Administrator

Administrator

2” ሐሙስ ይመረቃሉ ድምፃዊ፣ የዜማና ደራሲ ድምፃዊ ጌትሽ ማሞ ለህዝብ ጆሮ ያበቃቸው ሁለት ነጠላ ዜማዎች
(‹‹ተቀበል 1 እና 2››) የፊታችን ሐሙስ በፍሬንድሺፕ ሆቴል ኤቪ ክለብ ከምሽቱ 3፡00 ጀምሮ ይመረቃል፡፡
“ተቀበል” በተሰኘው ነጠላ ዜማው ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው ጌትሽ ማሞ፤ “ተቀበል 2”(እንከባበር) የሚል ነጠላ ዜማውም ተወዳጅነት
ማግኘቱ የተገለፀ ሲሆን የነዚህን ዜማዎች ቪዲዮ ክሊፕ ለማስመረቅ መወሰኑን ረቡዕ ረፋድ ላይ በፍሬንድሺፕ ሆቴል በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ከ15 በላይ ታዋቂ አርቲስቶች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡


ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ-
መፅሀፍትና ቤተ- መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ‹‹ኃሠሣ››በተሰኘው መፅሀፍ ላይ ውይይት ያካሂዳል፡፡
ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ ምሩቅ መሪ ጌታ
ፅጌ መዝቡ ሲሆኑ አዘጋጁ በውይይቱ ላይ ፍላጎት ያለው እንዲሳተፍ ጋብዟል፡፡

የክብር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ልጅ ዳንኤል ጥላሁን ገሰሰ “ኢትዮጵያን አትንኩ” የተሰኘው አዲስ ነጠላ ዜማና ቪዲዮ ክሊፕ ዛሬ ከምሽቱ 1፡00 ጀምሮ በካፒታል ሆቴል ይመረቃል። ድምፃዊ ዳንኤል ጥላሁን ከዚህ ቀደም ‹‹አባቴ ጥላዬ›› እና ‹‹እኔ ወይስ አንቺ›› የተሰኙትን የአባቱን ዘፈኖች አሻሽሎ መዝፈኑ ይታወሳል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊና የመዝናኛ ፕሮግራሞች ለታዳሚው መዘጋጀቱንም የሀብል ሚዲያና ማስታወቂያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚልኪያስ ጌታቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በደራሲ አሰግድ መኮንን የተፃፈውና እውነተኛ ታሪክ የሆነው ‹‹የቃል ፅናት›› መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ በአፋረንሲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ይመረቃል።መፅሀፉ ብሩክ ከበደ ስለተባሉ የጦር አርበኛ ታሪክና አሟሟት፣ ከመንዝና ግሼ ስንሰለታማ ተራሮች ጀምረው የተዋጉባቸውን ቦታዎች የጦርነቱን ሁኔና ይተርካል ተብሏል፡፡ በ230 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ81 ብር ከ60 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡
ፀሀፊው ከዚህ ቀደም ‹‹ኮብላይ››፣ ‹‹ጥብቅ ምስጢር››፣ ‹‹ነፀብራቅ››፣ ‹‹ማጎርሚ ሳቢብ››፣ ‹‹እኔና ህይወቴ›› ፣‹‹ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ›› እና ‹‹ሞትን
ቀደምኩት›› የተሰኙ መፅሀፍትን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወስ ሲሆን ‹‹የቃል ፅናት›› 8ኛ መፅሀፉ እንደሆነ ታውቋል፡፡

 የታዋቂው አፕል ኩባንያ ምርት የሆነው አይፎን ለገበያ መቅረብ የጀመረበትን አስረኛ አመት እያከበረ ሲሆን፣ ባለፉት አስር አመታት ከ1 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ አይነት የአይፎን ስማርት ስልኮችን ለተጠቃሚዎች መሸጣቸው ተነግሯል፡፡ ከአለማችን ፈርቀዳጅ የስማርት ስልኮች አንዱ የሆነው አይፎን ላለፉት አመታት ከፍተኛ ተወዳጅነት ይዞ በስፋት ሲሸጥ መቆየቱን የዘገበው ቴክ ኒውስ፣ አምራቹ ኩባንያ አፕልም ከትርፋማ ኩባንያዎች አንዱ ሆኖ መዝለቁን ገልጧል፡፡
በየሳምንቱ 500 ሚሊዮን ያህል አለማቀፍ ደንበኞች የአፕልን የአፕሊኬሽን ስቶር እንደሚጎበኙ የተነገረ ሲሆን፣ ባለፉት 10 አመታት ከ180 ቢሊዮን በላይ የአፕል አፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ መደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
አፕል በመጪው መስከረም ወር አዲሱን አይፎን 8 ስማርት ስልኩን ለገበያ ያበቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ የመሸጫ ዋጋው ከ1 ሺህ ዶላር በላይ ይሆናል መባሉንና ይህም ከአይፎን ስልኮች የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛው እንደሚሆን አስረድቷል፡፡

    ታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ ቴስላ እስካሁን ከተሰሩት ሁሉ በዋጋ አነስተኛው የተባለውን የመጀመሪያውን ቴስላ ሞዴል 3 የኤሌክትሪክ መኪና በትናንትናው ዕለት አምርቶ ማውጣቱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ አስታውቀዋል፡፡ ቴስላ ሞዴል 3 ተባለቺው በኤሌክትሪክ ሃየል የምትንቀሳቀሰውና አንድ ጊዜ ቻርጅ በመደረግ እስከ 215 ማይል ርቀት መጓዝ ትችላለች የተባለቺው አምስት ተሳፋሪዎችን የመያዝ አቅም ያላት አዲሷ የኩባንያው መኪና በ35 ሺህ ዶላር ለገበያ እንደቀረበች ሚረር ድረገጽ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው የአሌክትሪክ መኪና ለማምረት የሚያስችለውን ህጋዊ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ ከሚጠበቅበት ጊዜ በሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ማግኘቱን የዘገበው ሚረር ድረገጽ፣ እስከ ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ 32 መኪኖችን፣ እስከ መስከረም ወር ደግሞ 1ሺህ 500 መኪኖችን አምርቶ ለደንበኞቹ ለማስረከብ ስራ መጀመሩን ገልጧል፡፡
ቴስላ ኩባንያ የማምረት አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ እስከሚቀጥለው አመት ታህሳስ ወር ድረስ በወር 20ሺህ መኪኖችን የማምረት አቅም ላይ እንደሚደርስም ተነግሯል፡፡
ኩባንያው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ ከ25 ሺህ በላይ ሞዴል ኤክስ እና 51 ሺህ ያህል ሞዴል ኤስ የተባሉ መኪኖቹን ለደምበኞቹ በመሸጥ 7 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

  ቻይና በትልቅነቱ በአለማችን ቀዳሚነቱን ይይዛል የተባለውና በአመት 45 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለውን አዲሱ የቤጂንግ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በደቡባዊ ዳዢንግ አውራጃ እየገነባች ሮይተርስ ዘግቧል፡፡በ700 ሺህ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ይህ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ከሁለት አመታት በኋላ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቅቆ በአራት የማኮብኮቢያ መንገዶች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የጠቆመው ዘገባው፣ በቀጣይም ሌሎች ሁለት ማኮብኮቢያዎች እንደሚጨመሩለትና የማስተናገድ አቅሙ ወደ 100 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ገልጧል፡፡
በታዋቂው አርክቴክት ዛሃ ሃዲድ ዲዛይን የተደረገው አዲሱ የቤጂንግ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ፣ የመንገደኞችን መስተንግዶ የሚያቀላጥፍና በርካታ አውሮፕላኖችን ያለ አንዳች ችግር የሚያስተናግድ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

 በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰዋ የመን የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ1ሺህ 600 በላይ የመናውያንን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ ወረርሽኙ በስፋት በመሰራጨት ሁሉንም የአገሪቱ ግዛቶች ማዳረሱን ያስታወቀው ተመድ፣ ከ270 ሺህ ያህል ዜጎችም የኮሌራ ተጠቂ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ መገመቱን ገልጧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመግታትና
ታማሚዎችን በአግባቡ ለማከም ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ጃሪክ፣ ባለፈው ማክሰኞ 400 ቶን ያህል የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በኮሌራ የተጠቁ የመናውያንን ለማከም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 600 ያህል ጊዚያዊ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙም አመልክተዋል፡፡

  አሜሪካ ሰሜን ኮርያ በሳምንቱ መጀመሪያ ለፈጸመቺው የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ የከፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ ያደረገቺው ሰሜን ኮርያ እጅግ አደገኛ አካሄድ እየተከተለች ነው፤ ለዚህ ድርጊቷ ጠንከር ያለ ምላሽ ያስፈልጋታል ብለዋል ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ዋርሶ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብ ሰሜን ኮርያ ከዚህ አጥፊ ድርጊቷ እንድትታቀብ ማድረግ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የሰሜን ኮርያ ሚሳኤል ረጅም ርቀት በመጓዝ የአሜሪካዋን የአላስካ ግዛት የመምታት አቅም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሊ በበኩላቸው የሚሳኤል ሙከራውን ተከትሎ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ መጠነኛ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስታወቃቸውን አስታውሷል፡፡ ሰሜን ኮርያ የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለባትን ማዕቀብ በሚጥስ መልኩ የሚሳኤል ሙከራውን ማድረጓን ተከትሎ፣ የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን ድርጊቱን በጽኑ አውግዞታል፡፡ ደቡብ ኮርያን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መንግስታት ድርጊቱን ማውገዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር በሰሜን ኮርያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል፡፡
ሩስያና ቻይና በበኩላቸው ድርጊቱን ቢኮንኑም፣ እነ አሜሪካ የያዙትን ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ አማራጭ ለሌላ የከፋ ቀውስ የሚዳርግ አደገኛ አካሄድ በሚል እንደማይደግፉት አስታውቀዋል፡፡

 በሀዋሳ፣ የእኛው ለእኛ በጎ አድራጎት ማኅበር አባላት በበዓላት ወቅት ዶሮም ሆነ በሬ አርደው አረጋውያን አብረዋቸው በልተውና ጠጥተው ተደስተው ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ከእንብራ የማኅበር ሱቅ ዘይት፣ ዱቄት፣ ሳሙና፣… ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ገዝተው ለአረጋውን ይሰጣሉ፡፡ ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸውና በዝናብ ወቅት የሚያፈስ ቤት ክፍለ ከተማውን አስፈቅደው፣ ለጥገና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን የከተማው ባለፀጎች እንዲደግፏቸው ለምነው እነሱው አናጢ፣ እነሱው መራጊ፣ እነሱው ሁሉን ነገር ሆነው ቤታቸውን ይጠግኑላቸዋል፡፡
በየሳምንቱ እሁድ የአረጋውያን ቤት ይፀዳል፣ ልብሳቸው ይታጠባል፡፡ ሴት የማኅበሩ አባላት፤ እሁድ እሁድ ቡና አፍልተው በማጠጣት፣ ፀሐይ ሞቀውና ፈታ ብለው ወደ የቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ልብስ ከከተማው ማኅበረሰብ ሰብስበው (ለምነው) አረጋውያኑን ያለብሷቸዋል፡፡ የተሰበሰበው ልብስ ልካቸው ካልሆነ ተሽጦ በገንዘቡ በልካቸው ልብስ ይገዛላቸዋል፡፡ አንሶላ፣ ትራስ፣ ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣… እየገዙ ለአረጋውያኑ እንደሚሰጡ ወጣት አገኘሁ ወርቁ ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት ባለፈው ሳምንት የማኅበረሰብ ምሥርት ተቋማት የመልካም ተሞክሮ ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ለ3ኛ ጊዜ ባከበረበት ወቅት ተናግሯል፡፡
በባህርዳርም ከተማም ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዳለ፣ ለቀድሞ ባለውለታ አረጋውያን ክብር እየተሰጠ መሆኑን የባህርዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ተስፉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳኛቸው ከጥምረቱ ውጭ ፋና የሕፃናትና ማኅበረሰብ ልማት ማኅበር አስተባባሪ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን ለመደገፍ በከተማዋ ብዙ ተግባራት እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ፋና ማኅበር፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው፣ መሥራት ለማይችሉ፣ አልጋ ላይ ለወደቁ፣ ወጥተው መለመን እንኳ ለማይችሉና ለተረሱ 98 አረጋውያን ክብር በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው  ጠቅሰው፣ በራሳቸው መፀዳዳት የማይችሉትን የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር እንዲያፀዳዷቸውና ቤታቸውን በተራ እንዲያፀዱ፣ አረጋውያን ወደ ውጭ ወጥተው ፀሐይ የሚሞቁበት ተሸከርካሪ ወንበር የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር እንዲለግሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢሕማልድ) የዛሬ 32 ዓመት በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ለመታደግ የተቋቋመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ናቸው፡፡
በድርቁ ወቅት ድርጅቱ 6 የሕፃናት ማሳደጊያ ከፍቶ፣ ከ1000 በላይ ሕፃናትን ከተለያዩ አካባቢዎች ሰብስቦ ሲያሳድግ እንደነበረ የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ አንድ ሕፃን ኅብረተሰቡ ውስጥ አድጎ የኅብረተሰቡን እሴቶች ማወቅ፣ ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር ማግኘት ስላለበት ኅብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራ ውስጥ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን የልማት ሥራዎች ድርጅቱ ከዚያ ቢወጣ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? በማለት አንድ ማኅበር መስርተው 7 ዓመት አብረው ሰርተው ቢወጡም ምስርት ማኅበራትንና ዕድሮችን በማጎልበት ድርጅቱ ሲሰራ የነበረውን እነሱ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢሕማልድ በአሁኑ ወቅት እያከናውናቸው ያሉት 3 ፕሮግራሞች 1ኛ፡- በማኅበራዊ አገልግሎት በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ከቤተሰብ ጋር እያሉ መደገፍ፣ 2ኛው፡- የኑሮ ማሻሻያና የአካባቢ ጥበቃ፣ 3ኛው፡- የምስርት ተቋማትን አቅም ማጎልበትና ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የውጭ እጅ ከማየት ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አገር ውስጥ ያለን ሀብት በመጠቀም፣ ሀብቱ ውጤት እንዲያመጣ እየሠራን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤በዚህ ረገድ አንድ የስብሰባና የማሠልጠኛ ተቋም በቢሾፍቱ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ማሠራታቸውንና ይህ አሠራር ወደ ምስርት ማኅበራትም እየወረደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕንፃናትን በተቋም ከማሳደግ ይልቅ ማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ያለውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በመገንዘብ በ1996 ዓ.ም ከማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ጋር በሙከራ የተጀመረው የልማት ሥራ፤በአሁኑ ወቅት አድጎ በ22 የተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከ142 ማኅበራትና  ዕድሮች ጋር ዘላቂ የልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት የኢሕማልድ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ ቅጣው፤ቀደም ሲል አባላትን በማስተዛዘን ሥራ ላይ ብቻ ተጠምደው የነበሩ ዕድሮች የአሰራር ስልታቸውን በመቀየር ሕዝቡ የራሱን ችግር በራሱ ለመፍታት ኅብረተሰብ አቀፍ ልማት ውስጥ መግባታቸው ምርጥ ተሞክሮና ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡
በሐዋሳ ከተማ ከኢሕልማድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተው የእንብራ ራስ አገዝ ማኅበር ወጣት ቡድን አባል የሆነው አገኘሁ ወርቁ፣ አባቱን በሞት የተነጠቀው በኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ከእሱ ጋር የ3 ልጆች እናት የሆነችው እናቱ፤ምንም የሌላት የቤት እመቤት ነበረች። እቤት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ስለነበረባቸው አገኘሁ ወደ ጎዳና ወጣ፡፡ እየለመነና ትንንሽ ዕቃዎች በመሸከም የሚያገኘው መጠነኛ ገቢ፣ ጎዳና ከወጣ በኋላ ለለመደው ሱስ አልበቃ አለው፡፡ ስለዚህ እሱና ጓደኞቹ ጨለማን ተገን አድርገው ሞባይል መቀማትና ኪስ መበርበር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እሱ ከሌሎች ጓደኞቹ ፈርጠም ያለ ስለነበር ሰዎችን አንቆ ሲይዝ፣ ሌሎቹ ኪስ ገብተው ይበረብሩ ነበር፡፡ አሁን የእሱና የጓደኞቹ ሕይወት ተለውጧል፡፡
እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር አቅርቧቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክርና ስልጠና ሰጣቸው፡፡ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶላቸው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት ከቤት ወጥተው እንዲሰሩ አደረጋቸው፡፡ ፎቶ ኮፒ፣ መጠረዣና ማሸጊያ መሳሪያ ገዝቶ የሥራ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ከአገኘሁ ጋር ሲቀሙ ከነበሩት ጓደኞቹ አንደኛው አሁን 5ኛ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ፣ ወላይታ ሶዶ ውስጥ ሲኖትራክ እያሽከረከረ መሆኑን፣ አገኘሁ ደግሞ ሐዋሳ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ 2ኛ ዓመት ተማሪ መሆኑን ገልጾ፣ ሕይወቱ እንዲለወጥ ያደረገውን ኢሕማልድን ከልቡ አመስግኗል፡፡
በማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ምርጥ ተሞክሮ ቀን የተገኙ በርካታ ማኅበራትና ዕድሮች ኢሕማልድ ቢወጣ የራሳቸው ገቢ ማግኛ ፕሮጀክት ስላላቸው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንደማያቋርጡ ተናግረዋል፡፡  
የባህር ዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ሰይፉ ቤትና መጋዘን ሰርቶ በማከራየት፣ ሥጋ ቤት ከፍቶ በመነገድ፣ … በአጠቃላይ በተለያዩ የገቢ ማግኛ ፕሮጀክቶች በመሰማራት በዓመት ከ650 ሺህ ብር በላይ ስለሚያገኙ፣ ወላጅ አልባና የቤተሰባቸው የገቢ አቅም አነስተኛ የሆኑትን ሕፃናት አስፈላጊ ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ት/ቤት ልከው እያስተማሩ መሆኑን፣ ለቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ብድር በመስጠት የገቢ አቅም እንደፈጠሩላቸው፣ ለአረጋውያን የፈረሰባቸውን ቤት በመጠገን፣ በዓመት በዓል ጊዜ ከብት አርደው በማብላትና የተወሰነውን ወደ ቤታቸው ይዘው እንዲሄዱ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የተለያየ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሐዋሳና አካባቢው (ሻሸመኔና አቼቡራን ያጠቃልላል) ምስርት ማኅበራት ጥምረት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ከበደ የአቶ ዳኛቸውን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ጥምረታቸው 41 ዕድሮችና ማኅበራትን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢሕማልድ የሚያደርግላቸውን ድጋፍ ቢያቋርጥ ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን ማህበራዊ አገልግሎት ላለማቋረጥና ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ በ3,170,200 ብር ካፒታል አቋቁመው፣ 1,869,621 ብር ትርፍ ማግኘታቸው ገልጸዋል፡፡
ባገኙት ትርፍ፣ በማኅበሩ ውስጥ ላሉና ለሌሎች ችግረኛ ሕፃናት ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ወደ ጎዳና ለመውጣት እያኮበኮቡ እያሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው፣ ለወጣቶች 2500 ብር ተዘዋዋሪ ብድር በመስጠት የተለያየ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ ለችግረኛ ልጆች ቤተሰቦች 4000 ብር ብድር በመስጠት ነግደው የብድሩን 60 በመቶ ለራሳቸው ተጠቅመው፣ 40 በመቶውን እንዲመልሱ ይደረጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለገቢ ማግኛ በዕድሮችና ማኅበራት የሚተዳደሩ 15 ባጃጆች አሉ፡፡ እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር 3፣ የዕድሮች ኅብረት 4፣ 03 ቀበሌ መረዳጃ ማኅበር ዕድር 2፣ ሐረር ሰፈር መረዳጃ ዕድር 4 ባጃጆች፣ እንዳሏቸው የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ባጃጆቹ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ሲሠሩ ቆይተው ሌሊት ለሕሙማን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡