Administrator

Administrator

በኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ሙሉ ለሙሉ አልቆመም
“በተወሰኑ አካባቢዎች ግርግር አጋጥሟል፤ ግን እየተረጋጋ ነው”
ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር የግድቡን ህልውና የሚነካ አይደለም” (ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ)
          በአወዛጋቢው “ማስተር ፕላን”  መነሻነት ከሁለት ወራት በፊት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተከሰተው ተቃውሞና ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የክልሉ መስተዳድር ካሳ ለመክፈል እንዳሰበ ተገለፀ፡፡
ግጭቱ ሙሉ ለሙሉ አለመቆሙ በየጊዜው ሲዘገብ የቆየ ሲሆን፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ችግር ተፈጥሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች መረጋጋት እየተፈጠረ ነው፤ ትምህርት ቤቶችም መደበኛ ተግባራቸውን እየቀጠሉ ነው” ብለዋል፡፡ በቅርቡ በቦረና ጉጂ አካባቢና በተወሰኑ መንደሮች ግን ግርግሮች አጋጥመዋል ብለዋል - ሚኒስትሩ ትናንት በሰጡት መግለጫ፡፡
ግጭቱን አባብሰዋል ተብለው የታሰሩ ሰዎች በህግ ይዳኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሳያውቁ የተሳተፉ ሰዎች ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡ በጎንደር አካባቢና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ከቀረቡት የውሳኔ ሃሳቦች ላይም ሚኒስትሩ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ መንግስት ተቀብሎ ሊያጣራቸው የሚችሉ ሀሳቦች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሱው፤ በአጠቃላይ ግን ለአውሮፓ ፓርላማ ቀረበ ለተባለው የውሳኔ ሀሳብ መንግስት እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብፅና ከሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር የግድቡን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን የሚደረግ ድርድር አይደለም ብለዋል፡፡
ከግድቡ የጋራ ተጠቃሚ ለመሆንና በሁለቱ ሃገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ በመወያየት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ብቻ ያለመ ድርድር ነው ብለዋል -ሚኒስትር አቶ ጌታቸው፡፡

- “ኢትዮጵዊቷ የአሰሪዋን ልጅ ገድላ፣ ራሷን ለማጥፋት ሞክራለች”
- በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለጉዳዩ በቂ መረጃ የለንም ብለዋል

     በኩዌት አንዲት ኢትዮጵያዊ የቤት ሰራተኛ፤ የአሰሪዋን ልጅ ገድላ ራሷን ለማጥፋት ሞክራለች መባሉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ፓርላማ አባል የሆኑት ሳዶን ሃመድ አል ኦታቢ መንግስት በኩዌት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ አፋጣኝ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ ለአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአገር ውስጥ ሚኒስትር ጥያቄ ማቅረባቸው ተዘገበ፡፡
በአገሪቱ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደምም በአሰሪዎቻቸው ላይ አሰቃቂ ግድያ ፈጽመዋል ያሉት አል ኦታቢ፣ መንግስት በኢትዮጵውያን የቤት ሰራተኞች ላይ ወደ አገራቸው መመለስ፣ የስራ ቅጥር ውላቸውን የማቋረጥና የመኖሪያ ፈቃዳቸው እንዳይታደስ ማገድን የመሳሰሉ አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል ማለታቸውን “አረብ ታይምስ” ትናንት ዘግቧል፡፡አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ የአሰሪዋን ልጅ በስለት ወግታ ከገደለች በኋላ ራሷን ወግታ ለመግደል ስትሞክር በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏንና በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላት እንደሚገኝ የዘገበው “ኩዌት ታይምስ”፣ ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡ በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሞሃመድ ጉደታ በበኩላቸው፣ ኤምባሲው ጉዳዩን በተመለከተ በቂና ይፋዊ መረጃ እንዳልደረሰው ጠቁመው፣ ጉዳዩን የሚከታተል ተወካይ ወደ ኩዌት አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ ወደምትታከምበት ሆስፒታል መላካቸውን እንደገለጹ ዘገባው አስረድቷል፡፡

ደንብ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት ሊጣል ነው
       የደንብ ጥሰት በፈፀሙ አሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት የሚጥል አዲስ ህግ ሊተገበር ሲሆን በአሽከርካሪው ላይ ቅጣት ከመጣል በዘለለ በእያንዳንዱ ጥፋት ላይ በሚያዝ ነጥብ መሰረት፣ የመንጃ ፈቃድን ለስድስት ወራትና ለአንድ ዓመት ከማገድ አንስቶ ከእነአካቴው እስከ መሰረዝ የሚደርስ ነው፡፡
በክልሎች መንጃ ፈቃድ የማውጣት አሰራርም እንደሚቀርና ከአንድ ማዕከላዊ ሥፍራ ወጥ በሆነ መልኩ ብቃትን መሰረት አድርጐ መንጃ ፈቃድ የመስጠት አሰራር እንደሚጀመር ታውቋል፡፡የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፤ አዲሱ ህግ ተግባራዊ ስለሚደረግበት ሁኔታ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ለመወያየት ሰሞኑን አዘጋጅቶት በነበረው መድረክ ላይ የትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ የግንዛቤ ትምህርት ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ድል አርጋቸው ለማ እንደተናገሩት፤ ህጉ በ2003 ዓ.ም በአዋጅ ደረጃ ቢወጣም በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው ይኸው ህግ፤ ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ ተደጋጋሚ አጥፊዎችን ከመንገድ ለማስወጣት፣ በጥቂት ሥነ ምግባር የጐደላቸው አሽከርካሪዎች ምክንያት የሚጠፋውን ህይወት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመከላከል፣ የአጥፊ አሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመቀነስና ለህግና ደንብ የሚገዛ አሽከርካሪን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል አቶ ድልአርጋቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፎርጅድ መንጃ ፍቃዶች መሰራጨታቸው የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡ ወጥነት የጐደለው መሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድም ባለስልጣን መ/ቤቱ በአሻራ የተደገፈና በማዕከላዊነት ከአንድ ሥፍራ ላይ ብቻ የሚሰጥ አዲስ የመንጃ ፍቃድ አወጣጥ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ታውቋል፡፡ ይህ አሠራር የመንጃ ፍቃዶች በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች የሚሰጡበትን ሁኔታ የሚያስቀር ሲሆን ወጥ የሆነ በአሽከርካሪው ብቃት ላይ ብቻ ተመስርቶ መንጃ ፍቃድን ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው ዓመት ብቻ ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ የ3847 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ11ሺህ በላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋዎች እንደደረሱ የኤጀንሲው መረጃ ይጠቁማል፡፡

Saturday, 06 February 2016 11:34

ስምና ማንነት

 ከብዙ መነፋፈቅ በኋላ ካባቴ ታናሽ ወንድም፤ ካቶ አማረ በዳዳ ጋር ተገናኝተን አራት ኪሎ በሚገኘው ሮሚና ምግብ ቤት ምሳ በላን፡፡
አማረ ቢሏችሁ ቀላል ሰው እንዳይመስላችሁ፤ ከስድሳ ስድስት አብዮት ትንሽ ቀደም ብሎ በዩንቨርሲቲ ኮሌጅ በታሪክ ትምህርት ዘርፍ በዲግሪ ተመርቋል፡፡ በአብዮት ማግስት ዓመት በኢህአፓ አባልነት ተመልምሎ፣ በዚሁ ጦስ ተይዞ ዓለምበቃኝ አምስት ዓመት ታስሯል፡፡ እነ ማርታ ኩምሳ፣ ጌታቸው ኩምሳና ገነት ዘውዴ አብሮ ታሳሪዎቹ ነበሩ። ደራሲ ግርማይ አብርሃ በእሥር ቤት ማስታወሻው ላይ እንደጠቀሰው፤ አማረ በእሥር ቤት ቆይታው እሥረኞችን በነጻ የማስተማር አገልግሎት ከሚሰጡ ታራሚዎች አንዱ ነበር፡፡
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምርያ ያዲሳባ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ በምማርበት ወቅት የሻይ መጠጫ የሚቆርጥልኝ አማረ ነበር፡፡
አባቴና አማረ ያንድ አባት ያንድ እናት ቢሆኑም በመልክና በእጣ ፈንታ የተለያዩ ነበሩ፡፡ አባቴ የቀይ ዳማ ሲሆን አማረ ክስል ያለ ጥቁር ነው፡፡ ወንድማማቾቹ የሚጋሩት አንድ ምልክት ቢኖር፣ ከጥቁር ጸጉራቸው ማኽል እንደባትሪ ቦግ ብሎ የሚታየው ሽበታቸው ነበር፡፡ ከአማረ በተቃራኒ አባቴ ለፖለቲካ ያለው ስሜት በጣም የቀዘቀዘ ነው፡፡ አማረ የቢሮ ሰው ሲሆን፣ አባቴ የተፈጥሮ ሰው ነው። ከትምህርት ቤት ውጭ ያለውን ጊዜውን ያሳለፈው ከልጆቹ የማያንስ ፍቅርና ጊዜ ለሚሰጣቸው የጓሮ አትክልቱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በድህረ ምሳ ጨዋታ ላይ የዘመዳ-ዝማድ ጉዳይ ስናነሳ ስንጥል ቆይተን ልንሰነባት ስንል፣
“እስቲ ያባቴን የትውልድ ሐረግ ጻፍና ስጠኝ” አልኩት፡፡
“ምን አሳሰበህ” አለኝ በዋዛ፡፡
“እንዴት አያሳስበኝ፤ አባታዊነትን የሚያጋንን ማኅበረሰብ አባል ነኝ፡፡ አንድ ሰው ፍቅሩን ለመግለጽ “እንዲያው ምናባቴ ላርግህ” በሚልበት፤ ጠላቱ ክፉ እንደገጠመው ሲሰማ፣ “የታባቱ” ብሎ፣ በሚፈነጥዝበት ግራ ሲገባው፤ “ምናባቱ” እያለ በሚያጉተመትምበት ሀገር ውስጥ የምኖር ነኝ። አባት የነገሮች ሁሉ መስፈርያ ሆኖ የሚቀርብበት ማኅበረሰብ ውስጥ ስለአባቴ ማንነት ለማወቅ ብጥር ምን ይገርማል?”
በግርምት ለጥቂት ጊዜ አተኩሮ ሲያየኝ ከቆየ በኋላ ወደ መኪናው ውስጥ ይዞኝ ገባ፡፡ ከዚያ ከመኪና እረኛዋ (ከፓርኪንግ ሠራተኛዋ) እስክርቢቶ ተውሶ፣ በቢጫ ማስታወሻ ደብተሩ ውስጥ አንድ ቅጠል ገንጥሎ የሚከተለውን ጻፈልኝ፤
በዕውቀቱ ሥዩም - በዳዳ - ደስታ - ወየሳ
“ይሄው ነው?”
“እኔ የማውቀው እስከዚህ ድረስ ያለውን ነው፤ ሌላውን ደሞ የሁላችን ታላቅ የሆነችውን አበራሽን ጠይቃት”
ትንሽ አሰብ አድርጌ፤
“አባታችን አባቱ በዳዳ ተብሎ እንደሚጠራ ነፍስ ስናውቅ ጀምሮ ይነግረን ነበር፡፡ ግን በመሰለ ለምን እንደሚጠራ ጠይቀነው አናውቅም፡፡ ለምንድነው አባታችን በመሰለ የሚጠራው?  
አማረ ማብራራት ጀመረ፡፡
ምንጭ፡- (ከበዕውቀቱ ሥዩም
“ከአሜን ባሻገር”
አዲስ መፅሐፍ የተቀነጨበ፤ 2008 ዓ.ም)

Saturday, 06 February 2016 11:31

የኪነት ጥግ

(ስለ እግር ኳስ)
በእግር ኳስ ደስ የሚለው ነገር፣ ነገሮች በሰከንድ ውስጥ ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡
ዲዲየር ድሮግባ
ከእግር ኳስ ውጭ ህይወቴ ከንቱ ነው፡፡
ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ራሴን እንደ እግር ኳስ ተጫዋች ብቻ አልመለከትም፤ እንደ አዝናኝና ተምሳሌት እንጂ።
ካም ኒውተን
ለነገሩ እግር ኳስ ጨዋታ ነው ወይስ ሃይማኖት?
ጆሴ ሞሪኖ
የእግር ኳስ ቲፎዞ ነኝ፣ የስፖርት ቲፎዞ ነኝ፣ የውድድር ቲፎዞ ነኝ፡፡
ማቲው ማክኮናግሄይ
ብራዚል የምትበላው፣ የምትተኛውና የምትጠጣው እግር ኳስ ነው፡፡ የምትኖረው እግር ኳስን ነው!
ፔሌ
በህይወቴ የተማርኳቸውን የግብረ ገብነት እሴቶች የተማርኩት በእግር ኳስ ውስጥ ነው፡፡
አርሴን ቬንገር
እግር ኳስ ስህተት የመስራት ጨዋታ ነው፡፡ ጥቂት ስህተቶችን የሰራው ወገን ያሸንፋል፡፡
ጆሃን ክሩዩፍ
ዳንስ ጥበብ እንደሆነው ሁሉ የእግር ኳስም ጥበብ ነው - ነገር ግን በቅጡ ሲከናወን ብቻ ነው ጥበብ የሚሆነው፡፡
አርሴን ቬንገር
አንዳንድ ሰዎች እግር ኳስ የህይወትና የሞት ጉዳይ ይመስላቸዋል፡፡ እኔ ግን ከዚያም የጠነከረ መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ፡፡
ቢል ሻንክሊ
የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤቴ ሲወጣ እናትና አባቴ እግር ኳስ እንደማልጫወት ነገሩኝ፡፡
ጆ ቢዴን
እግር ኳስ ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር ነው።
ቶም ብራዲ
ሚሊዬነር ለመሆን ፈፅሞ አልሜ አላውቅም - የእግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን ነበር ያለምኩት፡፡
ቪክቶር ክሩዝ
መላ ህይወቴን እግር ኳስ ለመጫወት መስዋዕት አድርጌአለሁ፡፡
ብሪያን ቦስዎርዝ

 “ችግራቸው የቅርፅና የይዘት ነው”
(ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ)
የቴሌቪዥን ድራማዎች አልበዙም? መበራከታቸው በጥበቡ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ይኖራል?
 እኔ በግሌ የቲቪ ድራማዎች በዝተዋል ብዬ አላምንም፡፡ እዚህ ጎረቤት ኬንያ፣ በቀን 4 ተከታታይ ድራማ ይታያል፡፡ በMBC 2 አረብ ሳት፣ ቀንና ሌሊት ፊልም ነው የሚታየው፡፡ በሳምንት አንድ ድራማ ብቻ ይታይ ከነበረበት ጊዜ አንጻር ካየነው ጥሩ ነው፡፡ አዎንታዊ ጎኑ  በዋናነት፣ሰዎች አማራጭ የሚያዩት ነገር እንዲኖራቸው ማድረጉ ነው፡፡ አንድ ድራማ ብቻ በነበረ ወቅት ምርጫ የለም፤ መጥፎም ሆነ ጥሩ ያንኑ ማየት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ለተከታታይ ድራማ እድገት በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ እንግዲህ ብዛት ይቀድማል፤ጥራት የሚመጣው ዘግይቶ ነው፡፡ አሉታዊ ጎኑ ብዙ ሲሆኑ ተመሳሳይነትና ተደጋጋሚነት ይኖራቸዋል፤ በዚህም ተመልካቹን የማሰልቸት ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡  
የቲቪ ድራማዎች አጠቃላይ ይዘታቸው ምን ይመስላል?
እንግዲህ እንደነገርኩሽ በዙ ሲባል ያስቀኛል፡፡ የሚታየው ነገር ጥራት ቢኖረው እኮ ችግር የለውም፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የቅርፅና የይዘት ነው፡፡ በድራማዎቹ ምንድን ነው እየተላለፈ ያለው መልእክት? ጥልቀትና ብስለት አለው ወይ? ግልብ ነገር መስራት የትም አያደርስም፡፡ እና በይዘትም በቅርፅም ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ  የተሻሉ ስራዎች ይኖራሉ፡፡  
በድራማዎቹ መካከል --- ተወዳጅ ለመሆን እርስ በርስ የመፎካከር ነገር ይታያል?
 ገና አልተጀመረም፤ፉክክር የሚጀምረው ጥራት ሲመጣ ነው፡፡ ምናልባትም በቀጣዮቹ አምስትና አስር ዓመታት አሪፍ ስራዎችን ልናይ እንችላለን፡፡ ጥሩ የድራማ አፃፃፍና ምርጥ ፕሮዳክሽኖች ይመጣሉ፡፡   
አንዳንድ ድራማዎች በስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ታልመው ስለሚሰሩ ደረጃቸው የወረደ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ? …
በአሁን ሰዓት የቴሌቪዥን ድራማ ገንዘብ ያስገኛል የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ፕሮዲዩሰሮች ተበራክተዋል። ያለአቅማቸው የማይችሉትን እየጎረሱ ነው፡፡ ለገንዘብ መስራት ሃጢያት አይደለም፡፡ ግን ብቃት ያስፈልጋል። ገንዘብ ላይ ያተኮረ፣ ስምና ዝናን ያማከለ ስራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ብቃት የሌላቸው ዳይሬክተሮችና ፕሮዱዩሰሮች ይገጥሙሻል፡፡ እነዚህ ጥራት እያደገ ሲመጣ ከጨዋታ ውጭ ይሆናሉ፡፡
“አንዳንድ የቲቪ ድራማዎች አይመጥኑም”
(ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ)
የቴሌቪዥን ድራማዎች አልበዙም? መበራከታቸው በጥበቡ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ይኖራል?
አዎንታዊ ጎኑ ሁልጊዜ ከብዛት ጥራት ይገኛል፡፡ ሰዎች ከጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ከድክመትም ይማራሉ፡፡ ብዙ ጠንካሮች እድል ባላገኙበት ሁኔታ ከሆነ ነው አስቸጋሪ የሚሆነው፡፡ የቴሌቪዥን ድራማ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለልጆችና አዋቂዎች ተመሳሳይ ነገር ነው የሚቀርብላቸው፡፡ ለሁሉም አንድ ነው፡፡ እንደዚህ ያልጠራና ሁሉን ያላማከለ፣---- አቅጣጫ የሌለው ሲሆን ብዥታ ይፈጥራል፡፡
የቲቪ ድራማዎች አጠቃላይ ይዘታቸው ምን ይመስላል?
ምናልባት የኢቢሲ ኤዲቶሪያል ፖሊሲን መሰረት ተደርጎ ስለሚሰራ ይሆናል፡፡ የቲቪ ድራማዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና መሰል ጉዳዮችን እንዲፈትሹ ይፈለጋል፡፡ ነገር ግን  በሳይኮሎጂ ህብረተሰቡን የማከምና ፆታዊ፣ማህበራዊና ሌሎች ጉዳዮችን መዳሰስ ይቻላል።  አንዳንዴ በድራማዎች መካከል መመሳሰል ሊከሰት ይችላል፡፡ ሆኖም አተያያቸውና የትኩረት አቅጣጫቸውም ሊመሳሰል አይችልም፡፡ አንዳንድ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ድራማዎች ብቃታቸው ታይቶ ነው አየር ላይ የሚቀርቡት? የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በተለይ የተወሰኑት በህዝብ አይን፣ ጊዜ፣ አእምሮና ባህል ላይ እንደ መቀለድ የሚቆጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በጭራሽ ለቲቪ ድራማ የማይመጥን ሥራ እያየን ነው፡፡ ምስሉ ያብረቀረቀ ሁሉ ያምራል ማለት አይደለም፡፡ አሁን በሚሄድበት ሃዲድ ምን ያህል ይጓዛል የሚለው ያጠያይቃል፡፡
ከብዛታቸው አንፃር የቲቪ ድራማዎች ያለባቸው ተግዳሮት ምንድን ነው?
ሰው ለምሳሌ እያየሁ ያለሁት “መለከት” ነው “ዋዜማ” ሊል ይችላል፡፡ ሎጎውን እስኪመለከት ድረስ ኢቢኤስ ነው ኢቢሲ በሚል መደነጋገርም ይፈጠራል፡፡ ይህን የሚያመጣው የገፀ ባህሪያት መመሳሰል ነው፡፡ ደግነቱ የኛ ተመልካች ቶሎ የሚሰለች አይደለም፡፡ በጊዜ ሂደት ግን አዲስ ነገር መፈለጉ አይቀርም፤ካላገኘ የተሰራውን ባለመመልከት፣ በመዝጋት መቅጣት ይጀምራል። አማራጮች ሲያገኝ ወደ ማወዳደር ይገባል፡፡ ሰው እስኪሰለች ድረስ መጠበቅ ግን አይገባም፡፡ ድራማዎችና በጥራትና በሚመጥን መልኩ መስራት አለባቸው፡፡
አንዳንድ ድራማዎች በስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ታልመው ስለሚሰሩ ደረጃቸው የወረደ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ? …
የፊልሙ አካሄድ ወደ ቲቪ ድራማም እየመጣ ነው። ሰዎች ከፍለው ማፃፍ እየጀመሩ ነው፡፡ መኪናቸውን ሸጠው ወደዚህ ሥራ የሚገቡ አሉ፡፡ ታዲያ የተፃፈ ሁሉ ይታያል ማለት አይደለም፡፡ ገምጋሚው አካል ደረጃቸውን በጥራት ፈትሾ ማሳለፍ አለበት፡፡ ጥሩ ድራማ ከቀረበ እኮ የግዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ነጋዴው በሰልፍ ይመጣል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን ትውልዱ ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ልጆቻችን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገራዊ ጉዳዮችን ለነሱ በሚመጥን መንገድ ተሰርቶ ማየት ካልቻሉ ልንለያይ ነው፡፡ እኔና ልጆቼ በጋራ ተቀምጠን የምናየው ፕሮግራም መሰራት አለበት፡፡ አሁን የእኔ ልጅ ሳይማር አረብኛ ይናገራል፡፡ በአገሩ ቴሌቪዥን ቋንቋና ባህሉን ማሳደግ ሲገባው፣ የአረብ ቻናል በማየት አረብኛ ችሏል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የሚመጥኑና ሁሉንም ያማከሉ፣ የጠሩ ስራዎች ሊቀርቡ ይገባል፡፡   
“ድራማ ለፅድቅ ልስራው የምትይው አይደለም;
(የፊልም ዳይሬክተር፤ ተስፋዬ ማሞ)
የቴሌቪዥን ድራማዎች አልበዙም? መበራከታቸው በጥበቡ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ይኖራል?
መብዛታቸው አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ ተፅእኖ የለውም፡፡ መብዛት ችግር የለውም፡፡ ዋናው የበዙት ምን አይነቶቹ ናቸው የሚለው ነው፡፡ በተረፈ ብዙ መሆናቸው ውድድርና የእርስ በርስ ፉክክርን ያበረታታል፡፡
የቲቪ ድራማዎች አጠቃላይ ይዘታቸው ምን ይመስላል?
 የተጠና ነገር ሳይኖር በጅምላ መፈረጅ ይከብዳል። ግን የሚያስገርመው---- ስንት ዓመት ድራማ ስንሰራ ኖረን፣ገና ጀማሪ ስለሆንን፣ ሁሉም ይሞክር አይነት እየተባለ ነው፡፡ ይሄ “ጀማሪ ነኝ፣ ጀማሪ ነኝ” መቼ እንደሚቆም እግዜር ይወቀው፡፡ ብዙ ጊዜ ከድራማው ይልቅ ዝነኛ ሰዎችን፣ ታዋቂ ፊቶችን ---- ለማካተት ነው ትኩረት የሚሰጠው፡፡
ከብዛታቸው አንፃር የቲቪ ድራማዎች ያለባቸው ተግዳሮት ምንድን ነው?
ለምሳሌ በኢቢሲ እሁድ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ሁለት ድራማ አይጠፋም፡፡ ድራማ ሲባል ለምን ረቡዕና እሁድ ብቻ እንደሚታሰብ አይገባኝም፡፡ በሌሎች ቀናት ለምን አይበተንም፡፡ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሲሆን ተመልካች ሳይወድ በግድ አንዱን ብቻ መርጦ እንዲመለከት ያደርገዋል፡፡ ወደፊት ቻናል እየበዛ ሲመጣ ደግሞ ውድድሩ በነሱ መካከል ይሆናል፡፡ ያኔ እኛም የተሻለ ነገር እናያለን፡፡
አንዳንድ ድራማዎች በስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ታልመው ስለሚሰሩ ደረጃቸው የወረደ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ? …
 እንደሱ ብሎ መነሳት ይከብዳል፡፡ ለምሳሌ ገመናን ብናይ፣ገንዘብ የመሰብሰብ ሳይሆን በሙያ የማትረፍ አላማ ነበረው፡፡ ሰው ለሰውም እሱን ተከትሎ ስለመጣ፣ ከገመና የተሻለ ነገር ለማቅረብ በውድድር ስሜት በመሰራቱ፣ ጥሩ ነገር ለማየት ችለናል፡፡ አሁን አሁን  ሲጀመር ጥሩ ይሆንና በኋላ ጥድፊያ! በእርግጥ ድራማ ከፍተኛ ወጪ ያለው ስራ ነው፡፡ ለፅድቅ ልስራው የምትይው አይደለም፡፡ ግን እንደ ፊልሙ እየሆነ መጥቷል፤ ገንዘብ ስላለ ብቻ የሚገባበት፡፡
ገንዘብ ይዞ መምጣቱ ባልከፋ፤ግን የወጣውን ገንዘብ  ለመመለስ ሥራው ተወዳጅ መሆን አለበት፤ ያለበለዚያ ባለገንዘቡም ተመልካቹም አያተርፉበትም፡፡ እናም በተቻለ አቅም በባለሙያዎችና በጥራት መስራት ያስፈልጋል፡፡
*   *   *
“አማራጭ ከሌለሽ ያለውን ታያለሽ;
 “መብዛታቸው ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው!አሁን አማራጭ ስላለ የምትፈልጊውን ታያለሽ፡፡ `ለምሳሌ ”በቀደሙት ሳእታት ኢቲቪ ላይ Up”ßእሮብና እሁድ ነው ያለው፡፡ አማራጭ ከሌለሽ ያለውን ጠብቀሽ ታያለሽ፡፡ አሁን ላይ በእኩል ሰዓት ለምሳሌ እሮብን ብታይ ኢቢኤስ ላይም አለ፣ ኢቢሲ ላይም አለ፡፡ የመረጥሽውን መከታተል ትችያለሽ፡፡;
(ወጣት ቤተል:ሔም ባህሩ)
“የሚንዛዙ ድራማዎች አሉ”
 “መብዛታቸው መልካም ቢሆንም እየተንዛዙ ያሉ ድራማዎች ደግሞ አሉ፡፡ ለምሳሉ አንድ ሂደት ለማሳየት ረጅም ሰዓት የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ያ ደግሞ ጥራቱን ያጓድላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለተመልካችም ያሰለቻል። ሌላው ለምሳሌ ኢቢኤስና ኢቢሲ በተመሳሳይ ሰዓት ድራማ ያሳያሉ፡፡ ይሄ ለማንም ጥሩ አይደለም፤ተናበው ቢሰሩ ይመረጣል”
 (አካሉ ጴጥሮስ)
“መብዛታቸው ምርጫ ሰጥቶኛል”
“የተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተከፍተዋል፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ በነሱ አማካኝነትም በርካታ ድራማዎች ይታያሉ፡፡
ምን ያህል ጥሩ ናቸው፣ አይደሉም የሚለውን ሙያዊ ትንታኔ ለመስጠት ይከብደኛል፡፡ ባለኝ እውቀትና እይታ ግን አብዛኞቹ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ትኩረታቸው ፍቅር ላይ ነው፤ መጨረሻቸውም ፍቅር ነው፡፡ ልክ ፊልም ላይ እንደምናየው /አሁን የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም/ ሁሉም ፍቅር ላይ ነው፡፡ ሌሎች በፊልም፣ በድራማ፣ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮችን ሥራዎች ቨማየት፣ የአገራችንን የድራማ፣ ፊልምና ቲያትር እድገት ራሳችን ማሻሻል መቀየር እንችላለን፡፡ ተመሳሳይ ናቸው፤- የፍቅር ታሪኩ አመጣጡና ድንበሩ ይለያይ እንጂ ከመፋቀር አይዘልም፡፡ መሻሻል አለበት እላለሁ፡፡ ሆኖም መብዛታቸው ምርጫ ሰጥቶኛል፤ በምመርጠው ቴሌቪዝን የፈለግሁትን ለማየት ችያለሁ”
(ሄለን አይችሉም)  
“እኔ መብዛታቸው ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ድሮ ትዝ የሚለኝ ፣ድራማ ሲኖር ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ˜አንድ ብቻ ስለሆነ፤ ማታ እኮ እንትን ይታያል እል ነበር፡፡ አሁን ግን የመረጥኩትን ማየት አያለሁ፡፡”
(ትእግስት ወገኔ)

የታዋቂው ገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ የመጀመሪያው 20ሺ ቅጂ በግማሽ ቀን ውስጥ ተሸጦ ማለቁን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ባለፈው ሰኞ ጠዋት ገበያ ላይ የዋለው መፅሀፉ፤ ከሰዓት በኋላ ተሸጦ እንዳለቀ ታውቋል፡፡ ሁለተኛው ህትመት ከአስር ቀናት በኋላ በድጋሚ በገበያ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
የአንድ መፅሃፍ መደብር ባለቤት ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ “እስከዛሬ ከሸጥኳቸው መፃህፍት በአንድ ቀን ያለቀ አልገጠመኝም፡፡ ይሄ የመጀመሪያው ነው፡፡” ብሏል፡፡
ሌላው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የመፅሃፍ አከፋፋይ በበኩሉ፤ “ብዙ የመፃህፍት ሽያጭ እንቅስቃሴ በሌለበት በዚህ ወቅት በአጭር ጊዜ ተሸጦ ያለቀው “ከአሜን ባሻገር” የመፃህፍትን ገበያ አነቃቅቷል፡፡ እስካሁን ታትሞ በወጣ በግማሽ ቀን ውስጥ ተሸጦ ያለቀ መፅሃፍ አላየሁም፡፡ በህዝቡ ውስጥ የተለየ ስሜት የፈጠረና ሁሉም ነጋዴ የያዘው መፅሃፍ ነው፡፡” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ሌሎች መፃህፍት የራሳቸው አንባቢ አላቸው፤ ይሄኛው ግን ወጣት አዛውንት ሳይል በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የጠየቁትና የገዙት መፅሃፍ ነው፡፡” ሲልም አክሏል አከፋፋዩ፡፡
“ይህች መጽሐፍ ጉዞ ቀመስ፣ ፖለቲካ ቀመስና ታሪክ ቀመስ መጣጥፎችን ይዛለች” በሚል ደራሲው በመግቢያው የገለፀው ይኸው መጽሐፍ፤ በ70 ብር ነው ለገበያ የቀረበው፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም በአሜሪካ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡   

Saturday, 06 February 2016 11:11

የስኬት ጥግ

- ስኬት ምስጢር የለውም፡፡ የዝግጅት፣ ተግቶ
የመስራትና ከውድቀት የመማር ውጤት ነው፡፡
ኮሊን ፖል
- ከገንዘብ በቀር ምንም የማይፈጥር ቢዝነስ ደካማ
ቢዝነስ ነው፡፡
ሔነሪ ፎርድ
- አንተ አንድ ግሩም ሃሳብ ካለህ ሰዎች ሌላ 20
ያቀርቡልሃል፡፡
ሜሪ ቮን ኢብነር - ኢሼንባች
- ታላላቅ ኩባንያዎች የሚገነቡት በታላላቅ
ምርቶች ላይ ነው፡፡
ኢሎን ሙስክ
- መሸጥ የማይችል ከሆነ ፈጠራ አይደለም፡፡
ዴቪድ ኦጊልቪ
- ሌሎች ሰዎች ሲሸጡ እኔ እገዛለሁ፡፡
ጄ.ፓል ጌቲ
- ገንዘብ መስራት ቀላል ነው፡፡ በጣም የሚከብደው
ልዩነት መፍጠር ነው፡፡
ቶም ብሮካው
- ሁሉም ዘላቂ ቢዝነሶች የሚገነቡት በወዳጅነት
ላይ ነው፡፡
አልፍሬድ ኤ. ሞንታፔርት
- ቢዝነስ በራሱ ኃይል ነው፡፡
ጋሬት ጋሬት
- የሥራ ኃላፊ የውደሳ ጭብጨባዎችን አይሰማም።
አልቪን ዳርክ
- ስኬታማ ለመሆን ልብህን ቢዝነስህ ውስጥ፣
ቢዝነስህን ልብህ ውስጥ ማድረግ አለብህ፡፡
ቶማስ ጄ. ዋትሶን

Saturday, 06 February 2016 11:13

የዘላለም ጥግ

- እውነተኛ እጣ ፈንታችን ፍቅር ነው፡
፡ የህይወትን ትርጉም ለብቻችን ፈልገን
አናገኘውም - ከሌሎች ጋር ሆነን እንጂ፡፡
ቶማስ ሜርቶን
- እጣ ፈንታህ ቅርፅ የሚይዘው ውሳኔዎችን
በምታሳልፍባቸው በምትወሰንበት ቅፅበቶች
ነው፡፡
ቶኒ ሮቢንስ
- እያንዳንዱ ሰው የራሱን እጣ ፈንታ የመወሰን
መብት አለው፡፡
ቦብ ማርሊ
- እጣ ፈንታ የዕድል ጉዳይ አይደለም፡፡ የምርጫ
ጉዳይ ነው፡፡ ቁጭ ብለን የምንጠብቀው ነገር
አይደለም፤ የምናሳካው እንጂ፡፡
ዊሊያም ጄኒንግስ ብርያን
- ሰዎች እጣ ፈንታን አይቀርፁትም፡፡ ዕጣ ፈንታ
ለጊዜው የሚሆን ሰው ይፈጥራል፡፡
ፊደል ካስትሮ
- የአንተ እጣፈንታ የእኔ እጣፈንታ ነው፡፡ የአንተ
ደስታ የእኔ ደስታ ነው፡፡
አይስሎም ካሪሞቭ
- ሁላችንም ከእጣ ፈንታችን ጋር የታሰርን ነን፤
ራሳችንን ነፃ የምናወጣበት መንገድ የለም፡፡
ሪታ ሃይዎርዝ
- ሁሉም ሰው የየራሱ እጣ ፈንታ ፈጣሪ መሆን
አለበት፡፡
ማርቲን ዴላኒ
- እጣ ፈንታህን ተቆጣጠር፤ ያለበለዚያ ሌላ
ሰው ይቆጣጠረዋል፡፡
ጃክ ዌልሽ
- በእጣፈንታ፣ በእግዚአብሔር ጣልቃገብነትና
ተግቶ በመስራት አምናለሁ፡፡
ካትሪና ካይፍ
- ሁሌም ዲ ሞክራሲ ፍ ፁም እ ንዳልሆነ
ለማስረዳት ከመሞከር ወደ ኋላ ብዬ
አላውቅም፡፡ ነገር ግን ዕጣ ፈንታህን ለመቅረፅ
ዕድል ይሰጥሃል፡፡
ኤዩንግ ሳን ሱ ኬዩ
- ሁልጊዜ የሰውን ልጅ ለመብረር የሚያስችለው
ማሽን መስራት እጣ ፈንታዬ ነው አስብ ነበር፡፡
ሊኦናርዶ ዳቬንቺ
- የምትንቀውን ሥራ እየሰራህ እጣ ፈንታህን
እውን አታደርግም፡፡
ጆን ሲ. ማክስዌል
- ታሪካችን እጣ ፈንታችን አይደለም፡፡
አላን ኮኸን፡፡

አቤል በ6፣ ጀስቲን ቢበር በ5 ዘርፎች ታጭተዋል

   ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአር ኤንድ ቢ ሙዚቃ አቀንቃኝ አቤል ተስፋዬ ወይም ዘ ዊክንድ እና ታዋቂው ድምጻዊ ጀስቲን ቢበር የካናዳውያን የግራሚ ሽልማት ተብሎ በሚታወቀው የዘንድሮው የጁኖ የሙዚቃ ሽልማት በበርካታ ዘርፎች በመታጨት መሪነቱን መያዛቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘገበ፡፡
የ25 አመቱ ኢትዮ-ካናዳዊ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ በዘንድሮው 45ኛው የጁኖ አመታዊ ሽልማት በስድስት ዘርፎች መታጨቱን የገለጸው ዘገባው፣ አምናም በአመቱ ምርጥ አርቲስት እና በአመቱ የአር ኤንድ ቢ ሶል ሪከርዲንግ ዘርፎች ተሸላሚ እንደነበር አስታውሷል፡፡
አቤል በዘንድሮው የጁኖ ሽልማት በዕጩነት ከቀረበባቸው ስድስት ዘርፎች፣ የአድናቂዎች ምርጫ፣ የአመቱ ምርጥ አልበምና የአመቱ ምርጥ የዘፈን ደራሲ... ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡
ጀስቲን ቢበርና ሌላው ታዋቂ ካናዳዊ ድምጻዊ ድሬክም በ2016 የጁኖ አለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማት በአምስት ዘርፎች ለሽልማት መታጨታቸውን ያመለከተው ዘገባው፣ የሽልማት ስነስርዓቱ በመጪው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በካልጋሪ እንደሚካሄድም አክሎ ገልጿል፡፡