Administrator

Administrator


             በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አመራሮቹና አባላቱ በሰበብ አስባብ እየታሠሩበት መሆኑን የገለፀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፤ በየአካባቢው ህዝባዊ ውይይት ለማካሄድ መቸገሩንም አስታውቋል፡፡
በነቀምት የዞኑ የአፌኮ ጽ/ቤት አደራጅና ሰብሳቢ፣ በሆሮ ጉዳሩ የጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ በኢሊባቡር፣ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በቄለም ወለጋና በተለያዩ አካባቢዎች ከ20 በላይ አመራሮችና አባላት ከሰሞኑ እንደታሠሩበት ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
እስሩ እየተፈፀመ ያለው የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን በመፈለግ ነው ያሉት የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ አመራርና አባላቶቻችን ለምን ታሠሩ ብለን ስንጠይቅ፤ “ግማሾቹ በቤታቸው የጦር መማሪያ አከማችተው ተገኝተዋል፣ ግማሾቹ በመኖሪያ ቤታቸው ህገ ወጥ ስብሰባ አድርገዋል፤ በህገ ወጥ መንገድ አባላትን አደራጅተዋል” የሚል ምላሽ ይሠጠናል ብለዋል፡፡
የለውጥ ሂደቱን ተስፋ በማድረግ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በመላ ኦሮሚያ በሚገኙ 20 ዞኖች ውስጥ ጽ/ቤት መክፈቱንና በየወረዳዎቹም በርካታ የወረዳ ጽ/ቤቶችን በአንድ አመት ጊዜ ማደራጀቱን የገለፁት፤ አቶ ሙላቱ፤ ጽ/ቤቶቹን ብናደራጅም በየዞኖቹና በወረዳዎቹ ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ ተቸግረናል ብለዋል፡፡
በኛ የፓርቲ ስብሰባ ላይ የተገኙ ግለሰቦች በወረዳና አካባቢ አመራሮች ወከባና እስር እየተፈፀመባቸው መሆኑን ያስታወቁት ም/ሊቀመንበሩ፤ በተለይ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጽ/ቤታችንም በሃይል እንዲዘጋ ተደርጐብናል ብለዋል፡፡
አባሎቻችንና አመራሮቻችን ለምን ይታሠራሉ ብለን መንግስትን ስንጠይቅ፤ ህግን የማስከበር እርምጃ ነው የተወሰደው” የሚል ምላሽ ይሰጠናል ያሉት አቶ ሙላቱ፤ ማጣራት ሳይደረግ በስመ ህግን ማስከበር ዜጐችን በጅምላ ማሰር፣ ለሀገር ሠላም ጠቃሚ አይደለም፤ በመንግስት በኩል አስቸኳይ እርምት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡
የቀድሞውን አካሄድ በሚያስታውስ መልኩ ፖለቲከኞች በሰበብ አስባቡ መታሠራቸው በታችኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ባሉ አመራሮች ዘንድ የአስተሳሰብም ሆነ የአሠራር ለውጥ ባለመፈጠሩ የተከሰተ ነው ብለዋል - አቶ ሙላቱ፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢ በመከላከያ ቁጥጥር ስር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙላቱ፤ መከላከያ ወጥቶ በመደበኛ የፀጥታ ሃይል ሠላም መረጋገጥ አለበት ይላሉ፡፡
ከኦፌኮ አባላትና አመራሮች በተጨማሪም “የኦነግ ደጋፊ ናችሁ” በሚል ሰዎች እየታሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የክልሉ ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ፤ በህግ ማስከበር ሂደት ሰዎች እየታሠሩ ያሉት በወንጀል ብቻ ተጠርጥረው ነው ብሏል፡፡   

 ባለፈው ቅዳሜ ተማሪዎቹን ያስመረቀው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ሂውማን ብሪጅ የተባለው አለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በአገሪቱ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች የህክምና ቁሳቁሶችን በመለገስ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት የዋንጫና የምስክር ወረቀት ያበረከተ ሲሆን፣ ለሂውማን ብሪጅ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ለአቶ አዳሙ አንለይ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡
ተቀማጭነቱ በስዊድን የሆነው ሂዩማን ብሪጅ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፣ በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና በሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ ፎርማጆ ተመርቆ ስራ የጀመረውን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ላለፉት ረጅም አመታት ለበርካታ የህክምናና የትምህርት ተቋማት በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚገመቱ የህክምና መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን በመለገስ በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተነግሯል፡፡

Saturday, 13 July 2019 11:06

መልክቶቻችሁ

 በ‹‹ሰሎሜ›› ቶክሾው የታዘብኩት!


           የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ የነበረችውና በጣቢያው ላይ አስደማሚ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣችው ሰሎሜ  ታደሰ፤ በፋና ቴሌቪዥን እያዘጋጀች የምታቀርበውን ‹‹ሰሎሜ›› የተሰኘ ቶክሾው ሁሌም በፍቅርና በጉጉት ነው የምመለከተው:: በፕሮግራሙ የምትዳስሳቸው ርዕሰ ጉዳዮችና የምትጋብዛቸው እንግዶች (ብዙ ጊዜ ወጣቶችና ታዳጊዎችም ይሳተፋሉ) እንዲሁም የፕሮግራሙ አቀራረብ ይማርከኛል፡፡ ለኔ ዘና የሚያደርግም ትምህርት የሚሰጥም ነው የሰሎሜ ቶክሾው፡፡ ስለ አዘጋጇና ፕሮግራሟ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ባለፈው ረቡዕ በቀረበው ሳምንታዊ ፕሮግራሟ ላይ ብቻ አተኩሬ ትዝብቴን እገልጻለሁ፡፡
ፕሮግራሙ ላይ የደረስኩት ከጀመረ በኋላ ቢሆንም የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ በትምህርት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን ተገንዝቤያለሁ:: በትምህርት ፍኖተ ካርታው፣ በትምህርት
ጥራት፣ በማስተማር ዘዴ፣ በኩረጃ ባህል… ወዘተ ስማቸውን ከማላስታውሰው፣ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጋር ሁነኛ ውይይት እያደረገች ነበር፡፡
እንደተለመደው መሃል ላይ እሳት የላሱ የዘመኑ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በማስገባት፣  ከዕድሜያቸው በላይ የበሰለና የጠለቀ አስተያየት አስደምጣናለች - በኩረጃና በትምህርት ዙሪያ፡፡ እስከዚህ ድረስ የታዘብኩት የለም፡፡
በፕሮግራሙ መገባደጃ ላይ፣ ፕሮሰፌሰሩ በሰጡት ምላሽ ላይ ነው ትዝብቴ፡፡ ሰሎሜ የኤሊት (Elife) ት/ቤቶች የሚል ነገር አንስታ ማብራራት ጀመረች፡፡ እነ ዊንጌትን፣ ተፈሪ መኮንን… ወዘተ ለአብነት ጠቀሰች፡፡ ባህር  ማዶም ተሻግራ እነ ሃርቫርድን የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎችን በምሳሌነት አቀረበች:: የኤሊት ት/ቤት ስትል፣ የ‹ሃብታም ወይም ወድ› ት/ቤትን ሳይሆን ምርጦችንና የላቁ ተማሪዎች ማዕከል (Center & excellence) ማለቷ እንደሆነ በቅጡ በማስረዳት… በአሁኑ ዘመን ተማሪዎች የላቀ ብቃትና አቅም ያላቸው ተማሪዎች ለማፍራት፣ ተመሳሳይ የኤሊት ት/ቤት ወይም ተቋሙ ቢኖርስ…? የሚል አስተያየት አቀረበች ጥያቄው ቀላልና ይመስላል፡፡ በተለይ እንደ ፕሮፌሰሩ ላሉ የቀለም ቀንዶች!! ግን ተሳስቼአለሁ፡፡
ፕሮፌሰሩ የሰጡት ምላሽ አስገርሞኛል፡፡ የኤሊት ት/ቤት የሚለውን ነገር…  የተቀበሉት አይመስልም፡፡ ልብ ብሉ! የኤሊት የሚለውን ‹‹የልህቀት ማዕከል›› ስትል ሰሎሜ በግልፅ አብራርታዋለች፡፡ ፕሮፌሰሩ ግን በአሁኑ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የኤሊት ት/ቤት (ተቋም) የሚለው ሀሳብ… የሚተገበር ወይም የሚቻል እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡ ይልቁንም በመንግሥት የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተመሳሳይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ  ከጉዳዩ ለመሸሽ ሞከሩ፡፡
እንግዲህ የትምህርት ፖሊሲን እንዲቀየር ወይም ሥር ነቀል የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ እንዲደረግ… ሀሳብ፡፡ ጎበዝ ተማሪዎች የሚበራከቱበትና የሚበረታቱበት የልህቀት ማዕከል ቢቋቋምስ? ነው የተባለው፡፡
በመጨረሻ ላይም ፕሮፌሰሩ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሌላ ጊዜ በስፋት ተዘጋጅተው እንደሚወያዩ ቃል ገብተዋል።  
ፕሮፌሰሩ፤ ይህን ሀሳብ ለምን ሸሹት? ለምንስ እንደ ከባድ ነገር ለሌላ ጊዜ አስተላለፉት? ለእኔ አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው፡፡
የአገራችንን እንቆቅልሽ ይፈቱልናል ብለን የምንጠብቃቸው ምሁራን ጭራሽኑ ተጨማሪ እንቆቅልሽ እየፈጠሩብን ነው ልበል? ከእንቆቅልሽ ያውጣን!!
ትዕግስቱ ከአብነት      

Saturday, 13 July 2019 11:06

መልክቶቻችሁ

 በ‹‹ሰሎሜ›› ቶክሾው የታዘብኩት!


           የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ የነበረችውና በጣቢያው ላይ አስደማሚ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣችው ሰሎሜ  ታደሰ፤ በፋና ቴሌቪዥን እያዘጋጀች የምታቀርበውን ‹‹ሰሎሜ›› የተሰኘ ቶክሾው ሁሌም በፍቅርና በጉጉት ነው የምመለከተው:: በፕሮግራሙ የምትዳስሳቸው ርዕሰ ጉዳዮችና የምትጋብዛቸው እንግዶች (ብዙ ጊዜ ወጣቶችና ታዳጊዎችም ይሳተፋሉ) እንዲሁም የፕሮግራሙ አቀራረብ ይማርከኛል፡፡ ለኔ ዘና የሚያደርግም ትምህርት የሚሰጥም ነው የሰሎሜ ቶክሾው፡፡ ስለ አዘጋጇና ፕሮግራሟ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ባለፈው ረቡዕ በቀረበው ሳምንታዊ ፕሮግራሟ ላይ ብቻ አተኩሬ ትዝብቴን እገልጻለሁ፡፡
ፕሮግራሙ ላይ የደረስኩት ከጀመረ በኋላ ቢሆንም የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ በትምህርት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን ተገንዝቤያለሁ:: በትምህርት ፍኖተ ካርታው፣ በትምህርት
ጥራት፣ በማስተማር ዘዴ፣ በኩረጃ ባህል… ወዘተ ስማቸውን ከማላስታውሰው፣ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጋር ሁነኛ ውይይት እያደረገች ነበር፡፡
እንደተለመደው መሃል ላይ እሳት የላሱ የዘመኑ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በማስገባት፣  ከዕድሜያቸው በላይ የበሰለና የጠለቀ አስተያየት አስደምጣናለች - በኩረጃና በትምህርት ዙሪያ፡፡ እስከዚህ ድረስ የታዘብኩት የለም፡፡
በፕሮግራሙ መገባደጃ ላይ፣ ፕሮሰፌሰሩ በሰጡት ምላሽ ላይ ነው ትዝብቴ፡፡ ሰሎሜ የኤሊት (Elife) ት/ቤቶች የሚል ነገር አንስታ ማብራራት ጀመረች፡፡ እነ ዊንጌትን፣ ተፈሪ መኮንን… ወዘተ ለአብነት ጠቀሰች፡፡ ባህር  ማዶም ተሻግራ እነ ሃርቫርድን የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎችን በምሳሌነት አቀረበች:: የኤሊት ት/ቤት ስትል፣ የ‹ሃብታም ወይም ወድ› ት/ቤትን ሳይሆን ምርጦችንና የላቁ ተማሪዎች ማዕከል (Center & excellence) ማለቷ እንደሆነ በቅጡ በማስረዳት… በአሁኑ ዘመን ተማሪዎች የላቀ ብቃትና አቅም ያላቸው ተማሪዎች ለማፍራት፣ ተመሳሳይ የኤሊት ት/ቤት ወይም ተቋሙ ቢኖርስ…? የሚል አስተያየት አቀረበች ጥያቄው ቀላልና ይመስላል፡፡ በተለይ እንደ ፕሮፌሰሩ ላሉ የቀለም ቀንዶች!! ግን ተሳስቼአለሁ፡፡
ፕሮፌሰሩ የሰጡት ምላሽ አስገርሞኛል፡፡ የኤሊት ት/ቤት የሚለውን ነገር…  የተቀበሉት አይመስልም፡፡ ልብ ብሉ! የኤሊት የሚለውን ‹‹የልህቀት ማዕከል›› ስትል ሰሎሜ በግልፅ አብራርታዋለች፡፡ ፕሮፌሰሩ ግን በአሁኑ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የኤሊት ት/ቤት (ተቋም) የሚለው ሀሳብ… የሚተገበር ወይም የሚቻል እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡ ይልቁንም በመንግሥት የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተመሳሳይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ  ከጉዳዩ ለመሸሽ ሞከሩ፡፡
እንግዲህ የትምህርት ፖሊሲን እንዲቀየር ወይም ሥር ነቀል የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ እንዲደረግ… ሀሳብ፡፡ ጎበዝ ተማሪዎች የሚበራከቱበትና የሚበረታቱበት የልህቀት ማዕከል ቢቋቋምስ? ነው የተባለው፡፡
በመጨረሻ ላይም ፕሮፌሰሩ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሌላ ጊዜ በስፋት ተዘጋጅተው እንደሚወያዩ ቃል ገብተዋል።  
ፕሮፌሰሩ፤ ይህን ሀሳብ ለምን ሸሹት? ለምንስ እንደ ከባድ ነገር ለሌላ ጊዜ አስተላለፉት? ለእኔ አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው፡፡
የአገራችንን እንቆቅልሽ ይፈቱልናል ብለን የምንጠብቃቸው ምሁራን ጭራሽኑ ተጨማሪ እንቆቅልሽ እየፈጠሩብን ነው ልበል? ከእንቆቅልሽ ያውጣን!!
ትዕግስቱ ከአብነት      

 ከአሜሪካ የተሰረቀውን ሚስጥራዊ ወታደራዊ መረጃ በድብቅ ለቻይና አሳልፎ ሰጥቷል የተባለው ቻይናዊ ፕሮፌሰር፤ በ200 አመታት እስር መቀጣቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የኤሌክትሮኒክ የጦር መሳሪያዎችና የተዋጊ ጄቶች አፕሊኬሽኖችን እንደያዘ የተነገረለትን የኮምፒውተር ቺፕስ በድብቅ ወደ ቻይና ለመላክ በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፏል በሚል ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ፕሮፌሰር ይሺ ሺሽ የራዳር፤ በቀረቡበት 18 ክሶች ሁሉ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ200 አመታት እስር እንደተፈረደበት ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሎስ አንጀለስ ውስጥ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ የኤሌክትሪካል ምህንድስና መምህር የሆነው የ64 አመቱ ፕሮፌሰር ይሺ ሺሽ፤ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ይህንን እጅግ ፈጣንና ልዩ የኮምፒውተር ቺፕስ ቻይና ውስጥ ለሚገኝ አንድ ኩባንያ አሳልፎ በመስጠቱ ቅጣቱ እንደተጣለበት ተነግሯል፡፡
አገራዊ መረጃን አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ የውጭ አገራት ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው የአሜሪካን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አዳዲስ ወታደራዊ አፕሊኬሽኖችን የሚሰሩበትን ዕድል የሚከፍት አደገኛ ድርጊት ፈጽሟል የተባለው ፕሮፌሰሩ፤ ከዚህ በተጨማሪም የቻይና ኩባንያዎች የአሜሪካ ኩባንያዎችን ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመው ያልተገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያደርግ ወንጀል ሰርቷል በሚል የእስር ፍርዱ እንደተወሰነባቸው ተገልጧል፡፡

 የአለማችን አገራት ፕላስቲክና የምግብ ትራፊዎችን ጨምሮ በየአመቱ በድምሩ ከ2 ቢሊዮን ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ እንደሚፈጥሩ በ194 አገራት ላይ የተሰራና ባለፈው ረቡዕ ይፋ የሆነ የጥናት ሪፖርት መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአለማችን በየአመቱ ከሚመነጨው 2 ቢሊዮን ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ ለመልሶ መጠቀም የሚውለው 16 በመቶው ብቻ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ቀሪው 950 ሚሊዮን ያህል ቆሻሻ ግን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደሚወገድ ጥናቱን በመጥቀስ አመልክቷል፡፡
ከህዝብ ብዛታቸው አንጻር ከፍተኛ መጠን ያለው ደረቅ ቆሻሻ ከሚያመነጩ ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት መካከል አሜሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ህንድና ቻይና በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ሶስቱ አገራት በድምሩ ከአለማችንን አጠቃላይ ቆሻሻ 39 በመቶ ያህሉን እንደሚያመነጩም ገልጧል፡፡
ከምታመነጨው ቆሻሻ ውስጥ 68 በመቶውን መልሳ የምትጠቀመው ጀርመን፤ ቆሻሻዎችን መልሶ በመጠቀም ረገድ ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት ተቀምጣለች ያለው ዘገባው፣ በአብዛኞቹ አገራት ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም አዝማሚያ እየቀነሰ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
ጥናቱ የተሰራባቸው አገራት በየአመቱ የሚያመነጩት አጠቃላይ ቆሻሻ 820 ሺህ የኦሎምፒክ የመዋኛ ገንዳዎችን የመሙላት አቅም እንዳለው የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ቻይናንና ታይላንድን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ከውጭ አገራት እየገዙ መልሰው ይጠቀሙት የነበረውን ቆሻሻ መግዛት ማቆማቸው ቆሻሻ በከፍተኛ መጠን እንዲጠራቀም ሰበብ መፍጠሩንም አመልክቷል፡፡
በአለማችን የተለያዩ ውቅያኖሶች ውስጥ 100 ሚሊዮን ቶን የሚገመት ቆሻሻ እንደሚገኝ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህም የውሃ አካላትን ህልውና በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳውና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ገቢን በእጅጉ እንደሚቀንሰው ገልጧል፡፡

Saturday, 06 July 2019 14:42

የወቅቱ ጥቅስ

“ሕዝቦችን ሁሉ የሚፈጥር አንድ አምላክ ነው:: ይህም አምላክ የምንለው የሕዝቦች ፈጣሪ፤ ሕዝቦቹን ሁሉ ትክክል አድርጎ ፈጥሮ ላኗኗራቸውና ለልማታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ከሙሉ ፈቃድና ሥልጣን ጋራ በጃቸው ሰጥቷቸዋል:: ስለዚህ ማናቸውም ሕዝብ ቢለማም ቢጠፋም በገዛ እጁ ነው፡፡
ሕዝብ የሚጠፋበት አንዳንድ ጊዜ ምክንያት ቢገኝ፤ ያውም ምክንያት ባንዳንድ ሰው ቢመካኝ፤ ነገሩ ትክክል አይሆንም፡፡ የልማትን መንገድ ለማግኘት የሚጥር ሕዝብ ቢገኝ፤ ባንዳንድ ክፉ ሰው ምክንያት ሊጠፋ አይችልም፡፡  እንዲሁም ደግሞ የልማትን መንገድ ለማግኘት የማይጣጣር ሕዝብ ባንዳንድ ደኅና ሰው ኃይል ልማት ሊያገኝ አይችልም:: ደግሞም ማናቸውም ሕዝብ የሚለማበት መንገድ አንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ማናቸውም ሕዝብ የሚጠፋ ይህንን የልማት መንገድ ትቶ በሌላ መንገድ የሄደ እንደሆነ ነው፡፡ “
ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ

Saturday, 06 July 2019 14:41

የፖለቲካ ጥግ

(ስለ ሪፎርም)


 ኢኮኖሚ የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ ጠንካራ ኢኮኖሚ ከሌለህ፣ ስኬታማ የትምህርት ማሻሻያም ይሁን ሌላ ማሻሻያ ሊኖርህ አይችልም፡፡
ዴቪድ ካሜሩን
ሪፎርም፤ የቻይና ሁለተኛ አብዮት ነው፡፡
ዴንግ ዚያኦፒንግ
አዕምሮህን ክፍት ሳታደርግ ህብረተሰብን ወይም ተቋማትን ማሻሻል (መለወጥ) አትችልም፡፡
በሻር አል - አሳድ
ሃይማኖት ፈጽሞ የሰው ልጅን ሊያሻሽል አይችልም፤ ምክንያቱም ሃይማኖት ባርነት ነው፡፡
ሮበርት ግሪን ኢንገርሶል
የአሜሪካ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ትላልቅ ሃሳቦች፣ ትላልቅ ሪፎርም ይሻል፡፡
ራህም ኢማኑኤል
በፖለቲካ፤ ሪፎርም ፈጽሞ ከቀውስ በፊት አይመጣም፡፡
ቱከር ካርልሰን
ካልተለወጥን አናድግም፡፡ ካላደግን የእውነት እየኖርን አይደለም፡፡
ጌይል ሺሂ
ጠላቶችን ለመፍጠር ከፈለግህ፣ የሆነ ነገር ለመለወጥ ሞክር፡፡
ውድሮው ዊልሰን
በዓለም ላይ ምርጡ የህብረተሰብ ሪፎርም ፕሮግራም ሥራ ነው፡፡
ሮናልድ ሬገን
ሪፎርም ማለት የማያስፈልገውን ማስወገድ፣ የሚያስፈልገውን መጠበቅ ነው፡፡
ፔሪያር ኢ.ቪ ራማሳሚ
ሪፎርም ለማድረግ  አትፍራ፡፡
ኮንፊሽየስ

  የ18 አመቱ ኢትዮጵያዊ እስራኤላዊ ሰለሞን ተካ ባፈለው እሁድ ሃይፋ ከተባለችው ከተማ አቅራቢያ በአንድ እስራኤላዊ ፖሊስ በጥይት ተደብድቦ መገደሉን ተከትሎ፣ ድርጊቱ ያስቆጣቸው ቤተ-እስራኤላውያንና ደጋፊዎቻቸው ሰኞ ዕለት አደባባይ በመውጣት የጀመሩት ተቃውሞ ላለፉት ቀናትም ተባብሶ መቀጠሉ ተዘግቧል፡፡
በስራ ገበታው ላይ ባልነበረ ፖሊስ የተፈጸመውን ግድያ ተቃውመው በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ሰልፍ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ-እስራኤላውያንና ደጋፊዎቻቸው በፖሊሶች ላይ ድንጋይ በመወርወርና በጎዳናዎች ላይ እሳት በማቀጣጠል ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ፖሊስ በበኩሉ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጢስና ተኩስ መጠቀሙንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞችን መጉዳቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወጣቱን ገድሏል የተባለው ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንደዋለ የዘገበው የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ፣ ግድያው ከዘር ጥላቻ የመነጨ ነው የሚል አቋም የያዘው ተቃውሞ ግን ባለፉት ቀናት ቴል አቪቭን ጨምሮ ወደተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች መስፋፋቱንና በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የመኪና መንገዶችን በመዝጋትና መኪኖችን በማቃጠል ግድያውን ማውገዝ መቀጠላቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የእስራኤል ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን ባደረገው ጥረት በተፈጠረው ግጭት 111 ያህል ፖሊሶች መቁሰላቸውንና 136 ያህል ሰልፈኞች መታሰራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ተቃውሞው መባባሱን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በወጣቱ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽና ግድያውን በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ ሰልፈኞች ግን ህገወጥ ድርጊት ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የ18 አመቱ ኢትዮ-እስራኤላዊ የሰለሞን ተካ የቀብር ስነስርአት ባለፈው ማክሰኞ መፈጸሙን የዘገበው አልጀዚራ፣ ተቃዋሚዎቹ ወጣቱን የገደለው ፖሊስ በአፋጣኝ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ መጠየቃቸውንና ቤተ-እስራኤላውያን ከዘር ጥቃትና ግድያ ነጻ የሚሆኑባትና ያለስጋት የሚኖሩባትን እስራኤል ለመፍጠር የሚያደርጉትን ትግል በዘላቂነት እንደሚገፉበትም ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል ፖሊሶች በቤተ-እስራኤላውያን ወጣቶች ላይ ድብደባና ግድያ ሲፈጽሙ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ከአራት ወራት በፊትም አንድ ኢትዮ-እስራኤላዊ ወጣት በፖሊስ ጥይት ተመትቶ ለሞት መዳረጉን አስታውሷል፡፡


በአዳዲስ የቢዝነስና የስራ ፈጠራ ሃሳቦች አፍላቂነታቸውና በፈር-ቀዳጅ ኢንቨስተርነታቸው በሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስትና ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ስራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የተሰኘው የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
አጠቃላይ ዝግጅቱ ከስድስት አመታት በላይ ፈጅቶ የተጠናቀቀው መጽሐፉ፤ ከወላጆቻቸው የኋላ ታሪክ አንስቶ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወትና አስተዳደግ፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከጥበቃ ሥራ እስከ የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እንዲሁም እስከ ግዙፉ የአለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመጥር ባለሙያነት የዘለቁበትን የረጅም አመታት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከ20 አመታት በላይ የተጓዙበትን በስኬትና በውድቀት የታጀበ፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው ረጅም የሕይወት ጎዳናም በዝርዝር ይዳስሳል፡፡   
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የወጠኗቸውን አዳዲስና ሰፋፊ የፋይናንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ ያጋጠሟቸውን እሾህ አሜካላዎች፣ የተጋፈጧቸውን ፈተናና እንቅፋቶች በዝርዝር የተረኩበት መጽሐፉ፤ ከባለታሪኩ የግልና የስራ ሕይወት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አጓጊና አነጋጋሪ መረጃዎችን አካትቷል፡፡
በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፤ “ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ394 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡ “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ የመጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች፣ በአዲስ አበባ በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎችና በሸዋ ሱፐር ማርኬቶች፣ በስልክ ትዕዛዝ የቤት ለቤት ዕደላና በአማዞን ድረ-ገጽ አማካይነት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም 300 ብር እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የታሸገ ውሃ “ሃይላንድ” ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም “ዘመን ባንክ” እና “አክሰስ ሪል እስቴት”ን ጨምሮ ባቋቋሟቸው የተለያዩ ኩባንያዎች የሚታወቁት አነጋጋሪው የኢኮኖሚ ባለሙያ  አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በአሁኑ ወቅትም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በእስር ላይ በቆዩባቸው ወራትም፣ በተለይ ሥር በሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮች የሚተነትንና ዝርዝር የፖሊሲ ማሻሻያዎችን የሚያቀርብ Ethiopia:Tipping Point የተሰኘ መጽሐፍ አዘጋጅተው በAmazon.com አማካኝነት በኦንላይን እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በምዕራፍ ሦስት ላይ Ethiopian Economy at Cross Road  በሚል ርዕስ የቀረበውን ጥናታዊ የኢኮኖሚ ትንተና፣ ከ10 ወራት በፊት፣ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት፣ መላካቸውን አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በመጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡   
“የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የተሰኘውን የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ያዘጋጀው ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፤ ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፣ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል፡፡

Page 2 of 435