Administrator

Administrator

 የደቡብ ኮርያ መንግስት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ ጫና ለማቃለል በሚል 1.6 ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎቹ የነበረባቸውን የገንዘብ ዕዳ በከፊል ለመሰረዝ ማቀዱን ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የዕዳ ስረዛውን ተግባራዊ የሚያደርገው እስከ 9ሺህ 128 ዶላር ዕዳ ላለባቸውና የመክፈል አቅም ለሌላቸው ዜጎቹ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ስረዛው የሚመለከታቸው ዜጎች ከመጪው የካቲት ወር ጀምሮ የዕዳ ስረዛ እንዲደረግላቸው ማመልከቻ እንዲያስገቡ ጥሪ ማቅረቡን አመልክቷል፡፡ ለዕዳ ስረዛው ማመልከት የሚችሉት ዜጎች ወርሃዊ ገቢያቸው ከ910 ዶላር በታች የሆነና ዕዳቸውን ለመክፈል ከአስር አመታት በላይ የተሰቃዩና ያልተሳካለቸው መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ማቅረብ የሚችሉ ብቻ እንደሆኑም ዘገባው ገልጧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት “የደስታ እርዳታ” በሚል የሰየመውና ዕዳቸውን ለመክፈል ያልቻሉ ችግረኛ ደቡብ ኮርያውያንን አቅም የማጎልበት አላማ ያለው ፕሮግራሙ፤ ከዜጎች ያገኝ የነበረውን ገንዘብ ከሌሎች አበዳሪዎች አግኝቶ ለማካካስ ማቀዱንም ዘገባው አስረድቷል፡፡

 በየአመቱ እስከ 169 ሺህ ህጻናት በመሰል መድሃኒቶች ሳቢያ ይሞታሉ

   በማደግ ላይ በሚገኙ የአለማችን ድሃ አገራት ጥቅም ላይ ከሚውሉት የተለያዩ አይነት መድሃኒቶች ውስጥ 10 በመቶ ያህሉ ከሚገባው የጥራት ደረጃ በታች ወይም ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉና የተጭበረበሩ እንደሆኑ የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ማክሰኞ በጄኔቭ በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፣ የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁና በህገወጥ መንገድ ተመርተው ጥቅም ላይ የሚውሉት መሰል አደገኛ መድሃኒቶች በአለማቀፍ ደረጃ በስፋትና በፍጥነት እየተሰራጩ ሲሆን መድሃኒቶቹ ለከፋ የጤና ጉዳት ከመዳረጋቸው ባለፈ ለሞት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡
ከጥራት ደረጃ የሆኑና የተጭበረበሩ ሀሰተኛ ጎጂ መድሃኒቶች በብዛት በጥቅም ላይ የሚውሉት በአብዛኛው በአፍሪካ አገራት ውስጥ ቢሆንም፣ ችግሩ አለማቀፍ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ መሰል ጥራታቸውን ያልጠበቁ መድሃኒቶች መካከል ለወባ ህክምና የሚውሉና አንቲባዮቲክሶች እንደሚገኙበት እንዲሁም፣ ለካንሰር ህክምና የሚውሉና የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶችም ከጥራት በታች አልያም በተጭበረበረ መንገድ ተሰርተው በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መሰል መድሃኒቶች ከማዳን ይልቅ ህመምን በማባባስ ለከፋ ስቃይ የሚዳርጉ፣ ያለ አግባብ ወጪ የሚያስወጡና የመዳን ተስፋን የሚያጨልሙ ናቸው ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በሂደትም የትክክለኛ መድሃኒቶችን የማዳን አቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው በአለማቀፍ ደረጃ አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል፡፡
የአለማችን አገራት መንግስታት በገበያ ላይ ውለው በዜጎች ላይ እስከ ሞት የሚያደርሱ ጉዳቶችን የሚያደርሱ መሰል መድሃኒቶችን በጥብቅ ቁጥጥር እንዲያስወግዱና ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ከ48 ሺህ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ የመድሃኒት አይነቶች ላይ የተሰሩ 100 የጥራት ደረጃ ፍተሻ ጥናቶችን በመገምገም ባገኘው ውጤት እንዳለው፣ በየአመቱ እስከ 169 ሺህ የሚደርሱ የአለማችን ህጻናት አደገኛ መድሃኒቶችን በመውሰዳቸው ሳቢያ ለኒሞኒያ በሽታ ተጋልጠው ለሞት ይዳረጋሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

ዮናስ ነ.ማርያም የአዲስ አድማስ ፅሁፍ አቅራቢ ነው (Contributor) የአዲስ አድማስ ቤተሰብ የሚለው የበለጠ ይገልፀዋል፡፡ አዲስ አድማስን እንደ ራሱ ጋዜጣ ነው የሚያየው- ለሱ ተብሎ ብቻ እንደሚታተምለት የግል ጋዜጣው። በጣም ይሳሳላታል፡፡ ከልቡ ነው የሚወዳት! ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ በርካታ ምርጥ አጫጭር ልብወለዶቹን ለአድማስ አንባቢያን አስነብቧል። ተወዳጅም ነበሩ- ሥራዎቹ! ከድንገተኛ ህልፈቱ አንድ ቀን በፊትም “ሸረሪቷ” የተሰኘ ትርጉም አጭር ልብ ወለድ ቢሮ ድረስ መጥቶ ለፀሃፊዎች ሰጥቶ ነበር የሄደው- እንደተለመደው
በእውነቱ ህልፈቱ ድንገተኛ፣ አሰቃቂና አሳዛኝ ነው፡፡ ሐሙስ ዕለት ጠዋት ፍልውሃ ወድቆ መገኘቱን ከፖሊስ በስልክ ሰማን። ዘውዲቱ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር፡፡ ግን ህይወቱ አልተረፈም፡፡ በእጅጉ ያሳዝናል!! ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑረው!
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልና ማኔጅመንት፤ በዮናስ ነ.ማርያም ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹና ለሥራ ባልደረጎቹ ሁሉ መፅናናትን ይመኛል!
የዮናስ ነ.ማርያም የድሮ ተማሪዎች በፌስ ቡክ
የኔ መምህሬ ነበር፤ አስተማሪዬ ሆኖ የልቡን ይነግረኝ ነበር፡፡ የኳስና የቡና ፍቅር ነበረው። ለምንም የማይደንቀው ነበር፡፡ አዝኛለሁ። አንድ ነገር ላሥቸግርህ ፎቶውን ላክልኝ፡፡ ቢያንስ በሱ ልፅናና፡፡
ናርሲሲ እና ጎልድመንድ
ዮናስ 10ኛ ክፍል ሆኜ አማርኛ አሥተምሮኛል፤ የክፍል ሃላፊዬ ሆኖ መካሪዬ ነበር፡፡ አሁን ዳኛ ነኝ፡፡ አንድ ቀን ከሩቅ ጠርቶ መንገድ ላይ የመከረኝን አልረሳውም፡፡  እዚህ ለመድረሴ የእነሱ እጁ አለበት፡፡ ሁሌ ባገኘው እመኝ ነበር። ጌታ ያለው ሆነ፡፡ በጣምምምም ያሣዝናል።
ሮዝ የሉላ
ዮኒ መምህሬ ነበር፡፡ ጓደኛዬም ነው፡፡ ኳስ አብረን እንጫወት ነበር፡፡ መንፈሳዊ-ማንነቴንም ቀርፆታል፡፡ ባገኘሁ እያልኩ ሁሉ እጓጓ ነበር። የክፍላችን ተማሪዎች በቁጥር ሃምሳ ነበርን፡፡ ሃምሳችንም እንወደው ነበር ብልህ ታምናለህ!!
በሚያስተምርበት ክፍለ ጊዜ-ሃያ ደቂቃ ያህል ቀድሞ የሚገኝበት ጊዜ ነበር፡፡ በጣም ብዙ ነገር ያሣውቅሃል፡፡ ብዙ ነገር ትማራለህ፡፡ ስለ ዮኒ ምን ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ በቃ…በቃ
ዘላለም ከሚዛን ተፈሪ (በስልክ)
ከልቅሶ ጋር፡-
ጥበብ እና አዲስ አድማስ አንድ ውድ ልጅ አጡ!
በተስፋዬ አለነ
ዜና እረፍቱን ያነበብኩት ከደረጀ በላይነህ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ነበር። ዓይኖቼን ማመን አልቻልኩም፡፡
ቸው ወዳለኝ አንዳንድ ጋዜጠኞች ዘንድ ደዋወልኩ፡፡ ገሚሶቹ መርዶ አርጂ ሆንኩባቸው። ከዚያ ወደ አዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እና አንተነህ ይግዛው ዘንድ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ሰደድኩ፡፡ናፍቆት ፈጥና መልስ ሰጠችኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡  ‹‹ውይ! ግን እውነት ባልሆነ›› አልኳት፡፡
የመረጃ ምንጬ ደራሲና ጋዜጠኛ ደረጀ በላይነህ ነውና፤ እውነቱን እንዲያረጋግጥልኝ ጠየቅኩት፡፡የደራሲና ጋዜጠኛ ዮናስ ነማርያምን ህልፈት አረጋገጠልኝ፡፡ እውነት እስካሁን ማመን ከብዶኛል፡፡ በሳል ጸሐፊ እንደነበር ብዙዎች ያምኑበታል፡፡ ለሕትመት የተዘጋጁ ከ50 በላይ የአጭር ልብ ወለድ ድርሰቶች እጁ ላይ እንዳሉ ገልፆልኝ ነበር፡፡ (ይህ የቁጥር መረጃ በወርሃ ሐምሌ በራሱ አንደበት የሰጠኝነው) የዮኒ ሥራዎች ምርጥ ናቸው። አዲስ አድማስን የሚያነብ ሰው፣ የዮኒ ሥራ ምን ሊሆን እንደሚችል ያውቃል። ለመጻፍ እንጂ ለማሳተም የማይጓጓ ሰው ነበር፡፡ እባክህ ‹‹ጠርዝና መጽሐፍ አድርገህ ሥጠን!›› ብዬው ‹‹ሁሉንም ከጊዜ ጋር እናየዋለን››! ብሎኝ ነበር፡፡ እነሆ ጊዜ የፈቀደውን አደረገ፡፡
በቅርቡ የወጣውን መጽሐፌን በተመለከተደውሎ ሲያወራኝ፣ ለኔ ስኬት ፍጹም ተደሳቹ እሱ ነበር። በልጅነት ታሪኮቻችን ዙርያ የሚያትተውን  ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› የተሰኘውን መጽሐፌን፣ ወደ ሩሲያ ቋንቋ እንዲተረጎም እንደሚፈልግና ለዚህም አንድ ስመ-ጥር የሀገራችንን ተርጓሚ እያናገረ እንደሆነ ገልፆልኝ ነበር። ‹‹ነበር›› እያልኩ ሳወራ አፌን መረረኝ። ወዳጅ ዘመዶቹን ሁሉ እግዚአብሔር ያፅናችሁ!!፡፡
ነፍስህን በገነት ያኑረው ወንድሜ። ሁሌም በልቤ ውስጥ ትኖራለህ ዮኒዬ! በሰላም እረፍ!

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ የወደፊት የአገዛዝ ዕጣ-ፈንታውን ለማወቅ ወደ አንድ አዋቂ ዘንድ ይሄዳል፡፡ አዋቂውም ተመራምሮና አስቦ፤
“አገዛዝህ እንዲቃና ሰው መሰዋት አለብህ፡፡ ይህ የምትሰዋው ሰው እጅግ ሀብታም ነጋዴ መሆን አለበት” አለው፡፡
ንጉሡ፤ “ከአገሩ ነጋዴዎች ሁሉ እጅግ የናጠጠ ሀብታም የሚባለውን አምጡልኝ” ብሎ አዘዘ፡፡
የታወቀው ሀብታም ግን በጣም ራቅ ወዳለ ዳር-አገር ሄዶ ኖሮ ሊገኝ አልቻለም፡፡
ውሎ አድሮ ግን ያ ነጋዴ ከሄደበት አገር እየተመለሰ ሳለ፣ ወንበዴዎች ያገኙትና እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ደብድበው፣ እጅ እግሩን ሰባብረው፣ ገንዘቡን ሁሉ ዘርፈው፣ ሜዳ ላይ ይጥሉታል፡፡
ሌሎች በዚያ መንገድ የሚመጡ ነጋዴዎች፣ ያ ታላቁ ነጋዴ፣ እንዳይሆን ሆኖ ወድቆ ያገኙትና አዝነው ተሸክመው ያመጡታል፡፡
ይሄንን ያወቁት የንጉሡ ባለሟሎች፤
“ንጉሥ ሆይ! የምንፈልገው ነጋዴ መጥቷል፡፡ ሆኖም በጣም ተጎድቶ ከሰውነት ውጪ ሆኗል፡፡ ምን እናድርግ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ንጉሡም፤
“ዋናው በህይወት መገኘቱ ነው፡፡ አምጡትና ወደ አዋቂው ይዤው እሄዳለሁ” ይላሉ፡፡
ነጋዴው ተይዞ መጣ፡፡ ወደ አዋቂውም ይዘውት ሄዱ፡፡ ለአዋቂውም፤
“መሰዋት ያለበት ነጋዴ መጥቷል” ሲሉ አሳወቁ፡፡
አዋቂው ነጋዴውን፤
“ተነስና እስከዛሬ የት እንደነበርክ አስረዳኝ” አለው
ነጋዴው ግን፤
“መቆም አልችልም፡፡ እግሬም፣ እጄም ተሰባብሯል” አለው::
አዋቂው ወደ ንጉሡ ዞረና፤
“ንጉሥ ሆይ! በጣም አዝናለሁ፡፡ አማልክቱ ከሰውነቱ ምንም ነገር የጎደለን ሰው በመስዋዕትነት አይቀበሉም! ይህ ማለት ዙፋንዎ አደጋ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ነጋዴም በሽፍቶች መደብደቡ ለበጎ ቢለው ነው! ከእንግዲህ የሚመጣውን መቀበል ብቻ ነው ያለብዎት!” ብሎ አሰናበታቸው፡፡
ዕጣ- ፈንታችን አስቀድሞ የተፃፈልን ነው፤ ቢባልም የየዕለት ክፉና ደግ ተግባራችን አጠቃላይ ጥርቅም ነው! ስለሆነም የየቀኗን ተግባራችንን ማታ በተመስጦ ካላሰብናት ክፉና ደጉን ለመለየት ይሳነናል፡፡ ምናልባትም በሰው ላይ ያደረግነው ሁሉ ተጠራቅሞ ምሬትን፣ ብሶትንና ሐዘንን ባንድነት እያቆርን ይሆናል፡፡ ያም በቀልን፣ አመፃንና አሰቃቂ ፍፃሜን እየወለደ ሊመጣ ይችላል። የቆምንበትን መሠረት ቀስ በቀስ እየሰነጣጠቀ እየናደ ህልውናችንን ከናካቴው ሊያሳጣንም ይችላል። አበው  የፖለቲካ ጠበብት፤ “ገዢው መግዛት ሲያቅተው፤ ተገዢው በቃኝ፣ አልገዛም ሲል፣ ህሊናዊና ነባራዊው ቅድመ፣ ሁኔታ ተሟልቶ ላዕላይ-መዋቅሩ (Super-structure) ይፈረካከሳል። ያኔ ዝግጁ የሆነ የተደራጀ ኃይል አካል ከሌለ አገር ወዳልተጠበቀ ውጥንቅጥ ውስጥ ትገባለች፡፡ ይህንን የሚያስተውል አርቆ አሳቢ ያስፈልጋል” ይሉናል፡፡ ይህንን ጉዳይ ማንም የነቃ ዜጋ ሊስተው አይገባም፡፡ የፓርቲ የፖለቲካ መሸርሸር እንደ ፀጉር መመለጥ ሁሉ፤ አይታወቀንም። ፀጉር ከግንባር ሲሳሳ፣ ያልተመለጠውን ፀጉር በማበጠሪያ ወደፊት በመላግ ፀጉር አለን ማለት የተለመደ ሂደት ነው፡፡ ነፋስ ሲመጣ ግን የተሸፋፈና ፀጉር መገላለጡ ግድ ይሆናል፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነው፡፡ ሂደቱን መግታት እጅግ አዳጋች ነው! በየጊዜው ራሳችንን ሳንመረምር ቆይተን፣ ቁስሉ ካንሠር ደረጃ ከደረሰ በኋላ ልናድነው ብንሞክር የጭንቅ የምጥ ጉዞ ነው የሚሆንብን፡፡ በእርግጥ በፖለቲካ ህይወት አይቀሬ (inevitable) የሚባሉ ደረጃዎች አሉ። ያረጀው ይቀረፋል፡፡ አዲሱ ይተካል፡፡ ቀራፊውና ተተኪውም እንደዚያው በተራው የፋንታውን ይገኛል፡፡
“አንተም እሳት ነበርክ፣ እሳት አዘዘብህ
እንደገና ዳቦ፣ እሳት ነደደብህ”
የሚለው የአገራችን ባለቅኔ ይሄንኑ አጥልሎ ሲገልፅ ነው፡፡ ያረጁት ያፈጁት ፖለቲከኞች ይወገዳሉ፡፡ እነ ሌኒን፤ “The party purges itself” ይሉ ነበረ፡፡ ፓርቲው ራሱን ይቀጣል፤ የራሱን ሰዎች ያስወግዳል እንደማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲ ባለበትና ራሱን በገመገመ ቁጥር የሚከሰት ነው፡፡ አጥርቶ ላየው ነባሩ እየሳሳ፣ አዲሱ እየወፈረ መምጣቱ ይገነዘባል፡፡
“ነገሩ አልሆን ብሎ፤ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር”
ያለው በረከተ-መርገም ዛሬም ያስኬዳል፡፡ ወደድንም ጠላንም ከሮበርት ፍሮስት ጋር “The road less travelled”ን መዘመር አለብን፡፡ ያልተሄደው መንገድ፣ እግር ብዙ ያልረገጠው መንገድ የቱ ነው? መባባል አለብን፡፡ የሲቪል ተቋማትን ማስፋፋት አለብን፡፡ ያልተሳተፉ አካላትንና ግለሰቦችን ከፖለቲካው ማዕድ ይቋደሱ ዘንድ በራችንን መክፈት አለብን፡፡ የ “እኔ ብቻ” ፖለቲካ ወንዝ እንደማያሻግር መገንዘብ አለብን፡፡ ብልጣብልጥነት ሁልጊዜ እንደማያበላ ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡
“የማትረባ ፍየል፣ ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ፣ እሷም ትሞታለች” የሚባለውን የጥንት የአብዮታዊ እርምጃ መግቢያ ከመዝገበ-ቃላታችን ለማውጣት መታገል አለብን፡፡ ራሳችንን ጨርሰን ከመብላት ተደጋጋሚ የታሪክ ህፀፅ ለመዳን ሆደ-ሰፊ መሆን፣ መካርን እህ ብለን ማዳመጥ፣ ተሳስቼ ይሆን?  ብለን ራስን መጠየቅ፤ ብልህነት ነው፡፡ ደጋግመን ራሳችንን እንይ! ራሳችንን ሳንፈራ እንውቀስ! ህዝብ እስኪነሳብን ድረስ አንደባበቅ! ጨዋታው ካበቃ በኋላ አየር ጠባይ አልተሰማማንም፣ ዳኛው በድሎን ነው፣ በቂ ልምምድ አላደረግንም ወዘተ ብንል የሚተርፈን “ቢሆን ኖሮ” ማለት ብቻ ነው! ከዚህ ይሰውረን። ዛሬ ላይ ቆመን ትላንት ያለፈውን ታሪክ እንጂ ነገ የሚከሰተውን ታሪክ እናውቅም፡፡ ትላንት ያየናቸውን ሰዎች እንጂ ነገ የሚመጡትን ወዳጆችም ሆኑ ጠላቶች አናውቅም፡፡ በጥሞናና በአደብ ነገን ለማውጠንጠን ዕድል አለን፡፡ ያ ደግሞ የብዙዎች  አዕምሮ ጥርቅም እንጂ የጥቂቶች ግምት፤ የጥቂቶች ጥንቆላ፣ የጥቂቶች አስገዳጅ እርምጃ ውጤት አይደለም፡፡ “ያየኸው ያለፈውን ወንዝ እንጂ የሚመጣውን አይደለም” የሚለውን ተረት ልብ ማለት ያለብን ለዚህ ነው!    

ከዚህ በፊትም ዜጎች የእናቶች ቀንን እንዳያከብሩ ተከልክለው ነበር

   የሰሜን ኮርያ መንግስት የአገሪቱ ዜጎች በቤታቸውም ሆነ በመዝናኛ ስፍራዎች በጋራ ተሰባስበው እየዘፈኑና እየጠጡ እንዳይዝናኑ የሚከለክል አዲስ መመሪያ ማውጣቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ዜጎቹን በጋራ ከመዝናናት የሚያግደውን ይህንን መመሪያ ማውጣቱን በተመለከተ መረጃ እንዳገኘ የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ የስለላ ተቋም፣ ባለፈው ሰኞ በሰጠው መግለጫ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የሰሜን ኮርያ መንግስት በዜጎች ላይ ተመሳሳይ ክልከላዎችን ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ያለው ዘገባው፣ ባለፈው ሐምሌ ወር ላይም እጅግ ተወዳጁንና በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ለረጅም አመታት በስፋት ሲከበር የኖረውን የ”ፒንግያንግ የቢራ ፌስቲቫል” እንዳይከናወን ማገዱን አስታውሷል፡፡
ሰሜን ኮርያውያን በአለማቀፍ ደረጃ በሚከበረው “የእናቶች ቀን” በዓል ወቅት ለእናቶቻቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር እንዳይገልጹ በመንግስታቸው ክልከላ እንደተደረገባቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ይህንን እርምጃ የወሰደው “ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ቢራ መጠጣት አግባብ አይደለም” በሚል እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡

ድምጻዊቷ በዓመቱ በድምሩ 105 ሚ. ዶላር አግኝታለች

    አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ በፈረንጆች አመት 2017 ከፍተኛውን ክፍያ ያገኘች ቁጥር አንድ የአለማችን ሴት ድምጻዊት መሆኗን በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መረጃ ይፋ ያደረገው ፎርብስ መጽሄት፤ድምጻዊቷ በአመቱ ከአልበም ሽያጭና ከሙዚቃ ኮንሰርት በድምሩ 105 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች ብሏል፡፡
በአመቱ 69 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘቺው እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል፣ሁለተኛዋ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ሴት ድምጻዊት ስትሆን፣ ባለፈው አመት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረቺው ቴለር ስዊፍት ዘንድሮ በ44 ሚሊዮን ዶላር ወደ ሶስተኛነት ዝቅ ማለቷን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
ሴሊን ዲዮን በ42 ሚሊዮን ዶላር፣ ጄኔፈር ሎፔዝ በ38 ሚሊዮን ዶላር፣ ዶሊ ፓርተን በ37 ሚሊዮን ዶላር፣ ሪሃና በ36 ሚሊዮን ዶላር፣ ብሪትኒ ስፒርስ በ34 ሚሊዮን ዶላር፣ ኬቲ ፔሪ በ33 ሚሊዮን ዶላር፣ ባርባራ ስትሪሳንድ በ30 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ፎርብስ ዝርዝሩን ያወጣው በአጠቃላይ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሰማሩ ሴቶችን የአመቱ አጠቃላይ ገቢ በማጥናት ቢሆንም፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ተከፋይ ሆነው የተገኙት የዘርፉ ከዋክብት ድምጻውያን ናቸው ተብሏል፡፡

     ታዋቂው የደቡብ ኮርያ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ፣ ጋላክሲ ኤክስ የተባለውን እንደ ፕላስቲክ የሚታጠፍና የሚዘረጋ ልዩ ስማርት ፎን አምርቶ በመጪው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በገበያ ላይ እንደሚያውል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የመሸጫ ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን በይፋ ባይታወቅም ከነባሮቹ የጋላክሲ ምርቶች ውድ እንደሚሆን የተገመተው ጋላክሲ ኤክስ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ የሚውለው በደቡብ ኮርያ ሲሆን  በቀጣይም በብዛት ተመርቶ ለአለማቀፍ ገበያ እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡
ይህንን ልዩ የሆነ ተጣጣፊ ሞባይል እንደሚያመርት ለአመታት ሲነገርለት ቢቆይም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በይፋ መረጃ ሳይሰጥ የቆየው ኩባንያው፤ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አዲሱን ምርቱን በፈረንጆች አዲስ አመት መጀመሪያ ለገበያ እንደሚያቀርብ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ሳምሰንግ ከዚህ በተጨማሪም አዲሱን ጋላክሲ 9 የሞባይል ምርቱን በመጪው የካቲት ወር ላይ ለገበያ እንደሚያበቃ መግለጹን አመልክቷል፡፡

  ልጆች በወላጆቻቸው ሃጢያት ለከፋ በሽታ ሊጋለጡ ይችላሉ ብለዋል

   የህንድ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሂማንታ ቢስዋ ሳማራ፤ የካንሰር በሽታ የሚያጠቃው ሃጢያት የሰራ ሰውን ነው ሲሉ በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ፣ በሚኒስትሩ ንግግር የተቆጡ በርካታ ህንዳውያን የካንሰር ታማሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ባለፈው ረቡዕ ጉዋሂቲ በተባለቺው የህንድ ከተማ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ባደረጉት ንግግር፤ ሰዎች ራሳቸው በሰሩት የሃጢያት ድርጊት ምክንያት በካንሰር ከመያዛቸው ባለፈ፣ በወላጆቻቸው ሃጢያት ሳቢያም ለሌሎች ተመሳሳይ አደገኛ በሽታዎች ሊጋለጡ እንደሚችሉም በእርግጠኝነት ተሞልተው መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
“ኦል ኢንዲያ ዩናይትድ ዲሞክራቲክ ፍሮንት” የተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ሚኒስትሩ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሰውዬው ይህን ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ንግግር ያደረጉት የካንሰርን ስርጭት ለመግታት አለመቻላቸውን ባልሆነ መንፈሳዊ ሰበብ ለመሸፋፈን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
ጉዳዩ ህንዳውያንን ጨምሮ በአለማቀፍ ደረጃ በማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ በካንሰር የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝና በመጪዎቹ 3 አመታት ውስጥ በ25 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ገልጧል፡፡

  ኤመርሰን ማንጋግዋ ቃለ-መሃላ ፈጽመው ስልጣን ተረክበዋል

   ላለፉት 37 አመታት ዚምባቡዌን የመሩትና የአገሪቱ የጦር ሃይል ስልጣኑን በጊዜያዊነት መረከቡን ተከትሎ፣ ለቀናት ሲያንገራግሩ ቆይተው ባለፈው ማክሰኞ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ በጦር ሃይሉ ባለስልጣናት ያለመከሰስ ዋስትና እንደተሰጣቸው ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል።
ሙጋቤ “እስከ ዕለተ ሞቴ በአገሬ ምድር ላይ መኖር እፈልጋለሁ፤ ቀሪ ዘመኔን በስደት መገፋት አልሻም፤ ስለሆነም ለእኔም ሆነ ለባለቤቴ ደህንነት ዋስትና ከተሰጠኝ ስልጣኔን እለቃለሁ” በሚል ለጦሩ መደራደሪያ ሃሳብ መላካቸውን ተከትሎ፣ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ግሬስ በአዲሱ መንግስት ደህንነታቸው እንደሚጠበቅላቸው ቃል እንደተገባላቸው አንድ የአገሪቱ የጦር ሃይል ባለስልጣን መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሙጋቤ ጡረታቸው እንደሚከበርላቸውና የመኖሪያ ቤት ክፍያና የጤና ዋስትናን የመሳሰሉ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እያገኙ፣ ቀሪ ህይወታቸውን ከቤተሰባቸው ጋር በሰላም እንዲገፉ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል መባሉን ዘገባው የጠቆመ ሲሆን፣ ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፤ ሙጋቤ ከሶስት አስርት አመታት በላይ በዘለቀው የስልጣን ዘመናቸው፣ የግል ሃብት ለማካበት ያልዳዱና ከአገር ውጭ ምንም አይነት ሃብትም ሆነ ንብረት እንደሌላቸው ዘግቧል። ሚስታቸው ግሬስ በአንጻሩ፤ የከብት እርባታና የወተት ምርቶች ማቀነባበሪያን ጨምሮ በርካታ ንግዶችን እንደሚያከናውኑም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዋዞዌ በተባለው የአገሪቱ የገጠር መንደር ውስጥ የሚገኘው የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ንብረት የሆነ እርሻና የከብት ማድለቢያ ድርጅት፣ ባለፈው ረቡዕ በመቶዎች በሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መዘረፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ .
በቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣናቸው መባረራቸውን ተከትሎ፣ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰደዱትና ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የ75 አመቱ ኤመርሰን ማንጋግዋ፤ በትናንትናው ዕለት ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣን ይዘዋል፡፡
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ በበኩሉ፤ ዚምባቡዌ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደመዘፈቋ፣ አዲሱ የአገሪቱ መንግስት ከወጪ፣ ከውጭ ብድርና ከሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አፋጣኝ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባው ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ በበኩላቸው ተቀዳሚ ስራቸው ኢኮኖሚውን ማቃናት እንደሆነ ተናግረዋል። የሙጋቤን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ በርካታ የውጭ አገራት ኢንቬስተሮች ወደ አገሪቱ ለመግባት ፍላጎት እያሳዩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ይህም የዶላር እጥረትን ለመቅረፍና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የያዙትን ዕቅድ በማሳካት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ከጥንታውያን ፋርሶች ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖር እጅግ ሞገደኛና አስቸጋሪ ወጣት ነበር፡፡ ይህ ወጣት ልጃገረዶችን እየደበደበ ያስቸግራል፡፡ ንብረታቸውን ይቀማል፡፡ ወደ ቤታቸው በጊዜ እንዳይገቡ አግቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡ አባቱ አንቱ የተባለና የሚፈራ በመሆኑ፣ ደፍሮ የሚናገረውና ተው የሚለው ቤተሰብ የለም፡፡
ይኼ ወጣት፣ ከልጃገረዶችም አልፎ ወጣት ወንዶችን ያስፈራራል፡፡ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ያደርጋል፡፡ እያስፈራራ ፍራንክ ይቀበላል፡፡ ደብተር ይነጥቃል፡፡ ለሞገደኛ ተግባሩ ተባባሪ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል፡፡
ይኼ ወጣት በወጣት ሴቶችና ወንዶች ላይ የሚፈፅመው ጥፋት አልበቃ ብሎት፤ አረጋውያንና አሮጊት ሴቶች እያስፈራራ፣ ቁልቁል ይሄዱ የነበሩትን ሽቅብ፤ ሽቅብ ይሄዱ የነበሩትን ቁልቁል፣ ያስኬዳቸው ነበር። ይህ ሞገደኛ የሰፈር ወጣት፣ ለወላጆቹ ጥፋቱ ተነገረ፡፡ ተው ተባለ፡፡ አሻፈረኝ አለ። ለትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ  እንዳይነገር ትምህርቱን ጥሎ ከወጣ ቆይቷል፡፡ እንዲህ በሞገደኝነት እየተቀናጣ ብዙ ጊዜ ሲያስቸግር ከረመ፡፡
አንድ ቀን የሰፈር ልጆች ተሰበሰቡና፤
“እስከመቼ ይሄ ሞገደኛ ሲጫወትብን ይኖራል? አንድ ነገር ማድረግ ይገባናል” ማለት ጀመሩ፡፡
የሞገደኛውን ወጣት የዱሮ ዝና ያስታወሱ አፈገፈጉ፡፡
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ያሉትም አያመልጥም፤ በጋራ እናሳየዋለን፤ አሉ፡፡
ሁለተኞቹ ወገኖች፤ ሰፈሩን ዙሪያውን ከበን እንያዘው ተባባሉ፡፡ የሞገደኛውን ቤት ከበቡ፡፡ እንደተከበበ ያወቀው ወጣት እቤቱ አጠገብ ካለ ትልቅ ባህር ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ጫፉ ላይ ተቀመጠ፡፡
ተከትሎት ዛፉ ላይ የሚወጣ ጀግና ጠፋ፡፡ ስለዚህ መላ መምታት ተያዘ፡-
አንዳንዶች - እዛው እንዳለ በድንጋይ እንውገረው - አሉ፡፡
አንዳንዶች - የለም ዝም ብለን ብንጠብቀው ሲርበው ይወርዳል-አሉ፡፡
ሌሎች - ቀላሉ መንገድ ለፖሊስ ነግረን እንዲያስወርደው ማድረግ ነው አሉ፡፡
ተቃራኒዎቹ፤ ፖሊስ እጅ ከፍንጅ ሲያጠፋ አልያዝኩትም፤ ዛፍ ላይ መውጣት ወንጀል አይደለም፤ ማስረጃ ሰብስቡ ነው የሚለን አሉ፡፡
ደግሞ ሌሎቹ - ዛፉን ብንቆርጥበት ይወድቃልኮ! አሉ፡፡
የሰፈሩ ወጣቶች ይሄን ይሄንን ሲመክሩ፤ ሞገደኛው ወጣት ድንገት መውረድ ጀመረ፡፡ አካባቢው ሁሉ ፀጥ አለ፡፡ ወጣቶቹ ሲወርድ ምን እንዲያደርጉ ግራ ተጋቡ፡፡ ግማሾቹ ገለል ማለት ጀመሩ፡፡ ግማሾቹ ዱላ አዘጋጁ፡፡ ከፊሎቹ ድንጋይ ያዙ!
ዛፉ ወገብ ላይ ሲደርስ፤
“ለፖሊስ እጄን ልሰጥ ነው፡፡ እንደማትነኩኝ ቃል ግቡልኝ” አላቸው፡፡
“ውረድ ማንም አይነካህም” አሉት፡፡ ፖሊስ ተጠርቶ መጣ፡፡ ወጣቱ ወርዶ እጁን ሰጠ፡፡
“ለዚህ ለዚህ ለምን በፊት እንደዚህ አላደረግህም?” አሉት፡፡
“እንዳስቸገርኳችሁ ጀምሬ እንዳስቸገርኳችሁ ለመጨረስ ስለፈለግሁ ነው!” አላቸው፡፡
*      *     *
መሪዎች አሻፈረኝ ሲሉ ህዝቦች ልክ ያገቧቸው ዘንድ የዲያሌክቲክ ህግ ግድ ይላል፡፡ አምባ - ገነን መሪነት ከአፍ እስከ ገደፏ የሆነችው አፍሪካ፤ በጉልበት ወደ ሥልጣን የሚመጡ፣ በጉልበት ሥልጣን ላይ የሚቆዩና ያለ ጉልበት ከስልጣን አንወርድም የሚሉ መሪዎች ተለይተዋት አያውቁም፡፡ በእርግጥ ከስልሳዎቹ እስከ ዛሬ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆኑ የላቲን አሜሪካም መሪዎች አምባገነናዊ ባህሪያቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም እያወሩ ህዝብን ረግጠው ይገዛሉ፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም እያወሩ የህዝብን ሀብት ይመዘብራሉ፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም፣ ስለ መልካም አገዛዝ፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ብሄራዊ ብልፅግና፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮ መኖር… ወዘተ ያወራሉ፡፡ ድርጊታቸው ግን ተፃራሪ ነው! ከአፍሪካ ካውንዳ፣ ኢዲ አሚን፣ ሞቡቱ፣ ኦማዱ፣ ቦካሳ፣ አራፕሞይ፣ ሳሙኤል ዶ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ አሚን፣ ኬንያታ፣ ንጉማ፣ ቦንጎ፣ ሲያድ ባሬ፣ አልባሺር፣ ሴኩ ቲሬ፣ ሀሰን ጉሌድ፣ ካሙዚ ገንዳ፣ ሙጋቤ፣ የሚጠሩት ስሞች ሁሉ ቦታ ቢለዋወጡ ስለ አንድ ሰው የምናወራ ያህል አንድ ናቸው፡፡ የካምቦዲያው ፓል ፖት፣ የቺሊው ፒኖሼ፣ የፓራጉዋዩ ስትሮስነር፣ የፖላንዱ ጃሬ ሴልስኪ፣ የአርጀንቲና ዱዋርቴ፣ የስፔኑ ፍራንኮ ወዘተ… ሁሉም ያው ናቸው! አምባገነን አምባገነን ነው! ምንም ቦቃ አይወጣለትም - በጉልበት ይወጣል፣ በጉልበት ይኖራል፤ በመጨረሻ በጉልበት ይወርዳል!
ሐማ ቱማ የተባለው ኢትዮጵያዊ ፀሀፊ ስለ አካፋና ኢትዮጵያውያን (of spades and Ethiopians) በተባለው የግጥም መድበሉ What is in a name (ከስሙ ምን አለህ? እንደማለት ነው) እንዲህ ይለናል፡-
“… ሌሮይ ጆንስ አልከው ኢማሙ ባራካ
ጆሴፍ ዴ ሲሬ ሴሴኮ ዋዛባንጋ፤
ሊዎፖልድ ሆነ አማዱ
ኬራኩ ሆነ መንግሥቱ፤
አሚን ቦካሣ ቦንጎ
ሐቢብ ሞይ አሊያም ሳሚዶ፤
ስሙ ይቀያየር እንጂ
ሎሌማ ያው ሎሌ’ኮ ነው
ገዳይ ምንጊዜም ገዳይ ነው!
ስማቸውን ብትለዋውጥ
ወይ ቢቀያየር መልካቸው
ሎሌ ሁሌም ሎሌ ነው
ነብሰ - ገዳይ ያው ገዳይ ነው!!
ሁሉን የሚያስረው ሰንሰለት፣
ጫፉ ሌላ ቦታ ነው
አንተ ከሰሙ ምናለህ
ጠማማውን ጭንቅላት እየው እንጂ አዟዙረህ!
እየው ቦታውን ለዋውጠህ!”
ይለናል፡፡ የአምባገነን ስሙና መልኩ እንጂ ሥራውና ሤራው አንድ ነው፡፡
“አምባገነኖች መውረድ ከማይችሉበት የነብር ጀርባ ላይ ሆነው ወደፊትና ወደኋላ ይጋልባሉ፡፡ ነብሮቹ ግን ከቀን ቀን እየራባቸው ይሄዳሉ” ይላሉ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፀሐፊ፤ ዊንስተን ቸርችል። ሁሉም አምባገነኖች እናታቸው አንድ ናት! አንዳቸውም ከአንዳቸው አወዳደቅ አይማሩም! የታላላቅ ሰዎችን ማንነት፣ ማክበርና ማስከበር ከብዙ ደካማ አገዛዝና ውድቀት ያድናል፡፡ ትልቅን ለማክበር ዝግጁ መሆን፣ ወደ ትልቅነት መንገድ መጀመር ነው፡፡ ተገፍትረው እስኪወድቁ የሚጠብቁ ያልታደሉ መሪዎች ናቸው፡፡ ታላላቅ ሰዎቻቸውን የሚያዋርዱና የሚንቁ መጨረሻቸው አያምርም! ትልቅን ለመሸፈንና እንዳይታይ ለመጋረድ መሞከር የጅል ጥረት ነው! “ጀምበር በእበት አይመረግም” የሚለው የጉራጊኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ዕውነት ነው!