Administrator

Administrator

   የ22 ሺህ የአይሲስ ታጣቂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ማንነት በዝርዝር ያሳያል
     በአይሲስ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ለአመታት ሲከናወኑ በነበሩ የጸረ-ሽብር እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት የሚቆጠርና የቡድኑን ህልውና የከፋ አደጋ ውስጥ ይጥላል የተባለ፣ የ22 ሺህ የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎችንና የቤተሰቦቻቸውን ማንነት የሚገልጽ ሚስጥራዊ ዝርዝር መረጃ አፈትልኮ መውጣቱ ተዘገበ፡፡
ዴይሊ ሜይል ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ አፈትልኮ የወጣው መረጃ በሶርያና በኢራቅ የሚገኙ 22 ሺህ የቡድኑ ታጣቂዎችን ስም፣ ዜግነት፣ አድራሻ፣ የስልክ ቁጥር፣ ቤተሰቦች፣ የትውልድ ቦታና ዘመን፣ የቀድሞ የስራ ልምድ፣ የውትድርና ተሞክሮና የመሳሰሉ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ ሲሆን በቡድኑ የሽብር እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን ተልዕኮም ያሳያል፡፡
ታጣቂዎች ቡድኑን በአባልነት በሚቀላቀሉበት ወቅት በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ የተሰበሰበውና ሶርያ ውስጥ በምትገኘው ራቃ ከተማ ተቀምጦ እንደነበር በተገመተው በዚህ ዝርዝር መረጃ ውስጥ ከተካተቱትና ዜግነታቸውን ከገለጹት የቡድኑ ታጣቂዎች መካከል፣ 480 የሳኡዲ አረቢያ፣ 375 የቱኒዝያ፣ 140 የሞሮኮ፣ 101 የግብጽ፣ 35 የፈረንሳይ፣ 18 የጀርመን፣ 16 የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ዝርዝር መረጃ ውስጥ የ51 የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው የቡድኑ ምልምል ታጣቂዎች ዝርዝር ማንነት መካተቱን የጠቆመው ዘገባው፣ መረጃው አፈትልኮ መውጣቱ ቡድኑ በቀጣይ ያቀዳቸውን የሽብር ጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማክሸፍና የሽብር መረቡን ተከታትሎ ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል መባሉንም አስረድቷል፡፡ በአይሲስ ውስጥ አዋቂዎች ኤስ ኤስ ተብሎ በሚጠራው የቡድኑ የውስጥ ደህንነት ፖሊስ ሃላፊ እጅ ውስጥ የነበረው መረጃው፣ አቡ ሃሚድ በተባለ የቡድኑ አባል በሜሞሪ ካርድ ተሰርቆ መውጣቱንና ስካይ ኒውስ ለተባለው የዜና ተቋም መድረሱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና በኢራቅ የአይሲስ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ቀንደኛ ተመራማሪ የሆነው ሰልማን ዳኡድ አል አፋሪ የተባለ ቁልፍ ሰው ከሳምንታት በፊት በአሜሪካ ልዩ የጸረ ሽብር ግብረ ሃይል በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

 በዓለማችን ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችና ያንዣበቡ ስጋቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውንና መንግስታት በአለማቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ማስታወቁን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ትንበያ፣ የአመቱ የአለማችን የኢኮኖሚ እድገት እንደሚቀንስ መግለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ የተቋሙ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዴቪድ ሊፕተን ባለፈው ማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአለማችን ኢኮኖሚ ፈተናዎች ከመባባሳቸው በተጨማሪ አዳዲስ ስጋቶች መፈጠራቸውንና መንግስታት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው መናገራቸውን ገልጧል፡፡
ተቋሙ የአመቱ የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.4 በመቶ ይሆናል የሚል ትንበያ ባለፈው ጥር ወር ማውጣቱን ያስታወሱት ዴቪድ ሊፕተን፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች የተወሰነ መሻሻል ቢታይም በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ አደጋዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን ገልጠዋል፡፡
ሊፕተን መንግስታት በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የገንዘብ፣ የፊዚካል ፖሊሲና የተቋማዊ ለውጥ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይገባቸዋል ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ቻይና ሰሞኑን ባወጣችው መግለጫ ባለፈው ወር የወጪ ንግዷ በ25 በመቶ መቀነሱን አስታውሶ፣ ይህም በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ ከተጋረጡ አሳሳቢ ስጋቶች አንዱ ነው ብሏል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት በደቡብ አሜሪካ አገራት የተከሰተውና ነፍሰ ጡር ሴቶችን በማጥቃት የሚታወቀው የዚካ ቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና በመጪዎቹ ወራት በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀ፡፡
ቫይረሱ ከትንኞች በተጨማሪ በወሲባዊ ግንኙነት እንደሚተላለፍ መረጋገጡን የጠቆሙት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ማርጋሬት ቻን፣ ቫይረሱ የተሰራጨባቸው አገራት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ወቅቱ የዝናብ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቫይረሱ ስርጭት ይስፋፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጠዋል፡፡
ቫይረሱ በተስፋፋባቸው አገራት የሚገኙና ወደ አገራቱ የሚጓዙ ነፍሰጡር ሴቶች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ቫይረሱን ለመዋጋት እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የአለማቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ተቋም በደቡብ አሜሪካና በካረቢያን አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ተጨማሪ የ2.3 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

የአይፎን ሞባይል ቀፎ የሚገዛበት ገንዘብ ለማግኘት ሲል፣ ሴት ልጁን በተወለደች በ18ኛው ቀን በድረ-ገጽ አማካይነት ሽጧል በሚል ሰሞኑን በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው አ ዱኣን የተባለ ቻይናዊ፣ የ3 አመት እስር እንደተፈረደበት ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ነዋሪነቱ ፉጂያን በተባለቺው የቻይና ግዛት እንደሆነ የተነገረለት ግለሰቡ፣ ኪውኪው በተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ ልጁን ለመሸጥ ያወጣውን ማስታወቂያ የተመለከተ ግለሰብ ልጅቷን ለመግዛት 2ሺህ 500 ፓውንድ መክፈሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
አባትዬው ልጁን በመሸጥ ያገኘውን ገቢ አይፎንና ሞተር ብስክሌት ለመግዛት ሊያውለው አስቦ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ ልጅቷ የተረገዘቺው ያለ እቅድ እንደነበረና አባትዬውም ሆነ እናትዬው የ19 አመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች እንደሆኑ ዘገባው አስረድቷል፡፡
እናትዬው ዢያኦ ሚ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ገቢ ታገኝ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አባትዬው በበኩሉ አብዛኛውን ጊዜውን በኢንተርኔት ካፌዎች ተጎልቶ የሚያሳልፍ ስራ ፈት እንደነበረና ልጁን ለመሸጥ የወሰነውም ለማሳደጊያ የሚሆን በቂ ገንዘብ የለኝም በሚል ስጋት እንደሆነ አብራርቷል፡፡
ልጁን የሸጠው ይሄው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው እናትዬው ለፖሊስ በሰጠቺው ጥቆማ መሰረት እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Saturday, 12 March 2016 10:36

የኪነት ጥግ

(ስለ ካሜራ ባለሙያ)
- አባቴ ተዋናይና ፀሐፊ ነበር፤ እናቴ የድራማ
መምህርት ነበረች፤ ሴት አያቴ ደግሞ
ተዋናይት፡፡ ወንድ አያቴ እንዲሁ የካሜራ
ባለሙያ ነ በር፡፡ እ ኔ የ ጥርስ ሃ ኪም ወ ይም
በዚያ አይነት ሙያ ለመሰማራት ብፈልግ ኖሮ
ተገርመው አያበቁም ነበር፡፡
ቻርሊ ሮሄ
- የካሜራ ባለሙያ ወይም ዲዛይነር አሊያም
ተዋናይ ልሆን አልችልም - ዳይሬክተር
ነው መሆን ያለብኝ፤ ምክንያቱም ያ እንዴት
እንደሚሰራ ከአባቴ ተምሬዋለሁ፡፡
ጆ ራይት
- ሰዎች ሁልጊዜ ሙሉ የድጋፍ ቡድን -
(ሜክአፕ፣ አልባሳትና ሹፌር) የሚኖረን
ይመስላቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በጦርነት
ቀጠና ውስጥ ግን እኔና የካሜራ ባለሙያው
ብቻ ነን፡፡
ኬት አዲ
- ካሜራ ለሴቶች በጣም ከባድና ቀድሞውኑም
የተሰራው ለወንዶች በመሆኑ ደህና የካሜራ
ባለሙያ ያስፈልጋችኋል፡፡
ሚትራ ፋራሃኒ
- በእያንዳንዱ ምስል ላይ ሁለት ሰዎች አሉ
-ፎቶግራፍ አንሺውና ተመልካቹ፡፡
አንሴል አዳምስ
- የሰውን ፊት በትክክል የሚያየው ማነው?
ፎቶግራፍ አንሺው፣ መስተዋቱ ወይስ
ሰዓሊው?
ፓብሎ ፒካሶ
- ሁልጊዜም አማተር ፎቶግራፍ አንሺ ነው
የምሆነው፡፡
ኢሊዮት ኢርዊት
- የፋሺን ፎቶግራፍ አንሺ መሆን ምንም ችግር
የለውም፤ ግን ትንሽ ውሱንነት አለው፡፡
ዴቪድ ባይሌይ
- በአሜሪካ የፎቶግራፍ ባለሙያ ያለፈውን
የሚቀርፅ ብቻ አይደለም፤ የሚፈጥርም
ጭምር እንጂ፡፡
ሱሳን ሶንታግ
- እናቴ የፎቶግራፍ ባለሙያ ነበረች፤ እናም
ለሞዴሊንግ ሥራ ህፃን ልጅ ሲፈልጉ ካሜራ
ፊት ትገትረኛለች፡፡ እንደዚያ ነው ነገሩ
የተጀመረው፡፡
አሊሶን ሃኒጋን

በድሮው ዘመን አንድ አዛውንት እስር ቤት ይገባሉ፡፡ በዚያን ጊዜ እስረኞች እራሳቸው ባወጡት ህግ መሰረት፤ አዲስ ገቢ ሲመጣ ለእስር ቤቱ መኖሪያ ማዋጣት ያለበት ገንዘብ ነበር፡፡ የእስር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት፤
“እንግዲህ በክፍላችን ህግ መሰረት ያቅምዎትን አዋጡ” አላቸው አዛውንቱን፡፡
አዛውንቱም፤
“ቤተሰቤ ምን ይስጠኝ ምን ሳላውቅ ይሄን ያህል አዋጣለሁ ማለት ያስቸግረኛል” አሉ፡፡
“ግዴለም ከመጣልዎት ውስጥ ይሄን ያህሉን እለግሳለሁ፤ ቢሉና ቃል ቢገቡ እንኳ በቂ ነው” አላቸው፡፡
ይሄኔ አዛውንቱ፤
“እስቲ አሳቤን በወግ ልግለጥ” አሉና፤ “ጥንት ጎጃም ውስጥ ሁለት ሴቶች ሜዳ ሊወጡ ከቤት ወደ ደጅ ይሄዳሉ፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ማታ ነው፡፡
አንደኛዋ፤ ‹እንግዲህ አደራ፣ ነገ በተስኪያን ጠዋት ስንመጣ፣ አንቺ ከቀደምሽ አንቺ፤ እኔ ከቀደምኩ እኔ፤ ቀድመን ቦታ እንያዝ - እሴቶች መቆሚያ ቦታ› አለቻት፡፡
በተስኪያን ውስጥ ማልዶ መጥቶ ቦታ ካልያዙ ሰው ብዙ ስለሆነ ደጅ ሆኖ ማስቀደስ ግድ ስለሚሆን ቀድሞ መገኘት ዋና ነገር ነው፡፡ ይሄኔ፤ ሁለተኛይቱ ሴት፣ በሚያቅማማ ድምፅ፤
“እንግዲህ ማልዶ ቦታ ለመያዙም፣ በተስኪያን ውስጥ ገብቶ ለማስቀደሱም፤ ወንዶቹ እንዴት እንዳሳደሩን አይተን ነዋ!” አለች፡፡
(በዕምነታቸው መሰረት ከወንድ ተገናኝታ ያደረች ሴት፤ በተስኪያን ውስጥ መግባት ክልክል በመሆኑ ነው፡፡ ያ ደግሞ በድሮው ዘመን በተለይ የወንዱን ፍቃድና ፍላጎት የሚሻ ጉዳይ ነው!)
የእሥር ቤቱ አዲስ እስረኛ አዛውንት አሳሪዎቻችን (ወንዶቹ) እንዴት እንደሚያሳድሩን ሳናይ ‹እንዴት ብዬ ቃል ልግባላችሁ … ሊገድሉንምኮ ይችላሉ፤ በሰው እጅ ያለን ሰዎች ነን› ማለታቸው ነው!
*             *           *
በሰው እጅ ያለ ሰው በራሱ ለመቆም እጅግ ያዳግተዋል፡፡ በተለይ ፍትሕ በሌለበትና” “ንጉሥ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል” በሚባልበት ዘመን ከሆነ፤ በማናቸውም ሰዓት ህይወት ስጋት ላይ መውደቋ የዕለት የሰርክ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ካጠፉ ቅጣት አይቀሬ ነው! ዘረፋና ምዝበራ ሲበዛ ጥርጣሬ አንድ የማሰሪያ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ ህጋዊ ሽፋንን ተጠቅሞ ምዝበራውን የሚያካሂድ ሹም ራሱ መዝባሪ፣ ራሱ ጠርጣሪ ስለሚሆን በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም፡፡ ከተደረሰበት ግን “የነብርን ጅራት አይይዙም ከያዙም አይለቁም” የሚባል መሆን ይኖርበታል፡፡ አያሌ ሹማምንት ከሙስናም ከፖለቲካዊ ሁኔታም ጋር በተያያዘ የሚገመገሙበት ሰዓት እነሆ ደረሰ፡፡ በማናቸውም የሥራ ኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ሹም ማለትም ሚኒስትር፣ ኤክስፐርት፣ አማካሪ፣ ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ ሳይንቲስት፣ ኦዲተር፣ የመሬት አስተዳዳሩ፣ የፖለቲካ መሪ፣ ካድሬ ወዘተ … እከሌ ከእከሌ ሳይባል የሚመረመሩበት፣ የሚፈተሹበት ወቅት መጣ፡፡ “ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ የቪላ መዓት፣ የውድ ውድ መኪናዎች ጥርቅም፡፡ በዘር - ሐረግ የተያዘ መሬት ብዛት … አንድ የመንግሥት ሰራተኛ እንዴት ሊኖረው ይችላል? ብሎ መጠየቅ ማንም ጅል የማይስተው ነገር ነው፡፡ በሙስና የተገኘ ሐብት መሆኑ ከታወቀ ደግሞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መንግስትን መንግስት የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከየትኛውም ነጋዴ ወይም ሀብት ያካበተ - ዜጋ ጋር በመመሳጠር ያንድ ጀምበር ባለፀጋ (nouveau riche ኑቮ ሪሽ እንዲሉ) ለመሆን የቻለበትን ሁኔታ ለማጣራት፣ መፈራራት ከሌለ በስተቀር፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ ነገር ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን ማናቸውም ሌብነት፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚፈፅሙት፣ ስሙ “ቢዝነስ” ሆኗል፡፡ “ይሄኮ እልም ያለ ዘረፉ ነው” ሲባሉ “የሥራው ፀባይ ነው” ብሎ መመለስ እንደመመሪያ ተወስዷል፡፡ “የማይበላ ሰው” ፋራ መባሉም እንደ እለት ሰላምታ ተለምዷል፡፡
“ኢንቨስተሩ ከባንክ የወሰደውን ገንዘብ ለጥገኛ ጥቅም አውሎታል” ካልን፤ የደረስንበትን ማስረጃ ለፈጣን እርምጃ ማዋል መዘግየት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ ያውም እስካሁን ካልረፈደ! በችሎታውና በሙያው የሚተዳደር እንደ ሐቀኝነት ነውር ሆኗል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ይኖራል ማለት እጅግ አስቂኝ ጨዋታና ስላቅ (irony)  ይሆናል፡፡ ዊንስተን ቸርችል፤ “የዲሞክራሲ ሥርዓት ከሌሎች ተሞክረው ከከሸፉ ሥርዓቶች ጋር ሲነፃፀር ነው እንጂ ደግ ነው የሚባለው፤ በራሱ ፍፁም ሥርዓት አይደለም” ይሉናል፡፡ ዲሞክራሲ እንደኛ ባለና በሙስና አዘቅት በገባ አገር ውስጥ ሲታሰብ እንዴት ውስብስብና አያዎአዊ (paradoxical) እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ፤ የመልካም አስተዳደርን አናሳነት፣ የጠንካራ ተቋማትን መጥፋት፣ ወገንተኝነትን፣ የዕውቀት መንማናነትን፣ አለመቻቻልን፣ ከልብ አለመነጋገርን፣ ራስ - ወዳድነትን፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መታጣትን ወይም መሟሸሽን ወዘተ አክለን ስናስበው… “አይ ዲሞክራሲ እኔን ክንብል ያርገኝ!” ማለታችን አይቀርም፡፡ “አግዝፈው ያሞገሱት ለማማት ያስቸግራል” ነው ነገሩ፡፡ አሳሳቢ መንታ መንገድ ላይ ቆመን ነው ግምገማ እያካሄድን ያለነው። ሆኖም መገማገም ግዴታ ነው፡፡ አንዲት ክር ስትነካ አገሩ የሚታመስ ከሆነ ሁኔታውን መገምገም ግዴታ ነው፡፡
የተነካካውን ሰው ሁሉ ስናጠራ ጊዜ ማለፉ ደግሞ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም በአቅም ካልፈጠንን ሁኔታዎች ሊቀለበሱ ይችላሉ ብሎ መስጋት ያባት ነው፡፡ ወትሮውንም ሰዎቹን እናውቃቸው ነበርኮ፡፡ “እቃ ስላጣን አብረን በላን፤ እንጂ መች እኩያሞች ሆንን” የሚለውን ተረት ስናሰላስል፣ የዛሬው የበሰለ ቀን እንዳያመልጠን ጠንክረን እንሥራ፡፡ ሙስና የድህነት አቻ ጠላት የሆነበት ሰዓት ደርሷልና!

ዓመታዊ ትርፉን 10ቢ. ዶላር ለማድረስ አቅዷል
   በትርፋማነቱ ከአፍሪካ አየር መንገዶች መሪነቱን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በፈረንጆች የ2014-15 አመት የ3.53 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንና ትርፉ ከቀደመው አመት የ12 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን “ብሉምበርግ” ዘገበ፡፡
ምንም እንኳን አመቱ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ፈታኝ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን፣ ፈተናዎችን በመጋፈጥ፣ ወጪዎቹንና የሽያጭ አገልግሎቶቹን በማስፋፋትና አሰራሮቹን በማሻሻል በትርፋማነቱ መቀጠሉን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል፡፡
አየር መንገዱ ከ2.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ፣ 20 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙንና በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ አመታዊ ትርፉን 10 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ አቅዶ እየታተረ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ኤጀንሲዎች ህጻናትን እየላኩ ገንዘብ በመሰብሰብ ተጠምደዋል ተብሏል
    የዴንማርክ የማህበራዊ ጉዳዮችና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር፤ በኢትዮጵያውያ የሚታየው የጉዲፈቻ አሰራር ያልተገባና ህጻናትን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ጠቁሞ፣ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በጉዲፈቻ ላለመቀበል መወሰኑን አስታውቋል፡፡
“ዘ ኮፐንሃገን ፖስት” የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በኢትዮጵያ ያለው ህጻናትን በማደጎ ወደ ውጭ አገራት የመላክ አሰራር ዴንማርክ በአለማቀፍ የማደጎ ሂደት የምትከተለውን መርህ የማያሟላ ሆኖ በመገኘቱ ውሳኔው ሊተላለፍ ችሏል፤ ሲል ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የጉዲፈቻ አስፈጻሚ ኤጀንሲዎች ወደ ዴንማርክ የሚልኳቸውን ህጻናት በተመለከተ የሚሰጡት መረጃ በአብዛኛው ወጥነት የሌለው ነው ያለው ዘገባው፣ ኤጀንሲዎቹ ትኩረታቸውን ያደረጉት ከውጭ አገራት ኤጀንሲዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ መሆኑንና አገራዊ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ህጻናቱን ወደ ውጭ አገራት በማደጎ በመላክ እንደተጠመዱ ጠቁሟል፡፡ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2015 ብቻ በአለማቀፍ የጉዲፈቻ ቅበላ ሂደት 100 ያህል ህጻናት ወደ ዴንማርክ መግባታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከእነዚህ ህጻናት መካከል ሰባቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በአርባምንጭ ሆስፒታል ከ140 በላይ ህሙማን ህክምና እየተሰጣቸው ነው

     በደቡብ ክልል አርባምንጭ ዙሪያ አማሮና አባያ ወረዳዎች በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ገላን ወረዳና በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳዎች ላይ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ በሶስቱ ክልሎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በአተት በሽታ የተያዘ ሰው አፋጣኝ ህክምና ካላገኘ የመሞት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ያለው መግለጫው፤ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ብሏል፡፡
የአርባ ምንጭ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ቀፀላ ለማ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት በሽታው በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ከአለፈው እሁድ ጀምሮ ከ140 በላይ ህሙማን በዚሁ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ መጥተዋል፡፡ ለህሙማኑ የህክምና ማዕከል ተቋቁሞ ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ዶ/ሩ ገልፀዋል፡፡ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ስለመኖራቸው እንደማያውቁ የተናገሩት ዶ/ሩ፤ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ህሙማን ግን ተገቢው ህክምና እየተደረገላቸው በመሆኑ የሞት አደጋ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡  
ከሰሞኑ ዝናባማ የአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በሚከሰተው ጐርፍ፤ ምንጮች፣ የውሃ ጉድጓዶችና ወንዞች ስለሚበከሉና ይህም በሽታውን በቀላሉ ለማስተላለፍ የሚችል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ያለው ጤና ጥበቃ ሚ/ር፤ ለመጠጥነት የሚውሉ ውሃዎች በአግባቡ ተፈልተውና ቀዝቅዘው አሊያም በውሃ ማከሚያ መድሃኒቶች ታክመው ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡   

   - ቢል ጌትስ በ75 ቢ. ዶላር፣ ዘንድሮም አንደኛ ነው
                 - የፌስቡኩ ዙክበርግ ከፍተኛውን የሃብት ጭማሪ አግኝቷል
                 - ቻይና ዘንድሮ 70 አዳዲስ ቢሊየነሮችን አፍርታለች
    በየአመቱ የዓለማችንን ባለጸጎች የሃብት መጠን በመገምገም ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው 1ሺህ 810 ባለጸጎች የተካተቱበትን የ2016 የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ አድርጓል፡፡
የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ የሃብት መጠናቸው ከአምናው የ4.2 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት ወደ 75 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ቢልም፣ ዘንድሮም የፎርብስ የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር በአንደኛነት ከመምራት የሚያግዳቸው አልተገኘም፡፡ እኒሁ ስመጥር ባለጸጋ በሃብታቸው መጠን አለምን ሲመሩ የአሁኑ ለ17ኛ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡
ዛራ ፋሽን የተባለው አለማቀፍ የአልባሳት አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ስፔናዊው አማኒኮ ኦርቴጋ፤ በ67 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ 60.8 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያላቸው አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ ሜክሲኳዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም በ50 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ የአማዞን ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ፣ በ45.2 ቢሊዮን ዶላር አምስተኛው የዓለማችን ቢሊየነር ሆነዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 190 ሴት ቢሊየነሮች መካተታቸውና የወንዶች የበላይነት መግነኑ የታወቀ ሲሆን በ11ኛነት የተቀመጠችውና ከአለማችን ሴቶች በሃብት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው፣ 36.1 ቢሊዮን ዶላር ያፈራችው የታዋቂው የፋሽንና የመዋቢያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ ሎሪል መስራችና ባለቤት ፈረንሳዊቷ ሊሊያን ቤተንኮርት ናት፡፡
በአመቱ ዝርዝር ውስጥ 540 ዜጎቿ የተካተቱላት አሜሪካ በርካታ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ቻይና በ251፣ ጀርመን በ120፣ ህንድ በ84 እና ሩስያ በ77 ቢሊየነሮች ከሁለት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በ2016 በርካታ አዳዲስ ቢሊየነሮችን በማፍራት ቀዳሚነቱን የያዘቺው ቻይና ስትሆን፣ 70 ባለጸጎቿን በአመቱ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አካትታለች። በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር በዕድሜ ለጋዎቹ ባለጸጎች ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ፣ የ19 አመቷ የኖርዌይ ተወላጅ አሌክስንድራ አንደርሰንና አንድ አመት የምትበልጣት ታላቅ እህቷ ካትሪና አንደርሰን ናቸው፡፡
ባለፈው አመት 1826 የነበረው የአለማችን ቢሊየነሮች ቁጥር፣ ዘንድሮ ወደ 1810 ዝቅ ብሏል ያለው ፎርብስ፣ ባለፈው አመት ከነበራቸው ሃብት 20.1 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳዩት ሜክሲኳዊው ቢሊየነር ካርሎስ ስሊም ከፍተኛ ኪሳራ የገጠማቸው ባለጸጋ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በአንጻሩ ከአምናው ሃብቱ የ11.2 ቢሊዮን ዶላር የሃብት መጠን ጭማሪ በማስመዝገብ 44.6 ቢሊዮን ዶላር ያደረሰውና በዓለማችን የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ደረጃውን ወደ ስድስተኛነት ከፍ ያደረገው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ በአመቱ ከፍተኛውን የሃብት ጭማሪ ያስተናገደ ባለጸጋ ተብሏል፡፡