Administrator

Administrator

 

 

 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመብራት ችግር እየባሰበት መሆኑን መናገር ለቀባሪው አረዱት ይሆናል፡፡ በቀን ከሁለት እስከ አራት ጊዜ የሚቆራረጥበት ወቅት አለ፡፡ መብራት አለ ብለው እንጀራ ለመጋገር ሲዘጋጁ እልም ይላል፡፡ ይመጣል ብለው ሲጠባበቁ በዚያው ቀልጦ የሚያድርበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢ ሁለትና ሦስት ቀን ከዚያም ሲብስ ሳምንት፣ አስር ቀንና ከዚያም በላይ ጠፍቶ ሲቀር ነዋሪዎች “የመብራት ያለህ” እያሉ በየሚዲያው ይጮሃሉ፡፡ ይህ ችግር በዓመት አንዴ የሚከበሩ በዓላትንም አይፈራም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ለዘመን መለወጫ እንጀራ ለመጋገር አብሲት ተጥሎ መብራት እንደጠፋ በማደሩ በዓሉን በግዢ እንጀራ ማክበራችን ትዝ ይለኛል፡፡

መንግሥትና መብራት ኃይል ችግሩ ሲነገራቸው አንዳንድ ጊዜ “ዕድገት የፈጠረው ችግር ነው፤” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የኃይል ማነስ አይደለም፣ የማሰራጫ መስመሮች እርጅና ነው፣ በዚህ አካባቢ ያለው ትራንስፎርመር ፈንድቶ ነው” ይላሉ፡፡ በየአካባቢያችንም ብዙ ጊዜ ትራንስፎርመር ሲፈነዳ ሰምተናል፣ አይተናል፡፡

ክቡር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመገናኛና ኮሙኒኬሽን ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚ/ር፣ ባለፈው እሁድ የትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር፤ ከዓመት በኋላ ትራንስፎርመር በየመንገዱ እንደ ማስቲካ እንደማይፈነዳ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን ይህንን ያሉት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ በፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የትራስፎርመር ፋብሪካ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያላቸው ትራንስፎርመሮች እያመረተ በመላ አገሪቱ ስለሚያሰራጭ ነው፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ የአገሪቱን የትራንስፎርመር ፍላጐት አሟልተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ የገለጹት የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አሰፋ ዮሐንስ፣ በመላው ዓለም ቻይናም ሆነች አሜሪካ የሚጠቀሙት ትራንስፎርመር ፋብሪካቸው ከሚያመርተው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር በ350 ሚሊዮን ብር የተሠራው ፋብሪካ ለኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ፣ ማሰራጫና ለቁጠባ የሚያገለግሉ ልዩ ትራንስፎርመሮችን ያመርታል። በዓመት 10ሺህ ትራንስፎርመሮች ያመርታል፣ ይተክላል፡፡ የጥራት ደረጃው ዓለም አቀፍ መሆኑን ማን እንዳረጋገጠላቸው የተጠየቁት ሻለቃ አሰፋ፣ የጥራት ደረጃ የሚለካው በምርት ወቅት በሚጠቀሙት የግብአት ጥራት፣ በሚያልፍበት የምርት ሂደትና በዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ተፈትሾ (ቴስት) ተደርጐ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የምርታቸው የብቃት ደረጃ 99.7 መሆኑን፣ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ጥያቄ ስላቀረቡ ከዓመት በኋላ ለውጭ ገበያ እንደሚልኩ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው 1‚200 ሠራተኞች ሲኖሩት አብዛኞቹ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተመረቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ በፋብሪካው የኢንሱሌሽን፣ የዋይንዲንግ (ሽቦ መጠምጠም)፣ የአሴምቢሊንግ (መገጣጠሚያ) የኦይሊንግና ቴስቲንግ ወርክሾፕ የሚሠሩ አሉ፡፡

በእያንዳንዱ ወርክሾፕ የተመደቡት ወጣቶች ሁለት ሁለት ሆነው ነው የሚሠሩት፡፡ ሊዲያ ተስፋማርያምና ኢዮብ ዳና በኢንሱሌሽን ወርክሾፕ ሲሠሩ ነው ያገኀኋቸው፡፡ ሊዲያ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቃለች። ኢዮብ 23 ዓመቱ ሲሆን ከቲቪቲ ኮሌጅ የተመረቀ ቴክኒሻን ነው፡፡ የወጣቶቹ ሥራ በትራንስፎርመሩ የሚጠቀለሉት ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ሽቦዎች እንዳይገናኙ በየመስመሩ ልዩ ዓይነት ኦርጋኒክ ወረቀት ማስገባት ሲሆን  ወረቀቱ ሌላም አገልግሎት አለው፡፡ በትራንስፎርመሩ የሚጨመረውን ዘይት ይመጣል፡፡

በኮኔክሽን ወርክሾፕ ሲሠሩ ያገኘኋቸው መቅደስና ታደሰ ጂጌ ኤሌክትሪሻኖች ናቸው፡፡ የ24 ዓመቷ መቅደስ ከወሊሶ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ነው የጨረሰችው፡፡ ታደሰም የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተመርቋል፡፡ የወጣቶቹ ሥራ ከኃይል ማሰራጫ የሚመጣውን ኃይል ተቀብሎ ወደ ትራንስፎርመሩ የሚያደርሰውን ሽቦ መትከል ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በሁሉም ወርክሾፖች ወጣቶች ተመድበው እየሠሩ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

በአዲስ አበባ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ማርች 23 እና 24/ በምህጻረ FIGO የተሰኘው አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ8ኛው አህጉራዊ ስብሰባው ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥን በመከላከል ረገድ ምን ገጽታ አለ ወደፊትስ ምን መደረግ ይገባዋል የሚል ውይይት በአዲስ አበባ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ የደቡብ አፍሪካውንና የኡጋንዳውን ተወካይ በአገራቸው ስላለው ሁኔታ ሀሳብ እንዲሰጡ አነጋግረናቸዋል፡፡ በዚሁ አህጉራዊ ስብሰባ ላይ ከተነሱ ነጥቦች የምናስነብባችሁ እውነታ በዚህ እትም ተካቶአል፡፡ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥ በተለይም በአፍሪካ አነጋጋሪነቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን ሀገራቱ እንደ አመቺነቱ የየራሳቸውን የአሰራር ደንብ ቢቀርጹም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ጉዳት ሲከሰት መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ይህንን የሚመሰክሩት ከየሀገራቱ የመጡ ባለሙያዎች ሲሆኑ የኡጋንዳው ተወካይ የሚከተለውን ብለዋል፡፡“...ዶክተር ቺክ ጎምቸልስ እባላለሁ፡፡ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና እስፔሸሊስት እንዲሁም በኡጋንዳ የፅንስ እና የማህፀን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ነኝ፡፡ ፅንስ ማቋረጥ በኡጋንዳ በልማድ ሲሰራ የቆየ እጅግ ጎጂ ነገር ነው፡፡ በማህፀን ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን በመጨመር እንዲሁም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመውሰድ ጭምር የተፀነሰውን የመግደል ስራ ነው የሚሰሩት፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ፅንስን ማቋረጥ የተለመደ ነገር ቢሆንም አብዛኛው ድርጊት ግን ጎጂ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ በኡጋንዳ ሴቶች በተለያየ መንገድ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ፅንስን ማቋረጣቸው በህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሲያስከትል ቆይቷል፡፡ በየአመቱም 300,000/ ያህል ጥንቃቄ የጎደለው ፅንስን ማቋረጥ የሚኖር ሲሆን ይህም  በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ነው፡፡ፅንስን ማቋረጥን በሚመለከት በኡጋንዳ በህግ የተደነገገ አሰራር አለው፡፡ ለዚያም መነሻ የሆነው አብዛኛው ፅንስን ማቋረጥ የሚሰራው ንፅህናውን ባልጠበቀ እና ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች ፅንስን በማቋረጡ ሂደት በቂ ግንዛቤ አላቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ ጽንስን ማቋረጥ ግማሽ ያህሉ እውቀት ባላቸው ሰዎች የሚሰራ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ግን በሴቶቹ በራሳቸው እንዲሁም በተለያዩ እውቀቱ በሌላቸው የቤተሰብ ወይንም የህብረተሰብ አባላት ነው፡፡ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ፅንሱን በሚያቋርጡበት ግዜ ሴቶቹ ለተለያየ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ ደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሽን፣ የማህፀን መቧጠጥ፣ መቁሰል የመሳሰሉት ሁሉ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል ናቸው፡፡ በኡጋንዳ በቀን እስከ ስድስት ሴቶች ፅንስን በማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል። በአመትም እስከ 4,200/ ሴቶች ጥንቃቄ በጎደለው ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ አሁን ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡

በእርግጥ ልንደርስ ካሰብንበት ቦታ ለመድረስ ገና ይቀረናል ነገር ግን የሴቶቹን ህይወት ለማዳን በምናደርገው እንቅስቃሴ የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገልን ሲሆን ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል፡፡ በህጉም በኩል እንደገና የሚታዩ  ሚሻሻሉ ነገሮች ስለአሉ ሁኔታው  እየተሸሻለ ነው፡፡ ስለዚህም በወደፊቱ አሰራር ጉዳቱ እየቀነሰ እንደሚመጣ እሙን ነው፡፡

የምጨምረው የግል አስተያየቴን ነው በማለት ዶክተር ቺክ ጎምቸልስ የሚከተለውን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

“”....ያልተፈለገ እርግዝና አንድ ወንድና አንንዲት ሴት በፍቅር ተግባብተው የሚፈጥሩት ሲሆን በኋላ ግን የሴቷ ችግር ይሆናል፡፡ ከስነልቦና ጉዳቱ ባሻገር ወደ አካል ብሎም ህይወት እስከ ማጣት ድረስ ጉዳት የሚደርሰው በሴቷ ላይ ነው፡፡ ይህንን እንደ አንድ ትልቅ የሀገር ጉዳይ መመልከት ይገባናል፡፡ ሴቶች በወሲብ ግንኙት ወቅት እንዲወስኑ፣ መቼና ምን ያህል ልጆች እንደሚያስፈልግ፣ እርግዝናው እንደማያስፈልግ ሲታወቅ ምን ማድረግ እደሚገባ ምርጫ እንዲኖራቸው እና ከሚደርስባቸው ጉዳት እራሰቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡” ብለዋል፡፡

በማስከተል የጋበዝናቸው እንግዳ ከደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡  

“...ስሜ ኤኪ ሙስታንጋ ይባላል፡፡ የመጣሁት ከደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፅንስ ማቋረጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የዛሬ አፍሪካ ዩኒየን ቼር ፐርሰን የሆኑት ሰው ሴቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ እንዲያደርጉ የተቻላቸውን ሁሉ አደርገዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህብረተሰቡም መብቱን አውቆ በጤና ተቋማት እንዲገለገል ባለሙያዎችም የእናቶችን መብት በማክበር እና ሙያውን በትክክል በመተግበር የሚችሉበትን አቅም በስልጠና እና በመሳሰሉት መንገዶች እየገነባን ነው፡፡ ስለሆነም ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ በሚከናወን ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ህይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ አሰራሩን በህግ የተደገፈ ለማድረግ ሕግ የወጣው በ1996 ዓም/ ሲሆን ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው ግን በ1997 ዓም/ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሴቶቹን በህክምና ለመርዳት የተስማሙት ሶስት ዶክተሮች ብቻ ሲሆኑ ህጉ ከወጣ በኋላ እና አሰራሩ ከተሸሻለ በኋላ ግን በርካታ ባለሙያዎች ህይወት እያዳኑ ነው፡፡

ባጠቃላይም በደቡብ አፍሪካ ከሚሞቱት እናቶች 30% የሚሆኑት ምክንያታቸው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ነበር፡፡ አሁን ግን በዚሁ ምክንያት የሚሞቱት ሴቶች 8% ብቻ ናቸው፡፡ 

በስተመጨረሻም ኤኪ ሙስታንጋ የተናገሩት...

“...በአፍሪካ ያለን ሰዎች ሁሉ ለሴቶች ክብር እና ከፍ ያለ ግምት ልንሰጣቸው ይገባናል፡፡ እነዚህ ሴቶች ትውልድን ለመተካት የሚችል ተፈጥሮ ያላቸው ብርቅዬዎች ናቸው፡፡ የሚጠቅማቸውን እና የሚጎዳቸውን ለይተው ስለሚያውቁ ሌሎች ሊወስኑላቸው አይገባቸውም፡፡ ስለዚህ እንስማቸው፡፡ ምርጫቸውንም እንጠብቅላቸው ሊያደርጉ የሚፈልጉት ነገር ካለም እንደግፋቸው፡፡” ብለዋል፡፡  

ጽንስን በመድሀኒት ማቋረጥ ጠቀሜታው በተለያየ መንገድ ሊመዘን ይችላል የሚለን  ኮንሰፕት የተሰኘው በ1989 ዓ/ም የተቋቋመው በተለይም የመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ  ባላቸው አገሮች የስነተዋልዶ ጤና በጥሩ ሁኔታ እንዲጠበቅ ለማድረግ ከየሀገራቱ ጋር የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡

በመድሀኒት አማካኝነት ጽንስን በተገቢው መንገድ ማቋረጥ በተለይም በታዳጊ ሀገሮች ያለው ጠቀሜታ የጎላ ቢሆንም ይላል ኮንሰፕት አንዳንድ አመቺ ያልሆኑ ነገሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌም የመድሀኒቶች ውድነት ከሚጠቀሱ መካከል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጥራትና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላይሆን ይችላል እንደ ኮንሰፕት እማኝነት፡፡ ከአምራቾች አኳያ ጉዳዩን ስንመለከተው ይላሉ መድሀኒቱን ለማዘዝ የፍላጉት መቀዝቀዝ ፈቃደኝነት ማጣትና በመድሀኒቱ ተጠቅሞ ተገቢውን አገልግሎት የማዳረስ ችሎታ በታዳጊ ሀገራቱ እየታየ አይደለም፡፡

በመድሀኒት አማካኝነት የሚደረግ ጽንስን ማቋረጥ ከ96-99% ውጤታማ ነው። ምናልባትም ውጤት አልባ ነው ቢባል 5% ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም ጎጂ ጎኑ መጠነኛ እና በፍጥነት ያልተፈለገውን ጽንስ ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ህ/ሰቡ በቂ ግንዛቤው እንዲኖረው ማድረግና አገልግሎቱን ምቹ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት ድርጅቶች ፓስ ፋይንደር አንዱ ሲሆን ልምዱን እንዳካፈለው ከሆነ ከ55 አመት በላይ ጽንስን በማቋረጥ ረገድ በሁለቱም  ማለትም ሕግ ባወጡም ባላወጡም ሀገራት ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፡፡

እንደፓስ ፋይንደር እማኝነት ጽንስን ማቋረጥ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው በቀጥታ ከእናቶች ሞታ ጋር ስለተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ጋር በተገናኛ መሰረታዊ መብታ ቸው ሊከበር ስለሚገባውም ጭምር ነው።

በአለማችን ወደ 220/ሁለት መቶ ሀያ ሚሊዮን ሴቶች ዘመናዊ የሆነውን ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አያገኙም፡፡ የእርግዝና መከላከያውን ቢያገኙ ኖሮ፡-

ያልተፈለገ እርግዝና ከ60% በላይ ይቀንሳል

የጨቅላ ሕጻናት ሞት በ44% ይቀንሳል

150,000 ያህል የእናቶች ሞት ይቀንሳል

600,000 ህጻናት እናቶቻቸውን በሞት አይነጠቁም፡፡ ይህ መረጃ ከ Women Care Global (WCG) የተገኝ ነው፡፡

ድርጅቱ እንደገለጸውም፡-

“...ስኬት የሚለካው በሴቶች ሕይወት መሻሻል እንጂ በገንዘብ ትርፍ አይደለም...”

በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት በአማካይ 40/ ሚሊዮን የሚሆን ጽንስን የማቋረጥ ተግባር የሚፈጸም ሲሆን ከዚህም ከግማሽ በላይ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም፡፡

ወደ 90% የሚሆነው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈጸመው በታዳጊ ሀገራት ነው፡፡

ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት በዋና ምክንያትነት ከሚጠቀሱት ከ5ቱ ገዳዮች አንዱ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

              “መንግስት፤ እኔ ነኝ የአገሪቱ ደራሲ ይላል”

    ይኼንን ያለው አልበርት ካሙ ነው፡፡ አንድነት ግን በተጨባጩ አለም ሊገኝ የሚችል ነገር ሳይሆን ሲቀር፣ አርቲስቱ ተጨባጩን እውነታ በማፈራረስ ከፍርስራሹ ውስጥ የራሱን የምናባዊ አለም አንድነት እንዳለው አስመስሎ ያቀርበዋል፡፡ ይፈጥረዋል፡፡

“አንድነት በተለዋጭ አለም ይኸው እንዴት ውብ እንደሆነ” ብሎ ያቀርባል፡፡ እናም የፈጠረው አንድነት የተሳካ ከሆነ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ የፈለገ ምናባዊ ቢሆንም ግን ፈጠራው  ቀድሞ ከነበረው የእውነታ አለም የራቀ አይሆንም፡፡ ከራቀ የሚረዳውን አያገኝም፡፡ ካላገኘ፤ አንድነቱ የቱ ጋ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ግን ተሳካለት እንበል፡፡ ማለትም የፈጠረው ምናባዊ ጥበብ አንድነትን በሰው እና በፈጣሪ መሀል ወይንም በሰው እና በማንነቱ … መሀል ያሉትን ቲዎሪያዊ ጥያቄዎች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደፈነ፡፡ እና ምን ይከተል? ሲፈለግ የነበረው የፈጠራ ጥግ ተደረሰ ተብሎ ፍለጋው ይቆማል?

አይቆምም፡፡ የፈለገ አይነት ስኬታማ ድርሰት ቢዋቀር የሰው ልጅ የአንድነት ፍላጐት አይረካም። ደራሲው ራሱ እንኳን የመጨረሻው የውበት (አንድነት) ጥግን ነክቻለሁ ካለ በኋላ የራሱን መጨረሻ ለመብለጥ ሌላ ድርሰት ይጽፋል፡፡ ህይወቱ እስኪያከትም ድረስ ውድድሩን አይገታም። … የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ነው፡፡ ወይንም ከራስ ወዳድነቱ ጋር፡፡

ምናልባት ጥበበኝነት ከራስ ወዳድነትም ጋር የሚጣመርበት ስፍራ ሊታየን የሚችለው እዚህ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ማርሴል ፕሮስት፤ “In remembrance of the times past” በተባለው ዐብይ እና ትልቅ ስራው አንድነትን የፈለገበት መንገድ ወደራሱ የትዝታ አለም በመመነን ነው፡፡ ተጨባጩን አለም አፈራርሶ የእሱን ጠባብ የውስጥ ግዛት አለምን አሳክሎ በማብዛት ታላቅ ፈጠራን ሰራ፡፡ ከሰው ልጅ ጋር ራሱን “አንድ” ለማረግ የመረጠው መንገድ… የሰው ልጅን ሁሉ ወደ እሱ አተያይ በመቀየር ነው፡፡

ማርሴል ፕሮስት፤ ያደረገውን ያላደረገ ፈጣሪ በመሰረቱ የለም፡፡ የአንድነት ብቸኛ ፍቺ ነው የምንለው የሙሉኤ ኩሉው እውነታ ደራሲ (እግዚአብሔር) እንኳን… ሁሉንም ነገር የከወነው ከራሱ አልፋ እና ኦሜጋዊ አተያዩ አንፃር አይደል? የአንድነት ፍላጐት ከራስ ፍላጐት አንፃር እስከሆነ ድረስ ወደ ጠቅላይ ስምምነት የሚያደርስ ፈጠራ ሊኖር አይችልም፡፡

በዚህ ምክንያት የውበት ፍቅር፣ የእውነት ፍቅር ወይም የአንድነት ፍቅር ከራስ ወዳድነት ፍቅር ጋር ያልተከለሰበት ውበት ተሰርቶ  አያውቅም፡፡

ለምሳሌ ፍቅር ሁሉ አንድነት ነው፡፡ ወንድ እና ሴት አንድ ለመሆን ወደ ፍቅር ይገባሉ፡፡ ግን አንድነታቸው ተዋረድ አለው፡፡ በተለምዶ ወንዱ አንድ አድራጊው ሀይል ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ “የእኔ ነሽ … ባለቤትሽ ነኝ” ይላታል‘ኮ አፍ አውጥቶ። የፍቅራችን የአንድነት ደራሲ እኔ ነኝ ማለቱም ነው፡፡ ነገሩ ፍቅር ነው፣ ውበት ነው፤ ግን ውበቱ የተቀረፀበት አንፃር አለው፡፡

ማን ነበረ፤ “We are too small in mind and body to possess other people without pride or to be possessed without humiliation” ያለው እንደዚያ ነው ነገሩ፡፡

ነገሩ ደግሞ ሰው የሚፈጥራቸው ጥበባዊም ይሁን መንግስታዊ አንድነቶች ውስጥ ግዙፍ እውነት ሆኖ ይገኛል፡፡ “እኔ ነኝ የሀገሪቷ ደራሲ ይላል” መንግስት፡፡ ባልዬው፤ “እኔ ነኝ የቤተሰቡ እራስ” እንደሚለው፡፡

የመጽሐፍ ደራሲውም፤ “እኔ ነኝ የድሮውን እውነታ ፈታትቼ በአዲስ መልክ ፈጥሬ ያዋቀርኩት” ይላል፡፡ በራሱ ለመኩራት ሲል ፈጠራውን የሚከውነውን ያህል የአንድነት ፍላጐትም በተፈጥሮው አድሮ ውበትን ለመጨበጥ ያነሳሳዋል፡፡ ግን “እኔ አንድነቱን ካልፈጠርኩት ሳይፈጠር ይቅር! ወይንም ቢፈጠርም ተፈጠረ ሊባል አይችልም” የሚለው ምክኒያት ዋናው የተግባሩ የመነሻ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡

በአንድ ድርሰትም ሆነ በአንድ የመንግሥት አስተዳደር ጥንቅቅ ያለ የአንድነት ንድፍ ሊገኝ የማይችለውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ (ከመሰለኝ ደግሞ…!)

ህዝብና መንግስት መሀል ጭቆና የሚኖረው፣ መንግስት ራሱን እንደ ደራሲ ሲያይ ነው፡፡ መንግስትን የሚተካ ሌላ ደራሲ የሚነሳው ከበፊተኛው ድርሰት ራስ ወዳድነት ውስጥ ነው፡፡ ግን በዛው መጠን መዘንጋት የሌለበት አዲሱ ደራሲም አዲስ አንድነት ለማምጣት የሚጥረው ለህዝቡ ሲል ሳይሆን ከራሱ “Ego” (ፍላጎት) ተነስቶ ነው፡፡

ግን ማንም ደራሲ ቢመጣ፤ የቀደመውን ምናባዊ ድርሰት፣ በሌላ ምናባዊ አለም ቢለውጥ፣ ወይንም ተጨባጩን ቢሮክራሲ በሌላ አሻሻልኩ ቢል፣ ከራሱ እይታ አንፃር እስከሆነ ድረስ ጥቅሉ ውበት (አንድነት) አይጨበጥም፡፡

ባል ሚስቱ ጥላው ስትሄድ አልያም መንግስትን ህዝብ አልወድህም ሲለው…የፍቅሩ መቋረጥ ከሚቆረቁረው ይበልጥ ሚስት እሱን ትታው ሄዳ ሌላ ባል (ሌላ መንግስት) ማግኘቷ እንደማይቀር ማወቁ የስቃዩ እውነተኛ ምንጭ ነው፡፡

ብዙ የአንድነት አይነት አለ፡፡ ግን የራስ ወዳድነቱ አይነት አንድ ነው፡፡ “ሳዲስት” ከ “ማሶቺስት” ጋር አንድነት ይፈጥራሉ፡፡ ፍቅር ይመሰርታሉ፡፡ ህዝብን የሚሰድብ ደራሲን መጽሐፍ የሚገዛ፣ መሰደብ ከሚወድ ህዝብ … የገበያም ሆነ የመናበብ ትስስር ይፈጥራል፡፡ የፍቅር አይነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እንክብካቤ እና ጥሩ ህይወት በምትፈልግ ሚስት እና ፍላጐቷን በሚያሟላ ባል መሀል የሚፈጠር አንድነት አለ፡፡ ግን አንድነቱ በጥል እና ባለመስማማት ይፈታል፡፡ አለመስማማት ማለት ሁለቱም የአንድነት መስራች አካሎች ራሳቸውን ማስቀደማቸው ግልፅ ሲወጣባቸው፣ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሳያሳምን ሲቀር ነው፡፡

እስካሁን የተሰራው የሰው ልጅ የድርሰት መፅሐፍ ለምን አንድ ላይ ተደምሮ ትልቅ ውበት ማግኘት አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ከመጣ መልሱ፡- የማንም የራስ ወዳድነት ንድፍ ከሌላው ጋር ቢደመር ትልቅ ራስ ወዳድነት እንጂ ትልቅ ውበት ወይንም ፍቅር አይወጣም፤ የሚል ይመስለኛል፡፡

ትልቅ ራስ ወዳዶች ትልቅ ጥበብን ይፈጥራሉ። በጥበቡ የሚስማማላቸው፣ በእነሱ እይታ መነፅር አለምን ለማየት ህዝቡ ወይንም ተደራሲያቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ ሳይፈቅድ ሲቀር ሌላ ደራሲ የድሮውን አንድነት በራሱ አዲስ አተያይ ለውጦ እንዲያሳያቸው ይፈቅዳሉ፡፡ ሲፈቅዱ የወጣውን አውርደው የወረደውን አዲስ የአንድነት ደራሲ ያነግሳሉ፡፡

ትልቅ ራስ ወዳዶች ጥበብን ይፈጥራሉ፡፡ ራሳቸውን ከፈጣሪ፣ ከተፈጥሮ፣ ከስነምግባር ልዕለ ትርጉም ጋር ለማስተሳሰር ሲሉ፤ … ግን ለማሰር የሚሞክሩት በድርሰታቸው የደረሱትን ህዝብ ነው። ህዝብም ራስ ወዳድ ነው፡፡ ህዝብም ሰው ነው፡፡

ህዝብ ለመንግስት እንደ ሚስት ይመስላል፡፡ ባል ስልጣኑን ሲጭንባት ሚስት አሜን ብላ ትቀበላች፡፡ … ግን ጭነት ሲበዛባት ፍቅሯን (አንድነቷን) መጠርጠር ትጀምራለች፡፡ ጀምራ ከቀጠለች ባሏን ጥላ መሄዷ አይቀርም፡፡

ሚስቱ ጥላው የምትሄድ ባል፣ ህዝቡ ጥሎት የሚሄድ መንግስት ይበግናሉ፤ ይቃጠላሉ። የሚያቃጥላቸው ከህዝቡ ጋር የነበረው ፍቅር ከልባቸው አልወጣ ስለሚላቸው አይደለም፡፡ የሚያብከነክ ናቸው፡፡ ጥላ የሄደችው ሚስት ሌላ ባል ማግኘቷ እንደማይቀር በማወቃቸው ነው፡፡

በራስ ወዳድነት ላይ ተመስርተው የሚፈጠሩ አንድነቶች ሁሉ … አንድነት ሆነው የሚቆዩት ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ የተወሰነው ጊዜ ሲያልቅ … ሁሉም ፈጣሪ ነን ባዮች ወደ ተራነት ይመለሳሉ። መንግስትም ይቀየራል፣ ትዳርም ይፈርሳል፣ የገነነ ድርሰትም ከመፅሐፍ መደርደሪያ ላይ ወርዶ በሌላ ግነት ይተካል፡፡ የአንድነት ፅንሰ ሀሳብ ገናና የሚሆነው … የግለሰብ ራስ ወዳድነትን መጠን ያህል ነው፡፡

 

 

 

“የሳጥናኤል ሳል ኢትዮጵያ” የህይወት ዛፍ” “ገነት” “ኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለውና በጋዜጠኛና ደራሲ ፍሰሓ ያዜ ካሳ የተጻፈው መጽሃፍ በያዝነው ሳምንት በገበያ ላይ ውሎ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ መጽሃፉ የዓለም ሃያላን አገራትና መሪዎቻቸው በህብረት ሆነው በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩበትን ምክንያትና ዋነኛ ግባቸውን የሚተነትን ነው ያለው ደራሲው፤ 376 ገጾች እንዳሉትና በ80 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝም ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ፍሰሐ ያዜ ካሳ ከዚህ ቀደም “የኢትዮጵያ የ5ሺህ ዓመት ታሪክ፣ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ”፣ “ካልተዘመረለት እያሱ እስከተዘመረለት ኢህአዴግ” እንዲሁም “እኔና ቹ” የተሰኙ ሦስት መጽሃፍትን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

   ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው ጣይቱ የባህል ማዕከል ያዘጋጀው “መንገድ” የተሰኘ የስነጽሁፍ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ በአዲስ አበባው አክሱም ሆቴል ትልቁ አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ከቀኑ በ10፡30 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ የስነጽሁፍ ዝግጅት ላይ የተመረጡ ግጥሞች፣ ወጎች፣ የፍቅር ደብዳቤና አጭር ልቦለድ የሚቀርብ ሲሆን ባለሙያዎችም በአገራችን ወቅታዊ የስነ ግጥም እንቅስቃሴ ዙሪያ ሙያዊ አስተያየት እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ የሥነጽሁፍ ቤተሰቦች የጥበብ ድግሱን በነጻ እንዲታደሙት አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ጣይቱ የባህል ማዕከል፤ የአገሪቱን የስነጽሁፍ እድገት ማገዝ፣ ጥበብን ከጥበብ ወዳጆች ጋር ማገናኘት፣ ወጣት ጠቢባንን ማበረታታትና አንጋፋ የጥበብ ሰዎችን ማክበርና መዘከርን አላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Tuesday, 26 May 2015 08:43

“ዙቤይዳ”

     3ኛው ዕትም ሊወጣ ነው ተባለ

     በደራሲ አሌክስ አብርሃም ተፅፎ በቅርቡ ለአንባቢያን የደረሰው “ዙቤይዳ” የተሰኘው የአጭር ልብወለዶች መድበል የመጀመሪያና ሁለተኛ ዕትሞች ተሸጠው ማለቃቸው ተገለፀ፡፡ ሦስተኛው እትምም ከነገ በስቲያ ለገበያ እንደሚበቃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መፅሐፉ በአሜሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዌብ ሳይት አማካኝነት እንደሚሸጥም ደራሲው ጠቁሟል፡፡ 22 ታሪኮች የተካተቱበት መጽሐፉ፤ በ59 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

አሌክስ አብርሃም ከዚህ ቀደም “ዶ/ር አሸብርና ሌሎችም” የተባለ የአጭር ልቦለዶች መድበልና “እናት ፍቅር ሃገር” የተሰኘ የግጥም መፅሃፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

 

 

 

    የ73ቱ ዓመቱን የዕድሜ ባለፀጋ የዶክተር ተስፋፅዮን ደለለ ግለ-ታሪክ የሚያስነብበው “ከሚሽግዳ እስከ ዓለም ዳርቻ (ሕይወቴ ትምህርት ቤቴ)” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ ግለ-ታሪኩን የፃፉት ራሳቸው ዶ/ር ተስፋጽዮን ሲሆኑ የአርትኦት ሥራውን ያከናወነው ገጣሚ ወንድዬ ዓሊ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶ/ር ንጉሴ ተፈራ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔር በዶ/ር ተስፋፅዮን ህይወት ውስጥ ያደረገውን በጐ ነገር እንድታውቁ የሚረዳችሁ ብቻ ሳይሆን “‹በእኔ የህይወት ጉዞ የታየ ትርጉም ያለው ድርሻ ምንድን ነበር” ብላችሁ እንድትጠይቁ ያደርጋችኋል… ሁሉም ሊያነበው የሚገባ ቁምነገር የያዘ መጽሐፍ” ብለውታል፡፡

የመፅሐፉ አርታዒ ገጣሚ ወንድዬ አሊ በበኩሉ፤ “አተራረኩ ሲበዛ ተፈጥሮአዊ ከመሆኑ የተነሳ የጋሽ ተስፋን ረቂቅ ኩል መኳኳል፣ እንሶስላ ማሞቅ አላስፈለገኝም፤ በርኖስ ላይ ካቦርታ መደረብ ነውና፡፡” ሲል አስተያየቱን ገልጿል፡፡ በ10 ምዕራፎችና በ284 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ80 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

   

 

 

 

Tuesday, 26 May 2015 08:20

ምሳሌያዊ አባባል

 

የአዞ ጉልበት በውሃ ውስጥ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካውያን አባባል

ብልህ ወፍ ጎጆዋን በሌሎች ወፎች ላባ ትሰራለች

የዚምባቡዌያውያን አባባል

ሁለት መሪዎች በአንድ ቤት ውስጥ አይጣሉም፡፡

የኡጋንዳውያን አባባል

ደካማ መሪ ጭንቅላቱ ውስጥ ሸክም ያበዛል።

የኡጋንዳውያን አባባል

መሪ ካነከሰ ሌሎችም ማንከስ ይጀምራሉ፡፡

የኬንያውያን አባባል

የመሪ የተሳሳተ እርምጃ ለተከታዮቹ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡

የአፍሪካውያን አባባል

አገር በማስፈራሪያና በስድብ ጨርሶ አትመራም፡፡

የዛምቢያውያን አባባል

መሪ የሌለው ህዝብ ከተማ ያበላሻል፡፡

የጋናውያን አባባል

በዓለም ላይ እጅግ ኃይለኛው መሪ እንኳን በእንቅልፍ ይሸነፋል፡፡

የማላዊያውያን አባባል

አይጥን የሚገድል ዝሆን ጀግና አይባልም፡፡

የካሜሩያውያን አባባል

የመሪ ሃብቱ ህዝቦቹ ናቸው፡፡

የኮንጎአዊያን አባባል

ብቸኛ መሳሪያህ መዶሻ ከሆነ ችግሮችን ሁሉ እንደምስማር ትቆጥራቸዋለህ፡፡

የጋምቢያውያን አባባል

ውይይት ሲበዛ ወደ ፀብ ያመራል፡፡

የአይቮሪኮስት አባባል

አንበሳ ሳር ውስጥ መደበቅ አይችልም፡፡

የኬንያውያን አባባል

ሰው ረዥም ጥርስ ማብቀል ከፈለገ መሸፈኛ ከንፈር ሊኖረው ይገባል፡፡

የናይጄሪያውያን አባባል

 

የአዞ ጉልበት በውሃ ውስጥ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካውያን አባባል

ብልህ ወፍ ጎጆዋን በሌሎች ወፎች ላባ ትሰራለች

የዚምባቡዌያውያን አባባል

ሁለት መሪዎች በአንድ ቤት ውስጥ አይጣሉም፡፡

የኡጋንዳውያን አባባል

ደካማ መሪ ጭንቅላቱ ውስጥ ሸክም ያበዛል።

የኡጋንዳውያን አባባል

መሪ ካነከሰ ሌሎችም ማንከስ ይጀምራሉ፡፡

የኬንያውያን አባባል

የመሪ የተሳሳተ እርምጃ ለተከታዮቹ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡

የአፍሪካውያን አባባል

አገር በማስፈራሪያና በስድብ ጨርሶ አትመራም፡፡

የዛምቢያውያን አባባል

መሪ የሌለው ህዝብ ከተማ ያበላሻል፡፡

የጋናውያን አባባል

በዓለም ላይ እጅግ ኃይለኛው መሪ እንኳን በእንቅልፍ ይሸነፋል፡፡

የማላዊያውያን አባባል

አይጥን የሚገድል ዝሆን ጀግና አይባልም፡፡

የካሜሩያውያን አባባል

የመሪ ሃብቱ ህዝቦቹ ናቸው፡፡

የኮንጎአዊያን አባባል

ብቸኛ መሳሪያህ መዶሻ ከሆነ ችግሮችን ሁሉ እንደምስማር ትቆጥራቸዋለህ፡፡

የጋምቢያውያን አባባል

ውይይት ሲበዛ ወደ ፀብ ያመራል፡፡

የአይቮሪኮስት አባባል

አንበሳ ሳር ውስጥ መደበቅ አይችልም፡፡

የኬንያውያን አባባል

ሰው ረዥም ጥርስ ማብቀል ከፈለገ መሸፈኛ ከንፈር ሊኖረው ይገባል፡፡

የናይጄሪያውያን አባባል

 

 

 

ምርጫው በአንድ ሳምንት ተራዝሟል

ከ110 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል

33 ስደተኞች በታንዛኒያ ካምፕ በኮሌራ ሞተዋል

 

    የብሩንዲ መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሬ ንኩሩንዚዛ ባለፈው ረቡዕ ተቃዋሚዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ ብጥብጡ ከትናንት በስቲያ በመዲናዋ ቡጁምቡራ እንደገና ማገርሸቱንና ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተባብሶ መቀጠሉን ሮይተርስ ዘገበ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ህገመንግስቱን ጥሰው ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው አግባብ አይደለም ሲሉ የተቃወሙ በርካታ ዜጎች፤ ሃሙስ ዕለት ዳግም ወደ አደባባይ ወጥተው፣ ድንጋይ በመወርወርና እሳት በማቀጣጠል የከተማዋን ጎዳና ማጥለቅለቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ በመርጨትና ጥይት በመተኮስ ብጥብጡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክር እንደዋለ ገልጿል፡፡

ከፖሊስ በተተኮሰባቸው ጥይት የቆሰሉ በርካታ ተቃዋሚዎች እንዳሉና አንድ ወታደርም  ህይወቱ እንዳለፈ ዘገባው ጠቅሶ፣ ተቃውሞው ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች መስፋፋቱንና  በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት መፈጠሩን አስታውቋል፡፡

ለሳምንታት በቀጠለው የብሩንዲ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ መድረሱንና ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ታንዛኒያ የተሰደዱ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥርም ከ110 ሺህ በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ በታንዛኒያ የካጉንጋ ስደተኞች ካምፕ ከሚገኙ 70 ሺህ ያህል ብሩንዲያውያን መካከል 33 ያህሉ በካምፑ ውስጥ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ መሞታቸውን አክሎ ገልጿል፡፡

በዘንድሮው ምርጫ ለመሳተፍ መወሰናቸው ተቃውሞ ያስነሳባቸው ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፤  ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ ከዜጎቻቸውና ከውጭ ሃይሎች ጫና ቢደረግባቸውም፣ እወዳደራለሁ በሚለው አቋማቸው የፀኑ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ በአንድ ሳምንት በማራዘም ሰኔ አምስት ቀን እንዲከናወን መወሰናቸው ታውቋል፡፡

በሌሉበት የተቃጣባቸው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ድርጊቱን የመሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ ህዝብን በማበጣበጥና አብዮት በማነሳሳት ወንጀል ተከሰው በአገሪቱ የጦር ፍርድ ቤት ቅጣት ይጣልባቸዋል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ምርጫው በአንድ ሳምንት ተራዝሟል

ከ110 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል

33 ስደተኞች በታንዛኒያ ካምፕ በኮሌራ ሞተዋል

 

    የብሩንዲ መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሬ ንኩሩንዚዛ ባለፈው ረቡዕ ተቃዋሚዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ ብጥብጡ ከትናንት በስቲያ በመዲናዋ ቡጁምቡራ እንደገና ማገርሸቱንና ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተባብሶ መቀጠሉን ሮይተርስ ዘገበ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ህገመንግስቱን ጥሰው ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው አግባብ አይደለም ሲሉ የተቃወሙ በርካታ ዜጎች፤ ሃሙስ ዕለት ዳግም ወደ አደባባይ ወጥተው፣ ድንጋይ በመወርወርና እሳት በማቀጣጠል የከተማዋን ጎዳና ማጥለቅለቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ በመርጨትና ጥይት በመተኮስ ብጥብጡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክር እንደዋለ ገልጿል፡፡

ከፖሊስ በተተኮሰባቸው ጥይት የቆሰሉ በርካታ ተቃዋሚዎች እንዳሉና አንድ ወታደርም  ህይወቱ እንዳለፈ ዘገባው ጠቅሶ፣ ተቃውሞው ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች መስፋፋቱንና  በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት መፈጠሩን አስታውቋል፡፡

ለሳምንታት በቀጠለው የብሩንዲ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ መድረሱንና ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ታንዛኒያ የተሰደዱ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥርም ከ110 ሺህ በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ በታንዛኒያ የካጉንጋ ስደተኞች ካምፕ ከሚገኙ 70 ሺህ ያህል ብሩንዲያውያን መካከል 33 ያህሉ በካምፑ ውስጥ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ መሞታቸውን አክሎ ገልጿል፡፡

በዘንድሮው ምርጫ ለመሳተፍ መወሰናቸው ተቃውሞ ያስነሳባቸው ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፤  ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ ከዜጎቻቸውና ከውጭ ሃይሎች ጫና ቢደረግባቸውም፣ እወዳደራለሁ በሚለው አቋማቸው የፀኑ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ በአንድ ሳምንት በማራዘም ሰኔ አምስት ቀን እንዲከናወን መወሰናቸው ታውቋል፡፡

በሌሉበት የተቃጣባቸው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ድርጊቱን የመሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ ህዝብን በማበጣበጥና አብዮት በማነሳሳት ወንጀል ተከሰው በአገሪቱ የጦር ፍርድ ቤት ቅጣት ይጣልባቸዋል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

 

 

 

 

 

 

   የምዕራብ አፍሪካ አገራት ፕሬዚዳንቶች ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ እንዳይቆዩ ለማድረግ ታልሞ የቀረበውን የስልጣን ገደብ የሚያስቀምጥ ክልላዊ የስምምነት ሃሳብ፣ የአገራቱ መሪዎች ውድቅ እንዳደረጉት ቢቢሲ ዘገበ፡፡

የአገራቱ መሪዎች ባለፈው ማክሰኞ በጋና መዲና አክራ ባካሄዱት የኮሜሳ ክልላዊ ስብሰባ ላይ፣ በሃሳቡ ዙሪያ መምከራቸውንና ለጊዜው ሃሳቡን ውድቅ ማድረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ በቆዩ መሪዎች በመመራት ላይ ያሉት ቶጎ እና ጋምቢያ የስልጣን ዘመን ገደቡን አጥብቀው እንደተቃወሙት ገልጿል፡፡ አብዛኞቹ የምእራብ አፍሪካ አገራት በህገ-መንግስቶቻቸው አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል ቢደነግጉም፣ በተቃራኒው ከዚህ ገደብ አልፈው በስልጣናቸው የሚቆዩ መሪዎች አሉ ብሏል ዘገባው፡፡

አንዳንድ የምእራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት፣ እያንዳንዱ አገር የየራሱ የሆነ የተለያየ የፖለቲካ አውድ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ፣ በሁሉም አገራት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አንድ አይነት ህግ መተግበር አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡  

አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ የፕሬዚዳንቶችን የስልጣን ዘመን ቆይታ በክልላዊ ደረጃ በህግ መገደብ የሚለው ሃሳብ በስብሰባው ላይ ራሱን የቻለ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ እንደ አንድ የለውጥ ምእራፍ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምእራብ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሞሃመድ ኢብን ቻምፓስ  እቅዱን እንደሚደግፉት ገልጸው፣ ሃሳቡ የተጠነሰሰው የቡርኪናፋሶው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ ባለፈው አመት የአገሪቱን ህገመንግስት አንቀጽ በማሻሻል ለሶስተኛ ዙር በስልጣን ላይ ለመቆየት ያልተሳካ ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

በአገራቱ መሪዎች ላይ የስልጣን ገደብ ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ እቅድ፤ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት መሪዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቀው ዘገባው፣ የቶጎው ፕሬዚዳንት ፋኦሪ ጋሲንግቤ ለሶስተኛ፣ የጋምቢያው ፕሬዚዳንት  ያህያ ጃሜህ ደግሞ ለአራተኛ ዙር የስልጣን ዘመን አገራቱን እየመሩ እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡

   የምዕራብ አፍሪካ አገራት ፕሬዚዳንቶች ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ እንዳይቆዩ ለማድረግ ታልሞ የቀረበውን የስልጣን ገደብ የሚያስቀምጥ ክልላዊ የስምምነት ሃሳብ፣ የአገራቱ መሪዎች ውድቅ እንዳደረጉት ቢቢሲ ዘገበ፡፡

የአገራቱ መሪዎች ባለፈው ማክሰኞ በጋና መዲና አክራ ባካሄዱት የኮሜሳ ክልላዊ ስብሰባ ላይ፣ በሃሳቡ ዙሪያ መምከራቸውንና ለጊዜው ሃሳቡን ውድቅ ማድረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ በቆዩ መሪዎች በመመራት ላይ ያሉት ቶጎ እና ጋምቢያ የስልጣን ዘመን ገደቡን አጥብቀው እንደተቃወሙት ገልጿል፡፡ አብዛኞቹ የምእራብ አፍሪካ አገራት በህገ-መንግስቶቻቸው አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል ቢደነግጉም፣ በተቃራኒው ከዚህ ገደብ አልፈው በስልጣናቸው የሚቆዩ መሪዎች አሉ ብሏል ዘገባው፡፡

አንዳንድ የምእራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት፣ እያንዳንዱ አገር የየራሱ የሆነ የተለያየ የፖለቲካ አውድ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ፣ በሁሉም አገራት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አንድ አይነት ህግ መተግበር አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡  

አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ የፕሬዚዳንቶችን የስልጣን ዘመን ቆይታ በክልላዊ ደረጃ በህግ መገደብ የሚለው ሃሳብ በስብሰባው ላይ ራሱን የቻለ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ እንደ አንድ የለውጥ ምእራፍ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምእራብ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሞሃመድ ኢብን ቻምፓስ  እቅዱን እንደሚደግፉት ገልጸው፣ ሃሳቡ የተጠነሰሰው የቡርኪናፋሶው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ ባለፈው አመት የአገሪቱን ህገመንግስት አንቀጽ በማሻሻል ለሶስተኛ ዙር በስልጣን ላይ ለመቆየት ያልተሳካ ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

በአገራቱ መሪዎች ላይ የስልጣን ገደብ ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ እቅድ፤ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት መሪዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቀው ዘገባው፣ የቶጎው ፕሬዚዳንት ፋኦሪ ጋሲንግቤ ለሶስተኛ፣ የጋምቢያው ፕሬዚዳንት  ያህያ ጃሜህ ደግሞ ለአራተኛ ዙር የስልጣን ዘመን አገራቱን እየመሩ እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡