Administrator

Administrator

Saturday, 19 July 2014 11:45

የፖለቲካ ጥግ

የሥራ ማቆም አድማን አልታገስም፡፡ እኔ የሥራ ማቆም አድማ ባደርግና ደሞዝ አልፈርምም ብል ሰራተኞቼ ምን ይሉኛል?
አላን ቦንድ
(አውስትራሊያዊ የቢዝነስ ሥራ አስፈፃሚ)
ህገ-መንግስታዊው መንግስት ጥቃት እየተሰነዘረበት ነው - አጠቃላይ አድማው ለፓርላማው ፈተና ነው፡፡ የሥርዓት አልበኝነትና የጥፋትም ጎዳና ነው፡፡
ስታንሌይ ባልድዊን
(የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር)
ሁላችንም ካልተባበርነው በቀር ማንም ሰው አገርን ሙሉ ሊያሸብር አይችልም፡፡
ኢዲ ሙሮው
(አሜሪካዊ ጋዜጠኛ)
በሌላው ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያለው ሰው ሁሉ ጨቋኝ ነው፡፡
ፍራንሲስኮ ፒዋይ ማርጋል
(ስፔናዊ ፖለቲከኛና ደራሲ)
ሰዎች ቄሳሮችንና ናፖሊዮኖችን ማምለክ እስካላቆሙ ድረስ ቄሳሮችና ናፖሊዮኖች መከራ ሊያበሏቸው መነሳታቸው አይቀርም፡፡
አልዶስ ሁክስሌይ
(እንግሊዛዊ ደራሲና ወግ ፀሐፊ)
ራሱን እንዲወደድ ማድረግ ያቃተው፣ ራሱን እንዲፈራ ማድረግ ይሻል፡፡
ዣን ባንቲስት ራሲን
(ፈረንሳዊ ፀሐፌ ተውኔት)
ጭቆና ሁልጊዜ ከነፃነት የተሻለ የተደራጀ ነው፡፡
ቻርልስ ፒሬ ፔለጉይ
(ፈረንሳዊ ፀሐፊና ገጣሚ)
በጨቋኝ ሥርዓት ውስጥ ከማሰብ ይልቅ መተግበር ይቀላል፡፡
ሃና አሬንድት
(ትውልደ - ጀርመን አሜሪካዊ ፈላስፋና የታሪክ ምሁር)
ሰውየውን እየጨቆንክ ለታሪኩ፣ ለሰዋዊነቱና ለስብዕናው ዕውቅና መስጠት አትችልም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በዘዴ ከእሱ ላይ መውሰድ አለብህ፡፡ እናም ይሄ ሰው በታሪክ ውስጥ ያለውን ሚና በተመለከተ በመዋሸት ትጀምራለህ፡፡
ጆን ሄንሪክ ክላርክ
(አሜሪካዊ የታሪክ ባለሙያና የትምህርት ሊቅ)
ሁሉም ዘመናዊ አብዮቶች የተጠናቀቁት የመንግስትን ሥልጣን በማጠናከር ነው፡፡
አልበርት ካሙ
(ትውልደ - አልጀርያ ፈረንሳዊ ደራሲና ድራማ ጸሃፊ)

የ”ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” መግለጫ


መሰባሰብ ከጀመረ ሁለት ዓመት የሆነውና ሕጋዊ ዕውቅና በሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ያገኘው “ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” በተደጋጋሚ ስብሰባዎቹ ከሕዝቡና ከደንበኞቹ ለአባል ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚቀርቡትን ሐሳቦች አስተያየቶችና ቅሬታዎች ሲመረምርና ሲወያይበት ሰንብቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ስብሰባውም ለአንባቢዎች መልስ ለመስጠት ይህን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ከሚጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማ አይስማማ ሌላ ነገር ሆኖ በጋራ አንባቢው ኅብረተሰብ የሚያቀርበው ቅሬታ አለ፡፡ ቅሬታውም “ምነው በወቅቱ አትወጡም?”፣ ምነው ጊዜ ያለፈበት ወሬ ትሰጡናላችሁ፣ ምነው ጠቆረ፣ ምነው ባለ ቀለም የነበረው ጠፋ፣ ምነው ተዳከማችሁ፣ ምነው ጊዜ ያለፈበት የሥራና የጨረታ ማስታወቂያ ታስነብቡናላችሁ ወዘተ. ይላል፡፡
ከጋዜጣና ከመጽሔቶች ጋር በማስታወቂያና በስፖንሰርሺፕ የሚገናኝ አካልም ማስታወቂያችን በወቅቱ አልወጣም፣ ጊዜ አልፎበታል፣ ጭራሽ ባለቀለም የነበረው ጥቁርና ነጭ ሆኗል፣ ጭራሽ ቀለሙ ጠቁሮና ደብዝዞ አይታይም አይነበብም ለመክፈል እንቸገራለን ይላል፡፡
“ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” በማኅበሩ ተደጋጋሚ ስብሰባ እነዚህን በዝርዝርና በጥልቀት ተወያይቶ የሕዝብ ቅሬታና የደንቦች አቤቱታ እውነት እንደሆነ ተቀብሏል፤ አምኗል፡፡ ችግሩ ምን ላይ እንደሆነም ለሕዝብ ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡
በተከታታይና በተለያዩ መንገዶች በፕሬስ ሕትመቶች ላይ እየታየ ያለው ችግር በዋነኛነት ከማተሚያ ቤት ጋር የተየያዘ ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት እናሳትማለን። አንዳንዶቻችን በሌሎች ማተሚያ ቤቶች እናሳትማለን።
በተደጋጋሚ የሚታየው የማተሚያ ቤት ችግር አንዱ የሕትመት ማሽን ተበላሸ እየተባለ ጋዜጦችና መጽሔቶች በወቅቱ እንዳይወጡ መደረጉ ነው፡፡ የፈተና ወረቀት እየታተመ ስለሆነ ጋዜጣና መጽሔት በወቅቱ አይታተምም የሚልም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የፕሬስ ውጤቶች ቅዳሜና እሑድ መውጣት ያለባቸው ረቡዕና ሐሙስ ሲወጡ ይታያል፡፡ ይህ ሁኔታ የፕሬስ ቢዝነሱን በእጅጉ እየጐዳ ነው፡፡
ሌላው ችግር ገፅ ቀንሱ ወረቀት የለም ቀለም የለም የሚል ነው፡፡ ይህም ጋዜጦችና መጽሔቶች አንባቢዎች ከሚፈልጉትና ደንበኞች ከተዋዋሉት ጋር የሚሄድ ቁጥር እንዳያገኝ እያደረገና ሰውን እየጐዳ ነው፡፡
ቀለም የለም፣ ፕሌት የለም እየተባለ መልካችሁንና ይዘታችሁን ቀይሩ የሚል ጫናም ከማተሚያ ቤቶች እየመጣ ነው፡፡ ይህም በእጅጉ ቢዝነሱን እየጐዳ ነው፡፡
በተለይ በተለይ ደግሞ ደንበኞችን አክብሮና ተወያይቶ አወያይቶ የገበያ ዋጋን ከመወሰን ይልቅ በድንገት ዋጋ ተጨምሯል እያሉ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሣራና ጫና መፍጠር በእጅጉ አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ ሆኗል፡፡ የጥራት ጉድለትና ጋዜጦችና፣ መጽሔት ፎቶዎቻቸውና ጽሑፎቻቸው መነበብ በማይችሉበት ሁኔታ ተጨማልቆ መውጣትም ሌላው አስፈሪና አሳፋሪ፣ ቢዝነስን በእጅጉ እየጐዳ ያለ ተግባር ሆኗል፡፡
የተከበረው አንባቢ ኅብረተሰብና የቢዝነስ አጋራችን የሆነው አካል ችግራችን ከላይ እንደተጠቀሰው ከአቅማችን በላይ መሆኑን እንዲገነዘብልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ የምንጠቀምበት ማተሚያ ቤት የራሱ የፕሬሱ አይደለምና ‹‹ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ›› የማተሚያ ቤትን ችግር የራሱ ማተሚያ ቤት በማቋቋም ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህም በአጭር ጊዜ እውን ለማድረግ ቀላል ስለማይሆን ይህ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ከመንግሥት ጋር ሆኖ ብርሃንና ሰላምና ሌሎች ማተሚያ ቤቶች የሚፈጥሩትን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡
በቅርብም ችግሩን በጋራ ዓይተንና ተወያይተን በጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር በሚመለከተው አካል በኩል የቀጠሮ ቀን ጥያቄ አቅርበናል፡፡
እኛም የማኅበሩ አባላት የፕሬሶችን ችግር ለመፍታት ራሳችን ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ለማድረግና ድክመቶቻችንንም፣ ችግሮቻችንንም አስወግደን በመጠናከር የሚገባንን ሁሉ ለማድረግ ተነስተናል፡፡ ከመንግሥት ጋር ሆነን ችግሩን ለመፍታትም መንግሥትን ጠይቀናል፡፡
ይህ እንዲህ ሆኖ ሕዝብም ዋነኛውና ወሳኙ አካል ስለሆነና የቆምንለት ዓላማ ተገቢ መረጃ ለሕዝብ በወቅቱና በጥራት መስጠትና ሕዝብን ማገልገል ስለሆነ ሕዝብም ችግራችንን ተረድቶ ይበልጥ የምናገለግልበትን አቅም እንድንገነባ በትዕግስት ከጐናችን እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ
            ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም.          

(ኣፀቢቕና ኣይንበኣስ፣ እንተ ተዓረቕና ከይንጠዓስ)

አንድ የአሜሪካ ጋዜጣ ላይ የሚከተለው ሰፍሯል፡፡ የሚከተለው ኩባንያ (መሥሪያ ቤት) አባል መሆን ይፈልጋሉ?” በሚል ርዕስ፡፡ ነገሩ ዕውነት ነው፡፡ ግን ላታምኑ ትችላላችሁ፡፡
ይህ ኩባንያ ከ500 ጥቂት ከፍ ያሉ ሠራተኞች አሉት፡፡
ኩባንያው የሚከተለው ስታቲስቲክስ አለው፡-
ካሉት አባላት 29ኙ በሚስቶቻቸው ላይ ግፍ በመፈፀም ተከሰዋል፡፡
7ቱ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ታስረው ነበር፡፡
19ኙ የተሳሳተ ቼክ በፈረም ተከሰዋል፡፡
117ቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁለት የንግድ ተቋማትን ኪሣራ ላይ ጥለዋል፡፡
3ቱ አስገድደው ደፍረዋል፡፡
71ዱ ከዚህ ቀደም ባደረሱት ጥፋት ክሬዲት ካርድ ማግኘት አይፈቀድላቸውም፡፡
14ቱ ከአንደዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
8ቱ ከሱቅ ዕቃ ሲመነትፉ ተይዘው ታስረዋል፡፡
21ዱ በአሁኑ ጊዜ ክሳቸውን ለመከላከል ፍ/ቤት ይመላለሳሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 84ቱ ጠጥተውና ሰክረው በመንዳት ታስረዋል፡፡
እነዚህን ሁሉ ያቀፈው ይህ ድርጅት፤ የትኛው ይመስላችኋል?
ምናልባት የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ ነው ትሉ ይሆናል፡፡ ተሳስታችኋል (ሊሆን አይችልም ማለት ግን አይደለም)
አላወቃችሁም? ተስፋ ቆረጣችሁ?
መልሱ ምን መሰላችሁ?
535 አባላት ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ነው፡፡
በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጐችን የሚያወጡትና ሁላችንንም ቀጥ - ለጥ ብላችሁ ተገዙ የሚሉን እነዚሁ የግብዝ ጥርቅሞች ናቸው፡፡
*   *   *
አመራሮች “የራስህን ዐይን ጉድፍ ሳታይ የሌላውን ጉድፍ ለማውጣት አትሞክር” የሚለውን፣ ራስን የማፅዳት መርህ የማወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በሴቶች ላይ ያለን የበላይነት አባዜ ሳይወገድ፣ እጃችን ከማጭበርበር ወንጀል ሳይፀዳ፣ በየንግድ ተቋማቱ ውስጥ የተነካካንበትን ሁኔታ ሳናጠራ፤ ከተለያዩ ሱሶች የተገላገልን ሳንሆንና ከአልባሌ ወንጀሎች ክስ የራቀ የኋላ ታሪክ ሳይኖረን፤ ሌሎችን መምራት አዳጋች መሆኑ መቼም፤ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ በትምህርት ራስን ማብቃት ዋና ነገር ቢሆንም፤ በሥነ-ምግባራዊና ሥነ-ሰብዓዊ ክሂል ካልተደገፈ ጉዟችን ጎዶሎ ይሆንብናል፡፡
ዛሬ ሀገራችን የምትፈልጋቸው አያሌ ባለሙያዎች፣ በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉቱ፤ ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ልዩ ልዩ ንጥረ-ባህሪ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ክሂል ከነዚህ ውስጥ የሚከተሉትን ያገናዘበ ቢሆን ይበጃል፡፡
ልዩነትን መወያየት የሚፈልግ ሰው ያስፈልጋል፡፡ (a bone to pick እንዲሉ)
መቼም ቢሆን ድብቅ ፍላጐት ያለው ሰው ጣጣ ነው፡፡ (an axe to grind እንዲሉ) ከዚያ ይሰውረን፣ የሚል ግልጽ ሰው ያሻናል፡፡
አንድ የተበላሸ ፍሬ ሙሉውን በርሜል ያበላሸዋል፡፡ አንድ ሞሳኝ ሰውም እንደዚያው ሁሉንም ሰው ያበላሻል፡፡
የተሳሳተው ዛፍ ላይ መጮህ (Barking up the wrong tree እንዲሉ) የተሳሳተ ጉዳይ ላይ ከተሳሳተ ሰው ጋር ማውራት ጅልነት መሆኑን የተገነዘበ የፖለቲካ መሪ፤ ያሻናል፡፡
ፈረንጆቹ ወይ ህፃን ወይ አዋቂ አለመሆን አለመታደል ነው ይሉናል (Between hay and grass እንዲሉ) ይህንን ልብ ያለ የፖለቲካ ሰው ይስጠን፡፡
ታገስ (Hold your horses ነው ነገሩ) ትልቅ የህይወት መርህ ነው፡፡ ዕለት ሠርክ ትዕግስት የሚጠይቁ አያሌ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ እነዚያን ለመወጣት የሚችል ሰው ይባርክልን፡፡
ሁሉን ነገር (kit and caboodle እንዲሉ) አጠቃሎ የማየት አስተውሎት ያለው የበሰለ ተቃዋሚ ይሰጠን ዘንድ እንፀልይ፡፡
“ከፈረሱ አፍ ስማ” የሚለው መርህ የገባቸው ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ በወሬ፣ በሃሜት፣ በጥቆማ፣ በስማ - በለው ከሚወቅሱና ከሚከሱ ይገላግሉናልና፡፡
Iron in the fire ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ሁሉ ቦታ ጥልቅ ማለት አይገባም፡፡ ሁኔታዎችን ከማባባስና የከፉ ከማድረግ በቀር ምንም የረባ ዕድገት አናመጣም - በየነደደበት በመዶል፡፡
You aint the only duck in the pond ይህ ማለት በቁም ትርጉሙ ስናየው ኩሬው ውስጥ ያለኸው ዳክዬ አንተ ብቻ አይደህም የሚል ሲሆን፤ አገሩ ሁሉ ስላንተ የሚያወራ እንዳይመስልህ ማለትም ነው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸውን ያህል ጠባያት በአግባቡና በቅጡ ከተቀዳጀን፤ ለመጪው ምርጫ፣ ፋይዳ መኖር ለዕለት - ተዕለት ዲሞክራሲያዊ አሂዶአችን፣ መሳካት ለፍትሕ - ርትዕ ርሃባችን መወገድ፣ ለመልካም አስተዳደር ዕውነተኛ ገጽታችን መበልፀግ፣ ለእጅ አመላችንና ለዕምነት ክልስነታችን መወገድ መጠነኛ አስተዋጽኦ ያደርግልናል፡፡
 “በሀገራችን ምርጫ በመጣ ሰዓት መንግስት ደግ ይሆናል” የሚል ሐሜታ ሁሌ ይነገራል። መንግስትም ይሰማል፡፡ ህዝብም ያውቃል፡፡ ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ዲሞክራሪያዊት ሂደት መሆኑን ማመን አለብን፡፡ ተለዋጭ ሁኔታን መቋቋም ያስፈልጋል፡፡
እነሆ ይሆኑናል፣ ይበጁናል፣ የምንላቸውን ሰዎች ስንመርጥ ሙያ - ከምግባር፣ ልብ -ከልቦና ያላቸው ቢሆን መልካም ነው፡፡ “አስወርተህ ሹመኝ፣ ዘርፌ አበላሃለሁ” የሚሊ መሆን የለባቸውም፡፡ ገዢ ፓርቲና ተገዢ ፓርቲ የጋራ የጨዋታ ሜዳ፣ የጋራ የጨዋታ ሕግ፣ ባላቸው አገር ደግሞ ሁነኛ ምርጫ ይኖራል ብሎ ማሰብ፣ ጤናማ ላገር ማሰብ ነው፡፡ አዎንታዊነት ነው! የሻከረው ሊላግ፣ የከረረው ሊላላ፣ የጎደጎደው ሊሞላ ይችል ዘንድ የሁሉም ቅን ልቦና ያስፈልጋል፡፡ እስከመቼ ተሸካክረን? እስከመቼ ተቆሳስለን? እስከመቼ ተወነጃጅለን? እርስ በርስም ሆነ፣ ጎራ ለይተንስ እስከመቼ ተጠላልፈን? እስከመቼስ ብቻዬን እሰራዋለሁ ብለን እንዘልቀዋለን፡፡ ዕውነት ለሀገር ብለን ከሆነ ደፋ ቀና የምንለው፣ ዕውነት ለህዝብ ብለን ከሆነ በፖለቲካ የምንሞራረደው፤ በጠላትነት መፈራረጅና ለመጠፋፋት የምንሽቀዳደምበት ሜዳ ምንጠራ ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ የሄድነውን መንገድ ዘወር ብለን ስናይ በራሳችን ላይ መሳቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ታሪካችን የጠብ ነው፡፡ የመጣላት ነው፡፡ ቢያንስ ምርጫዎች ሲደጋገሙ ከጠቡ ቀነስ እያደረጉልን፣ እያሰለጠኑን መሄድ አለባቸው፡፡ “በጣም አንጣላ፤ ከታረቅን እንዳይቆጨን” የሚለው የትግሪኛ ተረት ይህን ይነግረናል፡፡

“የታሰሩት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ” የሚል ተቃውሞ ትናንት ከቀትር በኋላ በተካሄደበት የታላቁ አንዋር መስጊድ አካባቢ በርካታ ፖሊሶች ተሰማርተው የዋሉ  ሲሆን፤ ለሰዓታት በዘለቀው ግርግርና ረብሻ የተኩስ ድምጽ የተሰማ ቢሆንም የደረሰው ጉዳት እስካሁን በዝርዝር አልታወቀም፡፡ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ሲወሰዱ ታይቷል፡፡
ተቃውሞና ግርግር የተፈጠረው የጁምዓ ስግደት ከመጠናቀቁ በፊት እንደሆነ የተናገሩ የአይን እማኞች፤ ቆመጥ የያዙ ፖሊሶች ተሰማርተው እንደነበርና በርካቶች ድብደባ እንደደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡
በተክለሃይማኖት አደባባይ እና ከፒያሳ ወደ መርካቶ የሚወስዱ መንገዶች ለእግረኞችና ለተሽከርካሪ ተዘግተው የነበረ ሲሆን፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለእግረኞች መከፈቱን የተናገሩ የአካባቢው ሰዎች፤ ግርግሩ ግን ወዲያው አልቆመም ብለዋል፡፡
“የታሰሩት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ” ከሚለው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ “ድምፃችን ይሰማ” በተሰኘው ድረገፅ የተቃውሞ ጥሪ ሲተላለፍ እንደሰነበተ ምንጮች ገልፀዋል። አምናም በተመሳሳይ የረመዳን የጾም ወቅት፣ በሦስት የአዲስ አበባ መስጊዶች ሦስት ሰፋፊ ተቃውሞዎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

ለማይክሮ ሶፍት መስራችና ባለቤት ለአሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በመጪው ሐሙስ  የክብር ዶክትሬት እንደሚሰጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  አስታወቀ፡፡  ቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬቱን ለመቀበል በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ዩኒቨርሲቲው ማረጋገጡን ለአዲስ አድማስ ገልጿል።
ቢል ጌትስ የማይክሮሶፍት ኩባንያን በማቋቋም ባገኙት ሃብት አፍሪካውያን ተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረጋቸውና በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት በኢትዮጵያ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ መሰማራታቸው ለክብር ዶክትሬቱ እንዳበቃቸው ተጠቁሟል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ቅዳሜ  8ሺህ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ለ4 እውቅ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል። የቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ በተለየ ፕሮግራም እንዲካሄድ የተወሰነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነት የተዘጋጀ በመሆኑ ነው ያለው ዩኒቨርሲቲው፤ በመንግስት ደረጃ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ በመጪው ሃሙስ  በሚከናወነው የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ልዩ ስነ ስርአት ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አገር እንግዶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ምሁራን እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የዓለማችን እውቁ ባለሃብት ቢል ጌትስ ላለፉት 10 ዓመታት በሃብቱ መጠን ከዓለም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ላይ በመሆን የቆየ ሲሆን ዘንድሮም በ79.1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፎርብስ መጽሔት የወጣው መረጃ ይጠቁማል። ቢል ጌትስ አሁን በግዙፍነቱ የሚታወቀውን ማይክሮሶፍት ለመመስረት ትምህርቱን አቋርጦ ከወጣበት ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ ከተለያዩ የአለማችን ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ስምንት ያህል የክብር ዶክትሬቶችን እንዳገኘ ለማወቅ ተችሏል፡፡

           ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ዕለት ደራሽ የዕርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ብዙ ሚሊዮን ብሮች በሙስና ተመዝብሯል ተባለ” በሚል ርዕስ የድርጅቱ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ፣ የድርጅቱ የስነ-ምግባር መኮንን እና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ም/ሊቀመንበር ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል አቀረቡ የተባለውን ጥቆማ በተመለከተ የሰራችሁትን ዘገባ ለንባብ ማብቃታችሁ ይታወሳል፡፡
ጋዜጣው ለሕዝብ የወገነና ለሁሉም በእኩል አገልጋይነት የቆመ ነው ብለን ስለምናምን ጠቋሚዎች ላቀረቡት ጥቆማ በማስረጃ የተደገፉ ምላሾች ለመስጠት እንወዳለን፡፡
በቅድሚያ ከጠቋሚዎች መሀከል በተለይም የሕግ አገልግሎት ኃላፊውና የስነ-ምግባር መኮንኑ የተሻሻለውን በፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/1997 አንቀታ 27/7 የተገለፀውን ድንጋጌ በመጣስ፣ ጠቋሚዎች ለፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያቀረቡት ጥቆማ በምርመራ ላይ መሆኑን እያወቁ፣ ምርመራውን ከያዘው ክፍል ፈቃድ ውጪ ስለሁኔታው መጻፋቸው ለሕግ የበላይነት ያላቸውን አነስተኛ ግምት ያሳያል፡፡ ይህም ሊሆን አይችልም ከተባለ የጥቆማቸውን ውጤት ቀድመው በመገመት የመጨረሻውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ የድርጅቱን ስም፣ ክብርና ዝና በማጉደፍ ከድርጅታችን ጋር ጥሩ የስራ ግንኙነት ያላቸውን መንግስታዊም ሆኑ የግል ድርጅቶች ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡና ከድርጅቱ ጋር ቀጣይ ግንኙነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ድርጅቱ ከዕድገት ጉዞው እንዲገታ ዛሬም ተኝተው እንደማያድሩ ያሳያል፡፡ ስለሆነም የድርጅቱ ማኔጅመንት ለሕግ ያለውን ክብርና ተገዥነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለቀረቡት ጥቆማዎች ዘርዘር ያለ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ፣ ጠቋሚዎች ለጋዜጣው ባቀረቡዋቸው ጥቆማዎች ጠቅለል ያሉ ምላሾች ለመስጠት ተገዷል፡፡
ጠቋሚዎች በዚሁ ጋዜጣ እንደገለጹት ብዙ ሚሊዮን ብሮች በሙስና ተመዝብሯል በማለት ድርጅቱን በበላይት ለሚመራው የሥራ አመራር ቦርድ ያቀረቡ ሲሆን ቦርዱ በተቋቋመው ኮሚቴ ጥቆማው ተጣርቶ ውድቅ ሲሆንባቸው በቅርፅ ተመሳሳይነት ያላቸው በይዘት ተመሳሳይነት የሌላቸውን ጥቆማዎቻቸውን በፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ሌሎች ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ላሉዋቸው መንግስታዊ ተቋማት አቅርበዋል፡፡
ጠቋሚዎች በሙስና ተመዝብሯል ብለው በዝርዝር የገለጹዋቸው ነጥቦች፡-
ድርጅቱ የበላይ ተቆጣጣሪ መስሪያቤት ማለት በግብርና ሚኒስቴር የተቋቋመና ሦስት አካላት ያሉበት የባለሙያዎች ቡድን የማጣራት ስራ አከናውኖ ውጤቱን /ሪፖርቱን/ በፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አቅርቧል፤
በፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎችን መድቦ የድርጅቱን የግዥ አፈፃፀም ስርአት በተመለከተ የማጣራት ሥራ ተከናውኖ የምርመራው ሪፖርት ቅጂ ለድርጅቱ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ በምርመራው ሪፖርት ጠቋሚዎቹ እንዳሉት፤ ድርጅቱ የግዥ መምሪያ የለውም፣ በተሟላ የግዥ እቅድ አይመራም፣ ወዘተ… በማለት ለአንባቢ በቂ ስእል በማይሰጥና ግራ በሚያጋባ መልኩ አልተገለፀም፡፡
ድርጅቱ አዲስ ሰራተኞችን የሚቀጥርበት ግልፅ የሆነ መመሪያና ደንብ ያለው በመሆኑ በህገወጥ መንገድ የተቀጠረ አንድም ሰራተኛ የለም፡፡ ድርጅቱ ያሉት ሁለት የመለዋወጫ እና አንድ የፅ/መሣሪያዎች መጋዘኖች ሲሆኑ ወደመጋዘኑ ለሚገቡም ሆነ ለሚወጡ መለዋወጫዎችና የጽሕፈት መሳሪዎች ተገቢው የገቢና የወጪ ሰነድ እየተዘጋጀላቸው አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ በመጋዘኖቹ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አመታዊ የንብረት ቆጠራ በማካሄድ ከሒሳብ መዝገብ ጋር እንዲታረቅ ይደረጋል፡፡
የሂሳብ ማወራረጃ ደጋፊ ሰነዶች እንደወጪው አይነት የተለያዩ በመሆናቸው፣ የትኞቹ አይነት ደጋፊ ሰነዶች እንዲጠፉ፣ መቼ ስራ ላይ የዋሉና የየትኞቹ ተሽከርካሪዎች የተጠቀሙበት የጭነት ማዘዣዎችና የነዳጅ መጠየቂያ ፓዶች ሆን ብለው እንዲጠፉ እንደተደረገ የቀረበልን ማስረጃ የለም፡፡ እነዚህ ሰነዶች ደግሞ የሂሳብ ሰነዶች በመሆናቸው ድርጅቱ በየዓመቱ ሂሳቡን በወጪ ኦዲተሮች ሲያስመረምር በኦዲተሮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርመራ የሚደረግባቸው በመሆኑ በጠቋሚዎቹ እንደተገለፀው የሚሰወሩ አይደሉም፡፡
ድርጅቱ ያለጨረታ የገዛቸው የኢንጀክሽን ፓምፖች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ የቺፕውድ ግዥና ከቆሙ የጭነት ተሸከርካሪዎች የተፈቱ አሮጌ መለዋወጫዎችን /ካኒባላይዜሽን/ በተመለከተ በፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በተመደቡ ኦዲተሮች ተገቢው ምርመራ ተከናውኖ የምርመራው ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
የድርጅቱን የሂሳብ አያያዝ በተመለከተ በፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና  ኮሚሽን በተመደቡ የውጭ ኦዲተሮች ተገቢው ምርመራ ተከናውኖ የምርመራው ሪፖርቱ ለኮሚሽኑ ቀርቧል፡፡ ከቀረበው የኦዲት ሪፖርት ቅጅ መረዳት እንደተቻለው ብር 25 ሚሊዮን የመንግስት ገንዘብ ስለመመዝበሩ፣ የሂሳብ ማወራረጃ ደጋፊ ሰነዶች በመጥፋታቸው ደግሞ ከብር 5 ሚሊዮን በላይ ስለመመዝበሩ በምርመራው ሪፖርት የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ከምርመራው ሪፖርት ውጪ ተመዘበረ ተብሎ የተገለፀው ገንዘብ ጠቋሚዎች አእምሮ ውስጥ ብቻ የተፃፈ ወይም የተሳለ ስእል ነው ብለን እንገምታለን፡፡ ጠቋሚዎች እንዳሉት፤ በሂሳብ ምርመራ ወቅት በጉድለት የተመዘገበ ገንዘብ ተመርማሪው በፈለገበት ጊዜ የጎደለው ብር ተገኝቷል ብሎ ምርመራውን ላከናወነው የኦዲት ቡድን (ኦዲተር) ምለፁ ብቻ ያድነዋል ብሎ ማሰብ ጠቋሚዎች ስለኦዲት ሥራ ያለማወቃቸውን የማያውቁ መሆናቸውን የሚገልፅ ወይም እራሳቸውን እንደአዋቂ በመቁጠር ከሙያው ባለቤቶች ጠይቆ ለመረዳት ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡
በአጠቃላይ ደርጅቱ ከ1997-2001 ዓ.ም በነበሩት 5 ዓመታት በኪሳራ ሲጓዝ የነበረና ለሰራተኛው ደመወዝ እንኳ ለመክፈል አቅቶት ለመውደቅ ሲንገዳገድ የነበረ መሆኑን የድርጅቱን ትክክለኛ ገፅታ ከሚያሳየውና በውጪ ኦዲተሮች ትክክለኛነቱ የተረጋገጠውን የሂሳብ መግለጫዎች ማየት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ በጠቋሚዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደበት የሚገኘው ማኔጅመንት፤ ከተቋቋመበት ከ2002-2005 ዓ.ም ድርጅቱ ይጓዝ ከነበረበት የቁልቁለት መንገድ በማውጣት፣ በውጪ ኦዲተሮች የተረጋገጠ ትርፍ በማስመዝገብና የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአዲስ ለመተካት በተደረገ ጥረት 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው 15 ዘመናዊ የጭነት ተሽከርካሪዎች ባለቤት እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ዛሬም መንግስት በሰጠው ምቹ ዕድል ከ560 ኩንታል በላይ የመጫን አቅም ያላቸው 20 የጭነት ተሽከርካሪዎች ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ላይ የሚገኝና የድርጅቱ ሰራተኞች ከ2002 ዓ.ም በፊት አግኝተውት የማያውቁትን ከ2-3 ወር ደመወዝ ማበረታቻ /ቦነስ/ በየዓመቱ እንዲያገኙ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ሊዋጥላቸው ያልቻሉ ከማስረጃ ይልቅ ለአሉባልታ ቅርብ የሆኑ፣ የማኔጅመንቱን ጥንካሬና ከስራ አመራር ቦርድ ጋር ያለው የጠበቀ የስራ ግንኙነት ያላስደሰታቸው ጠቋሚዎች በሚያናፍሱት ተጨባጭ ያልሆነ ክስ ተደናግጦ ማኔጅመንቱ ድርጅቱን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አይገታም፡፡
እነዚህ ግለሰቦች በድርጊታቸው በሰራተኛው የተተፉበት ወቅት ላይ ስለሚገኙ በማስረጃ ባልተደገፉ ጥቆማቸው ድርጅቱ በአዲስ መልክ እየተደራጀ ባለበት በዚህ ወቅት በመሯሯጥ በመገናኛ ብዙሀን የድርጅቱን ስምና ክብር በማጉደፍ የስልጣን ጥማቸውን /ፍላጎታቸውን/ ለማርካት ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት የማያንኳኩት የባለስልጣን በር፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡
ከጠቋሚዎቹ መሃል ህይወታችን ለአደጋ ተጋልጧል፣ ሁለት ጊዜ በጥይት ተስቻለሁ የሚሉት የቀድሞው የደርግ ሻምበልና የአሁኑ አቶ ያለው አክሊሉ የፈጠራ ወሬዎችን ሲያወሩና ሲያስወሩ ድፍን አንድ አመት ሞልቷቸዋል፡፡ የነፍስ ግድያ ሙከራ ተደረገብኝ ለሚሉት የሀሰት አሉባልታቸው ይረዳቸው ዘንድ እነሱ ባሰቡትና በፈለጉት መልኩ የማኔጅመንት አባላት ላይ የትንኮሳ ስራ እየሰሩ ያሉ ቢሆንም የማኔጅመንት አባላቱ ጉዳዩ በፍ/ቤት እንዲታይላቸው ከማድረግ ባለፈ ጠቋሚዎች ድርጅቱ ግቢ ውስጥ ብቻቸውን ውለው ቢያድሩ እንኳ ነብሳቸውን እስከማጥፋት የሚያደርስ ወንጀል ለመስራት ፍላጎት ያለው የማኔጅመንት አባል እንደሌለ ልቦናቸው እያወቀ፣ ከድርጅቱ ውጪ ባሉ ወገኖች ከንቱ ውዳሴና ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርጉት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸው አካል ነው፡፡
(ከ“ዕለት ደራሽ የእርዳታ
ትራንስፖርት ድርጅት” ማኔጅመንት)

Saturday, 12 July 2014 12:55

አውሮፓ 10 ደቡብ አሜሪካ 9

20ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬ እና ነገ በሚደረጉት ሁለት የደረጃ እና የዋንጫ ጨዋታዎች ያበቃል፡፡ ዛሬ በደረጃ ጨዋታ አዘጋጇ አገር ብራዚል ከሆላንድ የሚጫወቱ ሲሆን በነገው እለት ደግሞ በዋንጫ ጨዋታ አውሮፓን የምትወክለው ጀርመንና ከደቡብ አሜሪካ የተወከለችው አርጀንቲና ይገናኛሉ፡፡ ጀርመንና አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ለሶስተኛ ግዜ መገናኘታቸው ነው፡፡
በዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ለስምንተኛ ጊዜ የሚሰለፈው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን  ለ4ኛ ጊዜ የውድድሩ ሻምፒዮን በመሆን በዓለም ዋንጫ ድል ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ከያዘችው ጣሊያን ጋር ክብረወሰኑን ለመጋራት ያነጣጥራል፡፡ አርጀንቲና ደግሞ ሶስተኛ የሻምፒዮናነት ክብሯን በማሳካት የጀርመንን የውጤት ክብረወሰን ለመስተካከል ታቅዳለች፡፡ በሌላ በኩል የሁለቱ ቡድኖች ውጤታማነት በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ አህጉራት መካከል ያለውን የዋንጫ ፉክክር የሚወስን ነው፡፡
ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ በፊት በሻምፒዮናነት ክብር አውሮፓ 10ለ9 ደቡብ አሜሪካን ይመራል፡፡


ጀርመን
ብሄራዊ 11 ወይም ‹ዘ ማንሻፍትስ› በሚል መጠርያ የሚታወቀው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ሌሎች ተጨማሪ ቅፅል ስሞች በሰንደቅ አለማ እና ማልያ ቀለማት እና ምልክቶች ንስሮች እና ጥቁርና ነጭ ተብሎም ይታወቃል፡፡
ለብሄራዊ ቡድኑ ብዙ የተሰለፈ - ሉተር ማትያስ 150 ጨዋታዎች
ለብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ያገባ -ሚሮስላቭ ክሎሰ 71 ጎሎች
የፊፋ ደረጃ -2
የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨዋታ - ከ106 ዓመት በፊት
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እና ውጤት 18 ጊዜ - 3 ጊዜ ሻምፒዮን (1954፤ 1974ና 1990 እኤአ)
ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ  የፍፃሜ ጨዋታ በፊት በዓለም ዋንጫ 105 ጨዋታዎች- 65 ድል- 20 አቻ- 20 ሽንፈት - 223 አገባ 121 ገባበት
የአውሮፓ ዋንጫ ተሳትፎ እና ውጤት 11 ጊዜ -3 ጊዜ ሻምፒዮን (1972፤ 1980ና 1996 እኤአ)
ጀርመን እግር ኳሷን እዚህ ለማድረስ ከ2000 እ.ኤ.አ ጀምሮ አገር አቀፍ የዕድገት ፕሮግራም በመንደፍ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ በፊት የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በዓለም እና በአውሮፓ ዋንጫ ተሳትፎዎቹ ከምድብ ማጣሪያ ማለፍ ሲያዳግተው ነበር፡፡ በጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን እና በአገሪቱ ከፍተኛ የስፖርት ባለሙያዎች እና አሰልጣኞች ተግባራዊ የሆነው ፕሮግራም ከ20 ሺ በላይ የስፖርት መምህሮችና ባለሙያዎች በማሳተፍ በጀርመን 366 ክልሎች ታዳጊ ተጨዋቾች በመመልመልና በማሰልጠን ተሰርቶበታል፡፡  ከአሰልጣኞች መካከል አሁን የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድንን የሚያሰለጥነው እና ቀድሞ የጀርመን ዋና አሰልጣኝ የነበረው ጀርገን ክሊንስማንና የአሁኑ ዋና አሰልጣኝ ጆኦኪም ሎው ዋና በዚህ ፕሮግራም ተዋናዮች ነበሩ፡፡


አርጀንቲና
‹ላ አልባሴላስቴ› በሚል ቅፅል ስሙ የሚጠራው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን በሰንደቅ አለማ ቀለም እና በማልያዎቹ ቀለማት ነጭና ውሃ ሰማያዊ  ይባላል፡፡
ለብሄራዊ ቡድኑ ብዙ የተሰለፈ - ሃቪዬር ዛኔቲ 145 ጨዋታዎች
ለብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ያገባ -ጋብሬል ባቲስቱታ 56 ጎሎች
የፊፋ ደረጃ -5
የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨዋታ - ከ113 ዓመት በፊት
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እና ውጤት 15 ጊዜ - 2 ጊዜ ሻምፒዮን (1978ና 1986 እኤአ)
ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ  የፍፃሜ ጨዋታ በፊት በዓለም ዋንጫ 75 ጨዋታዎች -41 ድል -13 አቻ -20 ሽንፈት - 131 አገባ 83 ገባበት
የኮፓ አሜሪካ ተሳትፎ እና ውጤት 39 ጊዜ -14 ጊዜ ሻምፒዮን
ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ  በዓለም የእግር ኳስ ገበያ ከፍተኛ ብዛት ያላቸውን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በማቅረብ አርጀንቲና አንደኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ በመላው አለም በሚካሄዱ የሊግ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ በሆኑ ክለቦች ከ1700  በላይ አርጀንቲናውያን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ይገኛሉ፡፡ ብራዚላውያን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛታቸው 1400 ነው፡፡

      ባለፉት 5 ዓለም ዋንጫዎ ኮከብ ግብ አግቢ ች ለግማሽ ፍፃሜ ከደረሰ 4 ቡድኖች ተገኝቷል፡፡ ግማሽ ፍፃሜ መግባት 7 ጨዋታ ማድረግ በመሆኑ ለፉክክር ያለውን እድል ያሰፋዋል፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ በ6 ጎሎች እየመራ ነው፡፡ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር በ5 ጎሎች የሚከተለው ሲሆን ሊዮኔል ሜሲ እና ኔይማር ዳሲልቫ በ4 ጎሎች ሶስተኛ ደረጃ አላቸው፡፡ ቶማስ ሙለር እና ሊዮኔል ሜሲ በዋንጫው ጨዋታ ከ1 በላይ ካገቡ ለወርቅ ጫማው ሽልማት እድል የሚኖራቸው ሲሆን እያንዳንዳቸው እኩል 3 ጎል ያስመዘገቡት የሆላንዶቹ ሮበን እና ቫንፕርሲ በደረጃ ጨዋታ ከሃትሪክ በላይ ጎል ካስመዘገቡም ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር በዋንጫ ጨዋታ አንድ ግብ በማስቆጠር በሁለት ተከታታይ ዓለም ዋንጫዎች በኮከብ ግብ አግቢነት በመጨረስ የወርቅ ጫማ ለመሸለም እድል የሚኖረው 3 ለጎል የበቁ ኳሶችን በማቀበል ነው፡፡ በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ ተፎካካሪዎች የሆኑት የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ፤ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር እና የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ናቸው፡፡ 

የኮሎምቢያው ጀምስ በ5 ጨዋታ 6 ጐል በማግባት  በ3 ግጥሚያዎች የጨዋታው ኮከብ ሽልማቶችን በመውሰድ እና ተጨማሪ ለጎል የበቁ ሁለት ኳሶችን በማቀበል ፉክክሩን እየመራ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው በ4 ግጥሚያዎች የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው ሊዮኔል ሜሲ በዋንጫ ጨዋታ በሚኖረው ብቃት በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ ለመሸለም ሰፊ እድል ይዟል፡፡ በዓለም ዋንጫው ኮከብ በረኛነት የወርቅ ጓንት ለመሸለም ሶስት በረኞች ዋና ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡  የአርጀንቲናው ሰርጂዬ ሮሜሮ በ4 ጨዋታዎች ጐል አልገባበትም፡፡ የጀርመኑ ማኒዌል ኑዌር  ደግሞ በ3 ጨዋታ ጎል ያልተቆጠረበት ሲሆን በፍፃሜው የሚኖረው ብቃት ለመሸለም ሰፊ እድል አለው፡፡ በሶስት ግጥሚያዎች የጨዋታው ኮከብ ለመሆን የበቃው የኮስታሪካው ግብ ጠባቂ ኪዬሎር ናቫስ ሌላው ተፎካካሪ ነው፡፡

የውጤት ደረጃ ከ5 እስከ 32
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ዛሬ እና ነገ በሚደረጉት ሁለት የደረጃ እና የዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉት አራቱ ቡድኖች ብራዚል፤ ሆላንድ፤ ጀርመንና አርጀንቲና በአጠቃላይ ውጤት ከ1 እስከ 4 የሚኖራቸውን ደረጃ ይወስናሉ፡፡  እስከ ሩብ ፍፃሜ ለመሳተፍ የበቁት 28 ቡድኖች ደግሞ ከ5ኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ 28ኛ በቅደም ተከተል በውጤታቸው ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለሩብ ፍፃሜ የበቁት እና እያንዳንዳቸው 14 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈላቸው 4 ብሄራዊ ቡድኖች ኮሎምቢያ፤ ቤልጅዬም ፈረንሳይና ኮስታሪካ  ከ5 እስከ 8ኛ ደረጃ ያገኛሉ፡፡ 16 ቡድኖች ለደረሱበት ጥሎ ማለፍ የበቁት እና እያንዳንዳቸው 9 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈላቸው 8 ብሄራዊ ቡድኖች ቺሊ፤  ሜክሲኮ፤ ስዊዘርላንድ፤ ኡራጋይ፤ ግሪክ፤ አልጄርያ፤ አሜሪካ እና ናይጄርያ ከ9 እስከ 16ኛ ደረጃ ያገኛሉ፡፡ በምድብ ማጣርያ ተሳትፏቸው የተወሰኑት እና እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት የሚከፈላቸው 16 ብሄራዊ ቡድኖች ኢኳዶር፤ ፖርቱጋል፤ ክሮሽያ፤ ቦስኒያ፤ አይቬሪኮስት፤ ጣሊያን፤ ስፔን፤ ራሽያ፤ ጋና፤ እንግሊዝ ደቡብ ኮርያ፤ ኢራን፤ ጃፓን፤ አውስትራሊያ፤ ሆንዱራስ እና ካሜሮን ከ17 እስከ 32ኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከስፖንሰሮች የተሳካለት አዲዳስ ነው
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ  በከፍተኛ ደረጃ የማስተዋወቅ እና የማሻሻጥ ዘመቻ ካደረጉት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ስኬታማ የሆነው የጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ነው፡፡ ፊፋ በዓለም ዋንጫው በአጋርነት ከሰሩት 8 ስፖንሰሮች 1.53 ቢሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡
አዲዳስ ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ በተያያዘ ለማስተዋቂያ እና ለገበያ ማስፋት ዘመቻው ወጭ ያደረገው 85 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በውድድሩ ያቀረባት ብራዙካ የተባለች ኳስ ባተረፈችው ተወዳጅነት እንዲሁም ታኬታና ማልያ ያቀረበላቸው 9 ብሄራዊ ቡድኖች በተለይ ጀርመን ባስመዘገቡት ስኬት እስከ  2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይጠብቃል፡፡ በዚህ ገቢም በዓለም ዋንጫው ስኬታማ በመሆን የጀርመኑ አዲዳስ ግንባር ቀደም ይሆናል፡፡
የቅርብ ተቀናቃኙ የሆነው የአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ በዓለም ዋንጫው የማስተዋወቅ እና የማሻሻጥ ዘመቻው  70 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጎ  እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በመጠበቅ ይከተላል፡፡ ለናይኪ ገበያ መቀነስ የማልያ እና የትጥቅ ስፖንሰር ከሆነለቻቸው አስር ብሄራዊ ቡድኖች በተለይ አዘጋጇ ብራዚል ለዋንጫ አለመድረሷ ነው፡፡ ከሌሎች የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮች ለማስተዋወቅ እና ለማሻሻጥ ዘመቻው ኮካ ኮላ በብራዚል ብቻ 600 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጉ ከፍተኛው ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

    ጀርመንና አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ 5 የሻምፕዮናነት ክብሮች  አግኝተዋል፡፡ ነገ በዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የሚገናኙት በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ ይሆናል፡፡  በሁለቱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በ1986 እኤአ ላይ አርንጀቲና ስታሽንፍ በ1990 እኤአ ደግሞ ጀርመን አሸንፋለች፡፡ ከ20ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ፍልሚያ በፊት የአውሮፓዋ ጀርመን ለ3 ጊዜያት (በ1954፤ በ1974 እና በ1990 እኤአ) እንዲሁም አርጀንቲና ለ2 ጊዜያት (በ1978 እና በ1986 እኤአ) የዓለም ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ የእነዚህ የዓለም ዋንጫ ድሎች ታሪክ ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በፊፋ የወርቅ ኢዮቤልዩ የደመቀው የጀርመን የመጀመርያ ድል
በ1954 እ.ኤ.አ 5ኛው ዓለም ዋንጫ  በአውሮፓዊቷ አገር ስዊዘርላንድ የተካሄደ ነበር፡፡   ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ትኩሳት ከረገበ ከ8 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ይህ ዓለም ዋንጫ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ጋር መያያዙ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ የቴሌቨዥን ስርጭት በጥቁርና ነጭ ለመጀመርያ ጊዜ የተከናወነበትም ነበር፡፡ በሌላ በኩል  በአጠቃላይ 140 ጐሎች ከመረብ ማረፋቸውና ባንድ ጨዋታ በአማካይ 5.38 ጐሎች መመዝገቡ እስካሁን በሪከርድነት ቆይቷል፡፡ በ5ኛው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የተገናኙት ምዕራብ ጀርመንና ሃንጋሪ ነበሩ፡፡ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በካፒታሊዝም ስርዓት ይተዳደር በነበረው የአገሪቱ ክፍል ተወካይነት ምእራብ ጀርመን ተብሎ የተሳተፈ ነበር፡፡   በ1950ዎቹ ምርጥ ከሚባሉ  ቡድኖች አንዱ የነበረውና እነ ፈረንስ ፑሽካሽ፣ ቦዝስክ ኮሲስኮና ሀይ ድግኡቲ የሚገኙበት የሃንጋሪ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ የውድድሩ አስደናቂ አቋም ያሳየ ነበር፡፡ የፍፃሜው ፍልሚያ በስዊዘርላንዷ በርን ከተማ በሚገኘው የዋንክድሮፍ ስታድዮም ሲካሄድ ከ60ሺ በላይ ተመልካች ነበረው፡፡ የሃንጋሪ  ቡድን 2ለ0 ሲመራ ቢቆይም ከኋላ ተነስቶ 3 ጐሎችን በማስቆጠር 3ለ2 በሆነ ውጤት የምዕራብ ጀርመን  ብሄራዊ ቡድን አሸነፈ፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያው የሻምፒዮንነት ክብር በማግኘት  የጁሌዬስ ሪሜት ዋንጫን ተቀዳጅቷል፡፡ የምእራብ ጀርመን ደጋፊዎች ብሄራዊ ቡድናቸው የጁሌዬስ ሪሜት ዋንጫን ሲረከብ በስታድዬሙ ምእራብና ምስራቅ ጀርመንን የሚያዋህደውን መዝሙር እንዳሰሙ ታሪክ ያስታውሳል፡፡
የአሁኗ ዓለም ዋንጫ ለሽልማት ቀርባ ለአስተናጋጇ ጀርመን  ሁለተኛ ድል
10ኛውን የዓለም ዋንጫ  በ1974 እ.ኤ.አ  ላይ የተካሄደው በምዕራብ ጀርመን ነበር፡፡  በ9 ዓለም ዋንጫዎች ለሻምፒዮኑ አገር ስትሸለም የቆየችው የጁሌስ ሪሜት ዋንጫ በአዲስ ተቀይራ የቀረበችበት ዓለም ዋንጫ ነበር፡፡ የጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫን  ብራዚል ለሶስተኛ ጊዜ ወስዳ በማስቀረቷ  አዲሷ የፊፋ ዓለም ዋንጫ መሰራቷ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ አዲስ የዋንጫ  ሽልማት ከ7 የተለያዩ አገሮች ቀራፂዎች የሰሯቸው 53 የተለያዩ ዲዛይኖች ለውድድር ቀረቡ፡፡ በጣሊያናዊው ቀራፂ ሲልቪዮ ጋዚንጋ  የቀረበችው ዋንጫ ተመረጠች፡፡ 10ኛው ዓለም ዋንጫ ከቀዳሚዎቹ 9 ዓለም ዋንጫዎች ልዩ ካደረጉት ሁኔታዎች አንዱ በባለቀለም ቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የሆላንዳዊያን የ‹ቶታል ፉትቦል› የአጨዋወት ፍልስፍና የሚወሳ ታሪክ ነበር፡፡ በዋንጫው ጨዋታ የምዕራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና በቶታል ፉትቦል የተደነቀው የሆላንድ ብሄራዊ ቡድን ተገናኙ፡፡ ምዕራብ ጀርመን  በብሄራዊ ቡድኑ አምበል  ፍራንዝ ቤከንባወር  እና  በዋና አሰልጣኝ ሄልሙት ሾን  የተመራ ነበር፡፡ ሆላንድ ደግሞ በአሰልጣኝ ሩኒስ ሚሸልስና በታዋቂው ተጨዋች ዮሃን ክሮይፍ አስደናቂ አቋም በማሳየት ለዋንጫው የታጨ ነበር፡፡  የምዕራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን 2ለ1 በማሸነፍ አዲሷን የዓለም ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲሁም በውድድሩ ታሪክ ሁለተኛው የዓለም ሻምፒዮናነት ክብር አስመዘገበ፡፡ ለምዕራብ ጀርመን የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ዘ ቦምበር በሚል ቅል ስሙ የሚታወቀው ገርድ ሙለር ነበር፡፡ ጀርመናዊያን ቄሳሩ እያሉ በሚያሞግሱት ፍራንዝ ቤከንባወር የተመራው ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ሚዬርና በርቲ ቮጎትስ የተባሉ ምርጥ ተጨዋቾች ይታወሳሉ፡፡
የአርጀንቲና የመጀመርያ ድል
በ1978 እ.ኤ.አ 11ኛውን  የዓለም ዋንጫ የማስተናገድ እድል ያገኘችው አርጀንቲና ናት፡፡ በ1ኛው ዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ተጫውታ ዋንጫውን በኡራጋይ ከተነጠቀች ከ48 ዓመታት በኋላ ወደ እግር ኳስ ሃያልነቷ ለመመለስ የበቃችበት ነበር፡፡  በዓለም ዋንጫው ዋዜማ አርጀንቲናን ያስተዳድር የነበረው መንግስት በመፈንቅለ መንግስት  ተገልብጦ አምባገነኑ መሪ ጄኔራል ቪዴላ ስልጣን መያዛቸው ነበር፡፡ ስለሆነም የዓለም ዋንጫው መሰናዶ በጄኔራል ቪዴላ መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰትና በአምባገነናዊ ስርአቱ ከበርካታ አገራት ተቃውሞ የተሰነዘርበት ነበር፡፡ የሻምፒዮናነት ክብሩን ለመጀመርያ ጊዜ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ በ11ኛው የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ጨዋታ የቀረቡት አስተናጋጇ አርጀንቲና እና ሆላንድ  ነበሩ፡፡ የፈረንሳዩ ለኢክዊፔ ጋዜጣ እና ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃናት አስቀድመው ከተደረጉት 10 የዓለም ዋንጫዎች ምርጡ የፍፃሜ ፍልሚያ ተብሎ ነበር፡፡ አርጀንቲና 3ለ1 በሆነ ውጤት ሆላንድን በማሸነፍ  በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ድል አግኝታለች፡፡ በወቅቱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ሴዛር ሜኖቲ ከቡድናቸው የ17 ዓመቱን ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና መቀነሳቸው ቢያስተቻቸውም ቡድናቸው የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ተከትሎት በነበረው ውበትን የተላበሰ አጨዋወት  አድናቆት አትርፈውበታል፡፡ ከተጨዋቾች አምበል የነበረው ዳንኤል ፓሳሬላ እና ማርዮ ኬምፐስ የተባለው አጥቂ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉ  ነበሩ፡፡ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ማርዮ ኬምፕስ በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ከነበሩ  ተጨዋቾች መካከል  በፕሮፌሽናልነት በስፔን ላሊጋ ለሚወዳደረው ሻሌንሺያ ክለብ በመጫወት ብቸኛው ነበር፡፡
በማራዶና ጀብድ የአርጀንቲና ሁለተኛ ድል
13ኛው የዓለም ዋንጫ በ1986 እ.ኤ.አ ላይ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን የምትገኘው ሜክሲኮ ጊዜ ያስተናገደችው ነበር፡፡  ይህ ዓለም ዋንጫ በመስተንግዶ ማራኪነት፤ በስታድዬሞች በታየው ሜክሲኳውያን ማዕበል የተባለው ድጋፍ አሰጣጥና በአርጀንቲናዊው ኮከብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ባሳየው የላቀ ችሎታ የማይረሳ  ነው፡፡  በዚህ ዓለም ዋንጫ ላይ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት አርጀንቲና ከምእራብ ጀርመን ጋር ነበር፡፡ ከ115ሺ በላይ ተመልካች ባስተናገደው ታላቁ አዝቴካ ስታድዬም የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ 2ለ2 በሆነ ውጤት እስከ 83ኛው ደቂቃ ቆየ፡፡  ማራዶና ለቡድን አጋሩ ጆርጌ ቡርቻጋ አመቻችቶ ያቀበለው ምርጥ ኳስ አማካኝነት  የማሸነፊያ ጎል ተመዘገበችና በአርጀንቲና 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ከ30 ሚሊዮን በላይ አርጀንቲናውያንም በድሉ ፌሽታ መላው አገራቸውን በደስታ አጠልቅልቀው ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ አርጀንቲናን በአምበልነት እየመራ ለታላቁ የዓለም ዋንጫ ድል የበቃው ማራዶና  በአንድ ተጨዋች ጀብደኛነት ውድድረን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየበት ነበር፡፡ አርጀንቲና እስከዋንጫው ባደረገችው ግስጋሴ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አምስት ጎሎችን ከማግባቱም በላይ ለሌሎች  አምስት ግቦች መመዝገብ ምክንያትም ሆኗል፡፡ ማራዶና በምርጥ ችሎታው ዓለምን ማንበርከክ ቢችልም በተለይ በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ላይ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ግን የብዙዎችን አድናቆት ወደ ቁጣ ቀይራዋለች፡፡ በወቅቱ ለንባብ የበቃው የፈረንሳዩ ጋዜጣ ሌኢክዌፔ ማራዶናን ‹‹ግማሽ መልዓክ ግማሽ ሰይጣን››  ብሎታል፡፡
የዓለም ዋንጫ ድል ሃትሪክ በጀርመን  
14ኛው ዓለም ዋንጫ በ1990 እኤአ ላይ በጣሊያን አዘጋጅነት የተደረገ ነው፡፡ በውድድሩ ታሪክ  ዝቅተኛ የግብ ብዛት የተመዘገበበት ወቅት ነበር፡፡ አዘጋጇ ጣሊያን በግማሽ ፍፃሜው ከጨዋታ ውጪ የሆነችው በአርጀንቲና ተሸንፋ ነበር፡፡ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ስለነበር ግን በክለብ ደረጃ የሚጫወትበት ናፖሊ ክለብ ደጋፊዎች ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ ጣልያን ትተው እሱን እንደግፍ በሚል ተወዛግበዋል፡፡
በዚህ ዓለም ዋንጫ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት  በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ አርጀንቲና እና ምዕራብ ጀርመን ነበሩ፡፡ በሮም ኦሎምፒክ ስታድዬም በተደረገው ጨዋታ የምእራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን  አርጀንቲናን 1ለ0 ረታ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በፍፃሜ ጨዋታ በታላቁ አዝቴካ ስታድዬም በማራዶና በተመራችው አርጀንቲና የደረሰበትን ሽንፈት በመበቀል ለ3ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው ፍራንዝ ቤከን ባወር ደግሞ የዓለም ዋንጫን በተጨዋችነት በ1974 እኤአ ላይ ካሸነፈ ከ16 ዓመታት በኋላ በአሰልጣኝነት በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ አስደናቂ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡

“ግብረ ሰዶማውያን
በድንጋይ ተወግረው መሞት አለባቸው”
የተለያዩ የአለማችን ሀገራት እንደሚከተሉት የፖለቲካ ስርአት በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ያራምዳሉ፡፡ ለምሳሌ የግብረ ሰዶማዊነትን ጉዳይ በተመለከተ ለአሜሪካና ለአውሮፓ መንግስታት ነገሩ የዜጎች ሰብአዊ መብት ጉዳይ ሲሆን ለአብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት ደግሞ ምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው የወንጀል ድርጊት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የኡጋንዳ መንግስት ግብረ ሰዶማዊነት በወንጀል የሚያስቀጣ የተከለከለ ድርጊት መሆኑን የሚደነግግ ህግ አውጥቶ በስራ ላይ አውሏል፡፡ በፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሚመራው የኡጋንዳ መንግስት፣ ይህን ህግ በማውጣቱ የተነሳ ከአሜሪካና ከበርካታ የአውሮፓ መንግስታት እንዲሁም ከሌሎች የመብት ተሟጋች ነን ከሚሉ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የዜጎቹን ሰብአዊ መብት ጥሷል ወይም አላስከበረም በሚል ያልተቋረጠ የውግዘት ናዳ ወርዶበታል፡፡
በተለይ የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፤ የኡጋንዳ መንግስት ግብረ ሰዶማዊነትን በመከልከል ያወጣውን ህግ ባስቸኳይ ካልሰረዘ ማዕቀብ እንደሚጣልበት አስጠንቅቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን ከአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ግብረ ሰዶማዊነት በተመለከተ አንድ ለየት ያለ ነገር ሲነገር ተደምጧል፡፡ ለአክላሆማ ከተማ ምክር ቤት ምርጫ የቲ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት ስኮት ኤስክ፤ ግብረ ሰዶማዊነትን መቃወም ብቻ ሳይሆን ግብረ ሰዶማውያን የሆኑ ሁሉ የብሉይ ኪዳን መጽሀፍ ቅዱስ አስርቱ ትዕዛዝ እንደሚደነግገው በድንጋይ ተወግረው እንዲገደሉ እንደሚፈልጉ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት በግልጽ አሳውቀዋል፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ “ግብረ ሰዶማውያንን ለመተቸትና በእነሱ ላይ ለመፍረድ እኔ ማን ነኝ?” በማለት የሰጡትን መግለጫ በተመለከተም ስኮት ኤስክ በፌስቡክ ገፃቸው ስለ ግብረሰዶም አስፀያፊነት በመጽሀፍ ቅዱስ የተፃፈውን በመጥቀስ፣ ለግብረ ሰዶማውያን የሚገባው ቅጣት በድንጋይ ተወግሮ መሞት እንደሆነ በማስፈር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይሄ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር የተደመጠው ከአሜሪካዋ ግዛት ከኦክላሆማ መሆኑ ብዙዎችን በግርምታ አፍ አሲዟል፡፡