Administrator
“በቀል’ና ፍትሕ” ለንባብ በቃ
በስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ ወደ አማርኛ የተተረጎመው “በቀል’ና ፍትሕ” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡
መጽሐፉ፤ ጦርነታ ያገናኛቸው፣ የማይተዋወቁ፣ ግን ደግሞ ግዳጅና ሞት አንድ ስላደረጋቸው ሰብዕናዎች የሚተርክ ነው ተብሏል፡፡
የኑሮ ሂደት ያጠላለፉትና ዘመናት ያወረዛው የተቀበረ የውስጥ ስሜት (የትውልድ ቂም- ወበቀል ወይም የዘገየ ፍትህ)፣ የሚንጸባረቅበት ነው - “በቀል’ና ፍትሕ” ፡፡
የትውልድ ቂም በፍቅር ሃይል ሲሻር የሚያሳይ ልብ አንጠልጣይ የውርስ ትርጉም እንደሆነ የተነገረለት መጽሐፉ፤ በ310 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፣ በ380 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ተቃውሞ ቀረበበት
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበው አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፣ በሁለት የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል። በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቃውሞ የሰነዘሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ን ወክለው ምክር ቤት የገቡ አባላት ናቸው።
በምክር ቤቱ የኢዜማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አወቀ ሐምዛዬ በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “ምክር ቤቱ እያጸደቃቸው ያሉት የታክስ አዋጆች የደኸየውን እያደኸዩ የሚሄዱ ናቸው” “ድሃው ላይ ነው እየጨመርን፤ ታክሶች እያጸደቅን ያለነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
“ድሃው በጣም እየጮኸ ነው” ያሉት ዶ/ር አወቀ ሐምዛዬ፤ “ታክስ ሲጣል፣ ተጠቃሚ ላይ ነው ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምናየው ሃብታሞች አይከፍሉም፤ ባለንብረቱ አይከፍልም። ድሆች ናቸው ታክስ የሚከፍሉት” ሲሉ ተደራራቢ ታክስ ድሆች ላይ ጫናው እየበረታ መምጣቱን በመጠቆም ትችት ሰንዝረዋል።
ሌላው የአብን የምክር ቤት አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ “እኔ ይሄ የንብረት አዋጅ መጽደቅ ‘የለበትም’ ብዬ ነው የምከራከረው” ሲሉ ተቃሟቸውን አሰምተዋል። በማያያዝም፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የመክፈል አቅም የለውም። አሁን ባሉ ተደራራቢ ታክሶችና የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ደረጃ፣ ኢትዮጵያውያን የንብረት ታክስን የሚከፍሉበት አቅም አላቸው ብዬ አላስብምና እንዲታይ ምክር ቤቱን መማጸን እፈልጋለሁ” ብለዋል።
“መኖሪያ ቤት የሚገነባው በሕይወት ዘመን አንዴ ነው” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ “በሕይወት ዘመኑ ሠርቶ ከሚያገኘው ንብረት ላይ መንግሥት እንዴት ታክስ ለመሰብሰብ ያስባል? አይከብድም ወይ?” ጥያቄ አቅርበዋል።
አክለውም በሰጡት አስተያየት፤ “ይህ የአዋጁ አስፈላጊነት መርህ መሰራት ያለበት ከመኖሪያ ቤት ውጭ ያሉ ትርፍ የንግድ ህንፃዎች ላይ ነው” ብለዋል- ዶ/ር ደሳለኝ።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የንብረት ታክስ መጣልን አስፈላጊነት ሲያብራራ፤ “በከተሞች ውስጥ የሚፈራው ቋሚ ንብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከከተሞቹ ዕድገት ጋር እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የክልል መንግስታት ከዚህ ሃብት ተገቢውን ድርሻ በታክስ አማካኝነት እየሰበሰቡ አይደለም” ይላል።
የቋሚ ንብረት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን የሚያትተው ማብራሪያው፤ ለዚህ የቋሚ ንብረት ዋጋ መጨመር በክልልና በማዘጋጃ ቤት ደረጃ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ይላል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደነገገው መሰረት፣ የንብረት ታክስ የሚጣልባቸው ንብረቶች፤ በከተማ ውስጥ የሚገኝ መሬት በመሬት ላይ የሚደረግ ማሻሻያና ህንፃ ናቸው።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን በሦስት ተቃውሞና በአብላጫ የድጋፍ ድምጽ ለቋሚ ኮሚቴው መርቶታል።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት በ2015 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ባደረጉት የጋራ ስብሰባ፣ የንብረት ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ስልጣን የክልል መንግሥታት እንዲሆን መወሰናቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የንብረት ታክስን ማዕቀፍ የሚወስን አዋጅ ደግሞ የፌደራል መንግስት እንዲያወጣ መወሰናቸው ይታወቃል።
ፓርቲዎች በምዕራብ ጎጃም፣ ጅጋ ከተማ ‘ተፈጸመ’ ያሉትን ግድያ አወገዙ
አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በምዕራብ ጎጃም ጅጋ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ሃይሎች ተፈፀመ ያሉትን “የንፁሃን ግድያ” አወገዙ፡፡ እናት ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ባወጡት መግለጫ፤ የመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች፣ በምዕራብ ጎጃም ጅጋ ከተማ ውስጥ “የፈጸሙትን ጭፍጨፋ እንቃወማለን” ብለዋል።
ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ “የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በንጹሃን ላይ የፈፀሙት ግድያ፣ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ” ፓርቲዎቹ ከትላንት በስቲያ ሐሙሰ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ፣ “የመንግስት ወታደሮች ጎህ በተባለ ሆቴል በመመገብ ላይ የነበሩ 12 ሰላማዊ ሰዎችን አሰልፈው ረሽነዋል” ሲሉ ከስሰዋል። የመንግስት ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ “የበቀል እርምጃ” የወሰዱት፣ ከጅጋ ከተማ ወጣ ብሎ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ እንደሆነ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
ከተገደሉት ሰዎች መካከል፤ የባንክ ሰራተኞች፣ መምህራንና የጉልበት ሰራተኞች እንደሚገኙበት ያመለከቱት ፓርቲዎቹ፣ “የመንግስት ሃይሎች ስድስት ሰዎችን ከንግድና መኖሪያ ቤቶች ጭምር እያስወጡ ረሽነዋል” ብለዋል። ሁለት በጥይት ተመተው የቆሰሉ ሰዎች በባሕርዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
“የፀጥታ ሃይሎች ጎዳና ላይ የምትኖር አንዲት የአዕምሮ ሕመምተኛን ጨምሮ ከሞባይል ቤት፣ ከፀጉር ቤትና ከመኖሪያ ቤት በማስወጣት ተጨማሪ 6 ሰዎች፣ በአጠቃላይ 18 ሰዎች መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል” ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
“የመከላከያ ሰራዊቱ በንጹሐን ዜጎች ላይ የወሰደውን አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ እናወግዛለን” ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ የተፈጸመው ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራና በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። “ከታሪክ መማር ብልህነት ነው” ያሉት አራቱ ፓርቲዎች፤ በመንግስት በኩል ለድርድር ቦታ እንዲሰጥ አሳስበዋል። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፤ የመከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች ተፋላሚ ወገኖች ዓለም አቀፍ የጦር ሕግን እንዲያከብሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የማላዊ መንግሥት 238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ሊመልስ ነው
የማላዊ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ገብተዋል ያላቸውን 238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ሊመልስ መሆኑን አስታውቋል። ስደተኞቹ በማላዊ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኙ እስር ቤቶች ታስረው እንደቆዩ ተገልጿል።
የአገሪቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ስደተኞቹ የማላዊን ሕግ በመተላለፍ ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ጠቅሷል።
የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሳጅን ፍራንሲስ ቺታምቡሊ፤ “238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት በዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ድጋፍ የሚከወን ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ “አሁን ላይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ከዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት አቻዎቻቸው ጋር በማዚምባ እና ምዙዙ እስር ቤቶች የሚገኙ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የመለየት ስራ ሰርተዋል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዘንድሮው ዓመት ጥር ወር አንስቶ በሰሜኑ የማላዊ ክፍል ለመግባት ሞክረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የውጭ አገር ስደተኞች ብዛት 173 ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 142 ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የ”ማላዊ 24” ድረ ገጽ ዘገባ ይጠቁማል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የማላዊ ፖሊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የነበሩ 29 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር ማግኘቱን ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ገልጾ ነበር። የጅምላ መቃብሩ የተገኘው ከማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ በስተሰሜን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሚዚምባ አካባቢ ነበር።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የቀድሞ የማላዊ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ልጅ የሆኑት ታዲኪራ ማፉብዛ፣ በጥቅምት 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን፣ ከእርሳቸው ጋር ሰባት ሰዎችም ታስረው ነበር። ይሁን እንጂ ታዲኪራ ላይ የቀረቡት የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰውን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል ክሶች ባለፈው ረቡዕ፣ ከ19 ወራት በኋላ ውድቅ ተደርገው፣ ተከሳሹ ነጻ መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡
ማላዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚሸጋገሩ ስደተኞች ሁነኛ የመተላለፊያ መስመር እንደሆነች ይነገራል።
“ላምህ ባትታለብ እንኳ እምቧ ትበልልህ” “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ!”
አንድ የአይሁዶች አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
አይሁዶች በአንድ ክፉ-አጋጣሚ የሆነ እርኩስ (እኩይ) መንፈስ ሲገጥማቸው፣ ያን መንፈስ ለማባረር ሦስት ነገሮች ያደርጋሉ ይባላል፡፡
አንደኛ- ወደ አንድ ጫካ ይሸሹና አንድ ልዩ ቦታ ይመርጣሉ፡፡
ሁለተኛ -እሳት ያነዳሉ፡፡
ሦስተኛ -ፀሎት ይደግማሉ፡፡
ይህንን ሲያደርጉ ያ እርኩስ መንፈስ ይሸሻል፡፡ ይጠፋል፡፡
አንድ አይሁዳዊ የዕምነት ሰው ከዕለታት አንድ ቀን እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ሰው ሦስቱን ህግጋት ያውቅ ስለነበር፣ ቶሎ ብሎ ወደ ጫካ ይሄድና ቦታ ይመርጣል፡፡
እሳት ያነዳል፡፡
ቀጥሎም ይፀልያል፡፡ ይደግማል፡፡
እርኩስ መንፈሱ በንኖ ሄደ፡፡ ድራሹ ጠፋ፡፡
ሌላ ጊዜ አንድ ሌላ የዕምነት ሰው እንደዚሁ እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ሰው ሦስቱን ህግጋት ለመፈፀም ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡
ምቹ ቦታ ይመርጣል፡፡
መፀለይና መድገም ያለበትን ያሰላስላል፡፡
እሳት ማንደድ ግን አልቻለበትም፡፡
ያም ሆኖ እሳቱን ሳያነደድ ፀለየ፡፡ እርኩስ መንፈሱ ድራሹ ጠፋ፡፡
ሦስተኛው የዕምነት ሰው እንደዚሁ ከዕለታት አንድ ቀን እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡
ይሄኛው፤ ቦታውን ያውቃል፡፡
እሳት ማንደድ አይችልም፡፡
የሚደገመውን ፀሎትም አይችልም፡፡ ሊያስታውሰው አልቻለም፡፡ ያም ሆኖ ቦታውን በመምረጡና ወደዚያ በመሄዱ እርኩስ መንፈሱ ተሰወረ፡፡
የመጨረሻው የዕምነት ሰው እንደሌሎቹ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡
ይሄ ሰው ግን፤ ቦታውን አያውቀውም፡፡
እሳት ማንደድም አያውቅም፡፡
የሚደገመውን ፀሎትም አያውቀውም፡፡
ምን እንደሚያደርግ ሲያሰላስል ቆይቶ እንዲህ አለ፡-
“በቃ፡፡ ከዚህ ቀደም እርኩስ መንፈስ ያጋጠማቸው ሦስት የዕምነት ሰዎች ታሪክ ልናገር” አለ፡፡
የሦስቱን ሰዎች ታሪክ ተናገረ፡፡
የነሱ ታሪክ መነገሩ በቂ ሆነ! እርኩስ መንፈሱ ድራሹ ጠፋ፡፡
***
ታሪኩ መነገሩ በቂ መሆኑን የሚያምኑና ታሪክ ለመናገር የሚችሉ ሰዎች ማግኘት መታደል ነው፡፡ እርኩስ መንፈስን ለማጥፋት ቦታ መምረጥ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸው እሰየው ነው! እርኩስ መንፈስን ለማግለል ፀሎት መድገም የሚችል ሰው ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ እርኩስ መንፈስ ለማጥፋት እሳት ማጥፋት የሚቻለው ሰው ማግኘት የሚችል ብልህ ሰው መኖሩን ማወቅ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ሦስቱንም ማግኘት በማይቻልበት ቦታ የሦስቱን ታሪክ የሚናገር ሰው ማግኘት አገር ማዳን ነው፡፡ እነማን ምን ሰሩ? እነማን ምን አደረጉ? እነማን የት ዋሉ? ታሪክ የሚናገር ሰው መኖር አለበት፡፡ እርኩስ መንፈስን ያስወግዳል፡፡ “ፃዕ እርኩስ መንፈስ!” የሚል ሰይጣንን ከየውስጣችንም ሆነ ከየአካባቢያችን የሚያወጣ ደጋሚ ያስፈልገናል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውና በጣም ድንቅ የሚባሉ የዘመናችንን መጻሕፍት (ለምሳሌ እንደ Clashes of Civilizations /የሥልጣኔዎች ግጭት እንደ ማለት፣) ያሉ፤ የፃፈውና በፖለቲካ ትንተና ባለሙያነቱ የሚታወቀው ሳሙኤል ሀንቲንግተን፣ የመደብ ፖለቲካ እያበቃ ሲሄድ ሀይማኖት እናም ባህል የግጭት ማትኮሪያ ነጥብ ይሆናል ይለናል፡፡ ቀጥሎ፤ “የአንድ አገር ህዝብ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያለው እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ድርጅቶችና አስተማማኝ የፍትህ አካላት (ፍርድ ቤቶች) ሊኖሩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ውጤቱ የባሰ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መግባት ነው” ይላል፡፡ ሀገራችን የተረጋጋ ህልውና ይኖራት ዘንድ ዲሞክራሲ ያሻታል ሲባል፣ ያንን የሚተገብሩ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ያላቸው ተቋማት ያሻታል የማለት እኩሌታ ነው፡፡ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ሲባልም ሀሳዊ-ዲሞክራሲያዊ (Pseudo-democracy) አለና ነው፡፡ አንድም በምሪት የሚሄድ ዲሞክራሲ (guided democracy) አለና ነው፡፡ የሚያማምሩ ዕቃዎች ስናይ በዐይናችን እንደምንማረክ፣ ውሎ አድሮ ግን በአገልግሎት ላይ ውለው ስናይ ከቶም ዕድሜ የሌላቸው ሆነው ስናገኛቸው እንደሚቆጨን ሁሉ፤ በመልካም ሀረጋትና ስሞች የሚጠሩ እንደ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ኮሙኒኬሽን፣ ኮሚሽን፣ ሚኒስቴር፣ ባለስልጣን፣ ኤጀንሲ፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፣ ዲሞክራሲያዊ መንግስት፣ ኮከብ አምራች፣ ሀቀኛ ካድሬ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ራእይ፣… ያሉ አያሌ መጠሪያዎች ተግባሪዎቻቸው በሌሉበት እንዲያው መጠሪያዎች ናቸው፡፡ የአራዳ ልጆች “የቻይና ሶኬት ስትገዛ፣ የሚይዝልህ ጩሎ አብረህ ግዛ” የሚሉት አባባል መንፈሱ ይሄው ነው፡፡ ተግባራዊነት ምኔም ወሳኝነት አለው፡፡ አፈፃፀምም አልነው ተግባራዊነት፤ “አንተ ዘፈን አልከው፣ እኔ ስልት ያለው ጩኸት አልኩት” ሁሌም ትርጉሙ ያው ነው እንዳሉት መምህር ያለ ነው፡፡
ምንም አይነት ጉዳይ ይሁን ምን፣ ምንም ዓይነት ለውጥ ይሁን ምን፣ ምንም ዓይነት ስያሜ ይሰጠው ምን፣ መለኪያው ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታው ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-አገር የሆነ አገዛዝ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ነው፡፡ ይህንን የሚናገሩ ታሪክ ተራኪዎች፣ አይጥፉ፡፡ የሚናገሩ አፎች አንጣ፡፡ የሚፅፉ ብዕሮች አይንጠፉ፡፡ “ላምህ ባትታለብ እንኳ፤ እምቧ ትበልልህ” ማለት ይሄው ነው፡፡ በፖለቲካዊ- ኢኮኖሚኛ “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ” ማለትም ነው፡፡
“ብልጥ ዋሾ፤ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ ብሎ ይፀልያል!”
አንድ ሰው አንዲት በጣም የሚወዳት ሴት ዘንድ ሄዶ “ዛሬ የት ውዬ እንደመጣሁ ታውቂያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡
ሴትዮይቱም፤ “የት ዋልክ የኔ ጌታ?” ትለዋለች፤ በፍቅር ቃና፡፡
ሰውዬው፤
“አንድ ጫካ ሄጄ፣ በእኔ ላይ ሸፍተው ከነበሩት ደመኞቼ ጋራ ተዋግቼ፣ ድባቅ መትቻቸው መጣሁ፤ በሙሉ ጨረስኳቸው” ይላታል፡፡
ሴትዮይቱ፤ “እንዲህ ነው እንጂ የኔ ጀግና! እኔ አንተን የወደድኩህ ለዚህ ለዚህ ታላላቅ ገድልህ ስል አይደል!” ትለዋለች፡፡
ሌላ ቀን ወደ ወዳጁ ዘንድ ሲመጣ፤ “ዛሬስ የት ሄጄ እንደመጣሁ ታውቂያለሽ?” ይላታል፡፡
“የት ዋልክልኝ የኔ ጀግና?”
“አንድ ጫካ ሄጄ፤ በእኔ ላይ ያደሙ ሽፍቶች አግኝቼ ጉድ አደረግኳቸው፡፡ አንድም ሳይቀረኝ ድምጥማጣቸውን አጥፍቻቸው መጣሁ!” ሲል ይፎክርላታል፡፡
ሴትዮይቱም፤ “እንዴ! የዛሬ ወር እዚያ ጫካ ሄደህ ድባቅ እንደመታሃቸው ነግረኸኝ አልነበር? ደግሞ ዛሬ ከየት መጡ?”
ሰውየውም ደንግጦ፤ “አይ ያኛው ሌላ ጫካ ነው!” ይላታል፡፡ ሴትየዋ ታዝባው ዝም ትላለች፡፡ ተጨዋውተው ይለያያሉ፡፡
ደሞ በሌላ ጊዜ ሲያገኛት፤ “ምነው ጠፋህ?” ትለዋለች፡፡
“ምን እባክሽ ወደ ጫካ ሄጄ ጠላቶቼን አንድ በአንድ ስለቅማቸው ውዬ፣ ድል በድል ተጎናጽፌልሽ መጣሁ፡፡ የመንደራችን ሰው ሁሉ “ጉሮ ወሸባዬ! እንዲያ እንዲያ ሲል ነው ግዳዬ!” እያሉ ነው ወዳንቺ የሸኙኝ፡፡”
ሴትየዋም ግራ በመጋባት፤ “እንዴ ባለፈው ጊዜ እዚያ ጫካ ሄጄ አሸንፌ መጣሁ አላልከኝም?” አለች ጥርጣሬዋ በግልጽ እየተነበበባት፡፡
“አ…ጫካው…ልክ ነሽ ያው ነው፡፡ ግን ጠላቶቼ፣ ….ሽፍቶቹ… ሌሎች ናቸው…”
ልቧ አልተቀበለውም፤ ግን ዝም ትለዋለች፡፡
አንድ ስድስት ወር አልፎ ሌላ ጊዜ መጣና፤
“እንደምን ከረምሽ? እኔ ጫካ ሄጄ ስንት ሽፍታ ዘርፌ ስመጣ፣ አንቺ የት ጠፋ ብለሽ እንኳ አልፈለግሽኝም?” ይላታል፡፡
ወዳጁም፤ “እንዴ ያንተ ጠላቶች አያልቁም እንዴ? ይኸው በመጣህ ቁጥር ዘረፍኳቸው፤ ድባቅ መታኋቸው፣ ለቀምኳቸው ትለኛለህ?” ስትል የምሯን ተቆጥታ ትጠይቀዋለች፡፡
እሱም፤ “አይ እነዚህ የኔ ጠላቶች ሳይሆኑ የህዝቡ ጠላቶች ናቸው!” ይላታል፡፡
ሴትየዋ ጉራውና ውሸቱ በቅቷታልና፤ “በል ከዛሬ ጀምሮ እኔ ዘንድ ድርሽ እንዳትል፡፡ በየቦታው እየሄድክ እየቀበጣጠርክ ስላስቸገርክ፣ ቆርጦ-ቀጥል የሚል ስም እንዳወጡልህ ያልሰማሁ እንዳይመስልህ” ብላ በሯን ዘግታበት ወደ መኝታዋ ትሄዳለች፡፡ እሱም ተስፋ ቆርጦ ይወጣል፡፡
ሰነባብቶ አስታርቁኝ ብሎ የነፍስ አባትዋን አማላጅ ይልክባታል፡፡ ሴትየዋም ለነፍስ አባትዋ “ከእንግዲህ ወዲያ ከእሱ የምታረቀው፤ ይህን መዋሸቱን እንዲተው፤ ጠበል የሚረጩት ከሆነ ብቻ ነው!” ትላለች፡፡ የነፍስ አባትዋ በሃሳቧ ተስማምተው ሰውየው ዘንድ ሄደው፣ የውሸት ሰይጣኑንን እንዲያርቅለት ዳዊት ደግመው፣ ፀበል ከረጩ በኋላ፤ “በል ልጄ፤ አንድ ነገር ልንገርህ “ብልጥ ዋሾ፤ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ” ብሎ ይፀልያል!” አሉት፡፡
***
ከውሸትና ከዋሾ ይሰውረን ማለት የፀሎቶች ቁንጮ ነው፡፡ ከእርግማኑ አድነን እንደማለት ነውና፡፡ ስለ ዲሞክራሲ ውሸት፣ ስለ ሹም-ሽር ውሸት፣ ስለ ሰላም ውሸት፣ ስለ ፍትህ ውሸት፣ ስለ ውስጠ-ፓርቲ ትግል ውሸት፣ ስለ ድል ውሸት፣ ስለ ታሪክ ውሸት፣ ስለ ዲፕሎማሲ ውሸት… ከመናገር ይሰውረን፡፡
የአንድ ሀገር የፖለቲካ ሂደት፤ ከተራ ቅጥፈት እስከ መረጃ ክህደት፤ ድረስ ከሄደ፤ እየዋለ እያደር “ሦስት የውሸት አይነቶች፡- ውሸት፣ የተረገመ ውሸትና ስታቲስቲክስ ናቸው” እንደሚባለው ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡
ልብ ብለን ካየነው ደግሞ፤ ማናቸውም የሀገራችን ፖለቲካ፤ አንዴ ውሸት፤ አንዴ እውነት እየተቀየጠ የሚመረትበት ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ አልፍሬድ ፔንሰን እንዳለው፤ “አይኑን በጨው ታጥቦ፤ ሽምጥጥ የሚያደርግን ቀጣፊ ፊት ለፊት ሙሉ በሙሉ በመጋፈጥ ይፋለሙታል፡፡ ከፊል እውነት ያለበትን ውሸት ግን መዋጋት አስቸጋሪ ነው፡፡”
እርግጥ ነው፤ ውሸትን ለማጋለጥ መቻል ሌላው መታደል ነው፡፡ ለአገርና ለህዝብ ትልቅ አስተዋጽኦ አለውና፡፡ በ1950ዎቹ በአንጎላና ኬፕ ቬርዲ ዋና የፖለቲካ ተዋናይና የነጻነት ታጋይ የነበረውና እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ሲፋለም የወደቀው አሚልካር ካብራል ስለ ታማኝነት ሲናገር፤ “ከህዝባችን ምንም ነገር አንደብቅ፡፡ ምንም አይነት ውሸት አንዋሽ፡፡ የተዋሹ ውሸቶችን እናጋልጥ፡፡ ችግሮችን አንሸፋፍን፡፡ ስህተቶችን ቀባብተን ትክክል አናስመስል፡፡ ለህዝቡ የስራችንን መልካም መልካሙን ብቻ አናውራለት፤ ውድቀታችንን አንደብቀው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድል በቀላሉ ይገኛል ብለን አናስብ” ይለናል፡፡
የአሜሪካ ልብ ወለድ ደራሲና ጋዜጠኛ ኖርማን ሜይለርም፤ “በየቀኑ ጥቂት ጥቂት ውሸቶች የትውልድ ሀረጋችንን እንደምስጥ እየበሉ ያመነምኑታል፡፡ በጋዜጣ ህትመት ውጤት ትናንሽ ተቋማዊ ውሸቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚያ ላይ የቴሌቪዥን አስደንጋጭ ሞገድ ይጨመርባቸዋል፡፡ ከዚያ ደግሞ የስሜትን ስስ-ብልት የሚያማስሉና የሚያታልሉ የፊልም ሰሌዳዎች ይደመሩበትና ሙሉ ውሸት ይሆናል” ይለናል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን እዋሽ ነበር ብሎ የሚያስብ ሰው፤ የባላንጣዎቹን እውነት መቀበል አዳጋች ይሆንበታል” እንዳለው፤ ሀያሲው የጋዜጣ አዘጋጅ ሜንከል፤ ብዙ እውነቶች ከውሸት ጎራ ተደምረው ሲወገዙ ማየትም ያዘወተርነው ፍርጃ ነው፡፡
በተጨማሪም፤ እንደሚታወቀው በየአገሩ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የመዋሸት ፍቃድ የተሰጣቸው ብቸኛ ፍጡራን የሚመስሉበት ጊዜም አለ፡፡ “አገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የሀገር መሪዎች ለሀገሪቱ ደህንነት ሲሉ ይዋሹ ዘንድ ይፈቀድላቸው ይሆናል” እንዲል ፕላቶ፤ የጆሯችን ግዱ ያንን ማዳመጥ የሆነበት ወቅት አንድና ሁለት የሚባል አይደለም፡፡
ይህ የሆነው በአገራችን የፖለቲካ አየር ውስጥ እስከዛሬም ጠፍቶ ያለ አንድ ዋና ነገር አሁንም የጠፋ በመሆኑ ነው፡፡ ትናንት የተናገሩትን አሊያም የዋሹትን፣ ዛሬ አለማስታወስ እናም በተደጋጋሚ መዋሸት፡፡ መቅጠፍ፡፡ ማንም አይጠይቀኝም፣ ወይም ልብ- አይልም ብሎ መኩራራት፡፡ ይሄ ደግሞ ለዋሺም ለተዋሺም ጎጂ ባህል ነው፡፡ ውሎ አድሮም ህዝብ ያልኩትን አያስታውስም አሊያም ለሱ ስል ነው የዋሸሁት ወደሚል ንቀትና ተአብዮ፣ ብሎም ወደ አምባገነንነት ሊመራ ችላል፡፡ “የረባ የማስታወስ ችሎታ የሌለው ሰው ከመዋሸት ቢታቀብ ይሻላል” የሚለው ገና በ15ኛው ክ/ዘመን ፈረንሳይ አገር የተነገረ ማስጠንቀቂያ ቢኖርም፣ እስከዛሬም ኢትዮጵያ የደረሰ አይመስልም፡፡
ያልሆንነውን ነን፣ ያላደረግነውን አደረግን ብለን መዋሸትና ራስን መገበዝ ፍፃሜው አያምርም፡፡
አንድ ልዑል መቃብር ላይ እንደተፃፈው ጥቅስ ማለት ነው፤
“ጀግና ነው ይሉታል ሣንጃ ሳይሞሸልቅ
ጨዋ ነው ይሉታል ማላውን ሳይጠብቅ
ይህ ያገሩ ልዑል፣ ያገር ሙሉው ግዛት
በህይወቱ እያለ፣ አገር ምድሩ ጠልቶት፣
እዚያም እሰማይ ቤት-
ገነት ፍትህ ነሳው፣ ፊቱን አዞረበት፡፡”
እንዳንባል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ቢያንስ “ብልጥ ዋሾ፣ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ ብሎ ይፀልያል የሚለውን አባባል አትርሳ” የሚለውን አለመዘንጋት ደግ ነው፡፡
ማርክ ትዌይንም በምፀት፣ “ውሸት መፀለይ አይቻልም፤ ያንን ደርሼበታለሁ” የሚለው ውሸት ከልብ የማይመነጭ መሆኑን ሲያስረዳን ነው፡፡ የማይዋሽ የፖሊቲካ ሰው ይስጠን!
በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ውጥረት ነግሷል ተባለ
- ነዋሪዎች ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ሰግተዋል
በአማራና ትግራይ ክልሎች የ”ይገባኛል” ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ውጥረት መንገሱ ተገለፀ። ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የትግራይ ሃይሎች ወደ እነዚሁ አዋሳኝ አካባቢዎች መጠጋታቸው ነው ውጥረቱን የፈጠረው።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪ በአካባቢው ከአማራ ክልል ዞኖች በአንጻራዊነት የተሻለ መረጋጋት እንዳለ ይገልጻሉ። ይሁንና እርሳቸው “የህወሓት ታጣቂ” ያሉት የትግራይ ሃይል አደጋ መጋረጡን ጠቁመዋል።
“ይኸው ሃይል በጠለምትና በዋልድባ አካባቢ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው” ያሉት እኚሁ ነዋሪ፣ በቅርቡ “ሰሜን ጎንደርና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖችን በሚያገናኘው፤ አዲአርቃይ ወረዳ፣ አሊ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ‘ዱሃር ግዛና’ የሚባል ስፍራ ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ጥቃት 15 ንጹሃን መገደላቸውንና 3 ሰዎች መቁሰላቸውን ጠቁመው፤ ከጥቃቱ ተጎጂዎች መካከል ታዳጊ ሕጻናት እንደሚገኙበትም አስረድተዋል።
ከጥቃቱ ባሻገር፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ከ500 በላይ ከብቶችና 300 ፍየሎች በትግራይ ሃይሎች መዘረፋቸውን ነው የገለፁት።
ነዋሪው “ጥቃቱን አድርሰዋል” ያሏቸው ታጣቂ ሃይሎች መቀመጫቸው እንዳባጉና መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪው፤ “ሃይሉን የሚመሩት ወርቂ ዓይኑ የተባሉ ጄኔራል” መሆናቸውን አመልክተዋል። የታጣቂ ሃይሉ ብዛት ከ250 እስከ 300 ድረስ እንደሚገመትና “አርሚ 11” ተብሎ እንደሚጠራም አመልክተዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የትግራይ ሃይሎች ትጥቅ ሳይፈቱ መቅረታቸው የደህንነት ስጋት ጋርጦብናል የሚሉት ነዋሪው፣ “አሁንም ለሌላ ጥቃት እየተዘጋጁ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የሰሜኑ ጦርነት እንዳያገረሽ ስጋት አለን።” ብለዋል።
በራያ አካባቢ፣ ቀደም ሲል አላማጣ ከተማ ይኖሩ እንደነበርና አሁን ግን ተፈናቅለው ኮረም እንደሚገኙ የነገሩን አቶ አማረ ደሳለኝ የተባሉ መምሕር፣ የጸጥታውን ሁኔታ ሲያብራሩ፣ “በየትምሕርት ቤቶች የትግራይ ታጣቂዎች ገብተዋል። ሕዝቡ ተገቢውን ማሕበራዊ አገልግሎት እያገኘ አይደለም።” ብለዋል። በእነዚሁ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ ታጣቂዎቹ የቡድን መሳሪያ ጭምር ይዘው መስፈራቸውንና መንግስታዊ ተቋማት ከስራ ውጭ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አንድ የባለ ሶስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪ በትግራይ ሃይሎች መገደሉን ተከትሎ፣ በነጋታው ከቀብር ስነ ስርዓቱ በኋላ በአላማጣ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን የተናገሩት አቶ አማረ፤ በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በእነዚሁ ሃይሎች ወረቀት መበተኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የራያ አካባቢ በአማራ ክልልም ሆነ በትግራይ አስተዳደር ስር አለመሆኑንና መደበኛ አስተዳደር አለመኖሩን በማመልከት፣ ሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እየከወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
“ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወደ ቆቦ ተጉዞ ነበር። ሆኖም መጠለያ አላገኘም። በቂ ዕርዳታ ከመንግስት አልቀረበለትም። ይህንን ተከትሎ ወደ አላማጣ ለመመለስ ተገድዷል። አንዳንድ በትግራይ ሃይሎች የሚታደኑ ግለሰቦች ከአላማጣ ሸሽተው ቆቦ ከትመዋል።” ሲሉ ነዋሪው ጠቁመዋል።
ኮረም፣ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣና አላማጣ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የራያ አካባቢዎች የትግራይ ሃይሎች እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ አማረ፣ ኮማንድ ፖስት በማወጅ የአማራ ክልል ግለሰቦችን ትጥቅ ከማስፈታት ባለፈ፣ የፌደራል መንግስቱ የሰጠው ተጨባጭ መልስ እንደሌለ ተናግረዋል።
ከወራት በፊት በፌደራል መንግስቱ፣ የራያ አላማጣ ነዋሪዎችን እንዲያወያዩ የተላኩት የአገር መከላከያ ሰራዊት አዛዦች፤ ከትግራይ ክልል ተፈናቃዮች እንደሚመጡ፣ የአማራ ክልል በራያ ያደራጀው የመንግስት መዋቅር እንደሚፈርስና በሕዝቡ ምርጫ መሰረት አዲስ የጋራ አስተዳደር እንደሚዋቀር መግለጻቸውን አቶ አማረ አውስተዋል።
አዲሱ አስተዳደር አሳታፊ የሆነ መዋቅር እንደሚኖረውና መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ጸጥታ እያስከበሩ ሪፈረንደም እንደሚደረግ ከአወያዮቹ መገለፁንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ቃል የተገባው ጉዳይ ተግባራዊ ከመሆን ይልቅ የትግራይ ታጣቂዎች የ”ይገባኛል” ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አልፈው ቀድሞም በአማራ ክልል አስተዳደር ስር ወዳሉ አካባቢዎች እየገቡ መሆናቸውን አቶ አማረ አስታውቀዋል።
ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ባለው ጊዜ፣ በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተመሰረቱ “ሕገወጥ” ያሏቸው አስተዳደሮች ሊፈርሱ፣ ተፈናቃዮች ደግሞ ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ከፌደራሉ መንግስት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረው ነበር።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፣ «ህወሓትና ግብረ አበሮቹ» ያላቸው አካላት፣ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሱባቸውና ሰሞኑን በሃይል ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበርም መጠየቁ ይታወቃል።
በሌላ በኩል፤ ከሳምንታት በፊት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ፤ “የፌደራል መንግስት የህወሓት ታጣቂዎችን በወረራ ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እንዲያደርግና በተደጋጋሚ ወረራ እየተፈጸመበት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጠው ህዝብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ” አሳስቦ ነበር።
እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ የፌደራሉ መንግስት የሰጠው ይፋዊ መግለጫም ይሁን ማሳሰቢያ የለም።
በኢሮብ 23 ት/ቤቶች በ ኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ተነገረ
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ፣ የኤርትራ ወታደሮች በኢሮብ ወረዳ 23 ትምሕርት ቤቶችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ የወረዳው ትምሕርት ጽ/ቤት ጠቁሟል።
በወረዳው የትምህርት ፅህፈት ቤት ስር ከሚታወቁና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩት መካከል፣ አንድ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙባቸው 23 ትምህርት ቤቶች ከ3 ዓመት በላይ በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መቆየታቸው ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።
ከትምሕርት ቤቶቹ ባሻገር፣ መምሕራንና ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅ እንዳልቻለ ተነግሯል።
በወረዳው አንጻራዊ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በመጪው ሐምሌ ወር ለሚሰጠው አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ታውቋል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በቂ የትምሕርት ቁሳቁስ አቅርቦት በሌለበት ለፈተና በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የዕገዛ እጃቸውን እንዲዘረጉ የወረዳው ትምሕርት ፅህፈት ቤት ጥሪውን አስተላልፏል።
ጦርነቱ ብዙ ነገሮች እንዳሳጣቸው የተናገሩ ተማሪዎች፤ አሁን በወረዳቸው ትምህርት ቤት የኢንተርኔት አቅርቦት ጨርሶ እንደሌለ ጠቁመዋል። በተጨማሪም የውሃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርትና የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት እንደሌለ ጠቅሰው ይህም በቴክኖሎጂ ታግዘው ከሚፈተኑ ተማሪዎች ጋር ተፎካካሪ ለመሆን አዳጋች እንደሚያደርግባቸው ነው የገለፁት።
እንዲያም ሆኖ፣ አሁን የተገኘው ዕድል እንዳያመልጣቸው ለመፈተን በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተማሪዎች ተናግረዋል።
መምሕራን በበኩላቸው፣ በወረዳው ያሉት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የክልሉና የፌደራል መንግስት ትምህርት ሚኒስቴር ዕገዛ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።
የኢትዮጵያ መንግስት፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት፣ በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ነፃ እንዲወጡ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ፣ በኢሮብ ወረዳ የትምሕርት መሰረተ ልማት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መውደሙ የትግራይ ቴሌቪዥን ዘገባ ያመለክታል።
የወባ በሽታ በደቡብ ምዕራብ ክልል ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል
- የወባ በሽታ ላይ የሚመክር ጉባኤ እየተካሄደ ነው
የወባ በሽታ በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክልል፤ የአምራቹን ወጣትና የሕጻናትን ሕይወት በመቅጠፍ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ። በሽታው የሕልውና ስጋት ወደ መሆን ተሸጋግሯል ያሉት አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪዎች፣ በበሽታው ተጠቂ የሆኑ ሕሙማን የህክምና አገልግሎት ባገኙበት በሁለትና በሦስት ቀናት ልዩነት ውስጥ እንደገና የበሽታው ምልክት ይታይባቸዋል ብለዋል። መድኀኒቱም የመፈወስ አቅሙ አናሳ እንደሆነ ተናግረዋል። በተደጋጋሚ ለበሽታው በመጋለጣቸው የተነሳ በአቅም ማነስ ሕይወታቸውን የሚያጡ ነዋሪዎች ቁጥርም ከቀን-ወደ ቀን እያሻቀበ መምጣቱ ተነግሯል።
የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም፤ ወጣቶች፣ ሕጻናት እንዲሁም አምራቹ ገበሬና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በሽታው ሕይወታቸውን እያጡ እንደሆነ ከአካባቢው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቦንጋ ከተማ አገልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው የገብረጻዲቅ ሻዎ ሆስፒታል የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ፤ በአብዛኛው ሕጻናት በበሽታው ተጠቂ ሆነዋል። ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ከአንድ መቶ ታካሚዎች መካከል ሠላሳ ያህሉ የወባ በሽታ ተጠቂዎች እንደሆነም ታውቋል። የሕጻናት በሽታ የመቆጣጠር አቅም አናሳ በመሆኑ ለአዋቂዎች የተበጀውን መድኀኒት መስጠት ቀላል አለመሆኑን የሚገልጹት የጤና ባለሙያዎች፤ በማስታገሻ መልክ የሚወስዱት መድኀኒት እንጂ በዶዝ የተዘጋጀላቸው መድኀኒት ባለመኖሩ የተነሳ ሕጻናትን መፈወስ ከአቅም በላይ እንደሆነ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል፤ በገጠር አካባቢዎች የጤና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች፣ በቂ የመድኀኒት አቅርቦት እያገኙ አይደለም ተብሏል።
በአካባቢው የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ እንዳይራባና የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ የሚያስችል የኬሚካል ርጭት መስተጓጎሉን ያመለከቱት መረጃዎች፤ በተወሰኑ አካባቢዎች እንጂ በሁሉም ቦታዎች የኬሚካል ርጭት እንዳልተከናወነ ይጠቁማሉ።
በርካታ ሕሙማን መድኀኒት ጀምረው በማቋረጣቸው፣ እንዲሁም የክልሉ የጤና ቢሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ በሽታው ስርጭት፣ መከላከልና ስለ መድኀኒት አወሳሰድ እንዲሁም በጥንቃቄ አወሳሰድ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ያለመፍጠሩ የበሽታው ስርጭት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ በወባ ሥርጭትና መከላከል ላይ የሚያተኩርና ለስድስት ወር የሚዘልቅ ልዩ ዘመቻ ለመጀመር በሚዛን አማን ከተማ ትላንት አርብ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የምክክር መድረክ ከፍቷል፡፡
በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ባለስልጣናት፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የተለያዩ በወባ መከላከያ ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ተዘግቧል። በጉባኤውም የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ውይይቶችና ተግባራቶች ይከናወናሉ ተብሏል።
የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል
አንድ ብልህ ንጉስ በከተማው ውስጥ ሦስት አዋቂዎች ነን እያሉ ህዝቡን ይመክራሉ፤ ያወናብዳሉ የሚባሉ ሰዎችን በተራ በተራ ጠርቶ ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፡፡
የመጀመሪያው አዋቂ እንደገባ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡-
“ህዝቡ ይውረድ ይውረድ እያለ እያስቸገረኝ ነው፡፡ እኔ ግን በስልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ፡፡ ምን ባደርግ ይሻላል?”
አንደኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ እርሶን የመሰለ ደግ ንጉስ ይውረድ ያለ ህዝብ ከእንግዲህ ሊታመን አይገባውም፡፡ ይልቁንም ሊቀጣ ይገባዋል፤ ስለዚህ ለመቀጣጫ ከህዝቡ መካከል ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን በአደባባይ ይቅጧቸው፡፡ ያኔ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” ሲል መለሰ፡፡
ሁለተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቡ ያላንተ መኖር አንችልም፤ ለዘላለም ቆይልን እያለ አስቸገረኝ፡፡ እኔ ግን ስልጣኔን ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ ኑርልን የሚለኝ እውነቱን ይሁን ውሸቱን ለማወቅ ተቸግሬያለሁ፤ ምን ትመክረኛለህ?”
ሁለተኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ ይህን ህዝብ አይመኑት፤ ይኑሩልን ሲል ይሙቱ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማወቅ ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን አስጠርተው በአደባባይ ቢቀጡ ማታለሉን ትቶ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” አለ፡፡
በመጨረሻም ሦስተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቤ ይውረድም አይለኝም፡፡ ይኑርም አይለኝም፡፡ ዝም ብሎ እየተገዛ ነው፡፡ የልቡን ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሦስተኛው አዋቂም፤
“ይህን ህዝብ አይመኑት፡፡ ይኸኔ ሴራ እየጎነጎነ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ተጠሪ ናቸው የሚባሉትን ሽማግሌዎች አስጠርተው ሸንጎ ፊት ቢያስገርፏቸው የተዶለተችው በሙሉ ትጋለጣለች፡፡”
ከዚህ በኋላ ንጉሱ ህዝቡ እንዲጠራ አዋጅ አስነገረና፤ ህዝብ ሲሰበሰብ እንዲህ አለ፤
“እነዚህን ሦስት አዋቂዎች አስጠርቼ ህዝቡ ይጠላኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ ይወደኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ መውደዱንም መጥላቱንም አልነግር አለኝ ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ምን ታስባላችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ህዝቡም መክሮ ሲያበቃ በተወካዩ በኩል መልስ ሰጠ፡፡ ተወካዩ የአገር ሽማግሌ፤
“ንጉስ ሆይ፤ ከህዝቡ ጋር ስንመክር አንድ እልባት ላይ ደረስን፡፡ እነዚህ ሦስት አዋቂዎች በተለያየ ጊዜ ስለ እርሶ ጠይቀናቸው የመለሱልን መልስ ’ንጉሱን አትመኗቸው’ የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም በወዲህም ወገን በወዲያም ወገን፤ መተማመን እንዲጠፋ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሊቀጡልን ይገባል” አሉ፡፡
ንጉሱም፤
“እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ፤ ስለሆነም ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ያም ሆኖ ለእናንተ አንድ ምክር ልምከራችሁ፡፡ ሁልጊዜ ተነጋገሩ፡፡ ተመካከሩ፡፡ ግልፅ ሁኑ፡፡ ጥፋት ስታገኙ ጥፋተኛውን ቅጡ፤ ንጉስ ያልፋል መንግስት ይለወጣል፤ ሁሌም ነዋሪው ህዝብ ነው” ሲል ነገራቸው፡፡
***
ብልህ ንጉስ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የአገር አዋቂዎች ማጣት መረገም ነው፡፡ የሚመካከር ህዝብ መላ ያገኛል፡፡ ችግሩን የማይፈታ ህዝብ በሽታውን እንደደበቀ ህመምተኛ ነው፡፡ ግልፅነት ሲኖር እውነት ወደ አደባባይ ትወጣለች፡፡ ግልፅነት ከመሪዎችም፣ ከምሁራንም፣ ከህዝብም የሚጠበቅ ፍቱን ወርቅ ነው፡፡ ግልፅነት ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ ከሆነ ሌላውን ወገን መሸፈኛ፣ የተንኮል ጭምብል ይሆናል እና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ግልፅነት አለቃ ምንዝሩ የሚተችበት መሳሪያ ብቻ ተደርጎ አንዱን ንፁህ፣ አንዱን አዳፋ፣ አንዱን ቀና፣ ሌላውን ጎልዳፋ ብሎ ለመፈረጅ፤ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ ግልፅነት ሁሉም ላይ የሚሰራ፣ ለሁሉም የሚያገለግል መርህ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
ግልፅነት ከብልጥነት መለየት አለበት፡፡ ግልፅ ነኝ ማለት ድብቅነትን መሸፋፈኛ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አዋቂ ሳይሆኑ የወቅቱን መፈክር በማንበብ ብቻ አዋቂ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት አይደለም፡፡ ከስህተት ሳይማሩ ከስህተት የተማሩ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት ከቶ አይደለም፡፡ በአፍ ቅቤ፣ በልብ ጩቤ ይዞ መቅረብ ግልፅነት አይደለም፡፡ “ብቅል ለመበደር የምትሄድ ብቅል ያላስቀመጠችውን ምን ሴት ትባላለች! ትላለች” እንዲሉ፤ አንዱ ካንዱ ላይሻል ነገር፣ ጥፋተኛ እራሱን እንከን-የለሽ አድርጎ ሌላውን ጥፋተኛ ሲወቅስ፤ ያኛውን አጋልጦ እራሱን ሸሽጓል እና ግልፅነት እሱ ዘንድ የለም፡፡ የግልፅነት ስርአት ሁሉን-አቀፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእሙናዊው ተግባር የፈለቀ መሆን አለበት፡፡ ግልፅነት ከሁሉ አስቀድሞ እውነተኝነት መጠየቁ ለዚህ ነው፡፡
የአስተዳደግ ጉድለት፤ የአስተዳደር ጉድለትን ያስከትላል፡፡ እራሱ በወጉ ሀላፊነት ያልተረከበ፣ እራሱ እድገቱን ያላግባብ የወሰደ፤ እራሱ ሹመቱን በኢርትኡ መንገድ የነጠቀ ሰው ስርአት ያለው አስተዳደር ለማስፈን ይቸግረዋል፡፡ ይልቁንም “ብልጥ ሌባ የቆጮ መቁረጫ ትሰርቃለች” እንደሚባለው፤ ከቆጮውም ይልቅ መቁረጫውን ይዟልና ህግ አውጭውም፣ ፈራጅም፣ ገምጋሚም አስገምጋሚም፣ ሰብሳቢም፣ መራጭም፣ ሆኖ ሁሉን ከእፍታው ይጨልፋል፡፡ ጠያቂ የለበትምና ልቡም እጁም አያርፍም፡፡ ሙስናን ለማስፋፋት ቅርብ ሆነ ማለት ነው፡፡ የአገርና የግለሰብን ጥቅም ያደበላልቃል፡፡ የተማረረን ከተማረ በላይ ያደርጋል፤ ባለሙያነትንና ባለእውቀትነትን ከአፋዊ ችሎታ በታች ያያል፡፡ ይህን መሳይ ድርጊት ሁሉ የመልካም አስተዳደር አለመምጣት መርዶ ነው፡፡ ያ በፈንታው የዲሞክራሲን በር ይዘጋል፡፡ የሰላምን ውጋጋን ይጋርዳል፤ የፍትህን ሚዛን ይነጥቃል፡፡
በተለይ እጅግ ወቅታዊ የሆኑትን፤ የሀገርም ሆነ የአገርና አገር ጥያቄዎችና ችግሮች በዲሞክራሲያዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አፍጦ የመጣበት ሰአት ነው፡፡ የችግር ቅደም-ተከተልን ጥያቄ (prioritization) ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሁኔታና ከተጎራባች አገሮቿ እንዲሁም ከሉላዊ እንቅስቃሴና መስተጋብር (global action and interaction) ጋር አጣጥሞ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ ለአቻ ቦታ አቻ ሰው መድቦ መራመድ ከወደቁ ወዲያ ከመንፈራገጥ ማዳን ብቻ ሳይሆን እስከ ፍልሚያ ሜዳ ያለውን ጎርበጥባጣና ኩርንችታማ ጎዳና ለመጥረግ በቅጡ ያግዛል፡፡ ጦርነት የሰላማዊ መንገድ መሟጠጫ እንጂ መነሻ መሆን በጭራሽ የለበትም፡፡ አለመዘናጋት ግን ሁሌም ወሳኝ ነው፡፡
የጥንቱ የጠዋቱ ሼክስፒር በሀምሌት ውስጥ “ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም፣ አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!” (ፀጋዬ ገብረመድህን እንደተረጎመው) ያለውን አለመርሳት ደግ ነው፡፡
ረጅም መንገድ አለብኝ ብሎ በርካታ ስንቅ የጫነ ሰው፤ ስንቁን ቅርብ ቦታ መጨረስ የለበትም፡፡ በትንሽ እንቅፋትም መውደቅ የለበትም፡፡ ነገ ሰፊ የምርጫ ትግል ያለበት የዛሬ አዘገጃጀቴ “የሚወጋ ጦር ከእጅ ሲወጣ ያስታውቃል” አይነት መሆን አለበት፡፡ የብዙዎችን ተሳትፎና ድጋፍ በጠዋት ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ መፎካከር ለማሸነፍ ብቻ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ነገም እንደዛው መሆኑን አውቆ መጓዝ ያሻል፡፡ መጋቢ ጅረቶች ሁሉ ወደ ወንዝ ለመቀላቀልና የአገር ሃይል ለመሆን እንደሚችሉ አጢኖ፤ ጊዜ መውሰድ አቅጣጫ ማግኘት ያሻዋል፡፡ ጊዜያዊ የሀገር ጉዳዮችን ከዘላቂ ፍሬ ነገሮች አነፃፅሮ አንዱ በሌላው እንዳይጋረድ ደህና አደርጎ ማስተዋል የሁሉም ድርጅቶች አጓጓዝ መሆን አለበት፡፡
ዳምኖም አጉረምርሞም ላይዘንብ እንደሚችል ሁሉ፣ ዘንቦም ሙሉ ጥጋብ ላይሆን እንደሚችል፣ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከህዝብ ያልመከሩበት፣ ህዝብን ያላሳተፉበት አካሄድ መሰረት-የለሽ ፒራሚድ ነው፤ ብዙ እድሜ የለውም፡፡ በአጭር ጊዜ ፈተና ይዳከማል፡፡ አዋቂዎቹን እንደፈተሸው ብልህ ንጉስ፣ ጠያቂ የመጣ እለት በአደባባይ መጋለጥ ይከተላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በቅንጣት ጥያቄ ግዙፍ ሀጥያት ይታያል፡፡ የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል የሚባለው እንግዲህ ያኔ ነው!