Administrator

Administrator

የናይጄሪያ ዓላማ ስማርት ስልኮችን በብዛት መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ እዚያው በሀገሯ መገጣጠምና ማምረት መጀመር ነው። በኢሞ ግዛት የሚገኘውና በ15 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው "ዲጂታል ሲቲ" በቀን እስከ 1,000 የሚደርሱ ስማርትፎኖችንና ራውተሮችን የመገጣጠም አቅም ባለው ፋብሪካው ይህንን ራዕይ እውን በማድረግ ላይ ይገኛል።
ፋብሪካው ከማምረት ባለፈ ወጣት ናይጄሪያውያንን በኤአይ፣ በሮቦቲክስ፣ በሳይበር ደህንነት እና በሌሎች የዲጂታል ክህሎቶች በማሰልጠን ላይ ያተኩራል።
ለዓመታት ናይጄሪያ ከውጭ በሚገቡ ስማርት ስልኮች ላይ ጥገኛ በመሆኗ፣ በምንዛሬ ተመን፣ በኢምፖርት ቀረጥና በሎጂስቲክስ ወጪዎች ምክንያት የስልኮች ዋጋ ውድ ሆኖ ቆይቷል። አካባቢያዊ የመገጣጠም ስራዎችን ማስፋፋት የስልኮች ዋጋ ለመቀነስ፣ የክህሎት ስራዎችን ለመፍጠርና የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማጠናከር ይረዳል። በተጨማሪም ይህ እንቅስቃሴ የናይጄሪያ የቴክኖሎጂ ማዕከል ከሌጎስ ከተማ ወጥቶ ወደ ሌሎች ግዛቶች እየተስፋፋ መሆኑን ያሳያል።
እንደ ኢሞ ዲጂታል ሲቲ ባሉ ፕሮጀክቶች፣ የተለያዩ የናይጄሪያ ግዛቶች ራሳቸውን የፈጠራ፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የታላንት ልማት ማዕከል አድርገው ማዘጋጀት ጀምረዋል። አሁን ያለው ዋናው ፈተና ግን ይህንን ስራ ማስፋፋት እና ማሳደግ ነው።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
"አፍሪካ በዓለም ላይ ሀብታሟ አህጉር ሆና ሳለ፣ እንዴት ወርቃችን በነጮች ይቆፈራል?
እንዴትስ አፍሪካ የአልማዝ መገኛ ሆና—ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ናሚቢያ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ አልማዝ እየወጣ—ዋጋውን ግን በቤልጂየም የሚገኙ ሰዎች ይወስኑታል?
ቶጎ፣ ኮትዲቯር እና ጋና ኮኮዋ ያመርታሉ፤ ነገር ግን ቸኮሌት የሚሰሩት አንድም የኮኮዋ ዛፍ የሌላቸው ስዊዘርላንድና ቤልጂየም ናቸው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
ሻይ ቅጠል በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በኡጋንዳ ተመርቶ ወደ እንግሊዝ ሲሄድ "የእንግሊዝ ሻይ" ይባላል። ይህ እንዴት ይሆናል?
ለስልክ መስሪያ የሚያገለግለው ኮልታን የተባለው ማዕድን ከኮንጎ እየወጣ፣ አንድም የአፍሪካ ሀገር ግን ሞባይል ስልክ አያመርትም።
ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው አእምሮአችን እንዲማረክ በመፍቀዳችንና ማንነታችንን በመዘንጋታችን ብቻ ነው።"
(PLO Lumumba)
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኙ የነበሩ ከ1 ሺህ 400 በላይ ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ ውስጥ በተደረጉ 6 ዙር በረራዎች ወደ ሀገራቸው በሰላም ተመልሰዋል። እንደ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ከተመላሾቹ መካከል 879 ወንዶች፣ 554 ሴቶች፣ 48 ጨቅላ ሕፃናት እና 82 ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል። መስከረም 5/2018 ዓ.ም በተጀመረው በዚህ ዜጎችን የማመለስ አገራዊ ዘመቻ እስካሁን ከ87 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ እናት ሀገራቸው መመለስ ተችሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት አስፈላጊውን እንክብካቤና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ተመላሾችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል፣ የመልሶ ማቋቋም እና በስነ-ልቦና የታገዘ ድጋፍ የማድረግ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሆነ ተገልጻል።

ወደፊትም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚያስከትለውን አስከፊ አደጋ ለኅብረተሰቡ የማስገንዘብ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። መንግሥት ሕገ-ወጥ ጉዞዎችን ለመከላከልና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሕጋዊ ፍልሰትን ለማበረታታት የጀመራቸውን አሰራሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስቴሩ አረጋግጧል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን እና የእንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ ክለብ ተጫዋች ዓሊ አህመድ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብቷል። ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ዲፓርትመንት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።

የተጫዋቹ ወደ ሀገር ቤት መምጣት በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ የተደረገ ሲሆን፣ ዓላማውም በሀገሪቱ የስፖርት ልማት ላይ አዎንታዊ አሻራ ለማሳረፍና ወጣቶችን ለማበረታታት ነው። የውጭ ጉዳይ፣ የባህልና ስፖርት፣ የቱሪዝም ሚኒስቴሮች እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ የሚያደርገው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን እየሰሩ ይገኛሉ።

ዓሊ አህመድ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን 28 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፣ በ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫም በአራት ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ታሪካዊ ጉዞ አድርጓል። በሜጀር ሊግ ሶከር ባሳየው የላቀ ብቃት በጥር 2026 ወደ እንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ ያመራው ዓሊ፣ የደረሰበት የስኬት ደረጃ ለበርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትልቅ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው።

አንድ ንጉሥ አንድ ብልህ አጫዋች ነበራቸው። በየጊዜው ከሚመክራቸው ምክር መካከል ሰሞኑን የነገራቸውን ለመቀበል ከብዷቸዋል። ሰሞኑን የመከራቸው “ከወዳጆችዎ ይልቅ፣ ስለርስዎ ድክመት ዕውነቱን የሚነግሩዎ ጠላቶችዎ ናቸውና አዳምጧቸው” የሚል ነበር። ንጉሡ አላመኑበትም። ስለዚህ ለማረጋገጥ መዘዋወር ጀመሩ።
ንጉሡ በጣም የሚፈሩና አይበገሬ ነኝ የሚሉ ናቸው። በሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚያገኟቸውን መኳንንቶች “እስቲ ስለ እኔ ጉድለት ንገሩኝ?” ይሉና ይጠይቃሉ።
“ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ላይ እንዴት አይነት ሰው ነው ጉድለት ሊያገኝ የሚችለው። ደግሞ እርስዎ ምን ይወጣልዎታል!” ይሏቸዋል።
ቀጥለው ወደ ሠራዊታቸው ይሄዱና፤
“ምን እንከን አለብኝ? እስቲ ስለራሴ ንገሩኝ?” ይላሉ።
ከሠራዊታቸው ታማኙ ባለሟል ብድግ ብሎ፣
“ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ከቁመናዎ ጀምሮ፣ ለጀግንነትዎ፣ ለዕውቀትዎ፣ ለዓለም ተደማጭነትዎ ምን የሚቀነስ የሚወጣልዎ ነገር አለብዎ!” ይላቸዋል። እንዲህ ከርመው አንድ ቀን በአጋጣሚ ከጠላቶቻቸው ጋር በሚሲዮን ይቀመጣሉ። አጠገባቸው የተቀመጠው ቀንደኛው ባላንጣቸው ቀስ ብሎ፤
“ስሙ ንጉሥ፤ ሲናገሩ አፍዎት መጥፎ ጠረን ያመጣል” ይላቸዋል።
ንጉሱ ይናደዳሉ። “እንዴት እስከዛሬ አንድ ወዳጄ ይሄን አልነገረኝም? እንዲህ በአደባባይ እንድጋለጥ ያደረጉኝ ወዳጆቼ ናቸው! ቆይ ግድ የለም! ባልሰራላቸው!” ይላሉ በሆዳቸው። ስብሰባውን እንደጨረሱ ሲገሰግሱ ወደ ቤተ-መንግስታቸው ይሄዱና ንግስቲቱን አስጠርተው፤
“አፌ ጠረን እንዳለው እስከዛሬ ያልነገርሽኝ ለምንድን ነው?” ሲሉ በቁጣ ጠየቁ። ንግስቲቱም፤ በንፁህ ልቦናና በቀናነት፤
“ንጉሥ ሆይ! የሁሉም ንጉስ አፍ እንደ እርስዎ አፍ አይነት ሽታ ያለው መስሎኝ ነው” ሲሉ መለሱ።
ንጉሡም እጅግ የቅርባቸው የሆነችው የገዛ ባለቤታቸው ጉድለታቸውን ሳትነግራቸው፤ ሩቅ የሚኖሩት ጠላቶቻቸው ማወቃቸውን ልብ ሲሉ፤ ያ አስተዋይ አጫዋቻቸው የነገራቸው ቁም ነገር እውነት መሆኑን ተገነዘቡ።
***
ማንኛውም መሪ፣ በማንኛውም ደረጃ ያለ ቢሆን፤ አንድ ሀቅ ልብ ማለት አለበት። ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ መሪ፤ ከወዳጆቹ የሚጠብቀው ምንጊዜም ምስጋናን ስለሆነ ጉድለቶቹን የማየትም የመስማትም እድል አያገኝም። ወገኖቹም አይደፍሩትም። እሱም ራሱን አይደፍርም። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሁሌ በሰላም ጊዜ በሆነ ባልከፋ። ሁኔታዎች በውጥረትና በችግር በሚሞሉበት ሰዓት ሲመጣ ነው አደጋው። ምክንያቱም የሁኔታዎች መወሳሰብን ተከትለው ሰዎችም ይለወጣሉና ነው። ችግሩ ግን በዚህ ብቻ አያቆምም። መሪውን መስለውና አክለው ማደግ ሲመኙ የቆዩ ባለሟሎቹና ተከታዮቹ አለማዳመጥ ሰናይ ስነምግባር እየመሰላቸው እነሱም እኩዮቻቸው የሚሉትን አልሰማ ይላሉ። በዚህ ምክንያት ካለመደማመጥ አልፎ፣ የሚፈጠረውን ጩኸት ለመገደብ ካለመቻል ደረጃ ይደረሳል። በየመንበራቸው እንደተቀመጡ በየራሳቸው ደሴት ውስጥ ይዋጣሉ። ውለው አድረውም የታችኞቹ በላይኞቹ ላይ ቅያሜን ያጠነክራሉ። ቀስ በቀስ በተለይ የመረረ የመከፋት ስሜት ውስጥ በገቡ ጊዜ፤ እንደ ሮማው ካሽየስ፣ ባለቃው ላይ ማሴርን፣ ራስን እንደማዳን ሲቆጥሩ፤ ከላይ ወደ ታች ይወርዱ የነበሩ ትእዛዛት ወደ ጎንም፣ ወደ ይም እንዲያመሩ ሲፈለግ፣ ለወትሮው የአለቃውን ድክመት ሁሉ የእኔ ነው እያለ አሜን ይል የነበረው ሁሉ፣ ድርሻ ድርሻችንን እንውሰድ በሚል፤ ሌላውን ማነሳሳትና ብሶቱን ሌላው ላይ ማጋበቱን ይያያዘዋል። ይሄኔ እንደ ሮማው ብሩተስ ያለው በትዕግስት የሚያገኘውን ስልጣን ቄሳርን በማስወገድ ሊፈጽመው እንዲሻ ሲተነኮስ፣ ወይም ሲወነባበድ፣ ነገር የተገላቢጦሽ ይሆናል። ቄሳር በመሞቻው “አንተም ብሩተስ?” ያለበት ሰዓት የሚመጣ እንግዲህ ያኔ ነው።በተለይ ስልጣንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመጋራት ልምድ በሌለበት እንደ እኛ ባለው አገር ብርቱ ጥንቃቄ የሚጠይቀው፣ በወንበሩ ዙሪያ አስፈላጊ ትዕግስትና መቻቻል አለመኖር ነው። መተማመን እንዲኖር ሀሳብን መግለጽ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ነጻነቱ አስፈላጊ ነው። ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት በሀቅና ከልብ ካልታመነበት፤ “ለብ ለብ ዲሞክራሲ” “ገባ ያለው ዲሞክራሲ” እና “ስፔሻል ዲሞክራሲ” እያልን እንድንከፋፍል ልንገደድ ነው። “አካሄዱ ፍጻሜውን ያሳያል” እንዳንል፤ አባይን ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲህ አላምነውም፤ የሚሉ ወገኖች ይሟገቱናል። የለም “ግቡ አካሄድን ያሳያል” - የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው ነው ነገሩ- ለሚሉት ደግሞ ካልታዘልኩ አላምንም፣ ስንቱ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ አይደል ወይ መላው የጠፋው የሚሉ ይኖራሉ። ሁኔታዎችን አጣጥመን መጓዝ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው። የሚያግባባንን መንገድ ከንፍቀ-ክበባችን ውጭም ቢሆን ማዳመጥ፣ ከባላንጣዎቻችንም ቢሆን መማር፣ ሁሌ ከመተላለፍ አንዳንዴ “ምን ይሆን?” ብሎ ለሌሎች ሀሳብ ትንሽ እድሜ መለገስ፤ ቀስ በቀስ ግትርነታችንን ሊያረግበው ይችላል።
አለንልህ ያልነውንና በእርሱም ትከሻ ለስልጣን የበቃንለትን፣ ከቀን በኋላ ከእርሱ እጅ የማንወጣውን ህዝብ ማዳመጥ እንደሚኖርብን እንድናስብም ፋታ ይኖረናል።
ስለሌላው ውሸት እንጂ እውነት በተናገርን ቁጥር፣ ስለሌላው ድክመት እንጂ አንድ አንኳር ጥንካሬ እንኳን ባነሳን ቁጥር፣ እኛ ብቻ ሀቀኛ፣ እኛ ብቻ ጠንካራ እያልን እንገበዛለን። ይህ ደግሞ ስለራሳችን እውነተኛ ገጽታ እናዳናውቅ ያደርገናል። የእኛኑ ቅኝት የሚያዳምጡ ወገኖቻችንና ደጋፊዎቻችን እውነተኛ ይዘትና ቅርጻችንን አይነግሩንም።
ስለዚህ ከእኛ ውጭ የማዳመጥ ባህል ማዳበር ደግ ነገር ነው- ከ”ጥላትም” ሰፈር ቢሆን። አበው “ክፋትህና ውሸትህ ሲጠፋብህ፤ ጠላትህን አስታውሰኝ በለው” የሚሉት ይሄንኑ ሊያስገነዝቡን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የቀድሞ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ከማንኛውም የፓርቲ ፖለቲካ እራሳቸውን በይፋ ማግለላቸውን አስታውቀዋል። ፕሮፌሰሩ ውሳኔያቸውን በይፋ በላኩት ልዩ ደብዳቤ የገለጹ ሲሆን፥ ይህ ከፖለቲካ የመውጣት ውሳኔያቸውም ከሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የጸና እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት በሀገሪቱ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ በንቃት ሲሳተፉ የቆዩት ፕሮፌሰር ዝናቡ፥ ይህንን ውሳኔ ለማሳለፍ የተገደዱት በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ትግሉ «ውጤት አልባ» ሆኖ ስላገኙት መሆኑን ገልጸዋል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

በአሜሪካው ኒው ጀርሲ ግዛት በሚገኘው የሜትላይፍ ስታዲየም እሁድ ዕለት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔንና አርጀንቲና የመጨረሻ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። ሊዮኔል ሜሲ የሚመራት አርጀንቲና ዋንጫውን በተከታታይ በማንሳት ታሪክ ለመድገም ስትጫወት፣ ስፔን ደግሞ ሁለተኛ የዓለም ዋንጫዋን ለማሸነፍ ትፋለማለች።

በጨዋታው ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሜክሲኮዋ ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሼይንባም ከ80 ሺህ በላይ ተመልካቾች ጋር በመሆን ይታደማሉ። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንን በሶስት ሀገራት (አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ) የተስተናገደውን ውድድር “በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ ስኬታማው የስፖርት ኩነት” ሲሉ አሞካሽተውታል።

የስፔኑ ካፒቴን ሮድሪ ከኦፊሴላዊ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገረው፣ ከአርጀንቲና ጋር የሚኖረው ፍልሚያ ከፍተኛ የአካል ብቃት እና ጉልበት የሚጠይቅ “ፊዚካል” ጨዋታ እንደሚሆን ይጠብቃል። ቡድናቸው ግን ለማንኛውም ዓይነት የጨዋታ ስልት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

በሌላ በኩል የአርጀንቲናው አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ፣ ደጋፊዎች የ39 ዓመቱን የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲን በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ማየት መታደል በመሆኑ በዚህ ታሪካዊ ቅጽበት እንዲደሰቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት እንግሊዝና ፈረንሳይ ለሶስተኛ ደረጃ ቅዳሜ ዕለት በማያሚ ይጫወታሉ። የእንግሊዙ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል በአርጀንቲና መሸነፋቸው ከፍተኛ ቁጭትና ህመም እንደፈጠረባቸው ሲናገሩ፣ የፈረንሳዩ አሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሻም ደግሞ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ ይህ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን የሚያሰናብቱበት የመጨረሻ የዓለም ዋንጫ ጨዋታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የአመራር ብቃት እና አስተዳደር ለመቀየር የተዘጋጀውና በሐምሌ 2018 ዓ.ም የወጣው አዲሱ መመሪያ ቁጥር 1146/2026፣ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች በግልጽ ውድድርና በብቃት መመዘኛ ብቻ እንዲሾሙ ወስኗል።

ይህ አዲስ አሰራር ከዚህ ቀደም በአካዳሚክ ዘርፍ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የአመራር ዕጩነት በማስቀረት፣ ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ባሉ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች (ኢንዱስትሪዎች) ውስጥ ከፍተኛ የአመራር፣ የሰው ኃይልና የበጀት ማስተዳደር ልምድ ያላቸው ስራ አስፈጻሚዎች በውድድሩ እንዲሳተፉ መንገድ ከፍቷል።

ዕጩዎች ለአካዳሚክ ዝግጅት 30 በመቶ፣ ለአመራር ልምድ 30 በመቶ፣ እንዲሁም ለሚያቀርቡት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ 40 በመቶ የሚይዝ አጠቃላይ መመዘኛ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ቢያንስ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ (ለሴት ዕጩዎች በቂ ተወዳዳሪ ከሌለ የማስተርስ ዲግሪ) ሊኖራቸው ይገባል።

ይህ ማሻሻያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ጥራትን እንዲያሻሽሉ፣ የፋይናንስ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያሳድጉ የታለመ ሲሆን፣ ክፍት የስራ መደቦቹ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ተደራሽ ሆነው ለ22 የስራ ቀናት ክፍት ሆነው ይቆያሉ። ምልመላውን ለማከናወን ባለ 4 አባላት ያሉት የአሰሳ (Headhunting) ኮሚቴ እና ባለ 7 አባላት ያሉት የመራጭ ኮሚቴ የሚዋቀሩ ሲሆን፣ ኮሚቴው ምርጥ 5 እጩዎችን ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ፣ ቦርዱ ደግሞ 3 የመጨረሻ እጩዎችን መርጦ ለትምህርት ሚኒስቴር በማቅረብ የመጨረሻው ሹመት ይጸድቃል። ተሿሚ ፕሬዝዳንቶች ለ6 ዓመታት የሚያገለግሉ ሲሆን፣ በየስድስት ወሩ ጥብቅ የአፈጻጸም ግምገማ ይደረግባቸዋል፤ በሁለት ተከታታይ ግምገማዎች ከ60 በመቶ በታች ያመጡ ወይም የዲሲፕሊን ግድፈት የፈጸሙ መሪዎችም ወዲያውኑ ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ መመሪያው በግልጽ ያስቀምጣል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

በኡጋንዳ ካፕቾራዋ አካባቢ በሚገኝ "ሴክዋቲት" በተባለ አደገኛ ኮረብታ ላይ፣ ከትምህርታዊ ጉዞ ይመለሱ የነበሩ የኪንግ ዴቪድ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን የጫነ አውቶብስ ከአሽከርካሪው ቁጥጥር ውጪ ሆኖ በመገልበጡ የ20 ተማሪዎችና የአንድ አዋቂ (የትምህርት ቤቱ መስራች እና ዳይሬክተር) ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አልፏል።

የመጀመርያ ደረጃ የምርመራ ውጤቶች እንደሚያሳዩት አደጋው ከመከሰቱ በፊት በአውቶብሱ ላይ የሜካኒካል ችግር አጋጥሞ የነበረ ሲሆን፣ አሽከርካሪው መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት ከመንገድ በመውጣት ከቋጥኝ ጋር መጋጨቱን የትራፊክ ፖሊስ አስታውቋል። በአገሪቱ ታሪክ እጅግ አስከፊ ከተባሉት የአደጋ መዝገቦች አንዱ በሆነው በዚህ ክስተት በርካታ የትምህርት ቤቱ ሰራተኞችና ተማሪዎችም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ይህን ተከትሎ የኡጋንዳ ትምህርት ሚኒስትር ጆን ችሪሶስቶም ሙዪንጎ ለአደጋው መንስኤ የሚደረገው ምርመራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እስኪያልቅ ድረስ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚደረጉ የትምህርት ጉዞዎች መታገዳቸውን አውጀዋል። ሚኒስትሩ "ለልጆቻችን ደኅንነት ሲባል ይህንን የአፋጣኝ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ነበረብን" በማለት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው፣ የተረፉት ሕጻናት ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

bbc-

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

ኢትዮጵያ የምታምረው በተራሮቿና በወንዞቿ ብቻ አይደለም፤ በፍቅር አብረው በሚኖሩ ዜጎቿና ሰላምን በሚተነፍሱ ቀዬዎቿ ነው።

የገጠሩ ኢትዮጵያ ትልቁ ምኞት ቀላል ነው። ከበሬው እስከ ገበሬው በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚመለስበት፣ እርሻው በተስፋ የሚለማበት፣ የሕፃናት ሳቅ በቀዬው የሚያስተጋባበት አማን ሕይወት ማየት ነው።

ቀዬው ሰላም ሲሆን ምድሩ መልካም እሸት ያፈራል፤ ልቦች ይበልጥ ይቀራረባሉ፤ ሕይወትም ይለመልማል!

የኔ ኢትዮጵያ! ???????? ክፉው ሁሉ አይንካሽ፤ በጎውም አይለፍሽ! በእያንዳንዱ ቀዬሽ ሰላም ይስፈን፤ በእያንዳንዱ ቤት ተስፋ ይብቀል፤ በእያንዳንዱ በልጆችሽ ልብ አንድነት ይኑር። ያኔ እውነተኛ ውበትሽ በምልዐት ይገለጣል። የሰላም ብርሃንሽም ከቀዬ ወደ አደባባይ፤ ከገጠር ወደ ከተማው ከአንዱ ልብ ወደ ሌላው ይጋባል። በጽኑ አምናለሁ አይቀርም!

የሰላም ቀን ይሁንልን!

ሶዶ ለማ-

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Page 7 of 818