Administrator

Administrator

    የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፣ ባለፈው ሳምንት ከምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ካነሷቸው ተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሏቸውን ስድስት ሚኒስትሮች፣ባለፈው ማክሰኞ ከስልጣናቸው ማባረራቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡በአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በሚጻረር መልኩ ሹም ሽር አድርገዋል በሚል ሲተቹ የሰነበቱት የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኬር፤እነዚህን ሚኒስትሮች ማባረራቸው አገሪቱን ወደ ከፋ ቀጣይነት ያለው ግጭት ሊያስገባት እንደሚችል እየተነገረ ነው ብሏል ዘገባው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ከስልጣናቸው ያባረሯቸው ሚኒስትሮች፡- የአገሪቱ የነዳጅ፣ የከፍተኛ ትምህርት፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ፣ የሰራተኞች፣ የውሃ እንዲሁም የመሬትና የቤቶች ልማት ሚኒስትሮች እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ሚኒስትሮቹ እንዲባረሩ ሃሳብ ያቀረቡት ከሰሞኑ በፕሬዚዳንቱ አነጋጋሪ ውሳኔ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙት ታባን ዴንግ ጋኢ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡ባለፉት 2 አመታት በአገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች፣በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሰደዳቸውን ያስታወሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ከሶስት ሳምንታት በፊት በሁለቱ ሃይሎች መካከል ዳግም ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎም ተጨማሪ 60 ሺህ ያህል ደቡብ ሱዳናውያን አገር ጥለው ተሰደዋል ማለቱን ዘገባው ገልጧል፡፡

ደራሲ ጄምስ ፓተርሰን በ95 ሚ. ዶላር ቀዳሚነቱን ይዟል
    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤በድርሰት ስራዎቻቸው ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአመቱ የዓለማችን እጅግ ሃብታም ደራሲያንን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረገ ሲሆን ባለፉት 12 ወራት ብቻ 95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው ታዋቂው ደራሲ ጄምስ ፓተርሰን በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በወንጀል ነክ ድርሰቶቹ የሚታወቀው ጄምስ ፓተርሰን፤ ባለፉት ሶስት አመታት በፎርብስ የሃብታም ደራሲያን ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚነቱን ይዞ መዝለቁን የጠቆመው መጽሄቱ፤ይሄው ደራሲ በቀጣዩ አመትም ክብሩን እንደጠበቀ ይዘልቃል ተብሎ እንደሚገመት አስታውቋል፡፡
በ2016 የአለማችን ሃብታም ደራሲያን ዝርዝር ውስጥ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው 19.5 ሚሊዮን ዶላር ያገኘው የህጻናት መጽሃፍት ደራሲው ጄፍ ኬኒ ሲሆን  ሃሪ ፖተር በሚለው ተከታታይ መጽሃፏ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው ጄ ኬ ሮውሊንግ ደግሞ በ19 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ጆን ግሪሻም በ18 ሚሊዮን ዶላር አራተኛ፣ ስቴፈን ኪንግ፣ ዳንኤላ ስቲልና ኖራ ሮበርትስ ደግሞ በተመሳሳይ በ15 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ደራሲያን መካከልም ጆን ግሪን፣ ዳን ብራውንና ቬሮኒካ ሮዝ ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የተለያዩ የአለማችን አገራትን ደራሲያን አመታዊ የመጽሃፍ ሽያጭና ገቢ በማስላት የላቀ ገቢ ያገኙ ደራሲያንን ዝርዝር ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መጽሄት፤ባለፉት 12 ወራት ከፍተኛ ገቢ ያገኙ በሚል በዝርዝሩ ያካተታቸው 14 የተለያዩ የአለማችን አገራት ደራሲያን በድምሩ 269 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን አስታውቋል፡፡

የወርቅ ዋጋ መናር ለትዳር ፈላጊ ወንዶች ፈተና ሆኗል ተብሏል
     በግብጽ የወርቅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ወንዶች ለሚያገቧት ሴት የወርቅ ጥሎሽ የሚሰጡበት ባህላዊ ልማድ እንዲቀር ለማድረግ የተጀመረው ዘመቻ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ሻብካ በተባለው የግብጻውን ባህላዊ የሰርግ ልማድ መሰረት፣ አንድ ወንድ ሊያገባት ለሚፈልጋት ሴት የወርቅ ጌጣ ጌጦችን መስጠት እንደሚጠበቅበት የጠቆመው ዘገባው፣ አሁን አሁን ግን የወርቅ ዋጋ እየናረ መምጣቱ ለትዳር ፈላጊ ወንዶች ፈተና መሆን መጀመሩን ገልጧል፡፡በግብጽ የአንድ ግራም ባለ 24 ካራት ወርቅ ዋጋ 50 ዶላር ያህል መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ይህም የትዳር ፈላጊ ወንዶችን አቅም እየተፈታተነ በመሆኑ በማህበራዊ ድረገጾች የወርቅ ጥሎሽ ባህሉ እንዲቀር ዘመቻ እንዲጀመር ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ዘመቻው መጀመሩን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ግብጻውያን፣ልማዱ አንዲቀር ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤የዘመቻው ደጋፊዎች በወርቅ ምትክ ብር ወይም ሌላ ውድ ያልሆኑ ጌጣጌጦች በጥሎሽ መልክ ቢሰጥ መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን እንደሰነዘሩ ገልጧል፡፡የወርቅ ጥሎሽ እንዲቀር ድጋፋቸውን የሰጡ አብዛኞቹ የዘመቻው ተሳታፊዎች ወንዶች ቢሆኑም፣በርካታ ግብጻውያን ሴቶች ይህንን ሃሳብ በመደገፍ ከወንዶች ጎን መሰለፋቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

   ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ መንደር ውስጥ በርካታ የአይጥ መንጋ ይፈላና አካባቢውን ይወርረዋል፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ የሚቻለው ድመት ወዳለው ሰው ሄዶ ድመቱን ተውሶ አይጦቹን እንዲያስወግድ ማድረግ ነው፡፡
ስለዚህ የሰፈሩ ሰው መክሮ ተመካክሮ ድመት  ወዳለው ሰው ዘንድ ሄዶ፤
“ጌታ፤ እንደምታውቀው መንደራችን በአይጥ ተወሮ መድረሻ አሳጥቶናል፡፡ የአንተ ቤት ከዚህ ችግር ነፃ ነው፡፡ ድመት ስላለህ፡፡ የእኛ ግን አሁንም እንደተወረረ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ድመትህን አውሰንና ሴት ድመቶችን አስወልዶ፡- አርብተን ከአይጥ ችግር ነፃ እንሁን?!” አለው፡፡
ባለ ድመቱም፤ ደግና አርቆ አሳቢ ሰው ኖሮ፤
“ዕውነት ነው፡፡ የእኔ ቤት ብቻ ከአይጥ ነፃ መሆን ችግሩን አያስወግደውም፡፡ ነገ የእናንተ ቤት አይጦች ወደ እኔ ቤት መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ችግሩ ዙሪያ ገጠም (Vicious circle) ነው፡፡ ስለሆነም በሁሉም የሰፈሩ ሰው ቤት ያሉትን አይጦች ማስወገድ ነው የሚሻለው”፤ አለና ድመቱን አዋሳቸው፡፡
ድመቱ ስራውን ሰራ፤ ብዙ ድመት አስወለደ፡፡ አድገው አይጦቹን አሳደው በሉ፡፡ መንደሩ ከአይጥ ፀዳ! ሰላም ወረደ፡፡ ሜዳው ሁሉ ስጥ የሚሰጣበት እህል እንደ ልብ ፀሐይ እንዲመታው ሰሌን ላይ የሚዘረጋበት ወቅት ሆነ! ጥጋብ የአደባባይ ጉዳይ ሆነ!
ያም ድመት ቀን ወጣለት፡፡ እንደ ልቡ መብላት፣ መጠጣት፣ በየቤቱ ምግብ ማግኘት ዕድሉ ሆነ፡፡ ከሌላ ሰፈር ድመቶች ጋር ስሪያ፣ መዳራት፣ ማስረገዝ፣ ማስወለድ ሆነ ስራው፡፡ ምድር ሰማዩ በድመት ተሞላ!    
“ደሞ በድመት ብዛት ምሬት መጣ! “እነዚህ ድመቶች ወደ አጎራባች አገሮች በጉዲፈቻ እንስጣቸው!” ተባለ፡፡ ሁሉም ተስማማ፡፡ ሰፈሩ ከድመት ነፃ ሆነ፡፡ ዋናው ባለ ድመትም የራሱን ድመት ከእንግዲህ እንዳይወልድ አኮላሸው!
ለጥቂት አመታት ከአይጥ - ነፃ የሆነ ኑሮ ቀጠለ፡፡ ሆኖም አይጦቹ ጊዜ ጠብቀው መንደሩ በተዘናጋባት ሰዓት ከች አሉ፡፡ እህል ተበላ፡፡ ልብስ ተቀረጠፈ፡፡ መጽሀፍ ተከረተፈ፡፡ ችግር አጠጠ፡፡
እንደገና ህዝቡ ወደ ባለ ድመቱ መጣ፡፡
“እባክህ እንደ ካቻምናው ድመትህን አውሰን? ሴት ድመቶችን ያጥቃልን?” ሲሉ በትህትና ጠየቁት፡፡
“አዬ ወዳጆቼ! እኔስ ድመቱን በሰጠኋችሁ በፈቀድሁ፡፡ ግን አይጠቅማችሁም፡፡ ምክንያቱም፤ ዛሬ ድመቴ ተኮላሽቷል፡፡ አሁን አማካሪ (consultant) ሆኗል፡፡ የምክር አገልግሎት ብቻ ነው ሊሰጥ የሚችለው” አላቸው፡፡
*         *         *
ዛሬ ከስራ አስኪያጅነት ወደ አማካሪነት የሚመደቡ አያሌ ናቸው! በውሰት ችግርን ለመፍታት መሞከር ዘላቂ ሂደት አይሆንም፡፡ አንድ ጊዜ በዘመቻ የፈታነው ችግር መሰረታዊ መፍትሄ አገኘ ማለትም አይደለም፡፡ ሥር - ነቀል መፍትሄ ማግኘት ካስፈለገ፣ በቂ አቅም በገዛ ሀብት መፍጠር የግድ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ስራን በሙሉ ልብ የምንሰራበት ሁኔታ ማመቻቸት ግዴታ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የተማረ ኃይልን በአመርቂ ሁኔታ ማሳተፍ ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምሁራን አድርባይ፣ ተጠራጣሪና ፈሪ ከሆኑ የስራ ሁኔታው የስጋት እንጂ የልበ - ሙሉነት አለመሆኑን ነው የሚያመላክተን፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሙሉ  አቅማቸውን ለተፈለገው ግብ አያውለውም፣ አልፈው ተርፈውም እንቅፋት እስከመሆን ይደርሳሉ ማለት ነው። “መሳም ፈልገሽ፣ ጢም ጠልተሸ አይሆንም” የሚለውን ተረት አለመዘንጋት ብልህነት ነው። አሳታፊ መድረክ መፈጠር አለበት ሲባል፤ ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ አሳታፊ መድረክ ይፈጠር ሲባል ፍትሐዊ፣ ኢ-ወገናዊ (non-nepotistic) ሁኔታ መኖር የለበትም ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፤ ስራ በብቃት፣ በጥራት፣ ጊዜን ቆጣቢ በሆነ መልኩ ያለብክነት የሚተገበርበት ሁኔታ ይፈጠር ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፤ ከታማኝነት አስቀድሞ የስራ ክህሎት መመዘኛ ይሁን ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሥራ ላይ ይዋል ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፣ ከሰራተኛው አማካሪው (consultant) አይብዛ ማለት ነው፡፡ ከሌላ ቦታ በድክመት የተነሳ፤ አማካሪ አይሁን ማለትም ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፤ የቅራኔና የእልህ መድረክ ሳይሆን ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትና ዕድገት ሁሉም ፈትል ከቀስም ሆኖ በአንድነት የሚሰራበት መድረክ ይፈጠር ማለት ነው፡፡፡ አሳታፊ መድረክ ሲባል፣ ሙስና አልባ መድረክ መፍጠር ማለት ነው፡፡
ከቶውንም ዛሬ በሀገራችን ስራ በማንኪያ መብል በአካፋ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ይኸውም ባቋራጭ መክበርን እንደ ርዕዮተ ዓለም ይዞ የሚንቀሳቀስበት ዘመን ሆኗል፡፡ ዕድገት እየፋጠነ ነው እየተባለ የቦጥቧጩ፤ የሸርሻሪው ከአፍ እስከ ገደፍ መሆን፤ በግልም፣ በመንግስትም፣ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅትም ያለ ምህረት ምዝበራን ማካሄድ በአዋጅ የታዘዘ ይመስላል፡፡ እርግጥ አዋቂዎች፤ ዝመና (modernization) እና ሙስና ቁራኛ ናቸው ይላሉ፡፡ “ሙስና ከዝመና ጋር የሚመጡት የግለኝነትና የህዝብ ሀብት ልዩነት ውጤት ነው፡፡ አንድም ደግሞ ስኬታማ ያልሆነ የፖለቲካ ተቋማ አለመኖር ምልክት ነው፡፡ … ሙስና ህዝባዊ ሚናን ከግል ጥቅም ማምታታትንም ያሳያል፡፡ የህብረተሰቡ ባህል ንጉሱን እንደ ግለሰብ ሚናውን ካልለየና ንጉሱን እንደ ንጉስ ሚናውን ካልለየ፤ ንጉሱ የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ብሎ ሊከሳቸው አይቻለውም፡፡ የንጉሱ አካሄድ አግባብ ነው፣ አደለም ብሎ መፍረድም ያዳግተዋል!” በእኛ አገር አንፃር ሲታይ፤ ግልፅ ሌብነት ይፋ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ እነ ናይጄሪያን ባንተካከልም በራሳችን የሚታይ፣ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ሙስና አለን፡፡ ኤም.ጂ ስሚዝ የተባሉ ፀሐፊ፤ “ብሪታኒያው ሙስና የሚለውን፣ አውሳው ግፍ ይለዋል፡፡ ናይጄሪያዊው ፍላኒ ግን አስፈላጊና ባህላዊ ተግባር ነው ይለዋል” ይሉናል። ዞሮ ዞሮ እየዘመንን ስንመጣ፣ ሙስናችን ዳር ድንበሩን እደጣሰ ታዝበናል፡፡ አስከፊው ነገር ደግሞ ሃይ ባይና ተቆጪ ብሎም ቀጪ፤ አለመኖሩ ነው፡፡ ሁሉ ተነክሮበት ማ፣ ማንን ይቅጣ? “እኔ ትንሽ ብቻ ነው የወሰድት” የሚሉ ሹማምነት እንዳሉ ቢሰማም ጆርጅ በርናርድ ሾ እንዲህ ይመልስላቸዋል፡- There is no little pregnancy! - የእርግዝና ትንሽ የለውም ማለቱ ነው፡፡ የሙስናም ትንሽ የለውም፡፡ ኃጢያት ከኃጢያት ማወዳደር ሳይሆን ከኃጢያት መንፃት ነው ታላቁ ቁም ነገር! ማንም ከህግ በላይ አይደለም ካልን፤ “all men are equal but some men are more equal” “ሁሉም ሰው እኩል ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” ማለትን ምን አመጣው?! ከዚህም እንንፃ!

    ኢትዮጵያ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመሸጥ የያዘቺው እቅድ ዋነኛ አካል የሆነውና 1.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግበት የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በዚህ ሳምንት መጀመሩን ስታንዳርድ ሚዲያ ዘገበ፡፡1 ሺህ 45 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውንና 2 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማስተላለፍ አቅም እንዳለው የተነገረለትን የዚህን የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የሚያከናውነው ቻይና ኤሌክትሪክ ፓዎር ኢኩፒመንት ቴክኖሎጂ የተባለው ኩባንያ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ግንባታው በታህሳስ ወር 2018 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡ኬንያ ከኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት ስምምነት መፈጸሟን የዘገበው ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ፣ በቀጣይም የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን በብዙ እጥፍ ለማሳደግ ማሰቧን አስነብቧል፡፡በሁለቱ አገራት መካከል የሚዘረጋው ይህ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር፣ በ2018 ዓ.ም ለ870 ሺህ አወዎራዎች የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ያሟላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ ልማት ባንክ ማስታወቁንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜናም ግልገል ጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ፣ 800 ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጨት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ተናግረዋል፡፡
የግልገል ጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ፤ 96 በመቶ እንደደረሰም ኢንጂነር አዜብ አስታውቀዋል፡፡

    በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአይን ህክምና መምህሮች የተቋቋመው “ዲማ” የአይን ህክምና ክሊኒክ፤ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ክሊኒኩ ከሌላው የአይን ህክምና በተለየ በአይን ቆብና በእንባ መፍሰስ ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራና በአገሪቱ ሁለቱ ህክምናዎች ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዶክተሮች ብቻ እንዳሉ የክሊኒኩ መስራች አባል ዶ/ር መሰረት እጅጉ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቀት የእንባ መፍሰስ፣ የአይን ቆብና የአይን ቆብ አካባቢዎችን በማከም ትኩረት ያደረገው ክሊኒኩ፣ ሌሎችንም የአይን ህክምናዎች እግረ መንገዱን እንደሚሰጥና በተለያዩ አደጋዎች አይናቸውን ያጡ ሰዎች፣ በቀዶ ጥገና አርቴፊሻል አይኖችን እንደሚተክሉ ዶ/ር መሰረት ተናግረዋል፡፡

በአለማቀፍ የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚነትን ይዞ የዘለቀውና አይፎን ስልኮችን አምርቶ ለአለማቀፍ ገበያ ማቅረብ ከጀመረ ዘጠኝ ያህል አመታትን ያስቆጠረው ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤በእነዚህ አመታት 1 ቢሊዮን የአይፎን ስልክ ምርቶቹን ለደንበኞቹ መሸጡን ባለፈው ረቡዕ አስታወቀ፡፡
የአፕል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ኤንቢሲ ኒውስ እንደዘገበው፤የአይፎን ስልክ ምርቱን እ.ኤ.አ በ2007 በሰኔ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽያጭ ያቀረበው ኩባንያው፣ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ባሉት አመታት በድምሩ አንድ ቢሊዮን አይፎኖቹን ለደንበኞቹ ሽጧል፡፡
ኩባንያው የአይፎን ምርቶቹን ጥራትና የቴክኖሎጂ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻሻለ በአለም የስማርት ስልኮች ገበያ ውስጥ ቀዳሚ ሆኖ መዝለቁን ያስታወሰው ዘገባው፤በ2016 ሶስተኛ ሩብ አመት ብቻ 40.4 ሚሊዮን አይፎኖችን መሸጡን ገልጧል፡፡
አፕል ኩባንያ ባለፈው ረቡዕ 1 ቢሊዮንኛዋን አይፎን ስልክ መሸጡን እንዳስታወቀ የጠቆመው ዘገባው፤ስልኳ የተሸጠችበትን አገርና መደብር በተመለከተ ግን ያለው ነገር የለም ብሏል፡፡

(በ‹‹ፖለቲካ በፈገግታ›› ስታይል የተዘጋጀ
አስተያየት መሰብሰቢያ)

1. የአዲስ አበባ አስተዳደር ‹‹ህገ ወጥ›› ቤቶች
በሚላቸው ላይ እየወሰደ ያለውን በጅምላ
የማፍረስ እርምጃ በተመለከተ አስተያየትዎ
ምንድን ነው?
ሀ ) ለ ድሆች እ ቆረቆራለሁ የ ሚል
መንግስት፤ዜጎችን በሃምሌ ጨለማ
ያፈናቅላል ብዬ አልጠበቅሁም!
ለ) ማፍረሱ ሳያንስ ነዋሪዎቹ ሁለት ሶስት ቤት
ያላቸው፤‹‹ቱጃሮች›› ናቸው ማለቱ
አስገርሞኛል!
ሐ) እርምጃው ተገቢ ነው! ህገ ወጦች ዝም
ከተባሉ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ ህገ ወጥ
ቤት ከመገንባት አይመለሱም
መ) “ህገወጥ ቤቶች” ሲስፋፉ ዝም ያሉ
የወረዳ ሃላፊዎች፣ቤቶቹ ሲፈርሱ
ከሃላፊነታቸው መነሳት ነበረባቸው!
ሠ) ብዙ ሺህ ስደተኞች ተቀብላ የምታስተናግድ
አገር፤እንዴት ለዜጎቿ መሆን
ያቅታታል!?
2. መዲናዋ ከሳምንት በላይ ቆሻሻ የምትጥልበት
አጥታ፣በአጣብቂኝና በስጋት ውስጥ መሰንበቷ
ከምን የመጣ ይመስልዎታል?
ሀ) ከመልካም አስተዳደር ችግር!
ለ) ግልፅነት ከጎደለው አሰራር!
ሐ) ከድርድር ጥበብ ማነስ
መ) ከአመራር ክሽፈት
ሠ) እኔ ምን አውቅላቸዋለሁ!
3. ከሚከተሉት ውስጥ የአውራው ፓርቲ የከፋ
ችግሩ የትኛው ነው ይላሉ?
ሀ) ልማታዊ ጀብደኝነቱ
ለ) እውነታውን በፕሮፓጋንዳ መጨፍለቁ
ሐ) አጉል ፍረጃና ጠላት ማብዛቱ
መ) ለዚህች አገር “ከእኔ በላይ ላሳር” ማለቱ
ሠ) ምን ያልከፋ ችግር አለው!
4. ኢህአዴግ መራሹን መንግስት የማይገልፀው
ባህሪ የትኛው ይመስልዎታል?
ሀ) ለመጪው ትውልድ ምቹ አገር መፍጠር
ለ) ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት
ሐ) ለዜጎች መቆርቆርና ቅድምያ መስጠት
መ) ከአገር በፊት ፓርቲን ማስቀደም
ሠ) እኔ ባህሪው ገብቶኝ አያውቅም!
(ማስታወሻ፡- ለእርስዎ የሚስማማ መልስ
ከምርጫዎቹ ውስጥ ካላገኙ የራስዎትን መልስ
ማካተት ይችላሉ፡፡)

ቢዮንሴ በ11፣ አዴል በ8 ዘርፎች ለሽልማት ታጭተዋል

   በዘንድሮው የኤምቲቪ የሙዚቃ ቪዲዮ አዋርድ “ሊሞናዴ” በተሰኘው የሙዚቃ ቪዲዮ አልበሟ በ11 ዘርፎች ለሽልማት የታጨቺው ታዋቂዋ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፣ በበርካታ ዘርፎች ለሽልማት በመታጨት ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቢዮንሴ በኤምቲቪ የሙዚቃ ቪዲዮ አዋርድ ለሽልማት ከታጨችባቸው ዘርፎች መካከል፣ የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ፣ ምርጥ ፖፕ ቪዲዮና ምርጥ ኮላቦሬሽን ቪዲዮ እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ከቢዮንሴ በመከተል በበርካታ ዘርፎች በመታጨት ሁለተኛ ደረጃን የያዘቺው አዴል መሆኗን አስታውቋል፡፡
“ሄሎ” በተሰኘው ተወዳጅ የሙዚቃ ቪዲዮዋ አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፈቺው አዴል፤ በኤምቲቪ ሚዩዚክ ቪዲዮ አዋርድ በስምንት ዘርፎች ለሽልማት መታጨቷን የጠቆመው ዘገባው፤ በዘንድሮው ሽልማት ከታጩት ድምጻውያን መካከል ሪሃና እና ካንያ ዌስት እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡
በኤምቲቪ የሙዚቃ ቪዲዮ አዋርድ ታሪክ በበርካታ ዘርፎች ለሽልማት በመታጨት ክብረ ወሰኑን የያዘቺው፣ አነጋጋሪዋ ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፤ድምጻዊቷ በ2010 በ13 ዘርፎች ለሽልማት ታጭታ እንደነበር አስታውሷል። የዘንድሮው የኤምቲቪ የሙዚቃ ቪዲዮ አዋርድ፣ በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ኒውዮርክ ሲቲ ውስጥ በሚገኘው ማዲሰን ስኩየር ጋርደን በሚከናወን ደማቅ የሽልማት ስነስርዓት ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በ2016 በብዛት በመሸጥ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ይጠበቃል


“ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ” የተሰኘውና ነገ ማለዳ በገበያ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የሃሪ ፖተር ስምንተኛ ክፍል መጽሐፍ፤ በአገረ አሜሪካ ያለፉት 9 አመታት የቅድመ ህትመት ሽያጭ ከፍተኛውን ደረጃ ማስመዝገቡን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባርነስ ኤንድ ኖብል የተሰኘው የመጻህፍት ሻጭ ኩባንያ በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ፣ በቲያትር ስክሪፕት መልክ የተሰናዳው ይሄው የታዋቂዋ ደራሲ ጄ. ኬ. ሮውሊንግ መጽሐፍ፣ ከ2007 ወዲህ በአሜሪካ ገበያ ከፍተኛው የቅድመ ህትመት ሽያጭ የተመዘገበበት እንደሆነ ማስታወቁን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ኩባንያው ምንም እንኳን መጽሃፉ በምን ያህል ኮፒ እንደተሸጠ በግልጽ ባይናገርም፣ ባለፉት 9 አመታት ከደንበኞቹ ከፍተኛውን የግዢ ትዕዛዝ የተቀበለበት እንደሆነ ገልጾ፣ መጽሐፉ በ2016 በአሜሪካ የመጻህፍት ገበያ በብዛት የተሸጠ ምርጥ መጽሐፍ ይሆናል ብሎ እንደሚጠብቅ መጠቆሙም ተነግሯል፡፡
መጽሐፍትን በህትመትና በሶፍት ኮፒ ቅጂዎች ለአለማቀፍ ገበያ በማቅረብ የሚታወቀው አማዞን ቡክስ ኩባንያ በበኩሉ፤ በአመቱ በአሜሪካ በወረቀትም ሆነ በሶፍት ኮፒ ለገበያ ካቀረባቸው መጽሐፍት ከፍተኛውን የቅድመ ህትመት የግዢ ጥያቄ ያስተናገደው በዚሁ መጽሐፍ መሆኑን ማስታወቁንም ዘገባው ገልጧል፡፡
ከዚህ በፊት በ79 የተለያዩ የአለማችን ቋንቋዎች ተተርጉመው ለአለማቀፍ ገበያ የቀረቡት የሃሪ ፖተር ሰባት ተከታታይ መጽሐፍት፣ ከ450 ሚሊዮን በላይ ኮፒዎች መሸጣቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤የሃሪ ፖተር ፊልሞችም ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘታቸውን አመልክቷል፡፡