Administrator

Administrator

 (የኬኒ ሮጀርስ የዘፈን ግጥም እንደ አጭር ልብወለድ)


              ሰው ሁሉ “ቦቅቧቃው” ይለዋል። እሱ ግን አንድም ቀን እንኳ አንገቱን ቀና አድርጎ አይደለሁም ብሎ ለማስተባበል ሞክሮ አያውቅም። እናቱ ያወጣችለት ስም ቶሚ ነው። የመንደሩ ሰው ግን “ቦቅቧቃው” በሚል የቅፅል ስም ይጠራዋል። እኔ መቼም የሰፈሩ  ሰው ለቶሚ የሰጠው ግምት ትክክል አለመሆኑ ይታወቀኛል።
አባቱ እስር ቤት ውስጥ ሲሞት እሱ ገና የአስር ዓመት ልጅ ነበር። የወንድሜ ልጅ ነውና ከዚያ ወዲህ በአደራ ቶሚን የማሳድገው እኔ ነኝ። ወንድሜ በአልጋ ጣር ላይ ሳለ፣ ለቶሚ የነገረው ነገር አሁንም ትዝ ይለኛል።
“ልጄ ሆይ፤ የእኔ ኑሮ እነሆ አበቃ፣ የአንተ ግን ገና መጀመሩ ነው። ስለዚህ ቃል ግባልኝ። መከራን መሸሽ ከቻልክ ሽሸው። ማምለጥ እየቻልክ ቆመህ አትጠብቀው፣ አንደኛውን ጉንጭህን ሲመቱህ ሌላኛውን ጉንጭህን ብትሰጥ ደካማ ነህ ማለት አይደለም። በዚህ ዕድሜህ መቼም ይህንን መረዳት አያቅትህም። አየህ ልጄ፤ ሰው ለመሆን የግድ  መታገል፣ የግድ  መጋፈጥ የለብህም፡፡"
ሁሉም ሰው የምትሆነውን ሴት ማፍቀሩ ያለ ነገር ነው። ቶሚም ቤኪን በጣም ያፈቅራታል። በእቅፏ ውስጥ በገባ ጊዜም ወንድ መሆኑን ማረጋገጥ አላስፈለገውም፡፡
አንድ ቀን የጋትሊን መንደር ልጆች ሶስት ሆነው እየተፈራረቁ ቤኪን ይሰድቧታል። ይባስም ብለው ይደበድቧታል - ጠግበዋል።
ቶሚ በሥራ ገበታው ላይ ነበር። ድንገት ድምጽ ሰምቶ ብቅ ብሎ ቢያስተውል የሱዋ ቤኪ ናት። ተደብድባለች፣ ታለቅሳለች። የተቀዳደደ ቀሚሷና የተመሰቃቀለ ሁኔታዋ ሩህሩህ ልቡ ከሚችለው በላይ አሰቃቂ ሆነበት።
ወደ ቤት ተመልሶ ገባ። ድንገት ዞሮ ከእሳቱ ማንደጃ ቦታ ላይ የነበረውን ያባቱን ፎቶግራፍ አየ። አነሳው። እያለቀሰም ተመለከተው። በእንባው ፊቱ እስኪታጠብ ድረስ ሲያስተውለው ከቆየ በኋላ በመጨረሻዋ እስትንፋሱ የመከረው ምክር ዳግም ጆሮው ላይ ደወለበት።
“…አንደኛውን ጉንጭህን ቢመቱህ እንኳ ሌላኛውን ጉንጭህን ብትሰጥ ደካማ ነህ ማለት አይደለም… አየህ ልጄ ሰው ለመሆን የግድ መታገል የለብህም።"
ቶሚ ቆጣ ብሎ ወደ ቡና ቤቱ መጣ። የጋትሊን ልጆችም በማንጓጠጥ ሳቁበት። ከመሃላቸውም አንዱ ተነሳና ወለሉን ማህል ለማህል አቋርጦ ወደሱ መጣ። ቶሚ ከዚያ ቦታ ዘወር እንደ ማለት ቃጥቶት ነበር።
“እዩት ይሄን ቦቅቧቃ ፈርቶ ሲሸሽ ተመልከቱ እንግዲህ…” ለከፋቸውንና ስድባቸውን ቀጠሉ። አላገጡበት።
ይሄኔ ቶሚ ትዕግስቱ ተሟጦ አለቀ። ደረቱን በሀሞተ- ሙሉነት ነፍቶ፣  በሩን በግዙፍ  ሰውነቱ ሞልቶ ቆመ። ማን ወንድ ይለፈው! ይሄኔ አካባቢው ሁሉ ፀጥ እርጭ አለ። ከዝምታው ጥልቀት የተነሳ እስፒል እንኳ ብትወድቅ ትሰማ ነበር። ሃያ ዓመት ሙሉ በችግር እየማቀቀ፣ እየዳኸ ያሳለፈው ሕይወቱ፣ በቡሽ እንደተከደነ ጠርሙስ ልቡ ውስጥ በጥንቃቄ ታሽጓል።
ድንገት ያ የልቡ ማሸጊያ ቡሽ ከመቅፅበት ተፈናጥሮ ተከፈተ። እልሁና ቁጣው እንደ ሻምፓኝ ገነፈለ። መቼ ገባ ሳይባል ተወንጭፎ ጠብ ውስጥ ጥልቅ አለ። ያለ የሌለ ጉልበቱን ሳይቆጥብ ይሰነዝርባቸው ጀመር። እያንዳንዳቸውን በቡጢ ማንጋጭል- ማንጋጭሊያቸውን እያለ እየቦቀሰ ዘረራቸው። አንድም የጋትሊን ልጅ ፊቱ ቆሞ አይታይም። ሁሏም ተራ በተራ ምሷን ቀመሰች።
የመጨረሻውን ልጅ መትቶ ሲጥል፣
“ይሄኛው ለቤኪዬ ማስታወሻ ይሁን; አለና ቡና ቤቱን በኩራት ለቅቆ ወጣ።
ወዲያው እንዲህ ሲል ሰማሁት፣
“አባባ አንተ ያጠፋኸውን ዓይነት ጥፋት እንዳልደግም ቃል አስገብተኸኝ ነበር። እነሆ መከራን የቻልኩትን ያህል ሸሸሁ። ከእንግዲህ እኔን ደካማ ነው ብለህ እንዳታስብ። ቀኜን ሲመቱኝም በፍፁም ግራዬን አልሰጠሁም። እንግዲህ አባባ፣ ሰው ሆኖ አንዳንድ ጊዜ መታገልና መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ አሁን እንደገባህ በፅኑ ተስፋ አደርጋለሁ።”

Thursday, 14 January 2021 11:41

የወግ ጥግ

 ንግሥት ዘውዲቱ ደብረ ብርሃን በአንድ ገዳም አንድ  ካህን ሾሙ። ያ ካህን ባሪያ ኖሯል። ስለዚህም ካህናቱ አልወደዱትም። በዚያ ላይ የተለመደውን የካህናቱን ግብር ሳያበላ ቀረና ንግስት ዘንድ ከሰሱት- ካህናቱ ተቆጥተው ማለት ነው። ችሎት ቀረቡ ተካሰው።
ንግሥትም- “አንተ፣ ምን ሆነህ ነው የተለመደ ግብራቸውን ሳታበላቸው የቀረኸው?” አሉና ጠየቁት።
ካህኑም- “ንግሥት ሆይ፤ እኔ ለስንት ጅብ ላበላ ነው?!!" አለና መለሰ
ይሄኔ- ከካህናቱ አንዱ፡-
“እንግዲያውስ ንግሥት ሆይ፤ ይህ ካህን ይነሳልን። ለነገሩ አንድ አህያስ ለስንት ጅቦች ሊሆነን ነው? ይነሳልን!”
ማስታወሻ፡- አህያ ነው ያሉት ባሪያ ነው ለማለትም ነው፤ በዚያ ዘመን ቋንቋ፡፡


Thursday, 14 January 2021 11:33

አባትና ልጅ በፖለቲካ ጉዳይ

 ልጅ- አባዬ፣ አንድ ጥያቄ ብጠይቅህ ትመልስልኛለህ?
አባት- በደንብ እንጂ ልጄ። ምንድን ነው ጥያቄህ?
ልጅ-  /ፖለቲካ/ ምንድን ነው?
አባት- ደህና። እንዲገባህ በምሳሌ ላስረዳህ።
ለምሳሌ፡- የእኛን ቤተሰብ እንደ አንድ ሀገር ብንወስድ። እኔ ለሀገሩ ገንዘብ የማገኝ ሰው ነኝ። እኔን የአሰሪዎችን መደብ እንደምወክል አድርገህ አስብ። እናትክን ደሞ ገንዘቡን ቦታ ቦታ እያስያዘች የምትመራ ናት እንበል። እሷን መንግስት ብለህ ጥራት። ሁለታችን የአንተን ጥቅምና ፍላጎት የምናሟላልህ ስለሆነ፣ አንተ ደግሞ ህዝብ ትባላለህ ማለት ነው። የቤት ሰራተኛችንን፣ የሰራተኛው መደብ ብለን እንጠራታለን።
ትንሹን ወንድምህን ደሞ የነገው ትውልድ እንለዋለን። አሁን ገባህ/ፖለቲካ/ ማለት?
ልጅ-  የለም አባዬ፤ በደንብ የገባኝ አልመሰለኝም። ትንሽ ላስብበት እስቲ።
*   *   *
የዚያኑ ዕለት ማታ ቤተሰቡ ሁሉ ተኝቶ ሳለ ልጁን የትንሽ ወንድሙ ለቅሶ ከእንቅልፉ ይቀሰቅሰዋል። ምን ሆኖ እንደሚያለቅስ ለማረጋገጥ ወደ ህፃኑ ሄዶ ቢያይ፤ የሽንት ጨርቁ እንዳለ ርሷል። ይሄንኑ ሊያስረዳ ወደ እናትና አባቱ መኝታ ቤት ሄደ። እናቱ ለጥ ብላ እንቅልፏን ትለጥጣለች። ከዛ ወደ ቤት ሰራተኛቸው መኝታ ክፍል ሄደና አንኳኩቶ አልከፍት ስላለችው፣ በበሩ ቀዳዳ አሾልቆ ሲያይ፣ አባቱ ሰራተኛዋን አቅፎ ይታገላል። ቢያንኳኳም ጨርሶ የሚሰሙት አልሆነም። ስለዚህ ልጁ ተስፋ ቆርጦ ወደ መኝታ ቤቱ ገብቶ ተኛ።
በማግስቱ።
ልጅ- አባዬ አባዬ፤ /ፖለቲካ/ ማለት አሁን ገባኝ፤ መሰለኝ- አለው።
አባት-  በጣም ጥሩ የኔ ልጅ። በል እስቲ አስረዳኝ።
ልጅ-  አየህ አባዬ፤ የአሰሪዎች መደብ የሰራተኛውን መደብ ያንገላታዋል! መንግስት ለጥ ብሎ ተኝቷል፡፡ ህዝብ ግራ ገብቶታል። የነገው ትውልድ ከእነ መፈጠሩም ተረስቷል። ይሄው ነው /ፖለቲካ/ ማለት::

በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት  በመላው አለም 40 የአውሮፕላን አደጋዎች መከሰታቸውንና በእነዚህ አደጋዎች በድምሩ 300  ሰዎች ለሞት  መዳረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአመቱ የተከሰቱ የአውሮፕላን አደጋዎች ቁጥር ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያህል ቢቀንስም፣ በአደጋዎቹ የደረሰው ጥፋት ግን በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላለፉት 20 ያህል አመታት እያደገ የነበረውን የአውሮፕላን መንገደኞችን ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቀንስ እንዳደረገው ሲሪየም የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የአለማቀፍ የአውሮፕላን መንገደኞች ቁጥር ከአመት በፊት ከነበረበት በ67 በመቶ ያህል ቀንሷል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ተቋሙ፣ የአገር ውስጥ በረራ መንገደኞች ቁጥር በአንጻሩ በ40 በመቶ ያህል መቀነስ  ማሳየቱን አስታውሷል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በአመቱ ከ40 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ ከማቆማቸው ወይም ከማቋረጣቸው ጋር ተያይዞ በቀጣዩ አመትም የመንገደኞች ቁጥር ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተቋሙ ጠቁሟል፡፡
የአለማችን አየር መንገዶች ባለፈው የፈረንጆች አመት በድምሩ 16.8 ሚሊዮን በረራዎችን ማድረጋቸውን ያስታወሰው የተቋሙ ሪፖርት፣ በ2019 የተደረጉት በረራዎች ግን 33.2 ሚሊዮን እንደነበሩ አክሎ ገልጧል፡፡


  እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ!
የዘንድሮውን የልደት በዓል የምናከብረው በዚህ ዓመት ያሳለፍነውን ፈታኝ ተጋድሎና ከፊታችን የሚጠብቀንን ወሳኝ ዕድል እያሰብን ነው። አሁን በፈተናና በዕድል መካከል እንገኛለን። ዓለምም የመጀመሪያውን የክርስቶስ ልደት ያከበረችው በፈተናና በዕድል መካከል ሆና ነበር። በአዳም በደል ምክንያት የመጣው የመከራ ዘመን እያለፈ፤ የመከራው ዋና ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ፣ በማኅጸን በተጀመረ የማዳን ሥራ እየተሸነፈ፤ የጨለማው ንጉሥ እየተረታ፤ የዘመናት ቋጠሮ እየተፈታ ነበር። ከፊት ደግሞ የመዳን፣ የብርሃን፣ የሰላም፣ የነጻነት እና የፍቅር ዘመን እየመጣ ነበር።
ነገሩ ግን ሂደቱ ቀላል አይደለም። የጨለማው ዘመን አበጋዞች እንዲነጋ አልፈለጉም። ሊመጣ ያለው ድኅነት የማያስቀሩት ቢሆንም እንኳን፤ የሚያሸንፉት እስኪመስሉ ድረስ ተፍጨርጭረዋል። እየበራ ያለውን መብራት የሚያጠፉት ያህል ታግለዋል። የተከፈተውን የብሩኅ ተስፋ መስኮት የሚከረችሙት ያህል ፎክረዋል። የተሸነፈውን ዘንዶ ዳግም ሕይወት የሚዘሩለት ያህል ተገዳድረዋል። ግን ይህ ሁሉ አልሆነም።
ሄሮድስ ተነሥቶ ነበር። ብዙዎችንም በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል። ዘመኑም የብሩኅ ተስፋ ሳይሆን የመከራ ዘመን መስሎ ነበር። በክርስቶስ መወለድ የተፈጠረው ደስታ፣ በቤተልሔም ሕጻናት ግድያ የደበዘዘ እስኪመስል። በበረት ውስጥ የተፈጠረው ተስፋ፣ በድንግል ማርያምና በክርስቶስ መሰደድ ያበቃለት እስኪመስል። በመላእክት ዝማሬ የተበሠረው አዲስ ዘመን፣ በሄሮድስ አበጋዞች ጭፍጨፋ ሕልምና ተረት እስኪመስል። የኦሪት ዘመን አበቃ ሲባል፤ በኦሪት ዘመን የማይሠራ ግፍ፣ በዘመነ ሐዲስ በቤተልሔም ከተማ ተከሠቷል። ብዙዎችንም ተስፋ አስቆርጧል።
ቢሆንም መከራው አላፊና ጠፊ እንጂ ዘላቂ አልነበረም። ያ እንደ ተራራ የገዘፈ የመሰለው ሽብር እንደ እንቧይ ካብ የሚፈርስ፤ እንደ ባሕር የሰፋ የመሰለው መከራ እንደ መጋቢት ወንዝ የሚነጥፍ፤ የማይሸነፉ የሚመስሉት ሁሉ እንደ ጎልያድ የሚወድቁ፤ አስጨናቂዎች ሁሉ መልሰው የሚጨነቁ መሆናቸውን - ያሳየ አጋጣሚ በዚያን ዘመን ተከሥቷል። ለዚያም ነው ሁሉም አልፎ ዛሬ ድረስ የልደትን በዓል ልዩ ትርጉም ሰጥተን የምናከብረው።
ውድ የሀገሬ ሕዝቦች፣
አሁን ኢትዮጵያ በልደቱ ቀን ቆማ ልደትን የምታከብር ሀገር ናት። ተስፋዋን፣ ሰላሟን፣ ንጋትና ብልጽግናዋን እንዳታይ በዙሪያዋ የቆሙ የሄሮድስ አበጋዞች አሉ። በቻሉት መጠን መከራችን እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። የተወለደልንን የተስፋ ብርሃን ለመግደል ይጥራሉ። ከተማዋን የዋይታ ከተማ ለማድረግ ይለፋሉ። ነገን እንዳናይ መስኮቶችን ሁሉ ይዘጋሉ። ወደ ተስፋ መጠጊያ ዋሻችንን በቋጥኝ ደፍነው በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንድንቆይ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
ሆኖም ግን ፈተናችንን ያበዙብን ሄሮድሶች ከብልጽግና መንገዳችን አያስቀሩንም፤ እስከ መጨረሻው ሕቅታቸው ወደ ኋላ ሊጎትቱን ቢጥሩም ጨርሶ ከጉዟችን ሊያስቆሙን አይችሉም። በመንገዱ ላይ የዘሩትን አሜከላ እየለቀምን፣ እንቅፋትና ጋሬጣውን ተሻግረን ከተራራው እናት መውጣታችን አይቀርም። የተሰበረውን ድልድይ ጠግነን፣ ከችግሮቻችን በላይ ከፍ ብለን ያለጥርጥር ኢትዮጵያን ወደ ተስፋዋ አድማስ እናደርሳታለን።
ገና ያኔ የለውጥ ጉዟችን ሲወለድ ጀምሮ ተመሳሳዩን ሲያደርጉ ነበር። በየወቅትና አጋጣሚው ጉዟችን እንዲሰናከል ያልወረወሩት ድንጋይና ያልጣሉት ጋሬጣ አልነበረም። ከመንገዳችን ሳንሰናከል ገፍተናል፤ በፈተናዎቻችን ትምህርት፣ በችግሮቻችን ጥንካሬ፣ በእንቅፋቶቻችን ብርታት እያገኘን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከእያንዳንዱ ጨለማ ወዲያ ንጋት መኖሩን እያመንን፣ ዐይናችንን ወደ ወጋጋኑ አቅንተን ጉዟችንን ቀጥለናል። እኛ አንድ ወደ ፊት በተራመድን ቁጥር ችግሮቻችን ወደኋላ ይሸሻሉ፤ እኛ ይበልጥ በበረታን ቁጥር እነሱ ይሸነፋሉ።
ያም ሆኖ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው እውነት አለ። ለኢትዮጵያ የፈነጠቀውን የተስፋ ብርሃን ከእንግዲህ ማንም ሊያጠፋው አይቻለውም ሲባል እስከናካቴው አይሞክርም ማለት አይደለም። የሄሮድስ ወታደሮች ሕጻኑን ክርስቶስ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ እንደተከታተሉት ሁሉ ፈታኞቻችን ነገም ይከተሉናል።
እንቅፋቶቻችን መልካቸውን እየቀያየሩ በመንገዳችን ላይ መቆማቸውን ይቀጥላሉ። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ የትንሣኤ ጉዞ ፍጥነቱ ከምንም በላይ የሚወሰነው በእኛ ጥንካሬ እንጂ በእነሱ ችግር ፈጣሪነት መጠን አይደለም፤ መሆንም የለበትም።
እኛ እስካልፈቀድንላቸው ድረስ ለሀገራችን የተወለደውን ተስፋ ሊያመክኑት፣ የተለኮሰውን ፋና ሊያጠፉት አይችሉም። ጨልሞባት የነበረችው ሀገራችን ምሽቷ መንጋት ጀምሯል - እኛ ከበረታን ዳግም በእነሱ ሤራ አይጨልምም። ያጎበጣት የዘመናት ፍዳ አንዴ መደርመስ ጀምሯል - እኛ ችላ እስካላልን ድረስ ዳግም አይቆለልም። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ስኬትና ውድቀት ማዕከሉ የእኛ ጥንካሬና ድክመት ነው ብለን ማመን አለብን።
ውድ ወገኖቼ፣ ከተስፋችን አንጻር ፈተናችን ብዙ ባይሆንም ወደፊት ይበልጥ መፈተናችን እንደማይቀር ማወቅ አለብን። ወደ ተስፋ በተጠጋን ቁጥር የመከራው ብርታት እንደሚጨምር ያለፉት ሦስት ዓመታት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። በመከራ ውስጥ ከሚመጣ መከራ ይልቅ በተስፋ ውስጥ የሚመጣ መከራ እጅግ ይከብዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። በአንድ በኩል ልቡና ተስፋ እያደረገ ፈተና ሲገጥመው ያማርራል። በመከራ ውስጥ ሆኖ መከራ ሲገጥመው ግን ‹የበሰበሰ ዝናም አይፈራም› እንደሚባለው በአማራጭ ማጣት ይታገሣል። በተስፋ ውስጥ ፈተና የሚያጋጥመው ሰው ግን እምነት ያጣል። አእምሮው ለሐሴት እንጂ ለሑከት አልተዘጋጀም። ከትግል ጊዜ ይልቅ በድል ጊዜ ብዙዎች ይሞታሉ የሚባለው ለዚህ ነው። በትግል ጊዜ የነበራቸው የመሥዋዕትነት ሥነ ልቡና በድል ጊዜ አይገኝም።
ኢትዮጵያ ሁለቱም ያጋጥማት ይሆናል። ተስፋ ባነገበች ሀገር ላይ ተስፋ መቁረጥ፤ ሰላም ባነገበች ሀገር ላይ ግጭት፤ ብልጽግናን ባነገበች ሀገር ላይ ውድመት ይመጣባት ይሆናል። መነሻችን ‹አያዎ› ነው - ‹አይ እና አዎ›። መድረሻችን ግን ‹አዎ› ብቻ ነው። ብርሃን ጨለማን፤ ሰላም ጦርነትን፣ ፍቅር ጥላቻን፤ አንድነት መለያየትን፣ ብልጽግና ኋላቀርነትን ማሸነፋቸው አይቀሬ ነው። በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ማጨዳቸው የማይቀር ነው።
ከወፍ ዕንቁላል ውስጥ ጠንካራው ቅርፊቱ ነው። ጫጩቷ ቅርፊቱን ሰብራው ከወጣች በኋላ ግን ጠንካራ መሆኑ ያበቃል። ጫጩቷ ታድጋለች፤ ቅርፊቱ ግን በተቃራኒው መፈራረስ ይጀምራል። ጫጩቷ ትበራለች፤ ቅርፊቱ ዱቄት ይሆናል፤ ብሎም ይበሰብሳል። ጫጩቷ ወፍ ሆና ሌሎች ዕንቁላሎች ትጥላለች፤ ሌሎች ጫጩቶችንም ትፈለፍላለች። ቅርፊቱ ግን ይበልጥ እየበሰበሰ ወደ አፈርነት ይለወጣል። የኢትዮጵያም ችግሮች እንደዚሁ ናቸው። ለጊዜው ጠንካራና ዙሪያችንን ከብበው የያዙን ይመስላሉ። ይህ የሚሆነው ግን እስክንሰብራቸው ድረስ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ እኛ ከችግሮቻችን መብለጣችን አይቀሬ ነው።
ከክርስቶስ ልደት የምንማረው ይሄንን ነው። የትናንቱ ሲያልፍ ዝም ብሎ አያልፍም። የመጨረሻ ሙከራውን አድርጎ ነው የሚያልፈው። ልክ እንደሄሮድስ ሙከራ። የነገውም ዝም ብሎ አይመጣም፤ በተጋድሎ ነው የሚመጣው። ልደት ግን በሚያልፍ መከራና በሚመጣ ዕድል መካከል መሆኑ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያም እያለፈችው በምትሄደው መከራና፣ እያገኘችው በምትመጣው ዕድል መካከል ናት።
‹ዛሬ› በትናንትና በነገ መካከል ስለሆነ የሁለቱም መልክ ይታይበታል። ከትናንት የወረሰው መከራ፤ ከነገ የተዋሰው ደስታ አለው። ንጋት ማለት በሚያልፍ ጨለማና በሚመጣ ቀን መካከል ነው። መሽቷል ያለ ይተኛል፤ ነግቷል ያለ ይነሣል። የእኛም ምርጫ ይሄው ነው። መሽቷል ብለን እንተኛለን ወይስ ነግቷል ብለን እንነሣለን?
መልካም የልደት በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
ታኅሣሥ 28፣ 2013 ዓ.ም


  አፍሪካ በ3 አመታት 60 በመቶ ህዝቧን ለመከተብ አቅዳለች

             የተለያዩ የአለም አገራት ዜጎችን መከተብ በጀመሩበት በአሁኑ ወቅት፣ ከአለማችን አገራት መካከል በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመስጠት ቀዳሚነቱን የያዘችው እስራኤል መሆኗ ተነግሯል፡፡
እስራኤል እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ፋይዘር የተባለውን የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መስጠቷንና ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 11 በመቶ ያህል እንደሚደርስ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ እስራኤል 11 በመቶ ያህል ሰዎችን በመከተብ ከአለማችን አገራት ብዛት ላላቸው ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመስጠት ቀዳሚነቱን የያዘች ሲሆን፣ 3.49 በመቶ፣ እንግሊዝ 1.47 በመቶ ሰዎችን በመከተብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
አሜሪካ 2020 ከመጠናቀቁ በፊት ለ20 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ክትባት ለመስጠት ብታቅድም፣ ለመከተብ የቻለችው 2.78 ሚሊዮን ያህሉን ብቻ እንደሆነም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዜና ደግሞ፤ እስከ መጪዎቹ ሶስት አመታት ድረስ ከአጠቃላዩ የአፍሪካ ህዝብ ለ60 በመቶው ወይም ለ980 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የኮሮና ክትባት ለመስጠት መታቀዱንና ለዚህም 9 ቢሊዮን ዶላር  እንደሚያስፈልግ መነገሩን ሮይተርስ ዘገቧል፡፡
1.3 ቢሊዮን ያህል ህዝብ በሚኖርባት አፍሪካ እስካሁን ድረስ 2.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአውሮፓና አሜሪካ የኮሮና ክትባቶች መሰጠት ቢጀመርም በአፍሪካ አገራት ግን እስከ መጨው አመት አጋማሽ መደበኛ ክትባት ይጀመራል ተብሎ እንደማይጠበቅ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ከሰሞኑ የሰጠውን መግለጫ ጠቅሶ አመልክቷል፡፡

 ከእለታት አንድ ቀን  አንድ ንጉስ ፈላስፋቸውን ጠርተው  እንዲህ አሉት።
“ሶስት ልጆች አሉኝ። የትኛው የተሻለ እንደሆነ ግን አላውቅም። እስኪ የእውቀታቸውን ልክ የሚያሳይ ጥያቄ ጠይቅልኝና ልኬታቸውን ልወቅ” ሲሉ አማከሩት።
ፈላስፋውም፡-  
“እሺ ንጉስ ሆይ! አንድ አይነት ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ ከዚያም መልሶቻቸውን እናወዳድራለን”  አላቸው።
 በዚሁ ስምምነት ላይ ተደረሰና ጥያቄው በተናጠል ቀረበላቸው።
ለአንደኛው- “ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ምን ያስፈልጋታል ብለህ ታስባለህ?”
እሱም-  “አራሽ ያስፈልጋታል" አለ
ለሁለተኛውም-  "ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ምን ያስፈልጋታል ብለህ ታስባለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ
መልሱ “ተኳሽ ያስፈልጋታል”
ሶስተኛውም- "ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ምን ያስፈልጋታል ብለህ ታስባለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ
"ቀዳሽ  ያስፈልጋታል" ብሎ መለሰ።
ፈላስፋውም ለንጉሱ እንዲህ አላቸው።
“ንጉስ ሆይ፤ ሁሉም በየበኩላቸው ትክክለኛ መልስ መልሰዋል፤ሁሉም ትክክለኝነታቸው  የዋናውን መልስ አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው።  ስለዚህ የሽልማቱን ነገር እርስዎ ቢያስቡበት ነው የሚሻለው” አላቸው።
ንጉሱም ነገሩን አሰላስለው፤
“እንደዚያማ ከሆነ ሽልማቱን ሲሶ ሲሶ መካፈል አለባቸው፤ ምክንያቱም  የጥያቄው ሙሉ መልስ፡-
ሀገር  አንድ አራሽ …. አንድ ቀዳሽ…. አንድ ተኳሽ ያስፈልጋታል ነው፤ በአንድም በሶስትም መንገድ  እምትንቀሳቀስ መሆኑ ላይ ነው። አሉና “ሶስቱንም ይባርክልን” ሲሉ አሳረጉ።
*   *   *
እነሆ ይህን አባባል  በተዘዋዋሪ መንገድ ስናጤነው፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ባህል  ለአንድ ሀገር  ወሳኝ አንጓዎች ናቸው እንደማለት ነው። ምነው ቢሉ፤ አራሹ አርሶ የምግብ ፍጆታችንን ካላሟላልን፤ ወታደሩም የመከላከያ ኃይሉም ተጨንቆና ተጠቦ ዳር ድንበራችንን በልበ ሙሉነት ካልጠበቀልን፤ ቄሱ  ከመቅደሱ ቆሞ  በምህላ ካላገዘን  አገር አትፀናም፡፡  ከዚህ በላይም ደግሞ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለን፤ “አገር እንደ ኮረዳ አካል ያለ ፍቅር አትጠናም።"  
የሀገር ፍቅር እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ሲባልም ለልጆቻችን የምንሰጠው ፍቅር፣ ለአባቶቻችንና ለእናቶቻችን የምንሰጠው ፍቅር፣ ለህዝባችን የምንሰጠው ፍቅር፣ ለመልክአ ምድራችንም የምንሰጠው ፍቅር ማለት ነው።
ለዚህ ሁሉ ማእቀፍ ይሆን ዘንድም ለታሪካችን፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ያለን አክብሮት ታላቅ ቦታ የሚቸረው ነው። እነዚህ ሶስት አላባውያውን በግማሽ-ጎፌሬ ግማሽ-ልጭት  ስንቆምባቸው ረጅም መንገድ ሄደናል። አሁን ግን ቢያንስ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ረግተው የሚኖሩባትን እናት ሀገር  እንተውላቸው እያልን ነው። ልቧ ባዶ ፣ሌማቷም ባዶ የሆነች ኢትዮጵያን እንዳናወርሳቸው እንጨነቅ፣ እንጠበብ።
- የሚታደጓትን ወጣቶች፣ ሴቶችና ሀገር ጠባቂዎች  ፈጥረንላታል ወይ?
- ትምህርትና ጤና  መስፈርቱን ባሟላ ሁኔታ ተይዟል ወይ?
- ኢኮኖሚዋ እያደገ ነው እየቀጨጨ?
-  ምሁራኗ ያገባኛል የሚል ተቆርቋሪነት አላቸው ወይ? ወይስ የምን ግዴ እየመሩ ነው?
- መምህራን ለተማሪዎች ያላቸው ኃላፊነት ምን ይመስላል?
- ፕላንና እቅድ አውጭዎቻችን የነደፉትን ሀሳብ  እስከ ፍጻሜው የመከታተል ሀሞት አላቸው ወይ?
- ጥያቄዎቻችን አያሌ ናቸው፡፡ ጥቂት ትጉሃን  ቢያንስ የሚያነሱት ጥያቄዎች  በቀና እንዲጠየቁ ማድረግና ለመፍትሄያቸው ቀና ሰዎች የሚታቀፉበት ቡድን  መፍጠር ጤናማ አካሄድ ይሆናል።
ዙሪያችንን በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ወረራ - ከበባ መኖሩ አያጠራጥርም።  የጥንትም የአሁንም ከባቢዎች የየበኩላቸውን እኩይ ወረራ  ለማካሄድ መለስ ቀለስ ማለታቸው  ዛሬ ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። ስለሆነም ዙሪያ ገባውን  በአይነ ቁራኛ ማየት  የሚመለከተው ሁሉ ግዴታ ነው።  በጥንቱ አነጋገር ፡-
"ለአፍ ልመና ሳይያዙ ገና
ከተያዙ ብዙ ነው መዘዙ” ማለት ግድ ነው።
ዛሬም  ደግመን ደጋግመን  ሀገር  አንድ አራሽ …. አንድ ቀዳሽ…. አንድ ተኳሽ  ትፈልጋለች የምንለው ከላይ ባነሳናቸው ምክኖች ሳቢያ ነው!


        አንጋፋው የህወኃት መሥራችና ቀንደኛ መሪ አዛውንቱ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመከላከያ ሰራዊት ገለፀ።
#ላለፉት 27 አመታት የማተራመስ ስትራቴጂ የነደፈ፣ ያስተባበረና ያደራጀ፣ በመጨረሻም ጦርነት እንዲቀሰቀስ በማድረግ በሀገራችን ሰራዊት ላይ እጅግ ዘግናኝ ጦርነት በመክፈት ሰራዊቱን ያስጨፈጨፈው የጁንታው ቁንጮ፣ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር ውሏል።; ብሏል፤ መከላከያ በመግለጫው፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለፁት፣ #የጁንታው ቁንጮ አመራር ስብሃት ነጋ ከተደበቀበት ለሰው ልጅ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሰርጥ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሏል። የጁንታውን ቁንጮ ስብሀት፣ የጥፋት ቡድኑ አባላት በሰርጡ ውስጥ ተሸክመው በማስገባት ደብቀውት እንደነበር ነው; ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ የተናገሩት፡፡   
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፌዴራል የፀጥታ አካላት በጋራ ባደረጉት ፍተሻና አሰሳ፣ ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር አውለውታል፤ ብለዋል። በተጨማሪም ከመከላከያ የከዱ ሌሎች የቡድኑ አመራሮች፣ ከጁንታው መሪ ስብሃት ነጋ ጋር አብረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ብርጋዴር ጄነራሉ አመልክተዋል። እነዚሁ ከመከላከያ የከዱ የቡድኑ አመራሮች፣ የጁንታውን ታጣቂ ሀይል በማዋጋትና በማሰልጠን እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈፀም ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ በመጨረሻም የጁንታውን አመራር ጥበቃ ሲያስተባብሩ ቆይተው፣ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመከላከያ ሰራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ገልፀዋል።
እነዚህን የጁንታውን አመራሮች ለመከላከል በአካባቢው ጥበቃ ላይ የነበረ ታጣቂ ሀይልም መደምሰሱን አክለው ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረት በቁጥጥር ስር የዋሉት፣
የህወኃት ቡድን መሪው ስብሃት ነጋ
ሌተናል ኮሎኔል ፀአዱ ሪች- የስብሃት ነጋ ባለቤትና ቀደም ሲል በጦር ሃይሎች ሆስፒተል ሃኪም የነበረች፣ በኋላም በጡረታ የተገለለች
ኮሎኔል ክንፈ ታደሰ- ከመከላከያ የከዳ
ኮሎኔል የማነ ካህሳይ- ከመለካከያ የከዳ
አስገደ ገ/ ክርስቶስ- ከመሃል ሀገር ተጉዞ ቡድኑን የተቀላቀለና ለጊዜው ሃላፊነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን
የሜጀር ጀነራል ሃየሎም አርአያ ባለቤት የነበረችና ኑሮዋን በአሜሪካ አድርጋ የቆየች በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ወደ ጁንታው ተቀላቅላ የነበረች፣ ወይዘሮ አልጋነሽ መለስ ጁንታውን በመያዝ ኦፕሬሽን ሂደት ውስጥ ለማምለጥ ስትሞክር ገደል በመግባት ህይወቷ ማለፉን ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ገልፀዋል።

ብዙዎች በመድረክ አተዋወኗ ብቃቷ የተለየች ናት የሚሏት ባዩሽ አለማየሁ የቬኑሱ ነጋዴ፣ የስለት ልጅ፣ ሰማያዊ አይን ትዳር ሲታጠን፣ ሰዓት እላፊ፣ ነቃሽ ... በትወና የተሳተፈችባቸው ተውኔቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
   ባዩሽ አለማየሁ አለማየሁ የታዋቂው ተርጓሚና ደራሲ መስፍን አለማየሁ ልጅ ናት።
በቴአትር ልምምድ ላይ እያለች ትንሽ አሞኛል ብላ በዛው የቀረችው ደራሲአዘጋጅ፣ ተዋናይት፣ ገጣሚ እና ተራኪ ባዩሽ አለማየሁ ዛሬ ታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በህክምና ስትረዳ በቆየችበት በየካቲት 12 ሆስፒታል ከዚህ ዓለም ሞት ተለይታለች።

Saturday, 02 January 2021 14:07

የግጥም ጥግ

 ምፀት

የዘንድሮው እግዜር የኦሪቱ አይደለም፣
ጥፋት ስታጠፋ- ከገነት አውጥቶ
አያባርርህም፤
የዘንድሮ እግዜር-ኃጢአንን ሲቆጣ፤
ፓርላማ ይሰዳል-ህሊናውን ትቶ እጁን
እንዲያወጣ
እየጠበኳት ነው
እየጠበኳት ነው- በሰው ሁሉ መሃል
እንደይረጋግጧት ብዬ- የኔን ውብ
ሀመልማል፤
እየጠበኳት ነው -እንዳትጠፋ ድንገት
መና ሆና እንድትኖር-ሳለ እርጅና ሞት፤
እየጠበኳት ነው - እንዳትጠፋ ጭራሽ
የኔን ገጸ ጸዳይ፤ የሕመሜን ፈዋሽ
እየጠበኳት ነው-ከሰው ከአራዊቱ፣
እስከ ነፃነት ቀን- እስኪነጋ ሌቱ፡፡
(“ነፃነት” ግጥሞችና ወጎች፤ ወሰንሰገድ ገብረ ኪዳን)

Page 7 of 516