Administrator

Administrator

 1700 ስደተኞች በ20 ዩኒቨርሲቲዎች በነፃ እየተማሩ ነው

     ከ850 ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ማስተናገዷ ያስመሰገናት ኢትዮጵያ፤ የዘንድሮውን የዓለም የስደተኞች ቀን በዓል የተመድ የስደተኞች ኮሚሽነር በተገኙበት የፊታችን ማክሰኞ በጋምቤላ ታስተናግዳለች ተብሏል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ በማስተናገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በስድስት የሀገሪቱ ክልሎች 27 የስደተኛ መጠለያዎችን አቋቁማ ማስተናገዷ እውቅና ተሰቶት “we
stand together with refugees” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን በዓል እንድታስተናግድ እድል ማግኘቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
“ስደተኞች እንደሀገሬው ዜጎች የሚኖሩባት ሀገር ነች ኢትዮጵያ” ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በ20 ዩኒቨርሲቲዎች ለ1700 ስደተኞች ነፃ የትምህርት እድል ተሰጥቷቸው በመማር ላይ መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሉን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በአለም አቀፍ ደረጃ ከስደት ጋር ተያይዘው እየተከሰቱ ባሉ ችግሮች መፍትሄ ዙሪያ ኃላፊነት በመሸከም ችግሩን ለማጋራት ባሳየችው ቁርጠኝነት ነው ተብሏል፡፡

     5G የቴሌኮም አገልግሎት አቀርባለሁ ብሏል

      የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ በኢትዮጵያ፤ የቴሌኮም ምርምርና ፈጠራ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር መፈራረሙን አስታወቀ። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለው የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከሉ፤ አዳዲስ የቴሌኮሚኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማራጮችን እዚሁ ሀገር ቤት በመፍጠር ለተጠቃሚዎች ያቀርባል ተብሏል፡፡
የምርምርና ፈጠራ ተግባር ከሚያከናውንባቸው ዘርፎች መካከልም በገመድ አልባ ኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነቶች፣ የኔትዎርክ ሽፋንና ጥራትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ምርምርና ፈጠራ እንዲሁም በሀገሪቱ የተዘረጋውን የቴሌኮም መዋቅር የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከሎች ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል የተባለውና በ3 ሺህ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው የፈጠራ ማዕከሉ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ያፈልቃል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ኩባንያው የ5ኛው ትውልድ (5G) የቴሌኮም አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማቅረብና ለማስፋፋት እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡

 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተመሰረተ 25 አመት ሞልቶታል። በዚህ 25 አመት ጊዜ ውስጥ ምን ሰርቶአል? ሲባል ብዙ ክንውኖችን ማሳካቱ 25ኛ አመቱን ሲያከብር ተወስቶአል።
ለማስታወስ ያህልም ፡-
በስነተዋልዶ ጤና የሚያገለግሉ ሙያዊ ትንተናዎችን ለማቅረብ በአገር ደረጃ በሚዋቀሩ የተለያዩ ኮሚዎች ውስጥ በመሳተፍ ሁነኛ የሆነ አስተዋጽኦ አድርጎአል።
ባለፉት 25 አመታት ከ20 በላይ የሆኑ እጅግ ተጠቃሽ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አከናውኖአል።
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለመግታት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲሰጥ ከማድረግ አኩዋያ ወደ 70 የሚሆኑ የህክምና ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን ማሰልጠንና በተጨማሪም ክትትል በማድረግ የበኩሉን ሚና ተጫውቶአል።
በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን በማዋለድ ተግባር ላይ የተሸለ ክህሎት ኖሮአቸው በተለይም በኦፕራሲዮን መውለድ የሚያስፈልጋቸውን እናቶች ከመደገፍ አኩዋያ ቁጥራቸው ወደ 47 ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቶአል። ይህ ስልጠና እስከ 6 ወር የደረሰ ተከታታይ ስልጠና ሲሆን በተለይም እስፔሻሊስት ሐኪሞች በማይገኙበት ቦታ ለወላድ እናቶች ባለሙያው አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ የሚችልበት ስራ ተሰርቶአል። በዚህም ፕሮጀክት እስከ መቶ ሺህ እናቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።
በወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ዙሪያ በተለይም ሴቶች ጥቃቱ ከደረሰባቸው በሁዋላ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ እና ክትትል እንዲደረግላቸው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በአዲስ አበባና በተለያዩ መስተዳድሮች ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ 6 ሞዴል ክሊኒኮችን በመመስረት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምናና እንክብካቤ እንዲያገኙ አድርጎአል።
በማደግ ላይ ባሉ ክልሎችና በአርብቶ አደሮች አካባቢ የማህረሰቡን የስነተዋልዶ እውቀ ትና ግንዛቤ ከማሳደግ አኩዋያ የሚሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሙያተ ኞች እርህራሔንና ተገቢ የሆነን የህክምና እርዳታ ለተገልጋዩ ለማዳረስ የሚችሉበትን ስልጠና ማህበሩ በመስጠት ላይ ነው።
ማህበሩ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሙያነክ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ደረጃውን የጠበቀ ግልጋሎት ለማህበረሰቡ እንዲሰጥ ሲያደርግ ቆይቶአል።
ከላይ ያነበባችሁት እውነታ በማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ርደረጀ ንጉሴ የተገለጸ ነው። የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በ25 አመታት ውስጥ እንዳካበተው ልምድ አሁንም የእናቶች ንና ጨቅላዎቻቸውን ጤንነትና ሕይወት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ከተለያዩ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።በኢትዮጵያ እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይልና በተገቢው ደረጃ በጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ያስፈል ጋል ሲባል አንዳንድ እንደችግር የሚታዩ ነገሮችን መንቀስ ወይንም እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንንም በሚመለከት ከታቀዱ ስራዎች መካከል ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር የሚሰራው ይገኝበታል።
 በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ አዳዲስና ነባር ዩኒቨርሲቲዎች በጠቅላላ ሐኪምነት ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በልዩ ሙያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምናን በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ የተለያዩ ተቋማት በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ስለማይገኙ አገሪቱ የምታፈራቸው ባለሙያዎች የተለያየ ደረጃ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ ጥራት ያለው እና በተመሳሳይ ደረጃ ብቃት ያለው ሕክምና ከመስጠት አኩዋያ ክፍተት እንዲመጣ ያደርጋል። ስለዚህም ይህንን ክፍተት በዋነኛነት በተሻለ ደረጃ መሙላት አስፈላጊ ሲሆን ይህንንንም የትም ህርት እና ሙያ ጥራትና ብቃት ለማምጣት እንዲያስችል የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስ ር በአምስት አመቱ የጤናው እቅድ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል። ከዚህም በመነሳት የማህ ጸንና ጽንስ ሕክምና ተማሪዎች በተሻለ ዝግጅት ሰልጥነው እንዲወጡ ማድረግና ስራ ላይ ያሉ ደግሞ የተሻለ ተከታታይ ትምህርት እንዲያገኙና ከዚህ በሁዋላ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካ ኝነት ለተገል ጋዩ ሕዝብ ጥራቱን የጠበቀ ግልጋሎት መስጠት እንዲያስችላቸው ማድረግ አንዱ ግብ ነው።
የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለመስራት እቅድ ከያዘባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ሐኪሞችን በብቃት እና በተመሳሳይ ደረጃ ማስተማር በመሆኑ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁን 5-6 ማለትም ግንቦት 28 -29 በአዲስ አበባ በተለያዩ መስተዳድር የሚገኙ ከ12 ድህረ ምረቃ ተቋማት ለተወከሉ የድህረ ምረቃ ዳይሬክ ተሮች ለሆኑ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ስልጠናውን ሰጥቶአል። እንደ ዶ/ርባልካ ቸው ንጋቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ መምህርና ተባባሪ ፕሮፌሰር የጽን ስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የድህረ ምረቃ ፕሮጀክት አስተባባሪ ገለጻ የድህረ ምረቃው ትምህርት በየተቋማቱ በተለያየ መንገድ ይሰጥ የነበረ ሲሆን መመራት ያለበት ግን በራሳችን ሀገራዊ ሁኔታ በመመስረት የፕሮግራሙን ባህል ሳይለቅ ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ ሳይንሳዊ ነገሮችን ሁሉም ጋ አንድ አይነት ለማድረግ ነው የስልጠናው ዋና አላማ።
በተለይም ስልጠናው ያስፈለገበት ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱ የማህጸንና ጽንስ ድህረ ምረቃ ትምህርቶች ላይ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጡ እና ትምህ ርቱ አግባብ ባለው መንገድ በመላ ሀገሪቱ ባሉ የትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ የትምህርት ሂደት እንዲኖራቸው ለማገዝ ነው። በዚህ ረገድም ለስልጠናው የተጋበዙት የየፕሮግራሙ ዳይሬክተሮች ሲሆኑ ለስልጠናውም ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር ባለሙያዎች ተጋብዘው አስፈላጊውን ሳይንሳዊ እውቀት አስጨብጠዋል። ይህ ስልጠና በድህረ ምረቃ ትምህርት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን በምን አይነት መንገድ ሁሉም ቦታ ያሉ የድህረ ምረቃ አስተባባሪዎች መያዝ አለባቸው የሚለውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማሳየት ከድህረ ምረቃ ተማሪዎች አቀባበል እስከ ተመርቆ መውጣት ድረስ ያለው ሂደት በምን መንገድ መመራት አለበት? ምን አይነት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ? ችግሮች ሲያጋጥሙስ እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው? ከየትምህርት ተቋማቱስ ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ ምንድነው? ተማሪዎቹስ በየአመቱ ማወቅ ያለባቸው የትኞቹን ነገሮች ነው? እነዚህን ነገሮች እያገኙ መሆናቸውን እንዴት መከታተል ይቻላል? የሚሉትና የመሳሰሉት ነገሮች ትኩረት ተሰጥቶአቸው ስልጠና ተሰጥቶአል።
እንደ ዶ/ርባልካቸው ማብራሪያ ከአሁን ቀደም ፕሮግራሞቹ ይመሩ የነበሩት በባህላዊ መንገድ ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን ተማሪዎቹ የአራት አመት ቆይታቸውን በምን መንገድ ስርአት ባለው መልክ በሁሉም ተቋማት በተመሳሳይ ሁኔታ መምራት ይገባል የሚለው የዚህ ፕሮጀክት ዋናው ማጠንጠኛ ነው። በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ብዛት በጣም ውስን በመሆኑ ተገልጋዩን ለመድረስ በማይችልበት ሁኔታ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ካሉት የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች 65ኀየሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚሰሩ ናቸው።
ቀሪዎቹ 35 ኀየሚሆኑትም የሚገኙት በየመስተዳድሩ ትልልቅ ከተሞች እንደ መቀሌ ፣አዋሳ ፣አዳማ በመሳሰሉት ነው።
ከላይ በተመለከተው መረጃ መሰረት የህክምና ባለሙያዎችን ብቃት እና ብዛት ማግኘት ወሳኝ ሁነት ነው። ይህ የድህረ ምረቃ ትምህርት ደግሞ የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና አገል ግሎቱንም በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዳረስ ለማድረግ እንደሚያስችል እሙን ነው። የአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ኮሌጅ ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር ለጀመረው ፕሮጀክት በአሜሪካ ዳይሬክተር በመሆን የሚሰሩት ዶ/ርብርሀኑ ታደሰ ሀሳባቸውን እንደሚከተለው ገልጸዋል።
“...የአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከኢትዮጵያው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር ከሚሰራው ስራ አንዱ የማህጸን ሐኪሞች ስልጠናን ማገዝ ነው። በዚህም ፕሮግራሙ የድህረ ምረቃው ትምህርት በሚሰጥባቸው በሁሉም ተቋማት ያሉ ዳይሬክተሮችን እውቀት ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና ነው። ተማሪዎቹ መሰልጠ ናቸው በትምህርት እና በስራ ጥራታቸው ብቁ መሆናቸው በኢትዮጵያ ለሚሰጡት አገልግሎት ብቻም ሳይሆን በመላው አለም ተገኝተው ብቃት ባለው መንገድ መስራት እንዲችሉ ያደርጋቸ ዋል። ስለዚህም ለስልጠናው የተጋበዙት በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ፕሮግራሙን የሚመሩ ዳይሬክተሮች በመሆናቸው የተሻለ አመራር መስጠት እንዲችሉ የሙያ ብቃታቸውን የሚያዳብር ስልጠና ነው። ስልጠናው የማህጸን ሐኪሞች ለመሆን የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለሚከታ ተሉ ሁለገብ የሆነ ድጋፍ በመስጠት በመርሐ ግብሩ ውስጥ በጥራት የሚወጡበትን መንገድ የሚያመቻች የአመራር ክህሎት ስልጠና ነው። ይህንን ስልጠና ለመስጠት የመጡት ሶስቱም ባለሙያዎች በአሜሪካ ከፍተኛ ሙያ ያላቸው ፕሮፌሰሮች ሲሆኑ ለአሜሪካ ሐኪሞች የሚሰጠ ውን ስልጠና በተመሳሳይ ደረጃ ኢትዮጵያ ላሉት ባለሙያዎችም እየሰጡ ነው። ስለዚህም ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ ልምዳቸውንም ያካፍላሉ።”

  በፌስቡክ በተሰራጨ አንድ ጽሁፍ ላይ የተሰጡና ያለአግባብ የአንድን ግለሰብ ስም የሚያጠፉ ናቸው የተባሉ ስድስት  አስተያየቶችን ላይክ ያደረገው ስዊዘርላንዳዊ፣ ዙሪክ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ውሳኔ የ4 ሺህ 100 ዶላር ቅጣት እንደተጣለበት አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የ45 አመቱ ስዊዘርላንዳዊ በአገሪቱ የሚሰራ አንድ የእንስሳት ተንከባካቢ ቡድን ሃላፊ የሆኑትን ኤርዊን ኬስለር የተባሉ ግለሰብ በተመለከተ በፌስቡክ በተሰራጨ ጽሁፍ ላይ የተሰጡ ስም አጥፊና ሃሰተኛ አስተያየቶችን ላይክ በማድረግ ብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዲመለከቷቸውና እውነት አድርገው እንዲቀበሏቸው በማድረጉ ጥፋተኛ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንደጣለበት ዘገባው ገልጧል፡፡
ኤርዊን ኬስለር፤ “መሰረተ ቢስ በሆኑ ሃሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱና ያለ አግባብ ስሜን የሚያጠፉ የፌስቡክ ጽሁፎችንና አስተያየቶችን ላይክ በማድረግ ህገወጥ ወንጀል ፈጽመውብኛል” በሚል አስራ አምስት ያህል የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መክሰሳቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡

    ከሳምንታት በፊት በ2 ራሰ-በራዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል
     ራሰ-በራ የሆኑ ሞዛምቢካውያን የባዕድ አምልኮ ተከታዮች በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል ያስጠነቀቀው የአገሪቱ መንግስት፤ ራሰ-በራዎች ራሳቸውን ከጥቃት ለማዳን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሞዛምቢክ የባዕድ አምልኮ ተከታዮች የሆኑ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ እነዚህ የባዕድ አምልኮ ተከታዮች ራሰ-በራ በሆኑ ሰዎች የራስ ቅል ውስጥ ወርቅ ይገኛል ብለው በማመን ግድያ እንደሚፈጽሙባቸው የአገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
የባዕድ አምልኮ ተከታዮች የሆኑ ግለሰቦች ዛምቤዚያ በተባለቺው የአገሪቱ ግዛት ከሳምንታት በፊት በሁለት ራሰ-በራ ሞዛምቢካውያን ላይ አሰቃቂ የግድያ ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ መሰል ጥቃቶች በቀጣይም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የአገሪቱ ፖሊስ ሰሞኑን ማስጠንቀቁን ገልጧል፡፡
ከሳምንታት በፊት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ሰለባ የሆነው አንደኛው ራሰ-በራ፣ በባዕድ አምልኮ ተከታዮች አንገቱ ተቀልቶና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቹም ተቆራርጠው መገኘታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ድርጊቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ቤት እንደሚገኙም አስረድቷል፡፡
ግድያውን በመፈጸማቸው በእስር ላይ የሚገኙት ሁለት ሞዛምቢካውያን ወጣቶች ለፖሊስ በሰጡት ቃል፣ የገደሏቸውን ራሰ-በራዎች የሰውነት ክፍሎች ለጠንቋዮች ለመሸጥ አቅደው እንደነበር መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ጠንቋዮቹም የሰውነት ክፍሎቹን በመቀመም ለደምበኞቻቸው ሃብት የሚያትረፈርፍ መድሃኒት እንደሚሰሩበት መግለጻቸውን አክሎ አብራርቷል፡፡

 በኢራቅ የአይሲስ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ብቻ ከምዕራባዊ ሞሱል ለማምለጥ የሞከሩ ከ231 በላይ ሰዎችን መግደሉ የተነገረ ሲሆን፣ አልሻባብ በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ በፑንትላንድ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸመው ጥቃት 70 ያህል ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል፡፡
ታጣቂዎቹ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ከአይሲስ ይዞታ በማምለጥ በኢራቅ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አካባቢዎች ለማምለጥ ሞክረዋል የተባሉትን ከ231 በላይ ኢራቃውያንን መግደሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ዛንጂሊ በተባለቺው የምዕራባዊ ሞሱል አካባቢ ሰሞኑን በተከፈተ የአየር ጥቃት እስከ 80 ያህል ኢራቃውያን መገደላቸውን የሚጠቁም መረጃ ማግኘቱን የገለጸው ተመድ፤ ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ በአሮጌዋ የሞሱል ከተማ ከ200 ሺህ በላይ ኢራቃውያን የስቃይ ኑሮ እየገፉ እንደሚገኙም ተመድ አመልክቷል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ፤ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የአልሻባብ ወታደሮች ከትናንት በስቲያ በፑንትላንድ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎችን መግደላቸውንና በርካቶችን ማቁሰላቸውን የዘገበ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በቅርብ አመታት ታሪክ የተፈጸመው የከፋ ጥቃት ነው በተባለው በዚህ የአልሻባብ ጥቃት ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ አንገታቸው ተቀልቶ የተገደሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡  
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው፤ ቦኮሃራም በናይጀሪያዋ ሜዱጉሪ ከተማ ከትናንት በስቲያ በፈጸመው የተኩስና የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 11 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡

ህንድ በጠፈር ምርምር ቴክኖሎጂ ታሪኳ ከሰራቻቸው ሮኬቶች ሁሉ በግዙፍነቱና በክብደቱ አቻ እንደማይገኝለት የተነገረውንና በክብደት ከአለማችን ሮኬቶች ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዘውን ጂኤስኤልቪ ማርክ 3 የተሰኘ ሮኬት በተሳካ ሁኔታ ወደ ጠፈር ማምጠቋን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
640 ቶን ክብደት እንዳለው የተነገረለት ይህ ግዙፍ ሮኬት፣ በጠፈር ምርምር ዘርፍ ለምታመጥቃቸው እጅግ ከባድ ሳተላይቶች በብዛት የአውሮፓ አገራት ሮኬቶችን ስትጠቀም ለነበረቺው ህንድ ትልቅ እመርታ መሆኑንና ከጥገኝነት በመጠኑም ቢሆን እንደሚያላቅቃት ተነግሯል፡፡
ህንድ በአለማቀፉ የሳተላይት ማምጠቅ ገበያ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ በስፋት እየሰራች እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ለአውሮፓ አገራት ሮኬቶች ከፍተኛ ክፍያ ከመክፈል የሚያድናትን ይህን ግዙፍ ሮኬት ሰርታ ለማምጠቅ መቻሏም ጥረቷ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሚያመለክት ነው ብሏል፡፡
የ43 ሜትር ቁመት ያለው ግዙፉ የህንድ ሮኬት ከአለማችን በክብደቱ ሁለተኛው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤በክብደት ክብረወሰኑን የያዘው የናሳው ሳተርን 5 ሮኬት እንደሆነም አክሎ ገልጧል፡፡
አገሪቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ በጠፈር ምርምሩ መስክ ጉልህ የሚባሉ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው ያለው ዘገባው፣ ለውጤታማነቷ ማሳያ ይሆናሉ ብሎ ከጠቀሳቸው ስኬታማ ተግባራት መካከልም፣ ከወራት በፊት ወደ ማርስ ያደረገቺው የጠፈር ጉዞና በአንድ ተልዕኮ ከ100 በላይ ሳተላይቶችን ያመጠቀችበት አጋጣሚዎች እንደሚገኙበት አስታውሷል፡፡

    ሳኡዲ አረቢያንና ግብጽን ጨምሮ ስድስት የአረብ አገራት፣ አሸባሪ ቡድኖችን በመደገፍ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነት እንዲስፋፋ፣ አካባቢውም እንዳይረጋጋ አድርጋለች በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን በሳምንቱ መጀመሪያ በይፋ አስታውቀዋል፡፡
አገራቱ ኳታር አይሲስና አልቃይዳን ጨምሮ ለተለያዩ አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ቢወነጅሏትም፣ አገሪቱ ግን ውንጀላውም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸው መሰረተ ቢስና በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ናቸው ስትል ምላሽ መስጠቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባህሬንና ሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ደህንነታቸውን ከሽብርተኝነትና ከጽንፈኝነት ለመከላከል በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ባለፈው ሰኞ ማለዳ በይፋ ያስታወቁ ሲሆን፣ በነጋታውም የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ፣ ግብጽ፣ የመንና ሊቢያ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ አገራቱ የየብስና የባህር ድንበርን እንዲሁም የአየር ክልልን ከመዝጋት ባለፈ፣ አምባሳደሮቻቸውንም ከዶሃ አስወጥተዋል፡፡
የአረብ አገራቱ ተማክረው ፊት ለነሷት፣ ተባብረው ላገለሏት ኳታር መጪው ጊዜ እጅግ ፈታኝና ዘርፈ ብዙ ቀውስ የምታስተናግድበት የፈተና ወቅት እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ ቀውሱ ከእለት ጉርስ እስከ ፖለቲካዊ ቀውስ ስር ሰድዶ አገሪቱን የከፋ አደጋ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፣ የአገራቱ ውሳኔ ይፋ በተደረገ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ ነበር ይህንን እውነታ የሚያጠናክሩ አደገኛ ክስተቶች መታየት የጀመሩት፡፡
ከዕለት ጉርስ እስከ ስርዓት ለውጥ?…
2.7 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኳታር ምንም እንኳን ቢዝቁት የማያልቅ የነዳጅ ባህር የታደለች ባለጸጋ አገር መሆኗ ባይታበልም፣ የምግብ ዋስትና ወሳኝ ክፍተቷ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አገሪቱ 40 በመቶ ያህሉን የምግብ ፍጆታዋን ከሳኡዲ አረቢያ ጋር በሚያዋስናት የየብስ ድንበር በኩል ነበር በየዕለቱ በመቶዎች በሚቆጠሩ ከባድ ተሸከርካሪዎች እያስጫነች በገፍ  የምታስገባው፡፡
የሰሞኑ ድንገተኛ ውሳኔም ታዲያ፣ ይህ ወሳኝ የምግብ አቅርቦት የሚገባበትን የሳኡዲ አረቢያ ድንበር የሚዘጋ በመሆኑ፣ የምግብ እጥረት በመፍጠር አገሪቱንና ህዝቧን የከፋ ችግር ውስጥ ይጥላቸዋል እየተባለ ነው፡፡ የአገራቱን ውሳኔ ተከትሎ መጪው ጊዜ ያሰጋቸው በርካታ የኳታር ዜጎች፣ ለክፉ ቀን የሚሆን የምግብና የውሃ ስንቅ ለመያዝ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ወደ ሱፐር ማርኬቶች በመጉረፍ ላይ እንደሚገኙም ዶሃ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡
የምግብ አቅርቦቱ ወደ አገሪቱ የሚገባበት ይህ የየብስ ትራንስፖርት መስመር ከመዘጋቱ ጋር በተያያዘም፣ በኳታር የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ይከሰታል፤ የህዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮም ወደ ቀውስ ያመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት ግን የምግብ እጥረት እንደማይከሰት በመግለጽ ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እንዲገፉ ለዜጎቹ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ከኳታር ጎን የቆመቺው ኢራንም የተባለው የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ አስቸኳይ የምግብ እህል ወደ ኳታር መላኳ ተነግሯል፡፡ የቱርክ ባለሃብቶችም ለኳታር የምግብና የውሃ አቅርቦት ለማድረስ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኞች ግን፣ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊቀሰቀስ የሚችለው የህዝብ ምሬት ከዕለታዊ የፍጆታ ጥያቄነት አልፎ የስርዓት ወይም የመንግስት ለውጥን ወደ መሻት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ጫና ከፍ ሊልና አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ሊያስገባት እንደሚችል አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
አደጋ ላይ የወደቀ ንግድና ኢንቨስትመንት
እነ ሳኡዲ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የአቡ ዳቢው ኢትሃድ ኤርዌይስ እና የዱባዩ ኤሜሬትስ አየር መንገድ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ወደ አገሪቱ መዲና የሚያደርጉትን በረራ ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
አገራቱ በዚህም አላበቁም፡፡ የአየር ክልላቸውን ለታዋቂው የአገሪቱ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ ዝግ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡ በየቀኑ ወደ እነዚህ አገራት በርካታ በረራዎችን ሲያደርግ የነበረውና በትርፋማነቱ የሚታወቀው ኳታር ኤርዌይስ፣ በአረብ አገራቱ ውሳኔ ሳቢያ በታሪኩ እጅግ የከፋውን ኪሳራ እንዳያስተናግድም ተሰግቷል፡፡ የአገራቱ ውሳኔ በኳታር ይሰሩ የነበሩ ታላላቅ ኩባንያዎች ስራቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገረ ሲሆን፣ ታዋቂው የሳኡዲ የእግር ኳስ ቡድን አል አህሊ ከኳታር ኤርዌይስ ጋር የነበረውን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ማፍረሱም ተዘግቧል፡፡
በኳታር እየተከናወኑ ከሚገኙ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የ2022 የአለም የእግር ኳስ ዋንጫን ሊያስተናግዱ የተወጠኑት ግዙፍ ስታዲየሞች፣ ወደብና የምድር ውስጥ የባቡር ትራንስፖርት መስመር ግንባታ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ኮንክሪትና ብረትን ጨምሮ ለእነዚህ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች በግብዓትነት የሚውሉት ወሳኝ ጥሬ ዕቃዎች ከጎረቤት ሳኡዲ በየብስና በውሃ ትራንስፖርት የሚገቡ መሆናቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፤ የየብስ ድንበሩ መዘጋቱ እንደ ምግቡ ሁሉ በግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ዕጥረትና የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንዲሁም ግንባታዎቹ እንዲጓተቱ ምክንያት መሆኑ እንደማይቀር ዘግቧል፡፡
የሰው ሃብት ቀውስ
የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ በግዛቷ ውስጥ የሚገኙ የኳታር ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዲለቅቁ አዝዛለች፡፡
ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና ባህሬንም ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰናቸውን ከማስታወቃቸው ባለፈ፣ በኳታር የሚኖሩ ዜጎቻቸው በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ማስቀመጣቸው ተነግሯል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ በአገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ወይም ለጉብኝት የመጡ የኳታር ዜጎችም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ እንዲወጡ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸዋል፡፡  በኳታር 180 ሺህ ያህል ግብጻውያን እንደሚኖሩና አብዛኞቹም ምህንድስናና ህክምናን በመሳሰሉ ቁልፍ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ የዘገበው ቢቢሲ፤ ግብጽም የእነ ሳኡዲን ፈለግ ተከትላ ዜጎችን የማስወጣት እርምጃ ከወሰደች በኳታር የሚፈጠረው የባለሙያ እጥረት ቀውስ እጅግ የከፋ እንደሚሆን መነገሩን ገልጧል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የፊሊፒንስ መንግስት የአገሪቱ ዜጎች ወደ ኳታር እንዳይሄዱ የሚከለክል ጊዚያዊ እግድ ባለፈው ረቡዕ ማውጣቱን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይሄም ሆኖ ግን የአገሪቱ መንግስት በኳታር በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የያዘው እቅድ እንደሌለም ጠቁሟል፡፡
 ኳታርን ማግለሉ ወደ አፍሪካም ተዛምቷል
በእነ ሳኡዲ የተጀመረውን የማግለል እርምጃ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆን ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን የሚያስታውቁ አዳዲስ አገራት ብቅ እያሉ ነው፡፡ የአረብ ሊግ አባል የሆነቺዋ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሞሪታኒያ ኳታርን፣ እንዳንቺ ካለው የሽብር ደጋፊ ጋር ህብረት የለኝም፤ በቃሽኝ በማለት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን በይፋ አስታውቃለች፡፡
ሴኔጋልም እነ ሳኡዲ በኳታር ላይ የወሰዱት እርምጃ አግባብ ነው፣ እኔም ከዛሬ ጀምሮ ከኳታር ጋር ያለኝን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጫለሁ በማለት ባለፈው ረቡዕ አቋሟን የገለጸች ሲሆን፣ በኳታር የሚገኘው አምባሳደሯ በአፋጣኝ ወደ አገሩ እንዲመለስ ጥሪ አስተላልፋለች፡፡
ቻድ በበኩሏ ከትናንት በስቲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ባወጣቺው መግለጫ፤ የኳታርን ቀውስ ለመፍታት አገራቱ የውይይትን አማራጭ እንዲወስዱ ብትመክርም፣ አምባሳደሯን ከኳታር እንዲመለሱ ከማድረግ ወደ ኋላ አላለቺም፡፡
ሌላኛዋ አፍሪካዊት አገር ጋቦንም ከትናንት በስቲያ ባወጣቺው መግለጫ፤ ኳታርን “ለሽብርተኝነት ድጋፍ የምትሰጥ ያለመረጋጋት አጋር” ስትል ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ማጣት ምክንያት በማድረግ አውግዛታለች፡፡
የመታረቅ ዕድል
ማግለል መፍትሄ አይደለም የሚል አቋም የያዙት ቱርክንና ኩዌትን የመሳሰሉ አገራት፤ እነ ሳኡዲ ከኳታር ጋር ያላቸውን ችግርና አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱና ያቋረጡትን ግንኙነት እንዲቀጥሉ ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን የኩዌቱ ኢምር ሼክ ሳባህ አል አህመድአል ሳባህም ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከርና መፍትሄ ለመሻት ባለፈው ማክሰኞ ወደዚያው ማቅናታቸው ተዘግቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በአንጻሩ፣ ኳታርን ማግለል የሽብርተኝነት ሰቆቃ ፍጻሜ ጅማሬ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው በማለት እነ ሳኡዲ የወሰዱትን እርምጃ ማድነቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡ በነጋታው ግን፣ ትራምፕ ለኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃመድ አል ጣኒ ስልክ በመደወል፣ ከአገራቱ መካከል የተከሰተውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሜሪካ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸውላቸዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ኳታር በአካባቢው አገራት የደረሰባት መገለል እንዲያበቃ ከፈለገች፣ ከፍልስጤሙ “ሃማስ” እና ከግብጹ “ሙስሊም ብራዘርሁድ” ቡድኖች ጋር ያላትን ግንኙነት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ማቋረጥ ይገባታል ብሏል፡፡
የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ሞሃመድ ጋርጋሽ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኳታር ጋር ወደነበራት የቀድሞ መልካም ግንኙነት የመመለስ አማራጭን ማጤን የምትጀምረው የኳታር መንግስት ከሽብርተኛና ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ያለውን ግንኙነት በተጨባጭ እንደሚያቆም የሚያረጋግጥ አስተማማኝ ፍኖተ ካርታ ሲያቀርብ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የዘንድሮ ተመራቂ በሆኑት ዮሴፍ ከተማ የተፃፈው “እሬቶ” የተሰኘ መፅሐፍ ነገ ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ይመረቃል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ደራሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ደራሲው ገልፀዋል፡፡በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ታዋቂ ደራሲ በመፅሀፉ ላይ ዳሰሳ ያቀርባል የተባለ ሲሆን ደራሲያንና ገጣሚያን ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ የዝግጅቱ አስተባባሪ ይፍቱ ስራ ፕሮሞሽን ገልጿል፡፡ መፅሐፉ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ ሲሆን ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመዳሰስ መረጃ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በ284 ገፆች የተመጠነው መፅሀፉ፣ በ65 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 እናት የማስታወቂያ ድርጅት ከወመዘክርና ከጀርመን የባህል ማዕከል ጋር በመተባበር “በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ›› በሚል ርዕስ በአርኖልድ ዲባዲ ተፅፎ በገነት አየለ ወደ አማርኛ በተመለሰው መፅሐፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት የታሪክ ባለሙያው አበባው አያሌው እንደሆነ የገለፀው አዘጋጁ፤ ፍላጎት ያለው ሁሉ በውይይቱ ላይ እንዲካፈል ጋብዟል፡፡