Administrator

Administrator

በመጪው ሳምንት ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀርባል
   ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ የ22 ታራሚዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቃጠሎውን በተመለከተ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት በመጪው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀርባል ተብሏል፡፡
አደጋው የደረሰ ሰሞን በስፍራው ተገኝተው ሁኔታውን የተመለከቱት የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች፤ የእሳቱን መንስኤና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ኮሚሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ የምርመራ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡  የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አባዲ፤ ምርመራውና ማጣራቱ ተጠናቆ ሪፖርቱ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ በመጪው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚቀርብ ገልፀዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ በወቅቱ 2 ታራሚዎች በጥይት፣ ቀሪዎቹ በቃጠሎው ህይወታቸው ማለፉ መገለፁ የሚታወስ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሌላ በጎንደርና ደብረ ታቦር ወህኒ ቤቶችም በደረሰው የቃጠሎ አደጋ የታራሚዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም፡፡  

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በዳንግላ ከተማ የቀድሞ ፍቅረኛው ላይ የአሲድ ጥቃት የፈፀመው ሰለሞን በላይ፤ የ18 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ የአማራ ክልል የዳንግላ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት በዋለው ችሎት ተጎጂዋ መሰረት ንጉሴ በአካል ተገኝታ የጥቃቷን መጠን አስረድታለች፡፡ ምንም እንኳ ጥፋተኛው የፈፀመው ጥቃት በሞትና በእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ቢሆንም ድርጊቱን መፈፀሙን በማመኑና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ፣ ፍ/ቤቱ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንደቀጣው የዳንግላ ከተማ ሴቶች፣ ህፃናትና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ አዛሉ ናደው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
‹‹ጥፋተኛው ወንጀሉን ከፈፀመበት ዕለት አንስቶ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን እኛም በጉዳዩ ላይ ጥብቅ ክትትል ስናደርግ ነበር›› ያሉት ሀላፊዋ፤ ምንም እንኳ በሞትና በእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ቢፈፅምም ፍ/ቤቱ አንዳንድ ነገሮችን ከግምት አስገብቶ የ18 ዓመት እስር መፍረዱ ሌሎችን የሚያስተምር ተገቢ ቅጣት ነው ብለዋል፡፡ ወጣቷ ተጎጂ አሁንም በከፍተኛ ስቃይ ላይ መሆኗን የገለፁት ሀላፊዋ፤ ወቅታዊው የፀጥታ ችግር ትኩረታቸውን ስቦት እንጂ ከዳንግላ ከተማ አስተዳደር፣ ከክልሉና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር ልጅቷ አስቸኳይ የውጭ ህክምና የምታገኝበትን መንገድ ለማፈላለግ እንተጋ ነበር ብለዋል፡፡
ወጣት መሰረት ንጉሴ አዲስ አበባ በሚገኙ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ ላለፉት አምስት ወራት የቀለብ፣ የህክምናና የቤት ኪራይ ወጪ ተሸፍኖላት፣ መጠነኛ ህክምና ብታደርግም ጤናዋ መሻሻል ባለመቻሉ ወደ ውጭ አገር ሄዳ ለመታከም እስከ 1 ሚ.ብር መጠየቋን ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡
ባለፈው ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም በአዜማን ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጅቶላት የነበረ ሲሆን በዚህ ዝግጅት ከ200 ሺህ ብር የበለጠ ባለመገኘቱ በአስቸኳይ ወደ ውጭ ሄዳ ለመታከም እንዳልቻለች ገልፃ፤ አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስላት ጥሪ አቅርባለች፡፡
ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛው ላይ የሰጠውን ፍርድ በተመለከተ ለአዲስ አድማስ አስተያየቷን የሰጠችው ተጎጂዋ፤ ‹‹በእርግጥ ሞት ወይም የእድሜ ልክ እስራት ይፈረድበት ብለሽ ይግባኝ ጠይቂ ተብዬ ነበር፤ 18 ዓመት ከህሊና ፀፀት ጋር በቂ ነው ብዬ ትቼዋለሁ›› በዋና የምግብ አብሳይነት (Chef) እየሰራች ራሷንና ወላጅ የሌላቸውን ታናናሽ እህቶቿን ታሳድግ እንደነበር ያስታወሰችው መሰረት፤ አሁን በደረሰባት ጉዳት እህቶቿ ያለ ረዳት መቅረታቸውን ጠቅሳ፤ ይህም ሌላ ህመም እንደሆነባት ተናግራለች፡፡

   ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል አመራሮቼ፣ አባላትና ደጋፊዎቼ እየታሰሩብኝ ነው አለ፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተሰማ፤ በአዲስ አበባ ከታሰሩት አመራሮች መካከል የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ሚኒሊክ ሆስፒታል የታመመ አባል ለመጠየቅ በሄዱበት ለእስር መዳረጋቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ከስራ አስፈፃሚዎች መካከል አቶ አበበ አካሉ፣ የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሪት ብሌን መስፍን፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት መርከቡ ሀይሌ፣ እያስቤድ ተስፋዬ፣ አቶ አወቀ ተዘራና የፓርቲው የቀድሞ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ አዲሱ ጌታነህ እንደሚገኙበት ገልፀው፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ከዋግህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ አቶ አበበ አየለና ሞገስ አበጀ የተባሉ አባላትም ታስረውብናል ብለዋል፡፡
ከአርሲ ዞን ደግሞ አቶ አበራ ታደሰ፣ አቶ ጀዋሮ ገልገሎ የታሰሩ ሲሆን ከደብረብርሃን አቶ አስራት እሸቴ፣ ከባህርዳርና አካባቢው አቶ በላይነህና አቶ ማሩ መታሰራቸውን ገልፀዋል፡፡
“አቶ በላይነህና አቶ ማሩ የተባሉት አባሎቻችን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት ቢታሰሩም እስካሁን ፍ/ቤት የመቅረብ መብታቸውን ተነፍገዋል” ያሉት አቶ ሰለሞን ሌሎቹ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ለእስር መዳረጋቸውንና እስካሁን ፍ/ቤት አለመቅረባቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡ ከአመራሮች፣ ከስራ አስፈፃሚዎችና አባላት በተጨማሪም የፓርቲው ደጋፊ የሆኑ፣ አርቲስቶች፣ መፅሀፍ አሳታሚዎችና የህትመት ውጤቶችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች ለእስር ተዳርገውብናል ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ለምሳሌ ደጋፊያችን አትሌት ግርማ ገርባባ ስፔን ለውድድር ሄዶ እንደተመለሰ ባልታወቀ ምክንያት ታስሯል ብለዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት አፈሳው፣ ወከባውና እንግልቱ በፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል” ያሉት ኃላፊው በምን ምክንያት እንደታሰሩ ለማወቅ የሚጠይቅም መልስ የሚሰጥም አካል የለም›› ሲሉ አማርረዋል፡፡ “አንድ ሰው ፍ/ቤት ቀርቦ የክስ ቻርጅ ሲደርሰው ቢያንስ ያጠፋው ይታወቃል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ‹‹አመራሮቻችን ከሶስት ሳምንት በላይ ቢታሰሩም ፍ/ቤት አለመቅረባቸው የህገ - መንግስቱን አንቀፅ 29 በእጅጉ ይቃረናል ብለዋል፡፡
‹‹መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ የሚያደርሰውን የመብት ጥሰት እንዲያቆምና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የህገ መንግስቱን መርሆዎች እንዲከተል እንጠይቃለን›› ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በያሉበት ቦታ ፍ/ቤት ቀርበው የተከሰሱበትን ምክንያት እንዲያውቁ፣ መብታቸው እንዲከበር፣ እንዲፈቱና ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡ 

በሩሲያ የሚነገር አንድ ተረት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የውሃ ክፍል ኃላፊ ሁለት የበታች ሰራተኞቻቸውን ይጠሩና፤
“ያስጠራኋችሁ አንድ አጣዳፊ ሥራ ስላለ ነው” ይላሉ፡፡
“ምንድን ነው ጌታዬ? እኛ ሥራውን ለመፈፀም ዝግጁ ነን” ይላሉ ሠራተኞቹ፡፡
አለቅየውም፤
“በጣም ጥሩ፡፡ ነገ ሹፌራችን ወደሚያሳያችሁ ቦታ ትሄዱና አንዳችሁ ቦዩን ትቆፍራላችሁ፡፡ አንዳችሁ ደግሞ ቧምቧ ትቀብራላችሁ፡፡ ሥራው ረዥም ርቀት ላይ የሚሰራ ስለሆነ ማለዳ ወፍ ሲንጫጫ ሄዳችሁ ነው ስራውን መጀመር ያለባችሁ” ሲሉ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡”
ሰራተኞቹ፤
“በሚገባ እንፈፅማለን” ብለው ወደየክፍላቸው ይሄዳሉ፡፡
በነጋታው ጠዋት ግን ቧምቧ እንዲቀብር የታዘዘው ሰራተኛ፤ ሹፌር ከቤት ሊወስደው ሲሄድ፣
“ዛሬ አሞኛል ሥራውን ልሰራ አልችልም” ብሎ ከነቧንቧው ቤቱ ይቀራል፡፡
ቦዩን እንዲቆፍር የታዘዘው ሠራተኛ ግን ወደተባለው ቦታ ሄዶ መቆፈር ይጀምራል። ሆኖም አቆፋፈሩ ያስገርማል፡፡ የተወሰነ ርቀት ይቆፍርና መልሶ አፈሩን እየመለሰ ይደፍነዋል፡፡ እንዲህ እያደረገ ቀኑን ሙሉ ሲቆፍርና ሲደፍን ውሎ የተባለውን ርቀት ጨርሶ ወደመሥሪያ ቤቱ ይመለሳል፡፡
አለቃው፤
“እህስ ጨረሳችሁ ወይ?” ሲሉት
“አዎ ጌታዬ፤ እኔ የተባለውን ርቀት ቆፍሬ ጨርሼ መጥቻለሁ”
“ባልደረባህስ የታለ?”
“እሱ ቧምቧውን እንደያዘ አሞኛል ብሎ ቤቱ ቀርቷል፡፡ እኔ ግን የታዘዝኩትን ቦይ ቆፍሬ መልሼ አፈሩን በሚገባ ደፍኜ ኃላፊነቴን ተወጥቼ ተመልሻለሁ ጌታዬ” አለ፡፡
*   *   *
የምንሰራው ሥራ ዓላማ ሳንገነዘብ ኃላፊነት መወጣትም ሆነ ከተጠያቂነት እድናለሁ ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” የሚባለው ተረት ዓይነት ነው፡፡ አንድም በሥራ መለገም፣ አንድም ዓላማ ቢስ ሥራ መስራት፤ ከተጠያቂነት አያድኑም፡፡ ባለቧንቧው ይታመም አይታመም ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ቧንቧውን ቢያንስ ለሥራ ባልደረባው አለመስጠቱ ግን ፍፁም ከተጠያቂነት አያድነውም፡፡ ቆፋሪው ቧንቧውን ይዞ ለመሄድ አልሞከረም፡፡ በመቆፈር ያፈሰሰው ላብ ቢያሳዝንም መልሶ በመድፈኑ ቢያንስ ለጅልነቱ ዋጋ ይከፍላል፡፡
ዋናው ነገር ግን ሥራው ሳይሠራ ቀርቷል፡፡ በዚህ ዓይነት የባከነ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ቧንቧው ሊሰጥ ይችል የነበረው አገልግሎት፤ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በሀገራችን ሁሌ እንደ ችግር ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ ብክነት ነው፡፡
አንድ ብክነት አለ ሲባል በተያያዥነት የሚነሱ እንደ ሠንሠለት የተሳሰሩ አያሌ ተመላካች ነገሮች እንደሚኖሩ አንዘንጋ፡፡ በቡድን የሚሠሩ ሥራዎች አንድ ሰው ሲጎድል ወይም ኃላፊነቱን ሲያጎል ቀጥ ይላሉ፡፡ የሥራ ፍሰት ምሉዕነት (System flow) ይዛባል፡፡ አንደኛው የሥራ ክፍል ኃላፊነቱን ሲወጣ ሌላኛው ክፍል ሥራውን ካልሠራ፣ የመሥሪያ ቤቱ ድፍን የሥራ ሂደት ሽባ እስከመሆን ሊደርስ ይችላል። የአመራር ደካማነት፣ የቁጥጥር ማነስ፣ የአልምጥ ሠራተኞች መብዛት፣ ስህተትን አንዱ ባንዱ ላይ መላከክ (Blame-Shifting)፣ የራሴን ከተወጣሁ ምን ቸገረኝ ማለት፤ ነገርን ከሥሩ አለማየት፣ ችግሮችን በወቅቱ አለመፍታት፣ ወገናዊነትን አለማስወገድ፣ ተቋማዊ ጥንካሬን ማጣት ወዘተ የተለፋበት ሥራ፣ የተደከመው ድካም ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጋል፡፡ ይህ በፈንታው የሀገርን ሀብት ለብክነት ይዳርጋል፡፡ ዕድገትን ያቀጭጫል፡፡ ህዝብ ትክክለኛ አገልግሎት እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡ በዚህ ላይ ነጋ ጠባ የምንወተወተው የናጠጠው ሙስና ሲጨመር፣ ምን ያህል የኢኮኖሚ ዝቅጠት ውስጥ እንደሚከተን ማስላት ነው፡፡
ለመልካም ሠራተኞች ምን ያህል የሞራል ድቀት እንደሚያመጣ ማስተዋል ነው። ልብ መባል ያለበት ድክመቶችና ጥፋቶች የበታች ሠራተኞች ላይ ብቻ የሚታዩ ክስተቶች አድርጎ መቁጠር ስህተት መሆኑ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የበላይ ኃላፊዎችም፣ በማን አለብኝነትም ሆነ በዕውቀትና ልምድ ማነስ ጥፋት ይፈፅማሉ። በሥልጣን ይባልጋሉ፡፡ ሙስና ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ሆነ ብለው ሥራ የሚያጓትቱና ተገልጋይን ህዝብ የሚያጉላሉም ይኖራሉ፡፡ መፈተሽ አለባቸው፡፡ ‹‹ወዳጄ፤ ለመሆኑ ብሣና ይሸብታል ወይ?›› ብሎ ቢጠይቀው፤ ‹‹ለዛፍ ሁሉ ያስተማረ ማን ሆነና ነው?›› አለው፤ የሚለው ተረት የሚጠቁመን ይሄንኑ ነው!


 በመካከለኛው የጣሊያን አካባቢ የምትገኘው ካልዳሪ ዲ ኦርቶና የተባለቺው ከተማ፣ እግር የጣለው ሰው ሁሉ እንዳሻው እየጠለቀ ሌት ተቀን በነጻ የሚጠጣው የወይን ፏፏቴ ሰርታ ከሰሞኑ በአገልግሎት ላይ ማዋሏ ተነግሯል፡፡
ወደ አንድ ታዋቂ የጣሊያን የእምነት መዳረሻ በሚወስድ መንገድ ላይ ወደምትገኘው ወደዚህች ከተማ ጎራ ያለ ሰው፤ባደረሰው ሰዓት ሁሉ አምስት ሳንቲም ሳያወጣ ከጣፋጩ ቀይ ወይን እየጠለቀ መጠጣት ይችላል ብሏል፤ ሜትሮ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ፡፡ ከተማዋ ወይን በነጻ ማቅረብ የጀመረቺው አንድ የጣሊያን የወይን እርሻ ኩባንያና መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ የእምነት መዳረሻውን አካባቢ ጠብቆ ለማቆየት በጀመሩት የጋራ ፕሮጀክት አማካይነት ነው ተብሏል፡፡
አካባቢው በየአመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የእምነት መንገደኞች የሚያልፉበት ነው ያለው ዘገባው፤ ጣሊያን ከዚህ ቀደምም እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ አካባቢ ተመሳሳይ የነጻ የወይን ፏፏቴ በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጋ እንደነበር አስታውሷል።

 “ኦባማ የፈየደው ነገር የለም፤ ድምጼን የምሰጠው ለትራምፕ ነው”

       የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወንድም የሆኑት ማሊክ ኦባማ፤ የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ዳግም ታላቅ አገር ሊያደርጋት ይችላል ማለታቸውን ኒውዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡
የአሜሪካና የኬንያ ዜግነት ያላቸው ማሊክ ኦባማ፤ከወራት በፊትም፣ “ወንድሜ ባራክ ኦባማ ለአሜሪካውያንም ሆነ ለኬንያውያን ቤተሰቦቻችን ፋይዳ ያለው ነገር አልሰራም፤ ስለዚህም በቀጣዩ ምርጫ ድምጼን የምሰጠው ለዶናልድ ትራምፕ ነው” ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ከተፎካካሪያቸው ሄላሪ ክሊንተን ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ዙር የምርጫ ክርክር ላይ እንዲገኙላቸው ከጋበዟቸው የክብር እንግዶቻቸው አንዱ እኒሁ የኦባማ ወንድም ማሊክ ኦባማ እንደነበሩ ታውቋል፡፡

 ሰሜን ኮርያ፤ የአሜሪካ መንግስት የኒውክሌር ሃይል ደህንነቷን አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ የሚያደርግ ከሆነ አስቀድማ በመከላከል ላይ ያተኮረ የኒውክሌር ጥቃት ልትፈጽም እንደምትልች አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ማስጠንቀቃቸውን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ አገራችንንና መሪያችንን ለማጥቃት ያለሙ የኒውክሌር መሳሪያዎችን በድንበራችን አካባቢ አደራጅታለች፤ የምትፈጽምብንን ጥቃት ለመመከት ወደ ኋላ አንልም ብለዋል፤ሊ ዮንግ ፒል የተባሉት የሰሜን ኮርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን፡፡
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደረጉባት ተጨማሪ ማዕቀቦችም ሆኑ የአሜሪካ ጫና ሰሜን ኮርያን የጦር መሳሪያ አቅሟን ከማጠናከር በፍጹም አይገታትም ሲሉም አስታውቀዋል፤ ባለስልጣኑ። ሰሜን ኮርያ በዚህ አመት ብቻ ለአምስት ጊዜያት ያህል የኒውክሌር ሙከራ ማድረጓን ያስታወሰው ዘገባው፤አገሪቱ በቀጣይም ሌሎች ሙከራዎችን ልታደርግ እንደምትችል ባለስልጣኑ ማስታወቃቸውንም ገልጧል፡፡ አለማቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ተቋም፤ ሰሜን ኮርያ እያስፋፋችው ያለውን የኒውክሌር ፕሮግራም እጅግ አሳሳቢ ሲል እንደተቸውም አስታውሷል፡፡

 - ከ370 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል

      በአፍጋኒስታን በተደረገው ጦርነት ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ2 ሺህ 600 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ5 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑትም የመቁስል አደጋ እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍጋኒስታን ድጋፍ ልኡክ ረቡዕ ዕለት ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በጦርነቶች ሳቢያ 639 የአገሪቱ ህጻናት ለሞት ተዳርገዋል፤ 1 ሺህ 822 ያህሉም የከፋ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ድርጅቱ ከ61 በመቶ በላይ ለሚሆነው ሰብዓዊ ጥፋት ተጠያቂ ያደረገው የመንግስቱን ተፋላሚ ቡድን ታሊባንን ሲሆን፣ ሁለቱ የአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች በዜጎች ላይ ጥፋት ከሚያስከትሉ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ባለፉት ሰባት አመታት በአገሪቱ በተደረጉ ጦርነቶች ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ45 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜናም ባለፉት 9 ወራት ብቻ በጎረቤት ፓኪስታን የስደት ኑሮን ሲገፉ የነበሩ ከ370 ሺህ በላይ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን በመጠቆም፣ በፓኪስታን ከ2.5 ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች እንደሚገኙም ተመድ ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት ብቻ 52 ሺህ የሚሆኑ አፍጋኒስታናውያን ድንበር አቋርጠው ወደ አገራቸው መግባታቸውን ዘገባው ጠቅሶ፣ በሳምንት ይሄን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኛ ወደ አገሩ ሲገባ ባለፉት 7 አመታት ይሄ የመጀመሪያው ነው ብሏል፡፡

ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የአገሪቱ ዜጎች ለመሆን አመልክተዋል
      ተቀማጭነቱ በቪየና የሆነው ኤሮስፔስ ኢንተርናሽናል ሪሰርች ሴንተር የጀመረውን አዲስ ፕሮጀክት የሚያስፈጽመው የጠፈር ተመራማሪዎች ቡድን፤ በጠፈር ላይ አስጋሪዳ የተባለች አዲስ አገር ሊመሰርት ማቀዱ ተገለጸ፡፡
የእቅዱ ባለቤቶች የሆኑት ሳይንቲስቶች፤አገሪቱ የሆነ ጊዜ ላይ በተመድ እውቅና እንደሚሰጣት ተስፋ አለን ቢሉም፣ አንዳንድ ባለሙያዎች ግን በጠፈር ላይ የሚቀርብን የአንዲት አገር ብሄራዊ ሉአላዊነት ጥያቄ የሚከለክሉ አለማቀፍ ህጎችን ጠቅሰው፣የእቅዱን ተፈጻሚነት ተጠራጥረውታል፡፡
የአገሪቱ ዜጎች መሆን የሚፈልጉ ሰዎች በድረ-ገጽ አማካይነት ለፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት ማመልከቻ በማቅረብ መስፈርቱን ካሟሉ፣ ዜግነትና ፓስፖርት ይሰጣቸዋል ብለዋል፤ የፕሮጀክቱ አባልና በአውሮፓ የጠፈር ምርምር ማዕከል ለ15 አመታት ያገለገሉት ሌና ዲ ዋይን፡፡ ሳይንቲስቶቹ በጠፈር ላይ ሊመሰርቷት ላሰቧትና አዲስ የንግድና የሳይንስ ምርምር አማራጭ ትሆናለች ለሚሏት አገር አስጋሪዳ የሚል ስም ያወጡላት ሲሆን በአንድ አፈታሪክ ውስጥ በሰማይ ላይ ትገኛለች ተብሎ ከሚነገርላት አስጋሪዳ የተባለች አገር የተወሰደ ነው ተብሏል፡፡
ለአዲሲቱ አገር ብሄራዊ መዝሙርና ሰንደቅ አላማ ለማውጣት ውድድር እየተደረገ ነው ያለው ዘገባው፤ እስካሁን ድረስ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች በድረ-ገጽ አማካይነት የአገሪቱ ዜጋ መሆን እንፈልጋለን በማለት ለፕሮጀክቱ ባለቤቶች ማመልከታቸውንም አስታውቋል፡፡

 በዶ/ር ጃራ ሰማ የተፃፈውና ‹‹ከሱስ የነፃ ትውልድ የመፍጠር ጥበብ›› የተሰኘ መፅሀፍ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ  በመወዘክር  አዳራሽ ይመረቃል። መፅሃፉ በኦሮምኛና በአማርኛ የተሰናዳ ሲሆን በዋናት ለሱሰኝነት ሊዳርጉ ስለሚችሉ ዋና ዋና ምክንያቶች፣ ሱስንና ሱሰኝነትን እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ ከሱሰኝነት መላቀቅ ስለሚቻልባቸው መንገዶች፣ ሱስ ሊያስይዙ ስለሚችሉ ነገነሮችና በአጠቃላይ ከሱሰኝነት ነፃ ሆኖ የሚኖርበትን መንገድ የሚያመላክትና የሚተነትን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በአማርኛ የተዘጋጀው መፅሀፍ፤ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ156 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ100 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡