Administrator

Administrator

መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ/ም ፤ በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ያካሂዳል ።
...
ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ ተወልደው ያደጉት በቀድሞው አጠራር በወሎ ክፍለ ሀገር በሰቆጣ ከተማ ነው።  በ 1973 ዓ/ም የቀድሞው ኢህዴን / ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ፖለቲካ ድርጅት ተመስርቶ ደርግን ለመጣል የትጥቅ ትግሉን በዋግ አካባቢ ሲጀምር እርሳቸውም እንደ ዘመኑ ወጣቶች የደርግን መንግስት አምርረው ይጠሉ ስለነበር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው በ 1975 ዓ/ም የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከ ጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሄዶ በ 1983 ዓ/ም የደርግ መንግስት ከስልጣን ሲባረር ቀደም ሲል ከአራት ድርጅቶች ጥምረት ኢህአዴግ ተብሎ በተመሰረተው ድርጅት የበላይነት የሽግግር መንግስት ሲቋቋም ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚንስትር እርሳቸው ደግሞ የአዲስ አበባ ሪጅን ፅ/ቤት የኢህአዴግ ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆነው እየሰሩ ቆዩ።

እርሳቸው እንደሚሉት በ 1989 ዓ/ም " በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም " በሚል የፖለቲካ ሴራ ኢህአዴግ አቶ ታምራትን ለእስር እንዲዳረጉ አደረገ። ይህኔ ታዲያ ወ/ሮ ሙሉ በህይዎቴ ይገጥመኛል ብለው ከማይገምቱት ፈተና ላይ ወደቁ። የአቶ ታምራት ሚስት በመሆናቸው  ከስራ ቦታቸው እና ከሃላፊነታቸው ያለአንዳች ርህራሄ ተባረሩ። በወቅቱ ምንም አይነት ገቢ ወይንም ጥሪት ሳይኖራቸው አራት ዓመት ከሆነው የመጀመሪያ ልጃቸው እና የአንድ ወር ጨቅላ ህፃን ከነበረቸው ሁለተኛ ልጃቸው ጋር ሲኖሩበት ከነበረው የመንግስት ቤትም ሳይቀር እንዲወጡ ተደረገ።

ከእለት ወደ እለት ማወከቦች ፣ የማፈን ሙከራዎች፣  ማስፈራሪያዎችና ልዩ ልዩ ፈተናዎች እየጨመሩባቸው ሲሄዱ በ 1992 ዓ/ም ሁለት ልጆቻቸውንና ታናሽ እህታቸውን ይዘው ወደ ኬንያ በግፍ ተሰደዱ።

ከሦስት ዓመታት የኬንያ አስቸጋሪ የስደት ቆይታ በኋላ በ 1995 ዓ/ም ወደ አሜሪካ በስደት እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው በኮሎራዶ ግዛት ዴንቨር ከተማ መኖር ጀመሩ ። በአሜሪካን ሀገርም ብቻቸውን ሆነው ልጆቻቸውን እንደሚያሳድግ እናት የጋዝ ማደያ ፣ የልብስ መሸጫ መደብርና የመሳሰሉት እየሰሩ ልጆቻቸውን ማሳደግና ማስተማር ቀጠሉ።

በ 2000 ዓ/ም ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ ከእስር ተፍትተው ወደ አሜሪካን ሀገር በመጡበት ወቅት ወ/ሮ ሙሉ ጋዝ ማደያ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ለ አስራ ሁለት ዓመታት ልጆቻቸውን ያለአባት ማሳደጋቸውና ልጆቻቸውም እነዛን ረጅም ዓመታት ያለ አባት ማደጋቸው እርሳቸው ባለፉበት የመከራ ህይዎት ውስጥ የሚያልፉ ልጆችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችን በተለየ መንገድ እንዲያስቡ አደረጋቸው። በሚወዷቸውና የኔ በሚሏቸው ሰዎች መጠላትና መገለል አሳዛኝ የህይዎት ክስተት መሆኑን ተገነዘቡ ። እናም የተቸገረን ሰው ቀርቦ ማፅናናትና መደገፍ ምንያህል የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ከህይዎታቸው ተማሩ።

ከዛም የእርሳቸው እና የቤተሰባቸው የመከራ ውጤት የሆነው እንዲሁም ለችግር የተጋለጡ ፤ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችና መበለቶችን የሚያግዘው ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት በ 2005 ዓ/ም ሊመሰረት ቻለ።

ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ ፤ በአዲስ አበባ ፣ በአማራ ክልል ዋግህምራ ሰቆጣ ከ400 በላይ መበለቶችንና ከ280 ወላጆቻቸውን ያጡ ለችግር የተጋለጡ ልጆችን በመርዳት ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ/ም በከተማችን አዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅቷል ። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በሚችለው ሁሉ አጋር እንዲሆንና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶችና ህፃናትን እንዲያግዝ በማዕከሉ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥሪ ቀርቧል።

በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር ጎርጎሪዮስ አደባባይ ፊት ለፊት የተገነባው ባለ 15 ፎቅ ዓለማቀፍ ሆቴል፤ የፊታችን ቅዳሜ  የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡
ለግንባታ 7 ዓመት የፈጀውና የኩራዝ ወንዝ ኃ.የተ.የግ. ድርጅት አጠቃላይ ፕሮጀክት አንደኛው እህት ኩባንያው ነው የተባለው ሽታዬ ስዊት ሆቴል፤ አባት አርበኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና አምባሳደሮች በተገኙበት ይመረቃል ነው የተባለው፡፡
በ600 ካ.ሜ ቦታ ላይ ያረፈው ሆቴሉ G†15 ከአንድ ቤዝመንት ጋር ያለው ሲሆን፤ በቂ የመኪና ማቆምያ ቦታም ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሆቴሉ የራሳቸው ማብሰያ ክፍሎች ያላቸው ሰፋፊ ምቹና ዘመኑ ያፈራቸውን መገልገያዎች የያዙ መኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ለየት የሚያደርገውም የፔንት ሃውስ ክፍል ምርጫ ያለው ነው ተብሏል፡፡
የባህል ምግብ አዳራሽ፣ የመዋኛ ሥፍራና የሰርግ ስብሰባ አዳራሾች ያካተተው ሽታዬ ስዊት ሆቴል፤ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡
በሆቴሉ የምረቃ ሥነስርዓት  ላይ ለአባት አርበኞች ምስጋናና ዕውቅና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

አንድ ንጉሥ አንድ ብልህ አጫዋች ነበራቸው። በየጊዜው ከሚመክራቸው ምክር መካከል ሰሞኑን የነገራቸውን ለመቀበል ከብዷቸዋል። ሰሞኑን የመከራቸው “ከወዳጆችዎ ይልቅ፣ ስለርስዎ ድክመት ዕውነቱን የሚነግሩዎ ጠላቶችዎ ናቸውና አዳምጧቸው” የሚል ነበር። ንጉሡ አላመኑበትም። ስለዚህ ለማረጋገጥ መዘዋወር ጀመሩ።
ንጉሡ በጣም የሚፈሩና አይበገሬ ነኝ የሚሉ ናቸው። በሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚያገኟቸውን መኳንንቶች “እስቲ ስለ እኔ ጉድለት ንገሩኝ?” ይሉና ይጠይቃሉ።
“ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ላይ እንዴት አይነት ሰው ነው ጉድለት ሊያገኝ የሚችለው። ደግሞ እርስዎ ምን ይወጣልዎታል!” ይሏቸዋል።
ቀጥለው ወደ ሠራዊታቸው ይሄዱና፤
“ምን እንከን አለብኝ? እስቲ ስለራሴ ንገሩኝ?” ይላሉ።
ከሠራዊታቸው ታማኙ ባለሟል ብድግ ብሎ፣
“ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ከቁመናዎ ጀምሮ፣ ለጀግንነትዎ፣ ለዕውቀትዎ፣ ለዓለም ተደማጭነትዎ ምን የሚቀነስ የሚወጣልዎ ነገር አለብዎ!” ይላቸዋል። እንዲህ ከርመው አንድ ቀን በአጋጣሚ ከጠላቶቻቸው ጋር በሚሲዮን ይቀመጣሉ። አጠገባቸው የተቀመጠው ቀንደኛው ባላንጣቸው ቀስ ብሎ፤
“ስሙ ንጉሥ፤ ሲናገሩ አፍዎት መጥፎ ጠረን ያመጣል” ይላቸዋል።
ንጉሱ ይናደዳሉ። “እንዴት እስከዛሬ አንድ ወዳጄ ይሄን አልነገረኝም? እንዲህ በአደባባይ እንድጋለጥ ያደረጉኝ ወዳጆቼ ናቸው! ቆይ ግድ የለም! ባልሰራላቸው!” ይላሉ በሆዳቸው። ስብሰባውን እንደጨረሱ ሲገሰግሱ ወደ ቤተ-መንግስታቸው ይሄዱና ንግስቲቱን አስጠርተው፤
“አፌ ጠረን እንዳለው እስከዛሬ ያልነገርሽኝ ለምንድን ነው?” ሲሉ በቁጣ ጠየቁ። ንግስቲቱም፤ በንፁህ ልቦናና በቀናነት፤
“ንጉሥ ሆይ! የሁሉም ንጉስ አፍ እንደ እርስዎ አፍ አይነት ሽታ ያለው መስሎኝ ነው” ሲሉ መለሱ።
ንጉሡም እጅግ የቅርባቸው የሆነችው የገዛ ባለቤታቸው ጉድለታቸውን ሳትነግራቸው፤ ሩቅ የሚኖሩት ጠላቶቻቸው ማወቃቸውን ልብ ሲሉ፤ ያ አስተዋይ አጫዋቻቸው የነገራቸው ቁም ነገር እውነት መሆኑን ተገነዘቡ።
***
ማንኛውም መሪ፣ በማንኛውም ደረጃ ያለ ቢሆን፤ አንድ ሀቅ ልብ ማለት አለበት። ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ መሪ፤ ከወዳጆቹ የሚጠብቀው ምንጊዜም ምስጋናን ስለሆነ ጉድለቶቹን የማየትም የመስማትም እድል አያገኝም። ወገኖቹም አይደፍሩትም። እሱም ራሱን አይደፍርም። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሁሌ በሰላም ጊዜ በሆነ ባልከፋ። ሁኔታዎች በውጥረትና በችግር በሚሞሉበት ሰዓት ሲመጣ ነው አደጋው። ምክንያቱም የሁኔታዎች መወሳሰብን ተከትለው ሰዎችም ይለወጣሉና ነው። ችግሩ ግን በዚህ ብቻ አያቆምም። መሪውን መስለውና አክለው ማደግ ሲመኙ የቆዩ ባለሟሎቹና ተከታዮቹ አለማዳመጥ ሰናይ ስነምግባር እየመሰላቸው እነሱም እኩዮቻቸው የሚሉትን አልሰማ ይላሉ። በዚህ ምክንያት ካለመደማመጥ አልፎ፣ የሚፈጠረውን ጩኸት ለመገደብ ካለመቻል ደረጃ ይደረሳል። በየመንበራቸው እንደተቀመጡ በየራሳቸው ደሴት ውስጥ ይዋጣሉ። ውለው አድረውም የታችኞቹ በላይኞቹ ላይ ቅያሜን ያጠነክራሉ። ቀስ በቀስ በተለይ የመረረ የመከፋት ስሜት ውስጥ በገቡ ጊዜ፤ እንደ ሮማው ካሽየስ፣ ባለቃው ላይ ማሴርን፣ ራስን እንደማዳን ሲቆጥሩ፤ ከላይ ወደ ታች ይወርዱ የነበሩ ትእዛዛት ወደ ጎንም፣ ወደ ይም እንዲያመሩ ሲፈለግ፣ ለወትሮው የአለቃውን ድክመት ሁሉ የእኔ ነው እያለ አሜን ይል የነበረው ሁሉ፣ ድርሻ ድርሻችንን እንውሰድ በሚል፤ ሌላውን ማነሳሳትና ብሶቱን ሌላው ላይ ማጋበቱን ይያያዘዋል። ይሄኔ እንደ ሮማው ብሩተስ ያለው በትዕግስት የሚያገኘውን ስልጣን ቄሳርን በማስወገድ ሊፈጽመው እንዲሻ ሲተነኮስ፣ ወይም ሲወነባበድ፣ ነገር የተገላቢጦሽ ይሆናል። ቄሳር በመሞቻው “አንተም ብሩተስ?” ያለበት ሰዓት የሚመጣ እንግዲህ ያኔ ነው።በተለይ ስልጣንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመጋራት ልምድ በሌለበት እንደ እኛ ባለው አገር ብርቱ ጥንቃቄ የሚጠይቀው፣ በወንበሩ ዙሪያ አስፈላጊ ትዕግስትና መቻቻል አለመኖር ነው። መተማመን እንዲኖር ሀሳብን መግለጽ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ነጻነቱ አስፈላጊ ነው። ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት በሀቅና ከልብ ካልታመነበት፤ “ለብ ለብ ዲሞክራሲ” “ገባ ያለው ዲሞክራሲ” እና “ስፔሻል ዲሞክራሲ” እያልን እንድንከፋፍል ልንገደድ ነው። “አካሄዱ ፍጻሜውን ያሳያል” እንዳንል፤ አባይን ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲህ አላምነውም፤ የሚሉ ወገኖች ይሟገቱናል። የለም “ግቡ አካሄድን ያሳያል” - የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው ነው ነገሩ- ለሚሉት ደግሞ ካልታዘልኩ አላምንም፣ ስንቱ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ አይደል ወይ መላው የጠፋው የሚሉ ይኖራሉ። ሁኔታዎችን አጣጥመን መጓዝ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው። የሚያግባባንን መንገድ ከንፍቀ-ክበባችን ውጭም ቢሆን ማዳመጥ፣ ከባላንጣዎቻችንም ቢሆን መማር፣ ሁሌ ከመተላለፍ አንዳንዴ “ምን ይሆን?” ብሎ ለሌሎች ሀሳብ ትንሽ እድሜ መለገስ፤ ቀስ በቀስ ግትርነታችንን ሊያረግበው ይችላል።
አለንልህ ያልነውንና በእርሱም ትከሻ ለስልጣን የበቃንለትን፣ ከቀን በኋላ ከእርሱ እጅ የማንወጣውን ህዝብ ማዳመጥ እንደሚኖርብን እንድናስብም ፋታ ይኖረናል።
ስለሌላው ውሸት እንጂ እውነት በተናገርን ቁጥር፣ ስለሌላው ድክመት እንጂ አንድ አንኳር ጥንካሬ እንኳን ባነሳን ቁጥር፣ እኛ ብቻ ሀቀኛ፣ እኛ ብቻ ጠንካራ እያልን እንገበዛለን። ይህ ደግሞ ስለራሳችን እውነተኛ ገጽታ እናዳናውቅ ያደርገናል። የእኛኑ ቅኝት የሚያዳምጡ ወገኖቻችንና ደጋፊዎቻችን እውነተኛ ይዘትና ቅርጻችንን አይነግሩንም።
ስለዚህ ከእኛ ውጭ የማዳመጥ ባህል ማዳበር ደግ ነገር ነው- ከ”ጥላትም” ሰፈር ቢሆን። አበው “ክፋትህና ውሸትህ ሲጠፋብህ፤ ጠላትህን አስታውሰኝ በለው” የሚሉት ይሄንኑ ሊያስገነዝቡን ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአገራቱ ስምምነት እንቅልፍ እንደማይነሳት ገልፃለች
- በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ

ሶማሊያ በቅርቡ ከቱርክ ጋር የፈፀመችውና የሶማሊያ ፓርላማ ሰሞኑን  ያጸደቀው ወታደራዊ ስምምነት፣ ለአጎራባች አገራት በተለይም ለኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት እንደሚጋርጥ ምሁራን ገለፁ። በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነቱ የተፈረመው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ፣ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ በገባች  ማግስት መሆኑ ደግሞ ስጋቱን የባሰ ያደርገዋል  ተብሏል።
ለ10 ዓመታት እንደሚዘልቅ በተነገረለት በዚህ ወታደራዊ ስምምነት፣ ቱርክ ለሶማሊያ የባህር ሃይል ሥልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ ተዘግቧል።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ የተፈረመውን ስምምነት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ቁጥራቸው በውል ያልተገለጹ የቱርክ የባሕር ኃይል መርከቦችና ወታደሮች በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ውስጥ ሆነው ለአገሪቱ ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ የሶማሊያ ባሕር ኃይልን መልሶ የማደራጀት ሥራም እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።
 “የቱርክ ወንድሞቻችን በስምምነቱ መሰረት፣ ባህሮቻችንን ለ10 አመታት ይጠብቃሉ፤ ከ10 አመት በኋላ ጠንካራ የባህር ሃይል እንፈጥራለን” ብለዋል-ፕሬዚዳንቱ።
የስምምነቱ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም ቱርክ የሶማሊያን ባህል ሃይል በማሰልጠን የምታስታጥቅ ሲሆን የሶማሊያን የባህር ጠረፍም ለመጠበቅም የራሷን ባህር ሃይል በአካባቢው ታሰማራለች ተብሏል። ስምምነት   በቅርቡ ከአገሪቱ ጋር ውዝግብ ለገባችው ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት እንደሚፈጥር የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ። የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ያለባትን  ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት ዕድል ባላገኘችበት በዚህ ወቅት   ሌላ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ መግባቷ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉ ተችተዋል።  በተለይ  በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ባጠላበት በአሁኑ ወቅት፣  አገሪቱ ከቱርክ መንግስት ጋር የፈጸመችው ወታደራዊ ስምምነት ስጋቱን ይበልጥ የሚያባባስ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለው የመግባቢያ ሠነድ መፈረሙን ተከትሎ፣ በሶማሊያና በሶማሊላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው የጠቆሙት ዶ/ር አንተነህ፤    በተለይም  የሶማሊላንድ  ሁለተኛ  ትልቋ   ከተማ በሆነችው ቦርኦ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ   የአካል ጉዳት ለማድረስ፣ ንብረት ለመዝረፍና፣ ቤታቸውን በእሳት ለማቃጠል ሙከራ ተደርጓል  ብለዋል። በሶማሊኛ ቋንቋ “ኢትዮጵያዊ ላይ በተገኘበት እርምጃ ይወሰድበት” የሚል አደገኛ በራሪ ጽሑፍ በሐርጌሳ ከተማ እየተበተነ መሆኑን ተናግረዋል-ወቅቱ  በሶማሊላንድ ለሚገኙ ወደ 50 ሺ የሚጠጉ  ኢትዮጵያውያን እጅግ አደገኛ መሆኑን በመግለፅ።ይህ በእንዲህ እያለ፣  የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ተፈጻሚ መኾኑ እንደማይቀር ለአገራቸው መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። “ሶማሊያ ቱርክን ወይም ግብጽን አጋሯ አድርጋ ብታመጣም፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም፤ “ሶማሊያና ቱርክ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን መግባቢያ ስምምት ሊጎዳ አይችልም” ብለዋል።
“ሶማሊያም ሆነች ቱርክ ሉአላዊ አገር ናቸው፤ የፈለጉትን ስምምነት ከየትኛውም አገር ጋር የማድረግ መብት አላቸው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አላት፤ ይህ ወታደራዊ ስምምነት እንቅልፍ አይነሳንም” ብለዋል።

ወመዘክር አዲስ ያስገነባውን ህንፃ የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል

•  የተቋሙ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓልም ይከበራል ተብሏል

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ያስገነባውን ባለ 13 ወለል የቤተመዛግብት ሕንጻ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚያስመርቅ ተገለጸ።

ከህንፃው ምርቃት ጎን ለጎንም ተቋሙ የተመሰረትበት የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓልም በአንድ ላይ ይከበራል ተብሏል፡፡

እነዚህን ሁነቶች ምክንያት በማድረግ በተቋሙ ተመዝግበውና ተጠብቀው የሚገኙና በሌሎች ተባባሪ ተቋማት እጅ የሚገኙ የጽሑፍ ቅርሶች አውደርዕይና ሌሎች ተቋሙን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ክንውኖች እንደሚካሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዝግጅቶቹ ከእሁድ የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለእይታ ክፍት እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡

አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ህልፈተ ህይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን ለወዳጆቹ እና ቤተሰቦቹ እንዲሁም አድናቂዎቹ መፅናናትን እንመኛለን።

Tuesday, 20 February 2024 00:00

"ዶቃ" አሸነፈ !!

በቅድስት ይልማ ተዘጋጅቶ በማህደር አሰፋ ፕሮዲዩስ የተደረገው ዶቃ ልብ አንጠልጣይ ፊልም "Los Angeles”ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው በፓን አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ተሳትፎ በ" Audience Choice Awards” አሸናፊ መሆን ችሏል::

በአፍሪካዊያን የጥበብ ስራዎች ላይ ትኩረትን ያደረገው ፓን አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ከ32 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ነው።

ቅድስት ይልማ ከአሁን ቀደም "ረቡኒ" ፣ "ታዛ" ፊልሞችንና "እረኛዬ" ድራማን ጨምሮ ከአስር በላይ ስራዎችን ለተደራሲያን ማቅረቧ ይታወሳል::


• በአማራ ክልል ትራክተር እንጂ ጥይት አያስፈልግም

• ይቅርታም ብለን ካሣም ከፍለን ቢሆን፣ እንታረቅ እንስማማ

• በምርጫ የሰጣችሁንን ሥልጣን በምርጫ ውሰዱት

-ሪፖርታዥ-

በትላንትናው ዕለት ከአማራ ክልል ተወካዮች ጋር በጽ/ቤታቸው የተወያዩት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በአማራና በኦሮምያ ክልል ነፍጥ አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ወገኖች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ሰላም ለማምጣት እንደሚፈልጉ ተናገሩ፡፡

አዲሱ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ ለሃይማኖት መሪዎችና ለአገር ሽማግሌዎች ባስተላለፉት ጥሪ፤ ”እባካችሁ በሰላማዊ መንገድ ገብቶ መነጋገር የሚፈልግ ሰው ካለ --ከየሰፈሩ አምጡ አወያዩና ይቅርታም ብለን ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን እንታረቅ፤ እንስማማ፡፡” ብለዋል፡፡

“ሰው መግደልና መዝረፍ የትም አያደርስም፤ መክራችሁ የሚመለስ ሰው ካለ በመመለስ እርዱን፤እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ለአማራ ክልል ተወካዮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተወክለው በውይይቱ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች በክልሉ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ፣ በመሰረተ ልማቶች ችግር፣ በግብርና ግብአቶች አለመሟላት፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በሌሎችም ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡

ከተወካዮቹ ለተሰነዘሩት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ስለ ታጣቂዎች፣ ስለ አማራ ተወላጆች የሥልጣን ድርሻ፣ ስለ ሃይማኖትና መንግስት ሚና፣ ስለ አንድነት ቤተ መንግሥት ፒኮክ ጉዳይ፣ ስለ ልማትና ሌሎች ሰፊ ጉዳዮች ተናግረዋል፡፡

የአማራ ተወላጆች ባለፉት 5 ዓመታት በአዲስ አበባ ላይ ያገኙት የሥልጣን ድርሻ ባለፉት 30 ዓመታት ኖሯቸው እንደማያውቅ የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ በኋላ የትኛውም ሥልጣን ለሁሉም ክፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ድሮ የአዲስ አበባ የሥልጣን ድርሻን በተመለከተ 25 ፐርሰንት ለኦህዴድ፣ 25 ፐርሰንት ለብአዴን፣ 25 ፐርሰንት ለህወኃት እና 25 ፐርሰንት ለደህዴን ነበር” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የፈለገ ቢያብጥ በአዲስ አበባ ላይ የአማራ የሥልጣን ድርሻ 25 ፐርሰንት ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“ዛሬ ግን ካላጋነንኩት አማራ በአዲስ አበባ ላይ ከ33–35 ፐርሰንት የሥልጣን ድርሻ አለው” ብለዋል፡፡

ከምክትል ጠ/ሚኒስትር ጀምሮ ደህንነት፣ መከላከያ፣ ውጭ ጉዳይ፣ አየር መንገድና ብዙ ተቋማት በአማራ ተወላጆች ሥልጣን ሥር መሆናቸውንም ጠ/ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የመንግሥት ሥልጣንን አስመልክቶ ያብራሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ሥልጣን በምርጫ ነው የሰጣችሁን፤ ስትፈልጉ በምርጫ ውሰዱት፤ ከኛ የተሻለ ካገኛችሁ ምረጡ፤ደሞ ታዩታላችሁ በምርጫ ህዝብ ሲወስን እንዴት እንደምናከብር፤ ጊዜው ሲመጣ ታዩታላችሁ” ብለዋል፡፡

ሥልጣን በአፈሙዝ ግን በፍጹም አይሞከርም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ፤ “እኛ ወታደሮች ነን፤ የአድዋ አርበኞች ልጆች ነን፤ ማንም በጉልበት ሊያሸማቅቀን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡በአማራና ኦሮምያ ክልል ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ “የኛ ፍላጎት በአማራ ክልል ያለውም ሸኔ በኦሮምያ ያለውም ሸኔ ህዝብ ከማገድ፣ ከማገት፣ ከመግደል፣ ከመጥለፍና ከመዝረፍ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ፣ ትጥቁን አስቀምጦ፣ ምርጫ ተወዳድሮ በሃሳብ አሸንፎ፣ እነሱ እዚህ መጥተው (ሥልጣን ላይ) እኛ እዚያ ብንቀመጥ ምንም ችግር የለብንም፡፡” ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ጥይት አያስፈልግም፤ ትራክተር ነው የሚያስፈልገው ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ እኛ ከናንተ ጋር በፍቅር ብቻ ነው መኖር የምንፈልገው፤ ከዚህ የተለየ አጀንዳ የለንም ብለዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ከተወከሉ ተሳታፊዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ሲቋጩ፤ “በትብብር እንሥራ፤ በምክክር እንስራ፤ አንናናቅ፤ እንተባበር፤ የሚሻለው እሱ ነው፤ከዚያ ውጭ ያለው ሃሳብ ጥፋት ነው፡፡” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

87ኛውን የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን በማስመልከት በሰማእታት ሀዉልት የአበባ ጉንጉን አኑረናል።
ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖች ሰማእታት!
የ87ኛው የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን ለማሰብ ነው የአበባ ጉንጉን ያኖሩት።
ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ኢትዮጵያ የዛሬ መልክና ቅርፅ የያዘችው የቀደምት አባቶቻችን በከፈሉት በደምና አጥንት ዋጋ ነው ብለዋል ።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ ከ87 ዓመት በፊት በፋሽስት ጣሊያን በግፍ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ሕይወት ያጡ ሰማዕታትን ስናስብ፤ የባለፈውን ታሪክ ብቻ በመዘከር ሳይሆን ያሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አባቶች እንዲማር ለማድረግ ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል ።