Administrator

Administrator

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ በቅርቡ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው ያገኘውን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበለው ጠቁመው ፓርቲው ስኬት ያላስመዘገበው በራሱ ችግር እንጂ በገዢው ፓርቲ ተጭበርብሮ እንዳልሆነ ሰሞኑን ለኢቢሲ ብቻ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ ትዕግስቱ አወሉ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ሞጋች ቃለምልልስ ለተለያዩ አወዛጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንት ስለሌለው ካቢኔያቸው፣ የፓርቲውን ውድቀት ከሚሹ አካላት ገንዘብ ተቀብለው መኪና ገዝተዋል ተብሎ ስለሚናፈሰው ወሬ፣ በዘንድሮ ምርጫ ፓርቲያቸው ባገኘው ውጤት ከመጨረሻዎቹ ተርታ ስለመሠለፉ ተጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሰጧቸውን ምላሾች ያንብቡ፡፡
              ለአወዛጋቢ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል

     “አንድነት” ምን ውጤት ጠብቆ ነበር ወደ ምርጫው የገባው? ያገኛችሁትን ውጤትስ እንዴት አያችሁት?
አንድነት ህጋዊና ሠላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው። ምርጫ የሠላማዊ ትግል አንዱ መገለጫ እንደመሆኑ ወደ ምርጫው ሲገባም አሸንፋለሁ ብሎ ነው፡፡ መንግስት ለመሆን የሚያበቃ በቂ ውጤት ያገኘ ፓርቲ ባይኖርና አንድነት ቢያሸንፍ ከማንኛውም ያሸነፈ ፓርቲ ጋር በጥምረት መንግስት የመመስረት አላማ ይዞ ነው ወደ ምርጫው የገባው። አንድነት ከሁሉም በላይ ግን ለዲሞክራሲያዊ ስርአት መጐልበት አስተዋጽኦ ለማድረግና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትርጉም ባለው ሁኔታ ወንበር ለማግኘት በማሰብ ነው ወደ ምርጫ የገባው፡፡
የምርጫ ውጤቱን በተመለከተ እስካሁን የተገለፀው የ442 ወንበሮች ነው፡፡ በዚህም ኢህአዴግና አጋሮቹ እንዳሸነፉ ነው የተነገረው። ስለዚህ እኛ ውጤት አላገኘንም ማለት ነው፡፡ ያገኘነው የምክር ቤት ወንበር  የለም፡፡
“አንድነት” ከሌሎቹ ተቃዋሚዎች አንፃር ያገኘው የድምጽ ብዛት ለምን ዝቅተኛ ሆነ? ቀደም ሲል ፓርቲው በተሻለ አቋም ላይ እንደነበር ይነገራል። ይሄን ጥያቄ ያነሣሁት፤ እርስዎም በተወዳደሩበት የምርጫ ክልል እጅግ ዝቅተኛ ድምጽ ማግኘትዎን ስላየሁ ነው?
ስንት ጣቢያ ላይ ነው ያየኸው?
የተወሰኑትን አይቻለሁ፡፡
እንግዲህ 57 ጣቢያ ነው ያለው፡፡ ምን ያህሉን አይተህ “ዝቅተኛ ውጤት ነው ያገኘኸው” እንዳልከኝ አላውቅም። እኔም ምን ያህል እንደሆነ ገና መረጃ እያሰባሰብኩ ነው፡፡ ግን ከአዲስ አበባ ውጪ በሌሎች እጩዎች ከኢህአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘንባቸው ቦታዎች አሉ፡፡
ቦታዎቹን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
በደቡብ አካባቢ እንዲሁም በአማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት አግኝተን 2ኛ የሆንባቸው ጣቢያዎች አሉ፡፡ ግን ውጤት መግለፅ አይፈቀድም፣ ምርጫ ቦርድ ማጠቃለያ ሠርቶ ውጤቱን ይፋ ያደርጋል፡፡ ለቀጣይ ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል የእጩዎችን ቁጥር ከ12 ያልበለጠ ለማድረግ አሁን የሚገኘው ውጤት ወሣኝነት አለው፡፡ እስከ 6ኛ ደረጃ የያዙት በቀጥታ እንዲወዳደሩ ይደረጋል፡፡ እኛም እዚያ ደረጃ ውስጥ መግባታችንን ለማወቅ የቦርዱን ጠቅላላ ውጤት መጠበቅ  ይኖርብናል፡፡
አንዳንድ ወገኖች፤ የፓርቲው የምርጫ ውጤት ዝቅ ማለት “አንድነት” በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ መቀነሱን ያሳያል ይላሉ በተለይ ከቀድሞው የአንድነት ተቀባይነት አንፃር በማለት፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ከነችግሩም ቢሆን ህዝቡ ልብ ውስጥ እንዳለን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ የአንድነት ችግር መነጋገሪያ የሆነው እኮ በህዝቡ ውስጥ ስላለን ነው፡፡ እኛ በህዝቡ ውስጥ ነን ብለን እናምናለን። የእርስ በእርስ ውዝግቡ ለትግሉ ስኬት በጐ ያልሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይሄን ሁሉ ታግሎ ማለፍ ይጠይቃል፡፡ እኛ በተለያዩ አደረጃጀቶቻችን አማካኝነት በህዝቡ ውስጥ እንዳለን እናውቃለን፡፡ ለዚህ ማሣያው የምርጫ ውጤት ብቻ አይደለም። ሀገራችን ለዲሞክራሲ ገና ጀማሪ እንደመሆኗ ነገሮችን ከነችግሩ መቀበል ያስፈልጋል፡፡
“አንድነት” ከአመራር ውዝግቡ በፊት ከሁሉም ተቃዋሚዎች የበለጠ በርካታ እጩዎችን እንደሚያቀርብ አስታውቆ ነበር፡፡ እናንተ 92 እጩዎች ብቻ ነው ያቀረባችሁት፡፡ ይሄ ከአመራር ለውጡ በኋላ ፓርቲው መዳከሙን ወይም ብዙዎች ከፓርቲው መሻሻቸውን አያሳይም?
አሁን ተዳክሟል፣ አልተዳከመም ለማለት ያስቸግራል። እኔ አመራሩን ስለያዝኩት ተዳክሟል ሊባል አይችልም፡፡ የበፊቱ አመራር ውስጥም ነበርኩበት፤ ዝም ብዬ መጥቼ የተቀመጥኩ ሰው አይደለሁም፡፡ ፓርቲው መጀመሪያም ድክመት አለው፡፡ ምናልባት በወቅቱ እዚያም እዚህም  የነበሩ ጩኸቶችን ሳታዳምጡ አልቀራችሁም። ያ ጥንካሬን አያሣይም፡፡ ፓርቲው ድክመት ነበረበት። አሁንም ፓርቲው ወደቀ አይባልም፤ በመካከለኛ ደረጃ እየተጓዘ ነው፡፡ በአመራር ደረጃ የተፈጠረው ችግር አሉታዊ ነገሮች አሉት፡፡ ውዝግቡ የወሰደው ጊዜ በቂ እጩዎች ማቅረብ እንዳንችል አድርጐናል። ፓርቲው ለሁለት አመት ያቀደውን ማከናወን አልቻለም፡፡ እቅዱ የጨነገፈበት ምክንያት የአመራሩ ውዝግብ ነው፡፡ እጩዎችን ለማቅረብ 7 ቀን ብቻ ነው የተሠጠን፡፡ ስለዚህ የተፈጠረው ችግር እቅዳችንን አፋልሶታል፡፡ እጩዎችንም በበቂ ሁኔታ እንዳናቀርብ አድርጐናል፡፡ በችግር ውስጥ እያለን በአጭር ጊዜ 92 እጩዎችን ማስመዝገብ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
ያለ ፓርቲው ሙሉ አባላት ተቀባይነት የእርስዎ ወደ አመራር መምጣት “አንድነት”ን እንዳልነበር አድርጐታል፣ የፓርቲውን መዋቅርም አፈራርሶታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ለፓርቲው መዳከም ተጠያቂ አይደለሁም ነው የሚሉት?
ተጠያቂ አይደለሁም፤ ምክንያቱም በህግ አግባብ የተሸነፉት ሰዎች አይደሉም እንዴ “አንድነት ፈርሷል የለም” ብለው አባላትን ወደ “ሠማያዊ” ያስኮበለሉት። “የሠማያዊ” አብዛኞቹ እጩዎች የማን ናቸው? የ “አንድነት” ናቸው፡፡
ግን እኮ አባላቱ ወደ “ሠማያዊ” የኮበለሉት የእርሶን አመራር ባለመቀበል እንደሆነ ነው የሚነገረው…?
ይሄንማ የኔ ተቀባይነት ማጣት ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም፡፡ የቀሩትንም አባላት ማሰብ አለብን፡፡
የቀሩ አባላት ቢኖሩም ፓርቲውን ከምስረታ ጀምሮ በአመራርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና ያደራጁ ሰዎች በአብዛኛው የእርስዎን አመራር አልተቀበሉትም ይባላል…
ተው እንደሱ አይደለም… ዋናዎቹ አልሄዱም። እስቲ ቁጠርልኝ… የትኛው አመራር የኔን አመራር አልቀበልም ብሎ ሄደ? አመራር ሳይሆን “እኛ ብቻ” የሚሉት ናቸው የሄዱት፡፡ ከዚያ ውጪ የቢሮ ሠራተኞች ሄደው ሊሆን ይችላል፡፡ በተረፈ ሚዲያውም ሆነ ሌላው የራሱን ስሜት ብቻ ነው የሚያራግበው፡፡
አሁን በእርስዎ አመራር ስር ምን ያህል አባላት አሉ?
በቁጥር ይሄን ያህል አልልህም፤ አንተም የሄዱትን በቁጥር ልትጠቅስልኝ አትችልም፡፡ ስለዚህ ያሉን አባላት ይሄን ያህል ናቸው ልልህ አልችልም። ፓርቲው እኮ አሁንም አደረጃጀቱንና መዋቅሩን አጠናክሮ እየሠራ ነው።
በክልሎች ያለው መዋቅራችሁ በአብዛኛው እንደፈራረሰ ይነገራል…
መዋቅር ቢኖረን አይደለም እንዴ 92 እጩዎችን በ7 ቀናት ማስመዝገብ የቻልነው፡፡ መዋቅራችንም ሆነ አደረጃጀታችን እንዳለ ነው ያለው፡፡ ያ ሁሉ “አንድነት”ን አፍርሱና ውጡ ጉትጐታ ሣይበግራቸው አባላቱ አብረውን አሉ፡፡ በየፕሬሱ ፓርቲውን እንዲለቁ ሲጐተጐት ነበር። ለነገሩ ፕሬሱ ምን አይነት አዝማሚያ እንደነበረው እኛ እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነፃ ሃሳብ ሣይሆን ግለሰብን በመውደድ የህዝብ ግንኙነት ስራ የሚሠሩ ፕሬሶች አሉ፡፡ ግን ያሁሉ ከሽፎ ምርጫው ተካሂዷል፡፡ የምርጫ ውጤት ማጣት የኛ ችግር ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም ፓርቲዎች በዜሮ ድምር ተባዝተዋል፡፡
የአመራር ውዝግቡ ባይፈጠር ግን “አንድነት” ከየትኛውም ፓርቲ በተሻለ ዝግጅት ወደ ምርጫው ገብቶ ውጤት ማስመዝገብ ይችል ነበር ብለው የሚቆጩ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ “አንድነት” ሠዎች እንደሚሉት አይደለም፡፡ የግለሰቦች ችግር የነበረበት ፓርቲ ነው። ፕሮግራሙን ከማስፈፀም አንፃር ሌላ ችግር የነበረበት ፓርቲ ነው፡፡ ምንም ውዝግብ ባይፈጠር እንደውም በራሱ ችግሮቹ ምክንያት ወደ ምርጫው ሁሉ ላይገባ ይችል ነበር፡፡ የአስተሳሰብ ችግር በውስጡ የነበረበት ፓርቲ ነው፡፡ እነዚያ ሰዎች እኮ ፓርቲውን አድምተውታል፤ አቁስለውታል፡፡ አሁን እያገገመ ነው ያለው፡፡
አንድነት እኮ አሁን ብቻ አይደለም አመራሩ የተቀየረው፡፡ ከዶ/ር ነጋሶ በኋላ እንኳ እኔ ሦስተኛ ሰው ነኝ፡፡ እነዚህ ጠንካራ ነበሩ የሚባሉት ግለሰቦች የ3 ወር የአመራር እድሜ ነው የነበራቸው፡፡ እንዴት ነው በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተገምተው ጠንካራ ናቸው የሚባሉት? እንደገና የመጡትም በአሻጥር ነው፡፡ በአመራር ላይ ሲሰሩ የነበረው አሻጥር ነው እነሱኑ መልሶ የበላቸው። “አንድነት” ተዳክሟል የሚባል ከሆነ፣ በኔ አመራር ሳይሆን ተያይዞ በመጣ ችግር ነው የደከመው፡፡ ችግሩ የጀመረው በዶ/ር ነጋሶ አመራር ጊዜ ነው፡፡ “እሣቸው ጠንካራ ስለነበሩ  አቻችለው ይዘው ቆዩ፤ ዛሬ ትዕግስቱ ስለያዘው ወደቀ” ማለት አይቻልም፡፡
እርስዎ ከዚህ በፊት ለፓርቲው ፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው 1 ድምጽ ብቻ ነው ያገኙት ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ይሄ ብዙ ጊዜ ይባላል፡፡ በዲሞክራሲ የማያምኑ ሰዎች የሚያወሩት ነው፡፡
እርስዎ 1 ድምጽ ብቻ ማግኘትዎ ግን እውነት ነው?
እሱን የሚያውቀው በወቅቱ የነበረው አስመራጭ ኮሚቴ ነው፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ተብሎ የሚወራ ነገር ነው። ይሄን ጥያቄ ደግሞ በዚህ ሰአት እንድጠየቅ ፈጽሞ አልፈልግም፡፡ ቆይ ለምን አሁን ስለተመረጥኩበት 160 ድምጽ አታነሳም፡፡ እሱን ለምን አትናገሩትም፡፡ ደግሞ አሁን ያለፈ ታሪክ አይደለም ማውራት ያለበን፡፡
ወደሱም ልመጣ ነበር እኮ… በውድድሩ አንድ ድምጽ ብቻ አግኝተው ብዙም ሣይቆዩ እንዴት በ160 ድምጽ ተመረጡ… የሚለውን የሚጠይቁ ወገኖች አሉ…
ይሄ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ፣ የፀለምተኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር የለም፡፡ ትናንት 1 ድምጽ አግኝቶ፣ ዛሬ እንዴት 160 ድምፅ ሊያገኝ ይችላል? የሚለው አያስኬድም። ይሄ የሂሣብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገሩ ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ የሚውል ስለሆነ አሁን ምንም የምለው ነገር የለኝም።
ቀደም ሲል ፓርቲው ከአሜሪካና በተለያዩ ሃገራት ካሉ ደጋፊዎቹ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ሲገለፅ ነበር፡፡ አሁንስ ድጋፉ ሳይቋረጥ ቀጥሏል? ወይስ…
ፓርቲው በፊት ስንት ያገኝ እንደነበር ስለማናውቅ ይሄን ለመግለጽ ይከብደናል፡፡ እኛ የምናገኘውን የድጋፍ መጠን በተመለከተም ለመናገር የምንገደድ አይመስለኝም፡፡ ፓርቲው ተቋም እንደመሆኑ ድጋፍ አለው፡፡ በአመራር ደረጃ የግለሰቦችን መፈራረቅ ተመልክተው የሚሸሹ ሰዎች የሉም፡፡ “እኔ ፓርቲውን ካልመራሁት ደክሟል” ማለት፣ የጨለምተኝነት አስተሳሰብ ነው እንጂ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ “አንድነት” ደግሞ እነዚህን ሰዎች ሠርጐ ገቦች አድርጐ ነው የሚወስዳቸው፡፡ ባህሪው አይደለማ!
ከምርጫ ቦርድ ለምርጫው ማስፈፀሚያ የተሰጣችሁን ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ ለምን ተግባር ነው ያዋላችሁት?
ሙሉ ለሙሉ ለምርጫው ቅስቀሳ ነው  ያዋልነው፡፡
አንዳንድ የፓርቲው እጩዎች ግን በገንዘብ እጦት የቅስቀሳ ፖስተራቸውን እንኳ
ሳይለጥፉ እንደቀሩ ይነገራል…
የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ለእጩዎች ገንዘብ ሰጥተናል። በስንፍና ያልለጠፈ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛ ግን ገንዘቡን ለፓርቲው ሙሉ እንቅስቃሴ ነው ያዋልነው፡፡ ሌላው የጀነራል ኦዲተር ስራ ነው፡፡
አሁንም በመካከላችሁ የአመራርና የአባላት ቅራኔና መከፋፈል እንዳለ ይወራል…?
የለብንም፡፡ ችግር ያለበት አመራር ካለ ሊጠየቅ ይችላል፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ የአመራር መከፋፈል  የለም፡፡
ፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የለውም፡፡ ለምንድን ነው?
አልሾምንም!!
እስካሁን ያልተሾመበት የተለየ ምክንያት አለው?
ምንም ምክንያት የለውም፡፡ በቃ ለቦታው የሚሆን ብቃት ያለውን ሰው ፈልገን እስከምናገኝ ድረስ ነው፡፡ እኛ እኮ ገና አሁን ነው ከችግር ውስጥ የወጣነው፡፡
የእርስዎን ካቢኔ ሊነግሩኝ ይችላሉ፡፡ እነማንን ያካትታል?
አሁን ካቢኔውን ማሳወቅ የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡
ግን ፓርቲው ካቢኔ አለው?
አዎ አለው! ግን አሁን ማሳወቅ አይጠበቅብኝም፡፡
ፓርቲው ግልጽ አሠራር የሚከተል ከሆነ፣ ደጋፊዎቹና ህዝቡ ካቢኔውን ቢያውቁ ምን አለበት?
ተወው እሱን! ከአመራርነት ወጣን የሚሉ ሰዎች “የካቢኔ አባል ነን” የሚሉ ከሆነ፣ እነሱን አግኝተህ ጠይቅ። በ“አንድነት” ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሯል የምትለኝም አያስደንቀኝም፤ ብዙ ፍላጐት ያለበት ቤት ስለሆነ ሰዎች የየራሳቸውን ነገር ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የምንመራው በስርአት ስለሆነ ስርአቱ ራሱ ይገዛናል፡፡
ቀደም ሲል “አንድነት” አልፈርምም ያለውን የስነ ምግባር ደንብ ፈርማችሁ,ኧ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የመግባት እቅድ አላችሁ?
አሁን እቅድ አለን የሚል መልስ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ከ “መድረክ” ጋር ስለነበርን የመድረክን አቋም ነው ፓርቲው ያራመደው፤ አሁን ከመድረክ ጋር አይደለንም፡፡ በሌላ በኩል ከመድረክ ጋር ያለን ግንኙነትም አለ፡፡ እስካሁን ግን በምርጫ ሂደት ውስጥ ስለነበርን በጉዳዩ ላይ ተወያይተን ውሳኔ አልሰጠንበትም። በቀጣይ የሚታይ ይሆናል። የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል መሆን ያለመሆን ጉዳይም ሆነ መድረክ መልሶ በመቀላቀል ላይ የተወሰነ ነገር የለም፡፡
“አንድነት በአመራር ሽኩቻ ምክንያት ተቀባይነት እያጣ መጥቷል” የሚለው ጉዳይ ከፓርቲው የወደፊት እጣ ፈንታ አንፃር አያሳስቦትም?
አያሳስበኝም፡፡ ምክንያቱም “አመራር ነን” ብለው “አመራር አይደላችሁም” የተባሉት ሰዎች፣ ትክክል ናቸው የሚል አዝማሚያ ስላለ ነው፡፡ ፓርቲዎች ለህግ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ እኛ በህግ አሸነፍን፤ እነሱ ግን በኔትወርክ ለመጓዝ ነበር ሃሳባቸው፡፡
አንዳንድ ወገኖች ከመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለዎት ይናገራሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ምንም ድጋፍ የለኝም! ህግን ከማስከበር አኳያ መንግስት ድጋፍ በማድረጉ ሃላፊነቱን ነው የተወጣው። እንዴ! እነሱ በኔትወርክ የሄዱት እኮ ለባለስልጣኖች ድጋፍ ነበር፤ ግን አልተሳካም። እዚህ ቤት ከዚህ በኋላም ባለፈው የተፈጠረው ስሜት ሊፈጠር ይችላል፤ ማንም ዋስትና የለውም። አሁንም የቡድን ስሜቶች ያሉበት ቤት ነው፡፡ አሁን “አንድነት”ን የሚመራው አንድ አመራር ነው። እነዚህ ሰዎች በፓርቲው ስም እንንቀሳቀሳለን ቢሉ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ ይሄን የሚያራግብ የሚዲያ አካልም ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
የአንድነትን አመራር ለመከፋፈል ላደረጉት ውለታ የፓርቲውን መዳከም ከሚፈልጉ ወገኖች  ገንዘብ ተሰጥቶታል፣ መኪናም ገዝተዋል…” የሚሉ መረጃዎች ይናፈሳሉ
ማን ነው ያለው?
“ከአንድነት” የወጡ የቀድሞ አባላት በማህበራዊ ሚዲያው በስፋት እየፃፉበት ነው
ማህበራዊ ሚዲያው ሃላፊነት የሚሠማው ስላልሆነ አላምንበትም፡፡ በሶሻል ሚዲያ ለሚወራው ነገር ብዙም ትኩረት ስለማልሰጠው በዚህ ላይ ጊዜዬን ማጥፋት አልፈልግም፡፡ በማላምንባቸው ሚዲያዎች የቀረበ ስም ማጥፋት ስለሆነ አልቀበለውም፡፡
ግን እኮ ይሄን የሚሉት የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች ናቸው፡፡ እናንተም በሬዲዮ የፓርቲውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ብላችሁ ስትወነጅሉ ነበር፡፡ የእርስዎን በተመለከተ ለምን ቀጥተኛ ምላሽ አይሰጡኝም?  
እኔ የገዛሁት መኪናም የለም፡፡ ያገኘሁት የውለታ ገንዘብም (Reward) የለም፡፡ “ሪዋርድ” ላገኝ የምችልበት መንገድም የለም፤ በዚያ ላይ ፓርቲውን አላፈረስኩም፤ ይዤ ነው የቀጠልኩት።
ለ20 አመት ያህል በተቃዋሚ ውስጥ ያለሁ ሰው ነኝ። ከኢህአዴግ ጉርሻ አግኝቷል የሚሉት  በሃሳብ የበላይነት ተሸንፈው የወጡት ናቸው፡፡
“ሠማያዊ” ፓርቲን የመሠረቱት ሰዎችም ዛሬ ጀግና ሊባሉ በፊት እንዲህ ተብለው ነበር፡፡ እዚህ ፓርቲ ውስጥ ሲታገሉ ለእስር የተዳረጉት እነ ሃብታሙ አያሌውም ታስረው እንኳ አያምኗቸውም ነበር…ከነዚህ ሰዎች ጋር ነው እንዴ የኖርነው፡፡
እናንተ የታሠሩትን የአንድነት አባሎችና አመራሮች ትጠይቃላችሁ?
አዎ፤ እኔ አልቻልኩም እንጂ የኛ ልጆች ሄደው ይጠይቃሉ፡፡
የታሠሩት የፓርቲው አመራሮች ለእርሶ ድጋፍ እንዳላቸው አረጋግጠዋል?
እነሱ በህግ ጥላ ስር ስለሆኑ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማወቅ ያስቸግራል። የነሱን ፍላጐት ለመረዳት ግን አልሞከርንም፡፡ እኔ እንደምረዳው… “አንድነት” የታገሉለት ፓርቲ እንደመሆኑ… ከሱ ውጪ ሌላ አተያይ አላቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኛ የምናስበው፤ የኛ አርአያና የትግል ጽናት ተምሣሌዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ትግላችንም እንዲፈቱ ነው፡፡

አራት ታላላቅ የአፍሪካ ኩባንያዎች ለመጨረሻው ዙር ደርሰዋል

    የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ ስኬታማ ኩባንያዎች  በማለት ለመጨረሻው ዙር ከመረጣቸውና ለቀጣዩ ሽልማት ካጫቸው አራት ግዙፍ የአህጉሪቱ አየር መንገዶች አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ፎረሙ ከአፍሪካ አልፈው በአለማቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚው ዘርፍ መሪ የመሆን አቅም ያላቸው የአህጉሪቱ ኩባንያዎችን ለመምረጥ ባከናወነው ሂደት፣ ለመጨረሻው ዙር የደረሱትን 4 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኩባንያዎች ዝርዝር ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ባካሄደው ጉባኤው ይፋ አድርጓል፡፡ ለመጨረሻው ዙር በዕጩነት የቀረቡት አራቱ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የዝምባዌው የንግድና የሆቴል ኢንቨስትመንት ኩባንያ ሜክሌስ፣ የደቡብ አፍሪካው ሲሚንቶ አምራች ፒፒሲ እና የናይጀሪያው ነዳጅ አምራች ኩባንያ ዋልተርስሚዝ ፔትሮማን ኦይል ናቸው፡፡
በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የኒው ሻምፒየንስ ማኔጂን ዳይሬክተርና ሃላፊ የሆኑት ዴቪድ አኪማን በጉባኤው ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ፎረሙ ሃላፊነት የሚሰማው የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና የስራ ፈጠራን በማስፋፋት ረገድ በአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ለሚመሩት ለእነዚህ አራት ኩባንያዎች እውቅና በመስጠቱ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በትርፋማነት እድገት፣ በፈጠራ የታገዙ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ተግባራዊ በማድረግና አመራር በኩባንያዎች እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ሚና በተግባር በመግለጽ ረገድ በአህጉሪቱ የላቁ ሆነው በመገኘታቸው ለመጨረሻው ዙር መብቃታቸው ተገልጧል፡፡
በመጪው መስከረም ወር በቻይና በሚካሄደው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የኒው ሻምፒዮንስ አመታዊ ጉባኤ ላይ በሚከናወን ስነስርዓት ከአራቱ ኩባንያዎች አሸናፊው ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

አስከሬኑ ወደ ለንደን ተወስዶ እንዲመረመር ተጠየቀ

       በደቡብ ሱዳን ዐማፅያን ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው ዋኒ ቶምቤ ላኮ በአዲስ አበባ በመኖርያ አፓርትመንታቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ፤ ቤተሰቦቻቸው አስከሬናቸው ወደ ለንደን ተወስዶ እንዲመረመር ጠይቀዋል፡፡
በለንደን በስደት ይኖሩ የነበሩት ቶምቤ፤ ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቀድሞው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻር የሚመራውን የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድን ተቀላቅለዋል፡፡ በተቃዋሚው ቡድን ውስጥ የተለየ የኃላፊነተ ቦታ ባይሰጣቸውም ሚያዚያ አጋማሽ ላይ በተደረገው የዐማፅያኑ የከፍተኛ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የተቃዋሚው መሪ ሬክ ማቻር የቶምቤን ሞት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ የእርሳቸው መሞት ለደቡብ ሱዳን፣ ለተቃዋሚ ቡድን እና ለቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደሆነ በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የሞታቸውን መንስኤ በተመለከተ ከሐኪም የተሰጠ መረጃ ባይኖርም በቅርብ የሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው በልብ ድካም ህይወታቸው አልፎ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የቶምቤ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ አስከሬናቸው ለንደን ሄዶ እንዲመረመር መጠየቃቸውን “ሱዳን ትሪቢዩን” ዘግቧል፡፡
ቶምቤ፣ በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በአውስትራልያ በመዘዋወር ደቡብ ሱዳናውያን አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለመጣል የትጥቅ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ሰፊ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል፡፡

  ፖሊስ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል

    በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን ምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ፣ የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና የደብሩ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት “ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
የወረዳው ፖሊስ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ እና በዚኽ ሳምንት ሰኞ ስድስት የሰበካ ጉባኤውንና የቤተ ክርስቲያኒቱን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት በቁጥጥር ሥር በማዋል በቂልጦ ወረዳ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል፡፡
ግለሰቦቹ “የድረሱልኝ ጥሪ” በሚል “ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ጽሑፍ ጽፈው በፌስቡክ አሰራጭተዋል” ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ግለሰቦቹ “የድረሱልኝ ጥሪ”  በሚል ደብዳቤ መጻፋቸውን ቢያምኑም በፌስቡክ አለመልቀቃቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ግለሰቦች ላይ የማጣራው ነገር አለ በሚል የ21 ቀን የምርመራ ጊዜ የጠየቀባቸው ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዶለታል፡፡
የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሓላፊ አቶ ቶፊቅ ከድር፣ ስለ ጉዳዩ በስልክ ጠይቀናቸው፤ “በሕግ የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት አልችልም” ብለዋል፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት የቂልጦ ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ እና ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት÷ ሊቀ መንበሩ መ/ር የማርያም ወርቅ ተሻገር፣ መ/ር ሀብታሙ ተካ፣ አቶ ሙሉጌታ አራጋው፣ ወ/ሪት ንጋት ለማ፣ አቶ ማስረሻ ሰይፈ እና አቶ ማሩ ለማ ሲሆኑ በወረዳው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት፣ የፖሊስ፣ የጤና እና የግብርና ጽ/ቤቶች እንዲሁም የባንክ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ናቸው፡፡
‹‹የድረሱልኝ ጥሪ›› በሚል ርእስ የተሰራጨውና የደብሩን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ማኅተም የያዘው ጽሑፍ÷ በስልጤ ዞን በምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን፣ በሃይማኖታዊ ማንነታቸው ላይ ባለሥልጣናት ይፈጽሙብናል ባሏቸው ግፎች መማረራቸውን፣ የአምልኮ ነጻነታቸው እና ሠርተው የመኖር ዋስትናቸውም አደጋ ላይ መውደቁን ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠባት መሆኗን በፅሁፋቸው የጠቆሙት ምእመናኑ፣ ስለሚፈጸምባቸው ግፍና ሥቃይ ለወረዳው የፖሊስ እና የሕግ አካላት በየደረጃው ቢያመለክቱም የአስተዳደሩ መዋቅር እና አሠራር ያልተገባ “ሕጋዊ ሽፋን” በመስጠቱ የጥቃቱ ስልት ዐይነት እየጠነከረ መጣ እንጂ መፍትሔ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በየመኖሪያ አካባቢያችንና በሥራ ቦታዎች እየደረሰብን ነው ያሉት እስር፣ እንግልት፣ ዛቻ፣ እንዲሁም በመ/ቤት ከደረጃ ዝቅ መደረግና መታገድ እና መባረር እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት ምእምኑ፣ ድርጊቱ የተባባሰው፤ የቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ተረክበው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጡበት ከጥቅምት 24 ቀን 2007 ወዲህ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለመንግሥት እና ለቤተ ክህነት አካላት አቤቱታቸውን ያሰሙበት “የድረሱልኝ ጥሪ” የሚለው ይኸው ጽሑፍ፣ የሀገረ ስብከቱን ፈቃድ በመጠየቅ የተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ምእመናኑ በአንዳንድ ባለሥልጣናት የሚደርስባቸውን ሥቃይ በመዘርዘር መፍትሔ የጠየቁበት እንደሆነ ጠቁመው፤ “ታምኑበታላችኹ ወይስ አታምኑበትም” እየተባለ ሃይማኖታዊ ግጭት እንደቀሰቀስንና የወረዳውን ስም እንዳጠፋን ተደርገን መታየታችን አሳዝኖናል ሲሉ ርምጃውን ተቃውመዋል፡፡
ቀድሞ ያስቀድሱበትና የመካነ መቃብር አገልግሎት ያገኙበት የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከ20 ዓመት በፊት መቃጠሉን ያስታወሱት ምእመናኑ፣ በምትኩ የሚያሠሩት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኒቱ መቃኞ በመጪው ሰኔ 21 ቀን የሚመረቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሃዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች እንዲሁም የሰበካው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከወረዳው አስተዳደር ጋር በጉዳዩ ላይ እየተነጋገሩበት እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹የድረሱልኝ ጥሪ›› በሚል በፌስቡክ ተሰራጭቷል ለተባለው ጽሑፍ የታሰሩት የሰበካ ጉባኤ አባላት ማስተባበያ እንዲሰጡና መሳሳታቸውን አምነው ይቅርታ እንዲጠይቁ በማግባባት ከእስር ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ምንጮቹ አክለው ገልፀዋል፡፡

Saturday, 30 May 2015 12:52

የትንፋሽ ህክምና

ክብደትን ለመቀነስ

በመሬት ላይ እግርዎን አጣጥፈው ይቀመጡ፤

ወገብዎን ቀና፣ ሆድዎን ወደ ውስጥ ሳብ ያድርጉት፤

ግራ እጅዎን ጉልበትዎ ላይ ያድርጉ፣ በቀኝ እጅዎ

ሌባ ጣት የግራ አፍንጫዎን ይዝጉት፡፡ ወደ ውጪ

ይተንፍሱ፣ ይ ህንን በ መደጋገም ይ ከውኑ። በቀን

ውስጥ በተመችዎ ጊዜ የቻሉትን ያህል ለመሥራት

ይሞክሩ፡፡ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ክብደትዎ

መቀነሱንና የምግብ ፍላጎትዎ መቆጠቡን

ይታዘባሉ። እስቲ አሁኑኑ ይሞክሩት …

(ምንጭ፡- ታይም መፅሔት

June 2011)

Saturday, 30 May 2015 12:44

የሰውነታችን እውነታዎች

 

 

 

- ጨጓራችን የላም ወተትን ለማብላላት አንድ

ሰዓት ይፈጅበታል

- የሴቶች አይን ከወንዶች ይልቅ በእጥፉ

ይርገበገባል

- አንድ ሰው በአማካይ 2 ሚሊዮን የላብ

እጢዎች ይኖሩታል

- ህፃናት ሲወለዱ የጉልበት ሎሚ

አይኖራቸውም፤ ይህ ሰውነት ክፍል

የሚወጣው ከ2-6 ዓመት ባለው የህፃናቱ

እድሜ ውስጥ ጊዜ ነው

- በፀደይ ወራት የህፃናት እድገት ፈጣን ነው

 

 

 

 

Saturday, 30 May 2015 12:40

የግጥም ጥግ

እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞገጉ

“ሥጋችን የት ሄደ” ብለው ሲፈልጉ

በየሸንተረሩ በየጥጋጥጉ

አስሰው አስሰው በምድር በሰማይ

አገኙት ቦርጭ ሆኖ አንድ ሰው ገላ ላይ፡፡

(“ኗሪ አልባ ጎጆዎች”፤ በዕውቀቱ ስዩም)

Saturday, 30 May 2015 12:39

የፍቅር ጥግ

 

 

 

* ፍቅር በፈገግታ ይጀምራል፤በመሳሳም ያድጋል፤በእንባ ይቋጫል፡፡

            ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር እንደ ነፋስ ነው፤አታየውም ግን ይሰማሃል፡፡

            ኒኮላስ ስፓርክስ

* ምክንያት የሌለው ፍቅር ዕድሜው ረዥም ነው፡፡

            ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር አብሮን የተፈጠረ ሲሆን ፍርሃት እዚህ የምንማረው ነው፡፡

            ማሪያኔ ዊላምሰን

* የሚወደን ሰው ከሌለ፣ ራሳችንን መውደድ ትተናል ማለት ነው፡፡

      ማዳም ዲ ስቴል

* ራሳችሁን ማፍቀር እንዳትረሱ፡፡

      ሶረን ኪርክጋርድ-

* ሰውን መውደድ የእግዜርን ፊት ማየት ነው፡፡

      ሌስ ሚዘረብልስ

* ፍቅር ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከባድ ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ይጎዳል፡፡

      ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር ሲይዘን በጣም የምናምነውን ነገር እንጠራጠራለን፡፡

      ላ ሮቼፎካልድ

* ስለፍቅር የምናውቀውን ብዙውን ነገር የምንማረው ከቤት ነው፡፡

      ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር ከምንም በላይ የራስ ስጦታ ነው፡፡

      ጄን አኖይልህ

* በፍቅር መውደቅ ቀላል ነው፤ከባዱ የሚያነሳህ ሰው ማግኘቱ ነው፡፡

      በርትራንድ ራሴል

* ልብህን ለከፈትክላቸው ሰዎች አንደበትህን አትዝጋባቸው፡፡

      ቻርልስ ዲከንስ

* ፍቅር፤የሌላው ሰው ደስታ ለራስህ ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ ነው፡፡

      ሮበርት ሄይንሊን

ሰው ሊደብቃቸው የማይችላቸው ሁለት ነገሮች፡ ስካር እና ፍቅር፡፡

አንቲፋንስ

* ሰዎችን የምትተች ከሆነ ለመውደድ ጊዜ አይኖርህም፡፡

ማዘር ቴሬዛ

 

 

 

 

 

 

 

ኢትዮጵያዊ ፊልሞችን የሚሰራው “ካም ግሎባል ፒክቸርስ” የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፈው ረቡዕ ለስድስት እውቅ ተዋንያን የክብር ሽልማት ሰጠ፡፡ ተሸላሚዎቹ አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ግሩም ኤርሚያስ፣ ማህደር አሰፋ፣ አማኑኤል ሀብታሙ እና የትናየት ታምራት ሲሆኑ ሁሉም ተዋናዮች ባለፉት ዓመታት ”ካም ግሎባል ፒክቸርስ” በሰራቸው ፊልሞች ላይ መተወናቸው ታውቋል፡፡ ድርጅቱ ከሰራቸው ፊልሞች መካከል “ስውሩ እስረኛ”፣ “በራሪ ልቦች”፣ “አማላዩ”፣ “ሼፉ” (ቁጥር 1 እና 2)፣ “ወደ ገደለው” እና “አማረኝ” ይገኙበታል፡፡

 

 

 

 

“እስኪ ተጠየቁ” የተሰኘው የዮሐንስ አድማሱ የግጥም መድበል ነገ በ8 ሰዓት በብሄራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት ይደረግበታል፡፡ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት አርክቴክትና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው እንደሆኑ ታውቋል፡፡ውይይቱን ያዘጋጁት እናት የማስታወቂያ ድርጅት፣ ጀርመን የባህል ማዕከልና ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ በጋራ ሲሆን የሥነፅሁፍ ቤተሰቦች በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡