Administrator

Administrator

በኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢህዲሪ) ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ሌ/ጀነራል አዲስ ተድላ አየለ “በገጠመኝ የታጀበ የህይወት ጉዞ” መፅሀፍ ዛሬ ሳምንት  ጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም አምስት ኪሎ በሚገኘው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ይመረቃል፡፡ በዕለቱ በጽሐፉ ላይ ዳሰሳ የሚደረግ ሲሆን ውይይትም ይካሄዳል ተብሏል፡፡
ሌ/ጀነራል አዲስ ተድላ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊ ሆነው በተሰማሩባቸው ተግባራት በዛ  ያሉና ጠቀሜታ ያላቸውን መረጃዎች የማካበት እድል የገጠማቸው ሲሆን፣እነዚህን መረጃዎች “በገጠመኝ የታጀበ የህይወት ጉዞ” በሚል በመፅሐፍ መልክ ያሳተሙት ስራቸው ነው፡፡ ዛሬ የሚመረቀው ዳጎስ ያለው ይሄው መፅሀፍ 686 ገፅ ያለው ሲሆን በ460 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  ሰአሊ አለባቸው ካሳ “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” (Travel with Enok 2) በሚል  ርእስ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የጠልሰም ስራዎች አውደ ርዕይ ዛሬ እንደሚከፈት ታወቀ፡፡  “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” 2 በሃያት መኖርያ ቤቶች ዞን 5 መንገድ ቁጥር 12 በሚገኘው የስነጥበብ ማእከል ከጥር 29 እስከ የካቲት 13 ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብ መፅሃፈ ሔኖክን ብዙ እየተጠቀምንበት ባለመሆኑ ሰዓሊ አለባቸው  “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” የሚል ፕሮጀክት በመቅረፅ የጠልሠም ጥበብን ለማስተዋወቅ  አስቧል፡፡  ከመፅሃፈ ሄኖክ  5 መፅሃፍት የሚያደርገውን ጉዞ በየዓመቱ በተከታታይ በሚያቀርባቸው ኤግዚብሽኖች በመስራት ነው፡፡ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” በሚል ርእስ ለመጀመርያ ጊዜ ባቀረበው የጠልሰም  ትርኢት ሰአሊዎችና የስነጥበብ አፍቃሪያን ምትሃታዊ ተሰጥኦውን ተመልክተዋል፡ ፡ሰአሊው የጠልሰም ስራዎቹን በአስደናቂ የቴክኒክ ቅልጥፍና ፤  አሰራሮችና በዳበሩ ጭብጦች ይሰራቸዋል፡፡  እንደገና ጥቅም ላይ በሚውሉ ጣውላዎችና የቆዩ  እንጨቶችን  ቀርጾ አክሪሊክ ቀለማትን ይቀባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የሚስላቸው የጥበብ ምልክቶች በእንጨት ላይ በዲጂታል መንገድ የታተሙ ይመስላል።
ትውልዱ በደሴ የሆነው ሰአሊ አለባቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ  የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተመረቀ ሲሆን ፤ ባለፉት 15 አመታት በተለያዩ የቡድን ኤግዚብሽኖች ላይም ተሳትፏል፡፡  ከጠልሰም ጥበብ ጋር  ከተገናኘ በኋላ በአስደናቂ የጥበብ ስራዎች ተመልሶ የመጣ ሲሆን በቀለማት ያሸበረቁት ስራዎቹ በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብ በአጭር  ጊዜ ለመታወቅ እያበቁት ናቸው፡፡



 የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብ አጽድቋል

           የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ባለፈው ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከሁለት ዓመት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን በዕለቱም የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብን አጽድቋል። በ2012 እና በ2013 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የም/ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤዎች ሳይከናወኑ መቅረታቸው ተጠቁሟል።
የምክር ቤቱን የሁለት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የም/ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ም/ቤቱ በአገሪቱ መሰረታዊ የሆኑት የሕግ የበላይነትና የፕሬስ ነጻነት እንዲከበሩ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፤
ም/ቤቱ ባካሄደው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያለፉት ሁለት ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብንም አጽድቋል።
ም/ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፈረንሳይ መንግስትና ከዩኔስኮ በተገኙ ድጋፎች፤ የአቅም ግንባታ፣ ጽ/ቤት የማደራጀት እንዲሁም የግልግል ዳኝነት የማቋቋም ሥራዎችን ማከናወኑ ተገልጿል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ፤ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ጠንካራ ሚናውን በአግባቡ የሚወጣ መገናኛ ብዙኃን ሲኖር፣ ሚናውን በአግባቡ የሚወጣ ህዝብና መንግስት ይኖራል” ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን፤ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት ህዝቡን በማንቃት፣ ምርጫ 2013 በሰላም እንዲጠናቀቅ እንዲሁም አገሪቱ ባጋጠማት የህልውና ፈተና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በማጋለጥ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱን የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ያቀረቡት የም/ቤቱ ጽህፈት ቤት አባል አቶ ታምራት ኃይሉ፤ የአባላትን ቁጥር ማሳደግ፣ የፕሮጀክት ስራዎች፣ ስልጠናና የገቢ ማስገኛ ሥራዎች፣ የዘገባ ማኑዋል ማዘጋጀት፣ የአባላት መዋጮን ማስፋት፣ የሚዲያ መከታተያ (ሞኒተሪንግ) ክፍል ማደራጀት እንዲሁም የግልግል ዳኝነትና የዕንባ ጠባቂ አካል ማደራጀት በዕቅዱ ውስጥ መካተታቸውን ጠቁመዋል።
በ19 መስራች አባላት  የተመሰረተው ም/ቤቱ፤ በዕለቱ ጉባኤ ላይ የአባልነት ጥያቄያቸው የፀደቀላቸውን 13 የመገናኛ ብዙኃንና የሙያ ማህበራትን ጨምሮ በአጠቃላይ የአባላቱ ቁጥር 60 መድረሱ ታውቋል። እንዲያም ሆኖ ሁሉም የም/ቤቱ አባላት የአባልነት መዋጮ በአግባቡ እየከፈሉ ባለመሆኑ ም/ቤቱ በፋይንስ እጥረት እንደሚቸገር ተነግሯል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት የራሱን ባለ 7 ክፍሎች ጽ/ቤት ማደራጀቱንና ራሱን የሚያስተዋውቅበት ድረ-ገጽ መጀመሩን በዕለቱ ይፋ አድርጓል።


የኦሮሚያ ፖሊስ ድርጊቱን የፈጸሙትን ለህግ አቀርባለሁ ብሏል
                      
              የከረዩ የሚቺሌ ገዳ የጅላ አባላት የተገደሉት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መሆኑን በምርመራ ማረጋገጡን የጠቆመው  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ድርጊቱን የፈጸመና  ያስፈጸሙ የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡና ለተጎጂዎች ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው የጠየቀ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በበኩሉ የኮሚሽኑን ሪፖርት ተቀብሎ የራሱን ማጣራት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም የከረዩ አባገዳን ጨምሮ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላትን የገደለው በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን ነው ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባደረገው ማጣራት ግን ግድያውን የፈጸመው የክልሉ የጸጥታ ሃይል መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው፣ በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያደረገውን ምርመራ የያዘ ሪፖርት ባለፈው ረቡዕ ጥር 25 ይፋ ባደረገ ወቅት ባወጣው መግለጫ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ህዳር 22 ቀን 2014 የከረዩ የሚቺሌ  ገዳ አባላት ተሰባስበው የገዳ ስነስርዓት ከሚፈጽሙበት አረዳ ጂላ 39 ያህሉ በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ታፍሰው መወሰዳቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
በወቅቱ ለግለሰቦቹ መታሰር ምክንያት የሆነውም ህዳር 21 ቀን 2014 ለስራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ በነበሩ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ሃይሎች የተፈጸመው ጥቃት ሲሆን በዚህም ጥቃት 11 የፖሊስ አባላት መገደላቸውንና 17 ያህሉ መቁሰላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ይህን ተከትሎ በነጋታው ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጂላ አባላት መኖሪያ ወደሚገኝበት ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ወደተባለ ሥፍራ የደረሱት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች፣ 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው በኮሚሽኑ ሪፖርት ተጠቁሟል።
ከእነዚህ በጸጥታ ሃይሎች ከተያዙ የከረዩ ሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተደብድበው መገደላቸውንና ሁለቱ ወደ ጫካ ሮጠው ማምለጣቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ግድያው ከተፈጸመ በኋላም የሟቾች ቤተሰቦች አስክሬን እንዳያነሱ በፖሊስ መከልከላቸውን፣ በዚህም በከፊል የሟቾች አስክሬን በአውሬ መበላቱን የጠቆመው ሪፖርት፤ ቀሪዎቹ 23 ግለሰቦች ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሁለት ሳምንት በኋላ አንደኛው አስክሬን ለቤተሰቦቼ መሰጠቱን፣ በዚህ አስክሬን ላይ በተደረገ ምርመራም፣ ግለሰቡ ክፉኛ መደብደቡን የሚያመላክት ውጤት መገኘቱን አስታውቋል።
ቀሪዎቹ 22 የሚችሌ ገዳ አባላት ከሳምንት በኋላ መለቀቃቸው በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን 15ቱ ግለሰቦች ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ ከህግ አግባብ ውጪ መገደላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታ አካላት እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳስቧል። ለሟቾች ቤተሰቦችና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውም ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲሰጣቸውም ጠይቋል- ኮሚሽኑ።
ይህን የኮሚሽኑን የምርመራ ሪፖርት በአዎንታ የተቀበለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ድርጊቱ ከህግ አግባብ ውጪ የተፈጸመ መሆኑን አምኖ፣ ድርጊቱን የፈፀሙ የፀጥታ አባላትን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።
“በድርጊቱ እጁ ያለበትን የትኛውም አካል ለህግ ያቀርባል” ያሉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን እስካሁን ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ቀሪ  የወንጀል ምርመራው በዝርዝር ተከናውኖ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

  ኢትዮ-ቴሌኮም በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ውስጥ 28 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 86.4% ማሳካቱ የተገለጸ ሲሆን ይህም ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6.7% ዕድገት ማሳየቱ ተጠቁሟል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ ባለፈው ሰኞ ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የኩባንያቸውን የዓመቱን የመጀመሪያ 6 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ይህን ገቢ ማግኘት የቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያዎችን፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 23 አዳዲስና 19 ነባር የሃገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን አሻሽሎ ለደንበኞች በማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 74.8 ሚሊዮን ዶላር በማግኘትና የዕቅዱን 89.3% በማሳካት ነው ተብሏል።
የተመዘገበው ውጤት፣ በሃገሪቱ በወቅቱ ከነበረው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር ሲታይ አመርቂ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኩባንያው የገቢ አማራጮችን ከማስፋት በተጨማሪም የወጭ ቅነሳ ስትራቴጂ በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግም፣ በ6 ወራት ውስጥ ከ1.2 ቢ. ብር በላይ ወጪ መቀነስ  መቻሉ ተመልክቷል።
በኢትዮ ቴሌኮም የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት፤ በአገሪቱ ከተከሰተው ችግር ጋር በተገናኘ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 3 ሺ 473 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የአገልግሎት መስተጓጎል የተፈጠረ ሲሆን በዚህም ሳቢያ 3.67 ቢሊዮን ብር አጥቷል፡፡ በጦርነቱ በተጎዱና እስካሁን መድረስ በተቻለባቸው አካባቢዎች ላይ የወደሙ ንብረቶችን ለመተካትና አገልግሎቱን ለማስጀመር 328.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተጠቁሟል።
አሁንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት መስጠት ያልተቻለባቸው ወረዳዎች እንደሚገኙ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም ብሏል።
በቅርቡ የተጀመረውን የቴሌብር አገልግሎት በተመለከተ፣ ከኢንዱስትሪው ልምድ በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የግብይት መጠኑ 5.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተጠቁሟል። የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያው አጋሮችንም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ ከ46 ሺ በላይ ኤጀንቶችና ከ11 ሺ በላይ ነጋዴዎች ተሳታፊ ሆነዋል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ከ11 ባንኮች ጋር የኢንተግሬሽን ስራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከ8 ባንኮች ጋር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር ማድረግ እንደተቻለ ተነግሯል፡፡
ኩባንያው ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 60.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዕቅድ አንጻር የ100% አፈጻጸም ተመዝግቧል ተብሏል። አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ20% ዕድገት አሳይቷል። በአገልግሎት ዓይነት ሲታይ የሞባይል ድምጽ ደንበኞች ብዛት 58.7 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንክ ደንበኞች 433 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 923 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 23.8 ሚሊዮን  መሆናቸው ታውቋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የኩባንያውን መሰረተ ልማቶች በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅም እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ ሰፊ የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህ ግማሽ ዓመት የ4G/LTE የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በድምሩ 136 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተደርገዋል ብሏል። “ደንበኞቻችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል 4G/LTE Advanced በተጀመረባቸው የክልል ዋና ከተሞች የ4G ቀፎ በቅናሽ የማቅረብና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል።” ብሏል- ኩባንያው።
 የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተም (Next Generation Business Support System (NGBSS)) የማዘመንና የማሳደግ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ይህም ከደንበኞች ምዝገባ ጀምሮ የቢሊንግና አዳዲስ ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ነው ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን ይህን አዲስ ሲስተም በመጠቀም በርካታ ምርትና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለም ታውቋል፡፡

ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በህብረተሰቡ ጥቆማ የተመለመሉ 42 እጩዎች ላይ ህዝቡ አስተያየቱን እንዲሰጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስም ዝርዝራቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ትናንት ስም ዝርዝራቸው ይፋ ከተደረጉት እጩዎች መካከል 11 ያህሉ በህብረተሰቡ ግምገማ ተመርጠው ኮሚሽኑን እንዲመሩ ይደረጋል ተብሏል።
ስምዝርዝራቸው ይፋ የተደረገው 42 እጩዎች የሚከተሉት ናቸው።
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
ፕ/ር አፈወርቅ በቀለ ስመኝ
አቶ ዘገየ አስፋው አብዲ
አምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል
ፕ/ር ጥላሁን ተሾመ
አቶ ሃይሌ ገብሬ ሱሌ
ፕ/ር ባዬ ይማም
ዶ/ር ሰሚር የሱፍ
ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ በማኖ
ፕ/ር ሀብታሙ ወንድሙ
አቶ ገመቹ ዱቢሶ ጉዲና
አቶ ሳሙኤል ጣሰው ተፈራ
አምባሳደር ሙአዝ ገ/ህይወት ወ/ስላሴ
አቶ አህመድ ሁሴን መሃመድ
ፕ/ር መስፍን አርአያ
ዶ/ር  አበራ ዴሬሳ
ሂሩት ገ/ስላሴ ኦዳ
አምባሳደር ሙሃመድ ድሪር
አቶ ንጉሴ አክሊሉ
ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ
ተስፋዬ ሃቢሶ
ዶ/ር አይፎርት መ/ድ ያሲን
ክፍሌ ወ/ሚካኤል ሐጀቶ
ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌጡ መንገሻ
ፕ/ር ካሳሁን ብርሃኑ አለሙ
አባተ ኪሾ ሆራ
ዶ/ር ዳዊት ዮሐንስ
ፕ/ር ህዝቅያስ አሰፋ
ዶ/ር ታከለ ሰቦቃ
ኢ/ር ጌታሁን ሁሴን ሽኩር
ፕ/ር በቀለ ጉተማ ጀቤሳ
ፕ/ር ዳንኤል ቅጣው
ዘነበወርቅ ታደሰ ማርቆስ
ፕ/ር ዘካሪያስ ቀነአ ተስገራ
መላኩ ወ/ማሪያም
ዶ/ር ዮናስ አዳዬ
ዶ/ር ወዳጆ ወ/ጊዮርጊስ
አንዳርጋቸው አሰግድ
ዶ/ር ሙሉጌታ አረጋዊ
ነጋልኝ ብርሃኑ ባዬ
ሎሬት ፕ/ር ጥሩሰው ተፈራ
ኢብራሂም ሙሉሸዋ እሸቴ
እነዚህ ስማቸው በይፋ የተገለጸው 42 ግለሰቦች በአጠቃላይ ለእጩነት ከተጠቆሙ 600 (ስድስት መቶ) ግለሰቦች መካከል ለመጨረሻው ዙር የተመረጡ መሆናቸው የተመለከተ ሲሆን ህብረተሰቡ እስከ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በግለሰቦቹ ላይ አስተያየቱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረ-ገጽ በመግባት መስጠት እንደሚችል ተገልጿል።

  በአብዬ ግዛት የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ በናይጄሪያዊው ጄኔራል ተተኩ


           ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ትገባኛለች በሚሏት የአብዬ ግዛት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ፣ በናይጄሪያዊ ጄኔራል እንደተተኩ የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የናይጄሪያ ጦር አዛዥ የሆኑትን ሜጀር ጄኔራል ቤንጃሚን ኦሉፌሚ ሳውየርን በአብዬ ለድርጅቱ ሰላም አስከባሪ አዛዥ አድርገው መሾማቸውን ድርጅቱ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት አብዬ ግዛት በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቲቷ እንዲወጣ ሱዳን መጠየቋን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስማማቱን ባለፈው ዓመት ማስታወቁ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ሱዳን ባወጣችው መግለጫ የኢትዮጵያ ጦር በሌሎች የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲተካ መስማማታቸውን ብትገልጽም፣ ከየትኛው አገራት እንደሆነ አልተጠቀሰም።
በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ከአብዬ ግዛት እንዲወጡና በሌላ አገር ጦር እንዲተኩ ሱዳን ተመድን በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል። በወቅቱ የሱዳን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የሱዳን ድንበር አካባቢ እየተጠናከረ ባለበት ጊዜ ስትራቴጂክ በሆነው የሱዳን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ምክንያታዊ አይሆንም” ብሎ ነበር።
በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው የአቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ካሰማራቸው ሰላም አስከባሪዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው። በዚህ ኃይል ውስጥ በአጠቃላይ 4,190 ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 158 ወታደሮችና ሰባት የፖሊስ መኮንኖች ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ተሰናባቹ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአብዬ ቆይታቸው ወቅት ላሳዩት ትጋት፣ ከፍተኛ አገልግሎትና ውጤታማ አመራር አንቶኒዮ ጉቴሬዝ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
 (ቢቢሲ)



መላኩ ሸዋረጋ የተባለው ተከሳሽ፣ በገቢዎች ሚኒስቴር አዳማ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የኦዲት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ አንድ ሚሊዮን ብር በባንክ አካውንት እንዲገባለትና 5 መቶ ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል በመገኘቱ በፈጸመው የሙስና ወንጀል በፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ መወሰኑን የፍትህ ሚኒስቴር አሰታወቀ።
ተከሳሹ የስራ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ”ኽርበርግ ሮዝ; ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለው ድርጅት የ2 ዓመት የንግድ ስራ ትርፍ ግብር 66 ሚሊዮን 616 ሺህ 818 ብር አንዲከፍል ሲወሰንበት፣ የድርጅቱ የአስተዳደር ሰራተኛ የሆነችው 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር፣ በውሳኔው ላይ ለቅ/ፅ/ቤቱ ቅሬታ ታቀርባለች፡፡
ተከሳሹ በበኩሉ የቀረበውን ቅሬታ ውሳኔውን ዝቅተኛ በሆነ መልኩ መወሰን እንደሚቻልና ለዚህም አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምቶ ግማሽ ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሲሆን ተከሳሽ በሙስና ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ህግ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 10(2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል።
በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በ1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ መላኩ ሸዋረጋ፣ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ፣ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ የተጠቀሰውን የጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል አለመፈፀሙን ክዶ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ 4 የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ የድርጊቱን መፈፀም በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሹም ክስና ማስረጃዎቹን ማስተባበል ባለመቻሉ፣ ችሎቱ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ወንጀለኛው መላኩ ሸዋረጋ በፅኑ እሥራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኖበታል።
በጉቦ የተሰጠው ገንዘብ ለተበዳይ እንዲመለስ ዐቃቤ ህግ በጠየቀው መሰረት፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ገንዘቡ ለተበዳይ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በጸደቀው ተጨማሪ በጀት የሚጠገኑ አራት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፤ ለስንዴ ማምረቻነት እንደሚውሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ። ለስኳር ልማት ታስበው የተገነቡት አራቱ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለምግብ ፍጆታ እንዲውሉ የተደረጉት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ነው ተብሏል።
በአቅራቢያቸው ለተገነቡ የስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆነውን የሸንኮራ አገዳ በስፋት ለማምረት ታስበው የተገነቡት  የኦሞ ኩራዝ፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ የመስኖ አውታሮች ናቸው። ግድብ እና የመስኖ አውታርን በአንድ ላይ ያቀፈው የከሰም ፕሮጀክትም ለተመሳሳይ ዓላማ እንዲውል የተገነባ ነበር።
ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 20 በፓርላማ በጸደቀው የፌደራል መንግስት ተጨማሪ በጀት ውስጥ፤ ለእነዚህ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥገና የሚውል የ2.2 ቢሊዮን ብር ገንዘብ መመደቡ ይፋ ተደርጓል። ለመስኖ ፕሮጀክቶቹ ጥገና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የተመደበው “አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታና ከመንግስት የትኩረት አቅጣጫ አንጻር” በመስኖ ልማት ረገድ ያለውን “ክፍተት ለማጥበብ” በሚል እንደሆነ ተጨማሪ በጀቱን ለማብራራት በቀረበ ሰነድ ላይ ተገልጾ ነበር።
(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Saturday, 05 February 2022 11:32

መልዕክቶቻችሁ

     የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ

              በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና በተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (UNOHCHR) አዘጋጅነት፣ በትግራይ ክልል ግጭት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ በሁለቱ ተቋማት የተደረገውን ጣምራ ምርመራ ሪፖርት፣ ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምና ክትትል አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከምሁራንና ከሀገራዊና ዓለም አቀፍ ሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የምክክር መድረክ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ከግንቦት 8 ቀን እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በኢሰመኮ እና በተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ የደረሱ የሰብአዊ መብቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ወይም የጦርነት ሕጎች እንዲሁም የስደተኞች መብቶች ድንጋጌዎችን ጥሰቶችን በተመለከተ የጣምራ ምርመራ ሲያካሄዱ ቆይተው፣ ሪፖርቱ እ.ኤ.አ. ኅዳር 3 ቀን 2021 ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽ/ቤት እና ኢሰመኮ የጣምራ ምርመራ ሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምና ክትትል አስመልክቶ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶችን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አድርገዋል። በዚህ ረገድ በኢሰመኮና በተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽ/ቤት የምክረ ሃሳቦቹን አፈጻጸም በውትወታ፣ በቴክኒካዊ ድጋፍና በአቅም ግንባታ የሚያግዝ ቡድን ተቋቁሟል። ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የተካሄደው የውይይት መድረክ ዋና ዓላማ ባለድርሻ አካላት የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱና እያንዳንዳቸው የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ተመሳሳይ አረዳድ እንዲኖር ማስቻል ነው።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ “የጣምራ ሪፖርቱ ግኝቶች ለክርክር ሊቀርቡ አይገባም። ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በጦርነቱ ለተከሰቱ ጥሰቶች ያለባቸውን ኃላፊነት ሊያምኑና ሊቀበሉ እንዲሁም ፍትሕ ለማስገኘት የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል” ብለዋል። አክለውም፤ በዝግጅቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበው፣ “በተለይም በግጭቱ የተሳተፉ ወገኖች የሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች ተቀብለው ለመተግበር የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች እንዲወስዱ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል።
የተ.መ.ድ. ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት (UNOHCHR) የምሥራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት ተወካይ ማርሴል አክፖቮ በበኩላቸው፤ በጣምራ ሪፖርቱ የተመለከቱትን ምክረ ሃሳቦች የማስፈጸምና የመተግበር ኃላፊነት ያለባቸው አካላት በሙሉ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም “ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ማዕቀፎችንና ደረጃዎችን በሙሉ እስካሟሉ ድረስ፣ ተጠያቂነትን ለማምጣት ሀገር በቀልና ሀገራዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል። ስለሆነም መንግሥታት ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ ያለባቸውን ቀዳሚ ኃላፊነት ለመወጣት ተነሳሽነትና ፖለቲካዊ ፍላጎት ካሳዩ፣ ያሉብንን ማናቸውንም ጥርጣሬዎች ወደ ጎን ብለን ልንደግፋቸውና ልናበረታታቸው ይገባል” ብለዋል።