Administrator

Administrator

   የሳዑዲ አረቢያው ልዑል መሃመድ ቢን ሰልማን በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ በሚገኘው ኒኦም በረሃ ውስጥ 500 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ልዩ ከተማ ሊቆረቁሩ መሆኑን ገልፍ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የሃይል አቅርቦቱን ከንጹህ ታዳሽ ሃይል ምንጮች እንደሚያገኝ የተነገረለትና “ዘ ላይን” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዘመናዊ ከተማ፣ አንድ ሚሊዮን ያህል ህዝብ እንዲኖርበት መታቀዱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
አዲሱ የበረሃ ከተማ ምንም አይነት በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች እንደማይገቡበት የተነገረ ሲሆን፣ አገሪቱ ኒኦም የተሰኘውን በረሃ ከፍተኛ የቱሪዝም እና የቢዝነስ ማዕከል ልታደርገው ያሰበችው በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኝ ስፍራ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ እ.ኤ.አ በ2030 ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ለያዘችው ዕቅድ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክሎ ገልጧል፡፡

  የ78 አመቱ የእድሜ ባለጸጋ ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ባለፈው ረቡዕ በዋይትሃውስ በተከናወነው በዓለ ሲመት ቃለ መሃላ ፈጽመው 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑ ሲሆን፣ ካማላ ሃሪስም ቃለ መሃላ ፈጽመው የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ጥቁር እስያዊት ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል። ከበዓለ ሲመቱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል የሚከተሉትን መራርጠንላችኋል፡፡
ከሳምንታት በፊት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን በሚገኘው ካፒቶል ሂል የፈጸሙትን ነውጠኛ ድርጊት ተከትሎ፣ በአገሪቱ ያንዣበበው ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት፣ መላውን አሜሪካ በውጥረት በዓለ ሲመቱንም በከፍተኛ የደህንነት እና ጸጥታ ጥበቃ አጨናንቆት እንደነበር ተነግሮለታል፡፡
የፌዴራሉ የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ፣ የዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎችና ጽንፈኛ ቡድኖች በትጥቅ የታገዘ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ፣ በ50 ግዛቶቿ ከፍተኛ ጥበቃና የጸጥታ ቁጥጥር ስታደርግ የሰነበተችው አሜሪካ፣ በዋሽንግተን ለጆ ባይደን በዓለ ሲመት ብቻ 25 ሺህ ወታደሮችን ያሰማራች ሲሆን፣ እንደተሰጋው ይህ ነው የሚባል እክል ሳያጋጥም በአሉ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ 59ኛው በአለ ሲመት ሆኖ የተመዘገበው የጆ ባይደን በዓለ ሲመት፣ ከጸጥታ ስጋቱ ባሻገር ከወትሮው ቀዝቀዝ ያለ እንዲሆን ያደረገው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ነበር፡፡
ድሮ ድሮ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በአደባባይ በተገኘበት ይከናወን የነበረው የአሜሪካ በዓለ ሲመት፣ ዘንድሮ ግን እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ መላ የጠፋለትን የኮሮና መስፋፋት፣ የባሰ ላለማስፋፋት ሲባል እንደ ወትሮው ብዙ ህዝብ ባልተገኘበት መከናወኑ ግድ ሆኗል፡፡
የዛሬን አያርገውና ድሮ ድሮ በበዓለ ሲመቱ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆየሩ ሰዎች ይታደሙ እንደነበር ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ለአብነትም ባራክ ኦባማ በ2009 ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ 2 ሚሊዮን ህዝብ ዋሽንግተን ዲሲን ከዳር እስከ ዳር አጥለቅልቋት እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡
ስልጣን ላለመልቀቅ ወዲያ ወዲህ ቢሉም ከባይደን በዓለ ሲመት ከሰዓታት በፊት ለአራት አመት የኖሩበትን ነጩን ቤተ መንግስት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሰናበቱት ዘንድ ግድ የሆነባቸው ተሰናባቹ ትራምፕ በበዓለ ሲመቱ ላይ ባይገኙም፣ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ ቢል ኪሊንተን እና ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ስነስርዓቱን መታደማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
1.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት በተነገረው በአለ ሲመት በ78 አመት ከ2 ወራት ዕድሜያቸው ቃለመሃላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት የገቡት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን፣ በአሜሪካ ታሪክ እድሜያቸው በጣም ከገፋ ወደ ስልጣን የመጡ ቀዳሚው ሰው ሆነው በታሪክ መዝገብ መስፈራቸውም ተነግሯል፡፡
ታዋቂዋ ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ በዓለ ሲመቱን በማስመልከት የአሜሪካን ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር የዘመረች ሲሆን፣ በዋሽንግተኑ የነጻነት ሃውልት ፊትለፊት በተዘጋጀውና በዝነኛው የፊልም ተዋናይ ቶም ሃንክስ የመድረክ አጋፋሪነት በተካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይም ጄኔፈር ሎፔዝ፣ ብሩስ ስፐሪንግስተን፣ ኬቲ ፔሪ፣ ቦን ጆቪ፣ ዴሚ ሎቫቶና ፉ ፋይተርስን ጨምሮ ታዋቂ ድምጻውያን የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
የ22 አመቷ ታዳጊ አሜሪካዊት ገጣሚ አማንዳ ጎርማን በበኩሏ፤ ለባይደን በአለ ሲመት የከተበችውንና የአብሮነትና የአንድነት ጥሪ ያስተላለፈችበትን ማራኪ ግጥም ያቀረበች ሲሆን፣ በአሜሪካ በአለ ሲመት ላይ ግጥም በማቅረብ በእድሜ ትንሽዋ ገጣሚ ለመሆን ችላለች፡፡
በዓለ ሲመቱን በማስመልከት በእለቱ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ከላኩት የተለያዩ አገራት መሪዎች መካከል፣ የታይዋን፣ የጃፓን፣ የብሪታኒያ፣ የኳታር፣ የጀርመን፣ የፓኪስታን፣ የጣሊያን፣ የቻይና፣ የኢራን፣ የካናዳ፣ የሩስያ፣ የፈረንሳይ፣ የህንድ፣ የስፔን፣ የግሪክ፣ የእስራኤል ወዘተ መሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቫንደር ሌይንም መልዕክት መላካቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

   የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለሁሉም የአለም አገራት በፍትሃዊነት ለማዳረስ ተይዞ የነበረው ዕቀድ በሃብታም አገራት የክትባት ሽሚያ ሳቢያ እየተሰናከለ እንደሚገኝና፣ እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ድረስ 49 የሚሆኑ ሃብታም የአለማችን አገራት ከ39 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች ለዜጎቻቸው ሲሰጡ፣ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ድሃ አገራት ክትባቱን ያገኙ ሰዎች ግን 25 ብቻ መሆናቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የአለማችን ድሃ አገራት መካከል ለዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መስጠት የጀመረችው ብቸኛዋ አገር ጊኒ መሆኗን ድርጅቱ እንዳስታወቀ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በጊኒ ባለፈው ሳምንት መሰጠት የጀመረውን ሩስያ ሰራሽ ክትባት ያገኙት የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጨምሮ 25 ሰዎች ብቻ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ ባለፈው ሰኞ በተደረገው የቦርድ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር እንዳሉት፣ በርካታ የአለማችን ሃብታም አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለዓለም ሕዝብ በፍትሐዊ መንገድ ለማከፋፈልና ድሃ አገራት ክትባቱን በወቅቱ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ታስቦ የተመሰረተውን ኮቫክስ የተባለ አለም አቀፍ ትብብር አሰራር በመጣስ ክትባቶችን በሽሚያ በገፍ እየገዙ በማከማቸት ድሃ አገራትን ለከፍተኛ ችግር እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡
ኢፍትሃዊው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አለማችንን እጅግ ለከፋ የሞራል ውድቀት እያንደረደራት ይገኛል ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ፍትሃዊነት የጎደለው የክትባት ክፍፍል ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረጉ ጥረቶችን ከንቱ የሚያስቀርና ኮሮና እያሳደረ የሚገኘውን ሰብአዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያባብስ በመሆኑ አገራት ለፍትሃዊ ክፍፍል ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ከ25 በመቶ በላይ እስራኤላውያን ክትባቱን ማግኘታቸውን ያስታወሰው ዘ ጋርዲያን፣ በእንግሊዝ ከ6 በመቶ በአሜሪካ ደግሞ 4 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ማግኘቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከሰሞኑ ከ95.5 ሚሊዮን ማለፉና ለሞት የተዳረጉትም ከ2.4 ሚሊዮን በላይ መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ባለፈው ማክሰኞ ከ400 ሺህ ማለፉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ በአንጻሩ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በሳምንቱ መጀመሪያ ከ3.3 ሚሊዮን ማለፉን የዘገበው ሮይተርስ፣ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም ከ79 ሺህ ማለፉን ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በደቡብ አፍሪካ በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በቦትስዋና፣ ዛምቢያ እና ጋምቢያ መገኘቱ የተነገረ ሲሆን፣ በኬንያ የደቡብ ምስራቅ ግዛት ውስጥ ደግሞ ሌላ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መገኘቱን አንድ የአገሪቱ የህክምና ምርምር ተቋም ባወጣው ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው የጥናት ሪፖርት ማመልከቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኦል አፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፤ የዚምባቡዌው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲቡሲሶ ሞዮ በሳምንቱ መጀመሪያ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ዘግቧል፡፡

    አንድ ንጉሥ ወደፊት ለልጆቹ ምን ማውረስ እንዳለበት ሲጨነቅ ሲጠበብ ቆይቶ፤ አንድ ቀን አንድ የፍተሻ ፈተና ለልጆቹ ሊሰጥ ይወስንና ልጆቹን ያስጠራቸዋል፡፡
ከዚያም የሚከተለውን ጥያቄ ይጠይቃቸዋል:-
“ልጆቼ! መቼም ‘ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት’ የሚቀር የለም፡፡ እኔም እድሜዬ እየገፋ፣ መቃብሬ እየተማሰ፣ መገነዣ ክሬ እየተራሰ ያለ መሆኑን ትገነዘባላችሁ፡፡ ስለሆነም፤ የትኛው ልጄ መንግሥቴን መውረስ እንዳለበት ለመለየት ቀላል ፈተና እሰጣችኋለሁ፡፡ በዚህ ትስማማላችሁ?”
አንደኛው - በደስታ!
ሁለተኛው - በጣም ፈቃደኛ ነኝ!
ሦስተኛው - ስመኘው የነበረ ነው! አሉ፡፡
ንጉሡ ደስ ብሎት፤
“እንግዲያው፣ በየግላችሁ ወደ ጫካ ትሄዱና በጣም ጠንካራና የማይሰበሩ ናቸው የምትሏቸውን ሁለት ሁለት እንጨቶች ይዛችሁ ትመጣላችሁ፡፡ የማይሰበረውንና የተሻለውን እጅግ ጠንካራ እንጨት ያመጣው ልጄ የዙፋኔ ተረካቢ ይሆናል!” ሲል ይገልፅላቸዋል፡፡ሦስቱም በሃሳቡ ተስማምተው ወደ ጫካው በረሩ፡፡ በነጋታው ሁሉም ጠንካራ ናቸው ያሏቸውን ሁለት ሁለት እንጨቶች ይዘው መጡ፡፡ ንጉሡ ትእዛዙን በመፈፀማቸው ሁሉንም አመሰገኑ፡፡

 “መልካም! ልጆቼ ሆይ! እንዳልኩት ያመናችሁባቸውን ጠንካራ እንጨቶች ይዛችሁ መጥታችሁዋል፡፡ ከሁለቱ አንዱን እንጨት ለብቻው አስቀምጡ፡፡ የቀረውን እንጨት አንዳችሁ ላንዳችሁ ስጡና መሰበር አለመሰበሩን እራሳችሁ አጣሩ፡፡”
እርስ በርስ እየተሻሙ አንደኛው የአንደኛውን እንጨት ባለ በሌለ ጉልበት ሰባበሩ፡፡ የማናቸውም እንጨት ጠንካራ አለመሆኑን ንጉሡ አስተዋሉና፤
“በሉ አሁን ደግሞ መሬት ያኖራችኋቸውን ሦስት እንጨቶች አምጡ” አሉ፡፡
ሦስቱን እንጨቶች አመጡላቸው፡፡
“በሉ አንድ ላይ እሰሯቸው” አሉ፡፡
አሰሯቸው፡፡    
“እያንዳንዳችሁ አንድ ላይ የታሰሩትን ሦስት እንጨቶች ስበሩና አሳዩኝ” አሉ፡፡
ሦስቱም ለመስበር ሞከሩ፡፡ በጭራሽ ለመስበር አቃታቸው!
ንጉሡም፤ “ይሄውላችሁ ልጆቼ፡፡ በተናጠል ሲታዩ የመረጣችኋቸው እንጨቶች ሁሉ በቀላሉ ተሰባሪ ናቸው! አንድ ላይ ሲሆኑ ግን የማይታበል ኃይል አላቸው፡፡ ዙፋኔ የሦስታችሁም ነው፡፡ የሁላችሁም እንጨት ነው፡፡ ልቦቻችሁን አስተሳስራችሁ አስቡ! ለየብቻ ሄዳችሁ የትም አትደርሱም!” ብለው አሰናበቷቸው!!
*   *   *
ዙፋኑን ለልጆቹ ለማውረስ ዝግጁ የሆነ መሪ አይንሳን!
በተናጠል ከመጓዝ ይሰውረን! የራሳችን እንጨት ዕጣ-ፈንታ መሆኑን ሳናስተውል የሌላውን እንጨት ለመስበር ከመጣደፍ ይሰውረን! የጊዜው ጥያቄ፤ Pern-men of the world unite! (የዓለም ፀሀፍት ተባበሩ!) የሚል ይመስላል፡፡ የፕሬስ ሰዎች ብዕሮቻችሁን አስተባብሩ እንደማለትም ነው፡፡
“አወይ ልቤ ደጉ፣ ይላል ትር-ትር
ሆዴ ባዶ እንዳይቀር፣ ሁሉን ስናገር” የሚል መንፈስ ሊኖረው ይገባል፡፡
ግፍ ባለበት ቦታ ሁሉ፤ ተገፊው ድምፁን ማሰማቱ አሌ የማይባል እውነት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሆዳችን በጮኸ ቁጥር የፖለቲካ ልሳናችን መከፈቱ፤ ማህበራዊ ተቋማችን መርበትበቱ፤ “ኤጭ አይባል የአገር ጉዳይ!” እንደሚባለው መሆኑም እውነት ነው፡፡
በዘመነ ካፒታሊዝም የሀብት ባለቤት አድራጊ-ፈጣሪነቱና አንድ ለእናትነቱ ሌላ ባለሀብት እንዳይፈጠር እንዳልሆነም ሊታበል አይችልም፡፡ በዘመነ-ካፒታሊዝም ሰው እንደ ሸቀጥ መታሰቡ ያረጀ ሀቅ የመሆኑን ያህል፤ የድንገቴ/የገጠመኝ (novis) ሀብታሞች ሸቀጥ ልውውጡን ራሱን የሙስና መናኸሪያ ማድረጋቸው፤ በእቅድ ይመራል የሚባለውን ካፒታሊዝም ራሱን፣ እቅደ-ቢስ ያደርገዋል፡፡ ይሄ በመንግሥት ደረጃ ከተከሰተ ደግሞ ለያዥ-ለገራዥ የሚያስቸግር የአገር አባዜ ይሆናል፡፡ በዚህ መንፈስ ሲታሰብ በጥንት ጊዜ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም፤ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው!” ይባል የነበረው መፈክር፤ ዛሬ “ማፍረስ ቀላል ነው! መገንባት ፈፅሞ አይቻልም!” ወደሚል እንዳይሸጋገር ልንሰጋ ይገባል!
ሰው እየረሳን ሸቀጥና ብር ብቻ እያሰብን ባገር ሰበብ በግል ወይ በቡድን ስንሄድ፤ ለዚች ማዕከላዊ መደብ (Middle Class) ላልተፈጠረባት አገር ምን አይነት የጥፋት ውሃ እየተመኘንላት መሆኑን ማስተዋል ተስኖናል፡፡ አንድ አበሻ ገጣሚ ስለ ዘመነ-ካፒታሊዝም እንዲህ ይለናል:-
“ውበትሽ የነበር፣ ኩል ሳይኖር ነበረ
ሙሉ-ልብሽ ጠፋ፣ ጌጥ ሆነ እያደረ!
ያ ንፁህ ገፅታሽ፣ ሰዓሊ እሚያነበው
ዛሬ አርተፊሺያል ፊት፣ የሽያጭ ዕቃ ነው!!”
(ላልታደለች አገር)
መረጃ-ያለው/ያገኘ ማህበረሰብ ሳይኖር ሥልጣኔን ማሰብ ዘበት ነው፡፡ የመረጃ ፍሰት የሚኖረው በጤናማ መንገድ የመረጃ ፍሰቱን የሚሰሩ ሚዲያዎች ሲኖሩ ነው፡፡ እኒህ ሚዲያዎች ተጣምረው ካልተጓዙ ደግሞ እንደ ግለሰቦች ትግል “አንድ አይነድ፣ አንድ አይፈርድ” ናቸው፡፡
መደራጀት ግድ ነው፡፡ አፍሪካዊው ገጣሚ “ለመጨነቅም ቢሆን አብረን እንሁን!” ይላል (Let’s frustrate together!) አለበለዚያ ሌላው አፍሪካዊ ገጣሚ እንዳለው፤ They only love the Dead (የሞቱትን ብቻ ይወዳሉ እንደማለት ነው!) ለሚለው አባባል መዘባበቻ ሰለባ እንሆናለን!”
ስለሞቱልን እናወራለን፡፡ ስለተሰዉልን እናወጋለን! ስለ ትላንት ፍቅራችን እንገልፃለን! ስለ ዛሬስ? ነው የሚለው ገጣሚው! “ለመጨነቅም ቢሆን አብረን እንሁን!”
ለደጉም ለክፉም አብረን ስንሆን ነው የሚበጀን፡፡ ለደስታም ለሃዘንም በህብረት መሆን ነው የሚያዋጣው፡፡ የራስን ሽምቅ ተዋጊ ሽፍቶችንም ሆነ ድንበር ተሻጋሪ ወራሪዎችን በቅጡ መመከትና ድባቅ መምታት የሚቻለው በአንድነት ስንቆም ነው፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችን መቼ ጥፋትና ጥቃት እንደሚያደርሱብን በግልጽ እያየነው ነው፡፡ በራሳችን ችግሮች ስንጠመድና እርስ በርስ ስንጋጭና ስንወዛገብ ነው፡፡
United we stand divided we fall! ከተባበርን እንቆማለን፤ ከተነጣጠልን እንወድቃለን፤ ማለት ነው! የዱሮ መፈክር - ግን የዛሬም እውነት ነው!  በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ ላይ ከቀረቡ ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፏል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች ከጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ጋር የተያያዙ መሆናቸውም ተገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረው ችሎት፣ አቃቤ ሕግ ክሶቹን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ማዘዙ ይታወሳል። ነገር ግን አቃቤ ሕግ ሌሎቹን ክሶች እንዳሻሻለ ጠቁሞ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሰረት በማድረግ የተከፈቱትን ክሶች ማሻሻል እንደማይፈልግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱም፤ክሶቹ በተጠቀሰው አዋጅ ስር መታየት እንደማይችሉ በመጥቀስ፣ እንዲቋረጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
የቀሩት አራት ክሶች “ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፣አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ”፣ የፀረ ሽብር አዋጅና የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን የሚመለከቱ ናቸው።
ፍርድ ቤቱ እነዚህን ማሻሻያዎች ጨምሮ ክሱን ለተከሳሾች ካነበበ በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠይቅ፣ ጠበቆች የእምነት ክህደት ከመስጠት በፊት ክሱ በተገቢው መንገድ መሻሻሉን ለማየት ቀነ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ ለፍርድ ቤቱ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙና የቀረበባቸው ክስ በመጪው አገራዊ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ምንም ወንጀል እንዳልፈፀምን አቃቤ ሕግ ራሱ ያውቃል፤ እኛ ብንወጣና ምርጫው ላይ ብንሳተፍ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጥቅም ይኖረዋል” ብለዋል፤አቶ ጃዋር፡፡

    የአገራትን አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም በመገምገም በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ግሎባል ፋየር ፓወር የተሰኘው አለማቀፍ ተቋም ከሰሞኑም የአዲሱ የፈረንጆች አመት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አሜሪካ በአመቱ እጅግ ከፍተኛው ወታደራዊ አቅም ያላት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗን አስታውቋል፡፡
በግሎባል ፋየር ፓወር የአመቱ ወታደራዊ አቅም ሪፖርት ውስጥ ከተካተቱት የአፍሪካ አገራት መካከል ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያና ሞሮኮ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ ኢትዮጵያ በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ከ138 የዓለም አገራትም በ60ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች - ኢትዮጵያ፡፡  
ግብጽ ከዓለም አገራት  በ13ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ሱዳን በ77ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል - ተቋሙ፡፡
ተቋሙ ወታደራዊ የሰው ሃይል፣ የገንዘብ አቅምና የጦር መሳሪያ ሃብትን ጨምሮ ከ50 በላይ በሚሆኑ መስፈርቶች በአለም ዙሪያ የሚገኙ 138 አገራትን ገምግሞ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ፤ ከአለማችን አገራት በወታደራዊ አቅም የሁለተኛነት ደረጃን የያዘችው ሩስያ ስትሆን፣ ቻይና፣ ህንድና ጃፓን እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ደረጃውን ያወጣው ግሎባል ፋየር ፓወር፤ የየአገራቱን ወታደራዊ የሰው ኃይል፣ ከታጠቁት መሳሪያዎች ጋር በማቅረብ አነጻጽሮ ነው የአገራቱን የወታደራዊ አቅም ደረጃን ያወጣው፡፡ በዚህ መሠረት፤ ከአፍሪካ በ6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ 162 ሺህ ወታደሮች፣ 24 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 8 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 365 ታንኮች፣ 130 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ 480 ከባድ መድፎች፣ 180 የሮኬት መተኮሻዎች እንዲሁም 65 ቀላል መድፎች ሲኖራት፣ የአገሪቱ ዓመታዊ ወታደራዊ በጀት ደግሞ 520 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን  ግሎባል ፋየር ፓወር አመልክቷል፡፡
ከአፍሪካ በወታደራዊ አቅም የምትመራው ግብጽ፣ ከ104 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን  930 ሺህ ወታደሮች፣ 250 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 91 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 3735 ታንኮች፣ 2200 ከባድ መድፎች፣ 11ሺህ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች  ሲኖራት፣ የመከላከያ በጀቷ 10 ቢሊዮን ዶላር  እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡  
ከ138 አገራት በ77ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሱዳን፣ ከ45 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሲኖራት፣ አጠቃላይ ያላት የወታደር ብዛት 190 ሺህ ነው። ሱዳን 45 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 43 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 830 ታንኮች፣ 450 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ያላት ሲሆን የአገሪቱ ዓመታዊ የመከላከያ በጀት 4 ቢሊየን ዶላር ነው።
በአፍሪካ አህጉር ግብጽ በወታደራዊ ኃይል የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ፣ ኢትዮጵያ 6ኛ፣ ሱዳን ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት መካከል ኬንያ ከአፍሪካ 12ኛ፣ ደቡብ ሱዳን 22ኛ፣ ሶማሊያ ደግሞ 34ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በወታደራዊ አቅም ቀዳሚዎቹ 20 የዓለም አገራት
አሜሪካ
ሩሲያ
ቻይና
ህንድ
ጃፓን
ደቡብ ኮርያ
ፈረንሳይ
ዩናይትድ ኪንግደም
ብራዚል
ፓኪስታን
ቱርክ
ጣልያን
ግብጽ
ኢራን
ጀርመን
ኢንዶኔዥያ
ሳኡዲ አረቢያ
ስፔን
አውስትራሊያ
እስራኤል

 በአመቱ በመላው አለም 1.24 ቢሊዮን ሞባይል ስልኮች ተሸጠዋል

            አለማችን በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥና መዘጋት ምክንያት በድምሩ 4 ሚሊዮን ዶላር ያህል ማጣቷን ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነው ቶፕ10ቪፒኤን የተባለ የጥናት ተቋም አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ በአመቱ በተደጋጋሚ ኢንተርኔትን በመዝጋት ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን የያዘችው ህንድ ስትሆን፣ አገሪቱ ላለፉት 12 ወራት ከ75 ጊዜያት በላይ ኢንተርኔትን በመዝጋቷ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ አጥታለች፡፡
በ2020 አለማችን በኢንተርኔት መዘጋት ሳቢያ ያጣችው ገንዘብ ካለፈው 2019 አመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያህል ቅናሽ ማሳየቱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በመላው አለም በድምሩ ለ27 ሺህ 165 ሰዓታት ያህል ኢንተርኔት መቋረጡንና በዚህም 268 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተጎጂ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ዜና ደግሞ፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 በመላው አለም 1.24 ቢሊዮን ያህል የሞባይል ስልኮች ለሽያጭ መብቃታቸውን ዲጂታይምስ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ያስታወቀ ሲሆን፣ አለማቀፉ የሞባይል ስልኮች ሽያጭ በ2019 ከነበረበት የ8.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገቡት የአለማችን ሶስቱ ግዙፍ የሞባይል አምራች ኩባንያዎች ሳምሰንግ፣ አፕል እና ሁዋዌ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ዚያኦሚ፣ ኦፖ እና ቪቮ ይከተላሉ ብሏል፡፡
በአመቱ ከ10 በመቶ በላይ የሽያጭ እድገት ያስመዘገቡት ሁለቱ ኩባንያዎች አፕልና ዚያኦሚ ብቻ እንደሆኑ ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ሳምሰንግ እና ሁዋዌ ሽያጫቸው በሁለት ዲጂት መቀነሱንም አክሎ ገልጧል፡፡

  ላለፉት 35 አመታት ኡጋንዳን ያስተዳደሩት ዩሪ ሙሴቬኒ ትናንት በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለ6ኛ ጊዜ ለመመረጥና የስልጣን ዘመናቸውን ወደ 40 አመታት ለማራዘም ቆርጠው መነሳታቸው ተነግሯል፡፡
አገሪቱን ወደ ውጥረትና ብጥብጥ እያስገባት የሚገኘው የዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ይሆናል ብሎ እንደማይጠብቅ የተባበሩት መንግስታት በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ፣ የውጭ አገራት መንግስታት በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላለፉት ሙሴቬኒ፣ ፌስቡክን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾችን ማስዘጋታቸውንም አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከስልጣን መውረድን እንደሞት እንደሚፈሩት የሚነገርላቸው ሙሴቬኒ፣ ከአራት አመታት በፊት ባደረጉት የህገ መንግስት ማሻሻያ የአገሪቱን መሪ የ75 አመት ዕድሜ ገደብ ማንሳታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ በዘንድሮው ምርጫ ከሚወዳደሩት 10 ዕጩዎች መካከል የ76 አመቱን አዛውንት ዩሪ ሙሴቬኒን ያሰጋቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው መንግስት ደጋግሞ ሲፈታ ሲያስረው የከረመው ቦብ ዋይኒ የተባለው ታዋቂ የአገሪቱ ድምጻዊ አንዱ ነው ብሏል፡፡
በአፍሪካ አህጉር ለረጀም ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩ 10 መሪዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገው ሮይተርስ በበኩሉ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒው ቴዎዶሮ ኦቢያንግ 41 አመታት ከ5 ወራት፣ የካሜሩኑ ፖል ቢያ 38 አመታት ከ2 ወራት፣ የኮንጎ ሪፐብሊኩ ዴኒስ ሳሱ ኑጌሶ 36 አመታት ከ9 ወራት፣ የኡጋንዳው ሙሴቬኒ 34 አመታት ከ11 ወራት፣ የኢስዋቲኒው ንጉስ ሳዋቲ 34 አመታት ከ8 ወራት፣ የቻዱ ኢድሪሲ ዴቢ 30 አመታት ከ1 ወር፣ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ 27 አመታት ከ7 ወራት፣ የጅቡቲው ኢስማኤል ኦማር ጌሌ 21 አመታት ከ8 ወራት፣ የሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ 6ኛ 21 አመታት ከ5 ወራት፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ 20 አመታት ከ8 ወራት በመግዛት እንደቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን አመልክቷል፡፡

ትራምፕን ከስልጣን ለማውረድና በወንጀል ለመክሰስ ታስቧል

           ባሳለፍነው ሳምንት በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ምርጫ አመጣሽ አመጽና ብጥብጥ ያስተናገደቺው አሜሪካ፣ በቀጣዮቹ ቀናትና በተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት ሰሞንም ታጥቀው በሚወጡ የትራምፕ ደጋፊዎችና ጽንፈኛ ቡድኖች ከዳር እስከ ዳር በአመጽ ልትናጥ እና ከፍተኛ ጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ኤፍቢአይ አስጠንቅቋል፡፡
የጆ ባይደን በዓለ ሲመት እስከሚፈጸምበት ጥር 12 ቀን ድረስ በ50 የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ የመንግስት መቀመጫዎች እንዲሁም በዋሺንግተኑ የፌዴራል መንግስት መቀመጫ ካፒቶል ሂል በትጥቅ የታገዙ አመጾች በትራምፕ ደጋፊዎችና በጽንፈኛ ቡድኖች ሊቀሰቀሱ እንደሚችሉ የፌዴራሉ ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ በዓለ ሲመቱ በትራምፕ ደጋፊዎች አመጽና ብጥብጥ እንዳይስተጓጎል ለመከላከል ካፒቶል ሂል ዙሪያውን እየታጠረ እንደሚገኝም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙት የአመጽ ድርጊት ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቱን በ25ኛው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ መሰረት ከስልጣን ለማውረድና ምክትሉ ስልጣኑን እንዲረከብ ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ በምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ተቀባይነት ማጣቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ትራምፕን በኢምፒችመንት ከስልጣን ለማውረድና አመጽ በመቀስቀስ ወንጀል ለመክሰስ መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡
ትራምፕ ባላመኑበትና ባልተቀበሉት የምርጫ ውጤት ተሸንፈው ከነጩ ቤተ መንግስት ሳይወዱ በግድ ሊወጡ የቀራቸው የቀናት እድሜ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ግን በአገሪቱ መንግስት መቀመጫ ህንጻ ላይ ደጋፊዎቻቸው የፈጸሙትን ህገወጥ ድርጊት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢምፒችመንት ከስልጣን ለማስወገድ መጣደፍ የጀመረው ሰውዬው በቀጣይ ምርጫዎች እንዳይሳተፉ ለማድረግ ነው መባሉን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥቂት ቀናት ከቀረው ሥልጣናቸው ለማባረር የሚያደርጉት ጥረት ከሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ድጋፍ እያገኘ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፣ ትራምፕ ከሥልጣን እንዲባረሩ የሚጠይቀው ክስ እንዲመሰረትባቸው ድጋፋቸውን ከገለጹት መካከል ከፍተኛዋ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴ ሊዝ ቼኒ እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
የትራምፕ ደጋፊዎች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በታላቁ የአገሪቱ ተቋም ካፒቶል ሂል ላይ በፈጸሙትና አምስት ሰዎችን ለሞት በዳረገው አጉራ ዘለል የአመጽና የብጥብጥ ድርጊት ተሳታፊ እና ተባባሪ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ የፖሊስ አባላት ከስራ መታገዳቸውንና በ15 ያህል ፖሊሶች ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ የዘገበው ቢቢሲ፣ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ ከስራ እስከማባረር የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል መባሉን ገልጧል፡፡
ከአመጽ ድርጊቱ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ትራምፕን በቋሚነትና በጊዜያዊነት ማገዳቸውን የገፉበት ሲሆን፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ትዊተር የትራምፕን አካውንቶች ከዘጉ ከቀናት በኋላ ሰሞኑን ደግሞ ዩቲዩብ ሰውዬውን ለአንድ ሳምንት አዲስ ቪዲዮ እንዳይለቅቁ ማገዱ ተነግሯል፡፡

   የተአማኒነት አቀራረብ
ጥንታዊያን ግሪኮችና ሮማያዊያን ንግግር ዐዋቂዎች፤ አንድ ክርክር ይበልጥ አሳማኝ የሚሆነው አድማጭ በተናጋሪው ላይ እምነት ሲኖረው ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ አርስጣጣሊስ (Aristotle) እምነት፤ አንዲህ ዓይነት ነገር የሚኖረው በተናጋሪው የቀደመ ዝና ሳይሆን በወቅቱ የሚቀርበው በራሱ በንግግሩ ውስጥ በባለው አሳማኝ ፍሬ ነገር ነው፡፡ የተናጋሪው ባህሪና የሚያቀርበው ነገር፣ የተናጋሪው የአነጋገር ቃና፣ የቃላት ምርጫ፣ ምክንያቶችን በአግባቡ መደርደሩ፣ የተለያዩ አማራጮች አመለካከቶችን ሲያቀርብ የሚያሳየው ሥርዓትን የተከተለ ሁኔታ በአድማጮቹ ዘንድ የተአማኒነት ሰብዕና እንዲፈጠር ያደርገዋል፡፡ አንድ ፀሀፊ ወይም ተናጋሪ ተአማኒነትን የሚፈጥርባቸው ሶስት መንገዶች አሉ፡፡ የእርስዎ መንገድ ከእነዚህ አንዱ ከሆነ የሚከተሉትን አስተያየቶች ተግባራዊ ያድርጉ፡፡
በሚያቀርቡት ርዕስ ላይ ዕውቀት ይኑርዎት፡፡
ሚዛናዊ ይሁኑ፡፡
ሀ.ተደራሾች ጋር የሚያገናኝዎትን ድልድይ ይገንቡ፡፡
እያንዳንዳቸውን በአጭሩ እንመልከት
ሀ. በሚያቀርቡት ርዕስ ላይ እውቀት ይኑረዎ።
ታማኝነትን የማግኛ የመጀመሪያው መንገድ ታማኝ መሆን ነው፤ ይህም ማለት ጠንካራ መሰረት ያለው ዕውቀት ይዞ መከራከር፣ በቂ ምሳሌዎች፣ የግል ተሞክሮዎችን፤ አህዛዊ መረጃዎችንና ሌሎች ለጉዳዩ አስፈላጊ የሆኑ ጠቃሚና ተጨባጭ መረጃዎችን ማቅረብ መቻል ማለት ነው። የቤት ሥራዎትን ከሰሩ በእርግጠኝነት የአብዛኛዎቹን ተደራሲያን (audiences) ትኩረት ይስባሉ፡፡
ለ ሚዛናዊ ይሁኑ?
በሚያቀርቡት ርዕስ ላይ ዕውቀት ያለዎት ከመሆን በተጨማሪ ለአማራጭ አመለካከቶችም ሚዛናዊነትንና ትህትናን በተግባር ማሳየት አለብዎት፡፡ ይህ የሚሆንበትም ምክንያት እውነተኛ ክርክር ሊከሰት ከሚችልባቸው አቀራረቦች አንዱ፣ ሰዎች ከሌላው ሀሳብ ጋር ያላቸውን ልዩነት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲገለፁ ብቻ ነው፡፡ የሌላውን ወገን ሀሳብና የቀረቡትን አማራጭ ነጥቦች የተረዱና የተገነዘቡ መሆንዎን በተግባር ካሳዩ፣ የእርስዎ ተአማኒነት የበለጠ ይጠናከራል፡፡ በእርግጥ ተቃራኒ አመለካከትን በአግባቡ ሊያጣጥሉ የሚችሉበት ጊዜ ይኖራል፡፡ እነዚህን ጊዜያት ግን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የሚከሰቱትም ተደራሲዎችን ስለ አመለካከትዎ በቅድሚያ ዝንባሌ እንዲያሳዩ መልዕክት ሲያስተላፍልፉ ነው። በአጠቃላይ ለአማራጭ አመለካከቶች ድጋፍና ክብር ማሳየት ከሁሉም የበለጠ ስልት ነው፡፡
ሐ. ከተደራሲዎች ጋር የሚያገናኙትን ድልድይ ይገንቡ።
ክርክርዎን በጋራ በሆኑ እሴቶችና ታሳቢዎች ላይ እንዲመሰረት በማድረግ መልካም ፈቃደኝነትዎን በተግባር ካሳዩ እምነት የሚጣልብዎትን በተደራሲያኑ ዘንድ የተደራሲውን አመለካከት የሚያከብሩ ሰው መሆንዎን የሚያሳይ ገፅታን ይገነባሉ፡፡
እምነታችንና ስሜታችንን እንዴት ማቅረብ ይቻላል?
አንድን ነገር መገንዘብ ማለት ስለዚያ ነገር የሚሰማንን ስሜት መረዳት በመሆኑ ስሜትን ገላጭ አቀራረብ የግድ ምክንያታዊ ባይሆንም አመክንዮ ያልሆነን ነገር የማወቅ ዕድል ሊሰጠን ይችላል፡፡ ስሜትን ገላጭ አቀራረብ አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ሲያቀርብ፣ በዚያ ጉዳይ ውስጥ ስለ አለው ጥልቅ ነገር እንድናይ ይረዳናል፡፡ ለዚህም  ነው ብዙ ጊዜ ክርክሮች፣ ታሪኮችን በመጠቀም የአንድ ችግር እውነታ በስሜታችን አማካይነት እንድናይ፣እንዲሰማንና ጎምዛዛም ቢሆን እንድናጣጥም  የሚያደርጉን፡፡
ሰሜትን ገላጭ አቀራረቦች ሕጋዊ የማይሆኑት አንድን ጉዳይ ግልጽ ከማደረግ ይልቅ ግራ የሚያጋባ ሲያደርጉት ነው። ፀሐፊዎች ወይም ተናገሪዎች የለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ስሜት ገላጭ የሆኑ አቀራረቦችን መፍጠር ይችላሉ፡፡ እነዚህም ተጨባጭ ቋንቋ፤ ልዩ ምሳሌዎችና ማነፃፀሪያ ነገሮች፣ ትረካዎች፣ ደርብ ትርጉም ያላቸው ቃላት፣ ዘይቤያዊ አነጋገርና ተመሳሳይ ማመሳከሪያዎች ናቸው፡፡
(በሲሳይ አሰፋ ተሰማ ከተዘጋጀውና “በክርክር እና በውይይት የማሸነፊያ ስልቶች” በሚል ርዕስ ከበቃው መጽሃፍ የተቀነጨበ)Page 6 of 516