Administrator

Administrator

- የሞቱ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛ አካል ይጣራ፤ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ በህግ ይጠየቁ ብለዋል

   የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ከተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ የታሰሩ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲፈታ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት እንዲያደርግ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰሩ 15 የተለያዩ ታዋቂ አለማቀፍ እና ብሄራዊ ተቋማት ጠየቁ፡፡
ተቋማቱ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በላኩት የጋራ ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ በቀጣዩ ሳምንት በሚያካሂደው አመታዊ ጉባኤው በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ቀዳሚ አጀንዳው እንዲያደርግና ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫ እንዲያወጣ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላትና ተቃዋሚዎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔ በአፋጣኝ እንዲፈታ እንዲሁም የጸጥታ ሃይሎች በሁለቱም ክልሎች ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተቃዋሚዎች ላይ ያልተመጣጠነና ተገቢ ያልሆነ የሃይል ጥቃት መፈጸማቸውን እንዲያስቆም ግፊት እንዲያደርግም ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የተገደሉና የሰባዓዊ መብቶች ጥሰቶች የደረሱባቸው ዜጎች ጉዳይ በአለማቀፍ ገለልተኛ ተቋማት እንዲጣራ እንዲፈቅድ፣ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግና ህገ መንግስቱን፣ አለማቀፋዊና አህጉራዊ የሰብዓዊና የፖለቲካዊ መብቶች ህግጋትና ስምምነቶችን እንዲያከብር ለማስቻል ምክር ቤቱ ጫና እንዲያሳድርም ጠይቀዋል፡፡
ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ የጋራ ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ከእነዚህ 15 ተቋማት መካከል፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፍሪደም ሃውስ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስና ወርልድ ኦርጋናይዜሽን አጌንስት ቶርቸር ይገኙበታል፡፡




- ፕሬዚዳንቱ ቡድኑን ለመደምሰስ ያቀዱት ከ8 ወራት በፊት ነበር

    የናይጄሪያ የጦር ሃይል ከፍተኛ መሪ ሜጀር ጄኔራል ላኪ ኢራቦር፣ ጦራቸው በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች የሚገኙትንና በአሸባሪው ቡድን ቦኮ ሃራም የተያዙትን ጠንካራ ይዞታዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ቡድኑን በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመስስ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ላለፉት ሰባት አመታት በአገሪቱ የከፉ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽምና ልጃገረዶችን ሲጠልፍ የቆየውን ቦኮ ሃራም፣ ሙሉ ለሙሉ የመደምሰስ ግብ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ጦር የሚመሩት ሜጀር ጄኔራል ላኪ ኢራቦር ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፣ቡድኑ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይደመሰሳል ብለዋል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃሙድ ቡሃሪ እስካለፈው ታህሳስ ወር ቦኮ ሃራምን እንዲደመስስ ለጦር ሃይላቸው ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ካለፈ 8 ወራት መቆጠራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤የጦሩ መሪ ሜጀር ጄኔራል ላኪ ኢራቦር በሰጡት መግለጫ፣ ቦኮ ሃራምን ለመደምሰስ የቀረው የሳምንታት ጊዜ ብቻ እንደሆነ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ሶስት ያህል ጠንካራ ይዞታዎችን በቁጥጥር ስር አድርጎ እንደሚገኝ የገለጹት ላኪ ኢራቦር፣ የጦር ሃይላቸው በሚወስደው የማያዳግም እርምጃ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመሰስ ገልጸው፣ በሽብር ቡድኑ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከአጎራባች አገራት የጦር ሃይሎች ጋር በተቀናጀ መልኩ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
ቦኮ ሃራም እ.ኤ.አ ከ2009 አንስቶ በናይጀሪያ፣ ቻድ፣ ኒጀርና ካሜሩን በፈጸማቸው አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶች ሳቢያ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውንና 2.3 ሚሊዮን ያህል የአገራቱ ዜጎች እንደተፈናቀሉም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

ታዋቂው የቴክኖሎጂ ምርቶች አምራች ኩባንያ አፕል፤ በአየርላንድ በሚያደርገው የንግድ እንቅስቃሴ በህገ-ወጥ መንገድ ሳይከፍለው የቀረውን የ14.5 ቢ ዶላር የግብር ዕዳ እንዲከፍል በአውሮፓ ህብረት አጣሪ ቡድን እንደተወሰነበት ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
ህብረቱ ለ3 አመታት ከዘለቀ ምርመራ በኋላ በኩባንያው ላይ ይህንን ክብረ ወሰን ያስመዘገበ የተባለ የግብር ቅጣት የጣለው አየርላንድ ለኩባንያው ያልተገባ የግብር ጥቅማ ጥቅሞችን በህገ ወጥ መንገድ መስጠቷን በማረጋገጡ ነው ተብሏል። አፕልና የአየርላንድ መንግስት ህብረቱ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ የገለጹ ሲሆን፣ ውሳኔው የኩባንያዎቼን ስኬት ለማደናቀፍ እየሰራ ነው ስትል ህብረቱን ስትከስ የቆየቺውን አሜሪካን ክፉኛ ያስቆጣል ብሏል - ዘገባው፡፡
 አየርላንድ የአሜሪካ ኩባንያዎች በስፋት ተሰማርተው ትርፋማ ለመሆን የሚያስችል ስራ እንዲሰሩ የከፈተቺው እድል ለውዝግቡ መነሻ እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡


                       - ከአልባግዳዲ ቀጥሎ የቡድኑ ሁለተኛው ቁልፍ ሰው ነበር
      የሽብርተኛው ቡድን አይሲስ ቃል አቀባይ በመሆን ሲሰራ የቆየውና በቡድኑ የአስተዳደር መዋቅር ሁለተኛው ቁልፍ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት አቡ ሞሃመድ አል አድናኒ፤ ሶርያ ውስጥ መገደሉን ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
አይሲስ ግድያውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ አል አድናኒ ሶርያ ውስጥ በምትገኘው አሌፖ አካባቢ የሚካሄዱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በሚቆጣጠርበት ወቅት ለህልፈት መዳረጉን ይግለጽ እንጂ፣ የሞቱን ሰበብ በተመለከተ በይፋ ያለው ነገር እንደሌለ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ የሽብር ቡድኑ የአል አድናኒን የሞት መንስኤ ባይናገርም፣ የከፍተኛ አመራሩን ሞት ለመበቀል ቁርጠኛ አቋም መያዙን እንዳስታወቀ የጠቆመው ዘገባው፤ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን፣አል አድናኒ በአልባብ ከተማ በተፈጸመበት የአየር ላይ ጥቃት መገደሉን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን ጠቅሷል፡፡
አል አድናኒ በሽብር ቡድኑ ታሪክ የተገደለ ከፍተኛው ባለስልጣን ነው ያለው ዘገባው፤ግለሰቡ የአይሲስ መሪ የሆነውን አቡበከር አልባግዳዲን ይተካል ተብሎ የሚጠበቅ ቁልፍ ሰው እንደነበር ጠቁሟል፡፡ ሟቹ የአይሲስ ቀንደኛ መሪ አል አድናኒ፤ የሽብር ቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ መሃንዲስ እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፤ከቡድኑ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ያልተናነሰ ቁልፍ ሚና ሲጫወት እንደነበርና ቡድኑን ለመደምሰስ በተደረጉ ዘመቻዎች በተሳተፉ የተለያዩ አገራት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ያስተላለፈውም እሱ እንደነበር ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1977 ሶርያ ውስጥ የተወለደው አቡ ሞሃመድ አል አድናኒ፣ የሽብር ቡድኑ ከቡድንነት አልፎ ራሱን የቻለ እስላማዊ  መንግስት አቋቁሞ የመምራት አላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ በይፋ ያስታወቀ የመጀመሪያው ሰው እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የሰሜን ኮርያ መንግስት፤ ከአገሪቱ ከፍተኛ ሚኒስትሮች አንዱ የነበሩትንና  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የትምህርት ዘርፍ ሃላፊ ሆነው ሲሰሩ የቆዩትን ኪም ዩንግ ጂንን፣ባለፈው ወር ገድሏል ስትል ደቡብ ኮርያ መናገሯን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ባለፈው የካቲት ወር ላይም ተገድለዋል ተብሎ ተወርቶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ይሄም ሆኖ ግን ከቀናት በኋላ በፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ሲካፈሉ መታየታቸውን ጠቁሞ ይሄኛው የደቡብ ኮርያ መረጃም አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል ገልጧል፡፡
ሰሜን ኮርያ ተገደሉ የተባሉትን ሚኒስትር በተመለከተ እስካሁን ያለቺው ነገር እንደሌለ የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ መንግስት በቅርቡ የሚኒስትሩን ቦታ ተክቶ የሚሰራ ሌላ ሚኒስትር ከሾመ የመሞታቸው ነገር እርግጥ ሊሆን ይችላል መባሉን አመልክቷል፡፡
የሰሜን ኮርያ መንግስት ከዚህ ቀደምም ከፍተኛ ባለስልጣናቱንና ሚኒስትሮችን በድብቅና በይፋ በወሰዳቸው እርምጃዎች መግደሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ትዊተር ባለፈው አመት ብቻ ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉ መልዕክቶችን አሰራጭተዋል ያላቸውን የ360 ሺህ የትዊተር ተጠቃሚዎች አካውንቶችን በመዝጋት ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡ እነዚሁ አካውንቶች ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉ መልዕክቶችን በማስተላለፍና ግለሰቦችን በማስፈራራት ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው እንዲዘጉ መደረጉን ያስታወቀው ኩባንያው፤ከእነዚህም መካከል 235 ሺህ የሚሆኑት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ እንደተዘጉ ገልጧል፡፡
ተቀማጭነቱን በሳን ፍራንሲስኮ ያደረገው ትዊተር የሚተዳደርበት ፖሊሲ፣ ሽብርተኝነትን ማስፋፋትን እንደማይፈቅድ ገልጾ፣ በቀጣይም በተመሳሳይ ህገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ተጠቃሚዎቹን እየተከታተለ አካውንታቸውን እንደሚዘጋ አስታውቋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቀበሮ ጉሮሮው ውስጥ አጥን ተቀርቅሮበት በጣም ሲሰቃይ ዋለ፡፡ ወደማታ ላይ አንዲት ረዝም ኩምቢ ያላት ወፍ አገኘና እንዲህ አላት፡-
“ወፊት ሆይ”
“አቤት” አለች ባለ ኩምቢዋ ወፍ፡፡
“አንድ ነገር ልለምንሽ?”
“የምችለው ከሆነ ምን ቸገረኝ”
“የምትችይው ነገር ነው፡፡ በዚያ ላይ ለውለታሽ ዋጋሽን እከፍላለሁ”
“ምን ትከፍለኛለህ?”
“የፈለግሺውን፡፡ ብቻ ከአቅሜ በላይ አይሁን”
“እሺ፡፡ እንግዲያው እኔን የሚያሳድዱኝ ጠላቶች አሉኝ፡፡ እነሱን አሳደህ ታጠቃልኛለህ?”
“ይሄማ በጣም ቀላል ነው፡፡ ብቻ አንቺ የምጠይቅሽን ፈፅሚልኝ”
“ምንድን ነው እንዳረግልህ የፈለግኸው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“ጉሮሮዬ ውስጥ አጥንት ተቀርቅሮ እያሰቃየኝ ነው፡፡ ስለዚህ ኩምቢሽን አፌ ውስጥ አስገብተሸ እንደ ምንም ብለሽ አውጪልኝ” አላት፡፡
“ይሄ ለእኔ ቀላል ነው፡፡ ፊትህን ወደ ብርሃን መልስና አፍህን በደምብ ክፈተው” አለችው፡፡
ወፊቱ ኩምቢዋን እጉሮሮው ድረስ አስገብታ አጥንቱን ጎትታ አወጣችለት፡፡ እፎይ አለ ቀበሮው፡፡
ከዚያም ወፊቱ፤ “በል እንደተዋዋልነውና ቃል እንደገባህልኝ ወደ ጠላቶቼ ልውሰድህና ተበቀልልኝ” አለችው፡፡ ቀበሮም ቃሉን አጠፈና፤
“ቀበሮ አፍ ውስጥ ገብቼ በሰላም ወጥቻለሁ፤ ብለሽ በኩራት መናገርሽ ይበቃሻል፡፡ ከፊቴ ጥፊ!” አለና አባረራት፡፡ ወፊቱም አቅራቢያዋ ወዳለው ዛፍ ላይ ወጣችና፤
“ሌላ አጥንት ጉሮሮህ ላይ የማይቀረቀር እንዳይመስልህ፡፡ ያኔ ምን እንደሚውጥህ እናያለን” አለችው፡፡ ከአካባቢው በርራ ጠፋች፡፡
*             *          *
በአንድ አገር ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ አንዱ ትልቅ ቁምነገር ለህዝብ ቃል መግባት ነው፡፡ ይህን ቁምነገር የሚያረክሰው ደግሞ የገቡትን ቃል ማጠፍ ነው፡፡ የገቡትን ቃል ማጠፍ ዕምነትን ያጠፋል፡፡ ዕምነተ-ጎዶሎ አመራር ደግሞ በጄ ብሎ መንግሥትን አምኖ የሚገዛ ህዝብ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሰላምን ያደፈርሳል፡፡ ጥርጣሬንና እየተገላመጡ መኖርን ያገዝፋል፡፡ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ከሀገር መሰደድን ያበዛል፡፡ ማንም ማንንም የማያምንበት፣ ነፃነቱን የሚጠራጠርበት፣ እኩልነቱን የማይቀበልበት፣ የሕግን የበላይነት በወጉ የማይረዳበት፣ ለምንም ነገር ብቃት እንዳለው የማይተማመንበት፣ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያዊነቱን ለጥያቄ የሚዳርግበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ሊገደድ የሚችልበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል። ስለዚህም ልንፈፅም የምንችለውን ቃል ብቻ በአደባባይ መናገር ብልህነት ነው፡፡ መንገዶች ሁሉ ሁሌ አልጋ ባልጋ ላይሆኑ እንደሚችሉ እንገንዘብ፡፡ መንገዶች ሁሉ ሁሌ ወደ ሮማ አይወስዱም፡፡ ሁሌም “የአፈፃፀም ችግር ነው” እያልን እንደማንዘልቅ እናስብ፡፡ ይልቁንም እቅዳችንን እንፈትሽ፡፡ ራሳችንን ወደ ውስጥ እንይ። እርስ በርሳችን ምን ያህል እንተማመናለን፤ ብለን እንጠይቅ፡፡ ስንወሻሽ እንጠያየቅ፡፡ በችግር ላይ ችግር ለምን ይደራረብብናል? ብለን እንጠይቅ፡፡ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ወደ ኃይል መሄድ ከትርፉ ኪሳራው የሚያመዝን ሁነት መሆኑን እንይ፡፡ ከቶውንም ኃይል ከቀውስ ወደቀ ውስ ሊከተን እንደሚችል ልብ እንበልና ልብ እንግዛ፡፡ “መካር የሌለው ንጉሥ፣ ያለ አንድ ቀን አይነግሥ” የሚለውን ተረት እናስታውስ። “እንደ ንጉሡ አጎንብሱ” የሚለው ተረትም ሁልጊዜ አያበላም፡፡ ጊዜው ያለፈበት ነውና፡፡ ይልቁንም ሐምሌት የሚለንን ከአንጀታችን እናዳምጥ፡-
“በንጉሥ ፍርፋሪ የፋፋን ትል
አሣ አገኘችና፤ ቅርጥፍ
አሣ-አጥማጅ፣ እሷን ቅርጥፍ!
ሆድን ሞልቶ እንደስልቻ
በልቶ ለመበላት ብቻ!!”
ከሀገራችን የችግር ቁንጮዎች አንዱ አድር - ባይነት ነው፡፡ የጥንቱ የጧቱ ወዳጃችን ሌኒን፤ ‹‹The Pendulum of Opportunism never stops Oscillating›› ይላል፡፡ የአድር-ባይነት ፔንዱለም ዥዋዥዌውን አይተውም፤ እንደ ማለት ነው፡፡ አድር-ባይነት፣ ብቃት የጎደላቸው ሰዎች የኑሮ ዘዴ ነው። አጉል መካሪ ሀገር ያጠፋል፡፡ አድር - ባዮች አጉል መካሪ ናቸው፡፡ የራሳቸውን ጥቅም ለማካበት ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለምና፡፡ ልታይ ልታይ ያበዛሉ፡፡ አደባባይ ይደፍራሉ፡፡ በአደባባይ ቃል መግባት አይፈሩም፡፡ ልሳናቸው ስል ነው፡ በሀገር ተቆቋሪነት ስም የማይዘላብዱት ነገር የለም! እንደ እስስት መልካቸውን ይለዋውጣሉ፡፡ በሠርግ ላይ ዘፈን አውጪ፣ በልቅሶ ቤት ሙሾ አውራጅ ናቸው! ሁሉንም የሚያደርጉት ለግል ጥቅማቸው ነው፡፡ ስለሆነም የሙስና ፈታውራሪ ናቸው፡፡ ሆኖም ደግሞ ሙሰኞችን ሲኮንኑ ይሰማሉ፡፡ የግምገማ መሪ ተዋንያን ናቸው፡፡ አልባሳት የመቀያየር ክህሎት አላቸው፡፡ ከነዚህ ያልተጠነቀቀ አመራር ወይም መሪ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ተንሸራታችና አንሸራታች ናቸውና፡፡ አፋቸው እንጂ ግብራቸው እኩይ ነውና!
‹‹አጓጉል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት፤
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ!››
ይለናል ጋጣሚ ፀጋዬ ገብረመድህን፡፡ ይህን ልብ ማለት ይበጃል፡፡ ሌላው የሀገራችን ቁንጮ ችግር፤ ብሶትና ምሬትን ቸል ማለት ነው፡፡ ውስጥ ውስጡን የሚቀጣጠል እሳት አንድ ቀን የማይጠፋ ቋያ ይሆናል፡፡
‹‹ከጥንት ጀምሮ እኛ እንደምናውቀው
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው
ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን  ወጥር!››
ዛሬም ያው በረከተ-መርገም ነው! የህዝብን ብሶት እናዳምጥ፡፡ ችግርን ፊት ለፊት መጋፈጥና ተነጋግሮ፣ ተመካክሮ መፍታት እንጂ መሸፋፈኑ፤ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› የሚለውን የአበው ብሂል መዘንጋት ነው፡፡ ‹‹እንደ ድመት አሥራ ሶስት ነብስ ነው ያለን!›› ማለት አያዋጣም፡፡
‹‹እኛ አድገናል ሌሎች ችግር ገጥሟቸዋል›› ማለትም ብዙ አያራምድም፡፡ ያለው›› ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ..›› ነው፡፡ ህዝብ እየተቃወም ነው ሲባል፤ ‹‹በእነ እገሌ ምክንያት ነው› ማለትም ያው ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነው፡፡ የተቃውሞዎች ሁሉ ማጠንጠኛ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግር ነው›› ማለትም ያነው ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነው፡፡ የአባዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ (Blame-shifting) ያው ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በአፍ ቀላል ቢሆንም፣ በተግባር ግን እየተፈፀመ አለመሆኑን አለማመንም ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ነው፡፡ ከሁሉም ይሰውረን! አዲሱ ዓመት አዲስ አድማስ ያሳየን! ልብና ልቦና ይስጠን!!

የሆላንዱ ኩባንያ በባህር ዳር ተቃውሞ የ11.1 ሚ. ዶላር የአበባ እርሻ ተቃጠለብኝ አለ

   የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ ተቃውሞ ወደተስፋፋባቸው የአማራና የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች እንዳይጓዙና ህዝብ ከተሰበሰበባቸውና ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስጠነቀቀ፡፡
ተቃውሞ ወደተቀሰቀሰባቸው የአማራና የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች መሄድ ለአደጋ ያጋልጣል ያለው ሚኒስቴሩ፤ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች በ10 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ መገኘት እጅግ አደገኛ ነው ሲል ለዜጎቹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ባለፈው ሰኞ በባህር ዳር በተቀሰቀሰው ተቃውሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች የአበባ እርሻ ኢንቨስትመንቱን በእሳት በማጋየት፤ ሙሉ ለሙሉ እንዳወደሙት “ኢስሜራልዳ ፋርምስ” የተባለው የሆላንድ ኩባንያ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡11.1 ሚሊዮን ዶላር ያወጣሁበት የአበባ እርሻ ኢንቨስትመንት በእሳት ወድሞብኛል ያለው ኩባንያው፣ ሌሎች በአካባቢው የሚገኙና ንብረትነታቸው የእስራኤል፣ ጣሊያን፣ ህንድና ቤልጂየም ኩባንያዎች የሆኑ ዘጠኝ ያህል የአበባ እርሻዎችም በተቃዋሚዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ የኩባንያው ረዳት ስራ አስኪያጅ ሬምኮ ቤርካምፕ ለአልጀዚራ በሰጡት መግለጫ፣ ኩባንያው የተቃጠለውን እርሻ እንደገና አቋቁሞ፣ ኢንቨስትመንቱን ከማስቀጠል ይልቅ ኢትዮጵያን ለቅቆ የመውጣት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ሴንተር በየዓመቱ የሚያከናውነውና “ጳጉሜን ለጤና” የተሰኘው ነፃ የምርመራ አገልግሎት የፊታችን ማክሰኞ ይጀምራል፡፡
ማዕከሉ ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና የፓናል ውይይት ላይ የማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ያለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ላለፉት ሰባት ዓመታት የሲቲስካን፣ ኤምአርአይ እና ሌሎች የተለያዩ የምርመራ አገልግሎቶችን ገንዘብ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ህሙማን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ የሚመጡና የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች በሀኪሞቻቸው ታዞላቸው በገንዘብ ማጣት ምክንያት ምርመራውን ለማግኘት ያልቻሉ ህሙማን፤ ከጳጉሜ 1-5/ 2008 ዓ.ም ድረስ በማዕከሉ በሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ማዕከሉ ላለፉት ሰባት ዓመታት በየዓመቱ በሚሰጠው በዚህ ነፃ የምርመራ አገልግሎት፣ ከ15ሺህ በላይ ህሙማን ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም አገልግሎቱን በስፋት ለመስጠት ዕቅድ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ ዓመቱን ሙሉ ገንዘብ ከፍለው አገልግሎቱን ማግኘት ለማይችሉ ወገኖች ከሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መሪ ቃል፣ በየዓመቱ በሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት ከ800-1000 ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል፡፡ የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች በሃኪሞቻቸው ታዞላቸው በአቅም ማጣት፣ አገልግሎቱን ማግኘት ያልቻሉ ህሙማን በተጠቀሱት ቀናት ወደ ማዕከሉ በመሄድ፣ ምርመራውን በነፃ ማግኘት እንደሚችሉም አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በክፍለ ከተማው ለሚኖሩ ወገኖች ነፃ የአንቡላንስ አገልግሎትን ከመስጠቱም ሌላ የሲቲስካንና የኤምአርአይ ምርመራዎች የለሚያስፈልጋቸው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች መታወቂያቸውን ይዘው በመቅረብ፣ የ20 በመቶ ቅናሽ ለማግኘት እንደሚችሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

   በርካታ ታላላቅ ዓለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማቶችን በማስገባት ስኬታማ የሙዚቃ ጉዞውን የቀጠለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፤ በ2017 የዓለም የክብረወሰን መዝገብ በሁለት ክብረ ወሰኖች መመዘግቡን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዘ ዊክንድ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የ26 አመቱ ድምጻዊ፤ “ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” በሚለው የሙዚቃ አልበሙ ባለፈው የፈረንጆች አመት በ“ስፖቲፋይ” ድረገጽ ተጠቃሚዎች በብዛት በመታየቱና ሙዚቃዎቹ በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ለረጅም ተከታታይ ሳምንታት በምርጥ አስር ዝርዝር ውስጥ በመቆየታቸው፣ በአለም የክብረ ወሰን መዝገብ ላይ በሁለት ክብረ ወሰኖች ስሙን ማስፈሩ ተገልጧል፡፡
“ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘው የአቤል የሙዚቃ አልበም ከታህሳስ 2014 እስከ ታህሳስ 2015 ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በ60 ሚሊዮን የ“ስፖቲፋይ” ተጠቃሚዎች በመታየት ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን የጠቆመው ተቋሙ፣ የድምጻዊው ዘፈኖች ከመጋቢት 2015 እስከ ጥር 2016 ባሉት ጊዚያት፣ ለ45 ተከታታይ ሳምንታት በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ምርጥ አስር ደረጃ ውስጥ ተካትተው መቆየታቸውን ገልጧል፡፡