Administrator
“ፓርቲው እጃችን ላይ እየሟሟ ሲመጣ ለቀቅሁ”
(የኢዜማ የቀድሞ ዋና ጸሐፊ)
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣
የቀድሞ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ
ከሃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።
የለቀቁበትን ምክንያት ለፓርቲው ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ሲገልጹ፣
ከፓርቲው አቋምና አካሄድ ጋር “ባለመስማማታቸው” መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ አበበ ከአዲስ
አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከኢዜማ የለቀቁበትን ምክንያትና
ስለፓርቲያቸው በዝርዝር ያብራራሉ፤
ቀጣይ የፖለቲካ መዳረሻቸውንም
ያመላክታሉ እነሆ፡-
ከኢዜማ ለመልቀቅ ያስገደድዎ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
እንግዲህ ላለፉት አምስት ዓመት ከሶስት ወራት አካባቢ የኢዜማ ዋና ጸሃፊ በመሆን፣ ፓርቲውን ሳገለግል ነበር። መጀመሪያ የነበረውን የፓርቲውን ቁመና ስናይ፣ በጣም ጠንካራ የሆነ መዋቅር በመላ አገሪቱ ያለው፤ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ የሆነ መገዳደርን ያሳየ፣ ብዙ ዕጩዎችን በማቅረብ ከገዢው ፓርቲ ሁለተኛ ሆኖ ቀጥሎ የነበረ ፓርቲ ነው። በዚያ ውስጥ መዋቅራችንን ዘርግተን በደንብ በጥንካሬ ነው የተንቀሳቀስነው። ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ግን ፓርቲው ቀስ እያለ ለሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ወይም የሕዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙ እየቀነሰ መጣ። መዋቅሩም ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ፓርቲው በሚይዛቸው የተለያዩ አቋሞች ምክንያት ከፓርቲው እየተነጠለ ሲመጣ፣ እጃችን ላይ ቀስ እያለ እየሟሟ መምጣት ጀመረ። አንድ የሚገዳደር ፓርቲ መሆን አልቻለም። የመለሳለስ ባሕርይው ተከታዮችንም፣ አባላትንም እያሳጣው መጣ። ይህን ጉዳይ በብዙ መልኩ ብንሞክርም፣ ማስታረቅ አልተቻለም። ከመንግስት ጋርም አብሮ በመስራት ሂደት ውስጥ “ምንድን ነው ፓርቲው ያገኘው? አገር ምን ተጠቀመች? ፓርቲውስ ምን ተጠቀመ?” የሚለው መገምገም ነበረበት። መጀመሪያ እኛ ማድረግ የነበረብን ፓርቲውን ማቆም ነው። ፓርቲው ቆሞ፣ እንደ አገር ተገዳዳሪ፣ ተፎካካሪ ሆኖ በደንብ መውጣት የሚችል ፓርቲ መሆን አለበት። በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ብቻ በየአምስት ዓመቱ እየተመረጠ አይደለም የሚገዛው። ሕዝቡ ሲከፋው፣ ‘’ይኼኛውን ፓርቲ ስልጣን ላይ አውጥተን እንሞክረው” የሚል መሆን አለበት። ይህን መሆን አልቻለም። ከዚህ ይልቅ እያደር እንደበረዶ እጃችን ላይ መሟሟት ሲጀምር፣ ጉዳዩን ቆም ብለን ማጥናት አልቻልንም። ከዚህ መታደግ ስላልተቻለ፣ በዚህ ዓይነት መቀጠሉ የትም እንደማያደርስ ሳይ፣ በቃ -- እዚያ ውስጥ ጊዜዬን ማባከን አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ፓርቲውን ትቼ ወጥቼያለሁ።
ቅድም የጠቃቀሷቸው ነገሮች አሉ። ፓርቲው በጊዜ ሂደት የሕዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙ እየቀነሰ “መጥቷል” ብለዋል። ይህን አቅሙን በትክክል መቼ ላይ ነው እያጣ የመጣው?
ከምርጫው ማግስት በኋላ፣ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት ከተደረገ በኋላ፣ ቀስ እያለ ይህን አቅሙን እያጣ መጣ። ከመንግስት ጋር መስራት ሌላ፣ የሕዝብ ድምጽ መሆን ሌላ። ይህን ብለን ነው አብሮ መስራት የሚለውን ያኔ የተቀበልነው። “አብሮ መስራት” የሚለው ቋንቋ በደንብ መገምገም አለበት። ቅድም እንዳልኩህ ምንድን ነው ለፓርቲው የጠቀመው? አንደኛ ፓርቲው ማደግ መቻል አለበት። አስራ አራት ሚሊዮን አባል “አለኝ” ከሚል ፓርቲ ጋር ነው የምንገዳደረው። አስራ አራት ሚሊዮን ማለት አንድ ሶስተኛ ወይም አንድ አራተኛ መራጭ ሕዝብ ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋር የሚገዳደር ፓርቲ የራሱን መዋቅር እየዘረጋ፣ 547 መቀመጫዎችን ጭምር ሸፍኖ፣ ስራ መስራት ሲገባው፣ በዚህ ደረጃ እጁ ላይ ያለውን መዋቅር ጭምር እስከ ማጣት ድረስ ቁልቁል መውረድ “ምንድን ነው ተስፋው?” የሚለው ነገር በጣም ነው ጥያቄ የሚፈጥርብኝ። ታግለህ ለውጥ የማታመጣ ከሆነ፣ ታግለህ ልዩነት ፈጥረህ ለሕዝብ ድምጽ መሆን የማትችል ከሆነ፣ ነገ ወደ ስልጣን የመምጫው መንገድ በየቀኑ እየጠበበ የሚመጣ ከሆነ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ …ተቃዋሚ ብቻ መሆኑ? ይሄ ደግሞ ሞልቷል በጣም! በዚህ መልኩ የሚቃወሙ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት። አማራጭ ይዘን የምንቀርብ አለመሆናችን በጣም ነው የሚያሳዝነው።
ወደ እርስዎ ስንመጣ፣ ኢዜማ በሚከተለው የፖለቲካ አካሄድ መቼ ነው አመኔታዎን የቀነሱት? በምን ምክንያት?
ይህን ነገር ማሰብ ከጀመርኩ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ይሆነኛል። ከአምና ጀምሮ ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም። ይሄ ነገር በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ የእኔ ከዚህ ፓርቲ ጋር መቀጠሌ “እስከ ምን ድረስ ነው?” የሚል ጥያቄ በውስጤ አነሳለሁ፤ ብዙ ጊዜ። ብዙ የምቀርባቸው ሰዎች ትንሽ እንድቆይ ይገፋፉኝ ነበር። ነገር ግን በየጊዜው የማያቸው ነገሮች -- አንደኛ ፓርቲው ቀድሞ ከነበረው ወደ 4 መቶ የምርጫ ክልሎች አካባቢ መዋቅር ዘርግተን እንንቀሳቀስ ነበር። ዛሬ ግን ያ የለም። ጭራሽ ቁልቁል ነው የሄደው። የቀሩትን አይደለም ለመድረስ፣ ያሉትንም ከእጃችን እያጣን ነው። የሸፈንናቸው አካባቢዎችን ጭምር … በጣም ነው የሚያሳዝነው … በየጊዜው አባላት እየቀነሱ እና እየጫጩ ነው የመጡት። መዋቅሩ ችግር ውስጥ ሲገባ እየተመለከትኩ ነው። ይህንን ቆም ብለን ገምግመን፣ “ምንድን ነው ችግሩ?” ብለን፣ ችግሩን ለይተን መስራት ነበረብን። ይህን ማሰራት የሚችል ነገር የለም። “ከመንግስት ጋር አብሮ መስራት” የሚለውን ነገር መገምገም አለብን። “በመስራት የተገኘው ጥቅም ምንድን ነው?” ማየት መቻል አለብን። የጎዳን ነገር ካለ፣ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል። “እንዴት ነው ከመንግስት ጋር እየሰራን ያለነው? በምን ያህል ፍጥነት እየሄደ ነው? ስንት ቦታ ነው የምንሰራንው? ምን ያህል ሰው ነው ሃላፊነት ላይ ያለው? ስንት ክልሎች ላይ ነው የምንሰራው?” -- ይህን በደንብ ተገምግሞ ቆም ብለን በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ማሰብ ነበረብን። ይሄን ማድረግ አልቻልንም። እንዴት አንድ ፓርቲ በየዓመቱ ያለውን ውድቀት እና ከፍታ አይፈትሽም? መቼም ኢዜማ በሰነድ አይታማም። የያዘው አቋም፣ ያለው ፕሮግራም በጣም አመርቂ ነው። ማኒፌስቶዎቹ በጣም አጓጊ ናቸው። የዜግነት ፖለቲካን በመስበክ እንደኢዜማ ዓይነት ፓርቲ የለም። በጣም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ነገር ግን ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ፣ ማኒፌስቶውን እና ፕሮግራሙን ብቻ እያደነቅን መኖር አያስኬድም። መተግበር አለበት። ሁለተኛ በአንድ ወቅት የነበረህን ድጋፍ እያጣህ ትመጣለህ። የአንድ ፓርቲ ትልቁ ሃላፊነት ለምርጫ ከመወዳደር ባሻገር፣ ገዢው ፓርቲ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ዕለት በዕለት፣ እግር በእግር ተከትለህ እየነቀስክ ማጋለጥ ነው፤ ትልቁ ነገር። ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች የተወሳሰበች አገር ነች። ችግሮቿ ፖለቲካዊ ናቸው። የመንግስትን አካሄድ እየነቀስክ አውጥተህ መንቀፍና እንዲያስተካክል መታገል አስፈላጊ ነው የሚሆነው። ዝም. . .ዝም የምትል ከሆነ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ? ሕዝቡ. . .በየጊዜው እየጠላን. . .እየራቀን. . .ድጋፉን የሚሰጠን እያጣን ሲመጣ፣ የራሱ አባላት እና አመራሮች ለቅቀው ሲሄዱ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ? ይሄን ማስተካከል አልተቻለም።
እንግዲህ እርስዎ በፓርቲ አመራር ላይ እያሉ፣ ሌሎች ቀድመው ፓርቲውን ለቀዋል። የእርስዎና የእነሱ የመልቀቅ ሰበብ ይለያያል?
የሁለታችን አለቃቀቅ ይለያያል እኮ! እነርሱ የለቀቁት ፓርቲው የመጀመሪያውን ጉባዔ አድርጎ፣ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሲያደርግ ነው። ምርጫው ላይ ተወዳድረዋል። መሪም፣ ሊቀ መንበርም ለመሆን። በዚያ ሂደት ውስጥ አልፈውበት ሄደዋል። ከዚያም በኋላ፣ ለወራት ያህል ከፓርቲው ጋር ቆይተዋል። እኔ ግን በዚያ ሰዓት ላይ በምርጫው ተሳትፌ፣ የያዝኩትን ቦታ እንደያዝኩ በከፍተኛ ድምጽ ተመርጬ አልፌ ነው የመጣሁት። የእነርሱ አለቃቀቅ እና የእኔ አለቃቀቅ አይገናኝም። “ለምን አንድ ላይ አልሆነም?” ለሚለው፣ ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም። ስለዚህ ያንን ማነጻጸር አይቻልም። በመሰረቱ፣ እኔ ሰውን ተከትዬ አልወጣም። በራሴ ጊዜ ነው። “ዘግይተሃል” የሚለውን አልቀበልም። “ከአሁን አሁን ይሻሻላል” የሚል ዕምነት ነበረኝ። በተለይ፣ ሁለተኛው ዙር ምርጫ ከተደረገ በኋላ፣ የነበረው መገፋፋት ይቆምና ፓርቲው በደንብ ተጠናክሮ ይወጣል የሚል የጸና አቋም ነበረኝ። ይህንን ደግሞ መጠበቅ ግድ ነው የሚለው። እርሱን ጠብቄያለሁ። እኔ ያሰብኩት ሃሳብ ባለመሳካቱ፣ “ዘግይቼያለሁ” ብዬም አልቆጭም። የወጣሁበት ተገቢ ሰዓት ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ የእኔ አወጣጥ ከእነርሱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። አሁንም ማንም “ውጣ” ብሎ ያስገደደኝ የለም። በዚህ ዓይነት መቀጠል እንደማልችል ሳውቅ፣ በፈቃዴ ነው ሃላፊነቴን የለቀቅኩት።
አንዳንድ ወገኖች “ኢዜማ የገዢው ፓርቲ ተላላኪ እንጂ ራሱን የቻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ፓርቲ አይደለም” የሚል ፍረጃ ያቀርባሉ። እንደ አንድ የቀድሞ አመራር ይሄን ፍረጃ እንዴት ይመለከቱታል?
በዚህ ደረጃ ፓርቲውን ማውረድ ጥሩ አይደለም። ብዙዎች ‘ተለጣፊ’ የሚል ስያሜ ይሰጣሉ። ከዚህ አንጻር ይህን ያስባለን አብሮ መስራት የሚለውን በግልጽ ለይተን መጠቀም ስላልቻልን ነው። የቱ ጋ ነው አብረን የምንሰራው? አገርን ከማልማት እና ሰላምን ከመጠበቅ አንጻር? የቱ ጋ ነው የምንቃወመው? የሚለውን ለይተን ባለመንቀሳቀሳችን የተፈጠረ ነው፤ ይህ ስያሜ። አንዳንዴ ሕዝቡ እንደዚህ ቢለን አትፈርድበትም። ስለዚህ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው የሚሆነው።
ያኔ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ጉዳይ እንደአጀንዳ ሲቀርብ፣ እርስዎ እንደደገፉት ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ የድጋፍ ድምጽ በመስጠትዎ የመጸጸት ስሜት ይሰማዎታል?
ምንም አልጸጸትም። እኔ ብቻ አይደለሁም። ለቅቀው የወጡት፣ እነ አንዱዓለምም -- እነ የሺዋስም -- በስራ አስፈጻሚም፣ በጉባዔው ላይም ደግፈነዋል እኮ፤ “አብሮ መስራት” የሚለውን ሃሳብ። ይህ ምንም ሊዋሽ አይገባውም። አብሮ መስራት ማለት እኮ ለዘላለም መጣበቅ አይደለም። ቆም ብሎ አስቦ የማያሰራ ጉዳይ ካለ፣ ገምግሞ ለቅቆ መውጣት ይቻላል። በወቅቱ ያንን ውሳኔ መወሰናችን ስሕተት አልነበረም። ስሕተቱ እኛ ጋ ነው። እኛ ያንን ገምግመን “ምን ላይ ደርሷል?” ብለን፣ የምንወጣ ከሆነ ገምግመንና ጉዳቱ ካመዘነ በጉባዔ አስወስነን ለቅቆ መውጣት ይቻላል፤ “አብሮ መስራት አያስኬደንም” ብለን። የእኔ ጥያቄ “ለምን መገምገም ተሳነን?” የሚል እንጂ የተወሰነውን ውሳኔ ሁላችንም ተስማምተን የወሰንነው ነው። በዚህ ቅር አይሰኝም። ያኔም ትክክል ነበርኩ፤ አሁንም ትክክል ነኝ። የተቃውሞ ሃሳባችን ለመግለጽ አያግደንም። ምክንያቱም በርካታ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር አብረው እየሰሩ፣ የሕዝብ ድምጽ ሲሆኑ እንሰማቸዋለን።
መጀመሪያ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (አንድነት)፣ በኋላም ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ነበሩ። አንድነት ሲፈርስ፣ እርስዎና ጓዶችዎ ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ገብታችሁ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያለው የእርስዎን የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ “ንግግራቸውና ተግባራቸው አይገጥምም የሚሉ ወገኖች አሉ። የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ራስዎን እንደ አንድ ፖለቲከኛ እንዴት ይገልጡታል?
እኔ የኢዜማ መዋቅሮችን ድምጽ የምሰማ፣ አባላቱ እና አመራሮቹ በሚገባ የሚወዱኝ፣ ድምጽ መሆን የሚገባኝ ቦታ ላይ ለእነርሱ ድምጽ የምሆን፣ በግሌ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሃላፊነትን ሳላይ የማገለግል፣ አንዳንዴም አስቸጋሪ ነገር ሲመጣ፣ በዚህ ዕድሜዬ ቢሮ አድሬ የማገለግል ነበርኩ። ለነፍሴ ሳልሳሳ በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከአዲስ አበባ እስከ አርሲ -- ሲሬ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ይርጋጨፌ ድረስ፣ ትልቅ ስራ ስሰራ የቆየሁ ሰው ነኝ። ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ ነገር ሆኖ፣ ምናልባት ቃል ገብተንላቸው ያልተሳካ ነገር ካለ፣ እኔ ብቻ ሳልሆን በጋራ ነው የምንጠየቀው። በግሌ የማደርገው ነገር ስለሌለ ማለት ነው። የጋራ አመራር ነው ያለው። አንድነት ፓርቲ ውስጥ በቆየሁበት አጭር ጊዜ በጣም በርካታ ስራዎችን ሰርቼ፣ ፓርቲው ሲፈርስ ዕንባ አውጥቼ አልቅሼ፤ በወቅቱ የታሰሩ የትግል ጓዶች ስለነበሩ፣ እነርሱን ጥለን ቤት አንቀመጥም ብለን ነው ሰማያዊን የተቀላቀልነው። የነበረው አማራጭ ሰማያዊ ፓርቲ ብቻ ነው። እዚያም የራሴን የትግል አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። መክፈል የሚገባኝን … ትብዛም፣ ትነስም …መስዋዕትነት ከፍያለሁ። ከዚህ አንጻር እኔ ቃል ገብቼ ያልተሰሩ ስራዎች ካሉ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ቢነገረኝ፣ ደስ ይለኛል፤ በደፈናው ከሚሆን።
አሁን ላይ -- ከኢዜማ ለቅቆ እንደወጣ አንድ ፖለቲከኛ … ፓርቲውን በሩቁ ሲመለከቱት፣ ምንድን ነው የሚሰማዎ? ለራስዎ ስለፓርቲው ምን ይነግሩታል?
ገና አስረኛ ቀኔ ነው ትቼ ከወጣሁ። እየሰራኋቸው ያሉ ስራዎች አሉ። በደንብ አድርጌ የማነብባቸው ነገሮች አሉ። የምፈትሻቸው ነገሮች አሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ አንድ የራሴን አስተያየት ስለኢዜማ እሰጣለሁ። ፓርቲው ተጠናክሮ ቢወጣ ደስ ይለኛል። ምንም ጥርጥር የለውም። የሚቀጥለው ትውልድ ተክቶት ቢሰራ፣ ጥሩ ፕሮግራም አለው፤ ጥሩ ማኒፌስቶ አለው። ራስን አጠንክሮ፣ ድክመትን ፈትሾ መውጣት ነው።
ቅድም ያነሷቸው የፓርቲው ሳንካዎች አሉ። እነዚያን ፓርቲው አርማለሁ ቢል፣ እርስዎ ወደ ኢዜማ ይመለሳሉ?
እኔ ከዚህ በኋላ፣ ወደ ኢዜማ አልመለስም። ጓዜን ጠቅልዬ ነው የወጣሁት። ከአባልነትም፣ ከአመራርነትም ነው ራሴን ያገለልኩት። ነገር ግን እኔ ካልበላሁ፣ ጭሬ ላጥፋው አልልም። የሚቀጥለው ትውልድ እኔ የምነግርህን ድክመቶች. . .አሁን አልተናገርኋቸውም፣ ወደፊት የምናገራቸውን አርሞ የሚወጣ ከሆነ፣ በጥንካሬው በጣም ደስ ይለኛል። ቅር አይለኝም። ትልቅ አማራጭ ፓርቲ አድርጎ ማውጣት ተገቢ ነው። “ለምን እኔ አልኖርኩበትም?” ብዬ አልቆጭም።
ከዚህ በፊት የጠቀሱልኝን ድክመቶች በሚመለከት፣ እርስዎ ያደረጓቸው የውስጠ ፓርቲ ትግሎች ነበሩ?
የጎንዮሽ ፍትጊያውን ሳልፋተግ፣ ዝም ብዬ አልወጣም። ስላልቻልኩ ወጥቼአለሁ። ሃይሌን መጨረስ የለብኝም ብዬ ነው የወጣሁት። ወደፊት እርሱን እገልጸዋለሁ።
በእርስዎ የቀድሞ የትግል አጋሮች “የንጋት ኮከብ” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ እየተቋቋመ ነው። ስለዚህ ፓርቲ መረጃ ነበረዎ? ወይስ እንደማንኛውም ሰው ነው የሰሙት?
እኔ እንደማንም ሰው ነው የሰማሁት። የእኔ ጉዳይ ከእነርሱ ጋር የሚነካካ አይደለም። አማራጭ ፓርቲ መመስረት ካስፈለገ፣ መመስረት ነው። እኔ ግን በግል ዕይታዬ ተፈልፍሎ ያለ ፓርቲ ብዙ ነው። አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ እንደገና ከዜሮ መጀመር ከባድ ነው። ያሉትም በዝተዋል። እንመሰርታለን ካሉ ደግሞ መብታቸው ነው። እኔ ምንም መረጃው የለኝም። በቀለ ይኑርበት ከበደ፣ አንዱዓለም ይኑርበት የሺዋስ ምንም የማውቀው ነገር የለም።
ለመቀላቀል ሃሳብ የለዎትም?
አዲስ ፓርቲ በተመሰረተ ቁጥር እያንኳኳሁ አልሄድም። እንዲህ ዓይነት ሱሰኛም አይደለሁም።
ስለዚህ አቶ አበበን በምን እንጠብቃቸው? ከዚህ በፊት መምሕር እንደነበሩ ሰምቼአለሁ። በእንጨት ስራ ላይ ሞያ እንዳለዎ ይታወቃል። በፖለቲካ ውስጥም እንቅስቃሴ አድርገዋል። እና፣ እርስዎን በምን እንጠብቅዎ?
እኔ በፖለቲካ ዕንቅስቃሴ ውስጥ እቀጥላለሁ፤ በሚቀጥለው የሕይወት ዘመኔ። በኢትዮጵያ እኔ የማስበው ዓይነት ዴሞክራሲ እስኪሰፍን ትግሉን አላቆምም። ሰላማዊ ትግል ነው የሚያዋጣው። በአንድ የፖለቲካ ዕንቅስቃሴ ላይ መገለጥ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። እርሱም ሩቅ ላይሆን ይችላል። ከዚያ ውጭ ግን ደራሲ ነኝ። ራሴን ማሞገስ ስለማልፈልግ ነው። ሁለት ለሕትመት በቅተው እስከ ሶስተኛ ዕትም የደረሱ መጽሐፎች ነበሩኝ። “የሲዖል ፍርደኞች 1 እና 2” መጽሐፍት አሉኝ። እግዚአብሔር ቢረዳኝ፣ በሚቀጥለው ዓመት በተከታታይ ሶስት መጽሐፍትን አወጣለሁ፡ አንድ ያልታተመ፣ የአርትዖት ስራ የማከናውንበት ቀድሞ የተሰራ መጽሐፍ አለ። የስዕል እና የቅርጻ ቅርጽ ሞያዬ ከፍተኛ ነው። አሁን ወደዚያ አልመለስም። ሰው በስተርጅናው የሚሰራው አንድም ጽሁፍ ነው። ወደ ጽሁፍ ስራዎቼ እመለሳለሁ። አሁንም እየሰራሁ ነው ያለሁት። ከሰላማዊ ትግሉ አልሸሽም። ሚዲያ ላይ ሄጄ አንዳንድ አስተያየቶችን እየሰጠሁ ነው። የአገሬን የፖለቲካ ሁኔታ መተንተን፣ በእኔ የዕውቀት ደረጃ ያለውን ሁኔታ መግለጽ፣ መንግስት ሊያስተካክላቸው የሚገባቸውን ነገሮች መተቸት፣ ሰላማዊ ትግል እንዴት እንደሚያስፈልግ፤ በተለይ አሁን አገሪቱ ካለችበት ውጥንቅጥ ለመውጣት፣ አሁን የተያዘው የዕርቅ ጉዳይ ጠንክሮ እንዲወጣ ምክረ ሃሳብ አቀርባለሁ፤ እንደአቅሜ።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የተጻፈው ደብዳቤ ሕገ መንግስታዊ መብቶችን ይጥሳል ተባለ
ሰሞኑን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለመንግስት መ/ቤቶች የፃፉት ደብዳቤ፤ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን የሚጥስ ነው ሲሉ በትግራይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነቅፈዋል። ደብዳቤው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጭ ሰልፍና ስብሰባ ማካሄድ እንደማይፈቅድ ይገልፃል።
ከአዲስ አድማስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ኪሩቤል ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት፤ አቶ ጌታቸው ረዳ “ለክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የጻፉት ደብዳቤ፤ የመንግስት ሰራተኛን የሚመለከትና ስምንት ሰዓት የመስራት ግዴታ እንዳለበት የሚያስረዳ እንዲሁም የሕግ ጉዳዮችን የጠቃቀሰ ነው”፤ ሲሉ አስረድተዋል። አንድ ፓርቲ የመንግስት አዳራሽን በልዩ ሁኔታ መጠቀም እንደማይኖርበትም ይኸው ደብዳቤ እንደሚያብራራ ነው የተናገሩት።
የአቶ ጌታቸው ደብዳቤው የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሃሳብን የመግለጽ መብቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ እንደማይቀርና በሕግ ሰበብ የሚፈጠር ችግር ሊኖር እንደሚችል አቶ ኪሩቤል ገልጸዋል። “በደፈናው ስብሰባ እና ሰልፍ ‘አይቻልም’ ማለት አግባብነት የለውም። ፈቃድ የሚጠየቀው ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የጸጥታ እንከን እንዳይፈጠር ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው” ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሕዝቡ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተውጣጥቶ እንደሚቋቋም ቢገለጽም፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምስረታ ላይ ፓርቲያቸው አለመሳተፉን አቶ ኪሩቤል አስታውሰዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩን ምስረታ “የአንድ ፈረስ ግልቢያ ይመስላል” ሲሉ የነቀፉት አመራሩ፣ “ባንክ እና ታንክ የሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጸጥታ አካሉ ገለልተኛ እስከሆነ ድረስ መንግስት ለማቋቋም አቅም አያንሳቸውም፤ በዚህ ስጋት ምክንያት ነው ፓርቲዎቹን የሚደፈጥጧቸው።” ብለዋል።
“አሁን በፈጠሩት ሽኩቻ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት አንድ ናቸው። ህወሓት ብቻውን መንግስት ሊሆን አይገባውም። ሕዝቡን ከሚወክሉ ተቋማት ተውጣጥቶ ነው መንግስት መቋቋም ያለበት።” ብለዋል-አቶ ኪሩቤል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው ክፍፍል ጋር በተያያዘ ሁሉንም የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ክልላዊ መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ፓርቲዎቹ ጥሪውን ያቀረቡት፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ዋነኛ አደጋ “ሥርዓት የወለደው ስንፍና ነው” በማለት ነው። “አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሲታመም የማይታመም መንግሥት ያስፈልገናል። ይህም የሚሆነው ሁሉንም ድርጅቶች ያካተተ እና ሕዝብን ማሰለፍ የሚችል መንግሥት ሲቋቋም ነው” ብለዋል፤ ተቃዋሚዎቹ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጪ ሌላ ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል የሚያትተው የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ፣ “የኮሌራ በሽታ መከላከል፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር፤ እንዲሁም በጀት መዝጋትና በጀት ማዘጋጀት የመሳሰሉ ሌሎች ሕዝባዊና መንግስታዊ ዕቅዶች” የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሆናቸውን ይገልጻል። “ከዚህ ውጭ የሚደረጉ ሰብሰባዎች የተያዘውን ዕቅድ ስለሚጎዱ አይፈቀዱም” ይላል-ደብዳቤው።
“ወርቅ የማውጣት ስራ ኮሌራን ለመከላከል ተግዳሮት ፈጥሯል
በትግራይ ክልል፣ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገደ ወረዳ በስፋት የሚከናወነው ባሕላዊ የወርቅ ማውጣት ስራ የኮሌራ በሽታን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የኮሌራ በሽታ ስርጭት ከዕለት ተዕለት እየተባባሰ መምጣቱንም አክሎ አመልክቷል።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ በሪሁ ኪሮስ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ የኮሌራ በሽታ ስርጭት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰተዋለው ሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ላይ ሲሆን፣ ቦታውም ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገደ ወረዳ እንደሆነ አስረድተዋል። አያይዘውም፤ በሽታው እስከ አሁን ድረስ 24 ወረዳዎች ላይ ተስፋፍቷል ብለዋል።
“በጥቅሉ 221 በሽተኞች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 151 ያህሉ አገግመዋል። 5 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።” ያሉት አቶ በሪሁ፣ በሽታው መቐለ አንድ ቦታ ላይ መታየቱን ገልጸዋል። ይሁንና የሕሙማኑን ብዛት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አብዛኛዎቹ በሽተኞች በሰሜን ምዕራብ ዞን 11 ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ 204 ሰዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ 146 ያህሉ በሽተኞች አስገደ ወረዳ እንዳሉ ነው አቶ በሪሁ ያስረዱት።
“በአጎራባች ክልሎች በሽታው ይታይ ስለነበር፣ የቅድመ መከላከል ስራ ለመስራት ተሞክሯል።” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው፣ ይሁንና የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በአስገደ ወረዳ የሚከናወነው ባሕላዊ የወርቅ ማውጣት ስራ ፈተና መጋረጡን አልሸሸጉም። በወረዳው በባሕላዊ መንገድ የወርቅ ማውጣት ስራ በግላቸውም ሆነ በማሕበር የተሰማሩ ከ10 ሺህ በላይ ወርቅ አውጪዎች መኖራቸውን ሃላፊው አረጋግጠው፣ በወርቅ ማውጣት ስራ ላይ ምክንያት፣ እንዲሁም የወቅቱ ክረምት መሆን የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ተደራራቢ ፈተና መጋረጣቸውን ጠቁመዋል።
“የጤና ባለሞያዎች ወደ ስፍራው ሄደው፣ የውሃ ማከም እና ጄሪካን ማቅረብ እንዲሁም ትምሕርት የመስጠት ስራዎችን እየሰሩ ነው። ቢሆንም፣ ቦታው አስቸጋሪ ነው።” ያሉት አቶ በሪሁ፣ በጤና ጣቢያና በሆስፒታል ደረጃ ጊዜያዊ የማከሚያ ማዕከላት መቋቋማቸውን አመልክተዋል። ራቅ ባሉ ቦታዎችም ጊዜያዊ የሕክምና ቦታዎችን የማደራጀት ስራ፣ በተጓዳኝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“ከዕለት ወደ ዕለት በወረዳ ሽፋን እና በበሽተኛ ቁጥር ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል። ሱር የሚባል ወንዝ፣ የበሽታው ስርጭት መነሻ ነው። በሌላ በኩል፣ ጊዜያዊ መጸዳጃ ቤት ለመስራት ለሕብረተሰቡ ትምሕርት ተሰጥቶ ቢሰራም፣ በከባድ ዝናብ የተነሳ ይፈርሳል። ቢሆንም፣ እንደገና እየተሰራ ነው” በማለት ሃላፊው ተናግረዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው የጸጥታ ችግር ያለባቸውና በኤርትራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ቦታዎች መኖራቸውን አውስተው፣ ገልፀዋል በዚህም ለሕዝቡ በአፋጣኝ ለመድረስ አዳጋች የሆነበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል።
በማገዶ ጭስና ተቀጣጣይ ነገሮች የሚመጣ የሳንባ ካንሰር መስፋፋቱ ተጠቆመ
በማገዶ እንጨትና ተቀጣጣይ ነገሮች አማካይነት የሚመጣ የሳንባ ካንሰር መጨመሩን የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ባወጣው ጥናት አመልክቷል፡፡ “የሳንባ ካንሰር የተጋላጭነት መጠን በሴቶችና በወንዶች መካከል ተመጣጣኝ ነው" ብሏል - ጥናቱ፡፡
ብዙዎቹ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች ወደ ሕክምና ተቋማት የሚመጡት ዘግይተው መሆኑ ያመለከተው ጥናቱ፤ የሳንባ ካንሰር አራት ደረጃዎች እንዳሉትም ይጠቁማል፡፡ በመጀመሪያው የሳንባ ካንሰር ደረጃ ላይ የሚገኝ ታማሚ ወደ ሕክምና ተቋም ከመጣ፣ የመዳን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ በሦስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ከመጣ ግን የመፈወስ ዕድሉ ጠባብ ነው ይላል።
በአገራችን ከ90 በመቶ በላይ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች ወደ ሕክምና ቦታ የሚመጡት የመጨረሻዎቹ ሁለት ደረጃዎች ላይ ከደረሱ በኋላ መሆኑን የገለጸ ጥናቱ፤ በኢትዮጵያ የሳንባ ካንሰር ሕሙማን አማካይ ዕድሜ፣ ከሌሎች አገራት አማካይ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች አንጻር ወጣት መሆናቸው ተጠቁሟል። በዚህም 55 ወይም 56 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ ታማሚ እንደሚሆኑ ነው ጥናቱ ያረጋገጠው፡፡
ጥናቱ በማገዶ እንጨቶች፣ በከሰል፣ በኩበት ጭስና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች የሚመጣው የሳንባ ካንሰር አይነት እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል፡፡ ይሁንና የትኛው የማገዶ ዓይነት የሚለው ተጨማሪ ጥናት ይፈልጋል ተብሏል።
“የሳንባ ካንሰር በሲጋራ ጭስ አማካኝነት የሚመጣ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች ቁጥር ከ1 በመቶ በታች ሆኖ እያለ ለሳንባ ካንሰር ያላቸው ተጋላጭነት ግን ከወንዶች እኩል ነው" ሲል የኢትዮጵያ ቶራሲክ ማሕበር በጥናቱ አመልክቷል።
“ባለጋሪው አንበሳ” የልጆች መጽሐፍ ለገበያ ቀረበ
”የኢትዮጵያ ልጆች” ቴሌቪዥን ላይ በምትሰራው ደራሲ ገሊላ ተስፋልደት የተዘጋጀው “ባለጋሪው አንበሳ” የተሰኘ የልጆች መጽሐፍ ከሰሞኑ ለገበያ ቀርቧል፡፡
መጽሐፉ፤ ክፉ አለመሥራትን፣ መዋደድን፣ ተባብሮ መኖርንና ፍቅርን ለልጆች ያስተምራል ተብሏል፡፡
“ባለጋሪው አንበሳ”፣ ለደራሲዋ አራተኛ ሥራዋ ሲሆን፤ የበኩር ሥራዋ “አመለኛ ልጅሽ” የተሰኘ የግጥም መድበል ነው፡፡ ሁለተኛ ሥራዋ “አንበሳ እና ነብር” የተሰኘ የልጆች መጽሐፍ ነው፡፡
ሦስተኛው መጽሐፏ “እሽኮኮ አድራጊዋ ቀጭኔ” የሚሰኝ ሲሆን፤ ለልጆች መልካምነትና ደግነት መልሶ እንደሚከፍል ያስተምራል - ብላለች ደራሲዋ፡፡
"ሲቢኢ ብር ፕላስ" የአዲስ ዓመት ኤክስፖ በዛሬው ዕለት ተከፈተ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕይወቷን በግፍ ለተነጠቀችው ሕጻን ሄቨን እናት የመኖሪያ ቤት አበረከተ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕይወቷን በግፍ ለተነጠቀችው ሕጻን ሄቨን እናት የመንግስት መኖሪያ ቤት አበርክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ የሄቨንን እናት በማግኘት አጽናንተዋል።
ከንቲባ አዳነች፤ ልጇን በግፍ ተነጥቃ ባለፈው አንድ ዓመት ፍትሕ ሳታገኝ ለቆየችው እህታችን የፍትህ ሂደቱን ለመከታተል፣ ያለችበት ሁኔታ የተሻለ እንዲሆንላት እና ተጋላጭነቷን ለመቀነስ እንዲመች የከተማ አስተዳደሩ አንድ የመንግስት የመኖሪያ ቤት እንዲሁም በሙያዋ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እንድትሰራ መመቻቸቱን ተናግረዋል።
የሕፃን ሄቨን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ ድርጊቱ ተገቢውን ፍትሕ ማግኘቱ የሌሎች ሕፃናት ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስተዋፅዖ እንዳለውም ከንቲባዋ ገልጸዋል።
አያይዘውም፤የዚህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንዳይፈፀም የማህበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ እና ችግሩ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባልም ማለታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የሕይወት ቀለማት
በሁለቱም ጉንጮቻቸው እንባቸው ይወርዳል። ጣሪያው ላይ የተስፋ ችቦ ጨብጦ የሚያነድደው መልዐክ፤የተንጠለጠሉ የተስፋ አበባዎች፣የሉም። የሚታያቸው የገረረ በረሃ፣የነደደ ምድረበዳ ነው።ግን በጀርባቸው ተንጋልለው የሚያዩት ወደዚያ ነው።
በዚያ ላይ ግራና ቀኛቸው ተኝተው የሚያቃስቱ ሕመምተኞች ድምፅ ይበልጥ የነፍሳቸውን ዜማ እያመሳቀለው ነው።
ጉልበታቸው ከድቷቸዋል፤ ድሮ ጎረምሳ እያሉ አልጋውን ከነሰው መሸከም የሚችሉ ወጠምሻ ነበሩ። አሁን ግን አልጋቸው ሌትና ቀን ተሸክሟቸዋል።...ዘመን ንዶት ሁሉ ነገራቸው ተንጠፍጥፏል። የቀራቸው ጥቂት ተስፋ ነበር። እርሱም ሰሞኑን ዶክተሩ በተናገራቸው ቃል እንደ በጋ ደመና ሰማያቸውን አራቁቶታል። ድሮ ኀይል ነበራቸው፤
አሁን የቀራቸው እንባ ብቻ ነው። ዘመናቸውን ሁሉ ጠብ ያላለ እንባቸው አሁን ቀናቸው ሲንጠፈጠፍ ጉንጫቸው ማጠብ ጀምሯል።
“አንተ ኀይሌ” አሉ የተገረሙት ታናሽ እህታቸው።
መልስ አልሰጡም።
“ምን መሆንህ ነው?...በምድር ሕይወቴ ለእማዬ በስተቀር እንባዬ ፈስሶ አያውቅም አላልክም ነበር?”
እንባቸውን ጠራረጉ። የጉሉኮሷ ጠብታ ቀስ እያለች ወደ እርሳቸው ትንጠባጠባለች። የእርሳቸው እንባ ደግሞ ጉንጫቸው ላይ ብቻ ሳይሆን የልባቸውን ግድግዳ ታጥባለች። ደም በእንባ ይታጠብ ይመስል።
“አሁን ምን ይሁን ብለህ ነው የምታለቅሰው?”
ዝም።...ድሮም ብዙ አይናገሩም። ከተናደዱ ያናደዳቸውን ሰው በቴስታ ማፍረስ ነው። አሁን ግን እንባቸውን በአይበሉባቸው ያብሱና ሽቅብ ያንጋጥጣሉ።
“አታልቅስ፣ለራስህ አልቀሀል”
“እሺ”
“ምኑ ነው የሚያስለቅስህ?...ራስህን ጎዳህ እንጂ ለቤትህ ምን አጎደልክ?...በሽታ ላይ የጣለህ ልጆችህን ለማሳደግ ላይ ታች ያልክበት፣ለሀገርህ የሮጥክበት ነው።”
ሐኪሙ መጥቶ” አባቴ በሽታው መጨናነቅ አይወድድም፤ራስዎን ከጭንቀት ያውጡ”አላቸው። ራሳቸውን አንቀሳቅሰው መስማማታቸውን ገለፁ።
ግን ደስታቸው ጠፍቷል። እንዴት አድርገው ይችሉታል?...እኔ በልጅነቴ አባቴን በማጣቴ ያየሁትን አበሳ አልረሳውም አባት የሌለው ልጅ ቅጥር የሌለው እርሻ ነው፤ማንም ይፈነጭበታል፤ያለፈ ያገደመው ይረጋግጠዋል።” ሐሳባቸው ከአፋቸው አመለጣቸው።
“ልጆቼ ..እረኛ እንደሌለው መንጋ..”
አጎነበሱ እህታቸው።
“ይልቅ እባክህ ለራስህ አስብ”
“ተዪ በልጆቼ አትምጪብኝ፤ገና ብዙ ይቀራቸዋል።”
እህትዬው እንደመናደድ ቃጣቸውና ነገር ላለማክረር ዝም አሉ።
ውሎ ሲያድር፣ችግሩ እየባሰ፣ሕመሙ እየጠናባቸው መጣ። እንደ አባት ሳይሆን እንደ እናት፣ጡት የሚያጠቡትን ልጅ ጥለው የሚሄዱ ያህል አዘኑ። ስለዚህም እንደ መጸሐፍ ቅዱሱ ሕዝቅያስ ዕድሜ ጨምርልኝ ብለው አለቀሱ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ምህረትን ለመኑ።
“ልጆቼን ለወግ ማዕረግ ሳላበቃ፣ሳልድር ሳልኩል፣ሳላስመርቅ አትግደለኝ፤እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ በቸርነትህ ዕድሜ ቀጥልልኝ።” አሁን
አለቀሱ እህትየው። ወንድማቸው እንዲህ ለሞት የሚንቀጠቀጡ ፍርክርክ አልነበሩም። ጀግና ነበሩ። በስንት የጦር ግንባር፣ስንት ሺህ ጦር ሲመሩ አንድ ቀን ለሞት በርግገው አያውቁም። ዕድሜ ልካቸውን ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸውም በዚህ እንደተደነቁ ነበር።
አሁን ግን ዘግይተው የወለዷቸው ልጆቻቸው ሞትን በጦር ሜዳ ደፍረው፣በመኝታ ላይ እንዲፈሩት ድፍረታቸውን ነጠቁት።
“የወለደ፣አልጠደቀ”አሉና በነጠላቸው ጫፍ እንባቸውን አበሱ።
“ለዛሬ ልጆች ይህን ያህል መጨነቅ!” አሉና ዝም አሉ።
አሁንም የወንድማቸው ምጥ ጨምሯል። ሐኪም
ሰውዬው እንዳይጨነቁ እያስጠነቀቁ ነው።
በዚህ መሐል አንድ ጓደኛቸው መጥተው ትክዝ ብለው አዩዋቸውና እንደ አዲስ ፣ “አይ ጀነራል፣ምድር የማይትችልህ ጀግና፣ወንዞችን የምታስደነግጥ ሰው፣አልጋ ችሎ ያዘህ?”
ከንፈራቸውን ነከሱ።
ምሥራቅ ቢሆን ምዕራብ፣ሰሜን ቢሆን ደቡብ ያልረገጠው ምድር፣ያላንቀጠቀጠው አልነበረም። ዛሬ አልጋ ላይ ወደቀ። ከበደ ሚካኤል ‘ጎበዝ ይሸነፋል፤ሐኪምም ይሞታል’ያሉት እውነት ነው።
እንደቆሙ ጠይቀዋቸው ሊወጡ ሲሉ፣ “ኮሎኔል”አሉ በደከመ ድምፅ “ልጆቼን አደራ!”
እህታቸው ጣልቃ ገብተው፣”አንተ ደሞ ለሁሉ አደራ አትበል!..”
“ጌታዬ ተጨንቆ እያስጨነቀን ነው። ልጆቹ ጨው አይደሉ፣አይሟሙ...ለሄደ ለመጣው ሁሉ ‘አደራ’ይላል። ያንተ ልጆች ከማን ልጆች ይለያሉ?”
ኮሎኔሉ መልስ አልሰጡም፤ትንሽ ቆም አሉና”እኔ ማንም አይደለሁም፤በጦር ሜዳ በእሳት መሀል ሞትን አንድ ላይ የተጋፈጥን፣ግማሽ ዳቦ ለሁለት የበላን፣በቀንና ሌት በአውሬ መካከል አብረን የተንከራተትን ነን። ኀይለ ልዑል ለእኔ ወንድሜ ነው። መወለድ ቋንቋ ነው። ስንት ደስታና መከራ አሳልፈናል። ስንት ክፉና ደግ አይተናል?”
እህትዬው ምን ለማለት እንደፈለጉ ለኮሎኔል ሲያስረዷቸው ጉንጫቸው ላይ ያለውን ጠባሳ አዩ። ወታደር ቤት ሆኖ ጠባሳ ፊት ላይ መኖሩ ብርቅ አይደለም። ብዙ ጊዜ እንደማኅተምና ማስታወሻ ምልክት ማኖሩ ግድ ይመስላል። ለሀገሩ አንዳንዱ እግሩን፣አንዳንዱ እጁን፤ሌላው ጆሮውንና ዐይኑን ይሰጣል።
ሆዳቸው እንደ መራራት ብሎ ኮሎኔሉን በዐይን ሸኙዋቸው። ሠሞኑን ደጋግመው መጥተው ጠይቀዋቸዋል። እየባሰባቸው ሄዶ እኒያ ጀግና አልጋ ላይ ታጠጥፈው መውደቃቸው እውን አልመስል ያላቸው ይመስል፣በመጡ ቁጥር ይገረማሉ። ሕይወትና ሞት በሰው ልጅ ውስጥ ተቃቅፈው ቢኖሩም፤ጀግና ግን ከአልጋ ይልቅ ጦርሜዳ ከነሙሉ ጉልበት መውደቅን ይመርጣል። ለዚያ ነው ተመትቶ፣ቆስሎ ሲገኝ”ጨርሰኝ”ብሎ የሚለምነው። ጀግና አልጋን ከሞት በላይ ይፈራዋል፤ይጠላዋል። ጀኔራል ግን ለልጆቻቸው ብለው ሞትን ታገሱ።
ቢሆንም ሰው እንደተመኘውና እንደተመቸው ብቻ አይኖርምና ሕመሙ ቀጥሎ፣ጸሎታቸው ተንጠልጥሎ ቆየ።
እርሳቸው “ትንሽ ዕድሜ”እያሉ ሲለምኑ፣እህትዬው ሲያስታምሙ ነጋ-መሸ።
አንድ ቀን በተመሳሳይ ስሜት፣በተመሳሳይ ሁኔታ ሳሉ፣ለጆሮም ለምናብም የራቀ ነገር ተሰማና ለታማሚው ጀነራል መናገር ምጥ ሆነ። እህታቸው ምድር ጠበባቸው።
እንባቸው ዱብ-ዱብ አለ።
ምን ብለው ይናገራሉ?
“ምንድነው?”
“ምንም”
“የሆነ ነገርማ አለ...የምታንሾካሹኩት ምንድነው?”
“ምንም የለም፤አርፈህ ተኛ አትጨነቅ”
ሳይታሰብ የሠፈራቸው ወፈፌ ጥልቅ አለች።
“ንገሪያቸው”
“እረፊ”
“ምን አርፋለሁ?...እርሳቸው ከዛሬ ነገ ‘ለልጆቼ በዳንኩ’ሲሉ ወንድም ወንድሙን መግደሉ አይገርምም?
“ማን ማንን ገደለ?”አሉ በድንገት ጥየቃ የመጡት ኮሎኔል።
የጀኔራሉ ልጅ የራሱን ወንድም”
“ምን ነው አለ?”
“በውርስ ተጣልተው ነዋ!”
“የምን ውርስ?”
“አባታቸው ሲሞቱ የሚካፈሉትን”
“በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ!”
ምልልሷ ጆሯቸው ላይ ጥልቅ አለች።
“ኸ?” አሉና ጭጭ አሉ።
እህት ደረት መምታት ጀመሩ።”እናቸው እንኳን ይህን ጉድ አላየች!”
የሕይወት ቀለማት ቡራቡሬ!...አባት ለልጆች፤ልጆች ለሀብት!
በ100 ብር የመግቢያ ትኬት መኪና ይሸለሙ
- በሲቢኢ ብር መተግበሪያ የመግቢያ ትኬት መሸጥ ተጀመረ
- ሲቢኢ ብር ኤክስፖ 2017 አዲስ ነገር በአዲስ ዓመት ረቡዕ በድምቀት ይከፈታል
- የፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ደማቅ ኮንሰርት ተዘጋጅቷል
- የ100 ብር ትኬት በ100 ብር ገዝተው የ2 ነጥብ 3 ማሊዮን አዲስ መኪና ይሸለሙ
-ትኬቱ ከሲቢኢ ብር በተጨማሪ በኤግዚቢሽን ማዕከልም ይገኛል
--ከ35 በላይ አንጋፋና ወጣት ተወዳጅ ድምፃዊያን በየቀኑ ሸማችና ጎብኚን ለማዝናናት ከፍተኛ ዝግጅት አድርገዋል
- በኤግዚቢሽን ማዕከል በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልጉትን እየሸመቱና እየጎበኙ እየተዝናኑና እየተሸለሙ ለ20 ቀናት ይቆያሉ
-ከመኪና በተጨማሪ ከ5 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር መጠን ያላቸው የዕቃ መግዣ ኩፖኖች፣ ኢባይክ እና የዲኤስ ቲቪ ዲኮደሮች በመግቢያ ትኬት ዕጣዎ ያገኛሉ
--ይህ ሁሉ ዕድል የሚገኘው በ100 የመግቢያ ትኬት እጣ ነውና መተግበሪያውን በማውረድ አሁኑኑ ትኬትዎን ከሲቢኢ ብር ይግዙ
በኤግዚቢሽን ማዕከል
-ሸመታውም በሽበሽ
-መዝናኛውም በሽበሽ
-ሽልማቱም በሽበሽ
አዘጋጅ
ታሜሶል ኮሙኒኬሽን ከአሴንቲክ ሶሉሽንና ከሊያን ኩባንያ ጋር በመተባበር
የኤክስፖው የክብር ስፖንሰር
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የወርቅ ደረጃ ስፖንሰሮች
ራይድ
ፔፕሲ
አኳኡኑ ውሃ
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት
ካቻ
ዋፋ
ስንቅ ማልት
ንጉስ ማልት
ለበለጠ መረጃ
0911516739 ይደውሉ
ታሜሶል ኮሙኒኬሽንስ