Administrator

Administrator

ፖለቲከኞች ምን ይላሉ?

የግንቦት 20 በዓል 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር መንግስት አስታውቋል፡፡ ግማሽ ክፍለ ዘመን
ባስቆጠረው የኢህአዴግ መራሹ መንግስት የተመዘገቡት ስኬቶችና ውድቀቶች እንዴት ይገመገማሉ? የግንቦት 20 ትርፍና ኪሳራ
እንዴት ይገለጻል? የተለያዩ የፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ
አንበሴ የሁሉንም ሃሳብና አተያይ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

“ለኔ ግንቦት 20፣ እንደ ማንኛውም ሰኞና ማክሰኞ ነው”    አቶ ግርማ ሠይፉ - የቀድሞ የፓርላማ አባል)

  ግንቦት 1983 ላይ ምናልባት የ23 አመት ወጣት ነበርኩ፡፡ እውነቱን ለመናገር የመንግስት ለውጡ ሲመጣ ምንም የተለየ ነገር አልጠበኩም ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ሲመጡ አገር መምራት ይችላሉ ወይም ይመራሉ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ከራሳቸው አስተሳሰብ እንኳ ስንነሣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በወቅቱ እየተጠላ የመጣውን ሶሻሊዝም ያውም የአልባኒያ ሶሻሊዝም ተከታይና ይሄንኑ ይሰብኩ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ለዚህች ሃገር ይጠቅማሉ ወይም ይህቺን ሃገር ይመራሉ የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ሆኖም በራሳቸው ባይችሉም እንኳን ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ አገሪቷን ወደተሻለ አቅጣጫ ሊመሯት ይችላሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ አቅምም ስለሌላቸው ሌላውን ያሳትፋሉ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡
በሽግግር ቻርተሩ ጊዜ ነፃ ሚዲያ፣ ሳንሱር ቀርቷል የሚሉ ቃላት የተጨመሩበት ስለነበር ጥሩ ነገር ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡
መጨረሻ ላይ ግን ሁሉንም ያሳተፈ ነው በሚል የራሳቸውን ኮንፈረንስ ሲያካሂዱ በዚያኑ ወቅት አንዱ ከሣሽ አንዱ ተከሳሽ ሆኖ የሚቀርብ ሣይሆን ሀገራዊ እርቅ የሚወርድበት ሁኔታን ስለአሸናፊነት ስነልቦና ወርደው ቢያመቻቹ ኖሮ ወደምንፈልገው ምዕራፍ የምንሸጋገርበት እድል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚያ በኋላም ይሻሻላሉ ተብለው ሲጠበቁ ብሶባቸው በ1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ እስኪንገሸገሽባቸው ድረስ ደርሰዋል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ያኔ ያዳናቸው በወቅቱ የተከሰተው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱ ለእድሜያቸው መራዘም መልካም እድል የፈጠረላቸው ይመስለኛል፡፡ ጦርነቱ ተከስቶ ኢትዮጵያውያን አንድ የሚያደርግ ነገር ባይፈጠር ኖሮ  ይገጥማቸው የነበረውን ችግር መቋቋም አይችሉም ነበር፡፡ ያ ለእነሱ አንድ እድል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአለማቀፍ ደረጃም ለመጀመርና ዘልቆ ለመግባባት ጦርነቱ እድል የከፈተላቸውም ይመስለኛል፡፡
ሌላኛው በኢህአዴግ የ25 አመት ጉዞ ውስጥ በጉልህ የሚጠቀሰው የ1997 ምርጫ ነው፡፡
በወቅቱ ከህዝቡ የቀረበባቸውን ተቃውሞ ሊቋቋሙ አልቻሉም ነበር፡፡ አጋጣሚውን ለበጎ መጠቀም ሲችሉ አልተጠቀሙበትም፡፡
 ከዚያ በኋላም “ስልጣናችን የሚያበቃው በመቃብራችን ላይ ነው” ብለው ቆርጠው ተነስተው ይኸው እስከዛሬ አሉ፡፡
የግንቦት 20 ፍሬዎች
ስኬታቸው ይሄ በመሠረተ ልማት አገኘን የሚሉንን ከሆነ እኔ አልስማማም፡፡ ስኬት በቁስ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ሰብዕና እና ነፃነት ላይ የሚመሰረት ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ከተማ ውስጥ ከምናያቸው አስፓልቶች በላይ ከ25 አመት በኋላም 20 ሚሊዮን ህዝብ በእለት ደራሽ እርዳታና በሴፍቲኔት የሚረዳ ህዝብ መኖሩን ነው የማስበው፡፡ ይሄን ሁሉ ጉድ ይዘን ተሣክቶልናል የምንል ከሆነ፣ እንደ ባህላችን ያው “ተመስገን” ብለን መኖር አለብን ማለት ነው፡፡
ከዚህ መለስ ብለን ማየት አለብን ብዬ የማስበው ጦርነት ባይኖር ኖሮ ደርግስ መሠረተ ልማት የሚባለውን መስራት አይችልም ወይ? የሚለውን ነው፡፡ በሚገባ ይሠራ ነበር፡፡ ከዚህች ድሃ ሀገር በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ባይሸሽ ደግሞ ምን ሊሠራ እንደሚችል ማሠብ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ በሚኒልክ ጊዜ ስልክ አልነበረም፤ዛሬ ሞባይል አምጥተናል ሲሉ ይገርመኛል፤ ሞባይልን እነሱ ባያመጡትም ማንም ሊያመጣው የሚችል ነው፡፡ ዘመኑ የፈቀደው የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ባይኖርም ሞባይል ይኖር ነበር፡፡ መንገድ ሠርተናል የሚለውም ቢሆን ጣሊያንም በሚገባ መንገድ ሠርቷል፡፡ በ5 አመቱ ብዙ መንገድ ሠርቷል፡፡ ስለዚህ ጣሊያን ይሻለን ነበር ልንል ነው?
መንግሥት ሲቀየር የነበርዎት ተስፋ ምን ነበር? ተስፋዎት ከ25 ዓመት በኋላ ተሟልቶ አግንተውታል?
እኔ እዚህ ሀገር የምኖረው በየዓመቱ ተስፋ ስላለኝ ነው፡፡ እኔ ተስፋ አልቆርጥም፤ በአገሪቱ ውስጥ ነገሮች እንዲሻሻሉ የራሴን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብኝ ብዬም አምናለሁ፤ በግሌም ከመሰሎቼ ጋር ሆኜም፡፡ የኔ ልጆች፤ “ይህቺን ሃገር እንዲህ አድርገው ያስረከቡን አባቶቻችን ናቸው” ብለው እንዲወቅሱኝ አልፈልግም፡፡ እንዲለወጥና እንዲሻሻል ጥረት አደርጋለሁ፡፡ መለወጥና ማሻሻል ባልችል እንኳ ልጆቼ፣ “አባቴ ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ ነው እንደዚህ አይነት ሀገር ያስረከበኝ” እንዳይሉኝ በግሌ ሙከራ አደርጋለሁ፡፡ እኔ እያንዳንዱ ሰው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለለውጥ የራሱ ድርሻ አለው የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ግን ብንተባበር ለውጡን እናፋጥናለን፡፡
ለኔ ግንቦት 20 እንደ ማንኛውም ሠኞና ማክሰኞ ነው፡፡ በትግል ለውጥ ለማምጣት ግንቦት 20ን መጠበቅ አያስፈልገኝም፡፡ አንድ ሴትዮ ምን አሉኝ መሰለህ? “ኢህአዴግ ያመጣልን ለውጥ ሴት ልጆቻችን በቪዛ ውጭ ሀገር እንዲሄዱ ማድረግ ብቻ ነው፡፡” እኔም እሱ ባይመጣ ኖሮ ይቀርብን ነበር የምለው ዛሬ ላይ ያለ አንድም ነገር የለም፡፡ አሁን ያሉት ነገሮች ሁሉ እሱ ባይመጣም ምናልባትም በተሻለ መጠን የሚመጡና የሚፈጠሩ ነገሮች ናቸው፡፡ እንደውም የተሻሉ ብዙ ነገሮች ይኖሩ ነበር፡፡ ሞባይልም፣ ቴሌቭዥንም ሌላውም እነሱ ቢኖሩም ባይኖሩም ይመጣሉ፡፡ እኔ የሚቆጨኝ ያልመጡ ብዙ ነገሮችን ሳስብና የተበላሸውን ነገር ሳስተውል ነው፡፡
ዛሬ አንድ ሚኒስትር ሲሾም ስሙን ለመስማትና በዘር ለመፈረጅ እንድንጣደፍ ያደረጉን እነሱ ናቸው፡፡ መታወቂያችን ላይ ብሄር የፃፉልን እነሱ ናቸው፡፡ በየእለቱ ስለ ብሄር እንድናስብ አድርገውናል፤ እነዚህ ሁሉ ጥሩ አይደሉም፡፡

========================================

“አገሪቱ የባህር በር ያጣችው ከግንቦት 20 በኋላ ነው”     አቶ ልደቱ አያሌው፤ ፖለቲከኛ)

የመንግስት ለውጡ ሲመጣ የተለያዩ ጭንቀቶች ነበሩ፡፡ ይህቺ ሀገር ወደ ሁከት ሜዳ ትሸጋገራለች የሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከሚያራምዳቸው አንዳንድ አቋሞች በመነሳት ደግሞ ሀገሪቱ ትበታተናለች የሚል ስጋትም ነበር፡፡ እኔም እንደ ማንኛውም የወቅቱ ወጣት በነዚህ ሀሳቦች መሃል ነበርኩ፡፡
በመጀመሪያ ግንቦት 20 ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ የተተካበት ነው፡፡ በአንፃራዊነት በሃገሪቱ ውስጥ ለረዥም አመታት በርካታ ወጣቶችን የጨረሰው ጦርነት የቆመበት ጊዜ ነው፡፡ እሱ በራሱ ስኬት ነው፡፡ ሁለተኛው ውጤት በሀገሪቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ተቀባይነት ያገኙበት ጊዜ ነበር፡፡ የነፃ ፕሬስ፣ የብዙሃን ፓርቲ አሰራር ቢያንስ በህግ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል፡፡ ቆይቶ ቢሆንም የኢኮኖሚ እድገትም የታየው ከግንቦት 20 በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡
 ያሳጣን ብዬ የማነሳው አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ የተነጣጠለው በግንቦት 20 አማካኝነት መሆኑ ነው፡፡ በታሪኳ የባህር በር ያጣችውም ከግንቦት 20 በኋላ ነው፡፡ የአንድነት ስሜት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአካባቢያዊ ስሜት የበለጠ ቦታ ያገኘበት ጊዜ የመጣው በግንቦት 20 ነው፡፡ የሀገሪቱ አንድነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ እስካሁን ዘልቋል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ቅራኔዎችና ግጭቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በሂደትም ደግሞ ስልጣን በአንድ ፓርቲ የበላይነትና ሁለንተናዊ ቁጥጥር ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉት ነገሮች ሁሉ የህብረተሰቡ አመለካከቶች ነፀብራቅ ሳይሆን የአንድ ፓርቲ ነፀብራቅ ነው በአጠቃላይ የህዝቡን ህይወት እየወሰነ ያለው፡፡ በህገ መንግስቱ የሰፈሩና በጎ ናቸው ያልናቸው ነገሮች በተግባር ላይ የውሃ ሽታ የሆኑበት አጋጣሚም በሂደት ተፈጥሯል፡፡
 አንፃራዊ ሠላም መገኘቱ በሌላ ጎኑ በበጎ የሚታይ ነው፡፡ ይሄን ስል ጦርነት የለም ማለቴ አይደለም፡፡ ግንቦት 20 ማክበር ከጀመርን 25 ዓመት ሆኖናል፡፡
በዚህ መሃል በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማህበረሰብ እድገት፣ በፍትህ … ዘርፍ ያሉ ጉዳዮች በሰፊው መገምገም አለባቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የሚያሳስበው የሀገሪቱ አንድነት አደጋ ላይ መሆኑ ነው፡፡

==================================


“ድርጅታችን ለስርአቱ አደጋ የሆኑትን በተሃድሶ አጥርቷል”     (አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው፤ የቀድሞ ታጋይ)
በእነኚህ 25 ዓመታት ውስጥ በርካታ ፖለቲካዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ድሎች ተመዝግበዋል፡፡ እንደሚታወቀው የስርአት ለውጥ ነው የተደረገው፡፡ ያለፉት መንግስታት ህዝቦችን በተለያየ መልኩ የሚጨቁኑ ነበሩ፡፡ ያንን የጭቆና ስርአት የገረሰሰ ድል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰብአዊና ዲሞክራሲዊ እድሎቻቸውን እንዲጠቀሙ፣ የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን የሚችሉበት፣ የግልም ሆነ የቡድን መብቶቻቸው እንዲከበር ያደረገ ነው፡፡
በዚያው መጠን ሀገራችን ከድህነት አረንቋ እንድትወጣ እያደረገ ያለ ድል ነው፡፡ በድህነትና በኋላ ቀርነት የምትታወቀውን ሀገራችንን በልማት እንድትታወቅ አድርጓል፡፡ የልማት አቅጣጫን በመቀየስ በሀገሪቱ ልማት የሚፋጠንበትና ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል መሰረት የተጣለበት ቀን ነው፡፡ በማህበራዊ መስኩም እንደዚሁ ዜጎች የሀገሪቱ አቅም በፈጠረው መጠን ከትምህርት፣ ከጤና፣ ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ ሰራተኞች የላባቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ ጥቅማቸው እንዲከበር መሰረት የተጣለበት ቀን ነው፡ በጨቋኝ ስርአት ስር የነበረን ህዝብ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሻገረ ቀን ነው፡፡
የሽግግር መንግስቱ ቻርተር የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች ያሳተፈ ነበር፡፡ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፕሬስ ነፃነት የታወጀበት እለት ነው፡፡ ኢኮኖሚውም ቢሆን ግብርና መር የሆነ ፖሊሲ ወጥቶ ሀገሪቱን ከውድቀት ታድጓል፡፡ ወደ እድገት ሊያመራ፣ የሠለጠነ የሰው ሃብት ሊያፈራ የሚችል ህገ መንግስት መሰረት የተጣለበት ቀን ነበር፡፡ በነዚህ አመታት አብዛኛውን ህዝብ ከድህነት ያወጣ፣ መሰረተ ሰፊ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡን ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ በጋራ የፌደራል ስርአት ተፈጥሮ፣ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የቡድን መብት ተከብሯል፡፡
በዚያው ልክ ባለፉት 25 ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችም አሉ፡፡ የህዝቡ ተጠቃሚነት እየሰፋ በሄደ ቁጥር በጣም ብዙ ፍላጎቶች ይፈጠራሉ፡፡ ጠያቂና ሞጋች የሆነ ህብረተሰብ እየተፈጠረ ነው ያለው፡፡
የመንግስት መዋቅርን አለ አግባብ ለመጠቀም የተደረጉ ሙከራዎች ታይተዋል፡፡ ድርጅታችንም ለስርአቱ አደጋ የሆኑትን በተሃድሶ አጥርቷል፡፡ አሁንም በመልካም አስተዳደርና በኪራይ ሰብሳቢነት የሚታዩ ችግሮች የስርአቱ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ኢኮኖሚው ባደገ ቁጥር በዚያው ልክ ፈተናዎቹ ውስብስብ እየሆኑ ነው የሄዱት፡፡ 25 ዓመቱን ሙሉ እንዲህ በቀላሉ አልዘለቅንም፡፡ እየታገልን ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ትግላችን ቀጥሎ እቺን ሀገገር ወደ ተሻለ ምዕራፍ የማሸጋገር ስራ ይሰራል፡፡ ሀገራችን ከኋላቀርነት ወጥታ የእድገት ማማ ላይ የምትደርስበትን አቅጣጫ ስለያዘች ደስተኞች ነን፡፡ በቀጣይ ጉዟችን ፈተናዎችን እያለፍን የታፈረች፣ የተከበረችና ህዝቦቿ በነፃነት የሚኖሩባት ሀገር እንገነባለን፡፡ በዚህ መንፈስ ነው የምናከብረው፡፡

=================================

“ኢህአዴግ በ25 ዓመት ወደ ቅቡልነት አልተሸጋገረም”      (ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤የፍልስፍና ምሁር

የግንቦት 20 በአል 25ኛ ዓመት ሲታሰብ፣ ያለፉትን 25 ዓመታት በሶስት ዘርፎች መገምገም ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ከዲሞክራሲ አንጻር፣ በነዚህ 25 ዓመታት ውስጥ ስርአቱ የዲሞክራሲ ጅማሮ ላይ ነው ቢባልም ከጉልበት ወደ ቅቡልነት ሲሸጋገር አላየንም፡፡ አልተሸጋገርንም፡፡
ይልቁንም ወደ ፈላጭ ቆራጭነት (አውቶሪቶሪያን) የበለጠ ተሸጋግሯል፡፡ ሁለተኛ በፌደራሊዝም ዙሪያ ጅማሮው በጎ የሚባል ነበር፤ኋላ ላይ ግን ፌደራሊዝሙ ቀርቶ ወደ ብሄረሰብ ተኮር አሃዳዊነት (ethnic totalitarianism) ተሸጋግሯል፡፡
የተወሰኑ ክልሎች አሉ፤በአሃዳዊ ስርአት የሚተዳደሩ፡፡ ሶስተኛ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ጅምሩ ጥሩ ነበር፤ኋላ ላይ የሙሰኛው ሲሳይ ሆነ እንጂ፡፡ ሙሰኛው እየበላው ነው ያለው፡፡ ሙሰኛው የደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ዝም ቢባልም  ጠንክረው እናሻሽል ቢሉም ስርአቱን የሚያፈርስ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ገብቷል ብለን ልንደመድም እንችላለን፡፡ያሉትን ማህበረ-ፖለቲካዊ  ቅራኔዎች ከባድ የሚያደርጋቸው ከኋላ የወረሳቸው ሳይሆን ራሱ የፈጠራቸው ችግሮች ፈጠው ሲመጡ አደጋው የከፋ መሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደሚያወራው ቢሰራ ኖሮ ከየአቅጣጫው ጥያቄ ባልተነሳ ነበር፡፡   

አደጋዎቹ 100 ያህል ሰዎችን ለሞት ዳርገዋል
ጎርፉ ተጨማሪ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊያፈናቅል ይችላል

   በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ከ20 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁንና መንግስትም 100 ያህል ዜጎች በአደጋዎቹ ለሞት ተዳርገዋል ማለቱን አልጀዚራ ዘገበ፡፡
በአገሪቱ በመከሰት ላይ ያሉት የጎርፍ አደጋዎች ዜጎችን ከማፈናቀል ባለፈ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች እርዳታን በማከፋፈል እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር የኢትዮጵያ ተወካይ ፖል ሀንድሊም የተፈጥሮ አደጋዎቹ በቀጣይ ሰብሎችንና እንስሳትን ከማውደም ባለፈ ዜጎችን ለከፋ ችግር ሊያጋልጡ ይችላሉ ማለታቸውን ገልጧል፡፡
የእርዳታ ድርጅቶችም የጎርፍ አደጋዎቹ ቀጣይ እንደሚሆኑና ሌሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊያፈናቅል እንደሚችል ግምታቸውን መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የተፈጥሮ አደጋዎቹ የተከሰቱባቸው አንዳንዶቹ አካባቢዎች የድርቅ ተጎጂ መሆናቸውንና ዜጎችን ለተጨማሪ ችግር መዳረጋቸውን አስረድቷል፡፡

የዘንድሮ የግንቦት 20፣ ሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዮ በአል - ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችንና ፈተናዎችን በመገምገም እንደሚከበር መንግስት የገለፀ ሲሆን አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች የግንቦት 20ን ትሩፋቶች በመተቸትና በማወደስ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በሰጡት አስተያየት፤ በ1983 ዓ.ም ለውጡ ሲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት አመራር ተፈጥሮ፤ ሀገሪቱ ለውጥ ታመጣለች የሚል ተስፋ ሰንቀው እንደነበር ጠቁመውና ዛሬ ላይ ሆነው ያለፈውን 25 አመት ሲገመግሙት ግን ያንን ተስፋቸውን በተግባር እንዳላዩት ይናገራሉ፡፡ የአንድ መንግስት ስኬታማነት በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ እድገት ብቻ አይመዘንም ያሉት አቶ ግርማ፤ ዋናው ስኬት የሰው ልጅ ሠብአዊ መብትና ነፃነት ሲከበር ነው ብለዋል፡፡ የኢኮኖሚው እድገትም ቢሆን ከሀገሪቱ ህዝብ 20 ሚሊዮን ያህሉን ከእለት ተረጅነት አላወጣም ሲሉ ተችተዋል- አቶ ግርማ፡፡
“ባለፉት 25 ዓመታት ቃልና ተግባር አልተገናኙም” ያሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ የግንቦተ 20 ትልቁ ትርፍ የደርግ መንግስት መወገዱ ነው ብለዋል፡፡ የመንግስት ለውጡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፤ ሆኖም ባለፉት 25 አመታት ይህ እንዳልተሳካ አስረድተዋል፡፡
“ግንቦት 20 በኢኮኖሚ እድገት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል” ያሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በዚያው ልክ የሀገሪቱን አንድነት እስከዛሬ ድረስ ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም በተጨማሪ ሀገሪቱን ወደብ አልባ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የአንድ ፓርቲ የስልጣን የበላይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረና ነፃ ሚዲያዎች እየደበዘዙ መምጣታቸውንም አቶ ልደቱ ተችተው ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ የቀድሞው ታጋይና አመራር የሆኑት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በ25 አመታት ውስጥ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊውና በፖለቲካዊው ዘርፍ በርካታ ድሎችና ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በአሁን ወቅት ዋነኛ አደጋ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም መንግስት በጠንካራ ትግል ላይ ነው ብለዋል፡፡   “ግንቦት 20 የመንግስት ሣይሆን የስርአት ለውጥ ነው ያመጣው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤  ስርአቱ እየተከተለ ያለው መሠረታዊ አቅጣጫ ትክክል መሆኑን ጠቁመው፤ የተገኙ ጠንካራ ድሎች የበለጠ የሚጠናከሩበትና ድክመቶች የሚታረሙበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል፡፡ ይሄን ስርአት ካለፉ ስርአቶች ጋር ማነፃፀር ተገቢ አለመሆኑን የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ “ይሄ መንግስት ነገ ከነገ ወዲያ ሊሄድ ይችላል፤ የስርአት ለውጡ ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡ 

• ከ2 ሺህ በላይ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑ ታውቋል
• ግጭቱን ተከትሎ ለ3 ቀናት ት/ቤቶች ተዘግተዋል

    በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ገርጂ ወረገኑ በተባለ አካባቢ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ ተገንብተዋል የተባሉ ቤቶችን ለማፍረስ በተሰማራ የደንብ ማስከበር ግብረ ኃይልና በነዋሪዎች መካከል  ውዝግብ ተነስቶ ከፖሊስ ጋር በተከሰተ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በግርግሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ሲናገሩ የፖሊስ ምንጮች በበኩላቸው፤ 3 ፖሊሶችን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ከመድረሱ በቀር የሞተ ሰው ስለመኖሩ አልተረጋገጠም ብለዋል፡፡ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታልም ከግርግሩ ጋር በተገናኘ ያስተናገደው አስክሬን አለመኖሩን አስታውቋል፡፡ በቦታው ላይ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተሰሩ ናቸው ያላቸውን ከ2 ሺህ በላይ ቤቶች ለይቶ በማፍረስ ላይ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ኃላፊዎች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ “ከገበሬው ላይ በውድ ዋጋ የገዛነው መሬት ላይ ጥሪታችንን አሟጠን የሰራነው ቤታችን አማራጭ ሳይሰጠን በኃይል በመፍረሱ ሜዳ ላይ ተበትነናል” ሲሉ አማረዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ኃይሎች ከአፍራሽ ግብረ ኃይሉ ጋር በመሆን ቤቶቹን ማፍረስ መጀመራቸውን የሚገልፁት ተጎጂዎቹ፤ በኃይል እቃችንን እንድናወጣ ከተደረገ በኋላ በ7 የመቆፈሪያ ከባድ ማሽኖች (ስካቬተሮች) ቤቶቹን ማፍረስ ጀመሩ ይላሉ፡፡ እስከ ትናንት ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ የቤቶቹን ፍራሽ፣ ቆርቆሮዎችን ጨምሮ በደንብ ማስከበሮች ተጭኖ ተወስዷል ብለዋል፡፡ በነዋሪዎችና በፖሊስ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎም ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ በሚኖርበት በዚህ አካባቢ ከረቡዕ ጀምሮ መንቀሳቀስና ከቤት መውጣት የሚቻል ባለመሆኑ ለ3 ቀናት ት/ቤቶች መዘጋታቸውንና ትምህርት መቋረጡን ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ውዝግብ ከባድ የመሳሪያ ተኩስ እንደነበር የጠቀሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ አምቡላንሶች የተጎዱ ሰዎችን ሲያመላልሱ እንደዋሉ ያስታውሳሉ፡፡ ምንጮቻችን፤ ከቤት መውጣት ባለመቻላችን እስከ 12 ሰው መሞቱን ከመስማታችን በቀር ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉ ሲሆን የከተማዋ ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ም/ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተሰማ ነጋሽ በበኩላቸው፤ “ፖሊስ ላይ መጠነኛ ድንጋይ ከመወርወሩ በቀር የተባለውን ያህል ጉዳት አልደረሰም፣ ጉዳት ደረሰብኝ ያለ አካልም የለም” ብለዋል፡፡
ቤታቸው እየፈረሰባቸው መሆኑን ለአዲስ አድማስ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ አብዛኞቹ በቀን ሰራተኝነት የሚተዳደሩ ሲሆን ከገበሬው ላይ ከ50-100 ካሬ ሜትር ቦታ፣ አንዱን ካሬ ሜትር እስከ 1500 ብር ሂሳብ እየገዙ፣ ከ20-30 ቆርቆሮዎችን የፈጁ ቤቶችን ቀልሰው ሲኖሩ እንደ ነበር ገልፀዋል፡፡ አካባቢው መሰረተ ልማት ያልተሟላለት መሆኑን የሚጠቅሱት ነዋሪዎቹ፤ “ከዛሬ 6 እና 7 አመታት በፊት ቦታውን ገዝተን ቤት ስንሰራ ወረዳውም ሆነ ክ/ከተማው ህገወጥ ናችሁ አላሉንም ነበር” ሲሉ ያማርራሉ፡፡ የቀን ስራ ሠርተን ያጠራቀምነውን ገንዘባችንን በቦታ ግዢና በቤት ግንባታው ላይ ካዋልንና ተረጋግተን መኖር ከጀመርን በኋላ መንግስት ቤታችንን ማፍረሱ ተስፋ-ቢስ አድርጐናል የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ መውደቂያ አጥተን ከነቤተሰባችን ሜዳ ላይ ተበትነናል ብለዋል፡፡
የወረዳው የስራ ኃላፊዎች ባለፈው ሚያዚያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም በቦታው ተገኝተው ቤቶቹ ህገ - ወጥ መሆናቸውን ሲነግሩን እንዳያፈርሱብን ብንማፀንም አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡንም ነበር ያሉት ቅሩታ አቅራቢዎቹ፤ እንዳልሰጧቸውና ባለፈው ረቡዕ በድንገት ቤቶቹን ማፍረሣቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ቤቶቹ በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተገነቡ በመሆኑ ህጉን ተከትዬ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል፡፡ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ም/ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተሠማ፤ ከ2ሺህ በላይ ቤቶች በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተሠሩ ሆነው በመገኘታቸው እንደሚፈርሱና በቀጣይም ተጨማሪ ህገ-ወጥ ቤቶችን የመለየት ስራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በህገ መንግስቱ መሬት መሸጥ መለወጥ እንደማይቻል የጠቀሱት ኮማንደሩ፤ ግለሰቦቹ በየትኛውም ህግና ደንብ ህገ-ወጥ ናቸው ይላሉ፡፡ ህጋዊ መሆን የሚችሉበት መንገድም እንደሌለ አክለው ገልፀዋል፡፡  


ንብረትነቱ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበረውና ባለፈው ህዳር ወር ላይ በታዋቂው ዓለምአቀፍ አጫራች ኩባንያ ክርስቲ አማካይነት በጨረታ ሊሸጥ በዝግጅት ላይ ሳለ፣ የንጉሱ ቤተሰቦች ባሰሙት ተቃውሞ ሳቢያ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታግዶ የቆየው 1 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የወርቅ ሰዓት በቅርቡ ዳግም ለጨረታ ሊቀርብ እንደሚችል ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
ንጉሱ ከአንድ ጣሊያናዊ ባለሃብት በስጦታ እንዳገኙት የተነገረለትና ፓቴክ ፊሊፒ የሚል ስያሜ ያለው ይህ እጅግ ውድ የወርቅ ሰዓት፣ ጄኔቫ ውስጥ ለጨረታ ሊቀርብ ሲል የንጉሱ ቤተሰቦች “ሰዓቱ ከንጉሱ የተዘረፈ ነው፤ ሊመለስልን ይገባል” በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ የጄኔቫ ፍርድ ቤት ሽያጩ ለጊዜው እንዲሰረዝ በመወሰን ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም ሰዓቱ የንጉሱ ቤተሰቦች እንዳሉት ተዘርፎ የተወሰደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ አለማግኘቱንና በመጪዎቹ ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም ሰዓቱን ለሽያጭ እንዳያቀርብ በአጫራቹ ድርጅት ላይ የጣለውን ጊዚያዊ እግድ ያነሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ኦሊቨር ጆርኖት ተናግረዋል፡፡
ጊዚያዊ እግዱ የሚነሳ ከሆነ አጫራቹ ድርጅት ሰዓቱን ዳግም ለጨረታ ሊያቀርበው እንደሚችል የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም በንጉሱ ቤተሰቦች፣ በአጫራቹ ድርጅትና ሰዓቱን ከንጉሱ በስጦታ ያገኘነው ስለሆነ ባለቤትነቱ የኛ ነው በሚሉት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም አቡድ ቤተሰቦች መካከል ቀጣይ የባለቤትነት ውዝግብ ሊፈጥር እንደሚችል ገልጧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን አቪየሽንን የ2016 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማት ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደ ስነ-ስርዓት መቀበሉን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ በፋይናንስ እንቅስቃሴና ትርፋማነት፣ በረራን በማዘመን፣ የበረራ መስመር ትስስርን በማስፋፋት፣ በአጠቃላይ የደንበኞች እንክብካቤና በአህጉሪቱ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ልማት አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ በአመቱ ባስመዘገበው የላቀ ውጤት ለሽልማት መብቃቱ ተነግሯል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማቱን የተቀበሉት የአየር መንገዱ ቺፍ ኦፐሬቲንግ ኦፊሰር አቶ መስፍን ጣሰው፤ ሽልማቱ አየር መንገዱ ላለፉት 70 አመታት አፍሪካን አንድ ለማድረግና ከተቀረው አለም ጋር ለማቀራረብ በቁርጠኝነት መስራቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡ ሽልማቱን ያበረከቱት የአፍሪካን አቪየሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኒክ ፋዱግባ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ መሪነቱን ይዞ መቀጠሉንና ለአፍሪካ ትልቅ የኩራት ምንጭ መሆኑን በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

    የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፉ ዳኘው የሜቴክ
ፕሮጀክቶችን የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ከትናንት በስቲያ በተመረቀበት ወቅት ስኳር ፕሮጀክቶችን
አስመልክቶ በተለይ በአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ዘጋቢ ፊልም መስራት ያስፈለገበት ምክንያት መነሻው ምንድነው?
ጥናት ሰርቼ ነበር፡፡ የታገልኩለት ስለሆነ ጥናት ሰርቼ ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡ ጽሑፉ፣ ከጋዜጠኛዋ ፍፁም የሺጥላ የዘጋቢ ፊልም መነሻ ሀሳብ ጋር በጣም የተቀራረበ ስለነበር ጽሑፉን ሰጠኋት ያንን የማዳበር ስራ፤ ከመስራት በስተቀር ተነሳሽነቱ የጋዜጠኛዋ ነው፡፡ዘጋቢ ፊልሙ ለመስራት ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ ወሰደ? ፊ ልሙን ላይ፤ የብረታብረት ኮርፖሬሽን ስራዎች ሁሉውጤታማ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው ተብሏል፡፡ ግን በፓርላማ እና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ደግሞ፣ በተለይ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ አገሪቱ ለብዙ ወጪ ተዳርጋለች ተብላችሁ ተተችታችኋል፡፡ የመጀመሪያውን ጥያቄ ስንመለከት፣ ፊልሙን ያዘጋጁዜጐች፣ ከፊልሙ የጽሑፍ ዝግጅት ጀምሮ፣ በቀረፃ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ሲሰሩ ከሶስት  ወር በላይ ሳይወስድ አይቀርም፡፡ መነሻ ሃሳቦቹ ከዚያ ቀደም ይላሉ፡፡ ብዙም ደክመውበታል፡፡ሁለተኛ ጥያቄሽን በተመለከተ፣ በዋናነት ማለት የምፈልገው፣ ምንም ክስ ቢነሳም፣ ለእኔ ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውና የሚመራው የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ፣ የሚሳካ መሆኑ ነው፡፡ በአንዳንድ ሰዎች ክስ ቢነሳም፣ ድክመታችንን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በዚያው ልክ፣ ንካሬያችንንም የሚያሳይ አይደለም፡፡ዋናው ጉዳይ እኛ ድክመት ቢኖርብንም ባይኖርብንም፣ የልማታዊ ኢኮኖሚ አቅጣጫ አይቆምም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ያድጋሉ፡፡ እኔ ካጠፋሁ ልቀጣ እችላለሁ፡፡ ተቋማት ግን ይቀጥላሉ፤ መቀጠልም አለባችሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ፣ በግሌ አስተያየት፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ውድቀት
አለው ብዬ አላምንም፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን የወደቀበት ምክንያት በእንቶኔ ነው በእከሌ ነው
ቢባልም፣ አይገባኝም፡፡

አንጋፋው ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህና “ዘመናይ ማርዬ” በተሰኘው አልበሙ የሚታወቀው
ልጅ ሚካኤል የሚያቀነቅኑበት “አዲስ ኮንሰርት” የዛሬ ሳምንት ከሚሊኒየም አዳራሽ ጀርባ በሚገኘው ፋና ፓርክ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ የጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ታደሰ ታምራት አስታወቁ፡፡ ከሚካኤል በላይነህና ከልጅ ሚካኤል በተጨማሪ ያሬድ ነጉ (የመርካቶ አራዳ)፣ ዳዊት ነጋ (ባባ ኤለን)፣ አስገኘው አሸኮ (ዲንዴሾ) እና በሀይሉ ባዩ (በሃይሉ ማታ) ታዳሚውን እንደሚያዝናኑ የገለፁት አቶ ታደሰ፤ ዲጄ ኪንግስተን (ወዝወዝ አዲስ)፣ ዲጄ ሼሪ፣ ዲጄ የሚ እና ዲጄ ሮፊም መድረኩን ያደምቁታል ብለዋል፡፡ ኮንሰርቱ የፌስቲቫል ይዘት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን ሁለት እውቅ ስጋ ቤቶች፣ ስምንት ሬስቶራንቶችና ስድስት ባሮች ይሳተፉበታልም ተብሏል፡፡ የመግቢያ ዋጋ እስከ አርብ 12 ሰዓት ለሚገዙ መደበኛው 200 ብር፣ ቪአይፒ 500 ብር ሲሆን በዕለቱ ትኬት ለሚገዙ መደበኛው 300 ብር እንደሚሆንና ቪአይፒው ላይ ጭማሪ እንደማይደረግ ተነግሯል፡፡ ቦሌ የሚገኘው ፋና ፓርክ 10ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው የተገለፀ ሲሆን ይህም ህዝቡ ሳይጨናነቅ እንደ ልቡ እንዲዝናና ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያ የኮንሰርቱ የክብር ስፖንሰር እንደሆነ ታውቋል፡፡

      የገጣሚ ዮሐንስ ሞላ ሁለተኛ ስራ የሆነው “የብርሃን ሰበዞች” የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ከነገ
በስቲያ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ከምሽቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃል፡፡በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ውስጠ ወይራ የሆኑ ከሰባ በላይ ግጥሞችን ያካተተው መጽሐፉ፤ በ110 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ46 ብር፣ ለውጭ አገራት በ18 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ከመጽሐፉ የተመረጡ ግጥሞች የሚነበቡ ሲሆን ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያንም ግጥሞቻቸውን ለታዳሚው እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የግጥም መድበሉን ሊትማን መጽሐፍት መደብር ያከፋፍለዋል ተብሏል፡፡
ዮሐንስ ሞ ላ ከ ዚህ ቀ ደም በ 2005 ዓ .ም “የብርሃን ልክፍት” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ለአንባቢ ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን “ጠይም በረንዳ” በተሰኘው የራሱ ጦማር ላይ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በመፃፍ ይታወቃል፡፡ ገጣሚውበተጨማሪም የዘፈን ግጥሞችን የሚጽፍ ሲሆን ቀደም ሲ ል በ ግጥም የ ተሳተፈበት የ ፀደንያ ገ / ማርቆስ ዘፈን፤ ሁለት የአገር ውስጥ፣ አንድ አህጉር አቀፍ ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡

Saturday, 14 May 2016 13:44

የዘላለም ጥግ

ስለ አመራር)
• ድርጊትህ ሌሎችን የበለጠ እንዲያልሙ፣
የበለጠ እንዲማሩ፣ የበለጠ እንዲሰሩና
የበለጠ እንዲሆኑ ካነቃቃ አንተ መሪ ነህ፡፡
ጆን ኩይንሲ አዳምስ
• መሪ ማለት መንገዱን የሚያውቅ፣ በመንገዱ
የሚጓዝና መንገዱን የሚያሳይ ሰው ነው፡፡
ጆን ሲ.ማክስዌል
• በበግ የሚመራ የአንበሶች ሠራዊት
አያስፈራኝም፤ እኔን የሚያስፈራኝ በአንበሳ
የሚመራ የበጐች ሠራዊት ነው፡፡
ታላቁ እስክንድር
• ብርሃኑን ልታሳያቸው ካልቻልክ፣ ሙቀቱ
እንዲሰማቸው አድርግ፡፡
ሮናልድ ሬገን
• ስህተት ፈላጊ ሳይሆን መፍትሔ (መድሃኒት)
ፈላጊ ሁን፡፡
ሔነሪ ፎርድ
• ሰዎች በመሪና በአለቃ መካከል ያለውን
ልዩነት ይጠይቃሉ፡፡ መሪ ይመራል፤ አለቃ
ይነዳል፡፡
ቴዮዶር ሩዝቬልት
• እሴቶችህ ግልጽ ሲሆኑልህ ውሳኔዎችን
መወሰን ይቀልሃል፡፡
ሮይ ኢ ዲዝኒ
• ራዕይ ከሌለ ተስፋ የለም፡፡
ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
• መሪነት፤ ራዕይን ወደ እውነታ የመተርጐም
አቅም ነው፡፡
ዋረን ቤኒስ
• ለውጤት በቅጡ ከተጨነቅህ፣
በእርግጠኝነት ታሳካዋለህ፡፡
ዊሊያም ጄምስ
• ማሰብህ እንደሆነ አይቀርም፤ ስለዚህ ለምን
በትልቁ አታስብም?
ዶናልድ ትረምፕ
• ተነሳሽነት ከሌላቸው፣ መሪዎች በአመራር
ቦታ ላይ የተቀመጡ ተራ ሠራተኞች ናቸው።
ቦ ቤኔት
• የዛሬ አንባቢ፣ የነገ መሪ ይሆናል፡፡
ማርጋሬት ፉለር
• ኦርኬስትራን መምራት የሚሻ ሰው፣
ጀርባውን ለጀማው መስጠት አለበት፡፡
ማክስ ሉቻዶ