Administrator
Saturday, 30 May 2026 00:00
ፒኤስጂ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በድጋሚ በላ!
የፈረንሳዩ ሀያል ክለብ ፒኤስጂ በታሪክ እጅግ አስገራሚ የሚባል ስኬት በማስመዝገብ፣ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር የደረሰውን አርሰናልን በመለያ ምት በመርታት ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የሻምፒዮናው ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል። በፑሽካሽ አሬና በተደረገው በዚህ እጅግ አስደናቂ የፍጻሜ ፍልሚያ፣ ካይ ሀቨርትዝ ለአርሰናል ቀዳሚዋን ግብ ቢያስቆጥርም ፒኤስጂዎች ተስፋ ሳይቆርጡ በመታገል በኦስማን ዴምቤሌ የ65ኛው ደቂቃ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜና የ30 ደቂቃ ጭማሪ ሰዓት 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት አምርቷል። ፒኤስጂዎች ባሳዩት የተረጋጋ ብቃትና ከፍተኛ ልምድ በመለያ ምት 4 ለ 3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን በድጋሚ ወደ ፓሪስ መውሰድ የቻሉ ሲሆን፣ በአውሮፓ እግር ኳስ መድረክ ላይ ያላቸውን ፍፁም የበላይነት በድጋሚ በተግባር አስመስክረዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ስፖርት አድማስ
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 15:01
የዒድ አል-አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ ስታድየም
Published in
ዜና
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:41
በ2032 የጨረቃ ላይ ኑሮ ይጀመራል፡ የናሳ አዲስ ዕቅድ ይፋ ሆነ!
ናሳ እ.ኤ.አ. በ2032 እና ከዚያ በኋላ "በጨረቃ ላይ መኖርና መስራትን" እውን ለማድረግ ያለውን እቅድ ይፋ አድርጓል። ይህ የጠፈር ተመራማሪዎች ተቋም በመቶዎች የሚቆጠሩ ስኩዌር ማይሎች ስፋት ያለው ቋሚ የጨረቃ ቤዝ ለመገንባት አቅዷል።
ተቋሙ ይህንን የጨረቃ ቤዝ "በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ላይ ቀጣይነት ያለው የሰው ልጅ ቆይታን እንዲሁም የሰፉ ሳይንሳዊና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማስቻል የተነደፈ ተነሳሽነት" ሲል ገልጾታል።
ዛሬ ይፋ በተደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ የሰው ልጆች ከ2032 ጀምሮ በቋሚነት ጨረቃ ላይ መኖር ይጀምራሉ።
The Mirror-
Published in
አግራሞት
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:40
አሜሪካ በኢቦላ የተጠረጠሩ ዜጎቿን ማቆያ በኬንያ ልትገነባ ነው
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በኡጋንዳ እየተስፋፋ ያለውን የኢቦላ ወረርሽኝ ተከትሎ፣ ለቫይረሱ የተጋለጡ ወይም በበሽታው የተያዙ የአሜሪካ ዜጎችን ለይቶ ማቆያ የሚሆን ተቋም በኬንያ ለመገንባት ማቀዱን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። ይህንን ተቋም ለማቋቋምም የአሜሪካ የህዝብ ጤና አገልግሎት የተባለው የሲቪል መኮንኖች ስብስብ አባላት ወደ ስፍራው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ እየቀረበላቸው ይገኛል። ይሁን እንጂ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ ይህንን ተቋም በተመለከተ የወጡትን መረጃዎች በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የዚህ ተቋም ግንባታ የታቀደው የዓለም ጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የ«ቡንዲቡግዮ» የኢቦላ ዝርያ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የህዝብ ጤና አስቸኳይ አዋጅ ብሎ ካወጀ በኋላ ነው። በሽታው በሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት በቀጥታ ንክኪ የሚተላለፍና ለሞት የሚዳርግ አደገኛ ወረርሽኝ ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ከኬንያው ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ወደ ተጎዱት አካባቢዎች የሚጓጓዙ የ4.7 ቶን የህክምና ቁሳቁሶችንና የአደጋ ጊዜ እርዳታዎችን እያስተባበረ ይገኛል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ሰራተኞቹ በአገሪቱ መግቢያ በሮች ላይ የኢቦላ ምርመራዎችን ለመደገፍ በአስቸኳይ እንዲሰማሩ ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም፣ እስካሁን በአሜሪካ ውስጥ የተረጋገጠ የኢቦላ ህመምተኛ አለመገኘቱንና ለአጠቃላይ ህዝቡ ያለው ስጋት አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቋል።
Published in
ዜና
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:39
በአማራ ክልል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰሩና የአካላዊ ቅጣት ሰለባ የሆኑ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በሚገኙ 32 ፖሊስ ጣቢያዎች ባደረገው የሰብዓዊ መብት ክትትል፣ “ወቅታዊ ጉዳይ’’ በሚል ምክንያት የተያዙ ተጠርጣሪዎች እስከ ሰባት ወራት ድረስ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸውን አስታውቋል። ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሚታሰሩ፣ በሕጉ በተቀመጠው 48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡና ቀን ላይ ማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ተዘግቶባቸው እንደሚውሉ ሪፖርቱ አመልክቷል። በተጨማሪም የታሳሪዎች የመጎብኘት መብት መነፈጉ እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥሠቶች ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ የተለየ ድጋፍ እንዲሁም ወጥ የሆነ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት አለመኖሩ አሳሳቢ ሆኖ መገኘቱ ተገልጧል።
በክትትል ሂደቱ በተወሰኑ ጣቢያዎች በፖሊሶች የሚፈጸሙ ማስፈራሪያዎች፣ ዛቻዎች፣ ስድቦችና አካላዊ ቅጣቶች መኖራቸውን ኢሰመኮ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይበልጥ የከፋ አድርጎታል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ የቀረቡትን ግኝቶች የነባራዊ ሁኔታው ነጸብራቅ መሆናቸውን በመግለጽ የተቀበላቸው ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻልና ሕጋዊ አሰራርን ለማስፈን አፋጣኝ የእርምት እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ ተመላክቷል።
Published in
ዜና
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:38
ከፈታኝ ድርቅ ወደ ምሳሌያዊ ምርታማነት
በምሥራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ እየታየ ያለው አስደናቂ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ታሪካዊ ጉዞ ህያው ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የአካባቢው አርሶ አደሮች ከ 176,223 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የቻሉ ሲሆን፣ ከዚህ መሬትም ከ 3.1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት የታቀደው ዕቅድ በከፍተኛ ስኬት ላይ ይገኛል።
ለዚህ ታላቅ ስኬት መገኘት ቁልፍ ሚና የተጫወቱት ከ 101,000 በላይ አባወራዎችና እማወራዎች የተሳተፉበት ሰፊ የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ ዘመናዊ ትራክተሮችንና የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም ውጤታማ የክላስተር እርሻ አሰራር ናቸው። እነዚህ የተቀናጁ አሰራሮች የአካባቢውን እምቅ አቅም ወደ ላቀ ምርታማነት ለመቀየር አስችለዋል።
በሊበን ወረዳ ከሚገኙት ሰፋፊ የስንዴ ክላስተሮች ጀምሮ እስከ ዋና ዋናዎቹ የጤፍ፣ የበቆሎ እና የቦሎቄ ምርቶች ድረስ እየታየ ያለው አበረታች ውጤት፤ የሀገር ውስጥ የምግብ አቅርቦትን የማረጋገጥ ጉዞ ከዕቅድ ባለፈ በተግባር መሬት ላይ እየተመሰከረ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:36
በቁጫ ምርጫ ክልል ሊደረግ የታሰበው ምርጫ እንዲታገድ ፓርቲው ጠየቀ
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በቁጫ ምርጫ ክልል የሚካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫና የምርጫ ውጤት ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበል በመግለጽ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ፓርቲው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ ሕገ-መንግሥታዊ መብት የገፈፈ፣ አግላይ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ደንቦችን የሚቃረን ነው ሲል ኮንኗል። ከ2013 ዓ.ም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ በፓርቲው አባላት፣ አመራሮችና መራጩ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ቁሕዴፓ፣ አሁን ባለው ነፃነትና እኩልነት በሌለው ምህዳር የሚደረግን “ለይስሙላ” ምርጫ እንደማይቀበል በቁራጭ አስታውቋል።

ፓርቲው በሰጠው መግለጫ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ፣ የመንግሥት የፀጥታ አካላትና የታጠቁ ኃይሎች በቁጫ ምርጫ ክልል የሚገኙ ከ16 በላይ ጽሕፈት ቤቶቹን በኃይል እንደዘጉበት ገልጿል። በተጨማሪም የፓርቲው ዕጩዎችና አባላት የምርጫ ማኒፌስቶ፣ ዓርማና ባንዲራ ይዘው የአደባባይ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ ሕገ-ወጥ ዕገታና የግድያ ሙከራ እንደተፈጸመባቸው ይፋ አድርጓል። በአሁኑ ወቅትም መራጮች ቁሕዴፓን እንዳይመርጡ የአደባባይ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን፣ የምርጫ ካርድ ከሕዝቡ እጅ በኃይል የመሰብሰብ፣ የመደብደብና በገንዘብ የመቅጣት ድርጊቶች በስፋት እየተፈጸሙ መሆኑን ፓርቲው በዝርዝር አስረድቷል።
በመሆኑም የቁጫ ሕዝብ መከራና ውጥረት እየበረታ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴራል መንግሥትና የሰብዓዊ መብት ተቋማት አስቸኳይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ቁሕዴፓ ጥሪ አቅርቧል። በቁጫ ምርጫ ክልል ሊደረግ የታሰበው ምርጫ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይና የተፈጸሙት ሕገ-ወጥ ግድፈቶች በአስቸኳይ ታርመው ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ድጋሚ እንዲካሄድ ምርጫ ቦርድን አበክሮ ጠይቋል። ፓርቲው የሕዝቡን ሕገ-መንግሥታዊ ጥቅምና ራስን የማስተዳደር መብት ለማስከበር የሚያደርገውን ፍጹም ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በክብር አረጋግጧል።
Published in
ዜና
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:35
የአክሱም አዲስ ስያሜ ተቃውሞና የአል-ነጃሺ መስጊድ የዩኔስኮ ጥሪ
የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በመቐለ በተካሄደው የዒድ ሶላት ላይ ባስተላለፈው መግለጫ፣ "ቅድስት ከተማ አክሱም" የሚለው አዲስ የከተማ መጠሪያ ስም ፍትሃዊ ባለመሆኑ እንደሚቃወመው አስታውቋል። ምክር ቤቱ በአክሱም ከተማ ላለው ወቅታዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ በሰላማዊ መንገድ እንደሚታገል የገለጸ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሆን ብለው የተዛባና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ሥርዓት እንዲይዙ በጥብቅ አሳስቧል።
በተጨማሪም፣ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪካዊውን የአል-ነጃሺ መስጊድ አስመልክቶ ጥሪ አቅርቧል። መስጊዱ ያለውን ጥልቅ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ዳራ መነሻ በማድረግ፣ ተገቢው ሙሉ እውቅና ተሰጥቶት በዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ በቋሚነት እንዲመዘገብ የፌዴራልም ሆነ የዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቋል።
Published in
ዜና
Tagged under
Wednesday, 27 May 2026 11:34
ቡርኪና ፋሶ የቀንድ ከብት ወደ ውጭ መላክን በጊዜያዊነት አገደች
ቡርኪና ፋሶ የአገር ውስጥ የእንስሳት አቅርቦትን ለማሟላት ስትል ማንኛውንም ዓይነት የቀንድ ከብትና እንስሳት ወደ ውጭ መላክን በጊዜያዊነት አግዳለች። ባለሥልጣናቱ እንደገለጹት፥ ውሳኔው በአገር ውስጥ ያለውን የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍና የዋጋ መናርን ለማረጋጋት ያለመ ነው።
ይህ እርምጃ በብዙ የአገሪቱ ዜጎችና ተጠቃሚዎች ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ ያገኘ ቢሆንም፥ የእንስሳት ነጋዴዎች ግን እገዳው በንግድ ሥራቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸውና ከአካባቢያዊ ንግድ ያገኙት የነበረውን ዋና የገቢ ምንጭ እንደገደበባቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
Published in
ከአለም ዙሪያ
Tagged under
Tuesday, 26 May 2026 19:47
እንኳን ለ1447ኛው የዒድ አል አድሐ በዓል አደረሰን፣ አደረሳችሁ!
ስለዒድ አል-አድሐ “ዐረፋ” በዓል ስናስብ ሦስት ነገሮች ቀድመው ይታወሱናል። መስዕዋትነት፣ መታዘዝ እና መተጋገዝ። አባት ልጁን ለመስዕዋት ያቀረበበት፤ ልጅ የአባቱን ትዕዛዝ የፈጸመበት፤ ሙስሊሞች የመተጋገዝን እሴት ለዓለም የገለጡበት በዓል ስለሆነ “ዐረፋ” በሕዝበ-ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ትርጉም አለው።
እስማኤል ለነብዩ ኢብራሂም የመጀመሪያ እና ተወዳጅ ልጃቸው ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ይሄን ተወዳጅና የመጀመሪያ ልጅ እንዲሠዉለት ሲጠይቃቸው ታዘዙ እንጂ ወደኋላ አላሉም። ለመታዘዝ የሞከሩት ነገሩ ቀላል ሆኖ አይደለም። ልጅን ያህል ነገር መስዕዋት ማድረግ ምኑ ይቀላል? የአባትነት ስሜት ይተናነቃል። የሰይጣን ሹክሹክታ ይፈታተናል። የቤተዘመድን ወቀሳ እና የጎረቤትን አስተያየት መቋቋምም ይከብዳል። ነብዩ ኢብራሒም፥ በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ አንድ ሐቅ ተገልጦላቸዋል። ከራስ ስሜት፣ ከሰው ሐሜት እና ከወዳጅ ፍላጎት የሚልቅ ታላቅ ዓላማ እንዳለ አምነዋል። ስለዚህም በፈተና ውስጥ ጸንተው ቆሙ፤ ቆራጥነታቸውም በተግባር ታየ።
ሀገር የምትገነባው ከራስ ጥቅም በላይ በሚያስቡ እና ከግላዊ ፍላጎታቸው በላይ ለመፈጸም በቆረጡ ዜጎች ነው። የሚወዱትን ነገር እንኳን ሳይቀር ለመሠዋት ዝግጁ የሆኑ ዜጎች ሲበዙላት ሀገር ትበረታለች። እስማኤላቸውን ለመስጠት የማያመነቱ ዜጎች የሞሉባት ሀገር ጽኑ ናት።
የለመድናቸው፣ የምንወዳቸው፣ የራሳችን ገንዘብ ያደረግናቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ከእነዚህ የሚበልጥ ዓላማ ግን አለ፤ እሱም “ሀገርነት እና ሉአላዊነት” ይሰኛል። ሀገርነት የሚገነባው ከመውሰድ ይልቅ በመስጠት ነው። ሉአላዊነት የሚጸናው በፈተና ሳይወድቁ በመቆም፤ በወጀብ ሳይናወጡ መጓዝ በመቻል ነው።
የእውነት ኢትዮጵያ ሲያልፍላት ማየት የምንሻ ከሆነ ምኞታችን በተግባር ይገለጥ። የሀገር ኩስመና ካሳሰበን ለግዝፈቷ እንድከም። ያጎበጣትን የድህነት ቋጥኝ ለመሸከም ትከሻችንን እናመቻች። ጎተራዋ እንዲሞላ እጃችን አፈር ይንካ። የጠየመ ገጽዋ እንዲፈካ በሥራ ሌት-ተቀን እንሰለፍ። የተቀማ ክብሯ እስኪመለስ ድርሻችንን እንወጣ። ሀገር መውደዳችን ከልብ ከሆነ መስዕዋት ለመሆን አናመንታ።
የዐረፋ በዓል የመታዘዝና የመስዕዋት ብቻ ሳይሆን የመደጋገፍና የመተጋገዝ በዓል ጭምር ነው። በዐረፋ ከሚከናወነው እርድ አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች እንዲሰጥ የእስልምና አስተምህሮ ያዛል። በዐረፋ ሕዝበ-ሙስሊሙ ደስታና ሐዘኑን እየተጋራ በዓሉን ያከብራል። የዐረፋ እለት አንድም ሰው ተከፍቶ አያሳልፍም፤ በዐረፋ ሰሞን ማንም ሰው ተርቦና ተጠምቶ አያድርም። በዓሉ ትርጉም የሚሰጠው ሕዝበ-ሙስሊሙ ያለውን ተካፍሎ ሲያከብረው ነው። ሰዎች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚሻገሩበት መፍትሄው መተሳሰብና መተጋገዝ እንደሆነ ከዐረፋ እንማራለን። ሀገርም ከፈተናዎችዋ በላይ እንድትሆን እኒህ እሴቶች ወሳኝ ናቸው።
ዐረፋ ማኅበረሰባዊ በዓል የሚባለው ለዚህ ነው። ሰዎች በግላቸው የሚያከብሩት አይደለም። ቤተሰቡ፣ ጎረቤቱ፣ ሠፈሩ፣ ከተማው የሚያከብረው በዓል ነው። ያላቸውና የሌላቸው፤ የሚችሉና የማይችሉ፤ ታላላቆችና ታናናሾች፤ ባለ ሥልጣናትና ተራ ዜጎች፣ በአንድነት የሚያከብሩት በዓል ነው። ሰው የሚኖረው በቤቱ ውስጥ አይደለም። በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው።
ማኅበረሰባዊ ትሥሥርና ትብብር ለዜጎች እና ለሀገር ደኅንነት ወሳኝ ናቸው። ማኅበረሰባዊ ትሥሥር ስለሌሎች እንድናስብ፣ ስለሌሎች እንድንሠራ እና ስለ ሌሎች ዋጋ እንድንከፍል ያደርገናል። ራሳችንን በሌሎች ጫማ ላይ አቁመን እንድናይ ያስችለናል። የሁላችንም ሰላም፣ የሁላችንም ደኅንነት እና የሁላችንም ጥቅም ካልተከበረ በቀር የግላችንን ብቻ ልናስከብር እንደማንችል ያስገነዝበናል። ስለዚህም ማኅበራዊ ግዴታን እንደ ዜግነት ግዴታ ወስደን እንድንሠራ ያደርገናል።
ምርጫ ማኅበራዊና ዜግነታዊ ግዴታዎችን ከምንወጣባቸው የዴሞክራሲ መገንቢያ መሳሪያዎች መካከል ዋነኛው ነው። ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲ አይሳካም። ያለ ምርጫም የሕዝብ ተሳትፎ ምሉዕ አይሆንም። የዴሞክራሲያችን መሰረት ጥንካሬው የሚለካው በተሳትፎአችን መጠን ነው።
የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሀገረ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን የሚጠነክርበት መሰረት ነው። የዴሞክራሲ ልምምዳችን አንድ ደረጃ ከፍ የሚልበት፤ የቀጣይ ዓመታት የሀገራችንን እጣ-ፈንታ የምንበይንበት፤ ከምንም በላይ ብዝሃ-ድምጽ የሚሰማበት የሕግ መወሰኛ ምክርቤት የምንመሰርትበት ወሳኝ አጋጣሚ ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ዜግነታዊ ግዴታችንን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን በካርዳችን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለማረጋገጥ እየተዘጋጀን እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በድጋሚ መልካም የዐረፋ በዓል እንዲሆን እመኛለሁ!
ዒድ ሙባረክ!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ግንቦት 18፣ 2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Published in
ዜና
Tagged under

