Administrator

Administrator

    “ዘ ዊኪንድ” በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው  ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ ባለፈው ሳምንት በአለም ደረጃ በቢልቦርድ ምርጥ አልበሞች ሰንጠረዥ የ1ኛነትን ደረጃ በዚህ ሳምንትም አለምን እየመራ ይቀጥላል ተብሎ  እንደሚጠበቅ ተዘገበ፡፡“ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘው አዲሱ የአቤል አልበም፣ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ሳምንት በሽያጭ ብዛት መሪነቱን እንደሚይዝ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከተገመተው በላይ እንደተሳካለት ፎርብስ ዘግቧል፡፡ በ350 ሺህ የአልበም ሽያጭ አንደኛ እንደሚሆን የተገመተው የአቤል አልበም፣ በ412 ሺህ ያህል ተቸብችቧል፡፡ በአዲሱ አልበሙ ውስጥ የተካተቱት 12 ሙዚቃዎችም በያዝነው ሳምንት የቢልቦርድ 50 ምርጥ ሙዚቃዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ፣ በቢልቦርድ የምርጥ ዘፈኖች ሰንጠረዥ፣ በአንድ ሳምንት ሁለት ዘፈኖቹ፣
 ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱለት የመጀመሪያው ወንድ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ብቻ መሆኑን ቢል ቦርድ ገልጿል የሰሞኑን የአቤል ስኬት ሲዘግብም፤ በ57 አመታት የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ታሪክ፣ አቤል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብዙ ዘፈኖቹ፣ በምርጥ 100 ዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱለት ስድስተኛው ድምጻዊ ነው ብሏል፡፡  ዘንድሮ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ፣ ከአቤል የአልበም ሽያጭ የሚበልጥ ሪከርድ ያስመዘገበ ድምፃዊ የለም - ከድሬክ በስተቀር፡፡ አመቱ የአቤል ተስፋዬ ነው ያለው ፎርብስ መጽሄት፤ የድምጻዊው የሙዚቃ ስራዎች የካናዳንና የአሜሪካን ሬዲዮ ጣቢዎች በስፋት መቆጣጠራቸውንና ከፍተኛ ተወዳጅነት ማትረፋቸውን ዘግቧል፡፡ የአቤል ዘፈን በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያዎች በብዛት በመሰራጨት አቻ አልተገኘላትም፡፡ “ስድ” ቃላትን በሙዚቃዎቹ ውስጥ ይደጋግማል በሚል ትችት የሚሰነዘርበት አቤል ተስፋዬ፤ በሙዚቃዎቹ ኢትዮጵያዊኛ ቃና  ይንፀባረቃል የሚለው አስተያየት ከሁሉም በላይ እንደሚያስደስተው ገልጿል፡፡ በዘፈን መሃልም አልፎ አልፎ አማርኛ ያስገባል፡፡

     የታዋቂው የጫማ አምራች ኩባንያ “ሶል ሪበልስ” መስራችና ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵዊቷ የቢዝነስ ሰው ቤተልሄም ጥላሁን፤ በታዋቂው የአሜሪካ የቢዝነስ መጽሄት “ኳርትዝ” የአመቱ የአፍሪካ 30 ፈርቀዳጅ፣ የድንቅ ፈጠራ ባለቤቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተተች፡፡ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው መጽሄቱ፤ ፈርቀዳጅ፣ አዲስ ሃሳብ አፍላቂና ለአካባቢያዊ ችግሮች ተስማሚ መፍትሄ የሚሰጡ ድንቅ ፈጠራዎችን አበርክተዋል ያላቸውንና ከ15 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመረጣቸውን 30 ምርጦች ይፋ ባደረገበት ዝርዝር የ35 አመቷን ቤተልሄም አካትቷታል፡፡ከ10 አመት በፊት ቤተልሄም ያቋቋመችው “ሶል ሪበልስ”፣ በአሁኑ ወቅት አለማቀፍ ተፈላጊነትን ያተረፉ የጫማ ምርቶቹን ወደተለያዩ 30 የዓለማችን አገራት ኤክስፖርት እያደረገ መሆኑን የጠቆመው መጽሄቱ፤ ቤተልሄም ያመነጨችው የቢዝነስ ሃሳብ ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረገና ውጤታማ በመሆኑ በዝርዝሩ ውስጥ ልትካተት እንደቻለች ገልጿል፡፡

ዓመቱ ብዙ ሥራ የተሰራበት ነው፡፡ የንባብ ባህል በማሳደግ አቅጣጫ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሰኔ 30 የንባብ ቀን በመላው ኢትዮጵያ እንዲከበር አድርገናል፡፡ ቀኑም የንባብ ባህል ንቅናቄ ተምሳሌት ሆኖ ይታይ ዘንድ፣ በመንግስት በኩል ታስቦ እንዲውል ጥያቄ ያቀረብንበትም አመት ነው፡፡ የማህበሩ አባላት ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየሄዱ ልምድ እንዲያካብቱ የተደረገባቸው ጉዞዎች ነበሩ፡፡
ለምሳሌ “የጥበብ ጉዞ ወደ ፀሃይ መውጫ ሀገር” በሚል ወደ ድሬደዋና ወደ ሃረር ያደረግነው ጉዞ ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ ህዳሴው ግድብም የተደረገ ጉዞ አለ፡፡ ባለፈው አመት ከበርካታ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ማህበሩን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ አብረን ስንሰራ ከርመናል፡፡ የተለያዩ የሥነ ፅሁፍና የኪነጥበብ ዝግጅቶችንም አከናውነናል፡፡
ሌላውና ዋነኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘመናት የዘለቀ የትውልድ ጥያቄ መልሷል፡፡ ይኸውም የመሬት ጥያቄ ነበር፡፡ ወደ 3ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ በቦታው ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን መቀመጫ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ደራሲያን መቀመጫ ፅ/ቤት እንዲሆን አስበን ለመገንባት እቅድ አለን፡፡
በቀጣይ አመት የምናስበው በየክልሉ ያሉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ማጠናከርና ማስፋፋት ነው፡፡ ከተማን መሰረት ያደረጉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ወደ ክልል ፅ/ቤትነት ለማሳደግ ነው ያቀድነው፡፡ የንባብ ባህልን በሚመለከት በየኮንደሚኒየሞቹ የማስፋፋት አዲስ አይነት እቅድ አለን፡፡ በተንቀሳቃሽ ቤተመፅሃፍት አማካይነት ወደ ህብረተሰቡ እንደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡ የአዲስ አበባውን ተሞክሮ ወስደን በክልሎችም እንተገብራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ የምናደርጋቸውን የመፃህፍት ኤግዚቢሽኖች አጠናክረን በክልሎች ጭምር እናካሂዳለን፡፡ የህንፃውን ግንባታ ሂደትም ወደ አንድ ምዕራፍ እናሸጋግራለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡

ጨጨሆ የባህል አዳራሽ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአገሪቱ ላይ በባህል፣ በቱሪዝምና በበጐ ሥራ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡
“የጨጨሆ ባህል ሽልማት” በሚል ርእስ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ ውብሽት ወርቃለማው የአስር ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ሲያገኙ፣ በውዝዋዜ የምትታወቀውና በቅርቡ ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰችው እንዬ ታከለ የአስር ሺህ ብርና የዋንጫ ሽልማት አግኝታለች፡፡ እንዲሁም ከአራት ሺህ በላይ የባህል ግጥምና ዜማ የሰራው ሙሉጌታ አባተ፤ተመሳሳይ ሽልማት ሲያገኝ፣ተወዛዋዥዋ ዳርምየለሽ ተስፋዬም ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በቆዳ የተሰራ ምስላቸው የተበረከተላቸው ሲሆን የቱሪዝም አባት የሚባሉት አቶ ሃብተስላሴ ታፈሰም ተሸልመዋል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ልዩ ተሸላሚ የሆነው የመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ማዕከል መስራች ወጣት ቢኒያም በለጠ ደግሞ 20 ሺህ ብር ተበርክቶለታል፡፡ አርቲስት መሰረት መብራቴ፤የጨጨሆ የባህል አዳራሽ አምባሳደር ሆና ለአንድ ዓመት ለመስራት ተፈራርማለች፡፡

የአለም ኢኮኖሚ እድገት ከተገመተው በታች ይሆናል ተብሏል
             አዝጋሚው የቻይና ኢኮኖሚ በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል
                           አህጉረ እስያ በአለም ኢኮኖሚ መሪነቷ ትቀጥላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ማስታወቃቸውን ዘ ሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
አለማቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ከዚህ በፊት ተገምቶ ከነበረው አነስ ባለ መጠን በመካከለኛ ደረጃ ላይ ሆኖ እንደሚቀጥል የገለጹት ክርስቲያን ላጋርድ፣ በአለማችን የኢኮኖሚ እድገት መሪነቱን የያዘችው እስያ፤ ምንም እንኳን የእድገት መጠኗ እየቀነሰ ቢሆንም በመሪነቷ ትቀጥላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢንዶኔዥያ ያመሩትና ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ ጋር በአለማቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ዙሪያ የመከሩት ላጋርድ፣ ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ አለማቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ኢንዶኔዢያን በመሳሰሉ ያላደጉ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል፡፡
የአምናው የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.4 በመቶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አይ ኤምኤፍ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ የዘንድሮው የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.3 በመቶ ሊያድግ ይችላል ብሎ መገመቱንና ዕድገቱ ግን ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ዳይሬክተሯ መናገራቸውን አስረድቷል፡፡ አምና 2.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበችው አሜሪካ፤ ዘንድሮ በ2.5 በመቶ ታድጋለች ተብሎ መገመቱን የጠቀሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት 7.4 በመቶ ያደገችው ቻይና በበኩሏ፤ የዕድገቷ መጠን ቀንሶ 6.8 በመቶ ሊደርስ ይችላል ተብሎ እንደተገመተ ጠቁሟል፡፡
ያደጉ አገራት ኢኮኖሚ በተወሰነ መጠን ማገገም ይታይበታል ቢባልም፣ በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች ግን ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ይላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ክርስቲያን ላጋርድ ተናግረዋል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ ክርስቲያን ላጋርድ አዝጋሚው የቻይና ኢኮኖሚ በአለማቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘግቧል፡፡
“የቻይና ኢኮኖሚ እድገት በሌሎች የአለማችን አገራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ከዚህ በፊት ከተገመተው በላይና የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም ቻይና የጀመረቻቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማስቀጠል ይገባታል” ብለዋል ላጋርድ፡፡
በቻይና ኢኮኖሚ ላይ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ነዳጅና ማዕድናትን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህም ሸቀጦቹን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ብራዚልና ሩሲያን የመሳሰሉ አገራት ክፉኛ እየተጎዱ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

     የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሚስት ግሬስ ሙጋቤ፤ ከሃራሬ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የተዘረፉ ልባሽ ጨርቆችንና አልባሳትን ያለአግባብ ለፖለቲካ ደጋፊዎቻቸው በማከፋፈላቸው ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሆነ ተዘገበ፡፡
የሃራሬ ከተማ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ፖሊስ የወረሰባቸውን ልባሽ ጨርቆችና አልባሳት ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው አከፋፍለዋል በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ የዚምባቡዌ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ድርጅት በሴትየዋ ላይ ክስ እንደሚመሰርት ማስታወቁን ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ህገወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ የሃራሬ ከተማ ፖሊስም በቅርቡ ባደረገው አሰሳ፣ በሺህዎች ከሚቆጠሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በርካታ ቶን የሚመዝኑ ልባሽ ጨርቆችና ሌሎች ቁሳቁሶችን መንጠቁን ገልጧል፡፡
ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊ ዚምባቡዌ በተከናወነ የፖለቲካ ቅስቀሳ ላይ፣ ፖሊስ ከነጋዴዎቹ የነጠቃቸውን 150 ቦንዳ ልባሽ ጨርቆችና አልባሳት ዛኑፒኤፍ ለተባለው ፓርቲያቸው ደጋፊዎች በነጻ ሲያከፋፍሉ መታየታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ ድርጊቱን ያወገዘው የዚምባቡዌ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ድርጅትም ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፤ የግል ንብረታቸው ያልሆነን ልባሽ ጨርቅና አልባሳት ለደጋፊዎቻቸው ማከፋፈላቸው ህገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ ይሄን ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ በአፋጣኝ ክስ እንመሰርታለን ብለዋል፣ የድርጅቱ ዳይሬክተር ፕሮሚዝ ክዋናንዚ፡፡
ግሬስ ሙጋቤ ከነጮች የተወረሱ ሰፋፊ መሬቶችን የግል ይዞታቸው በማድረግ በአገሪቱ አቻ እንደማይገኝላቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ልባሽ ጨርቆቹን ሲያከፋፍሉ በደስታ ተውጠው ገዝተው እንዳመጡላቸው ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ እንደነበርም አመልክቷል፡፡
በርካታ የአገሪቱ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በፖሊስ እየታደኑ እየተደበደቡና ንብረቶቻቸው እየተወረሰባቸው መሆኑንና  በ17 ያህል ነጋዴዎች ላይ ክስ መመስረቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

    የፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ መንግስት ሞሃመድ ሙርሲን ከመንበረ መንግስቱ አስወግዶ ስልጣን ከያዘ በኋላ በአገሪቱ የመጀመሪያው በሚሆነውና ከሚጠበቀው ጊዜ ዘግይቷል በሚል ሲተች ቆይቶ በጥቅምት ወር ሊካሄድ ቀን በተቆረጠለት የግብጽ ፓርላማ ምርጫ፣ በውጭ አገራት የሚገኙ ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ መፈቀዱ ተዘገበ፡፡
ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በርካታ ግብጻውያን በሚኖሩባቸው 139 የተለያዩ የአለማችን አገራት በሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ዜጎች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማስቻል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃምዲ ሳንድ ሎዛ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ በ139 አገራት ውስጥ በሚገኙ የግብጽ ኤምባሲዎች የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ዘገባው ገልጧል፡፡
ማክሰኞ በተጀመረው የአገሪቱ የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ 2 ሺህ 745 ያህል ዜጎች በተወዳዳሪነት መመዝገባቸውንና ምዝገባው ለ10 ቀናት ያህል እንደሚቆይ የግብጽ ከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፣  55 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውንም አሃራም የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የምርጫ ኮሚሽን፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ምርጫው በጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚካሄድና የድምጽ አሰጣጡም ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ማስታወቁን የጠቆመው የቴሌግራፍ ዘገባ፣ አገሪቱ ከሰኔ ወር 2012 አንስቶ ፓርላማ እንደሌላትና ምርጫ እንድታካሄድ የተወሰነው ቀደም ብሎ ቢሆንም በፕሬዚዳንቱ ቸልተኝነት መዘግየቱን አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፤ ከነባር የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ለመቀላቀልም ሆነ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በቀጣዩ ምርጫም ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማይወዳደሩ ጠቁሟል፡፡
ምርጫው ከተያዘለት ጊዜ እንዲራዘምና ባለፈው መጋቢት ወር እንዲካሄድ ቢወሰንም፣ የአገሪቱ ፍርድ ቤት አንዳንድ የምርጫ ህጎች ህገመንግስቱን የሚጥሱ ናቸው በማለት ምርጫው ዳግም እንዲራዘም መወሰኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ጆሃንስበርግ 23‚400፣ ካይሮ 10‚200፣ ሌጎስ 9‚100 ሚሊየነሮች አሏቸው
            አፍሪካ በድምሩ 670 ቢ. ዶላር ሃብት ያካበቱ 163 ሺህ ሚሊየነሮች አሏት

   የደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ በአፍሪካ አህጉር በርካታ ሚሊየነሮች የሚገኙባት ቀዳሚ ከተማ መሆኗን አፍርኤዥያ ባንክ እና ኒው ወርልድ ዌልዝ የተሰኙ ተቋማት ሰሞኑን ይፋ ያደረጉትን አህጉራዊ የጥናት ውጤት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘገበ፡፡ “የወርቅ ከተማ” ተብላ የምትጠራው ጆሃንስበርግ፤ 23 ሺህ 400 ሚሊየነሮች የሚኖሩባት የአፍሪካ የባለጸጎች ከተማ መሆኗን የገለጸው ዘገባው፣ ደቡብ አፍሪካ በአህጉሩ ከሚገኙ ሚሊየነሮች 30 በመቶው የሚገኙባት አገር መሆኗንም አስታውቋል፡፡
10 ሺህ 200 ሚሊየነሮች ያሏት የግብጽ መዲና ካይሮ፤ በሚሊየነሮች ብዛት ከአህጉሩ ከተሞች ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን 9 ሺህ 100 ሚሊየነሮች ያሏት የናይጀሪያዋ ሌጎስ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
ባለሃብቶቹ በዝርዝሩ ውስጥ ለመካተት ቢያንስ 1 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ሊኖራቸው እንደሚገባ የጠቆመው ዘገባው፣ አፍሪካ በድምሩ 670 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያካበቱ 163 ሺህ ሚሊየነሮች እንዳሏትም አክሎ ገልጿል፡፡

 ጋዜጠኛ የደስደስ ተስፋ በቅርቡ ያሳተመው “እንጀራ ከመከራ” የተሰኘ የግጥም መድበል በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት በሀገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በ72 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤ በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  በዶክተር ምህረት ደበበ በተፃፈውና በቅርቡ ለንባብ በበቃው “ሌላ ሰው” የተሰኘ ልቦለድ መጽሐፍ ሃሳብ ላይ የአንባቢያን ውይይትና የመጽሐፍ ማስፈረም ዝግጅት ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ በደሳለኝ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ መጽሐፉም ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የተቆለፈበት” የተሰኘ በተደጋጋሚ የታተመ ልብ ወለድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡