Administrator

Administrator

Saturday, 21 March 2015 10:29

ከበደች ተክለአብ አርአያ

ሰዓሊ፣ ቀራጺ፣ ገጣሚ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር
  የስነጥበብ ትምህርት መማር የጀመርኩት በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በ17 ዓመቴ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በስነጥበብ ሙያ እተዳደራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ስነጥበብን የመስራት ፍላጎት ብቻ ነው የነበረኝ፡፡ ህይወት ግን መንገዴን ወደ ስነጥበብ አቅጣጫ መራችው፡፡ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በተካሄደው የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳትፎ በማድረጌ መታደን ስጀምር፣ በጅቡቲ በኩል ለማምለጥ ሞከርኩ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በወቅቱ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በድንበር ግጭት ውስጥ ስለነበሩ፣ ድንበር ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች በቁጥጥር ውስጥ አዋሉኝ፡፡ ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍኩት በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነበር፡፡ ህይወት ግን ለሁሉም ነገር ምክንያት ነበራት፡፡ “በገሃዱ አለም የምናስተናግዳቸው ሽንፈቶቻችን፣ በስነጥበቡ አለም ድሎቻችን ይሆናሉ፡፡ በስነ ውበት አይን ሲታይ፤ ችግሮቻችንን፣ ስቃዮቻችንንና ሽንፈቶቻችንን በመውደድና በእነሱ ከመማረር ይልቅ ወደ ስነጥበብ ስራነት በመቀየር፤ የኋላ ኋላ በቁጥጥራችን ውስጥ እናደርጋቸዋለን” በማለት ጽፋለች ሜልቪን ራደር። በእስር ቤት ያሳለፍኳቸው አመታት፣ ከተቀረው አለም የሰው ልጅ ጋር ትስስር ለመፍጠሬ ሰበብ ሆነውኛል፡፡ ለስነጥበብ ስራዎቼ የመነቃቃት ምንጭ የሆኑኝም እነዚያ የግዞት አመታት ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ መርካቶ የሚባለው ሰፈር ውስጥ በ1950 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ መጠነኛ ገቢ ያላቸው ወላጆቼ ካፈሯቸው አራት ልጆች፣ እኔ የመጨረሻዋ ነኝ፡፡ ዛሬም ድረስ የሚከተለኝን ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረችብኝ አሁን በህይወት የሌለችው እናቴ ናት፡፡ እናቴ መንፈሳዊውን አለም ከምድራዊው አለም ጋር በሚገርም ሁኔታ አጣጥማ ህይወቷን ስትመራ የኖረች፣ ፍጹም ሃይማኖተኛ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበረች፡፡ መደበኛ ትምህርት ባትከታተልም እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላትና ለስነጽሁፍ ፍቅር የነበራት ሴት ነበረች። የማክሲም ጎርኪን መጽሃፍት አነብላት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከጎርኪ ስራዎች፣ ‘እናት’ ለሚለው ረጅም ልቦለድ የተለየ አድናቆት ነበራት፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍ የቻለችው በራሷ ጥረት ነው፡፡ ለስነግጥም፣ በተለይ ደግሞ ለቅኔ እንዲሁም ለቲያትር የተለየ ፍቅር ነበራት፡፡ የስነጥበብ ስሜትም ነበራት። የራሷን የጥልፍ ዲዛይኖች ትሰራ ነበር፡፡ ለፍትህ መከበር ጠንካራ አመለካከት ያላት እናቴ፣ ከቁሳዊ ስኬቶች ይልቅ ለእሴቶች ራሳቸውን ከሚያስገዙ ጥቂት ሰዎች አንዷ ነበረች፡፡ በትምህርት አጥብቃ ታምናለች፡፡ አባቴ ወደ መቀሌ ከተማ ሄዶ መድሃኒት ቤት ሲከፍትና ፊቱን ወደ ንግድ ሲያዞር፣ እሷ ግን እኛን ልጆቿን ለማስተማር አዲስ አበባ መቅረትን ነው የመረጠችው፡፡ ከትምህርት ቤት ስንመለስ  ውሏችንንና የተማርነውን  ትጠይቀናለች፡፡ የቤት ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራም ታበረታታናለች፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህራን  መጽሃፍትን ሲያነቡልን በጽሞና አዳምጣቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይሄን የማደርገው ወደ ቤቴ ስመለስ ታሪኩን በአግባቡ ለእናቴ ለመተረክ ስል ነበር፡፡ እናቴ ሁሌም ከጎኔ ነበረች፡፡ በተደጋጋሚ ባጋጠሙኝ ፈታኝ የመከራ ጊዜያት ሁሉ በጽናት እንድቆም ትደግፈኝ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ስነጽሁፍ የመማር ሃሳብ  ነበረኝ፡፡ ንባብ ስወድ ለጉድ ነው፡፡ ግጥም ነፍሴ ነው፡፡ ቅኔ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እየሄድኩ ግዕዝ መማር የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በየጉራንጉሩ ግጥሞችን እየጻፉ መበተን ትልቅ የትግል ስልት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ግጥሞችን መጻፍ የጀመርኩት፡፡ እርግጥ የስዕል ስሜትም ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሆኜ፣ የሳይንስ ትምህርት ስዕሎችን መሳል እወድ ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ስዕልና ቀለም ቅብ ይወዱ የነበሩት ወንድሜና አንድ ጓደኛዬ  ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ፣ አስራ አንደኛ ክፍልን ተምሬ እንደጨረስኩ ስነጥበብ ለማጥናት ወስኜ፣ በ1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅም ትምህርቴን ተከታተልኩ፡፡
በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግስት፤ የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት፡፡ ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን፡፡ በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን፡፡ በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር፡፡ አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ ይህ መሆኑን ሳናውቅ ነው፣ በእግራችን ጉዞ የጀመርነውና የሶማሌ መደበኛ ጦርና  የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን የገባነው። በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን። በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍናቸው በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነው፡፡ በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በአለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት አግባቢነት ይመስለኛል፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ፡፡ እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን፡፡
እነዚያ በእስር ያሳለፍናቸው አመታት እጅግ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከእስር ቤቱ ቅጽር ውጪ ካለው አለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረንም። ከጉሮሮ የማይወርድ ምግብ እየበላን፣ ንጽህና በጎደለው ማጎሪያ ውስጥ አስከፊ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ውለን ማደር ነበረብን፡፡ ወባና በደም ኢንፌክሽን የሚፈጠረው ቺስቶሶሚያሲስ የተባለ በሽታ፣ ዘወትር ከእስር ቤቱ የማይጠፉ የተለመዱ የእስረኞች የስቃይ ምንጮች ነበሩ፡፡ ልንፈታ አንድ አመት ገደማ ሲቀረን፣ የኮሌራ ወረርሽኝ ሳይቀር ተከስቶ ነበር፡፡ እስር ቤት ውስጥ፣ ፍጹም ስለ ራሳቸው ግድ የሌላቸው አልያም ፍጹም አደገኛና ራስ ወዳድ ሰዎችን ልታገኚ ትችያለሽ፡፡ እኛ ጋ ሁለቱም አይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ከዚያ መከራ ያተረፈኝ ለእናቴ ብሎ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እሷ ለኔ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ትልቅ ስጦታ ነበረች፡፡
 እንደ እስረኛ እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር - በቁሳቁስ ሳይሆን መከራን አብሮ በመጋፈጥ። የጽሁፍ መሳሪያዎችን  ባገኘሁበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በርካታ ግጥሞችን ጽፌያለሁ፡፡ የመድሃኒት ፓኮዎችንና የዱቄት ወተት ክርታሶችን እንደ ወረቀት እየተጠቀምን ነበር የምንጽፈው፡፡ እርግጥ በአማርኛ መጻፍ ክልክል ስለነበር፣ የጻፍኳቸውን ግጥሞች በየስርቻው እደብቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ግጥሞቼ በአይጥና በድመት ተበልተዋል፣ በርካቶችም ጠፍተዋል፡፡ መጻፌ ከአእምሮ መቃወስ አድኖኛል። ቀስ በቀስ ትምህርት ቤት አቋቁመን ለእስረኞች ፊደላትን ማስቆጠርና ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር ጀመርን፡፡ ሳይንስ እና እንግሊዝኛን የመሳሰሉ ትምህርቶችን አስተምር ነበር፡፡ ትልቁ አስተዋጽኦዬ አማርኛ ማስተማር ሲሆን የተለያዩ ታሪኮችና ግጥሞችን እየጻፍኩ ለማስተማሪያነት እጠቀምባቸው ነበር፡፡ እኛ ከእስር ስንፈታ ማንበብና መጻፍ የማይችል እስረኛ አልነበረም። ትምህርቱም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል አድጎ ነበር፡፡ መጽሃፍትን የምናገኘው አልፎ አልፎ ነው። በተለየ ሁኔታ የማስታውሳቸው፣ የፕሪሞ ሌቪን መጽሃፍትና የአሌክስ ሄሊን ‘ሩትስ’ የተሰኘ መጽሃፍ ነው፡፡ በሄሊ መጽሃፍ ውስጥ የተሳሉት የመስክ ሰራተኞች ህይወት፣ ከእኛ ህይወት ጋር በሚገርም ሁኔታ መመሳሰሉ ቀልቤን ማርኮት ነበር፡፡ ራሳችንን ዋጋ እንዳለው ሰብአዊ ፍጡር እንድናስብ ያገዙን  እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡
እንደተፈታሁ ወዲህ ወዲያ ሳልል በቀጥታ የመጣሁት ወደ አዲስ አበባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወንድሜ እኔን ፍለጋ አዲስ አበባ መምጣቱን ሰምቻለሁ፡፡ ወንድሜ ያንን ማድረጉ ለእኔም ሆነ ለእሱ አደገኛ ነበር፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቄ፣ መላው ቤተሰቦቼ ወደሚኖሩባት አሜሪካ አቀናሁ፡፡ ከረዥም ጊዜያት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከእናቴ፣ ከወንድሜ፣ ከእህቴና ከቀሩት ቤተሰቦቼ ጋር ለመቀላቀል ቻልኩ። ለዓመታት ያቋረጥኩትን የስነጥበብ ትምህርት በመቀጠልም፣ በዋሽንግተን ዲሲው  ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በስነጥበብ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ስከታተል ግሩም  መምህራን  ገጥመውኛል፡፡ ሁለት ድንቅ መካሪ ዘካሪም  አግኝቻለሁ፡፡ የስነጥበብ መምህሬ እስክንድር ቦጎሲያንና የፊልም መምህሬ አብይ ፎርድን፡፡ ከእስክንድር ጋር በመሆን ‘ኔክሰስ’ የተሰኘ የሥነጥበብ ስራ ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመስራት እድል አግኝቻለሁ፡፡
በስዕሎቼ ስሜቶቼን፣ ትዝታዎቼን እንዲሁም ጊዜና ቦታ ከሚገድባቸው ግላዊ ገጠመኞቼ፣ ዘመን እስከማይሽራቸው አለማቀፍ ጉዳዮች የተዘረጋውን ምናቤን መግለጽ ጀመርኩ፡፡ ራሴን በግላዊ ገጠመኞቼና ልምዶቼ ላይ ብቻ አልገደብኩም። ምናቤን ሰፋ በማድረግ ጦርነት፣ ስቃይና በስተመጨረሻም ፈውስን ወደመሳሰሉ አለማቀፍ ጉዳዮች ገባሁ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ፣ በቀላሉ የሚለዩ የእይታ ተረኮችን በመጠቀም የግል ልምዶቼን በአለም ዙሪያ ከሚታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር እያስተሳሰርኩ፣ ኤክስፕሬሽኒስት በተባለው የአሳሳል ዘዬ ነበር ስዕሎቼን የምሰራው። በመቀጠልም ከዚህ ቀደም እንደማደርገው ሁሉ ትኩረቴን በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ከቀድሞዎቹ በበለጠ ምስል አልባ የሆኑ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ቴክስቸር፣ ቀለምና ቅርጽን በመሳሰሉ የእይታ  መሰረታዊ ነገሮች በመጠቀም፣ ስሜትን የሚያጭሩ ሙሉ ለሙሉ ምስል አልባ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መሳል ቀጠልኩ፡፡ አሁን ብርን የመሳሰሉ ባህላዊ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ብር በውስጡ ብርሃን ስለሚያሳልፍ እወደዋለሁ፡፡ ከሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በመሸመን የተለያዩ ተደራራቢ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ስዕሎችንና ቅርጻቅርጾችን ከስነግጥም፣ ሙዚቃና ስነጽሁፍ ጋር እያዋሃድኩ የራሴን ህብር እፈጥራለሁ፡፡ አንደኛው ጥበብ በሌላኛው እንዲሁም በእኔ ላይ መነሳሳትና ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ በስቱዲዮ ስራዬን እየሰራሁ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስነጥበብ ትምህርት አስተምር ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጆርጂያ በሚገኘው ሳቫና የስነጥበብና የዲዛይን ኮሌጅ እያስተማርኩ እገኛለሁ፡፡ መምህር መሆኔን እወደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ራሴን ሙያው በየጊዜው ከሚደርስበት  ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለማድረስ ስል፣ በስፋት እንዳነብና ጥናት እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ሌላው ሙያውን እንድወደው የሚያደርገኝ ነገር ደግሞ፣ ከዚህ በፊት ልምዱ ባልነበረኝ የስነጥበብ ጉዞዎች ላይ በተደጋጋሚ እንድሳተፍ ዕድል የፈጠረልኝ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ባስተምር ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም በሙያዬ  የማበረክተው አስተዋጽኦ በእነዚህ አገራት የተሻለ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ቀን የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሰዓሊ የምሆንበትና በጽሁፍ ስራ ላይ ብዙ ጊዜዬን ማሳለፍ የምችልበት ዕድል ይፈጠርልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስነጥበብ ለኔ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ነው። ስነጥበብን የምኖርለት ሙያዬ ለማድረግ ችያለሁ ብዬ የማስበው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንድም ስለ ቁሳዊ ስኬት ተጨንቄ አላውቅም፡፡ ሁለትም ሙያው የሚጠይቀውን ዲስፕሊን አክብሬና ሙሉ ትኩረቴን በእሱ ላይ አድርጌ ነው የኖርኩት፡፡
የዛሬ ዘመን ወጣት ሴቶች ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባሉ የምላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ነገር አደጋዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ፈቃደኛ ካልሆኑ ምንም ነገር ሊያሳኩ አይችሉም። አደጋን መጋፈጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርጸው የኖሩና ቅቡል የሆኑ አመለካከቶችን መገዳደር ሊሆን ይችላል፡፡
ሴቶች ይህን ማድረጋቸው ህልማቸውን እውን ለማድረግ ያግዛቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ አደጋን መጋፈጥንና ከባህል  ልንማራቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማክበራችንን በተመጣጠነ ሁኔታ ማስኬድ ይኖርብናል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ወጣት ሴቶች እውቀትን መሻት ብቻ ሳይሆን እውቀትን ፍለጋ ከተጉ፣ ግሩም የሚባሉ ነገሮችን ለማሳካት እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡
(ሰዓሊና ገጣሚ ከበደች ተክለአብ የዛሬ 15 ዓመት አዲስ አድማስ መታተም ስትጀምር  የጋዜጣው እንግዶች ሆነው ከቀረቡት የጥበብ ባለሙያዎች መካከል ቀዳሚዋ ነበረች፡፡ ከላይ የቀረበውን ግለ ታሪክ የወሰድነው ባለፈው ጥቅምት ወር ለንባብ ከበቃውና የስኬታማ ኢትዮጵያውያንን ሴቶች ታሪኮች ከሚያስነብበው ተምሳሌት የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡)

Saturday, 21 March 2015 10:31

የፍቅር ጥግ

ፍቅርንና ጉንፋንን መደበቅ አይቻልም፡፡
ጆርጅ ኸርበርት
የብቸኝነት እስረኛ ሆኖ የሚያውቅ ሰው፣ የፍቅር እስረኛ ሆንኩ ብሎ አያማርርም፡፡
ሮበርት ብራውልት
ፍቅር፤ ማብሪያ ማጥፊያውን ሌላ ሰው የሚቆጣጠረው የኤሌክትሪክ ብርድልብስ ነው፡፡
ካቲ ካርሊሌ
ህይወት የሚጀምረው ፍቅር ሲመጣ ነው፡፡
“Bill of Divorcement” ከ
ሚለው ፊልም”
ትክክለኛውን ፍቅር ከመፍጠር ይልቅ ትክክለኛውን አፍቃሪ በመፈለግ ጊዜ እናጠፋለን፡፡
ቶም ሮቢንስ
ፍቅር የህይወት ህግ ነው፡፡
ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ
ፍቅርን በልብ ቅርፅ የምንስለው የነፍስን ቅርፅ ስለማናውቀው ነው፡፡
ሮበርት ብራውልት
ላንቺ ያለኝን ፍቅር ሁሉ ለመሸከም 100 ልቦች በቂ አይደሉም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
ፍቅር ሰዎችን ይፈውሳል - ሰጪዎቹንም ተቀባዮቹንም፡፡
ካርል ሜኒንገር
ፍቅር እንደ ድንጋይ ባለበት ዝም ብሎ አይቀመጥም፤ እንደ ዳቦ መጋገር አለበት፤ ሁልጊዜ እንደገና መሰራት፣ እንደ አዲስ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ኡርሱላ ኬ.ሊ.ጉይን
መሸ ተብሎ የፍቅር ጨዋታ አይቀርም፡፡
ቶም ማሶን
ፍቅር የያዘው አዛውንት፣ እንደ ክረምት አበባ ነው፡፡
የፖርቹጋሎች ምሳሌያዊ አባባል
ፍቅር የስሜቶች ቅኔ ነው፡፡
ኦኖር ዲ ባልዛክ
ፍቅር ሁለቱም ተጫውተው ሁለቱም የሚያሸንፉበት ጨዋታ ነው፡፡
ኢቫ ጋቦር

Saturday, 21 March 2015 10:21

የፈገግታ ጥግ

የእንቅልፍ ችግር ያለበት ህመምተኛ ሃኪሙ ዘንድ ሔዶ ምርመራ ያደርግና መድኀኒት ይታዘዝለታል፡፡ ከዚያም ሃኪሙ፤ “እነዚህን መድኀኒቶች ከወሰድክ ቤትህ ተኝተህ አለምን ስትዞር ታድርና ፓሪስ ላይ ታርፋለህ” ይለዋል፡፡ በነጋታው ህመምተኛው ወደ ሃኪሙ ጋ ተመልሶ ይሄድና “ዶ/ር፤ መተኛቱን በደንብ ተኛሁ፤ ጠዋት ስነቃ ግን የተነሳሁት እዚያው ቤቴ ውስጥ ነው” ይለዋል፡፡
ሃኪሙም፤ “ምን ዓይነት ቀለም ያለው መድኀኒት ነው የሰጠሁህ?” ታማሚው “ቢጫ”
ሃኪሙም፤ “በጣም ይቅርታ፤ የሰጠሁህ የደርሶ መልሱን ክኒን ነው”

ውሃን መጠጣት የምግብ ስልቀጣ ሂደትን ለማፋጠንና የሰመረ ለማድረግ እንዲሁም  ቆዳን ለማጥራት፣ ድካምን ለማብረድና ትኩረት የመስጠት ችሎታን ለመጨመር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከልክ ሲያልፍ ለሞት እንደሚዳርግ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች በቅርቡ ይፋ ያደረጉት መረጃ አመልክቷል፡፡
ከመጠን ያለፈ ውሃ መጠጣት የኩላሊትን የማጣራት ተግባር እንደሚያውክና ደማችንን በማቅጠን የሰውነታችንን የጨው ክምችት ቀንሶ ለሞት እንደሚዳርግ የጠቆመው መረጃው፤ የውሃው መጠን እጅግ ሲበዛ የአዕምሮአችን የውስጠኛው ክፍል እንዲያብጥና የአዕምሮ ስራ እንዲስተጓጎል ያደርጋል ብሏል፡፡ የደም ዝውውራችንንና ትንፋሻችንን የሚቆጣጠረው የአዕምሮአችን ክፍል በእብጠቱ ሳቢያ በሚደርስበት ጉዳት ስራው ሲስተጓጎል በትንፋሽ እጥረትና በደም ዝውውር መዛባት ምክንያት ለህልፈት ልናደርግ እንደምንችል መረጃው አመልክቷል፡፡
አንድ ሰው በየሁለት ሰዓቱ ከአንድ ጊዜ በላይ ሽንቱን ለመሽናት ወደመፀዳጃ ቤት ከተመላለሰና የሽንቱ ቀለም ንፁህ ውሃ የሚመስል ከሆነ፣ የጠጣው ውሃ ከመጠን ማለፉን እንደሚያመለክትም ተማራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት መረጃ ይጠቁማል፡፡

   ጉንፋን፣ ሳልና ብሮንካይትስ እየተመላለሰ ያሰቃያችኋል? በእነዚህ የጤና ችግሮች በተደጋጋሚ የምትጠቁ ከሆነ ፋርማሲ መሄድ ሳያስፈልጋችሁ ወጥ ቤት ብቻ ጎራ ብላችሁ ራሳችሁን ልትፈውሱ ትችላላችሁ፡፡
በርበሬ፣ ሚጥሚጣ፣ ቃሪያ… እንደ ሰናፍጭ ያሉ የመሰንፈጥ ባህርይ ያላቸው ምግቦች፡- ኮምጣጤና ነጭ ሽንኩርት በሳምባ ውስጥ ያሉ የአየር ቧንቧዎችን በመክፈት አየር ወደ ሳምባ እንደ ልብ እንዲገባና እንዲወጣ ወይም በዚህ ችግር ምክንያት የሚፈጠረውን ሳል የማቆም ኃይል እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡
እንደ ቃሪያ ያሉ የማቃጠል ባህርይ ያላቸው ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት አፋችንን የሚያቃጥለን ካፕሲካን (capsican) የተባለው ኬሚካል ጋውፊሲን (Guaifenesien) ከተባለው የመተንፈሻ አካላት መድኀኒት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡
በብሮንካይትስ ወይንም በጉንፋን ምክንያት ጉሮሮአችሁን መከርከር ሲጀምራችሁ ወይም ጉንፋን ሊይዛችሁ ከመሰላችሁ 3 ቀይም 4 ፍሬ ነጭ ሽንኩርት ልጣችሁ በውሃ ዋጡት፡፡ ነጭ ሽንኩርት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን በተለይም ጉንፋንና ብሮንካይትስ የሚያሲዙ ቫይረሶችን 95 በመቶ የመግደል አቅም አለው፡፡
በሾርባ ውስጥ ቃሪያ፣ ሚጥሚጣና ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ መመገብ፤ ትኩስ በዝንጅብል የተፈላ ሻይ ላይ ማር ጨምሮ መጠጣት በጉንፋን የመያዝ ዕድልን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

“የዛምቢያን ባህል ሳልረሳ የፖላንድን ባህል ተምሬአለሁ”

በትውልድ ዛምቢያዊ የሆኑት ፕሮፌሰር ኪለን ሙንያማ፤ የፖላንድ የፓርላማ አባል ሲሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በፖላንድ በተካሄዱ ምርጫዎች ተወዳድረው በከፍተኛ ድምፅ በማሸነፍ ለመመረጥ በቅተዋል፡፡ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እዚያው ፖላንድ የተከታተሉ ሲሆን በኢኮኖሚክስ የማስትሬትና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከፐዝናን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ ፕሮፌሰን ኪለን ባለፈው ሳምንት ከኢትዮ - ፖላንድ የፓርላማ ቡድን ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ከፕሮፌሰሩ ጋር በነበራት ቆይታ በጉብኝታቸው፣ በፖለቲካ ህይወታቸው፣ በአውሮፓ የኢኮኖሚ ቀውስና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

     የኢትዮጵያ ጉብኝታችሁ በምን ላይ ያተኮረ ነው?
ጉብኝታችን ለኢትዮ-ፖላንድ የፓርላማ ቡድን በተደረገው ግብዣ መነሻነት የተከናወነ ነው፡፡ ግብዣው የተላከው በ2013 ዓ.ም ሲሆን ለጉዞው የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት አሁን ልንመጣ ችለናል፡፡ በጉብኝቱ የሚሳተፈው የልኡካን ቡድን በፓርላማ አባላቱ ብቻ ከሚወሰን ከኢትዮጵውያን ጋር በትብብር ለመስራት የሚፈልጉ   የተለያዩ የፖላንድ የቢዝነስ ኩባንያዎችን እንዲያካትት ባደረግነው ጥረት ስድስት ትላልቅ ኩባንያዎችን ይዘን ነው የመጣነው፡፡ የአፍሪካ ፖላንድ የንግድ ምክር ቤት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚፈልጉትን ኩባንያዎች በማደራጀት በኩል አግዞናል፡፡ ስለዚህ የጉብኝቱ አላማ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮ - ፖላንድ የፓርላማ ቡድን ዓላማ ምንድን ነው?
ፓርላማዎች የሚመሳሰሉባቸውና የሚለያዩባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የፖላንድ ፓርላማ የራሱ አወቃቀር አለው፡፡ ፓርላማው የተለያዩ ኮሚቴዎችና የፓርላማ ቡድኖች አሉት፡፡ የፓርላማው ቡድኖች ከተለያዩ አገሮች ፓርላማዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይሰራሉ፡፡ የፓርላማ አባላቱም የሚፈልጉትን አገር የፓርላማ ቡድን ይቀላቀላሉ፡፡ የቡድኖቹ አላማ በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ላይ ያለመ ነው፡፡ ፓርላማችን ከአስራ አምስት የአፍሪካ አገሮች ጋር የፓርላማ ቡድን ግንኙነት አለው፡፡ የኢትዮ-ፖላንድ የፓርላማ ቡድንም አንዱ ነው፡፡ እኔ የኢትዮ-ፖላንድ፣ የዛምቢያ - ፖላንድ እና የኬኒያ - ፖላንድ የፓርላማ ቡድኖችን በሊቀመንበርነት እመራለሁ፡፡ በሌሎች በተለይ ከአፍሪካ ጋር የተገናኙና በፖላንድ አሜሪካን ቡድን፣ በብሪቲሽ ፖላንድ፣ በፖርቹጋል ፖላንድ የፓርላማ ቡድኖች ውስጥ በአባልነት እሳተፋለሁ። የፓርላማ ቡድኖቹ  ሊቀመንበር ወይም አባል ከሆኑባቸው አገሮች የሚመጡ ልኡካንን ተቀብሎ ያነጋግራል፣ በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ይሰራል፡፡ የኢትዮ ፖላንድ የፓርላማ ቡድን አላማም ይኸው ነው፡፡
በብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ ኮርፖሬሽን ያደረጋችሁት ጉብኝት አላማ ምን ነበር?
አብረውን የመጡት ኩባንያዎች ስለ ስራቸው አስተዋውቀዋል፡፡ የድርጅታቸውን የሥራ ታሪክና በትብብር መስራት የሚፈልጉባቸውን መስኮችም ለብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ ኮርፖሬሽን ሰጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹ መስኮች ኮርፖሬሽኑ  በጣም ትብብር የሚፈልግባቸው እንደሆኑ ተገንዝበናል፡፡ ጉብኝታችንና የተደረጉት ውይይቶች ጥሩ ውጤት ያመጣሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ አብረውን የመጡት ኩባንያዎች የብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ ኮርፖሬሽን ከሚሰራቸው ስራዎች ጋር የሚገናኝ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡
እንዴት ነው ወደ ፖለቲካው የገቡት? አፍሪካዊ ሆነው እንዴት የፖላንድ የፓርላማ አባል ለመሆን ቻሉ?
ሁሉም ነገር የሆነው የፖላንድ ዜግነት ካገኘሁ በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያ ወደ ፖላንድ የሄድኩት እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም ለትምህርት ነበር። ከኔ ጋር አራት ዛምቢያውያን ስንሆን፣ አስራ አራት ኢትዮጵያውያንም አብረውን ነበሩ፡፡ አንድ አመት የቋንቋ ኮርስ ከወሰድኩ በኋላ  ትምህርቴን በመቀጠል በ1987 ነበር ያጠናቀቅሁት፡፡ በነገራችን ላይ ሁላችንም አገራችንን ስንለቅ የመጀመሪያ ዲግሪያችንን ይዘን ለመመለስ በሚል ነበር፡፡ ወደ አገራችን የተመለስነው ግን የማስተርስ ዲግሪያችንን ሰርተን ነበር፡፡ ትምህርቴን እንደጨረስኩ እዚያው ፖላንድ ስልጠና የማግኘት እድል ስለተሰጠኝ ስልጠናዬን ጨርሼ ነው ወደ ዛምቢያ የተመለስኩት። ለሶስት ወራት ያህል በዛምቢያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ከሰራሁ በኋላ እንደገና የዶክትሬት ዲግሪዬን ለመስራት እዚያው ፖላንድ ስኮላርሺፕ በማግኘቴ፣ በ1988 ዓ.ም ወደዚያው ሄድኩ፡
ኮሙኒዝም እየከሰመ የነበረበት ወቅት ነው። በዚህ የተነሳ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታዎች እየተለወጡ ነበር፡፡ በመጨረሻም ኮሙኒዝም ሙሉ በሙሉ ሲወድቅ በሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ መጣ። የዶክትሬት ዲግሪ የመመረቂያ ፅሁፌን ከማቅረቤ በፊት የዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ የፖላንድ ዜግነት አገኘሁ፡፡
ይኼኔ ነው ወደ ፖለቲካው የገቡት?
በ2002 ዓ.ም የአካባቢ ምርጫ ይደረግ ነበር፡፡ የዲስትሪክት (አውራጃ) ሀላፊው ለዲስትሪክት ምክር ቤቱ እጩ ሆኜ እንድቀርብ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ በጣም ነበር ያስገረመኝ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ምንም አይነት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ እዚያ ብዙ አመታትን ያሳለፍኩ ብሆንም ምርጫ ተወዳድሬ አሸንፋለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም፡፡ ለሃላፊው  “ምርጫ እኮ የመራጮች ድምፅ ነው” ስለው፤ “ምርጫውን ተወዳድረህ ማሸነፍ ትችላለህ፤ ስለዚህ መወዳደር አለብህ” ብሎ ገፋፋኝ፡፡ እንግዲህ የሚሆነውን እናያለን ብዬው ተስማማሁ፡፡ ምንም አይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ አላደረግሁም፣ ድምፅ የማገኝ ከሆነ የራሴንና የባለቤቴን ሁለት ድምፅ ብቻ እንደሚሆን በመገመት ወደ ምርጫው ገባሁ። ግምቴ ግን በጣም የተሳሳተ ነበር፤ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ምርጫውን አሸነፍኩ፡፡ ያልጠበቅሁት ውጤት ስለነበር በጣም አስገረመኝም አስደሰተኝም።
ከዚያ በኋላ መራጮች ከኔ የሚፈልጉትን መስጠት እችላለሁ ወይ የሚለው ነገር የሚያሳስበኝ ሰው ሆንኩ፡፡ የተመረጥኩት ለአራት አመት ስለነበር የስራ ዘመኑ ሲያበቃ፣ ራሴን ለአውራጃ ምክር ቤት  ሳይሆን ከሱ ከፍ ወዳለው የክልል ፓርላማ እጩ አድርጌ አቀረብኩ፡፡ የክልል ፓርላማው ተመራጭ ለመሆን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ “ሲቪክ ፕላትፎርም” የተባለውን የሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ተቀላቀልኩና በ2006 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ አሸንፌ የክልል ፓርላማ ገባሁ፡፡ ከአራት  አመት በኋላ እንደገና በክልል ምርጫ አሸነፍኩ፡፡ በ2011 ዓ.ም በተደረገው አገራዊ የፓርላማ ምርጫ ፓርቲዬ እንድወዳደር እጩ አድርጎ ሲያቀርበኝ “ተወዳድሮ ማሸነፍ ይችላል ብላችሁ ካመናችሁ እወዳደራለሁ” ብዬ ተስማማሁ፡፡ የፖላንድ የፓርላማ ስርአት ተመጣጣኝ ውክልና (ፕሮፖርሽናል ሪፕረሰንቴሽን) ስለሆነ እኔ በምወዳደርበት የምርጫ ጣቢያ አራት የኔን የፓርቲ ወኪሎች ጨምሮ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ነበርን፡፡ ከኔ ፓርቲ አባላት ውስጥ እኔ በማሸነፌ ፓርላማውን ተቀላቀልኩ፡፡
መራጩ ህዝብ ከእርስዎ የሚፈልገውን አሟልቻለሁ ብለው ያስባሉ?
ይህን ሊመልሱ የሚችሉት የመረጡኝ ሰዎች ናቸው፡፡ በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሄደው ምርጫ ላይም ለመወዳደር አስቤያለሁ፡፡ ያኔ የማገኘውን ድምፅ አይቼ መናገር እችላለሁ፡፡ በእኔ በኩል ለተመረጥኩበት ቦታ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ማድረግ የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ ባይ ነኝ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ  ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዴት ይገልፁታል?
አውሮፓን በአራት መክፈል እንችላለን፡፡  38 አገሮችን የሚያካትተው የአውሮፓ ህብረት፣ 19 አገሮችን ያቀፈው ዩሮላንድ የሚባለው የአውሮፓ ሞኒተሪ ህብረት፣ የአውሮፓ የነፃ ገበያ ቀጠና አገሮች እና የአውሮፓ ህብረት አገሮች ያልሆኑት የምስራቅ አውሮፓ አገሮች እነ ራሺያ፣ ዩክሬይን፣ቤላሩስ፣ ሰርቢያ፣ሞንቴኔግሮ፣ ቦስኒያሄርዞጎቪኒያ  የሚገኙበት ምድብ አለ፡፡ ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ በዋነኛነት የማተኩረው ዩሮን በመገበያያ ገንዘብ በሚጠቀሙ  ዩሮላንድ ወይም የአውሮፓ ሞኒተሪ ህብረት በሚባለው ምድብ ላይ ባሉ አገሮች ነው። የኢኮኖሚ ቀውሱ የተፈጠረው ገንዘብ በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር በተያያዘ ሳይሆን በአባል አገሮቹ በተለይ በግሪክ፣ ስፔን ፣ ፖርቹጋል፣ ጣሊያንና  አየርላንድ ውስጥ በተከሰቱ ውጣውረዶች ሳቢያ ነው፡ አገራቱ የኢኮኖሚ እድገታቸው መሻሻልን ቢያሳይም አሁንም ችግሮች አሉባቸው፡፡  ለምሳሌ ግሪክ  የበጀት እጥረትና ከፍተኛ የዕዳ ጫና አለባት፡፡ የነዚህ አገሮች እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዩሮ ጥንካሬ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የዩሮ የመግዛት አቅም ማጣት ይበልጥ ችግሩን ያወሳስበዋል፡፡ አንድ ሰው ከሰውነት ክፍሉ የተጎዳ ቦታ ካለ፣ ያንን ክፍል መቆጣጠር መከታተል ይጠበቅበታል፡ ግሪክ በአሁኑ ወቅት ልዩ ክትትል የሚያስፈልጋት የህብረቱ አገር ሆናለች። አዲሱ የግሪክ መንግስት አገሪቱ በህብረቱ ውስጥ የሚጠበቅባትን ግዴታ ለመፈፀም ጊዜ እንዲሰጣት እየተደራደረ ነው፡፡ ከዩሮላንድ ውጪ ያሉ አገሮችን ስናይ ለምሳሌ ፖላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስዊድንና ብሪቴይን አፈፃፀማቸው የከፋ አይደለም። እኛን (ፖላንድን) ብታይ እያደግን ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረትና አይኤምኤፍ፤  ስፔይንና  ግሪክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ብድር እንዲያገኙ ቢጥሩም በተለይ በግሪክ ስልጣን የያዘው አክራሪው ግራ ፓርቲ ለማሻሻያዎቹ ዝግጁ አይደለም፡፡ አይኤምኤፍና የአውሮፓ ህብረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ብድር እንዲለቁ ይፈልጋል። በፍላጐቱ መሰረት ምላሽ ቢያገኝ ዕዳውን የሚከፍለው ማነው?
አገሮቹ ኢኮኖሚያቸው የሚያገግምበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡ የገንዘብ ብድርን በተመለከተ ቅድመ ሁኔታ አስፈላጊ ነው፡፡ የግሪክን ሁኔታ ስናይ አክራሪነት ብቸኛ መፍትሄ አይደለም፤ ለስለስ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የአለምአቀፍ የገንዘብ ተቋም አባል ለመሆን ተቋሙ ለሚያስቀምጠው ህግ ተገዢ መሆን ይገባል፡፡ ዕዳውን ማነው የሚከፍለው ላልሽው… ከፋዮቹ ዜጎች ናቸው፡፡ እንግዲህ ግሪክ አትሸጥ፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ታክስ በመጣልና በመሳሰሉት መንገዶች ዜጎች ዕዳውን ይከፍላሉ፡፡ አፍሪካ እንደ አህጉር 300 ቢሊዮን ዩሮ ቢሰጣት ምን ያህል መሰረተ ልማት ሊገነባ እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡ ግሪክ 10 ሚሊዮን የማይሞላ ህዝብ ይዛ ይህን ያህል ገንዘብ ነው የጠየቀችው፡፡  ከዚህ አንፃር በአገሪቱ ጠንካራ የሆነ የሀላፊነት ስሜት፣  የተጠያቂነት ስርአት ሊኖር ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ፖለቲካ እየተለወጠ ነው፡ አክራሪ የግራ ፓርቲዎች በግሪክና በስፔይን እንዲሁም አክራሪ የቀኝ ኃይሎች በፈረንሳይና በእንግሊዝ፤ ብሔርተኞች ደግሞ በሀንጋሪ እየተጠናከሩና ምርጫዎችንም እያሸነፉ ነው፡፡ የዚህ አንደምታው ምንድን ነው?
አክራሪ ሀይሎች በአውሮፓ እየተጠናከሩ የመምጣታቸው ጉዳይ ምቾት የሚሰጥ አይደለም። ለዚህ ሁኔታ መከሰት  ብዙ ምክንያቶች አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ አውሮፓ ለአውሮፓውያን ብቻ እንድትሆን እንዲሁም የአውሮፓ የመገበያያ ገንዘብ አውሮፓ ውስጥ ብቻ በስራ ላይ እንዲውል የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡  አውሮፓውያን ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ ባህሎች እንዲሁም  ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ ደስተኞች ያልሆኑ  ወገኖችም አሉ። በኔ አስተያየት አለም አንድ እየሆነ በመጣበት በግሎባላይዜሽን ዘመን የራሴ በሚል ተከልሎ መኖር አይቻልም፡፡ አሁን የሚያስፈልገው የራስን ከልሎ መያዝ ወይም ሌሎችን አግልሎ መኖር ሳይሆን ውህደት ነው፡፡
እኔ “ዘ ፓርላሜንታሪ አሴምብሊ ፎር ዘ ካውንስል ኦፍ ዩሮፕ” አባል ነኝ፡፡ 47 አገሮች በአባልነት ይገኙበታል፡፡ በስደተኞች ጉዳይና በተፈናቀሉ ሰዎች ዙሪያ እንወያያለን፡፡ አክራሪዎቹ እየጠነከሩ ነው፡፡ በግሌ ከባህልና ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ  ግጭቶች መቀነስ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ “ሮም ስትኖር ሮምን ምሰል” ይላል ተረቱ፡፡  የራስ ባህል ይረሳ ማለት አይደለም፡፡ እኔ የዛምቢያን ባህሌን ሳልረሳ የፖላንድን ባህል  ተምሬያለሁ፡፡ ፖላንድ ውስጥ በተካሄደ ጥናት፤ አክራሪዎች ከ7 በመቶ በታች ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ሚዛን ሲኖረው ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡
በምስራቅ አውሮፓ በዘረኝነት ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠሩ አገሮች ውስጥ ፖላንድ አንዷ ናት፡፡ እንዲያውም ፖላንዳውያን ጥቁሮችን “ሙዢን” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ እርስዎ ደግሞ በፖላንድ ፓርላማ ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እስቲ ስለዘረኝነቱ ጉዳይ ይንገሩኝ?
ሙዚን ማለት ኒገር ማለት ነው፡፡ ቃሉ እንደ አጠቃቀሙ ሁኔታ ነው ትርጉም የሚሰጠው። የሚቀርብሽ ሰው ሙዢን ሲልና እንደ ስድብ የሚጠቀምበት ሰው ሲያጋጥም ትርጉሙ ይለያያል። ሙዚን ማለት ቆዳው የጠቆረ ማለት ነው፡፡ ፖላንዳውያን እርስ በርስ ሲጠቀሙበት ችግር የለውም፤ ጥቁር የሆኑ ሰዎች ሙዢን ሲባሉ ግን የሚያስቀይም  ይሆናል፡፡  ይህ ቃል ጥቅም ላይ እንዳይውል የምንፈልገው አሉታዊ ነገር ስላለው ነው፡፡ እኛ ከሙዚኖች በአንድ መቶ አመት ያህል እንደምንርቅ ይነገራል፡፡ ይህ አባባል ሌሎችን ስለሚያስቀይም ጥቅም ላይ ባይውል እንመርጣለን፡፡ እኔ ተማሪ ሆኜ በመጣሁበት ጊዜ ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደማንኛውም ወጣት ተበሳጭቼና ግብግብ ገጥሜ አውቃለሁ፡፡ ያ ማለት ግን ፖላንዳውያን ዘረኞች ናቸው ማለት አይደለም። በመጀመሪያ ምርጫ ተወዳድሬ  እንዳሸነፍኩ ከዋርሶ ድረስ  እኔን ኢንተርቪው ለማድረግ የመጣ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ሰዎችን ቃለመጠይቅ ሲያደርግ፤ “ምን ያስገርምሀል? ከዋርሶ ድረስ መጥተህስ ለምን ቃለ መጠይቅ ልታደርግልን ፈለግህ? እሱ ከኛ ጋር የኖረ የኛ ሰው ነው፤ ስለዚህ  መረጥነው” በማለት መልሰውለታል። “እኛ የመረጥነው ኬለንን እንጂ ነጭ ወይም ጥቁር ብለን አይደለም” ብለውታል፡፡ አንቺ እንዳልሽው ስለ ፖላንድ ከዘረኝነት ጋር ተያይዘው ብዙ ነገሮች ይፃፋሉ፤ ነገር ግን የፖላንድ ፓርላማ እኔና አንድ ናይጄሪያዊን በፓርላማ አባልነት ይዟል።  ይህን ምን ትይዋለሽ?

Saturday, 21 March 2015 10:08

የፀሐፍት ጥግ

ፀሐፊ፤ የበለጠ ገንዘብ እንዴት አገኛለሁ ሳይሆን ብዙ አንባቢያን ጋ እንዴት እደርሳለሁ ነው ማለት ያለበት፡፡
ብሪያን አልዲስ
 ታሪክ ፀሐፊ ይመዘግባል፤ ልብ ወለድ ፀሐፊ ይፈጥራል፡፡
ኢ.ኤ.ፎርስተር
በአርታኢዎች ወይም በሃያሲያን አስተያየት አትዘን፡፡ እነሱ የጥበብ ትራፊክ ፖሊስ ናቸው፡፡
ጊኒ ፎውለር
ግንብን በመሬት ላይ ከመገንባት ይልቅ በአየር ላይ መገንባት የበለጠ እርካታ አለው፡፡
ኢድዋርድ ጊቦን
ስለምታውቀው ነገር ከመፃፍ ይልቅ  ስለሚሰማህ ነገር መፃፍ የተሻለ ነው፡፡
ኤል.ፒ.ሃርትሌይ
ፀሃፊ ጨርሶ እረፍት የለውም፡፡ የፀሐፊ ህይወት አንድም መፃፍ ነው አሊያም ስለሚፅፈው ማሰብ ነው፡፡
ኢዩጂኔ ሎኔስኮ
ጠዋት እነሳለሁ፤ መተየቢያ ማሽኑን እስኪያቃስት ድረስ እቀጠቅጠዋለሁ፤ ከዚያ አቆማለሁ፡፡
ክላረንስ ቡዲንግቶን ኬላንድ
የምንፅፈው ስለፈለግን አይደለም፤ የምንፅፈው መፃፍ ስላለብን ነው፡፡
ሶመርሴት ሟም
ፀሃፊውን ያላስለቀሰ፣ አንባቢውን አያስለቅስም፡
ጆርጅ ሙሬ
ሥራው መናገር ሲጀምር ደራሲው አፉን መጠርቀም አለበት፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
 በትንሽ ድፍረት ማጣት ብቻ ዓለም ተሰጥኦዎችን ታጣለች፡፡
ሲድኒ ስሚዝ
የመጀመሪያው ምዕራፍ የአሁኑን መፅሃፍት ሲያሸጥ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ቀጣዩን መፅሃፍ ያሸጣል፡፡
ሚኪ ስፒላኔ
ሃያሲ መንገዱን የሚያውቅ ግን መኪና መንዳት የማይችል ሰው ነው፡፡
ኬኔዝ ቲናን
ለቃላት ድምፅ ትኩረት ስጥ፡፡
ዴቭ ዎልቨርተን
መፃፍ በወረቀት ላይ ማሰብ ነው፡፡
ዊሊያም ዚንሰር

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ለአቅመ -ሄዋን የደረሰች የደረሰች ሴት ልጅ የነበረቻቸው እናትና አባት
በአንዲት መንደር ይኖሩ ነበር፡፡
ልጅቱ ከቀን ቀን እየወፈረች ሆዷ እየሞላ ትሄዳለች፡፡ የመንደሩ ሰው ሊጠይቃቸው ሲመጣ ጥያቄው

አንድ ዓይነት ሆነ፡፡
አንዷ ትመጣና፤
“እንዴት ዋላችሁ?”
“ደህና እግዚሃር ይመስገን”
“ጤናዎትን እንዴት ከረሙ?”
“አልፎ አልፎ ይጫጫነኝና እተኛለሁ እንጂ ብዙውን ጊዜ ተመስገን ነው ጤናዬን ደህና ነኝ”
እንግዳዋ ትንሽ ታመነታና፤
“እንደው የዚች የልጅዎ ነገር እንዴት ነው?”
እናትየው እንዳላወቀ ሆነው፤
“ምኗ?”
“እንዲያው አወፋፈሯ የጤና ነው ይላሉ?”
“አይ እንዲሁ የልጅ ገላ ሆኖ ባንዴ ወፍራ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤
“እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላማረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤
“እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላመረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
እንዲህ በተከታታይ ሲመልሱ፣ ለመጣው ሁሉ የልጅ ገላ ነው ሲሉ፤ እዳር ሆነው የሚያስተውሉት

አባት በመጨረሻ ተነፈሱ፤
“እናንተ ይሄን ያህል ምን አስጨነቃችሁ?
የምግብም ከሆነ ሲቀንስ እናየዋለን፡፡
የልጅም ከሆነ ሲገፋ እናገኘዋለን!” አሉና ገላገሏቸው፡፡
*   *   *
“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደማለት ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር መደበቅ፣ መሸፋፈኑ አይጠቅምም - ሁሉንም ጊዜ ይገልጠዋልና፡፡ ግልፅነት ዛሬ ወቅታዊ ወረት (fashion) የሆነ ይመስላል፡፡ ስንቶች በአደባባይ እየተናገሩ ጓዳ ጓዳውን ግን የልባቸውን እንደሚሰሩ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ They shout at most against the vices they themselves are guality of ይላሉ ፈረንጆች፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ” እንደምንለው መሆኑ ነው በአማርኛ። ስለመልካም አስተዳደር ያወራሉ፡፡ ግን መልካም አያስተዳድሩም፡፡ ስለፍትህ ያወራሉ ግና የህግን መርህ አይከተሉም፡፡ ስለዲሞክራሲ ይናገራሉ፡፡ ግን ዲሞክራት አይደሉም፡፡ ስለእኩልነት ያወራሉ ግን ወግነው ሰው ይበድላሉ፡፡ በእኩል አያኖሩም፡፡ ስለ እጅ ንፅህና ያወራሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ከሙስና የፀዱ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ግልፅነትን እንደሽፋን ነው የሚጠቀሙበት፡፡ ከእነሱ ጋር መከራከር ከንቱ ነው፡፡ አንድም “ዜጋና ሹም ተሟግቶ ደንጊያና ቅል ተላግቶ” ነው፡፡ አንድም ደግሞ ማርክ ትዌይን እንዲህ ይለኛልና፡- “ከደደብ ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡ ወደ እነሱ ደረጃ ያወርዱህና በልምዳቸው ያሸንፉሃል” የሚለን ለዚህ ነው፡፡ (Don’t argue with stupid people, they will drag you down to their level and then beat you with experience) በትክክለኛው ሜዳ ተጫወት እንደማለት ነው፡፡ ልህነት የሌለበት ግጭት ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ “ተምረህ ተምረህ ደንቆሮ ሆነሃል” ይላሉ መንግሥቱ ለማ፡፡ በዚያው ጽሑፋቸው:-
“አንድ ዓለም ተሰጠ ለአዳም ለሄዋን
ለሁለቱ፤ ተረቱ እንደሚነግረን
…ምንስ ልጆቻቸው ቢረቡስ ቢራቡ
ጥቂቶቹ ጠግበው ብዙዎች ይራቡ
ጥቂቶች ሲያምራቸው ያንሱ ጦርነት
ብዙዎችም ይሂዱ ለመሞት ለዕልቂት!”
ይላሉ፡፡ ስለብዙሃኑ እናስብ ዘንድ ማስገንዘባቸው ነው፡፡ ጥቂቶች በሀብት የናጠጡበት ብዙሃን ይልሱት ይቀምሱት ያጡበት ሥርዓት መቼም በጅቶን አያውቅም፡፡ የናጠጡት የበደሉ የማይመስላቸው ሲሆን ደግሞ የባሰ መደናቆር ነው፡፡ ዳቦው ሳይኖር ለሰልፉ ሲሉ ብቻ ይሰለፉ ነበር እንደሚባሉት ምስኪን ሩሲያውያን እንዳንሆን መጠንቀቅም ብልህነት ነው፡፡ ለምርጫ ዝግጅት እየተደረገበት ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተቃዋሚዎች ለአየር ሰዓትና ለበጀት በሚታገሉበት ባሁኑ ሰዓት፣ አሸናፊው ፓርቲ የለየለት በሚመስልበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ሆነዋል የሚል ይሆነኝ ተብሎ የተቀናጀ መንፈስ ያለበት በሚመስልበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተሳትፈናል ማለት እንደ ድል በተቆጠረበት ባሁኑ ሰዓት፣ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ማለት በቀረበት ባሁኑ ሰዓት…ድል እንደ ዛፉ ብስል ፍሬ ስትርቅ፤ ቀበሮዋ ዘላ ዘላ ፍሬዋን መያዝና ማውረድ ሲያቅታት፤ “ለዛውም ሩቅ ናት፤ ደሞም መራራ ናት” አለች እንደተባለው እንዳይሆን ቆም
ብሎ ማሰብ ለሁላችንም ይበጀናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!!

- ቢል ጌትስ ለ16ኛ ጊዜ መሪነቱን ይዘዋል
- ቻይና በአንድ አመት 71 አዳዲስ ቢሊየነሮችን አፍርታለች
   በየአመቱ የዓለማችንን ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር የሚያወጣው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ባሳለፍነው ሳምንት የ2015ን ምርጥ 500 የዓለማችን ቢሊየነሮችን ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ ለ29ኛ ጊዜ ይፋ ያደረገውን የዘንድሮ የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር በቀዳሚነት የመሩት አሜሪካዊው የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ መስራች ቢል ጌትስ ሲሆኑ፣ አጠቃላይ የሃብት መጠናቸውም 79.2 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው አመት በነበራቸው ሃብት ላይ የ3 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ በማሳየት ለ16ኛ ጊዜ የዓለማችን ቁንጮ ባለጸጋ መሆናቸውን ያረጋገጡትን ቢል ጌትስ፣ በአመቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለበጎ ምግባር በስጦታ መልክ ቢለግሱም፣ ልግስናቸው አተረፈላቸው እንጂ አልቀነሰባቸውም፡፡
እሳቸውን ተከትለው የሁለተኛነትን ደረጃ የያዙት ደግሞ፣ 77.1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያላቸው ሜክሲኳዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም ሄሉ ናቸው፡፡
ሌላኛው ስመጥር አሜሪካዊ ባለሃብት ዋረን ቡፌት በ72.7 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአመቱ የዓለማችን ሶስተኛ ባለጸጋ ተብለዋል፡፡
አመቱ በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች የታዩበት እንደሆነ በሚያሳየው የዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ፣ እስከ 500ኛ ደረጃ የያዙ በድምሩ 1826 ቢሊየነሮች የተካተቱ ሲሆን፣ አለማችን ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ 181 ቢሊየነሮችን አግኝታለች፡፡

 በየዕለቱ የተወሰነ ስኒ ቡና አዘውትሮ መጠጣት ከደም ስር መዘጋት ችግር እንደሚታደግና በሰውነት ውስጥ ያለው የደም ዝውውር በአግባቡ እንዲከናወን በማድረግ ለልብ ህመም ከመጋለጥ እንደሚታደግ በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የኮርያ ተመራማሪዎች በ25 ሺህ ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሰራውን ጥናት ዋቢ በማድረግ ዘገባው እንዳለው፣ በየዕለቱ ከሶስት እስከ አምስት ስኒ ቡና አዘውትረው የሚጠጡ ሰዎች ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል፡
ቡና በልብ ጤንነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተ ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶች የተለያዩ ድምዳሜዎች ላይ እንደደረሱ ያስታወሰው ዘገባው፣ አንዳንዶቹ ቡና ለልብ ህመም ያጋልጣል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለታቸውን ገልጧል፡፡
የኮርያ ተመራማሪዎች ያወጡት የጥናት ውጤት በቡና እና በልብ ጤንነት መካከል ያለውን ትክክለኛ ግንኙነት በተመለከተ ግልጽ መረጃ እንዳልሰጠ የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ አነጋጋሪ መሆን መጀመሩን አስረድቷል፡፡
የብሪቲሽ የልብ ፋውንዴሽን ባልደረባ የሆኑት ቪክቶሪያ ቴለርም፣ የተመራማሪዎቹን የጥናት ውጤት ለማረጋገጥና በቡና እና በልብ ጤንነት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥራት ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡