Administrator

Administrator

      በማረሚያ ቤት አያያዝ ተበድለናል ያሉት የሽብር ተካሳሾቹ የአሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ አመራሮችና የሠማያዊ ፓርቲ አባላት ላለፉት 9 ቀናት የረሃብ አድማ ያደረጉ ሲሆን ከማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ትናንት መመገብ መጀመራቸውን የረሃብ አድማ ካደረጉት አንዱ የሆኑት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለፍ/ቤት አስረድተዋል፡፡
መንግስት በኦሮሚያ ከተቀሠቀሰው ግጭትና ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል ክስ ያቀረበባቸውና በቂሊንቶ ማረሚያ ቤት የሚገኙት የአፌኮ ተ/ም/ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የፓርቲ አመራሮች፡- አቶ ገርሣ አያኖ፣ አቶ ደጀኔ ጠፋ እና አቶ አዲሱ ቡላላ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ በሌላ ጉዳይ በሽብር የታሰሩት አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ አቶ ፍቅረ ማርያም አስማማውና ማስረሻ ሰጠኝ በረሃብ አድማ ላይ መሠንበታቸው ታውቋል፡፡
ተከሳሶቹ “በማረሚያ ቤቱ ከሌሎች እስረኞች ተለይተን በጨለማ ክፍል ውስጥ መታሠር የለብንም፤ በቤተሰብም እንዳንጠየቅ ተደርገናል” በሚል የረሀቡን አድማ ላለፉት ማድረጋቸውን የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የረሃብ አድማውን ካደረጉት መካከል ትናንት ፍ/ቤት ቀጠሮ መሰረት የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ ቆሞ ችሎት መከታተል አለመቻሉን ለፍ/ቤቱ በማስረዳቱ፣ ተቀምጦ ጉዳዩን እንዲከታተል የተደረገ ሲሆን ማክሰኞ እለትም ጉሉኮስ ተሰጥቶት እንደነበር ጠበቃው አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ እነ አቶ በቀለ ገርባም፤ በረሀቡ መንቀሳቀስ እስኪያቅታቸው ሰውነታቸው መጎዳቱንና ጉሉኮስ እንዲያገኙ መደረጉን ቤተሰቦቻቸው አስረድተዋል፡፡
የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ እስረኞቹን በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ማነጋገራቸውንና ያላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ጉዳዩን “እናየዋለን” ማለታቸውን ተከትሎ፣ ታሳሪዎቹ መመገብ መጀመራቸውን አቶ ዮናታን ለፍ/ቤት ተናግረዋል፡፡

   የበጎ አድራጎት ስራ በግለሰቦች መልካም የማድረግ ጽኑ ፍላጎትና ሃሳብ ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ተግባር ሲሆን በሃገራችን ረጅም ታሪክ ያለዉና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የማንነት መለያ ዓርማ ሆኖ የሚያገለግል ሃብት ነዉ:: ይህ የበጎ ተግባር ስራ እንደግለሰቡ ወይም ተቋሙ አቅምና አጠቃላይ ይዘት የሚሰጠዉ የድጋፍ አይነት፤ ብዛትና መጠን ይለያያል፡፡ በመሆኑም ከትንሽ እስከ ትልቅ ከግለሰብ እስከ ተቋም በተለያዬ ሁኔታ ዉስጥ ለሚገኙ ድጋፍ ፈላጊዎች የተለያዬ ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ምናልባትም በሃገራችን በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ ድጋፎች በአይነትም በብዛትም በርካታ እንደሆኑ ቢገመትም ተቌማዊ ቅርጽ ያልያዙ ከመሆናቸዉ አንጻር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የድጋፉን አይነትና መጠን ለማወቅ ስለማይቻል ይህን ያህል ብሎ በቁጥር ለማስቀመጥ አዳጋች ይሆናል፡፡
ከዚሁ ስራ ጋር በተያያዘ በተለይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አሁን ባለንበት ዘመን ሰፊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚታመን ሆኖ አመሰራረታቸዉን ስንመለከት ቀደም ባለዉ ጊዜ ረሃብና ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ነፍስ የማዳን ተልዕኮ ይዘዉ በመንቀሳቀስ በርካታ ህይወት ማትረፍ የቻሉ ሲሆን ከድርቁ በመለስ መልሶ የማቋቋም ስራዎችንና ብሎም ዘላቂ የልማት ግቦችን በማንገብ የልማት ስራዎችን በስፋት ሲያከናዉኑ ቆይተዋል፤ አሁንም እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በሃገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በ1965 ዓ.ም በወሎና ትግራይ ደርሶ በነበረዉ ከፍተኛ ድርቅ ቁጥራቸዉ በርከት ያለ መንግሰታዊ ያልሆኑ ዕምነት ተኮር ድርጅቶች የማይናቅ ተሳትፎ ከማድረጋቸዉም በላይ ለአሁኑ በሽህ የሚቆጠር የበጎ አድራጎት ድርጅት መፈጠር ምክንያት ነበሩ ለማለት ያስችላል፡፡ ከአስር አመት በኌላ እንደገና በ 1977 ዓ.ም ድርቁ በተመሳሳይ በወሎና ትግራይ አካባቢ በስፋት በመከሰቱ በወቅቱ እነኚህ ድርጅቶች ሰፊ ድጋፍ በማድረጋቸዉ ምንም እንኳ ብዙ ጉዳት ቢደርስም ችግሩን ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡
ከላይ በተገለጸዉ ሁኔታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሃገራችን ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ሲሆን በተለይም ከደርግ ዘመን በኌላ በአዲሱ ህገ መንግስት የመደራጀት መብትን በመጠቀም በርካታ የሃገር ዉስጥና የዉጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መፈጠር ችለዋል:: ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረዉ እነኚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተለይም ሃገራዊ የልማት ግቦችንና ዕቅዶችን በማገዝ የመንግስትና የህዝብ የልማት አጋር ሆነዉ የወጡበት ሂደት በግልጽ ይታያል:: በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን ከ 3000 የሚልቁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚገኙ ሲሆን በአሰራር ስርዐት በርካታ ችግሮች ቢገጥሟቸዉም ችግሮቻቸውን ተቋቁመዉ በተለያዬ የልማት፤ የእርዳታና መልሶ ማቋቌም ስራ ላይ ተሰማርተዉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በተለይም በአሁኑ ሰአት አጠቃላይ የልማት ዕቅዳቸዉን አገሪቱ ካጸደቀችዉ ሁለተኛዉ የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በማጣጣም፤ የዕቅዱን ተፈጻሚነት በየጊዜዉ ከሚመለከታቸዉ የመንግስት መ/ቤቶች ጋር በቅርበት በመገናኘት በመገምገምና የማስተካከያ እርምጃ በመዉሰድ የልማት አጋርነታቸዉን የበለጠ ያሳዩበት ወቅት ቢሆንም ከሚያከናዉኑት ስራ አንጻር ሲታይ ለህዝብ ግልጽ መሆን ያለባቸዉ በርካታ ጉዳዮች ማለትም ከዉጭ ለጋሽ ድርጅቶች የሚያመጡት ገንዘብ፡ በሴክተሩ ዉስጥ ያለዉ የሰዉ ሃይል፡ እንዲሁም በተጨባጭ ለህዝብ የሚያደርጉትና ያደረጉት የልማት ስራ ጥቅል ይዘት ለማህበረሰቡ በሚፈለገዉ መጠን ታዉቌል ለማለት ያስቸግራል።
አንዳንዴም ከዚህ ባለፈ መልኩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለህብረተሰቡ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ይልቅ የግለሰብ መጠቀሚያና መክበሪያ ተደርገዉ የመታየታቸዉ ጉዳይ ህዝቡ የተዛባ አመለካከት እንዲይዝ ከማድረጉም ባሻገር የሴክተሩን ገጽታ የሚያበላሽና ጥላሸት የሚቀባ ሆኖ ይታያል፡፡
በዚህ  ጽሁፍ አዘጋጅ - የኢትዮጵያ በጎ አደራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክ አመለካከትም በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እጅግ ብዙ ዉጤታማ የልማት ስራዎችን የማከናወናቸዉን ያህል የተወሰኑት ደግሞ በጎ ባልሆነ ተግባር ዉስጥ ሲሳተፉ ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክም ሴክተሩ፤ በአጠቃላይ ተገዥ የሚሆንበትን የስነ ምግባር ደንብ በማዘጋጀትና በማጽደቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን ይህም ጥረት በሴክተሩ ዉስጥ ተጠያቂነትን በማስፈን ግልጽ አሰራር እንዲሰፍን እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በሌላ ወገን ሌሎች ስራቸዉን በትጋትና በቅንነት የሚያከናዉኑትን በማበረታታት፤ ችግሮቻቸዉ ላይ በመወያየትና መፍትሄ በማፈላለግ የተቀላጠፈ የስራ ማዕቀፍ እንዲፈጠርላቸዉ መድረኩ በትጋት ይሰራል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በርካታ ስራ ቢሰሩም ድጋፋቸዉ ለህዝብ በቅጡ ያልታወቀ ከመሆኑ አንጻር የተለያዩ የመገናኛ ብዘሁንን በመጠቀም ስራዎቻቸዉን ለህዝብ ማሳወቅ ተገቢ  በመሆኑ ይህንኑ ስራ መስራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም በሃገራችን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምን ምን ድጋፍ እንዳደረጉ በተወሰነ መልኩ ከዚህ በታች በተቀመጠዉ ሁኔታ ለመግለጽ ጥረት ተደርጔል፡፡ ከዚህ በላይ በጥቂቱ ለማየት እንደተሞከረዉ በኢትዮጵያ የተለያዬ ይዘት ያላቸዉ በፌደራል ደረጃ ቁጥራቸዉ ከ 3000 የሚልቅ በክልል ደግሞ ከ 1000 የሚበልጡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ይገኛሉ፡፡
በእነኚሁ መረጃዎች መሰረት በሃገራችን ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያተኩሩባቸዉ የልማት ስራዎች በቅደም ተከተል የሚከተለዉን ይመስላሉ፤ ጤና፤ የህጻናት ልማት፤ ትምህርት፤ ማህበራዊ ድጋፍ፡ አቅም ግንባታ፤ ገቢ ማስገኛ አካባቢ ጥበቃ እና እርሻ ስራ ይገኙበታል፡፡ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር በ 2012 በሃገሪቱ በአጠቃላይ 4904 ፕሮጀክቶች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ ዉስጥም 113 በአዲስ አበባ፤ 856 በኦሮሚያ፤ 621 በደቡብ፤ 610 በአማራ፡ 450 በትግራይ፡ 283 በአፋር፤ 267 በድሬዳዋ፤ 59 በቤንሻንጉል፡ 238 በሃረሪ፤ 237 በሶማሌ፤ እንዲሁም 170 ፕሮጀክቶች በጋምቤላ ክልል ተተግብረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉት የጤና ተቌማት ዉስጥ 7% ያህሉ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሙሉ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በተጨማሪም በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ሪፖርት መሰረት  እ.ኤ.አ በ2011፣ 1626 የጤና ፕሮጀክቶች እንደነበሩ የተጠቆመ ሲሆን ወደ 200 የሚጠጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በኤች አይቪ ኤድስ መቆጣጠርና መከላከል ስራ ላይ ተሰማርተዉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ ሪፖርት እ.ኤ.አ ከ 2004 እስከ 2007 ብር 575 ሚሊዬን ለዉሃ ስራ የዋለ ሲሆን ብር 3 ቢሊዬን ደግሞ በ 336 ፕሮጀክቶች ለእርሻና ተያያዥ ተግባራት ዉሏል፡፡ በተመሳሳይ በሃገሪቱ ካሉ 388 የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ዉስጥ 74 የሚሆኑት በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሙሉ ድጋፍና ቁጥጥር በስራ ላይ የሚገኙ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡                                          
በአመታዊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሪፖርት መሰረት እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2011 ባሉት ጊዚያት ዉስጥ ብር 544,201,454.98 ለዉሃና ተያያዥ ስራዎች ብቻ ተመድቦ ስራ ላይ ዉሏል፡፡
በኢትዮጵያ ዉስጥ ቁጥራቸዉ ከ54 የሚልቅ ህብረቶችና ጥምረቶች ያሉ ሲሆን ለናሙናነት በክርስቲያን ልማትና ተራድዖ ማህበር ህብረት (ሲሲአርዲኤ) ሪፖርት መሰረት እ.ኤ.አ በ2011 10.8 ቢሊዬን ብር በ 320 አባል ድርጅቶች መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ አብዛሃኛዉ ገንዘብም ለምግብ ዋስትና፡ ልህጻናት ድጋፍና ለጤና አገልግሎት ስራ በቅደም ተከተል የዋለ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ከአንድ አመት በኃላ በ2012 በተጠናቀረ ሪፖርት ጥቅል ብር 11,841,356,007.87 ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ዉሏል፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በተገኘ መረጃ መሰረት በ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 2007 ሙሉ አመትና 2008 – 10 ወር ጊዜ ዉስጥ (አንድ አመት ከአስር ወር ዉስጥ) ከ 2 ቢሊዬን ዶላር (40 ቢሊዬን ብር) በላይ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የዉጭ ምንዛሬ ገንዘብ ለማግኘት ተችሏል፡፡ 

• ባለፉት 12 ወራት ብቻ፣ 55 ሚ. ዶላር ገቢ አግኝቷል
• ለ117 ታላላቅ ሽልማቶች ታጭቶ፣ በ36 አሸንፏል
    በወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ መድረክ ጎልቶ በመውጣት ከፍተኛ ስኬትን የተቀዳጀውና የበርካታ ታላላቅ አለማቀፍ ሽልማቶች ባለቤት ለመሆን የበቃው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፤ ከአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ተርታ መሰለፉን ዘ ኢንኩዚተር ዘግቧል፡፡
አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያፈራው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ ፎርብስ መጽሄት ከሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የ2016 ከፍተኛ ተከፋይ 100 የዓለማችን ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካተቱት 15 ዝነኞች መካከል አንዱ መሆኑንና ከእነዚህ መካከልም ከፍተኛውን ገቢ ያገኘው እሱ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የ25 አመቱ ድምጻዊ አቤል ባለፉት 12 ወራት ብቻ 55 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጧል፡፡
“ዘ ዊክንድ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የግራሚ ተሸላሚው አቤል፤ ከዘንድሮ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ 100 ዝነኞች መካከል የ30ኛ ደረጃን መያዙን የጠቆመው ዘገባው፣ “ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘውና ከ2 ሚሊዮን ኮፒ በላይ የተቸበቸበው የሙዚቃ አልበሙ ለድምጻዊው ከፍተኛ ገቢ ማግኘትና በዝርዝሩ ውስጥ መካተት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጧል፡፡
ለ117 አለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማቶች በመታጨት፣ ሁለት የግራሚና ስምንት የቢልቦርድ ሽልማቶችን ጨምሮ 36 አለማቀፍና ክልላዊ የሙዚቃ ሽልማቶችን ያገኘውና በወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ መድረክ፣ አብሪ ኮከብ ሆኖ የወጣው አቤል፤ ባለፉት 12 ወራት ከአልበም ሽያጭ፣ ከሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ከኩባንያዎች ስምምነትና ከመሳሰሉት በድምሩ 55 ሚሊዮን ዶላር ሰብስቧል፡፡

Monday, 25 July 2016 09:35

የዘላለም ጥግ

(ስለ ታሪክ)

ታሪክ ሊወገዱ የሚችሉ ነገሮች ድምር ውጤት
ነው፡፡
ኮንራድ አድኖር
- ታሪክ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ተረት
አይደለምን?
ናፖሊዎን ቦናፓርቴ
- በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የምርምርን ፋይዳ
ተገንዝበናል፡፡
አማር ቦሴ
- ትልቁ ጠላቴ ጊዜ ነው፡፡
ኢቪታ ፔሮን
- የሰው ልጅ ታሪክ የሃሳቦች ታሪክ ነው፡፡
ሉጂ ፒራንዴሎ
- የታሪክ ፀሐፊ፡- ያልተሳካለት የረዥም ልብወለድ
ፀሐፊ ነው፡፡
ኤች.ኤል.ሜን
- እግዚአብሔር ያለፈውን ለመለወጥ አይችልም፤
የታሪክ ፀሃፍት ግን ይችላሉ፡፡
ሳሙኤል በትለር
- ታሪክ፤ ማብቂያ የለሽ የተሳሳተ የአኗኗር ዘይቤ
ድግግሞሽ ነው፡፡
ሎውረንስ ዱሬል
- አብዮቶች የታሪክ አሽከርካሪ ሞተሮች ናቸው፡፡
ካርል ማርክስ
- የዘመናዊ መንግስታትን ማህበራዊና ፖለቲካዊ
ታሪክ ለማጥናት ከፈልግህ፣ ስለ ገሃነም አጥና፡፡
ቶማስ ሜርቶን
- የጥበብ ባለሙያ ስራ የዘመኑ ታሪክ እማኝ መሆን
ነው፡፡
ሮበርት ራውስሽንበርግ
- ታሪክ በአጠቃላይ መጥፎ መንግስት እንዴት ያለ
እንደሆነ ብቻ ነው የሚነግረን፡፡
ቶማስ ጄፈርሰን
- የነፃ ሰዎች ታሪክ የሚፃፈው በአጋጣሚ ሳይሆን
በምርጫ ነው፤ በራሳቸው ምርጫ!
ድዋይት ዲ. አይዘንአወር
- ቤተ-መፃህፍት የሃሳቦች ማዋለጃ ክፍል ነው -
ታሪክ ነፍስ የሚዘራበት ሥፍራ፡፡
ኖርማን ኮውሲንስ

በፖሊስ መኮንንነትና በመረጃ ባለሙያነት ሀገራቸውን ያገለገሉትሌተና ኮሎኔል ተፈራ ካሳ “ዘፍ
ያለው” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መፅሃፍ ለገበያ ቀርቧል። ኮለኔሉ በ20 ዓመት አገልግሎታቸው የአይን እማኝ የሆኑበትን የኢትዮ ሶማሌ ጉዳይ እንዲሁም በወቅቱ የነበረውን የአገራችን አጠቃላይ ፖለቲካ ትኩሳት በመረጃ አስደግፈው በትረካ መልክ ያቀረቡበት ይሄው መፅሀፍ
የስለላና የአፈና ትንቅንቅን የሚያስቃኝ እውነተኛ ታሪክ ሲሆን በሁለተኛው ‹‹ለንባብ ለህይወት›› የመፅሀፍት አውደርዕይ መክፈቻ ላይ በድምቀት ተመርቋል፡፡ሌተናል ኮሎኔሉ መፅሐፉን ፅፈው ለህትመት ያዘጋጁት በ1985 ዓ.ም ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የህትመት ብርሀን ሳያገኝ እንደቆየ የተገለፀ ሲሆን እርሳቸው ካለፉ በኋላ ልጃቸው ቴዎድሮስ ተፈራ መፅሐፉን የበለጠ በአርትኦት አበልፅጎ ለንባብ እንዳበቃው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ሌተናል ኮሎኔሉ 12 ዓመት በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ በአስተዳደር፣ በወንጀል ምርመራ በቴክኒክ ክፍል ስምንት ዓመት
ደግሞ በፀጥታ ጥበቃ መስሪያ ቤት የመረጃ ሀላፊዎች የቅርብ ረዳት ሆነው ባገለገሉበት ወቅት በአይናቸው ያዩዋቸው የተሳተፉባቸው እውነተኛ ክንውኖች በመፅሀፉ ተካተዋል መፅሀፉ በ341 ገፅ ተመጥኖ በ150 ብር እና በ25 የአሜሪካ ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

   ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት፣ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳትያ ናዴላ ማክሰኞ ዕለት ይፋ ማድረጋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው በተጠናቀቀው ሩብ አመት 20.6 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ያስታወቁት ናዴላ፤ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ያገኘው ገቢ ግን 22.2 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ማይክሮሶፍት ኩባንያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘዋል ተብሎ ከተገመተው በላይ ገቢ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን ገቢው ሊያድግ የቻለውም የምርታማነትና በቢዝነስ ፕሮሰስ ክፍሉ ያከናወነው ስራ ውጤታማነት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ማይክሮሶፍት ባለፉት ሶስት ወራት ከጌሞች ሽያጭ ያገኘው ገቢ በ9 በመቶ ቢቀንስም፣ ከማስታወቂያ ያገኘው ገቢ በአንጻሩ በ54 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሰኔ ወር በ26 ቢሊዮን ዶላር ሊንክዲን የተባለውን ማህበራዊ ድረገጽ መግዛቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህም በቀጣይ ገቢውን ያሳድግለታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡





እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ሰራተኞችን አባሯል

     ባለፈው ሳምንት የተቃጣበትን መፈንቅለ መንግስት ያከሸፈው የቱርክ መንግስት፤ በድጋሚ ተመሳሳይ ሙከራ ሊደረግ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ እንደገባ የተጠቆመ ሲሆን በርካታ ዜጎችን ከተለያዩ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ማባረሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት የተቃጣበትን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማክሸፉን ተከትሎ በበርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና መምህራን ላይ የወሰደው የእስራትና ከስራ ገበታቸው የማባረር እርምጃ፣  በአገሪቱ ተመሳሳይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ዘገባው ገልጧል፡፡
የኤርዶጋን መንግስት ባለፈው ማክሰኞ፣85 ያህል የአገሪቱን ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎችና መኮንኖች ማሰሩን የጠቆመው ዘገባው፤ አንዳንድ ምንጮች ግን የታሳሪዎቹ ቁጥር 125 እንደሚደርስ መናገራቸውን ጠቅሶ፣ይህም መንግስት በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የጦር ሰራዊቱ ሃላፊዎ እጃቸው አለበት ብሎ መጠርጠሩን ያመለክታል መባሉን አውስቷል። መንግስት የጦሩን እንቅስቃሴ ለመግታት በርካታ የጦር ሰፈሮችን በከባድ የጦር መሳሪያዎች ማስከበቡ የተነገረ ሲሆን የአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የኢስታምቡል ተወካይ አስሊ አይዲንታስባስም፤ መንግስት ይህንን እርምጃ መውሰዱ በድጋሚ የመፈንቅለ መንግስት ጥቃት ይፈጸምብኛል የሚል ስጋት ውስጥ መግባቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ቢቢሲ በበኩሉ፤ የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ እየወሰደው ያለው እርምጃ ጥብቅ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ፣ ከስራ ገበታቸው ያገዳቸው ወይም ያባረራቸው ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ መድረሱን ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የጠረጠራቸውን 15 ሺህ 200 የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞችና መምህራን ከስራ ገበታቸው ማባረሩንና የሌሎች ተጨማሪ 21 ሺህ መምህራንን የስራ ፈቃድ መቀማቱን የጠቆመው ዘገባው፤ 1ሺህ 577 የዩኒቨርሲቲ ዲኖችም ስራቸውን እንዲለቁ መጠየቁን ገልጧል፡፡
የፖሊስ ባልደረቦች የነበሩ 8 ሺህ ሰዎች፣ 1 ሺህ 500 የገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ 2 ሺህ 745 የፍርድ ቤት ዳኞች፣ 8 ሺህ 777 የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ ከ100 በላይ የብሄራዊ ደህንነት ተቋም ባልደረቦች፣ 257 የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሰራተኞችና ሌሎች በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ከስራቸው መባረራቸውንም ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ፓርቲ የተላላካቸው 300 ሺህ ያህል የኢሜይል መልእክቶች አፈትልከው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ዊኪሊክስ የተባለውንና መረጃዎቹን ዘርፎ ያሰራጨውን ተቋም ድረገጽ መዝጋቱን የዘገበው ደግሞ ዘ ጋርዲያን ነው፡፡
ስካይ ኒውስ በበኩሉ፤የቱርክ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ማንኛውም የአገሪቱ ምሁር ወይም ተመራማሪ ላልተወሰነ ጊዜ ከአገር መውጣት እንደማይችል ማስታወቁንና በውጭ አገራት የሚገኙትም በአፋጣኝ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማስተላለፉን ዘግቧል፡፡


በህንድ ጉጅራት አውራጃ የሚገኘው ሲንዱ የተባለ ሆስፒታል ሴት ልጆችን ለሚወልዱ ነፍሰጡር እናቶች ያለምንም ክፍያ የማዋለድና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
በአገሪቱ የሚገኙት አብዛኞቹ ነፍሰጡር እናቶች ወንድ ልጅ ለመውለድ እንደሚፈልጉና ሴት ሲወልዱ እንደሚበሳጩና እንደሚያዝኑ የጠቆመው ዘገባው፤ሆስፒታሉም ነፍሰጡሮች ሴት ልጆች ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ በማሰብ ነጻ የህክምና አገልግሎቱን እንደ ማበረታቻ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
በህንድ ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት የተዛባ በመሆኑ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሴት ልጅ ጽንሶች በውርጃ እንደሚቋረጡ ወይም እንደተወለዱ እንደሚገደሉ የጠቆመው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ይህን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር እየሰራ እንደሚገኝና  የሆስፒታሉ ነጻ የህክምና አገልግሎትም የዚህ ጥረት አካል እንደሆነ ገልጧል። በሆስፒታሉ ሴት ልጆችን የሚገላገሉ ነፍሰ-ጡር እናቶች ለህክምና አግልግሎቱ መክፈል ከሚገባቸው 20 ሺህ የህንድ ሩፒ  ነጻ እንደሚደረጉ ተነግሯል፡፡
እናቶች የአገሪቱ መንግስት ከ1994 አንስቶ ተግባራዊ ባደረገው ህግ ነፍሰጡር ሴቶች ከወሊድ በፊት የጽንሱን ጾታ በምርመራ እንዳያውቁ መከልከሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ይህም የተደረገው እናቶች ሴት ማርገዛቸውን ቀደም ብለው በማወቅ ጽንሱን ከማስወረድ ለመግታት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ይህም ሆኖ በህንድ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ብቻ 12 ሚሊዮን የሚደርሱ የሴት ጽንሶች በወላጆቻቸው የተዛባ የጾታ አመለካከት ሳቢያ በውርጃ እንዲቋረጡ መደረጋቸው በጥናት መረጋገጡን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በአመቱ 211 ጥቃቶች ተፈጽመው፣151 ሰዎች ሞተዋል

    ያለፈው የፈረንጆች አመት 2015፣አውሮፓ በታሪኳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሽብር ጥቃት ማስተናገዷንና በአመቱ ከፍተኛው የሽብር ጥቃት የተመዘገበው በእንግሊዝ መሆኑን ዩሮፖል የተባለው የአህጉሪቱ ተቋም ማስታወቁ ተዘገበ፡፡
ዓመቱ በአውሮፓ አህጉር በርካታ ቁጥር ያላቸው የሽብር ጥቃቶች የታቀዱበት፣የከሸፉበትና የተፈጸሙበት ነው ያለው ተቋሙ፤በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ 211 ያህል የሽብር ጥቃቶች መፈጸማቸውን ጠቁሞ፣ 103 ጥቃቶችን ያስተናገደቺው እንግሊዝ ከአህጉሩ ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን አስታውቋል፡፡ በአመቱ በፈረንሳይ 72፣ በስፔን ደግሞ 25 ያህል የሽብር ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያስታወቀው የተቋሙ የአውሮፓ ህብረት የሽብርተኝነት ሁኔታና አዝማሚያ አመላካች ሪፖርት፤ በአመቱ የጂሃዲስት የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ 687 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 94 በመቶው ጥፋተኛ መሆናቸው መረጋገጡን ገልጧል፡፡
በ2015 በአውሮፓ አገራት ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዙ ህገወጥ ድርጊቶች ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች ከ1ሺህ በላይ እንደሆኑና ከእነዚህ መካከልም 424 የሚሆኑት በፈረንሳይ እንደታሰሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤151 ሰዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች መሞታቸውንና ከ360 በላይ መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡




እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ሰራተኞችን አባሯል

     ባለፈው ሳምንት የተቃጣበትን መፈንቅለ መንግስት ያከሸፈው የቱርክ መንግስት፤ በድጋሚ ተመሳሳይ ሙከራ ሊደረግ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ እንደገባ የተጠቆመ ሲሆን በርካታ ዜጎችን ከተለያዩ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ማባረሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት የተቃጣበትን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማክሸፉን ተከትሎ በበርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና መምህራን ላይ የወሰደው የእስራትና ከስራ ገበታቸው የማባረር እርምጃ፣  በአገሪቱ ተመሳሳይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ዘገባው ገልጧል፡፡
የኤርዶጋን መንግስት ባለፈው ማክሰኞ፣85 ያህል የአገሪቱን ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎችና መኮንኖች ማሰሩን የጠቆመው ዘገባው፤ አንዳንድ ምንጮች ግን የታሳሪዎቹ ቁጥር 125 እንደሚደርስ መናገራቸውን ጠቅሶ፣ይህም መንግስት በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የጦር ሰራዊቱ ሃላፊዎ እጃቸው አለበት ብሎ መጠርጠሩን ያመለክታል መባሉን አውስቷል። መንግስት የጦሩን እንቅስቃሴ ለመግታት በርካታ የጦር ሰፈሮችን በከባድ የጦር መሳሪያዎች ማስከበቡ የተነገረ ሲሆን የአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የኢስታምቡል ተወካይ አስሊ አይዲንታስባስም፤ መንግስት ይህንን እርምጃ መውሰዱ በድጋሚ የመፈንቅለ መንግስት ጥቃት ይፈጸምብኛል የሚል ስጋት ውስጥ መግባቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ቢቢሲ በበኩሉ፤ የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ እየወሰደው ያለው እርምጃ ጥብቅ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ፣ ከስራ ገበታቸው ያገዳቸው ወይም ያባረራቸው ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ መድረሱን ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የጠረጠራቸውን 15 ሺህ 200 የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞችና መምህራን ከስራ ገበታቸው ማባረሩንና የሌሎች ተጨማሪ 21 ሺህ መምህራንን የስራ ፈቃድ መቀማቱን የጠቆመው ዘገባው፤ 1ሺህ 577 የዩኒቨርሲቲ ዲኖችም ስራቸውን እንዲለቁ መጠየቁን ገልጧል፡፡
የፖሊስ ባልደረቦች የነበሩ 8 ሺህ ሰዎች፣ 1 ሺህ 500 የገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ 2 ሺህ 745 የፍርድ ቤት ዳኞች፣ 8 ሺህ 777 የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ ከ100 በላይ የብሄራዊ ደህንነት ተቋም ባልደረቦች፣ 257 የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሰራተኞችና ሌሎች በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ከስራቸው መባረራቸውንም ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ፓርቲ የተላላካቸው 300 ሺህ ያህል የኢሜይል መልእክቶች አፈትልከው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ዊኪሊክስ የተባለውንና መረጃዎቹን ዘርፎ ያሰራጨውን ተቋም ድረገጽ መዝጋቱን የዘገበው ደግሞ ዘ ጋርዲያን ነው፡፡
ስካይ ኒውስ በበኩሉ፤የቱርክ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ማንኛውም የአገሪቱ ምሁር ወይም ተመራማሪ ላልተወሰነ ጊዜ ከአገር መውጣት እንደማይችል ማስታወቁንና በውጭ አገራት የሚገኙትም በአፋጣኝ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማስተላለፉን ዘግቧል፡፡