Administrator

Administrator

በየዓመቱ አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹን የሚያስነብበን ታዋቂው ወጣት ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፣ ዘንድሮም “ክቡር ድንጋይ” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ ለንባብ አቀረበ፡፡ ባለ 200 ገፁ መጽሐፍ ለገበያ የቀረበው በ45 ብር ነው፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም በ100ሺ ቅጂዎች የተቸበቸበለትን ዴርቶጋዳን ጨምሮ ራማቶሐራና ተከርቸም ሌሎች የረዥም ልቦለድ ሥራዎች ለንባብ ያቀረበ ሲሆን፤ በግጥም መድበሎቹም ዝናን ማትረፉ ይታወቃል፡፡

ነዋሪነቱ በሰሜን አሜሪካ በሆነው ገጣሚ ሳምሶን ይርሳው ጌትነት የተጻፈው ምልክት የተሰኘ የግጥም መድበል የገጣሚው ቤተሰቦችና የጥበብ አፍቃሪዎች በተገኙበት ትናንት በብሄራዊ ቤተ መዛግብት አዳራሽ ተመረቀ፡፡ከዚህ በፊት በአሜሪካ የተመረቀው የግጥም መድበሉ 100 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ግጥሞች ተካተውበታል፡፡ ለገጣሚው የመጀመሪያ ስራው እንደሆነ የተነገረለት መድበሉ በ23 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በቅርቡ “ላይፍ ሃፕንስ” የተባለ አዲስ አልበም በእስራኤል ለገበያ ያበቃችው ቤተእስራኤላዊቷ ድምፃዊት ኤስተር ራዳ፤ በእስራኤል የሙዚቃ ኢንዱስትሪ መድመቅ ጀምራለች ተባለ፡፡ የኤስተር ራዳ አዲስ አልበም አርቲስቷ ኢትዮጵያዊ የዘር ግንዷን ሙሉ ለሙሉ የገለፀችበት ነው ያለው “ኒውስፖይንት አፍሪካ” ፤ “ላይፍ ሃፕንስ” በተባለው ዘፈኗ ዋሽንትና ማሲንቆን እንደተጠቀመች ጠቅሷል፡፡ የ28 አመቷ ድምፃዊት፤ የዘፈን ግጥም ደራሲ እና ተዋናይቷ በአዲሱ አልበሟ ውስጥ “ላይፍ ሃፕንስ” የተሰኘውን የአልበሙን መጠርያ ጨምሮ “ሞንስተርስ”፤ “ኤኒቲንግ ፎር ዩ” እና “ኩድ ኢትቢ” የተባሉ ዘፈኖችን አካትታለች፡፡ በኢትዮ ጃዝ እና በሶል የሙዚቃ ስልቶች የተሰሩት የድምፃዊቷ ዘፈኖች በእስራኤላውያኖቹ እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች ኩቲ እና ሳቦ የተቀናበሩ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኤስተር ቤተሰቦች እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም በተከሰተው ረሃብ ሳቢያ ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ እስራኤል የተሰደዱ ሲሆኑ ኤስተር የተወለደችው ቤተሰቦቿ እስራኤል ገብተው ኪራያት ኡባ በተባለ ስፍራ መኖር ከጀመሩ ከአንድ አመት በኋላ ነው፡፡ ኤስተር እና ቤተሰቧ 10ኛ ዓመቷን እስክትይዝ ድረስ በሄብሮን ዳርቻ የኖሩ ሲሆን እድሜዋ ለእስራኤል የውትድርና አገልግሎት ሲደርስ ወደ ውትድርናው ገብታ እግረመንገዷን እዚያው በነበረ የሚሊታሪ ባንድ ድምፃዊ በመሆን ሰርታለች፡፡

ቤተእስራዔላዊ ብትሆንም በፀጉረ-ልውጥነቷ ብዙ አሳዛኝ ገጠመኞችን በወጣትነቷ ያሳለፈችው ኤስተር፤የሚሰማትን የመገለል ስሜት በሙዚቃዋ ስትከላከልና ስትዋጋ እንደኖረች አልደበቀችም፡፡ የውትድርና አገልግሎቷን ከጨረሰች በኋላ ኑሯዋን በቴል አቪቭ በማድረግም ወደ ትወና ሙያ እንደገባች ትናገራለች፡፡ በተዋናይነቷ የቴሌቭዥን ፊልሞች የሰራችው ኤስተር፤ ከአራት በላይ የሙሉ ጊዜ ፊልሞች ላይ መተወኗንና “ስቲል ዎኪንግ” እና “ዘ ሩቫቤል” የተባሉት ሁለት ፊልሞች በእስራኤል ፊልም አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡

በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ በደሴ ከተማ ውስጥ ይገነባል ለተባለው የወሎ ተርሸሪ ኬርና ቲቺንግ ሆስፒታል ግንባታ የሚውል ገቢ የማሰባሰብ ሥራ በይፋ ተጀመረ፡፡ ለሆስፒታሉ ማሰሪያ የሚሆን ገቢ የማሰባሰቡ ሥራ ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ በይፋ በተከፈተበት ወቅት እንደተገለፀው፤ ሆስፒታሉ በብሔራዊ ደረጃ ከፍተኛ የህክምና ተቋም እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪ የስልጠናና የምርምር ማዕከል ይሆናል፡፡ ከ750 በላይ አልጋዎች ይኖሩታል ለተባለው ለዚህ ሆስፒታል ግንባታ፤ የወሎ ተወላጆች የሆኑ ባለሀብቶችና በውጭ አገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የክልሉ ተወላጆች የሆኑ ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በሸራተን አዲስ በተካሄደው ፕሮግራም ላይ እንደተገለፀው፤ በመጪው ዓመት የሆስፒታሉ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ዓመት እንዲሆን እቅድ ተይዟል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ጢጣ በተባለው ሥፍራ ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚውል 40 ሄክታር መሬት የሰጠ ሲሆን የሆስፒታሉ የመሰረት ድንጋይም ህዳር 16 ቀን 2004 ዓ.ም የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚ/ር እና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጐበዜና የፕሮጀክቱ የበላይ ጠባቂ ሼክ አሊ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ በተገኙበት መቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡

ከነአያ አንበሶ በታች ያሉት የዱር አራዊት ሁሉ ተሰብስበው ትልቅ ግብዣ ተደረገና ዳንሱ፣ ጭፈራው፣ ዳንኪራው ቀለጠ! ደራ!
ከደናሾቹ መካከል ጥንቸል ተነስታ፤
“ዝም ብለን ከምንደንስ እንወዳደርና ምርጥ ዳንሰኛው ይለይ!” አለችና ሃሳብ አቀረበች፡፡
በሃሳቡዋ ሁሉም ተስማሙና ጭፈራው ቀጠለ፡፡ ሁሉም በተራ በተራ ወደ መድረክ እየወጣ ችሎታውን አሳየ፡፡
በመጨረሻ ዳኞች ተሰይመው ውጤት ተነገረ፡፡ በውጤቱ መሰረት አንደኛ - ዝንጀሮ፣ ሁለተኛ ቀበሮ፣ ሶስተኛ - ጦጣ ሆኑ፡፡
ዝንጀሮ መመረጡን በማስመልከት መድረክ ላይ ወጥቶ ተጨማሪ ዳንስ በማሳየት ታዳሚዎቹን አራዊት አዝናና፡፡ ንግግርም አደረገ፡፡
አራዊቱ በጣም በመደሰት ንጉሣችን ይሁን ብለው ወሰኑ፡፡
በዝንጀሮ ንጉሥ መሆን ቀበሮና ጦጣ ቅናት እርር ድብን አደረጋቸው፡፡ ስለዚህ መዶለት ጀመሩ፡፡
ጦጣ፤ “አያ ቀበሮ መቼም ከዳኝነት ስተት ነው እንጂ ዝንጀሮ ከእኛ በልጦ አይመስለኝም፡፡ አንተስ ምን ይመስልሃል?”
ቀበሮም፤
“እኔም እንዳንቺው ነው የማስበው፡፡ የዘመድ ሥራ ነው የተሰራው፡፡ ግን አንዴ ሆኗል ምን ይደረጋል?”
ጦጣ፤ “አንዴ ሆኗል ብለንማ መተው የለብንም”
ቀበሮ፤ “ምን እናደርጋለን ታዲያ?”
ጦጣ፤ “እኔ ወጥመድ ላዘጋጅ፡፡ አንተ እንደምንም ብለህ ወጥመዱጋ አምጣልኝ” አለችው፡፡ “ወጥመድ ላይ ሥጋ አድርጌ እጠብቃችኋለሁ፡፡ አንተ ዝንጀሮን ትጋብዘዋለህ”
ቀበሮ በሃሳቡ ተስማምቶ ዝንጀሮን ሊያመጣው ሄደ፡፡
ዝንጀሮ በአዲስ የሹመት ስሜት እንደሰከረ፤ እየተጐማለለ ይመጣል፡፡
“ይህን የመሰለ ሙዳ ሥጋ አስቀምጬልሃለሁ” አለው ወደ ሥጋው እያሳየው፡፡
ዝንጀሮም፤ “አንተስ? ለምን አልበላኸውም?” ይሄን የመሰለ ሙዳ እንዴት ዝም አልከው?” አለው፡፡
ቀበሮ፤ “ውድ ዝንጀሮ ሆይ! ለንግሥናህ ክብር ይሆን ዘንድ ብዬ ያዘጋጀሁት ነውና ስጦታዬን ተቀበለኝ?” አለው እጅ በመንሳት፡፡
ዝንጀሮ “ስጦታህን ተቀብያለሁ፤” ብሎ ወደወጥመዱ ዘው አለ፡፡ እዚያው ታስሮ ተቀረቀረ!!
ተናደደ!! በምሬትና በቁጭት በደም ፍላት ተናገረ፤
“ለዚህ አደጋ ልትዳርገኝ ነው ለካ ያመጣኸኝ? አንት ሰይጣን! ለንዲህ ያለ ወጥመድ ነበር ለካ ስታባብለኝ የነበረው? አረመኔ!” አለው፡፡
ቀበሮም፤ እየሳቀ፤
“ጌታዬ ዝንጀሮ ሆይ! የአራዊት ንጉሥ ነኝ እያልክ፤ ግን እቺን ቀላል አደጋ እንኳን ማለፍ አልቻልክም!” ይሄ የመጀመሪያ ትምህርት ይሁንህ ብሎ ጥሎት ሄደ፡፡
***
“ሹመት ያዳብር” የሚለውን ምርቃት የሀገራችን ህዝብ ጠንቅቆ ያቃል፡፡ በልቡ ግን “አደራዬን ተቀበል” የሚል ጠንካራ ማስጠንቀቂያና ጠንካራ መልዕክት ልኮ ማስገንዘቡ ነው፡፡ ካልሆነ አደራ በላ ትሆናለህ!
አደራ! ሲባል፤ የመብራት የውሃዬን ነገር አደራ ማለቱ ነው፡፡
አደራ! ሲባል፤ የትምህርትን ነገር ጠንቅቀህ ምራ ማለት ነው፡፡ ውስጡን በደምብ መርምር ማለት ነው፡፡
አደራ ሲባል፤ የኢንዱስትሪውን ሂደት፤ የትራንስፖርቱን (የባቡሩን፣ የመኪናውን፣ የአየሩንና የእግሩን ጉዞ) ነገር በቅጡ በቅጡ ያዙት ማለት ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃውንና የሳይንስና ቴክኖሎጂው ጉዳይ ዕውነተኛ አሠራር፣ ብስለትና ከዓለም ጋር የሚሄድ እንዲሆን ማድረግ ዋና ነገር ነው ማለት ነው፡፡
አደራ! ሲባል በተለይ የገቢዎችን ነገር፣ እከሌ ከእከሌ ሳትሉ ኢወገናዊ በሆነ ዐይን በማየት፤ የታረመ፣ የተቀጣ፣ ከስህተቱ የተማረ አካሄድ እንድትሄዱ ማለት ነው፡፡
አደራ ሲባል በአጭሩና በጥብቁ ቋንቋ
“አደራ - በላ አትሁኑ” ማለት ነው፡፡
በተለምዶ እኛ አገር “ባለፈው ሥርዓት” የሚል ፈሊጥ አለ፡፡ “ያለፈው ሹም ጥፋተኛ ነበር፣ ደካማ ነበር እኔ ግን አንደኛ ነኝ…” ዓይነት አንድምታ ያለው ነው ያለፈው ሹም የበደላችሁን እኔ እክሳለሁ! እንደማለትም አለበት፡፡ ይህን እንጠንቀቅ፡፡
የተሻሪም የተሿሚም ሂደት ተያያዥ ሥርዓት ነውና ሰንሰለቱ ተመጋጋቢ ነው፡፡ እንጂ የወረደው ጠፊ፣ የተሾመው ነዋሪ ነው ማለት አይደለም፡፡ በቅንነት፣ በሰብዓዊነት፣ በለሀገር አሳቢነት ካላየነው፤ ሁሉም ነገር ከመወነጃጀል አይወጣም፡፡ በተሰበሰበ ቀልብ፣ በሙያ ክህሎትና በዲሞክራሲያዊ አረማመድ ነው ፍሬያማ ለመሆን የሚቻለው፡፡ ያንን ካልተከተልን “ንጉሥ ነኝ እያልክ ይቺን ቀላል አደጋ እንኳን ለማለፍ አቃተህ” እንባባላለን፡፡
ጐባጣውን የምናቃናው፣ ጐዶሎውን የምንሞላውና የምናስተካክለው፤
መዋቅር የምናጠናክረው፣ እዚህጋ ተሳስተናል እንተራረም የምንባባለው፤ ለሀገር ይበጃል፣ ብለን ነው፡፡ የሾምነውና ያስቀምጥነው ሰው ተስተካክሎ የተበጀውን ሥርዓት ለግል ጥቅሙ ካዋለ፤ አደራውን ከበላ፣ አድሎኛ ከሆነ፣ በመጨረሻም ያለውን ሁኔታ ከመጠበቅ አልፎ በማሻሻል፤ ለውጥ ካላመጣ፣ የወላይትኛው ተረት እንደሚለው፤ “ፈርጅ ያለው ነጠላ አሰርቼ፤ መልክ የሌለው ሰው ይለብሳል” ሆነ ማለት ነውና ከወዲሁ እንጠንቀቅ፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”ን እንዋጋ!
“ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፡፡ መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው” የሚለውንም አንዘንጋ!

“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት በታፈኑ ዕውነቶች አምድ ላይ ለንባብ ባበቃው “ቀናት የሚታደጓቸው እድሜ ልኮች” የሚል ተንታኝ ሃተታ (ፊቸር ስቶሪ) የዓለም አቀፉን የጋዜጠኞች ማዕከል (ICFJ) የሁለተኛ ደረጃ ቀዳሚ ሽልማት አሸነፈ፡፡ ማዕከሉ ከአፍሪካ የጤና ጋዜጠኞች ማህበር እና ከአረብ ሚዲያ ፎረም ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በክትባት ጉዳይ ላይ የሚያተኩር የዘገባ ውድድር ላይ 200 የእስያ፣ የአፍሪካና ስድስት የባህረሰላጤው አገራት ሚዲያዎች እንደተሳተፉ ታውቋል፡፡
መጽሔቱ በኢትዮጵያ የክትባት ተደራሽነት አናሳ መሆኑን አስመልክቶ የሰራው ተንታኝ ሃተታ፤ ከመላው አፍሪካ፣ ከእስያና ከባህረሰላጤው ሀገራት ሚዲያዎች ጋር ተወዳድሮ ነው ያሸነፈው፡፡
ከ14 ሀገራት በተውጣጡ በሙያው አንቱ በተባሉ ጋዜጠኞች በተዋቀረው ኮሚቴ በተሰጠው ዳኝነት ከ200 ዘገባዎች ውስጥ የአዲስ ጉዳይ “ቀናት የሚታደጓቸው እድሜ ልኮች” ከሁለተኛ ደረጃ ተሸላሚዎች የአንደኝነት ደረጃን ለማግኘት ችሏል፡፡
“ኢትዮጵያን ወክለን መወዳደራችንና ማሸነፋችን ዝግጅት ክፍሉን በጣም አስደስቶታል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት አዲስ ጉዳይን በአዲስ መልክ ለአንባቢያን ለማቅረብና በይዘቱ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ አድርገን በባለሙያዎች የሚሰራ መጽሔት ለማድረግ ከልዩ ልዩ ዘርፎች ባለሙያዎችን እና አማካሪዎችን ቀጥረን እየተንቀሳቀስን ባለንበት ወቅት ይህ ውጤት መገኘቱ ሞራላችንን ገንብቶታል፡፡ ለበለጠ ስራም አነሳስቶናል” ብሏል የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን፡፡
የውድድሩ ዋና አላማ በክትባት ማጣት ሳቢያ በየዓመቱ ህይወታቸውን የሚያጡ ህጻናትን ቁጥር ለመቀነስና ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚዳረጉ ዜጐችን ጤና መታገድ የሚያስችል እውቀት መፍጠር ሲሆን የመጽሔቱ ዘገባ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በማሳየት ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረውና መንግስትም ክፍተቶቹን እንዲደፍን መረጃ የሚያስጨብጥ ነው ተብሏል፡፡
ቢሮውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የአለምአቀፉ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጆይስ ባርናታን አሸናፊዎቹ ይፋ በተደረጉበት ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ “አሸናፊዎች ያቀረቧቸው ስራዎች እንደ ፖሊዮ ያሉ ከፍተኛ ጉዳት አድራሽ የሆኑ ነገር ግን በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን መቋቋምና ማሸነፍ የሚቻልባቸውን መንገዶች ያመላከቱ ትምህርት ሰጪ ዘገባዎች ናቸው፡፡ ለህዝባቸው እና ለጤና ባለሙያዎቻቸው እንቅፋትን አስወግደው ስኬትን የሚያገኙባቸውን መንገዶችም የጠቆሙ ናቸው” ብለዋል፡፡
በውድድሩ አንደኛ የወጡት የናይጀሪያ “ቲቪሲ ኒውስ” ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የፓኪስታኑ “ኒውስ ዋን” ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የኮትዲቩዋሩ “አቬኑ 225 ኒውስ ሳይት” ድረገጽ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች “ፊላንትሮፒ ኤጅ ማጋዚን” ሲሆኑ ጽሑፎቹ አንደኛ የወጡት ሚዲያዎቻቸው ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው የቴሌቪዥን ኔትወርኮች በመሆናቸውና በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በታገዘ ስርጭታቸው አህጉራዊ ሽፋን በመፍጠራቸው መሆኑን የውድድሩ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ ዋና አዘጋጁ አቶ ዮሐንስ እንዳለው፤ አዲስ ጉዳይ መጽሔት ከነዚህ ታዋቂ አህጉራዊ ሚዲያዎች ጋር ተወዳድሮ በ2ተኛ ደረጃ ተሸላሚነት ከተመረጡት የዩጋንዳው “ኤንቲቪ”፣ የፓኪስታኑ “ሳውዝ ኤሺያን ሜጋዚን”፣ እና የሳውዲአረቢያው “ሳውዲ ኒውስፔፐር ቱዴይ” ጋር የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ ይህ ውጤትም ኢትዮጵያውያን ሚዲያዎች በቴክኖሎጂ ቢታገዙና መልቲሚዲያ ቢሆኑ አህጉራዊ ተደራሽነትና ከየትኛውም አገር ጋር የሚፎካከር ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ያመላከተ ነው፡፡

የደደቢት የእግር ኳስ ክለብ የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› አሸናፊ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት ጨዋታ እየቀረው ደደቢት ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 17 አሸንፎ፤ በአራቱ አቻ ተለያይቶ እና በ3 ተሸንፎ 55 ነጥብ እና 35 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ነው፡፡ ደደቢት በአንድ ጨዋታ በአማካይ የሚያገባው 2.39 ጎሎች ሲሆን ይህም በሜዳው 2.91 ጎሎች ከሜዳው ውጭ ደግሞ በ1.92 ጎሎች የሚመነዘር ነው፡፡ ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቹ ላይ 59 ጎሎች አስቆጥሮ 24 ጎሎችን ያስተናገደው ክለቡ ጎል ማግባት ያቃተው በ1 ጨዋታ ብቻ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮንነቱም በ2014 በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ መሥራችና ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ለስፖርት አድማስ እንደገለፁት ክለቡ የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው ዕቅዱና አላማውን መሠረት አድርጐ በመንቀሳቀሱ ነው ብለው፤ በተገኘው ውጤት የትኩረት አቅጣጫው ለአገሪቱ እግር ኳስ ሙሉ አስተዋጽኦ ማበርከት መሆኑን አስመስክሮበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ክለቡ በ2002 ዓ.ም ፕሪምየር ሊጉን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀላቀል ለብሔራዊ ቡድን አንድ ተጨዋች ብቻ ማስመረጡን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ከአራት የውድድር ዘመን በኋላ ግን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተሳተፈው ብሔራዊ ቡድን 8 ቋሚ ተሰላፊዎችን ከማስመረጡ በላይ ከአፍሪካ ዋንጫውም በኋላ ከክለቡ 11 ተጨዋቾች ተመልምለው 9ቱ በቋሚነት ተሰላፊነት ማስመረጥ መቻሉ ዓለማውን ያንፀባረቀ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ደደቢት ፕሪሚዬር ሊግን መሳተፍ በጀመረ በ4ኛ የውድድር ዘመኑ ላይ የመጀመሪያውን የሻምፒዮንነት ክብር መጐናፀፉ በክለቡ ታሪክ አበይት ምዕራፍ የሚከፍት ነው ያሉት የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አብዱራሂም፤ዘንድሮ ውድድሩ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያነት ተዘጋጅቶ ደደቢት ዋንጫውን መውሰዱ ልዩ ታሪክ እና ትርጉም ሰጥቶታል ብለዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘት ከክለቡ ባለድርሻ አካላት ባሻገር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ሞተር ሆነው ወሳኝ ሚና በመጫወት፤ የክለቡን ሞራል በመገንባትና የሚሰራን በማነሳሳት መመስገን ያለባቸው እግር ኳስ አፍቃሪያን ናቸው፤ በማለትም ኮሎኔል አወል ለስፖርት ቤተሰቡ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ለደደቢት የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮናነት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ወዲያውኑ በማድረስ የፈፀመው ተግባር በጣም እንደማረካቸው የሚናገሩት ኮሎኔል አብዱራሂም ከከፍተኛ ፉክክር በኋላ ለአሸናፊው ወገን አድናቆት መስጠት በአርአያነት ሊታይ የሚገባው ነው፤ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከአመት ወደ አመት የፉክክር ደረጃው እያደገ መጥቷል የሚሉት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም፤ ክለቦች ለመሸናነፍ በጥሩ ፉክክር መወዳደራቸው፣ በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ተቀራራቢ ነጥቦች መስተዋላቸው እንደሚበረታታ አስገንዝበው በየመካከሉ ኢንተርናሽናል ውድድሮች በዝተው በውድድር ፕሮግራሞች ላይ በሚፈጠሩ መዛባቶች ከሚያመጡት የመቀዛቀዝ ችግር በስተቀር ጠንካራና ፈታኝ የውድድር ዘመን አሳልፈናል ብለዋል፡፡ ከ4 የውድድር ዘመን በፊት ደደቢት ፕሪሚዬር ሊጉን ለመጀመርያ ጊዜ ሲቀላቀል ባልተጠበቀ ሁኔታ ከባድ ፉክክር በማሳየት የፕሪሚዬር ሊጉን የመጀመርያ ዙር በመሪነት ቢያጠናቅቅም የውድድር ዘመኑን በ2ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰው፡፡ በዚሁ የውድድር ዘመን ግን ክለቡ በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር ከፍተኛ ደረጃ ባለው የጥሎ ማለፍ ውድድር ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል፡፡ ካች አምና በኮንፌደሬሽን ካፕ እየተወዳደረ በመጀመርያ ዙር ማጣርያ ከውድድር የተሰናበተው ክለቡ በፕሪሚዬር ሊጉ ደግሞ ከቡና እና ጊዮርጊስ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ አጠናቅቋል፡፡ አምና በፕሪሚዬር ሊጉ ለ3ኛ ጊዜ ተሳትፎ በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ደደቢት በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የመሳተፍ እድል አግኝቶ እስከ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ በመጓዝ ተስፋ ሰጭ ውጤት አሳይቷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ክበብ ሠራተኞች በደል እንደሚፈፀምባቸው ተናገሩ የብሔራዊ ባንክ ክበብ አስተዳደር፣ በሠራተኞቹ ላይ በደል እንደሚፈፅምና ያለ ህግና ማስጠንቀቂያ ከሥራ እንደሚያባርር በደል ደረሰብን ያሉ የክበቡ ሠራተኞች ገለፁ፡፡ የባንኩ የሠራተኞች ክበብ ከባንኩ ሠራተኞች በተጨማሪ ለውጭ ተጠቃሚዎች አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የሠርግ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ላለፉት 20 ዓመታት ሲሠራ የቆየ ሲሆን በክበቡ ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ተቀጥረው በቋሚነት ሲያገለግሉ የቆዩ 92 ሠራተኞች ለረዥም ዓመታት ዕድገትና የደሞዝ ጭማሪ አግኝተው እንደማያውቁ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የአመት እረፍት፣ የህመም ወይም የወሊድ ፈቃድ የሚባል ነገር ያልተለመደና እንደ መብትም እንደማይቆጠር ነው በቅርቡ ከስራቸው የተባረሩ የክበቡ ነባር ሠራተኞች የገለፁት፡፡

ሠራተኞቹ በህመምና በሐዘን ምክንያት ከሥራቸው ሲቀሩ በጥበቃ ሠራተኞች ወደ ውስጥ እንዳይገቡ እንደሚከለከሉና በሥራ ላይ እያሉ ለሚደርስባቸው አደጋና የአካል ጉዳት ምንም ዓይነት ህክምና እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡ በሥራ ላይ እያለች እግሯ ላይ ቢላ ወድቆ በደረሰባት ጉዳት ለከፍተኛ ህመም የተዳረገችው የክበቡ ሠራተኛ፤ ከጉዳቷ ጋር በተገናኘ የሥራ ገበታዋ ላይ ባለመገኘቷ ደሞዟ እንደተቆረጠባት ሠራተኞቹ ይናገራሉ፡፡ ሌለው የክበቡ ሠራተኛም ፔርሙዝ ይዞ ደረጃ ላይ ሲወጣ ተንሸራቶ በመውደቁ እግሩ ቢሰበርም የሰበረውን ፔርሙዝ ሂሣብ እንዲከፍል ተደርጐ ከሥራ መሰናበቱን እነዚህ ሠራተኞች ይገልፃሉ፡፡ በክበቡ ውስጥ ለ15 ዓመታት በወጥ ቤት ኃላፊነት የሰሩትና ከህግና ስርዓት ውጭ ያለ ማስጠንቀቂያ የተባረሩት አቶ ቀፀላ ተሾመ፤ የበዓላት ቀናትን ጨምሮ የተለያዩ የትርፍ ጊዜ ሥራዎችን ቢሠሩም የሚያገኙት የትርፍ ሰዓት ክፍያ በሰዓት 3 ብር ብቻ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ከሥራ ገበታቸው ላይ እንዲታገዱ ከተደረጉ በኋላም ወደ ውስጥ ገብተው ዕቃቸውን ለማውጣት እንኳን መከልከላቸውን የገለፁት አቶ ቀፀላ፤ ቀሪ ደመወዛቸውን ለመውሰድ ወደ መ/ቤታቸው ቢሔዱም ወደ ውስጥ መግባት እንደማይችሉ ተነግሮዋቸዉ፣ ገንዘብ ከፋይዋ ውጪ ድረስ ወጥታ እንደከፈለቻቸው ተናግረዋል፡፡ ከአቶ ቀፀላ ተሾመ ጋር ከሥራ ከታገዱት ሠራተኞች መካከል ወ/ሮ ሰላም አማኑኤል እና ወ/ሮ መሠረት ደምሴ በበኩላቸው፤ የክበቡ አስተዳደር ለሠራተኛው ደንታ የሌለውና የሠራተኛውን መብት ለማክበር ፈፅሞ የማይፈልግ መሆኑን ጠቁመው፤ መብቱን የጠየቀ ሠራተኛ እጣ ፋንታው ከሥራ መታገድ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። በክበቡ ውስጥ ለሃያ ዓመት የሠሩ ሠራተኞች ቢኖሩም ሁሉም ሠራተኛ ቋሚ አይደለም እየተባለ ኃላፊዎች በፈለጉት ጊዜና ሰዓት ከሥራው ሊያፈቅናሉት እንደሚችሉ ስለሚያስፈራሩ መብታቸውን ለማክበር ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱ ሠራተኞች አለመኖራቸው፣ ለሃላፊዎቹ የልብ ልብ ሰጥቶ እንደፈለጉ እንዲገዙን አድርጓቸዋል ብለዋል - ተበዳዮቹ፡፡ የሠራተኞቹን ቅሬታ አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡን የክበቡን የሥራ ኃላፊዎች ለማግኘት ባደረግነው ጥረት ከብዙ እንግልት በኋላ የክበቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መሰረትን ብናገኝም ጥያቄዎችን ማቅረብ ከመጀመራችን “ሥራችንን እያወካችሁ ነው” በማለት በጥበቃ ሠራተኞች ከቢሮአቸው ተገደን እንድንወጣ አድርገዋል፡፡

Saturday, 29 June 2013 11:08

አዘኔታ!

ምሽቱ ገፍቷል፤ ለኮሌጁ ዘበኞች ደግሞ በጣም ገፍቷል፤ አንድ ተማሪ የግቢውን በር ማንኳኳት የሚፈቀድለት እስከ ምሽቱ 4፡30 ድረስ ነው፤ አሁን 4፡40 ሆኗል፤ በጣም መሽቷል፤ በዚህ ሰዓት ደፍሮም የሚያንኳኳ ተማሪ የለም፤ ዘበኞቹም አዝነው አይከፍቱም፡፡ አሁን ወደ ግቢው ለመግባት ሁለት አማራጮች ናቸው ያሉት፡፡ አንድ፣ በአጥር መዝለል ሌላም፣ዘበኞቹን በጥቂት ብሮች መደለል፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው አደጋ አላቸው፡፡ በአጥር ሲዘል የተገኘ ተማሪ ቢያንስ ለአንድ ሴሚስተር ከኮሌጁ ይታገዳል። ዘበኞቹ ደግሞ እንደ ጉስቁልናቸው አይደሉም፤ በብር አይታለሉም፤ በዚህ ላይ ሁለት እና ሶስት ስለሚሆኑ እርስ በርስ ይጠባበቃሉ፤ብቻ ደረቆች ናቸው፤ በሰላም ጊዜ እንኳ ተማሪዎችን የሻይ ግብዣ አይቀበሉም፡፡ ሌላኛው የተሻለ እና ብቸኛ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ቤርጎ ማደር ነው፡፡ ክፋቱ ግን እርሱ ሁሉንም መፈፀም አይችልም፡፡

“አምላኬ! ምን አይነት ጣጣ ውስጥ ነው የከተትከኝ!” አባቱ ደግሞ ደውለው ነበር፡፡ አደራቸውን ለማደስ፡፡ እሺ ታዲያ አሁን የት ሄዶ ነው? ይህን ያህል ከቶም አምሽቶ አያውቅም፡፡ 4፡53 እንደ አለመታደል ሆኖ ጊዜውም የፈተና ወቅት ነው፡፡ ደብተርና መፅሃፎቼን ለአመል ያህል ልግለጣቸው እንጂ አንዲት ዐረፍተ ነገር እንኳ መረዳት አልቻልኩም፡፡ የስሜት ህዋሳቶቼ በሙሉ ውጭ ነው ያሉት፡፡ ጆሮዎቼ የበሩን መንኳኳት ይጠብቃሉ፡፡ ሲራመድ ዱቄት ላይ ይሄድ ይመስል ኮቴው ባይሰማም መተላለፊያው ላይ ኮቴ ባዳመጥኩ ቁጥር አይኖቼን በር ላይ እሰካለሁ፡፡ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት፣ ከዚያ ድምጹ እየራቀ ይሄዳል፡፡ ጸጥታ፡፡ ነፋስ፡፡ ኃይለኛ ነፋስ፡፡ በመኝታ ክፍላችን ውስጥም ከባድ ጸጥታ ሆኗል። ቀና ብዬ ሌሎች ሶስት የመኝታ ክፍል ጓደኞቼን ቃኘኋቸው፡፡ ሁሉም አንገታቸውን ወረቀት ላይ ደፍተዋል፡፡ ጭንቅላታቸውን መጽሐፍት ውስጥ ደብቀዋል፡፡

እስቲፋኖስ በመሰላቸት ደጋግሞ ፀጉርን ያካል፤ ይፎክታል፤ የዘወትር ልምዱ ነው፡፡ አትክልቲ ጉንጮቹን እጆቹ መዳፎች ውስጥ ቀብሮ ደብተሩ ላይ አድፍጧል፡፡ መኩሪያ አንዳች ነገር ይጫጭራል፣ ሲያጠና እጁ አያርፍም፤ ካልጻፈ አይገባውም ወይም የገባው አይመስለውም፡፡ ክፍላችንንም ቃኘሁት፡፡ ያልተጠረገ ቤት፣ ያልተነጠፈ አልጋ፣ የተዘበራረቁ መጻህፍት፣ ያልተከደነ ደብተር፣ በአልጋው ስር የወደቁ ካልሲዎች፣ ያለቁ እስኪርቢቶዎች… ዐይኔን ወደ ጓደኞቼ መለስኩት። ያልተበጠረ ፀጉር፣ የደፈረሱ አይኖች፣ የጎበጠ ትከሻ፣ መረጋጋት የማይታይበት ፊት… ጥናቴን ትቼ አይኔን ሳንከራትት ጭንቀቴ ገብቷቸው ሶስቱም ካቀረቀሩበት ቀና ቀና እያሉ በቦዙ ዓይኖቻቸው ሲያፈጡብኝ የባሰ ጨነቀኝ፡፡ ሰዓቴን አየሁ፡፡ 5፡10፡፡ ማድረግ የምችለው ነገር ስላልነበር ወጥቼ ቀጥታ ወደ ግቢው በር አመራሁ፡፡ የእስጢፋኖስ የመሰላቸት እና የንጭንጭ ድምጽ ተከተለኝ፡፡ ነፋሻ ምሽት ነው፡፡

እንደምትሀት ይወረወራል ነፋሱ፡፡ ባሕር ዛፎቹን ገንድሶ ሊጥል የፈለገ ይመስላል፡፡ ያ ባይቻለውም ጎንበስ ቀና እያደረጋቸው ነው፡፡ ዛፎቹ መቅኔያቸው እንደተንጠፈጠፈ የሽማግሌ ጉልበቶች እየተንቋቁ አጎንብሰው ይመለሳሉ፡፡ ወደ ግቢው በር እየቀረብኩ በመጣሁ ቁጥር የሰዎች አጀብ ቢጤ ታየኝ፡፡ እርምጃዬን አፈጠንኩ፡፡ ረጃጅም ቅልጥሞቼን አወናጨፍኳቸው፡፡ የክርስቶስ ያለህ! ይህ ተዓምረኛ ልጅ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆኖ ዘበኞቹ መኻል ቆሟል፤ ቀጫጫ ሰውነቱ በብርድ ይንዘፈዘፋል፤ ረዥም ሉጫ ጸጉሩ ተንጨባሯል፤ ጥቋቁር አይኖቹ ወዲያ ወዲህ ይንከባለላሉ፤ ግትር አፍንጫውን ቅዝቃዜ አርጥቦታል፡፡ ተንደርድሬ መሀላቸው ገባሁ፡፡ አዟዙሬ አየሁት፡፡ ደህና ነው። ቆዳው ብቻ በብርዱ ሳቢያ ተጉረብርቦ ፎጣ መስሏል። የምለውን አጣሁ፡፡ ምላሴ እንኳን በእንዲህ አይነት ቀውጢ ሰዓት ይቅርና በደህናው ጊዜም አይታዘዝልኝም፡፡ በጥያቄ ዐይን አየሁት። ወተት ጥርሶቹ ስስ ከንፈሮቹን ሸርተት አድርጎ አሳየኝ። አሁን የሆነውን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብኝም። ድሮውንም ሳየሁ ጠርጥሬያለሁ፤ እስከ አሁንም መሳቀቄ ራሱ ከንቱ ነበር፡፡ ቶማስን እንኳንስ የመቀሌ ኮሌጅ ማህበረሰብ፣ የመቀሌ ህዝብ ሳያውቀው አይቀርም፡፡

ዘበኞቹ በዚህ መኻል አዝነው ከህግ ውጭ እንዲገባ ፈቀዱለት፡፡ ይህን ጊዜ በእፎይታ ተነፈስኩ፡፡ እንዲያውም ትህትናቸዉ ለጉድ ነበር፤ ይግረምህ ብለው ነው መሰለኝ አንደኛው ዘብ እራሳቸውን ለብርድ አጋልጠው ጋቢያቸውን ከላያቸው ገፈው አለበሱት፡፡ ፊታቸው ላይ ያየሁት ርህራሄ ልቤን ዘልቆ ተሰማኝ፡፡ “የት ነበርክ?!” አልኩት፡፡ ፈገግታ - የእሱ ምላሽ፡፡ ቶማስ፣ “የት ነበርክ?!” ደግሜ ጠየቅሁት፡፡ ንጻታቸው የሚያስፈራ ጥርሶቹን በሰፊው ገለጻቸው፡፡ “የት ነ-በ-ር-ክ?!” አሁንም ፈገግታ፡፡ ትከሻውን ይዤ እንደ ጆንያ አራገፍኩት፡፡ “ለምጠይቅህ ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ የት ነበርክ?! ደግሞስ ልብሶችህስ?! ትከሻውን አማታብኝ፡፡ ይዤው መንገድ ጀመርን፡፡ ትዕግስቴ ተሟጦ ቢያልቅም ምን እንደምለው ግራ ገብቶኛል፡፡ የመጨረሻ ልናገር የምችለው ክፉ ነገር ቢኖር፡- “ከእንግዲህ ስለ አንተ አያገባኝም፡፡ ገደል ግባ!” ይሆናል፡፡ በቃ፡፡ “ጃኬቱን ዛሬም አውልቀህ ሰጠህ አይደል?!” ከግድ-የለሽነት በተቀላቀለ አዎንታ ትከሻውን ነቀነቀ። በወዲያኛው ሳምንት የተገዛ ጃኬት ነበር፡፡

እሱንም አውልቆ በሰጠው ጃኬት ምትክ ነበር የገዛነው። ምናልባት የዋጋው ውድነት አሸንፎት አይሰጥ እንደሁ ብዬ ለአንድ ጃኬት 500 ብር ስንከፍል ቅር አላለኝም ነበር፡፡ ይኸው ጉድ ሰራኝ፡፡ ያለ ወትሮዬ የማደርገውን መቆጣጠር ተሳነኝ፡፡ በድጋሚ ይዤ ወዘወዝኩት፡፡ “ለምስኪኑ አባትህ እንኳን አታዝንላቸውም?! እኔንስ ያለ ዕዳዬ ለምን ታሰቃየኛለህ?! ለምን ነብሴን ታስጨንቃለህ?! ለሰው ማዘን፣ የተቸገረን መርዳት፣ መጥፎ አይደለም፡፡ ግን እንዲህ ቅጥ ሲያጣ ደግሞ በምንም መልኩ ቢሆን ጥሩ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዴት ያን ያህል ብር አውጥተን የገዛነውን ጃኬት አውልቀህ ትሰጣለህ?! ለዚያውም በዚህ ብርድ …” አቋረጠኝ፡፡ “ምንተስኖት፣ ሰውየውን ብታያቸው እንዲህ አትልም ነበር፡፡ በዚህ ብርድ በብጣሽ ሸሚዝ ግንብ ስር ኩርምት ብለው ሳያቸው ልተባበራቸው ይገባኝ ነበር፤ ተባበርኳቸው፡፡ እስከ አሁን የቆየሁትም ሳጫውታቸው ነው፡፡ አየህ እናቴ “የተቸገሩ ሰዎች ከምንም በላይ ሰው ይናፍቃቸዋል” ትል ነበር፤ እና ከአንዱ የኔ-ቢጤ ጋር ማውራት ከጀመረች ቀኑ ይመሽ፣ ምሽቱ ይነጋ ነበር…” ጆሮዎቼ በሁለት እጆቼ ደፈንኳቸው፡፡ ሁሌም የሚነግረኝ ይህንኑ ነው፡- እናቴ፣ እናቴ፣ እናቴ … ኪሱ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በሙሉ አራግፎ “የኔ-ቢጤ” ለሚላቸው ያከፋፍላል፡፡

“ለምን?” ስል፡- “አየህ እናቴ ድሆችን መርዳት ያለብን ከተረፈን ላይ ቆንጥረን ሳይሆን ከሚያስፈልገን ጭምር ላይ መሆን አለበት፤ ትለኝ ነበር” ነው መልሱ፡፡ የራሱን ትቶ የሌሎች ተማሪዎችን አሳይመንት ይሰራል፡፡ “ተው” ስል እየፈገገ፡- “አየህ እናቴ ከራሷ በፊት ሌሎችን ታስቀድም ነበር” ይላል፡፡ እንዲህ እንደዛሬ ጃኬቱን አውልቆ የሰጠ ጊዜም፡- “ለምን?” ብዬ ስሞግተው፡- “እናቴ ሁለት ነጠላ ካላት አንዱን ለታረዘ ታለብስ ነበር’ ነው ያለኝ፡፡ ምን ዓይነት ልክፍት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ለተቸገሩ የሚቸረው ንብረቱን፣ ገንዘቡን እና ጊዜውን ብቻ አይደለም፤ እንባውንም ጭምር ነው፡፡ ሳንቲም አጥቶ ኪሱ ሲራቆት (ያው ሰጥቶ ሲጨርስ) እንባው ይጎርፋል፡፡ ደውሎ አባቱ ላይ ይጮህባቸዋል፤ እንደመታደል ሆኖ ደህና ኑሮ አላቸው አባቱ፤ እናም ገንዘብ ይልኩለታል፡፡ ለአራት ወራት መከርኩት፤ ተቆጣሁት፤ አብሬው ላይ ታች አልኩ፤ አሁን ግን ሰለቸኝ፤ መረረኝ፡፡ እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባሁበት ቀን ብላሽ ቀን ነው። አባቱ ናቸው እዚህ ጣጣ ውስጥ የነከሩኝ፡፡ እናም ደግሞ የኮሌጁ ዲን፡፡

ብቻ መጀመሪያ አደራውን ስቀበል ይህን ያህል እቸገራለሁ ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር፡፡ … ከአምስት ወራት በፊት፣ እዚህ ኮሌጅ በገባሁ ማግስት አንድ አባት ልጃቸውን አስከትለው ወደ ዶርማችን መጡ፡፡ የኮሌጁ የተማሪዎች ዲን አብሮአቸው አለ፡፡ ካሉት አምስት አልጋዎች አራቱ በእኔ፣ በእስጢፋኖስ፣ በመኩሪያ እና በአትክልቲ ተይዘው አንድ አልጋ ብቻ ነው ያልተያዘው፡፡ እንግዳው ሰውዬ እና ዲኑ ጎርደድ እያሉ ክፍሉን ቃኙት፡፡ እንደ አጋጣሚ አራታችንም የዚያ መኝታ ክፍል ተጋሪዎች እዚያው ነበርን፡፡ ዲኑ ሲቀሩ አባትና ልጅ በየተራ ተዋወቁን፡፡ ልጅ ቶማስ፣ አባት ሙሉ ወርቅ ይባላሉ፡፡ ቶማስ በቅጽበት ተዋሀደን፡፡ አራታችን መኻል ሆኖ ሲያወራን ለረዥም ጊዜ የምንተዋወቅ እንመስል ነበር፡፡ ሁኔታው ገርሞኛል፡፡ የመጣንበትን ቦታ፣ የተማርንበትን ትምህርት ቤት፣ ሌላው ቀርቶ ውጤታችንን በየተራ አስለፈለፈን፡፡ እርሱም እንደ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነው፤ መኩሪያ የሲዳሞ፣ እስጢፋኖስ የጅማ፣ አትክልቲ ደግሞ የዚሁ የመቀሌ ልጅ ነው፡፡ ቀልቤ ቶማስ የጫረው ጨዋታ ላይ እንደሆነ፣ ድንገት ቀና ስል የቶማስ አባት እና ዲኑ ባይናቸው መልዕክት ሲለዋወጡ አየኋቸው፡፡ አፈጠጡብኝ።

ዐይኔን ሰበርሁ፡፡ ተሰናብተውን ሊወጡ በር ጋ ከደረሱ በኋላ ከጓደኞቼ ነጥለው ጠሩኝ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ሄድኩ፡፡ አቶ ሙሉ ወርቅ ባንድ እጃቸው እኔን፣ በሌላ እጃቸው ቶማስን ይዘው መንገድ ጀመሩ፡፡ ዲኑ ከጎኔ ሆኖ ተከተለን፡፡ ወደ እርሱ ቢሮ ነበር የሄድነው፡፡ ቶማስን የፊተኛው ክፍል ውስጥ አቁመው እኔን ይዘውኝ ወደ ዋናው ቢሮ ዘለቁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አንዳችም አልተናገርኩም። ቀጣዩ ነገር ምን እንደሚሆን በጉጉት ሳይሆን በአግራሞት እየጠበቅሁ ነበር፡፡ ሁለቱ ጎን ለጎን፣ እኔ ከፊት ለፊታቸው ተቀመጥን፡፡ አቶ ሙሉወርቅ “ልጄ…” አሉኝ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፡፡ ልክ እንደ ልጃቸው ቶማስ ብስል ቀይ ይሁኑ እንጂ የሱን ያህል ዐይን አይስቡም፡፡ ቀጭን ናቸው፤ ጆሮአቸው ትልልቅ፣ ጥርሶቻቸውና ዐይኖቻቸው ትንንሽ፣ አፍንጫቸው ደግሞ አጠር አጠር ብሎ ወደ ግንባራቸው ሰቀል ያለ ነው፤ ጸጉራቸው ሉጫ ነው፤ ጥቁር ሉጫ፡፡

ጅምር ንግግራቸውን አቋርጠው ኪሳቸውን መዳበስ ጀመሩ፡፡ ከኪስ ቦርሳቸው ጉርድ ፎቶ አውጥተው አቀበሉኝ፤ ያለችበትን የዕድሜ ክልል መገመት የሚያስቸግር ሴት ምስል አለበት፤ በምንም በምንም ቶማስን የምትመስል ሴት ፎቶ፤ ጸጉር፣ ግንባር፣ ዓይን፣ አገጭ፣ አፍንጫ … ሁሉ ነገራቸው ይመሳሰላል ሳይሆን አንድ ነው፤ እህቱ ወይ እናቱ መሆን አለባት፡፡ “ልጄ” ቀጠሉ የቶማስ አባት፡፡ “ልጄ እርሷ የምታያት ሴት የቶማስ እናት ናት፤ አምና ነው በድንገተኛ ሕመም ያረፈችው፡፡ ቶማስ፣ የኔም የሷም ብቸኛ ልጃችን ነው፤ እና ለእርሱ የነበራት ፍቅር ፍፁም ልዩ ነበር፡፡ እኔን ከነመኖሬም አያስታውሱኝም፡፡ ሁለቱ አብረው ይበላሉ፤ አብረው ይጠጣሉ፤ በአንድነት ይጫወታሉ፤ አንድ ላይ ይተኛሉ … አሁን እንግዲህ አስራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው፡፡ እስከ አስራ ስምንተኛው ዓመት ማብቂያው ድረስ … ማለትም በሞት እስክትለየው ድረስ ግን ጡቷን ይጠባ ነበር፤ ደረቅ ጡቷን ይመጠምጥ ነበር። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ለመኻላ እንኳን አንድም ቀን ተለያይተው ተኝተው አያውቁም፤ እና ይህን ሁሉ ያነሳሁት ለምንድነው? …እ… ዲኑ እንደነገሩኝ በኮሌጁ ውስጥ አንድ አልጋ ለሁለት መጋራት አይፈቀድም፡፡ የኔ ልጅ ደግሞ በዚህ በኩል ከፍተኛ ችግር አለበት። በምንም ዓይነት ብቻውን መተኛት አይችልም።

እና አብሮት የሚተኛ ሰው ከተገኘ ያን ማድረግ እንደሚችል ተነግሮኛል፡፡ ማለት፣ ፍቃደኛ ከሆነ ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አልጋ እንዲጋራ ተፈቅዶለታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እናንተ መኝታ ክፍል ውስጥ ተመድቧል …” ንግግራቸውን ገታ አድርገው አዩኝ፡፡ ስሜቴን ለማንበብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዲኑ ዓይኖችም እንዲሁ ላዬ ላይ ይተራመሳሉ፡፡ አንገቴን ደፋሁ፡፡ አካሄዳቸው ገብቶኛል፡፡ ቀጠሉ፡- “…እ…ምን ነበር ያልኩት? …እ…አዎ እናም ደግሞ ያች እናቱ፣ ፍጹም ደግ ነበረች፤ ካፏ ነጥቃ ታጎርሳለች፤ ተጠምታ ታጠጣለች፤ ተርባ ታበላለች፤ እሷ መሬት ወርዳ እንግዳን አልጋ ላይ ታስተኛለች፡፡ የብቻ ነበር የሷስ ደግነት፡፡ እንደኔ ልፋት ቢሆን ይሄኔ ስንት ጥሪት ባየቆየን ነበር፡፡ እርሷ ግን ያመጣሁትን ሁሉ አንዳንዴ ለቤት እንኳ እስኪቸግረን ድረስ ታከፋፍለው ነበር፡፡ ቶማስ ታዲያ ከርሷ ብሶ ቁጭ አለ፡፡ ምኑም አይቀረው፡፡ ልብሱ፣ ጫማው፣ ለኪሱ የሚሰጠው ገንዘብ፣ ሁሉንም እናቱ ታደርግ እንደነበረው ተቸግሮ ላያቸው ያከፋፍላል … ታዲያ አሁን እኔ ብዙ ነገር ያስፈልጋልና ከአዲስ አበባ ገንዘብ ብልክለት አንዳችም አይጠቀምበትም፡፡ ይረጨዋል፡፡ ለዚህም ከጎኑ ሆኖ የሚረዳው ሰው ያስፈልገዋል፡፡

በዚህም በኩል ዲኑ ሊተባበሩኝ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ገንዘቡን በሳቸው ስም እልካለሁ …እ… ለትምህርት የሚያስፈልጉ መገልገያ መሳሪያዎች ሆኑ ሌሎች አላቂ የየዕለት መገልገያ ቁሳቁሶች የሚያጋዛው ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ እንደ አንተ ተማሪ የሆነ፣ ለተማሪ የሚያስፈልጉትን እቃዎች የሚያውቅ ሰው መሆን አለበት፤ እና በእነዚሀ ሁለት ጉዳዮች ላይ ብትተባበረኝ …እ” ብለው ድንገት ሳግ አፈናቸው፡፡ እንባቸውም ተከተለ፡፡ ነገሮች ግራ አጋቡኝ፡፡ መናገር አልቻልኩም፡፡ ፀጥታ፡፡ የለቅሶ ድምጽ፡፡ ፀጥታ፡፡ የመናገር ተራ ዲኑ ወሰዱ፡፡ የችግሩን ሁኔታ በገባቸው አቅጣጫ ነገሩኝ፡፡ ብተባበራቸው በትምህርቴም ሆነ በሌላ ልጎዳ እንደማልችል ሊያሳምኑኝ ሞከሩ፡፡ ካልፈለግሁ እና የማልችል ከመሰለኝ ግን አለመተባበር ሙሉ መብቴ እንደሆነ አስረዱኝ፡፡ ዝምታ ሰፈነ፡፡ በዚህ ቅጽበት አስቤ ፍቃደኛ ብሆን የሚከተለውን መዘዝ ወይም ፈቃደኛ ባልሆን የሚሰማኝን ፀፀት ማመዛዘን አልቻልኩም።

ፊት ካለው ክፍል የዲኑ ፀሐፊ ታይፕ ስትቀጠቅጥ ይሰማል፡፡ “ላግዝሽ? ታይፕ መምታት እችላለሁ፡፡” የቶማስ ድምጽ፡፡ ማሰብ አላስፈለገኝም፡፡ “እሺ፤ ልተባበራችሁ ዝግጁ ነኝ፡፡” አልኩ፡፡ አቶ ሙሉወርቅ ተንደርድረው በመምጣት አቀፉኝ፡፡ “እንግዲህ እኔም አንተን ቶማስን በማይበት ዐይኔ ነው የማይህ፤ ቃል ኪዳን ፈፀምን ማለት ነው፡፡” አሉኝ፡፡ እኚህ መከረኛ አባት ታዲያ ዛሬም ደውለው ነበር፡፡ ከአሳቤ ስመለስ ጐንበስ ብዬ አየሁት ቶማስን፡፡ አሻቅቦ ያየኛል፡፡ “እሺ አባትህም በሰቀቀን እንዲሞቱ ትሻለህ?!” የሞት ነገር ሲነሳ ስሜቱ በጣም እንደሚነካ አውቃለሁ፡፡ ያለሁበት ሁኔታ ግን ስሜቱን እንድጠብቅለት የሚያደርግ አልነበረም፡፡ የተደበላለቀ ስሜት ሰፍኖብኛል፡፡ ሐዘን፡፡ መታከት፡፡ ንዴት፡፡ ተስፋ መቁረጥ፡፡ ወደ ዶርም ስናመራ መንገድ ላይ እነ እስጢፋኖስን አገኘናቸው፡፡ እኛን ፍለጋ መውጣታቸው ነበር። ቶማስ በወፍራም አዲስ ጃኬት ፈንታ አዳፋ ጋቢ ለብሶ ሲያዩት ምን እንደተከሰተ ለመገመት ጊዜ አልወሰደባቸውም። ሁላቸውም ቃል እንኳን ሳይናገሩ ተያይዘን ወደ ዶርም ገባን፡፡ ብርድ ልብሳችንን ከአልጋችን ላይ አንስቼ አለበስኩት። መቼስ የኔ የምለው ነገር የለኝም፤ ሁሉ ነገር የኛ ሆኗል፤ ጊዜዬ እንኳን የኔ አይደለም፡፡

መኩሪያ እና አታክልቲ ቀኑን ሙሉ ከመጽሐፍ ጋር ሲታገሉ ስለዋሉ በተቀመጡት ማንቀላፋት ጀመሩ፡፡ እስጢፋኖስም ወፍራም ጉንጮቹ ተንጠልጥለዋል። ዐይኖቹ ደክመዋል፡፡ እየተነጫነጨ ራሱን ያካል፡፡ መኩሪያና አታክሊቲ ገፍቶ የመጣ እንቅልፋቸውን መቋቋም ስላልቻሉ ተኙ፡፡ ቶማስ፣ እስጢፋኖስ እና እኔ ብቻ ቀረን፡፡ ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ ማላዘን ጀመረ። እስካሁን ባለው ህይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ ሰዎች ከቶማስ እኩል የሚገርመኝ ሰው ቢኖር እስጢፋኖስ ነው፤ ምንም ነገር አያስደስተውም፤ ሁሌ ይነጫነጫል፡፡ በትምህርቱ ከማንም አያንስም፤ በኑሮውም ብዙ አይጐድለውም፤ ቤተሰቦቹ ከጅማ በየወሩ በቂ ብር ይልኩለታል፤ ግን ሁሌ እንዳላዘነ፣ እንደተነጫነጨ ነው የሚኖረው፡፡ ሲለው የኮሌጁ ምግብ አልተስማማኝም፤ የአገሩ አየር ፀባይ ጥሩ አይደለም፣ እከሌ የሚባል መምህራችን ደካማ ነው፣ ሴቶች አፍጠው ያዩኛል፣ የቤተሰብ ደብዳቤ ዘገየብኝ፣ እያለ እዬዬ ይላል፡፡ ሁሉም ነገር ሞትን ያስመኘዋል፡፡ “ሕይወት ዋጋ ቢስ ናት፣ ከመኖር አስር ጊዜ መሞት ይሻላል፡፡” የሚለው የዘወትር መነባንቡ ነው፡፡

በእርሱ የተነሳ ዶርማችን ውስጥ ሰላም ጠፍቷል። እርሱ መነጫነጭ ሲጀምር ቶማስ እያባበለው ያለቅሳል፡፡ እስጢፋኖስ ግን አይጽናናም፡፡ ቶማስ ሊረዳቸው ያልቻለ ሰዎች ቢኖሩ እስጢፋኖስ ዋነኛው ይሆናል፡፡ አሁንም መነጫነጭ ሲጀምር ቶማስ ማባበሉን ያዘ፡፡ “እስጢፍ ለምን አትረጋጋም? ሁሌ ለምን እንዲህ ትሆናለህ?!” “በዚህች ዓለም ውስጥ ምን መረጋጋት አለ? ይታይህ ቀን ከሌት ማጥናት ነው፤ ለአስራ ስንት ዓመት ፍዳ ማየት፤ መሰቃየት፤ ከዚህ ሁሉ ታድያ ሞቶ መገላገል አይሻልም?!” ጠረጴዛውን በቡጢ ደለቀው፤ እና የሚወደውን የመጽሐፈ መክበብ ጥቅሶች አዥጐደጐዳቸው፤ መጽሐፈ መክበብን በቀን ቢያንስ አንዴ ሳያነብ አይውልም፤ ሙሉ መጽሐፉን በቃሉ ሸምድዷል፡፡ “….ከፀሐይም በታች የተሰራው ሥራ ሁሉ ከብዶኛልና ህይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ንፋስንም እንደመከተል ነው…ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ ሃሳብ የሰው ጥቅም ምንድነው? ዘመኑ ሁሉ ሀዘንና ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው…አሁንም ቢሆን ከኛ ይልቅ የሞቱት ከነሱም ደግሞ ገና ያልተፈጠሩት ይሻላሉ…ፈተና፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መባዘን፣…ከንቱ ነው፤ ሁሉ ነገር…” ቀባጠረ የራሱንም እያከለ፡፡ በቃ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ነገር ነው የሚያስመርረው፤ ሞት የሚያስመኘው፡፡ ቶማስ ብዙም አልገፋም፡፡ የእስጢፋኖስ ጭንቀት አስጨነቀው፡፡ ሊያለቃቅስ ጀመረ፡፡ እስጢፋኖስ ደግሞ ካለ ነገሩ ለሰው ግድ የለውም፡፡ ቶማስ ሰውን መርዳት ሲያቅተው ምን ያህል እንደሚጨነቅ፣ ምን ያህል መንፈሱ እንደሚረበሽ አውቃለሁ፡፡ ደግነቱ እስጢፋኖስ ወዲያውኑ ተነስቶ ተኛ፡፡ እኔም አካሌ ዝሎ ስለነበር ጋደም አልኩ፡፡

እንቅልፍ ሊወስደኝ አካባቢ ቶማስ ነቅነቅ አድርጐ ቀሰቀሰኝና ጠጋ ብሎ በጆሮዬ “እስጢፎን የምረዳበትን ዘዴ ሳስብ ነበር፤ አሁን አገኘሁ፡፡” አለኝ፡፡ አየት አድርጌው ፊቴን አዙሬ ተኛሁ፡፡ ጠጋ ብሎ አቀፈኝ፡፡ ጠዋት አንድ ሰዓት ግድም ዶርማችን ውስጥ ትርምስ ሰምቼ ነቃሁ። ቶማስ አጠገቤ የለም፡፡ አትክልቲና መኩሪያ ዶርማችንን ያምሱታል፡፡ ዘልዬ ተነሳሁ፡፡ ምን እንደሆኑ ብጠይቅ የሚመልስልኝ ጠፋ፡፡ ኋላ መኩሪያ በጣቱ ወደ እስጢፋኖስ አልጋ ጠቆመኝ፡፡ ተንደርድሬ ሄድኩ፡፡ እስጢፋኖስ ዓይኖቹ ተገለባብጠው አልጋው ላይ ተዘርሯል፡፡ “ምን?!” ብዬ ጮህኩ፡፡ ለጥንቃቄው ደንታ አልነበረኝም፡፡ አቅፌ ነቀነቅሁት፡፡ ዝም፡፡ ሰውነቱን ዳበስኩት፤ ይቀዘቅዛል፡፡ ደረቱ ላይ እጄን ጫንኩ፤ ምንም፡፡ ሰውነቴ መንዘፍዘፍ ያዘ፡፡ ቀድሞ የነቃ ሌላውን የመቀስቀስ ልማድ ስለአለ ከእንቅልፉ ሊቀሰቅሱት ሲሉ ነበር እንዲያ ሆኖ ያገኙት፤ ሞቶ። አትክልቲ ፊቱ ገርጥቶ ባለበት ሐውልት መስሎ ተገትሯል፡፡ ከንፈሮቹ ደርቀዋል፡፡ መኩሪያም ምንም አይናገርም፡፡ ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አፉን በሰፊው ከፍቶ ቆሟል፡፡

“ሰዎች እርዳታ እንጥራ እንጂ፡፡ ተንቀሳቀሱ።” እያልኩ በባዶ እግሬ ወጥቼ ሮጥኩ፡፡ ወዴት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ኋላ ነው መንገድ ቀይሬ ወደ ዲኑ ቢሮ ያመራሁት፡፡ እዚያ ስደርስ ቶማስ በር ላይ ቆሞ አገኘሁት፡፡ እርሱም እንደኔው ሁኔታውን ሊነግር እንደመጣ ገባኝ፡፡ “ዲኑ አልገቡም?” አልኩት፡፡ ጥያቄዬን ችላ ብሎ “አየህ ምንተስኖት እስጢፋኖስ በጣም ነበር የሚያሳዝነኝ፤ ልረዳው ባለመቻሌ ዘወትር እንደተጨነቅሁ ነበር፡፡ የተቸገረ ጓደኛን መርዳት አለመቻል በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ አስቤ እንደደረስኩበት ደግሞ ከዚህ የተሻለ እስጢፋኖስን የምንረዳበት መንገድ የለም፤ እና…” አላስጨረስኩትም፡፡ እጄ ቡጢ ሆኖ ሲወናጨፍ ይታወቀኛል፡፡ አጓርቶ ወደ ኋላ ተዘረረ፡፡ ደነዘዝኩኝ፡፡ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁኝ፡፡ እንደምንም ከወደቀበት ተነሳ፡፡ “አንተምኮ ታሳዝነኝ ነበር፡፡” አለኝ ፈገግ እንደማለት ብሎ፡፡ ሲናገር ጥርሶቹ በምላሱ እየተገፉ ወደቁ፤ ባዶ ድድ፡፡ ጭንቅላቴን ይዤ መጮህ ጀመርኩ፡፡ እንባዬ ጅረት ሆኖ ፈሰሰ፡፡ በዚህ መሃል አእምሮዬ ውስጥ አንድ ነገር ፈነዳ፡፡ “ለእናቱም ያዝንላቸው ነበር ማለት ነው?” ከዚህ በኋላ ማሰብ አልቻልኩም፡፡ ጨለማ ሆነ፡፡ ፀጥታ ሆነ፡፡ (ውድ አንባቢያን- ከዚህ በላይ የቀረበው ታሪክ በድጋሚ የወጣ ነው)

ከሁለት ሳምንት በፊት 36ኛ ዓመት ልደቱን ያከበረው እና “ጄይዙስ” የተባለ አዲስ አልበሙን ከሰሞኑ ለገበያ ያቀረበው ካናዬ ዌስት፤ የዘመኑ ስቲቭ ጆብስ እኔ ነኝ ሲል ተናገረ፡፡ በሌላ በኩል ካናዬ ዌስት እና ፍቅረኛው ኪም ካርዴሽያን ከሳምንት በፊት የመጀመርያ ሴት ልጃቸውን የወለዱ ሲሆን ኖርዝ ኖሪ ዌስት የሚል ስምም አውጥተውላታል፡፡ ሁለቱ ዝነኞች ለሴት ልጃቸው ያወጡት ስም ለብራንድ አይመችም ተብሎ ቢተችም ከተወለደች ወር ያልሞላትን ህፃን የመጀመርያ ፎቶ ለማግኘት የመገናኛ ብዙሃን እሽቅድድም ላይ እንደሆኑ የጠቀሱት ዘገባዎች፤ የህፃኗ ፎቶ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ሰሞኑን ሁለት ሚዲያዎች የኖርዝ ኖሪ ዌስት የመጀመርያ ፎቶን አግኝተናል በማለት ህትመታቸውን ቢያሰራጩም ፎቶው ሃሰተኛ እንደሆነ መታወቁን ቲኤምዜድ ዘግቧል፡፡

“ፒፕል ማጋዚን” የብራድ ፒት እና አንጀሊና ጆሊ ሁለት መንታ ልጆችን የመጀመርያ ፎቶ በ14 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶ ማተሙን ያስታወሰው ዘገባው፤ ቤተሰቡ ይህን ገንዘብ ለበጎ አድራጎት እንደለገሱ እና ካናዬ እና ፍቅረኛውም ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጽሙ ይገመታል ብሏል፡፡ የመጀመርያ ሴት ልጁን ባገኘ በማግስቱ “ቀጣዩ ስቲቭ ጆብስ እኔ ነኝ” ሲል የተናገረው ካናዬ ዌስት፤ “በኢንተርኔት፤ በሙዚቃ፤ በፋሽንና በባህል የምፈጥረው ተፅእኖ እንደ ስቲቭ ጆብስ አብዮተኛ ያደርገኛል” ብሏል፡፡

በራፐርነቱ የሚታወቀው ካናዬ ዌስት፤ 100 ሚሊዮን ዶላር ሃብት ሲኖረው፤ በቴሌቭዥን ሪያሊቲ ሾው እና በፋሽን ኢንዱስትሪው አውራነቷን ያስመሰከረችው ፍቅረኛው ኪም ካርዴሽያን 40 ሚሊዮን ዶላር ሃብት አስመዝግባለች፡፡ ካናዬ ዌስት ከ7ኛ አልበሙ “ጄይዙስ” በፊት አስቀድሞ ባሳተማቸው ስድስት አልበሞች በመላው ዓለም 15 ሚሊዮን ቅጂዎች የተሸጡለት ሲሆን 14 የግራሚ ሽልማቶችን ጨምሮ ከ47 በላይ የተለያዩ ሽልማቶች በማግኘት ከፍተኛውን ስኬት የተቀዳጀ ራፐር ነው፡፡