Administrator

Administrator

 ከጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም  ጀምሮ በጎንደር ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከናወን የቆየው የጥምቀት ክብረ  በዓል ያላንዳች የፀጥታ ችግር   መጠናቀቁ ተገልጿል። ከተማዋ ለበዓሉ 1.5 ሚሊዮን እንግዶችን ጠብቃ የነበረ ቢሆንም፣ በበዓሉ የታደመው  ግን ከተጠበቀው ቁጥር በላይ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
  በህዝቡ ትብብር በአመራሩ ቅንጅትና በወጣቶችና  በፀጥታ አካላት ብርቱ ስራ በዓሉ ያለምንም ኮሽታ መጠናቀቁን  የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት ተናግረዋል። በዕለተ ጥምቀት በፋሲል ጥምቀተ ባህር ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ይልቃል (ዶ/ር)፤ የውጭ ጠላቶቻችን በሚያሰራጩት የሃሰት መረጃ ምክንያት የተጠበቀውን ያህል የውጪ ቱሪስቶች ባይገኙም፣ ከተገመተው በላይ  ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ ጥግ የመጡ ወንድምና እህቶች በበዓሉ መታደማቸውን ጠቁመው፤ ይህም እንደ ሃገር የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡
የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ጦርነቱና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ  በከተማውና በአካባቢው የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ማነቃቃቱም ተነግሯል።
ባለፈው አንድ ሳምንት የከተማው ሆቴሎች፣የባጃጅና የታክሲ አሽከርካሪዎች፣ የባህል ምሽት ቤቶች፣ ቡና ጠጡ ቤቶች፣ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆችና  በአጠቃላይ ሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች የጥምቀትን እንግዶች በማስተናገድ ስራ ላይ ተጠምደው   የሰነበቱ ሲሆን በዚህም ሁሉም በየፊናው ተጠቃሚ መሆኑ ታውቋል፡፡
 በክልሉ እስከ ቅርብ ጊዜ  ድረስ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መነሳቱና የፀጥታ አካላት የነቃ የፀጥታና የደህንነት ጥበቃ ስራ ዳያስፖራውም ሆነ የሃገር ውስጡ የበዓሉ ታዳሚ እንደልቡ እንዲንቀሳቀስና እንዲዝናና ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ያነጋገርናቸው እንግዶች ነግረውናል።
በተያያዘ ዜና፤ ከጥምቀት በዓል መጠናቀቅ በኋላ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ትብብር  “ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሃገራችን ዲፕሎማሲ፣ ሰላምና ልማት ላይ የሚኖራቸው ሚና እና በጎንደር ከተማ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች” በሚል ርዕስ በሐይሌ ሪዞርት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር  የውይይትና የምክክር መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመድረኩ  በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በከተማዋ ባሉ የኢንስትመንት አማራጮችና በዲያስፖራው ሚና ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ጥናት በማጥናትና በማማከር ድጋፍ እንደሚያደርግ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደ ወይን  ቃል ገብተዋል። በዚህ መድረክ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ፣የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ም/ከንቲባና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ዘውዱ ማለደ፣ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ኘሬዚዳንት አስራት አፀደወይን እና ሌሎችም በርካታ እንግዶች ታድመዋል።
የዲያስፖራው ተወካዮች በበኩላቸው፤ በሃገራቸው ባሉት አማራጮች ኢንቨስት ለማድረግና በዲፕሎማሲውም ረገድ አበክረው ለመስራት ቃል ገብተዋል። በቀጣዮቹ ቀናትም ወልቃይትና አካባቢውን እንደሚጎበኙ ታውቋል፡፡


  ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የኢንተርኔት ግንኙነትን  በማፈን ናይጀሪያና ኢትዮጵያ በቀዳሚነት በተጠቀሱበት ሪፖርት፣ ከሠሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት በዚሁ የአፈና ተግባራቸው በአጠቃላይ 1.93 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣታቸውን በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ የሚደረግለት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ተቋሙ ባደረገው ጥናት፣ ከሠሃራ በታች ካሉ ሃገራት የኢንተርኔት አገልግሎትን ሆን ብሎ በማፈን ናይጄሪያ ቀዳሚ ስትሆን፤ ኢትዮጵያ በሁለተኛነት ተጠቅሳለች፡፡
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በ2021 በኢትዮጵያ ለ8 ሺህ 760 ሰዓታት ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ዝግ መደረጉን ተከትሎ ሃገሪቱ ታገኛው የነበረውን 164.5 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች፡፡
144 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚ ዜጎች ያሏት ናይጀሪያ ደግሞ በዓመቱ ለ5 ሺህ  40 ኢንተርኔት በማቋረጥ 1.45 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሃገራቱ ኢንተርኔትን ለማቋረጥ ምክንያት  ተብለው ከተጠቀሱት በዋናነት የፖለቲካ መብቶችን ለመገደብ የሚደረግ ጥረት ተጠቃሽ ሆኗል፡፡
ሃገራቱ ኢንተርኔትን በሚገድቡበት ምክንያት 69 በመቶ የመሰብሰብ መብትን ለማፈን፣29 በመቶ በምርጫ ጉዳይ የሃሳቦች መንሸራሸርን ለመገደብ እንዲሁም 29 በመቶ የፕሬስ ነፃነትን ለመገደብ በማሰብ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ  በትግራይ የአማፂያንን እንቅስቃሴ ለመገደብ ኢንተርኔት ማቋረጡን አመልክቷል፡፡
ኢንተርኔት ይገድባሉ ተብለው በሪፖርቱ ስማቸው ከተጠቀሱ ሃገራት መካከል  ደቡብ አፍሪካና ኬኒያም ይገኙበታል፡፡


በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ሐሙስ ዕለት የወይብላ ማርያምን ታቦት በማስገባት ሥነ ሥርዓት ላይ በምእመናንና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱና  የአካል ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡
የወይብላ ማርያምን ታቦት በማስገባት ሥነ ሥርዓት ላይ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግርግርና አለመግባባት፣ የፀጥታ ኃይሎች ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ መተኮሳቸውንና በዚህም ሳቢያ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን በሥፍራው የነበሩ ምዕመናን ተናግረዋል፡፡  
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመላው አገሪቱ የተከበረውን የጥምቀት በዓል አስመልክቶ ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ በሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ መከበሩን ጠቁሞ፤ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና በቡራዩ አዋሳኝ ወይብላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉንና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ገዳመ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ወንጌል የሆኑት መምህር እሱባለው፤ የወይብላ ማርያምን ታቦት ካደረበት ወደ መንበሩ ሲመልሱ መንገድ ላይ በወጣቶችና በፀጥታ አካላት አታልፉም ተብለው መከልከላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሺ ደበሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ አታልፉም ብለው የከለከሉት የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች፤ ካህናትና መዘምራን እንዲያልፉ ፈቅደው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉባቸውን አልባሳት የለበሱትን ግን እንደማያሳልፉ ተናገሩ ብላለች፤ ንግስት የተባለች ምዕመን ለቢቢሲ፡፡  
“አብዛኛው ምዕመን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ያለበት ቀሚሶችን፣ ቲሸርቶችን ለብሷል። እነሱ ደግሞ መርጠን እናስገባለን አሉ። አስተባባሪዎቹ አልተስማሙም። ከዚህ ንግግር በኋላ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ተጀመረ። የወደቁና የተረጋገጡ አሉ”ስትል ሁኔታውን አስረድታለች።
“ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተመሳሳይ ችግሮች ሲከሰቱ ነበር፤ እኔ እንኳ በማውቀው ይሄ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በጉዳዩ ላይ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ሲሞከር ‘ከላይ ነው የታዘዝነው’ የሚል ምላሽ ብቻ ነው የሚሰጡት”ብለዋል፤መምህር እሱ ባለው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን፤ በተከሰተው ችግር ምክንያት በዓሉ በመስተጓጎሉ  እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፤ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለአካል ጉዳት ምክንያት የሆነውን ክሥተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለሕግ እንደሚቀርቡም በመግለጫው አመልክቷል።
ሐሙስ በተፈጠረው ግርግር  ቀራንዮ መድኃኔዓለም ያደረችውን ወይብላ ማርያም ታቦትን ለማስገባት አርብ ጠዋት በርካታ ምዕመናን በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ታቦቱን ሸኝተው በሰላም ሥነሥርዓቱ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡



በፊልም ገቢና በሲኒማ ቤቶች ብዛት ከአለም 1ኛ ደረጃን ይዛለች በአገሪቱ 82,248 ሲኒማ ቤቶች ይገኛሉ

         የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአለማችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ክፉኛ በጎዳበት ያለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በአገረ ቻይና 6 ሺህ 667 አዳዲስ ሲኒማ ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውና አገሪቱ በአመቱ ከቦክስ ኦፊስ 7.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ከአለም አገራት 1ኛ ደረጃን መያዟ ተነግሯል፡፡
ቻይና በ2021 የፈረንጆች አመት ከቦክስ ኦፊስ ካገኘችው አጠቃላይ ገቢ 85 በመቶ ያህሉን ያገኘችው በአገር ውስጥ ከሰራቻቸው ፊልሞች መሆኑን የዘገበው ግሎባል ታይምስ፣ በአመቱ 6 ሺህ 667 አዳዲስ ሲኒማ ቤቶችን መክፈቷንና የሲኒማ ቤቶቿን አጠቃላይ ቁጥር ወደ 82,248 ከፍ በማድረግ ባለብዙ ሲኒማ ቤት አገር ለመሆን መብቃቷንም አመልክቷል፡፡

 በፍጥነት በመስፋፋት ላይ የሚገኘውና ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ  በአውሮፓ አገራት ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱ የሚነገርለት አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን፣ እስከ መጪዎቹ 2 ወራት ከአህጉሩ አጠቃላይ ህዝብ ግማሽ ያህሉን ሊያጠቃ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
ቫይረሱ በተለይ በአውሮፓ አገራት በከፍተኛ ሁኔታ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው የአለም የጤና ድርጅት፣ እስካለፈው ሰኞ ቫይረሱ በሳምንት የአገራቱን 1 በመቶ ህዝብ ሲያጠቃ እንደነበር ማስታወሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ባለፈው ማክሰኞ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ232 ሺህ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፣ ወደ 200 ሚሊዮን የሚደርሱ ክትባቶች መሰጠታቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከአለማችን አገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ገደብ በመጣል ቀዳሚዋ እንደሆነች የሚነገርላት ኡጋንዳ በበኩሏ፣ ለሁለት አመታት ያህል ዘግታቸው የከረሙ ትምህርት ቤቶችን ከቀናት በፊት መክፈቷና ትምህርት አቋርጠው የኖሩ ከ10 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ወደ ገበታቸው ማስመለሷ ተዘግቧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ በካናዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ እንደሞተባት የምትነገረዋ የኪዩቤክ ግዛት፣ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ባልወሰዱ ነዋሪዎች ላይ ከፍ ያለ ልዩ የግብር ቅጣት ልትጥል ማቀዷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ግሪክ በተመሳሳይ መልኩ፣ ክትባት ያልወሰዱ ዕድሜያቸው ከ60 አመት በላይ የሆናቸው ሰዎች በየወሩ 113 ዶላር እንዲከፍሉ ማድረጓን ያስታወሰው ዘገባው፣ ሲንጋፖር በበኩሏ ያልተከተቡ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የህክምና ወጪያቸውን ራሳቸው እንዲሸፍኑ የሚያስገድድ መመሪያ በስራ ላይ ማዋሏን አክሎ ገልጧል፡፡

 ባለ 37 ፎቅ ህንጻው 2.8 ቢ.ብር ፈጅቷል

                ህብረት ባንክ አክስዮን ማህበር ሰንጋ ተራ አካባቢ ያስገነባውን ባለ 37 ወለል የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ህብር ታወር፣ ዛሬ ከረፋዱ 3፡00 ጀምሮ ይመረቃል። ለግንባታው 2.8 ቢሊዮን ብር የወጣበትና ግንባታው 6 ዓመት የወሰደው ህብር ታወር በባንኩ ላይ ከፍተኛ ለውጥና እድገት እንደሚያመጣም ነው የተገለፀው፡፡
የባንኩ ሀላፊዎች ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ በዚሁ ታወር ላይ ምርቃቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ህንጻው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ፋሲሊቲዎች ያሉት ሲሆኑ ዘመናዊ በኮምፓስ የሚሰሩ 13 አሳንሰሮች፣ በሴንሰር የሚሰራ መብራትና ውሃ፣ ከ147 በላይ ካሜራዎች፣ የማይቋረጥ የሀይል አቅርቦት ቢዩልዲንግ ማኔጅመጀነት ሲስተም (BMS) የተገጠመለትና ሌሎችንም በርካታ አገልግሎት ያሟላ መሆኑን አስታውቀዋል። በመዲናችን አዲስ አበባ “የፋይናንስ ተቋማት በሚገኙበት ሰንጋ ተራ አካባቢ የተገነባው ይሄው ህንጻ፤ ለከተማዋ ልዩ ውበትን ከማላበሱም በላይ ትልቅ አልሞ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚችል ማሳያም ጭምር እንደሆነ ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለፁት፡፡
ህንጻው በተለያዩ ወለሎቹ የተለያዩ መጠን ያላቸው አዳራሾች፣ ካፊቴሪያዎችን  ዘመናዊ ጅምናዚሞችና ኩሽናዎችን ያደራጀ ሲሆን ለባንኩ ደንበኞችም ባለ አራት ወለል የመኪና ማቆሚያ ማዘጋጀቱም ተገልጿል።
አርክቴክቸራል ዲዛይኑ በአገር  በቀሉ ኩባንያ  “እስክንድር አርክቴክት” ተሰርቶ ግንባታው በእውቁና በዓለም አቀፉ በየኮንስትራክሽን ዘርፍ ተጠቃሽ በሆነው “ቻይና ዢያንጉሹ” ኢንተርናሽናል ኩባንያ መከናወኑም ተገልጿል፡፡ የህብር ታወር የሚገኙ መሆኑም ታውቋል። መጀመር ባንኩ ከዚህ ቀደም ለዋና መስሪያ ቤትነትና ለሌሎች ሁለት ቅርንጫፎች ኪራይ ያወጣ  የነበረውን ከ1.5 ሚ ብር በላይ ወጪ እንደሚያስቀርለትና አሁን በአዲሱ ታወር ላይ በርካታ ክፍሎችን ለኪራይ ማዘጋጀቱን ጠቅሶ፤ ይህ ኪራይ ለሌሎች  ቅርንጫፎቹ የሚያወጣውን የኪራይ ወጪ እንደሚያካክስለት ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡
በህብር ታወር የምረቃ ሥነ ሥርአት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ባለ አክስዮኖች፣ የባንኩ ደንበኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙ መሆኑም ታውቋል።

 ከዕለታት አንድ ቀን፣አንድ ኑሮው የሞቀለት፣ይለጉመው ፈረስ፣ይጭነው አጋሰስ ያለው፤የናጠጠ ሀብታም ሰው በአንድ መንደር ይኖር ነበር፡፡ እጅግ ቆንጅዬ ወጣት ሚስትም ነበረችው፡፡ አንድ ችግር ግን ነበረበት። ይዋሻል!
ታድያ ይህ ሰው ብዙ ጊዜ ህሊናውን የሚከነክነው “መቼ ነው እኔ እውነት የምናገረው?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ቀን በጣም ከመጨነቁ የተነሳ፤ለሚስቱ እንዲህ አላት፡- “ሰማሽ ወይ የኔ ቆንጆ?”
“አቤት የኔ ጌታ?” አለች ባለቤቱ፡፡
“ኑሮዬ ተደራጅቶ ሁሉ ነገር ሞልቶልኝ ሳለ አንድ ነገር ይቆጨኛል”
“ምን?”
“ዕውነትን አለማግኘቴ”
“ዕውነት ነው ያልከኝ?”
“አዎን፡፡”
“እባክህ አትልፋ፡፡ በአገራችን ዕውነት ኖራ አታውቅም”
“አለች! እኛ መፈለግ አቅቶን ነው!”
“እንደዛ የምታምን ከሆነ ፣ቤትህ ቁጭ ብለህ ሳይሆን ዞር-ዞር ብለህ መፈለግ ነው ያለብህ!!” አለችው፡፡
ባልየውም፤
“ካልሽስ የዛሬ ማለዳ ዕቅዴ በጠዋት ወጥቼ ዕውነትን ፍለጋ መዞር ነው፡፡”
“ይቅናህ፡፡ ስታገኛት ግን ከኔ ልታገናኛት ቃል ግባልኝ” አለችው ሚስቱ፡፡
ባል ሊያገናኛት ቃል ገብቶ ንብረቱን ሁሉ አውርሷት ከቤቱ ወጣ፡፡
በየመንገዱ ከለማኝ ጀምሮ ይጠይቅ ጀመር፡፡ ተራሮች ላይ ወጥቶ ዕውነትን ለማግኘት ሞከረ፡፡ ዕውነትን አላገኛትም፡፡ ሸለቆዎች ውስጥ እየገባ በረበረ፡፡ ትናንሽ መንደሮችንና ከተሞችን አሰሰ፡፡ የለችም፡፡ ባህሮችንና የባህር-ዳርቻዎችንም መረመረ፡፡ ጨለማና ብርሃንን አጤነ፡፡ የቆሸሹ ቦታዎችንና በአበባ የተሞሉ ጽዱ ቦታዎችን እየገባ አጣራ፡፡ ዕውነት እዚያም የለችም፡፡ ቀንና ሌሊቶችን አጠና፡፡ ሳምንታትን፣ ወራትንና ዓመታትን ውስጣቸውን ፈተሸ፡፡ አሁንም እውነት አልተገኘችም፡፡
   አንድ ቀን በተራራ ግርጌ ባለ አንድ ዋሻ ውስጥ ዕውነት ተሸሽጋ እንደምትኖር ሰዎች በጠቆሙት መሰረት ወደዚያው ሄደ፡፡ እዚያ ያየው አስገረመው፡-
ለካ፤ዕውነት አንድ የጃጀች አሮጊት ነች!ብልህ ናት፡፡ አስተዋይ ናት፡፡ ማዳመጥ እንጂ መናገር አትወድም። በመላ ድዷ ላይ የምትታየው እንዲት ጥርስ ብቻ ናት፡፡  እሷ ግን የወርቅ ጥርስ ናት፡፡ ፀጉሯ ሽበት ብቻ ነው። እሱንም ሽሩባ  ተሰርታዋለች! የፊቷ ቆዳ የደረቀና የተጨማደደ ፤የዱሮ ብራና ይመስላል! ይህ ሁሉ ሆኖ የአሞራ ኩምቢ የመሰለ የእጅ ጣቷን እያወናጨፈች መናገር ታውቅበታለች፡፡ ድምጿ የሚያምር፣የተቃና ፣ለስላሳና ጣፋጭ ናት፡፡
ሰውየውም ለማጣራት ፡-
“ዕውነት፣ዕውነት አንቺ ነሽን?”ብሎ ጠየቃት፡፡
ዕውነት አሮጊቷም፤
“አዎን ነኝ” አለችው፡፡
አብሯት አንድ አመት በመቆየት ትምህርት ከጥበቧ ሊቀስም ወሰነ፡፡ ሀሳቡን ተቀብላው አብረው ከኖሩ በኋላ፤በመጨረሻ እንዲህ አለችው፤
ከእንግዲህ በየመንገዱ ላይ እግኝቶ ለሚጠይቅህ ለማንኛውም ሰው፤”ከየት መጣህ? “ሲልህ ከዕውነት ቤት መመለስህን ንገረው፡፡ ምን መሳይ ናት ካለህ፡-“ወጣት፣ፀጉሯ ጥቁር-ዞማ የመሰለ፣ ዐይኖቿ ጎላ ጎላ ያሉ፤የእጅ-ጣቶቿ ቀጥ ቀጥ ያሉ የሚያማምሩና ፤ቆዳዋ የልጅ ቆዳ የሚመስል ናት ብለህ ንገር” አለችው፡፡
ሰውየውም እየተደሰተ፤
“ለአገሩ ሁሉ ያልሽኝን እነግራለሁ” ብሎ እየሮጠ ሄደ፡፡ ዕውነትም እያየችው በትዝብት ሳቀችበት!
ሰዎች ራሳቸው ያልሆኑትን ነገር ሲነግሩን ለመቀበል ከመቸኮላችን የተነሳ በአይናችን የምናየውን እንኳ ለማመዛዘን ያቅተናል፡፡ ያም ሆኖ አንድ ነገር ውል ይለናል፡፡ ከእውነት ይልቅ በእጅጉ ዓለምን የሞላት ውሸት መሆኑ! ከተጨባጩ ነገር ይልቅ የተጭበረበረው ፍሬ ጉዳይ ውሃ እንደሚያነሳ እናስተውላለን፡፡ ይባስ ብለን ደግሞ ያንኑ ውሸት በሴራ እንተበትበዋለን!
ይኸንን እንዲያፀኸይልን ህንዳዊው ፈላስፋ ካውቲላ የሚለንን እንስማ፡-
“በዓላሚ ቀስተኛ፤የተሰደደ ቀስት
ሁለት ዕድል አለው፤መግደል ወይም መሳት፡፡
ግን በስል ጭንቅላት፣ሴራ ከተሳለ
ህፃንም ይገድላል፣እናት ሆድ ውስጥ ያለ!”     
      ይህ ግጥም ሴረኞችን እንከላከል ዘንድ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ አደገኛነቱን እንድናጤንም የሚያሳስብ ነው፡፡ እንደእኛ ያለ ከአያት ቅድመ አያት ጀምሮ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፣ቂም በቀልና የውርዴ ያህል ተንኮል የተጠናወተውን ማህበረሰብ አዝሎ የሚጓዝ “ሊቅ- አዋቂ” ያለው፣መከረኛ ህዝብ፤ ሁሌ ለአሮጌውም ይሁን ለአዲሱ ሹም እጅ-እየነሳ እየኖረ ነው፡፡  ያ ባይሆን ኖሮ፡-
“ለመቶ አምሳ ጌታ፣ ስታሰር ስፈታ ነጠላዬ፤ አለቀ በላዬ….
ለምስለኔው ሙክት ለጭቃው ወጠጤ
እንዲህ ሆኜ ነው ወይ፣በአገር መቀመጤ! እያለ እያንጎራጎረም ነበር፡፡
ያም ሆኖ እጅግ የከፋው እለትም፡-
ገዴ ዞራ ዞራ በዕንቁላሉ ላይ….(“ይ” ይጠብቃል)
“ጊዜ እሚጠብቅ ሰው ጅል ሊባል ነወይ?
…አ.ረ ምረር ምረር፣ ምረር  እንደቅል
አልመርም ብሎ ነው፣ዱባ እሚቀቀል!”
ይላል፡፡
የሃገራችን ዴሞክራሲ ደጋግመን እንዳየነው፤ ወይ የይስሙላ ዲሞክራሲ (pseudo- democratey) ነው አሊያም ባንድ ስሙ ኢ-ዲሞክራሲ ወይም ፀረ ዲሞክራሲ ነው፡፡ አንድነትም፣የፓርቲዎች ጋብቻንም፣ ተፈጥረው ሳይጨርሱ በየቡድኑ ገብተው ጠብ የሚያጫጭሩትንም “የትልቁ ዓሳ ትንሹን አሳ ይውጣል” ፖለቲካንም “ፍየል ፈጁን አውሬ ፍየል አርደህ ያዘው” ባዩንም፣የዕድል-አጥቢያው አርበኛውንም፣ከኔ ካልሆንክ የዚያኛው ነህ ባይ  ወዶ ገባው ኮርማውን፣ አዲስ ግልብጡንም ወዘተ ወዘተ ፈሪውንም ከላይ ባየንበት ፖለቲካዊ መነፅር ለማየት አዳጋች አይደለም፡፡ አሰቃቂው ነገር ግን ሁሉም በህዝብና በአገር ስም መማል፣መገዘቱ ነው! ከዚህ ይሰውረን፡፡ በዚህ ላይ ስደት ለወሬ ይመቻልን ስንጨምርበት እጅግ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ይከትተናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሐዘን ቤት ሙሾ አውራጆች፣ሠርግ ቤት ዘፈን አውጪዎች የሆኑት የየዘመኑ አድርባዮች የሚያደርሱት ጥፋት ፍጹም አደገኛ ነው፡፡ የጥንቱ የሩሲያ ፖለቲካ መሪ ቭላዲሚር ሌኒን the PENDULUM OF OPPORTUNITY  NEVER STOPS OSCILATING ይላል (የፔንዱለም እጅ ዕድሜ ልኩን መወዛወዙን በጭራሽ አያቆምም፣ አንደማለት ነው፡፡)  እጅግ ከጉዳዮች  ሁሉ ባስፈሪ ሁኔታ ዛሬ አሳሳቢ   የሆነው ግን በየሰበቡ፣ወይም በየሽፋኑ የሚጫረው የሃይማኖት ግጭት ነው! ከሁሉም  ይሰውረን!! ዛሬ በሀገራችን ብዙ ድርጅቶች፣ፓርቲዎች የፖለቲካ ብሔራዊ እንቅስቃሴዎች መፍጠራቸው ይነገራል፡፡ መፈጠራቸው ባልከፋ!  “የአንተ  እውነት ውሸት ነው፡፡ ትክክለኛው ዕውነት የእኔ ነው፡፡ እኔ ብቻ  ነኝ ሀቀኛ” ካሉ ነው ጣጣ እሚመጣው፡፡ ምን ያህል ህዝብ በዚህ ዓይነት ቅስቀሳ ይወናበዳል? ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ፣ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት እጃቸውን ሲያስገቡበት ምን ያህል የተወዛገበ ሂደት ውስጥ እንደሚገባ እናጢን፡፡ “ዕውነት ቦት ጫማውን ሳታጠልቅ፤ ውሸት ዓለምን ዞሮ  ይጨርሳል” የሚለው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡፡
ለክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የጥምቀት በዓል!
ለሁላችንም ሁነኛ የአመለካከት ጥምቀት ይስጠን!

  "ክብር ለመከላከያ ሰራዊታችን" የተሰኘው ኢምር በኮልፌ 2014 ቶርናመንት፣ ባለፈው እሁድ፣ በኮልፌ መላጣ ሜዳ፣ በተለያዩ የስፖርትና የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች በከፍተኛ ድምቀት መካሄዱ ታውቋል፡፡
"በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ጀግኖች ተመስግነዋል፣ ለሀገራቸው ከፊት የቀደሙ ተወድሰዋል፣ ኢትዮጵያን ዘብ ሆነው ሁሌም የሚያገለግሉ ተዘክረዋል፡፡" ብለዋል፤ የቶርናመንቱ አዘጋጆች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የደም ልገሳ የተደረገ ሲሆን በስፖርት ጋዜጠኞችና በኮሜዲያን መካከል የእግር ኳስ ጨዋታ መካሄዱ ታውቋል፡፡ የቦክስ ግጥሚያና አስደናቂ የሰርከስ ትርኢቶችም የፕሮግራሙ ድምቀቶች ነበሩ ተብሏል፡፡ በእሁዱ የመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚዎች፣ አርቲስቶች፣ የቀድሞ የእግር ኳስ ዝነኛ ተጫዋቾች እንዲሁም የኮልፌ ነዋሪዎች ተገኝተው ነበር።

“ፍሬገነት ኪዳን ለህፃናት”፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቢሾፍቱ ከተማ በተሰጠው ቦታ ላይ ያስገነባውን ዘመናዊ ሞዴል ት/ቤት፣ ነገ ከጠዋቱ 3፡00-7፡00፣የትምህርት አመራሮች፣ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና የማህበረሰብ መሪዎች በተገኙበት እንደሚያስመርቅ ተገለፀ፡፡
ፍሬገነት ደንቢ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተብሎ የተሰየመው ይህ ዘመናዊ አፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፤ ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ሲሆን በውስጡ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መፃህፍት፣ክሊኒክ፣ የኮምፒውተር ክፍል፣የህፃናት ማሸለቢያ ክፍል፣የመምህራን ማሰልጠኛ እንዲሁም የሥዕልና የሙዚቃ መለማመጃ ሁለገብ አዳራሽ በተጨማሪም የወጥ ቤትና የመመገቢያ አዳራሽ ይዟል ተብሏል፡፡
 “ፍሬገነት ኪዳን ለህጻናት” ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና ግንባታውን ፍሊንትስቶን ኢንጂነሪንግ የስራ ተቋራጭ በጥራት ማከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
“ፍሬገነት ኪዳን ለህጻናት” በ1997 ዓ.ም የተቋቋመ አገር በቀል የግብረ ሠናይ ድርጅት ሲሆን ዓላማውም ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚመጡ ህጻናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ነፃ ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ለ17 ዓመታት በርካታ ህጻናትን ነፃ የምግብ፣የጤናና፣የአልባሳት ድጋፍ እያደረገ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በነፃ በመስጠት ህብረተሰቡን እያገለገለ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ዩቬኔል ሞይሴ ከወራት በፊት በታጣቂዎች ጥቃት በተገደሉባት ሃይቲ፣ ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርየል ሄንሪ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ለጥቂት ማምለጣቸው ተሰምቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ጎናቪስ በተባለችው የአገሪቱ ከተማ የአገሪቱን የነጻነት በዓል ለማክበር በተከናወነ ስነስርዓት ላይ በታደሙበት አጋጣሚ በታጣቂዎችና በፖሊስ መካከል ግጭት መቀስቀሱንና ተኩስ እንደተከፈተባቸው የዘገበው አልጀዚራ፣ ፕሮግራሙን አቋርጠው እንዲሄዱ ከተደረገ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ #አገራችንን ለገንዘብ ሲሉ ቀውስ ውስጥ ለመዝፈቅ ለሚታትሩ ሃይሎች እጅ አንሰጥም; ሲሉ መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርየል ሄንሪ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዩቬኔል ሞይሴ ባለፈው ሃምሌ ወር በቤተመንግስታቸው እያሉ በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱን የማስተዳደር ስልጣኑን ይዘው እንደሚገኙ ያስታወሰው ዘገባው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በተከፈተው ተኩስ አንድ ሰው መሞቱንና ሁለት ሰዎች መቁሰላቸው መነገሩንም አስረድቷል፡፡