Administrator

Administrator

   አንጋፋዋ ድምፃዊት አስቴር አወቀና ማዲንጎ አፈወርቅ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ዛሬ ምሽት  በጊዮን ሆቴል የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ፡፡ ከቀኑ 10፡30 ላይ የኮንሰርቱ መግቢያ በሮች እንደሚከፈቱ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ እዩኤል ልዑልሰገድ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤በኮንሰርቱ ላይ ድንገተኛ (surprise) እንግዳ የሚኖር ሲሆን እንግዳው 2 ወይም 3 ዘፈኖችን ያቀነቅናል፡፡ አስቴር በዋዜማው ኮንሰርት 25 ዘፈኖችን የምታቀርብ ሲሆን ማዲንጎ 8 ወይም 9 ዘፈኖችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡
የ2008 አዲስ ዓመትን ለመቀበል ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ የርችት ተኩስ ሥነስርዓት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ የVIP አቀማመጡ ከመድረኩ ፊት ለፊት መደረጉን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ቲኬቶቹ ኤሌክትሮኒክ ስለሆኑ ግፍያ አይኖርም ብለዋል፡፡  

 የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከፖሊስ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመተባበር በነገው ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ልዩ የዓውዳመት የመዝናኛ ፕሮግራም ማዘጋጀቷን አስታውቋል፡፡ በእለቱ አጫጭር ድራማዎችን ጨምሮ ዘመናዊና ባህላዊ ዘፈኖች ከነውዝዋዜያቸው ይቀርባሉ፡፡ ፕሮግራሙን ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 በ30 ብር መግቢያ መታደም እንደሚቻል አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡

 “የአባባ ተስፋዬ ተረቶች የስዕል አውደ ርዕይ” ባለፈው ማክሰኞ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ተከፍቶ ለ4 ቀናት ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡ አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት አባባ ተስፋዬ፤በኔክስት ጄነሬሽን የበጎ አድራጎት ማህበር ህፃናትና ወጣቶች የተዘጋጀላቸው በሙካሽ የተጌጠ ካባ ተበርክቶላቸዋል፡፡ “በዓለም ላይ ብዙ አገራትን አይቻለሁ፤ሰርቶ ለመኖር እንደ ኢትዮጵያ የተመቸ አገር አላየሁም” ያሉት አባባ ተስፋዬ፤“አገራችሁንም ሥራንም ውደዱ፤እኔ አርቲስት ሆኜ እየሰራሁ  ሻሸመኔ ላይ በግብርና ሥራም ተሰማርቼ ነበር፡፡ ከግብርናው ባገኘሁት ትርፍም የራሴን ቤት ሰርቻለሁ፤መኪናም ገዝቻለሁ” በማለት የሥራን ጥቅም አስረድተዋል፡፡
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረገው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤“እኛ ዛሬ ላይ የደረስነው በቀደመው ትውልድ ታግዘንና ተረድተን ነው፡፡ ይህንን ውለታ ታሳቢ በማድረግ አባባ ተስፋዬን የሚዘክር መድረክ መሰናዳቱ መስፋፋትና መቀጠል አለበት” ብሏል፡፡
በአባባ ተስፋዬ ሳህሉ መኖሪያ ቤት ይዞታ ላይ ሊሰራ የታቀደው ቴአትር ቤትና የባህል ማዕከል ጋለሪ ህንጻ ዲዛይን በዕለቱ ቀርቦም ገለፃ ተሰጥቶበታል፡፡

 በብሩክ ከድር የተዘጋጀው “የአረቦች ፀደይ” የተሰኘ መፅሃፍ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ፣ የፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌ መታሰቢያ አዳራሽ ተመርቋል፡፡
መፅሀፉ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀው ንቅናቄ ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅልና ሁለንተናዊ ገፅታውን ይዳስሳል፡፡
በ253 ገፆች በተቀነበበው “የአረቦች ፀደይ” መፅሃፍ ላይ አጭር ውይይት እንደተካሄደም ታውቋል፡፡

በጀምስ ሬድፊልድ “The Celestine Prophecy” በሚል ርዕስ ተፅፎ በደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ተብሎ የተተረጐመው መጽሐፍ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በ11 ሰዓት በዋቢሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ ለደራሲው አምስተኛ የትርጉም ሥራው ሲሆን በምረቃው ሥነስርዓት ላይ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችና ጥበብ አፍቃሪያን እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

    በዓመቱ እስካሁን ያሳለፍነው መልካም ነበር፡፡ በስራ ነው ያሳለፍነው፡፡ ከአመት ወደ አመት የስራ አፈፃፀማችን እየተሻሻለ ነው፡፡ ሠራተኞቻችን ጤናቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ፣ እንዲማሩ ማድረጋችን፣ ተማሪዎችን ማስመረቃችን እንደቀጠለ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየቦታው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የመፍታት ብቃታችን ከእለት ወደ እለት እየተሻሻለ ነው፡፡ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ረገድ ጥሩ ክንውን ነበረን፡፡
በቀጣይ አመት ደግሞ የጀመርናቸው የ8 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ወደ ውጭ መላክ ብቻ አይደለም ትልቅ የሚያደርገን ብለን ስለምናምን፣ ሀገር ውስጥ ያለውን ተጠቃሚ ፍላጐት ማሟላት መቻል አለብን፡፡ የሀገር ውስጥ ተጠቃሚው እያደገ ነው፡፡ ይሄን ፍላጐት ለማሟላት በአዲሱ አመት ጠንክረን እንሠራለን፡፡

  የስልጣን ዘመናቸውን 100ኛ ቀን ባለፈው ሳምንት ያከበሩት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፤ በባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ውስጥ ያለው ገንዘብ 100 ሺህ ፓውንድ ብቻ መሆኑን በይፋ መግለጻቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ከዚህ ገንዘብ ውጭ ያላቸው ንብረት በጭቃ የተሰሩትን ሁለት ቤቶቻቸውን ጨምሮ አምስት የመኖሪያ ቤቶችና 270 ከብቶች ያሉበት የእርሻ ቦታ ብቻ መሆኑን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፤ሰውዬው ያላቸው ሃብት ከተራው የናይጀሪያ ህዝብ እጅግ የበዛ ቢሆንም፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዜጎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የግል ሃብታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩና የህዝቡን ሃብት ወደ ካዘናቸው በማስገባት ከሚታሙ እጅግ ባለጸጋ ፕሬዚዳንቶች የተለዩ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ከቡሃሪ ሃብት 9 እጥፍ የሚበልጥ የ900 ሺህ ፓውንድ ባለቤት መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ቡሃሪ ስልጣን በያዙ ማግስት ከመንግስት ካዘና 100 ቢሊዮን ዶላር መንትፈው የግል ሃብታቸው አድርገዋል በሚል የሚታሙትን ሙሰኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በ1980ዎቹ የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ቡሃሪ፤በስልጣን ዘመናቸው ከሙስና የጸዱ መልካም ሰው እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፣ናይጀሪያን ለአምስት አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙት አምባገነኑ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ በአንጻሩ 3 ቢሊዬን ፓውንድ ሃብት እንደነበራቸውና አብዛኛውን ገንዘባቸውን በስዊዝ ባንክ እንዳስቀመጡት አስታውሷል፡፡

     ፖሊስ በአይፎን ተጠቃሚ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ጀምሯል
             ማይክሮሶፍትም የወንጀል ተጠርጣሪን ኢሜል ባለመስጠቱ ተከሷል
   የአሜሪካ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ እና ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ ለምናደርገው ምርመራ የሚጠቅሙ የጽሁፍ መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠን አልፈቀደም ያሉት ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት የሚጣልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው መንግስትን መጠየቃቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ አፕል በሚያመርተው አይፎን አማካይነት ከሰዎች ወደ ሰዎች የተዘዋወሩ አጭር የጽሁፍ መልክቶችን ለወንጀል ምርመራ አሳልፎ አልሰጥም ብሎ በእምቢተኝነት በመጽናቱ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት ሲሉ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ወንጀል መርማሪዎች የአፕል ምርት የሆነውን አይፎን በሚጠቀሙ የአደንዛዥ ዕጽ እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ድርጊቶች ተጠርጣሪዎች ዙሪያ ለሚያደርጉት ምርመራ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መናገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
አፕል ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ የተላለፉበት አይሜሴጅ የተሰኘ የመልዕክት መላላኪያ ሲስተሙ ነባር መረጃዎችን የሚያጠራቅምበት ቋት የሌለው በመሆኑ የተጠየቀውን መረጃ ስለማያገኝ አሳልፎ መስጠት እንደማይችል ማስታወቁን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ዙሪያ ለሚደረግ የወንጀል ምርመራ ጠቃሚ የሆኑ የኢሜይል መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠው ባለመፍቀዱ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የፍርድ ቤት ክርክር እያደረገ እንደሚገኝም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

አሜሪካዊው ታዋቂ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን፤ያለ ፈቃዴ ዝናዬን ተጠቅሞ ሃብት አፍርቷል ባለው አንድ ኩባንያ ላይ ለመሰረተው ክስ በካሳ መልክ እንዲከፈለው በፍርድ ቤት የተወሰነለትን 8.9 ሚሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሊለግስ እንደሆነ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የ52 አመቱ ጆርዳን፤ሴፍዌይ የተባለው የአሜሪካ የምግብ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ፣ ሳያስፈቅደኝ ምስሌን ለምርቶቹ ማስታወቂያ ተጠቅሟል፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል በሚል የመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት፤ 8.9 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡
ቺካጎ ውስጥ የተሰየመው ችሎት፤ውሳኔውን ማሳለፉን ተከትሎ ጆርዳን ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፤ጉዳዩ ክብርን የማስጠበቅ እንጂ በካሳ ገንዘብ የማግኘት አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ኩባንያው የሚሰጠውን 8.9 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡ ነዋሪነቷ በኒውዮርክ ኢስት ሀምፕተን የሆነው አሜሪካዊቷ ሚሊየነር ሌስሊ አን ማንዴል በበኩሏ፤4 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣው እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ለምታረባቸው 32 ወፎች፣ 100 ሚሊየን ዶላር ማውረሷን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሚሊየነሯ በፈረመችበት ህጋዊ የውርስ ሰነድ ላይ፣ ወፎቼ ጎጇቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተጸዳላቸውና ከሱፐርማርኬት ደረጃቸውን የጠበቁ ጣፋጭ ኬኮች፣ ካሮትና ፈንድሻ እንዲሁም የተጣራ ውሃ እየተገዛላቸው በአግባቡ እየተመገቡ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ ብላለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 ሊዎና ሄልምስሌ የተባለች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማረች አሜሪካዊት ሚሊየነር ለአንድ ውሻዋ 12 ሚሊየን ዶላር ማውረሷንም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡

      ኢትዮጵያችን ራሷን ከዓለም አግልላ በብቸኝነት አዲስ ዓመትን ለማክበር ሽርጉዷን አጠናቃለች፡፡ ኢትዮጵያውያንም እንደ ህዝብ አሮጌ ሃሳባችን ሳይለወጥ አዲስ ዓመትን ልናከብር ተዘጋጅተናል፡፡ ጀምረነዋል፡፡ ይሁን እንጂ “አዲሱ ዓመት” አዲስ መሆኑ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል፡፡ በተፈጥሮ የጊዜ ቅመራ ሰሌዳ ላይ ለኢትዮጵያም ይሁን ለዓለም የጳጉሜ 6 ሌሊትና የመስከረም 1 ንጋት ከሌሎቹ ቀናት የተለየ ምንም የላቸውም፡፡ ልዩነታቸውም በእያንዳንዱ ቀን መሀል ላይ ያለ ልዩነት ነው፡፡ አዲስ ዓመት ከማንም የተሰጠን ሳይሆን የለመድነው ነው፡፡ በስምምነት ያፀደቅነውና ይሁነኝ ብለን አምነን የተቀበልነው ነው፡፡ “መስከረም” ፣ “ጥቅምት”፣ “ህዳር”፣ “ምንትስ” ብለን ደርድረን፣ ለእያንዳንዱ ወርም ስያሜ አበጅተን፣ “የመጀመሪያ” ያልነውን ወር የመጀመሪያ ቀን “ዓመት መለወጫ” ያደረግነው እኛው ነን፡፡ በቃ አዲስ ዓመት “ዘንድሮም አለን” ለማለት ካልሆነ በቀር የአሮጌው አይነት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ስም ስላልሰጠነው እንጂ የትኛውም ቀን በራሱ የአዲስ ዓመት መጀመሪያም መጨረሻም ነው፡፡
ስለ አዲሱ ዓመት ትተን ስለአሮጌው ሃሳባችን እንነጋገር፡፡ አዲሱ ዓመት፣ ቀኑ አይጠቅመንም፡፡ ሃሳባችን ነው የሚበጀን፡፡ የእኛ የሆነውና የምናዝበትም እሱው ነው፡፡ በጥቅሉ መፈረጅ ቢቸግርም ኢትዮጵያውያን ግን እንደ ህዝብ ለአዲስ አስተሳሰብ ክፍት አይደሉም፡፡ ዘመናዊ እውቀት ሲመጣ ከሃይማኖትም ከሞትም ጋር አያይዘን እንደገፋነው፣ ሲኒማ አይተንም ጥበቡን የሰይጣን ሥራ አድረን ቦታውን “ሰይጣን ቤት” ብለን እዚህ ድረስ ለምዕተ ዓመት ገደማ ይኸው ስያሜ ቀንቶን፣ እየጠራን በአሮጌው ሃሳብ ላይ የመጣበቅ ልምዳችን ዛሬም ድረስ ከእቅፋችን አልወጣም፡፡
ግርር አቋማችን ጐልቶ ከሚታይባቸው (አሮጌው ሃሳባችን ከሚገመትባቸው) መስኮች አንዱ ፌስቡክ ነው፡፡ ለመገናኛና ለታላቅ ቁምነገር ጠቢባኑ አምጠው ከወለዷቸው ማህበራዊ ድረገጾች አንዱ የሆነውን ፌስቡክን በጠቃሚ ሚዲያነቱ እውቅና ከሚሰጡትና ከሚገለገሉበት አንዱ ነኝ፡፡
ይሁንና ፈጣሪያኑን የዓለም ቁንጮ ቱጃር አድርጐ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ከአፅናፍ አፅናፍ እያገናኘ ያለው ይኸው ቴክኖሎጂ ወለድ ብዙሀን መገናኛ፤ እኛ ሀገር በወጉ የሚጠቀሙበት፣ ሃሳባቸውን አስበውበት ወደ ህዝብ የሚያደርሱበት ጥቂቶች ቢሆኑ ነው፡፡
አመዛኞቹ ግን እንደጊዜያችን ሁሉ በብክነት የምንጠቀምበት ነው፡፡  
ዓመት ሄዶ ዓመት ሲመጣ፣ ክፍለ ዘመንም ሲቀየር እኛ በሃሳብ ካልተለወጥን፣ ከጊዜው ጋር መዘመን ካቃተን የአዲስ ዓመትን የመቀበል ጉጉታችን ከበዓል ማክበር የተለየ አይሆንም፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብ ማለት ሌላ ሳይሆን ከርረው የያዙትን ላላ አድርጐ ማሰብ ማለት ነው፡፡ ለነገሮች አንድ መንገድ ብቻ አለማበጀት ነው፡፡ እውነት ሌላውም ቤት እንዳለ ማሰብ ነው፡፡ እኛ ያመንነው ፍፁማዊው እውነት፣ እሱ ብቻ እንዳልሆነ ማሰብ ነው፡፡ ወደ አንድ “እውነት” ለመድረስ የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን መቀበል ነው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ጭፍን እምነት አለማሳደር ነው፡፡ ሰዎች እንደኛ ሁሉ የራሳቸው ምርጫ እንዳላቸው ማመን ነው፡፡ ሰዎችን ከእምነታቸው ጋር መተው ነው ስልጣኔ የራስን “እውነት” በሌሎች ላይ ለመጫን መነሳት ወደፊት ማንንም ሊያራምድ አይችልም፡፡ ይህን ሳይጥሉ አዲስ ዓመት ውስጥ መግባት አዲስ አያደርግም፡፡
በፌስቡክ የአጠቃቀም ልምዴ ብዙሀኑን እየጐተቱ አላራምድ ያሉ፣ ብዙዎች ከያዙት አልፈው ሌላ ሊያዩ የማይፈቅዱባቸው የጽንፍ መንገድ እየሆኑ ያሉ ሁለት መንገዶች አሉ፤ ፖለቲካና ሃይማኖት፡፡ ዓመታት እየተለዋወጡም እዚያው በነበርንበት ጐትተው የጐለቱን ጽንፎች ሆነው ይታዩኛል ለእኔ፡፡ ሃይማኖትና ፖለቲካ የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይ መቧደንን መሰረት ያደረጉ መሆናቸው ነው፡፡ የአንዱ ፖለቲካ ወይም ሃይማኖት አባል የራሱን ቤት ትቶ በሌላው ሳሎንና ጓዳ እየተምነሸነሸ ውሎ የሚያድርበት አካሄድ በሰለጠኑትም ብዙ የሚያጋጥም አይሆንም፡፡ ሁለቱም በተግባራቸው ብቻ ሳይሆን በአባላቶቻቸው ቁጥርም ጭምር ላይ ነው ህልውናቸው የተመሰረተው፡፡ ይህ በመሆኑም ከቻሉ ሌላውን አፍርሰው የራሳቸውን ቢያደራጁ ላይደንቅ ይችላል፡፡ ሌሎች እንዳይደራጁ ማድረግ ግን ተፈጥሯዊው መንገድ አይደለም፡፡
ዛሬ ዛሬ ፌስቡክ ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች አንፃር ፖለቲካና ሃይማኖት በሁለት በሁለት የተከፈሉ ይመስለኛል፡፡ ደጋፊና ተቃዋሚ፡፡ የሃይማኖትም ሆነ ፖለቲካ ደጋፊዎች (የአንዱ ቡድን) የተቃዋሚዎቻቸውን፣ ተቃዋሚዎቹም የእነሱን ተቃዋሚዎች ድምፅ ላለመስማት የተማማሉ ይመስላሉ፡፡ ሆደባሻነት በሀገር ደረጃ ማጐንቆሉን ፌስቡክ በከፈትኩት ቁጥር ይነግረኛል፡፡
በሁለቱም ፅንፎች (በፖለቲካውም በሃይማኖቱም) በራስ ጥንካሬ ሳይሆን በሌሎች ድክመት የመበልፀግ አዝማሚያ ውስጥ ገብተው ይታያል፡፡ የአንዱ ድክመት የራሱ ወድቀት እንጂ በየቱም መልኩ የተቃራኒው ጥንካሬ ሊሆን አይችልም፡፡ በማንም ሞት ዳንኪራ መርገጥ ደስታን ሊያመጣ አይችልም፡፡ እየታየ ያለው ግን ይህ ነው፡፡
እዚያው ፌስቡክ ላይ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ሳነሳ፣ በየትኛውም መልኩ የዚያ ሃይማኖት አባላት እንዲያዝኑ የማድረግ ዓላማ የለኝም፡፡ እንደዚያ አይነት ሀሳብን አንስቼም አላውቅም፡፡ የአንድ ሀይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ብሔር አባላት ላይ በደምሳሳው ቅሬታ የሚያስነሳ ሀሳብን ማሰራጨት ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ ጠንቅቄ እረዳለሁ፡፡ ይሁንና በሃይማኖቱ ወይም በፖለቲካው አናት ላይ ቆም ብለው ብዙኃኑን ስለሚያሳንሱ ዋልጌዎች ማንሳት በየትኛውም መመዘኛ ስለተቋሙ ወይም መላ አባላቱ ማንሳት ሊሆን አይችልም፡፡ እንደውም በግልባጩ እነሱን ከውርደት ማዳን ተደርጎ መወሰድ ነው ያለበት፡፡
1960ዎቹ መጨረሻ ገደማ፣ በዘመነ ቀይ - ነጭ ሽብር ዘመን መንገድ ሁሉ አንድ ብቻ ሆኖ ነበር፡፡ ግራው ወይም ቀኙ፣ ነጩ ወይም ጥቁሩ፣ ከእኔ ወይም ከጠላቴ ብቻ ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህ ያልሆነ ከዚያ እንደሆነ ተደርጎ በጭፍን የሚፈረጅበትና የሚፋጅበት ወቅት ነበር፡፡ መካከለኛውን ወይም ከሁለቱ ውጭ ያለውን መምረጥ በሁለቱም ወገን አደጋን ሲጠራ ታይቷል፡
“መሀል ሰፋሪ” የሚል ስም ይሰጥ ነበር፡፡፡ መሀል ሰፋሪነት ደግሞ በተለይ በአብዮቱ በኩል በግልፅ ተወግዟል፡፡ ማስወንጀያ ምክንያትም ሆኗል፡፡ ያ የእሳት ዘመን ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ጊዜ ስላልነበረው፣ ቀላቅሎ አብኩቶ መጋገርና መብላት አሊያም ጠቅሎ ገደል መጣል አይፈረድበት ይሆናል፡፡ በተረጋጋ ጊዜ፣ ጦርነት ሳይመጣ መሸበር ግን የጤንነት ጉድለት ነው፡፡ አሁን እኛ ጤንነት የጎደለን ይመስለኛል፡፡ እንዲህ በሀሳብ አድፈን በዓመት መለወጥ ለመንፃት እየሞከርን ይመስለኛል፡፡ ጊዜ የማንንም እዳ ተሸክሞ አያውቅም፡፡ ሰው ግን የጊዜ ባለዕዳ ይሆናል፡፡
ወደ ፖለቲካውም ስንመጣ (አሁንም እዚያው ፌስቡክ መንደር) ነፃ አሳቢ ሰው እኔ አላገኘሁም፡፡ አግንኜ ካሰብኩት ራሴን ጨምሮ አንድም ሰው እንኳ ወደ ግራም ወደ ቀኝም እኩል በተሰማው ልክ የሚንቀሳቀስ ማንንም አላየሁም፡፡ ፌስቡክ ላይ የሚታየኝ የፖለቲካ መስክ መሀሉ ወለል ያለ ባዶ ሆኖ፣ ግራና ቀኝ በየቁጥራቸው ልክ የተቧደኑ ጨለምተኞችን የያዘ ነው፡፡ በማውቀው ደረጃ አንዳችንም መሀሉ ላይ የለንም፡፡ እኛም መቆም አንፈልግም፣ ብንቆምም ሌሎች ገፍትረው አሊያም ጎትተው ይጥሉናል፡፡ ፍርሀት በፌስቡክ ሰማይ ላይ ነግሷል፡፡ በጭፍኑ ደፋር ፀሐፍት፣ ደፋር ተሳዳቢዎች ያሉ ቢመስልም ከዚያው ከቅርባችን ክብ ውጭ ሌላውን ለማየት ግርዶሽ አለብን፡፡
ገዢውንም ሆነ ተገዢዎቹን የፖለቲካ ድርጅቶች ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ውጭ ያለው ምርጫ ተጥሏል፡፡ ቢገኝም ተራምዶ የማለፍ እንጂ የማንሳት ፍላጎት አይታይም፡፡ ሜዳው ሰፊ ይምሰል እንጂ አያራምድም፡፡ ገዢውን ግንባር የሚቃወሙት ወገኖች እርስ በእርስ ባይስማሙ እንኳ ስለግንባሩ አንዳች መልካም ነገር ላለመተንፈስ የተማማሉ ይመስላሉ፡፡ (አሁንም ይህን ሲያነቡ “ድሮስ ምን መልካም ጎን አለውና!” የሚሉ ብዙዎች እንደሚሆኑ ይታመናል) የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ እየበረርን፣ “ይህን መንገድ ጥሩ ሰርተውታል” ስለው፣  “ኤጭ! ደግሞ ይሔ መንግሥት ምን ደህና ነገር ይሰራል?” ያለኝ ወዳጅ አለኝ፡፡ ስለ ብርቱካን ጣዕም ስትነግሩት፣ ስለሽንኩርት ዓይን ማቃጠል የሚመልስላችሁ አለ፡፡ ይህ ወዳጅም እንደዚያ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ከገዢው ጎን የተሰለፉትም ተቃዋሚዎች ለዚች ሀገር እስካሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ረብ ያለው ተግባር እንደማይከውኑ አምነው ለማሳመን የሚታትሩ ናቸው፡፡ ይህ መሬት ላይ ያለ ግርርና ቀር ሀሳብ ቢሆንም ፌስቡክ ላይ ደግሞ አይሎ ይታያል፡፡ አዲስ ዓመት ለመቀበል ሽር ጉድ የምንለው ከዚህ አሮጌ ሀሳባችን ጋር ፅኑ ጋብቻ ፈፅመን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ገላን ሞዥቆ መታጠብ ብቻውን ንፁህ አያደርግም፡፡ ንፁህ መልበስንም ይጠይቃል፡፡ አዲስ ዓመት እኛን በተወሰነ መልኩም አዲስ ሊያደርገን ካልቻለ …