  መጽሐፉ ደቀመዛሙርቱ፣  አርድዕቱ፣  ነጋዴው፣ መድኃኒት ቀማሚው፣  እረኛው፣ ራሱ ደራሲው የፈጠራቸው በሚመስሉ ገጸባህርያት… ኢየሱስን እንዴት እንዳወቁት፣ ከምን ወደ ምን እንደመለሳቸው፣ የበፊት ሕይወታቸውና አሁናዊ ገጽታቸው ምን እንደሚመስል ያሳየናል፡፡ እያንዳንዱ ባለታሪክ ‹እኔ› እያሉ ነው የሚተርኩት፡፡  እያንዳንዱ ትረካም በራሳቸው እግር ሲቆሙ የማይወለካከፉ፣ አንድ ላይ ተጣምረው ሲቀርቡ ደግሞ ህብረ ዝማሬያዊ መልክ የሚሰጡ፡፡
የዚህኛው መጽሐፍ ግብም እንደ ባራባስ ነው፤ ምንም እንኳን ቋንቋው (ለምሳሌ ማርያም መግደላዊት ራሷን ‹ከነፍሴ ጋር ፍቺ የፈጸምኩ ሴት ነበርኩ› …‹የአይኖቹ ጨረር  በውስጤ የነበረውን ዘንዶ ሲውጠው ተሰምቶኛል› በማለት ትገልጻለች፡፡)፣  አገላለጹ ጣፋጭ ቢሆንም፣ ዋናው ግቡ፣ አንባቢው መስቀሉ ስር እንዲገኝ ለማድረግ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ፣  በርባንን ራሱን ሲገልጽ ፣ ‹‹አሁን በእኔ ፋንታ እሱን የሰቀሉት ሰዎች ለእኔ የዘላለም ስቃይ እንዳስቀመጡልኝ ተረዳሁ፡፡ የእሱ ስቅለት የቆየው ለአንድ ሰዓት ብቻ ነበር፡፡ እኔ ግን እስከዘመኔ ፍጻሜ ድረስ እንደተሰቀልሁ አለሁ!›
በተለይ የይሁዳ እናት የታየችበት ዕይታ አጃኢብ የሚያሰኝ ነው፤ ሀዘኗ ይጋባል፤  ደራሲው በማርያም ልክ ሊታዘንላት የሚገባ ዓይነት እናት አድርጎ ነው የቀረጻት፡፡ ለእናት፣ መሲህም ይሁን ከሃዲ፣ የልጅ ሞት እኩል ነው ሕመሙ፡፡


በመጽሐፉ ስለኢየሱስ ይነገርበታል እንጂ ኢየሱስ ሲናገር አናነብም፤ በአጭሩ ኢየሱስ በተለያዩ ማዕዘናት ነው የተቃኘው፡፡ ይሁዳ በሃይማኖት ትምህርት ለሰላሳ ዲናር ብሎ ጌታውን አሳልፎ እንደሸጠ ሲሰበክ ይሰማል፡፡ ጂብራን ግን ይሁዳ ጌታውን የሚሸጠው በአፍቅሮተ ንዋይ ስለተለከፈ አይደለም፡፡ ራሱ ይሁዳ ራሱን በድንጋይ ፈጥፍጦ ከማጥፋቱ በፊት፣ ‹‹የይሁዳ ንጉሥ እንደሚሆን ተስፋ ያደረግኩበት ይኸ ሰው እያደር የተንከራታቾችና የወንበዴዎችን ልብ የሚያለሰልስ ዋሽንት ተጫዋች መሰለኝ›› ሲል ያስደምጠዋልና፡፡
ሌላው ሦስተኛው ሰሙነ ህማማት ተኮር መጽሐፍ ‹የመጨረሻው ፈተና› (The Last Temptation of Christ) የተሰኘው ነው፤ ይህ መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ የበቃ ኒኮስ ካዛንታኪስ የጻፈው ልቦለድ ሲሆን፣ ተርጓሚው ደግሞ ማይንጌ ነው፡፡
መጽሐፉ በአጭሩ የጦርነት መጽሐፍ ነው፤ ጦርነቱም መንፈስና ስጋ የሚያደርጉት ነው፡፡ የጨለማና የብርሃን፡፡ ‹‹የውስጤ ስቃይ በጣም ኃይለኛ ነው፤ ስጋዬን እወደዋለሁ፤ እንዲጠፋ አልፈልግም፤ ነፍሴንም እወደዋለሁ እንዲበሰብስ አልፈልግም›› ይላል፣ ደራሲውም በመቅደሙ፡፡
መጽሐፉ ከጊዜ ጋር የሚደረግ ትንቅንቅ ነው፤ ባለታሪኩ ሰላሳ ሦስት ዓመቱ ነው፤ መጽሐፉም በሠላሳ ሦስት ምዕራፍ መቀንበቡም አለምክንያት አይደለም፡፡
እርግጥ እኔ በበኩሌ ክርስቶስ በምድር ሳለ ሰውም አምላክም ነበር ብለው ከሚያምኑት ወገን ነኝ፡፡ መለኮታዊ ኃይሉ በብዙ መንገድ ሲተነተን አንብቤያለሁ፡፡ ሰውነቱ (ስጋ ለባሲነቱን) በዚህ ልቦለድ ልክ የገለጠለኝና ህመሙን የታመመልኝና ያጋባብኝ ግን አልገጠመኝም፡፡ ያ ማለት በተጻፈው ሁሉ እስማማለሁ ማለቴ አይደለም፤  ደራሲው ሰው አድርጎ ሲጽፈው የደነገጥኩባቸው ገጾች መኖራቸውን መካድ አልፈልግም፡፡
በዚህ በመጨረሻ ፈተና በይሁዳ እና በክርስቶስ መካከል ያለው ወዳጅነት በክርስትና አስተምህሮ ከምንሰማው በተገላቢጦሽ ነው የተጻፈው፤ የተጻፈው ማለቴ ይሁዳ በዘመኑ ተወዳጅ ተከታዩ ነበር ማለቴ አይደለም፤ ሃዋርያቱ ይሁዳን የሚያዩበት መንገድ ዛሬ ዛሬ ብዙዎቻችን እሱን እንደምንረዳው ነበር፡፡ ክርስቶስስ? ክርስቶስማ ሲያቀርበው፣  ሲያበቃው ነው የሚታየው፡፡
ኢየሱስ፣ ‹‹…ምንም ዓይነት ሌላ መንገድ የለም፤ አትርበድበድ፤ ይሁዳ የኔ ወንድም በሦስት ቀናት ውስጥ እንደገና እነሳለሁ›› አለ፡፡
ይሁዳም፣ ‹‹ይሄንን የምትነግረኝ ልታጽናናኝና ልቤን ሳይከፋው እንድከዳህ ለማድረግ ነው፡፡  ጽናት አለህ ብለኸኛል-  ይህን ያልከው እኔን ልታበረታኝ ነው፡፡ በፍጹም፣ ወደ ቁርጡ ጊዜ ስንቃረብ---በፍጹም፣ መምህር ልቋቋመው አልችልም!›› አለ፡፡
‹‹ትችላለህ ይሁዳ የኔ ወንድም፡፡ ፈጣሪ አንተ ያጣኸውን ያህል ብርታት ይሰጥሃል፡፡ ምክንያቱም አስፈላጊ ስለሆነ-ለእኔ መሞት አስፈላጊ ሲሆን፣ የአንተም እኔን መካድ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለታችን ዓለምን ማዳን አለብን፡፡ እርዳኝ!›› አለው፡፡


ይሁዳ አንገቱን ደፋ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጠየቀ፡፡ ‹‹አንተ በኔ ቦታ ሆነህ ጌታህን ካድ ብትባል ታደርገዋለህ?›› አለው፡፡
ኢየሱስም ለረጅም ጊዜ አብሰልስሎ በመጨረሻም ‹‹በፍጹም! እኔ የማደርገው አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው ፈጣሪ አዝኖልኝ ቀላሉን ተግባር የሰጠኝ- መሰቀሉን!›› አለ፡፡ (ከገጽ 402-403)
በዚህ ልቦለድ የማርያም ህመም እጅጉን ይጋባል፤ ለእሷ መሲህ እንዲሆንላት አይደለም ምኞቷ - ሰው ሆኖ፣ አግብቶ ወልዶ፣ የልጅ ልጅ እንዲያሳያት እንጂ፡፡ እና መሲህ ነው ከተባለች ጊዜ ጀምሮ  በመቃተት ነበር፣ ህይወቷን ያሳለፈችው፡፡ እሱ ራሱ መሲህ እንደሆነ ያወቀው ዘግይቶ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አይደለም የሚሰቀልበትን ቀን እያሰበ የቆየው፡፡ እሱ ራሱ መሲሁን ተጠባባቂ ነበር፡፡
መጽሐፉን ስናነብ በክርስቶስ ዙርያ የተሠሩ  አብዛኞቹ ፊልሞች በበቂ ሁኔታ ቅዱስ ተጋድሎውን እንዳልገለጹት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡  ጦርነቱ በግልጽ ይታያል፤ መታየቱ ብቻ አይደለም፣ ተሳታፊም ያደርጋል፡፡ በነጻ ስሜት ከተነበበ እምንታገልለትና እምንጋደልለት ተልዕኮ እንዴት ‹ሰውነት›ን እንደሚፈታተንና ያንን ፈተና መወጣት ጀግንነት መሆኑን ይመሰክራል፡፡
(በነገራችን ላይ ተርጓሚው አይደፈሬውን በመድፈሩ ብቻ አይደለም የምናደንቀው፤  …. ሥነጽሑፋዊ ውበቱ፣ ሙዚቃዊ ቃናው፣ ለዛው ሳይሟጠጥ ነው ልቦለዱን ያቀረበልን፡፡ የትርጉሙ ከፍታ ከዚህ ቀደም  ዘመን አይሽሬ  ሥነጽሑፋዊ ሥራዎችን ተርጉመው ካስነበቡን ከእነ ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም እና መስፍን ዓለማየሁ ተርታ የሚያስመድበው ሆኖም አግኝቸዋለሁ፡፡)
***
ከአዘጋጁ፡-  እንዳለጌታ ከበደ፤  የ14 መጻሕፍት ደራሲ ሲሆን፣  ከሥራዎቹ መካከል፣ ‹ከጥቁር ሰማይ ሥር›፣ ‹ደርሶ መልስ›፣  ‹በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ› እና  ‹ኬር  ሻዶ›.  ይጠቀሳሉ፤  የዛጎል የመጻሕፍት ባንክ መሥራች፣  የነገረ መጻሕፍት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፤ የፎክሎርና የሥነጽሑፍ ተመራማሪም ነው፡፡


Read 274 times